Monday, December 4, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ለሒሳብ አያያዝና ለታክስ ሥራዎች አጋዥ ሶፍትዌር ተሠራ

ተዛማጅ ፅሁፎች

ላለፉት አራት ዓመታት ሲጎለብት የቆየና ለሒሳብ አያያዝ ሥራዎች እንዲሁም የታክስ አገልግሎት አጋዥ የሆነውን ሶፍትዌር ያመረተው አገር በቀል ኩባንያ፣ ምርቱን ለሽያጭ ከማቅረብ ባሻገር በፋይናንስ መስክ ግዙፍ ኩባንያዎች የሚጠቀሙባቸውን ሶፍትዌሮች የማምረት ዓላማ እንዳለው ገልጿል፡፡

ቢዝኔት አይቲ ሶሉሽንስ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር የሠራው አዲሱ ሶፍትዌር በመንግሥት ድርጅቶች ተተግብሮ ውጤታማ ከመሆኑም ባሻገር የሪል ስቴት ኩባንያዎችም እየተጠቀሙበት እንደሚገኙ፣ ከኩባንያው መሥራቾች አንዱ የሆኑትና ሥራ አስኪያጁ አቶ ቢንያም ሐድጉ ገልጸዋል፡፡

ቢዝኔት ኩባንያ የሠራው ሶፍትዌር ተፈትሾ ውጤታማ በመሆኑ የአዳማ ውኃ ልማት ቢሮ ብቻ ከአንድ ሚሊዮን በላይ ሰነዶች በሶፍትዌሩ አማካይነት ተጭነውለት ደንበኞቹን ለማስተናገድ እንደቻለ ተናግረዋል፡፡ ኢምፓክት ሪል ስቴትም የአንድ ዓመት አሥር ሺሕ ሰነዶችን በሰርቨር ጭኖ በሶፍትዌሩ አማካይነት የሒሳብ ሥራዎችንና የታክስ ክፍያዎችን እያስተናገደ እንደሚገኝ ታውቋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም የሐረር ክልል፣ የድሬዳዋና የቢሾፍቱ ከተማ ውኃ ልማት ሥራዎች በሶፍትዌሩ እየተጠቀሙ መሆናቸው ተነግሯል፡፡ ከውኃ ልማትና ከኢምፓክት ሪል ስቴት ባሻገር የችርቻሮ ንግድ ተቋማት፣ አማካሪ ድርጅቶችና ሆቴሎች ሶፍትዌሩን ለመጠቀም ግዥ መፈጸማቸውን አቶ ቢንያም አስታውቀዋል፡፡ 

‹‹ቢዝኔት ኮስት አካውንቲንግ ሶፍትዌር›› የሚል ስያሜ የተሰጠው አዲሱ ሶፍትዌር፣ አገሪቱን የታክስ ሕግ ተከትሎ መሠራቱ ሲገለጽ፣ ነባሩ ‹‹ፒችትሪ አካውንቲንግ›› የተባለውና በስፋት ጥቅም ላይ የዋለው የሒሳብ አሠራር አጋዥ ሶፍትዌር ከሚያከናውናቸው ተግባራት ተሻሽሎ፣ ትልልቅ ኩባንያዎች እንደሚጠቀሙበት ከሚነገርለት ‹‹ኢንተርፕራይዝ ሪሶርስ ፕላኒንግ›› ሶፍትዌር ዝቅ ተደርጎ የተመረተው ሶፍትዌር፣ የአንድን ድርጀት ዕለታዊ ግዥዎች፣ የዕቃ ወይም የግብዓት ክምችት፣ መክፈል የሚጠበቅበትን የተጨማሪ እሴት ታክስ መጠን ራሱ ሠርቶ የሚያሳውቅ ሶፍትዌር እንደሆነ የአቶ ቢንያም ማብራሪያ ያስረዳል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ የደመወዝና የጡረታ መዋጮዎችን አስልቶ እንደሚያቀርብ ተነግሮለታል፡፡

አዲሱ የሒሳብ አያያዝና ሥራዎች ሶፍትዌር የሒሳብ ሥራዎችን ለማቀላጠፍ ይረዳል፣ የግድ የሒሳብ ባለሙያ መሆንን አይጠይቅም የሚሉት አቶ ቢንያም፣ የአንድ ድርጅት ሒሳብ ያዦች ወይም መሠረታዊ የሒሳብ አሠራርና አያያዝ ዕውቀት ያላቸው ሰዎች ሊገለገሉበት እንዲያስችል ተደርጎ መዘጋጀቱን ይገልጻሉ፡፡ ይህም ሆኖ ግን ሶፍትዌሩ የሒሳብ ባለሙያዎችን ሥራ ለመንጠቅ የመጣ ሳይሆን ሥራቸውን በማቅለል በሪፖርቶችና በበጀት ሥራዎች ላይ እንዲያተኩሩ ለማገዝ የሚረዳ እንደሆነ ይገልጻሉ፡፡ ‹‹የአገሪቱን የፋይናንስ ችግሮች አይተን የፈጠርነው ሶፍትዌር ነው፡፡ የፋይናንስ ሥርዓቱ በግለሰቦች ላይ ከሚመሠረት ይልቅ ሥርዓት ላይ እንዲያተኩር የሚያስችል ስልት ፈጥረናል፤›› ብለዋል፡፡ በሒሳብ አያያዝ ውስጥ የአቶ ቢንያምና ሁለት ጓደኞቻቸው በአክሲዮን የመሠረቱት ኩባንያ፣ ለሠራው አዲሱ ሶፍትዌር ከ85 ሺሕ ብር እስከ ሦስት ሚሊዮን ብር በማስከፈል እየሸጠ ይገኛል፡፡

በዚህ ዓመትም 700 ሶፍትዌር ለመሸጥ መዘጋጀቱን ይፋ አድርጓል፡፡ የስድስት ወራት ነፃ አገልግሎትና ሥልጠና አብሮ የሚሰጥበት ሽያጭ የሶፍትዌር ፈቃድ ክፍያ እንደማይፈጸምበት ተነግሯል፡፡

በአገሪቱ ያለው የሶፍትዌር ገበያ ለማንኛውም አምራች ክፍት ነው የሚሉት አቶ ቢንያም፣ ይህ ዕድል ግን የማይሠራና አገልግሎት የማይሰጥ ሶፍትዌር በሚያመርቱ አካላት እየጎደፈ ይገኛል ይላሉ፡፡ በዚህ ሳቢያም ገበያው ከአገር ውስጥ ይልቅ በውጭ ምርቶች ላይ እንዳይጥለቀለቅ ሥጋት እንዳላቸው ይናገራሉ፡፡ አገር በቀል ድርጅቶች ከዚህ ቀደም ከአገር ውስጥ ሶፍትዌር አምራቾች በገዙት የማይሠራ ሶፍትዌር ሳቢያ ፊታቸውን ወደ ውጭ አምራቾች ካዞሩ፣ የአገሪቱን የአይሲቲ ዘርፍ አደጋ ላይ ሊጥለው እንደሚችልም ፍራቻ አላቸው፡፡ ይህም ሆኖ ኩባንያው ወደፊት የዋጋ ትመናዎችን፣ የፋይናንስ መረጃዎችንና ሌሎች ትንታኔዎችን የሚሠሩ ሶፍትዌሮችን የማምረት ሐሳብ ሰንቋል፡፡

መንግሥት ለአገር ውስጥ ሶፍትዌር አምራቾች ትኩረት መስጠቱን በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የፋይናንስና ኢኮኖሚ ክላስተር አስተባባሪ፣ የመገናኛና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዶክተር ደብረ ጽዮን ገብረ ሚካኤል ሲገልጹ ይደመጣሉ፡፡ በቅርቡ ተመርቆ ሥራ የጀመረው የአይሲቲ ፓርክ ለሶፍትዌር ፈጣሪዎች ቦታ ማዘጋጀቱን አስታውቀው ነበር፡፡ በተለይ በዝቅተኛ ደረጃ ለሚሠሩና ለጀማሪ ወጣቶች የፈጠራ ሥራ የሚውል ሕንፃ በፓርኩ ከሚገኙት መካከል ይጠቀሳል፡፡ በአንፃሩ ሌሎች የመንግሥት ተቋማት ለጥቂት ኩባንያዎች የአቅራቢነት ዕድል በመስጠት አነስተኛ የአይሲቲ ባለሙያዎች ከገበያ ውጭ እንዲሆኑ የሚያደርጉ ዕርምጃዎችን በመውሰድ የሥራ ፈጠራና ዕድሎችን አቀጭጨዋል ተብለው ይታማሉ፡፡ ከእነዚህ መካከል የሚመደበው የኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ነው፡፡

ባለሥልጣኑ ከጥቂት ዓመታት በፊት የሽያጭ መመዝገቢያ ማሽን በአገሪቱ ተግባራዊ እንዲደረግ ማሳወጁን ተከትሎ፣ በሶፍትዌር ሥራ ላይ የተሰማሩ አነስተኛ አምራቾችን ከገበያ ውጭ ያደረገበትን አሠራር መተግበሩ አይዘነጋም፡፡ ይኸውም ሶፍትዌር የሚያመርቱ ኩባንያዎች አንድ ሚሊዮን ብር እንዲኖራቸው የሚያዝ ሕግ ማውጣቱ ነው፡፡ ከዚህ በተጨማሪም በጣት የሚቆጠሩ ኩባንያዎች ብቻ የሽያጭና የሒሳብ መመዝገቢያ ማሽኖችን እንዲያቀርቡለት በማድረግ ሌሎችን ገሸሽ ማድረጉም በአይሲቲ ዘርፍ የተሰማሩ ኩባንያዎች የሚያሰሙት ቅሬታ ነው፡፡

 

 

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች