Thursday, December 1, 2022
ሌሎች ዓምዶች

  ‹‹አንቀጽ 39 ከመገንጠል መብት የላቁ መብቶችንም ያቀፈ ነው››

  - Advertisement -spot_img

  በብዛት የተነበቡ

  አቶ ውብሸት ሙላት፣ የሕገ መንግሥት ተመራማሪና መምህር

  አቶ ውብሸት ሙላት በቅርቡ ‘አንቀጽ 39’ በተሰኘ ርዕስ የራስን ዕድል በራስ የመወሰን መብት የኢትዮጵያ አፈጻጸም የሚዳስስ መጽሐፍ አሳትመው ለገበያ አቅርበዋል፡፡ የሕግ ባለሙያው አቶ ውብሸት ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በሕግ የመጀመሪያ ዲግሪ አግኝተዋል፡፡ በማኔጅመንት የማስተርስ ዲግሪም የሠሩ ሲሆን፣ በሕገ መንግሥት ጥናት ሁለተኛ የማስተርስ ዲግሪያቸውንም በማገባደድ ላይ ይገኛሉ፡፡ በደሴ ሥራ አመራርና ቢዝነስ ኮሌጅ በመምህርነት ሥራ የጀመሩት አቶ ውብሸት፣ በወይዘሮ ስህን ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅም የጥራት ጉዳዮች ኃላፊ ሆነው ሠርተዋል፡፡ አቶ ውብሸት ከማንነት ጥያቄ ጋር የተገናኙ ጉዳዮችን ሪፖርተር ጋዜጣን ጨምሮ በተለያዩ የሚዲያ ውጤቶች ላይ ሐሳባቸውን በማካፈል ይታወቃሉ፡፡ የሕግ አማካሪና ጠበቃ፣ እንዲሁም መምህርና ተመራማሪ የሆኑት አቶ ውብሸት ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱ ወደ ሥራ ከገባ ሃያ ዓመታት ቢሆነውም እንኳን፣ በአንቀጽ ደረጃ ጠቅላላ ሕገ መንግሥቱ ላይ ትንታኔና ማብራሪያ የሚሰጡ ሥራዎች አለመኖራቸው መጽሐፉን ለማዘጋጀት መነሻ እንደሆናቸው ይናገራሉ፡፡ የመጽሐፍ እርሾ የተጠነሰሰው በመጀመሪያ ዲግሪ መመረቂያ ጽሑፍ ከዘጠኝ ዓመት በፊት ሲያዘጋጁ ቢሆንም፣ ከየትኛውም ሥራ ተገልለው ሥራውን ለማጠናቀቅ አንድ ሙሉ ዓመት እንደፈጀባቸው ገልጸዋል፡፡ ‘አንቀጽ 39’ ስለ ብሔር ጥያቄ፣ የጎሳና ነገድ ጥያቄ፣ የመገንጠል መብት፣ የግለሰቦችና የቡድኖች መብት አፈጻጸም የሚዳስስ ሲሆን፣ ሰለሞን ጐሹ በመጽሐፋቸው ላይ ከተነሱ ጉዳዮች በተወሰኑት ላይ አቶ ውብሸትን አነጋግሯቸዋል፡፡

  • ፡- ‘አንቀጽ 39’ የሚለውን ይህንን ርዕስ ለምን መረጡ?

  አቶ ውብሸት፡- ይህን ጽንሰ ሐሳብ የጽሑፌ ማጠንጠኛ እንዲሆን የመረጥኩባቸው በርካታ ምክንያቶች ቢኖሩኝም፣ ከእነዚህ ውስጥ የተወሰኑትን ብቻ ልንገርህ፡፡ የመጀመሪያው  ብዙ ያወራንለት ነገር ግን በአግባቡ ያልተገነዘብነው ስለሆነ ነው፡፡ ሁለተኛው ሁለት እጅግ ጽንፍ ላይ የቆሙ አመለካከቶች ብቻ፣ በመካከሉ ምንም የሌለው ይመስል፣ የሚስተናገድበት አንቀጽ በመሆኑ ነው፡፡ ለአንዱ ቤዛ ለሌላው አዛ የሆነ አንቀጽ ነው፡፡ እናም  ድምፃዊቷ ‹‹የማነሽ ይሉኛል የማን ልበላቸው፣ አይቻልም ወይ መኖር የማንም ሳይሆኑ….››  እንዳለችው የማንም ሳልሆን የሁሉንም ወገን ሐሳብ ለማዳመጥ በመሞከር ይኼንን አንቀጽ በአግባቡ ለመረዳት እንድንችል እገዛ ለማበርከት ነው፡፡ ሌላው ሕገ መንግሥቱ ሥራ ላይ ከዋለ ሃያ ዓመት ሊሞላው ጥቂት ቀናት ይቀሩታል፡፡ የዚህ አንቀጽ መውጣት መነሻ ስለሆነው የብሔር ጥያቄ፣ ብሔርተኝነት፣ የብሔር ብሔረሰብና ሕዝብ ምንነት፣ የራስን ዕድል በራስ የመወሰን መርህና መብት ይዘት ኢትዮጵያዊ በሆነ ቋንቋ ለአብዛኛው ሕዝብ በሚሆን በመጽሐፍ መልክ የተሠራ ስለሌለ ነው፡፡

  ከዚህ በተጨማሪም በብዙ መልኩ ዓይነ ጥላ የሆነችብን አንቀጽ ናት ብዬ ስላማስብ፣ እናም በአግባቡ እንድንወያይ ነው፡፡ ብዙ መሻሻል ያለባቸውንም ጉዳይ አካታ ስለያዘችና ሌላው ደግሞ ይኼ አንቀጽም ይሁን አጠቃላይ ሕገ መንግሥቱ አሁን ያለውን ይዘትና ቅርፅ እንዲኖረው ከፍተኛ አስተዋጽኦ የነበራቸው ሰዎች በሌሎች አገር እንደሆነው ሁሉ መጽሐፍ ያለማዘጋጀታቸው ነገር ነው ምክንያቴ፡፡ የተወሰኑት እንዲያውም  አልፈዋል፡፡ በሕይወት ያሉትም ቢሆን ጋዜጣ ላይ ወይም ደግሞ መጽሔት ላይ ካልሆነ በስተቀር ‹‹የሕገ መንግሥት አባት ወይንም እናት›› የምንላቸው ሰዎች እነማን እንደሆኑ ማወቅ እስከማንችልበት ድረስ ጎልተው ሲወጡ አለመታየቱ ነው፡፡ በመሆኑም የተለያዩ የአርቃቂ ኮሚሽኑንና የአፅዳቂ ጉባኤውን ቃለ ጉባዔዎችን በመመርመርም ጭምር ይኼንን ክፍተት ለመሙላት ነው ጥረት ያደረግኩት፡፡ እግረ መንገዱንም በርካታዎቹ በሕይወት ስላሉ ተጨማሪ አስተያየቶችን እንዲሰጡ መነሻ እንዲሆን ለማድረግም ጭምር ነው፡፡

  በተጨማሪም የብሔርን ሐቲት ልብ ብለን ስናጤን እየተቀየረ መጥቷል፡፡ አንድ የኅብረተሰብ ክፍል የተለየ ብሔር ነው ለማለት ይወሰዱ ከነበሩት መሥፈርቶች ውስጥ ሁሉም እየጠፉ ሄደው ተመሳሳይ ሥነ ልቦናዊ ማንነት የሚለው ብቻ የቀረ ይመስላል፡፡ በተለየ ቋንቋ መግባባት፣ በአንድ አካባቢ ተከማችተው መገኘት፣ ወዘተ አሁን አሁን ሥራ ላይ አይውሉም፡፡ የተለየ ባህል መኖርም እንደዚያው፡፡ እናም የእኛ ሕገ መንግሥት የማንነት ጥያቄ ለሚያነሱ የኅብረተሰብ ክፍሎች መለኪያው ያው የጥንቱ የነሌኒንና የነስታሊን መሥፈርት በመሆኑ ዘመኑን የዋጀ አይደለም፡፡ በዘርፉ ያለው ክርክር፣ ትርጉም፣ ንድፈ ሐሳብ በጣም ተቀይሯል፡፡ እኛ ግን ዛሬም እዚያው ላይ እነ ሌኒንና ስታሊን እንዳስቀመጡን ነን፡፡ እዚህ ላይ ምን ትዝ አለኝ መሰለህ ወሎ ውስጥ የሚነሳ ዘፈን፡፡ የከንፈር ወዳጁ ሌላ ባል አግብታበት በዚያው ስለቀረችበት ‹‹የእኔ ዓለም ዛሬም እዚያው ነሽ ወይ መካሪም የለሽ ወይ?›› የሚለው ነው፡፡ እኔም ልሂቃኖቻችንን ዛሬም እዚያው ናችሁ ወይ? መካሪም የላችሁ ወይ? ለማለት ነው፡፡ እናም አንዱ ዓላማዬ ይኼ ነው፡፡

  • ፡- የመጨረሻውን ነጥብዎትን በተመለከተ አንድ የኅብረተሰብ ክፍል አንድ የተለየ ብሔርም እንበለው ሌላ መለኪያዎቹ ምንድናቸው?

  አቶ ውብሸት፡- እርግጥ ነው አንድ ወጥ የሆነ ብያኔና መሥፈርት ላይኖር ይችላል፡፡ ይሁን እንጂ በመጽሐፌ ላይ ለማብራራት እንደሞከርኩት ዘመኑ አንድ አገር ለአንድ ብሔር (Nation-State) የሚለው አካሄድ ከቀረ ሰነባበተ፡፡ አሁን ኅብረ ብሔራዊና ብዝኃ ባህላዊ አካሄድ ነው እየሰፈነ ያለው፡፡ እናም የበርካታ ማኅበረሰብ ባህላቸው ጠፍቶ፣ ቋንቋቸውን አጥተው፣ የብሔር ስሜታቸው ግን እንዳለ ሆኖ ታገኘዋለህ፡፡ አሜሪካ አገር ያሉ ሬድ ኢንዲያንስ ወይንም ሒስፓኒኮች ከሌላው አሜሪካዊ ጋር ተመሳሳይ ቋንቋና ባህል እያላቸው በምንም ነገር መለየት በሚያዳግትበት ሁኔታ የተለየ ማንነት ሲጠይቁ ታያለህ፡፡ እናም መሥፈርቱ ምን ሆነ መሰለህ? ሥነ ልቦናዊ አንድነት ወይም ተመሳሳይነት፡፡ ይኼን ጉዳይ በቅርቡ ዕውቅና ወዳገኙት የቅማንት ሕዝብ ብናመጣውም ያው ነው፡፡ በተራዘመው የሕዝቦች ግንኙነትና መስተጋብር የቅማንት ቋንቋ እየጠፋ ቢመጣም፣ ባህልና ሃይማኖታቸው ከሌላው ጋር ቢወራረስም፣ ቁልፉ ጉዳይ ሥነ ልቦናዊ ተመሳሳይነት ነውና ቅማንትነት ግን አልጠፋም፡፡ በመሆኑም  በብሔርና ብሔርተኝነት ላይ በርካታ ጥናቶች የሠሩት ማዕምራን  ይኼንኑ ነው እንደ መሥፈርት እየወሰዱት ያሉት፡፡

  • ፡- እርስዎ አንቀጽ 39 ሁለት ጽንፍ በያዙ ወገኖች ያላግባብ ተተርጉሟል ብለው ያስባሉ?

  አቶ ውብሸት፡- በትክክል! አንደኛ ነገር ይኼ አንቀጽ የያዘው መገንጠልን ብቻ እንደሆነ ከማሰብ የመነጨ ነው፡፡ ለምሳሌ አንቀጹ ሲፀድቅ የነበረውን ቃለ ጉባዔ ብታይ ክርክሩ በሙሉ የነበረው መገንጠል ሕገ መንግሥታዊ ሽፋን ይሰጠው ወይስ ይቅር ነው፡፡ በአንድ በኩል መገንጠል በሕገ መንግሥቱ ዋስትና ካልተሰጠው አገሪቱ ብትንትኗ ይወጣል ሲሉ፣ ሌሎቹ ደግሞ በሕገ መንግሥቱ ውስጥ ማካተት ማለት በኢትዮጵያ አንድነት ላይ በቀጭን ጭራ እጅግ ስለታም ጎራዴ ማንጠልጠል ነው ባይ ናቸው፡፡ አንዱ ነካ ቢያደርገው ወይም ጭራው በጊዜ ቆይታ ቢበጠስ ጎራዴው ወድቆ ኢትዮጵያንም ይቆራርጣታል ነው፡፡  ለዚያም ነው የመጽሐፌን ማስታወሻነት በሁለቱም ጽንፍ ላይ ከቆሙት ወገኖች ውስጥ ወካይ ለሆኑት ለአቶ መለስ ዜናዊ እንዲሁም ለሻለቃ አድማሴ ዘለቀ እንዲሆን ያደረግኩት፡፡

  ሌላው እና የሚገርመው ይኼ አንቀጽ እኮ ስለ ቋንቋ፣ ባህል፣ታሪክ፣ ራስን በራስ ስለማስተዳደር፣ ስለውክልናና ስለሌሎችም በርካታ ጉዳዮችን ያቀፈ ሆኖ ሳለ፣ በሁለቱም ጽንፍ ላይ የቆሙት ወገኖች ትኩረታቸው መገንጠል ላይ ብቻ ነው፡፡ እንዲያውም ምን ሆነ መሰለህ? ስለ አንቀጽ 39 መጽሐፍ ማዘጋጀቴን የሰሙ ወዳጆቼ ‹‹አንድ መጽሐፍ እንዴት ልትሆን ትችላለች?›› ሲሉ ጠየቁኝ፡፡ ሌሎች ረቂቁን ያሳየኋቸው ደግሞ ‹‹አይ መጽሐፉ በርካታ ሐሳብ ስለያዘ በአንድ መጽሐፍ ብቻ መወሰኑ አንባቢ ዘና ብሎ ሐሳቡን እንዳያጣጥም ስለሚያደርግ ቢያንስ ሦስት መጽሐፍ መሆን አለበት›› አሉኝ፡፡ ቁም ነገሩ ምን ያህል ሰፊ መሆኑንና በቅጡ ለመረዳት አለመሞከራችንን ለማሳየት ነው፡፡

  • ፡- አንቀጽ 39 ሕገ መንግሥት የሕግ ሰነድ ብቻ ሳይሆን የሕግና የፖለቲካ ቅይጥ ነው የሚለውን ሊያስረግጥልን ይችላል?

  አቶ ውብሸት፡- እርግጥ ነው ሕገ መንግሥቱን ለማፅደቅ የተደረገውን የአፅዳቂው ምክር ቤት ቃለ ጉባዔ ላነበበ ሰው የፖለቲካ ሰነድ ብቻ እንደሆነ የተገለጸው ይበዛል፡፡ ግን እኮ ሕግ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ማኅበራዊና ባህላዊ ጉዳዮችን ከቀነስንበት ምን ላይ ድንጋጌው ይቀመጣል? ወይም ያርፋል? በመሆኑም ሕገ መንግሥቱ ኢኮኖሚ፣ ባህል፣ ማኅበራዊ ጉዳዮችና ፖለቲካን በተመለከተ ምን ምን መምሰል እንዳለበት የሚደነግግ ሰነድ ነው፡፡ ስለሆነም ይህ አንቀጽ ፖለቲካዊነቱ ከፍ ያለ ነው፡፡ ዙሮ ዙሮ ግን ሕግ ሆኗል፡፡

  • ፡- አንቀጽ 39ን የሚያስፈጽሙ ተቋማትን አፈጻጸም እንዴት ያዩታል?

  አቶ ውብሸት፡- የተቋማትን ነገር ሳስብ ሐዘኔ ብርቱ ነው፡፡ ገዳን ውሰድ እጅግ በጣም ጠንካራ ተቋም ነበር፡፡ የካፋን ሚኪርቾ ብትወስድም እንደዚያው፡፡ ለነገሩ እኮ ይክፋም ይልማም ሰሎሞናዊ ሥርዓተ መንግሥትም ለረጅም ዘመናት አገልግሏል፡፡ እናም እጅግ በጣም ድህነት የተጣባን የዴሞክራሲ ተቋማት ግንባታ ላይ ይመስለኛል፡፡ አንድ ነገር ተቋም ሆነ ስንል ልክ እንደ ባህል ሕዝቡ ውስጥ ሰርፆ  የገባ መሆን አለበት፡፡ ቅቡልነት አንዱ ባህርይው ነው፡፡ አመኔታ የሚጣልበትም ሊሆን ይገባል፡፡ ከዚህ አንፃር ይኼንን አንቀጽ በተመለከተ ያሉን ተቋማት ቀድሞ እንዲመጣ የታሰበውን ለማሳካት ፈጽሞ የሚችሉ አይመስሉኝም፡፡ አራት ጉዳዩችን ብቻ ምሳሌ በማድረግ ላስረዳ፡፡

  የመጀመሪያው ከውክልና ጋር ይያያዛል፡፡ ከሰማንያ ያላነሱ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ባሉባት አገር፣ የሕገ መንግሥቱም ግድግዳውም፣ ማገሩም፣ ምሰሶውም፣ ዋልታውም እነሱው በሆኑባት አገር፣ ከፍተኛ የአስፈጻሚው አካል አሁንም አሥር ለማይሞሉት ብቻ ነው ክፍት የሆነው፡፡ ሁሉም ብሔር፣ ብሔረሰብና ሕዝብ የሚኒስትር ቦታ ያግኝ ማለት አዳጋች ቢሆንም ከአንድ ብሔር አምስትም፣ አራትም ሦስትም ሚኒስተሮችን ግን በቋሚነት እየሾምን ነው፡፡ ሌሎቹን ደግሞ በቋሚነት ድርሽ እንዳይሉ እያደረግን ይመስላል፡፡

  ሌላው እንግዲህ በየትኛውም የፌደራል ሥርዓት የፌደሬሽኑ መሥራቾች በማዕከላዊው መንግሥት በፍትሐዊነት ሥልጣን መከፋፈል አለባቸው፡፡ ውሳኔ ሲሰጥ ሊሳተፉ ይገባል፡፡ የእነሱም ድምፅ ሊካተት ይገባል፡፡ እንግዲህ በዚህ አንቀጽ የተካተተው አንዱ መብት ይኼ ነው፡፡ ይሁን እንጂ ተግባራዊነቱን የሚከታተል ወይም ሊፈጸም የሚችልበት ምንም ዓይነት ተቋም የለንም፡፡ ስለሆነም በገዥው ፓርቲ ይሁንታ ላይ የተመሠረተ ድልድልና ክፍፍል ብቻ ነው ያለው፡፡ ከዚህ አንፃር በተለይ አምስቱ ክልሎች ተቋማዊ በሆነ መልኩ፣ ከማዕከላዊው መንግሥት እጅግ ወሳኝ ጉዳዮች ላይ ተገልለዋል፡፡ ምክንያቱም ቁልፍ ጉዳዮች በፓርቲው ነው የሚወሰኑት፡፡ የፓርቲው አሠራር ደግሞ ጥብቅ የሆነ ማዕከላዊነትን የተከተለ ነው፡፡ ስለሆነም እነዚህ የአምስቱ ክልሎች ፓርቲዎች (የአፋር፣ የሐረሪ፣ የኢትዮጵያ ሶማሊ፣ የጋምቤላና የቤኒሻንጉል ጉሙዝ) የኢሕአዴግ ‹‹አሕዛቦች›› ሆነዋል፡፡ የኢሕአዴግ ሕዝቦች ቢሆኑ ተሳታፊ ይሆኑ ነበር፡፡ ድሮ ድሮ በግልጽ በተቀመጠ ሳይሆን በገቢር ብቻ ነበር የተገለሉት፡፡ አሁን ደግሞ ተቋማዊ በሆነ መልኩ፡፡

  ሦስተኛው ደግሞ የፌደሬሽን ምክር ቤትን ይመለከታል፡፡ የፌደሬሽን ምክር ቤት አባላት አመራረጣቸው በሕገ መንግሥቱ ከተቀመጠው ግብ ከማሳካት አንፃር እጅግ ያነሰ ነው፣ አይመጥንም፡፡ ምክንያቱም አሁን ባለው አሠራር በክልል ምክር ቤት አሸናፊ የሆነው ፓርቲ ለፌደሬሽን ምክር ቤት መርጦ ይልካል፡፡ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀጥተኛ ተሳትፎ የላቸውም፡፡ ብሔሮቹ ለብቻቸው የብሔራቸውን ተወካይ አይመርጡም፡፡ ለአብነት ሐዋሳ ከተማ የሚገኝ የማንኛውም ብሔር አባላት የመረጠው አንድ ብሔሩ ሲዳማ የሆነ ሰው፣ ለፌደሬሽን ምክር ቤት አባል ሲሆን የሚወክለው የመረጠውን ሕዝብ ሳይሆን ብሔሩን ብቻ ይሆናል፡፡ በዚያ ላይ የሕገ መንግሥት ትርጉም ስለሚሰጥ ከአንድ ፓርቲ ብቻ ተመራርጠው የገቡ አባላት በገለልተኝነት ሳይሆን ፓርቲያቸውን ማስቀደማቸው ስለማይቀርእንደተቋም በቂ ቁመና እንዳይኖረው መሰናክል መሆኑ አይቀሬ ነው፡፡ እናም የፌደሬሽን ምክር ቤት ወይ ሕገ መንግሥት መተርጎሙ ቀርቶ (ለምሳሌ የሕገ መንግሥት ፍርድ ቤት ቢቋቋም) ሌሎቹን ሥልጣኖቹን ይዞ ቢቀጥል፡፡ አለበለዚያ አባላቱ ሲመረጡ ከፖለቲካ ፓርቲ ያልሆኑና በብሔሩ በቀጥታ ምርጫ መከናወን አለበት ባይ ነኝ፡፡

  ሦስተኛው ማሳያዬ መገንጠልን የተመለከተ ነው፡፡ የሰይጣን ጆሮ አይስማና አንዱ ብሔር ልገንጠል ቢል ከዚህ ጋር ተያይዞ የሚከናውንን ሕዝበ-ውሳኔ የሚከውን ምርጫ ቦርድ የለንም፡፡ እንበልና አፋር ልገንጠል ቢልና ድምፅ ቢሰጥ እኮ የፌደራሉ መንግሥት ምርጫ ቦርድ ነው ሊያስፈጽም የሚችለው፡፡ ይታይህ ግንጠላው የሚፈጸምበት በጊዜያዊነትም ቢሆን ቅራኔ ውስጥ የገባህበት አገር ተቋም፡፡ ቅሬታ ቢኖርህም መልሰህ ውደ ኢትዮጵያ (ቀሪው አገር) ተቋም ነው የምትመለሰው፡፡ ከእኛ ከአሥራ ሁለት ዓመታት በፊት የመገንጠል አንቀጽ በሕገ መንግሥቷ ያካተተችው ሴንት ኪትስና ኔቪስ ግን ኔቪስ መገንጠል ብትፈልግ አስተዳዳሪዋ አንድ ኃላፊ ይሰይማል፡፡ የአገሪቱ ጠቅላይ ሚነስትር አንዱ ዕጩና ተቃዋሚ ፓርቲዎች አንድ ዕጩ አቅርበው በኔቪስ አስተዳዳሪ ሲፀድቅ አባል ሆነው የምርጫ ቦርድ ያዋቅራሉ፡፡

  ከዚሁ ከመገንጠል ጋር የሚያያዘው የሚገነጠለው ብሔር ምክር ቤት በ2/3ኛ አብላጫ ድምፅ መወሰን አለበት፡፡ እንግዲህ የተወሰኑ ክልሎች ላይ ይኼም ችግር ያለበት መሥፈርት ነው፡፡ ለአብነት አማራ ክልል ልገንጠል ቢል የአማራ ብሔር ብቻውን ምክር ቤት የለውም፡፡ በመሆኑም አገው ኽምራዎቹ፣ አዊዎቹ፣ አርጎባዎቹ፣ ኦሮሞዎቹ፣ ቅማንቶቹ ከምክር ቤቱ ሊወጡ ነው፡፡ ድምፅ አይሰጡም ማለት ነው፡፡ በተጨማሪም ሕዝበ ውሳኔ ሲካሄድ በክልሉ ውስጥ የሚኖሩት የሌሎች ብሔር ተወላጆች ለምሳሌ አማራ ያልሆኑት ምንም ሚና የላቸውም፡፡ ሕገ መንግሥታችን ምንም ያለው ነገር የለም፡፡ በመጽሐፌ የገለጽኳቸው ሌሎች በርካታ ያላላቸው ነገሮች አሉ፡፡ በድንገት የመገንጠል ጥያቄ ቢመጣ በሰላማዊ መንገድ ለመጨረስ የሚጠቅሙ ያልተካተቱ ጉዳዮች አሉ፡፡ ካልሆነ ግን የዚህ አንቀጽ መቀመጥ ስማዊ ወይም ትዕምርታዊ (Symbolic) ብቻ ሆኖ ይቀራል፡፡

  • ፡- አንቀጽ 39ን በተመለከተ አንድም በማስረፅ በሌላ በኩል ደግሞ ፍርኃትና ጥርጣሬ በማንገስ ልሂቃኑ የተጫወቱትን ሚና እንዴት ይገልጹታል?

  አቶ ውብሸት፡- አንዳንዱ ከስም አጠራሩ ጀምሮ ነው ችግር ያለበት፡፡ ሥርዓቱ ላይ ላላቸው ጥላቻ ያልተገባ አጠራር ሁሉ ይጠቀማሉ፡፡ ጎሳ፣ ዘር፣ ነገድ፣ ወዘተ. በማለት፡፡ መቼም አፋርን ወይም ሶማሌን ጎሳ ብለው ከጠሯቸው በሥራቸው ያሉትን ምን ሊሏቸው እንደሆነ አይገባኝም፡፡ ኦሮሞን ጎሳ ነው ማለትም ንቀት ይመስለኛል፡፡ እነዚህን አጠራር የሚጠቀሙት ባለማወቅ አይመስለኝም፡፡ ምንጩ ጥላቻ ነው የሚመስለኝ፡፡ በነሌኒን እስታሊን አተረጓጎምም ይሁን የአገራችን ሕዝብ ከሚያውቀው አንፃር ስህተት  ነው፡፡

  በተቃራኒው ደጋፊዎቹ ደግሞ እጅግ ብዙ ስህተት እንዳለበት እንኳን ለማሰብ ሳይሞክሩ፣ የችግራችን ሁሉ መፍትሔ ሥራይ አድርገው የመቁጠር አባዜ ተጠናውቶናል፡፡ ከችግሮቹ ውስጥ የተወሰኑት ከላይ የገለጽኳቸው ሲሆኑ ሌሎች በርካታ ችግሮች አሉ፡፡ መጽሐፌ ውስጥ ገልጫቸዋለሁ፡፡ እናም ሁለቱም ወገኖች እርስ በርስ በመኮናነናቸው ጽንፍ እንደረገጡ እየተሰዳደቡ እንደቀጠሉ ናቸው፡፡ እኔ ግን በተቻለ መጠን ስድባዊ የሆኑ አገላለጸችን ለማጥፋት ሞክሬያለሁ፡፡ ይኼን አንቀጽ በመደገፍህ ወይም በመቃወምህ ባንዳም ይሁን አርበኛ መባል የለብህም፡፡ ጣሊያን አምስት ዓመት ኢትዮጵያ ውስጥ ሲቆይ ቀጥሮ ያሠራቸውንም፣ አስሮ ለዕለት ጉርስ የሚሆንን ቀለብ የቆረጠላቸውን ባንዳ፡፡ በድንገት በረሃ ገብተው ሲፋለሙ ለነበሩት አንድ ጠቦት ስለሰጡ አርበኛ እያሉ በየመጽሐፉና በየጋዜጣው ሥራዬ ብለው የሚጽፉትን መድገም ያለብን አይመስለኝም፡፡ ሐሳብን በነፃ የማራመድ፣ ወይም የመሰለንን አመለካከት የመያዝመብት እንጂ፡፡

  ሕገ መንግሥት ላይ ሲካተት ግን ከዚህመላቅ አለበት፡፡ የጋራችን ነዋ፡፡ በውይይት ብሎም በመግባባት ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓት ማስፈን አለብን፡፡ አንድ መንግሥት ሲወድቅ ወይም ሲሻር አብሮ የሚሻር ሕገ መንግሥት እንዳይሆን የቅቡልነቱን መጠን መጨመር አለብን፡፡ አለበለዚያ አሁን ያሉት የተወሰኑት ፓርቲዎች ፕርግራም ላይ እንደሚታየው ሥልጣን ቢይዙ የሚሻሻሉ ሰላሳና አርባ አንቀጾች ካሉ አሁንም እንደ አዲስ መጀመራችን አይቀሬ ነው ማለት ነው፡፡ ስለሆነም በሁሉም ወገን ያሉት ልሂቃን ውግዘታዊ ናዳቸው በማቆም ለጋራችን ቤት መጣር አለብን፡፡ አጉል ጥርጣሬም ማስፈን፣አጉል መተማመንም መጣል ብዙ ተገቢ አይመስለኝም፡፡ እናም ወደ ስምምነት ሊያመጣ በሚችል መልኩ አስተዋጽኦ ሊያበረክቱ ይገባል፡፡

  • ፡- አንዳንዶች አንቀጽ 39 የተወሰኑ ብሔር፣ ብሔረሰብና ሕዝብን ሲጠቅም የተወሰኑትን ደግሞ ይጎዳል የሚሉ አሉ:: የእርስዎ አስተያየት ምንድነው?

  አቶ ውብሸት፡- እ…ሆን ተብሎም ይሁን በቸልተኝነት፣ ወይም ባለማወቅ፣ ወይም ከአቅም በላይ በሆነ ምክንያት የዚህ አንቀጽ አንድምታ በተወሰኑ ብሔሮች ላይ የተለያየ ነው፡፡ ሕገ መንግሥቱ በእርግጥ እኩል እንደሆኑ ቢደነግግም በተጨባጭ ሁሉንም ብሔር፣ ብሔረሰብና ሕዝብ እኩል እየጠቀሙ ነው ብሎ መናገር ትልቅ ክህደት ነው የሚሆንብኝ፡፡ በሕግ እኩል ብንሆንም በተግባር እኩል ነን ማለት ግን አዳጋች ነው፡፡ ከፓርቲ ስያሜ ብትጀምር የብሔረ አማራ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ ይልና በውስጡ ግን ሁለቱንም አገዎች፣ በክልሉ የሚገኙ ኦሮሞዎችንም ይይዛል፡፡ እነዚህ ግን አማራ አይደሉም፡፡ ስሙ ይኼንን ሊያጠቃልል ይገባ ነበር፡፡ የትግራይም ያው ነው፡፡ አንድ የሚገርም ነገር ልንገርህ፡፡ የአማራ ክልል የሕዝብ መዝሙር አለ፡፡ ይኼ መዝሙር ‹‹ለአማራነት ክብር…›› የሚል ሐረግ አለው፡፡ እንግዲህ ያሳይህ ኦሮሞውም፣ አገውም በሠልፍ ቆመው ‹‹ለአማራነት ክብር›› እያሉ ይዘምራሉ፡፡

  የነፍጠኛ ሥርዓትን እየተዋጋሁ ነው የሚል ፓርቲ ወይም መንግሥት ሌላ የነፍጠኛ ሥርዓት እንዳያሰፍን ጥንቃቄ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ ይኼ ሥርዓት ቢወርድ ከዚህ አካባቢ የተነሱ ጥቂት የእንቶኔ ብሔር አባላት ማለት እንዳይመጣ ነው፡፡ በፌደራልም ይሁን በክልል ተመሳሳይ አድራጎቶች አሉ፡፡ ለአብነት ደቡብ ብትሄድ ርዕሰ መስተዳድርነት ለሲዳማ ወይም ለወላይታ ብቻ ከሆነ፣ ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ደግሞ ለበርታ ወይንም ለጉሙዝ ብቻ ከሆነ ተመሳሳይ ሥርዓት በክልል እንዳናሰፍን መሥራት አለብን፡፡

  ወያኔ ወይም ኢሕአዴግ የሚለውም አጠራር ሊያሳስበን ይገባል፡፡ አጠራር በሕግ አይቀርም፡፡ የሚያስጠራውን ድርጊት ባለመፈጸም እንጂ፡፡ ሌሎች ዝርዝር ጉዳዮች መግባት ተገቢ አይመስለኝም፡፡ ጉዳዩ የብሔር ጉዳይ አይደል? የምናውቀው የማንናገረው፣በጓደኝነት ደረጃ ብናወራው እንኳን በአደባባይ የማንናገረው፣ ወይም የማይጻፍ ብዙ ነገር አለ እኮ፡፡ አንዳንዴየብሔር ጉዳይና ብሔርተኝነት በተኛ ውሻ ባህርይ ይመሰላል ይላሉ፡፡ ተኝቷል ስትለው በድንገት ነቅቶ ሊጠራርግ የሚችል፡፡ ዩጎዝላቪያና ሩዋንዳ እንደዚያ አይደል የሆነው? ዘር ጠራጊ ዴሞክራሲ ይሉሃል ይኼ ነው፡፡ ደግሞ አንዴ ከተነሳ በቀላሉ የማይበርድና የሚመክተው ኃይል እንኳን የለም፡፡ በመጽሐፌ ጀርባ ላይ ዶ/ር ዳኛቸው አሰፋ የሰጠው አስተያየት ላይ ይኼንኑ ነው የምታገኘው፡፡ ከዴሞክራሲ፣ ከሶሻሊዝም፣ ከሊብራሊዝም ጋር ብትጋጭ ታሪክ የመሰከረው አሸናፊዋ ብሔርተኝነት እንደሆነች ነው፡፡ በመሆኑም ተጎድተናል የሚሉ ብሔሮች እንዳይኖሩ መሥራት አለብን፡፡ ሌላው ‹‹አልተጎዳችሁም›› ቢላቸው እንኳን መልስ አይሆንም፡፡ መልሱ ራሳቸው ‹‹አልተጎዳንም›› ማለታቸው እንጂ፡፡

  • ፡- አንቀጽ 39 የአገዛዙ አወቃቀር ዋናው መሠረት ከመሆኑ አንፃር በኢሕአዴግ የሥልጣን ዘመን የመሻሻል ዕድል ሊኖረው ይችል ይሆን?

  አቶ ውብሸት፡- ይኼንን ለመመለስ ከኢሕአዴግ ውስጥ በጣም በጣት የሚቆጠሩትን ሰዎች መሆን የሚጠይቅ ይመስለኛል፡፡ ግን እንዲህ ልገምት እችላላሁ፡፡ ለምን ተካተተ? እናም በምን ምክንያት ሊሻሻል ይችላል? የትውልድ ሕልፈት መልስ ሊሆን ይችል ይሆን? ብዬም አስባለሁ:: አሁን በሕገ መንግሥቱ የተቀመጠው ከተጋድሎ ሓርነት ህዝቢ ትግራይ (ተሓህት) መግለጫ ከ1968 ዓ.ም. በፊት እኮ የኢሕአፓው ብርሃነ መስቀል ረዳ (ጥላሁን ታከለ በሚል የብዕር ስም) አልጄሪያ ሆኖ የጻፈው ቃል በቃል በሚል ደረጃ ግልባጭ ነው፡፡ ያ ትውልድ ኢሕአፓም ሁን ሕወሓት  መልሱ ተመሳሳይ መሆኑን ይነግረናል፡፡ እነ ዋለልኝም፣ ብርሃነ መስቀልም፣ ሌሎች የሕወሓትም፣ የኢሕዲንም፣ የመኢሶንም፣ ወዘተ.  እያልክ ብትቆጥር የእነዚህ ሁሉ አባላት ቢጠና  የመደብ ጥያቄ ሲመለስ የብሔር ጥያቄ አብሮ ይመለሳል ሊሉ ይችሉ ይሆናል እንጂ፣ የብሔር ጥያቄን ያላነገበ የለም፡፡ ስለዚህ ያ ትውልድ በዋናነት በሥልጣን ላይ እያለ መሠረቱ ይቀየራል የሚል እምነት አይኖረኝም፡፡ አንድ ነገር ግን ግልጽ ይመስለኛል፡፡ የሕገ መንግሥቱ ዋና መሠረት የመሆኑ ጉዳይ የሚሻሻል አይመስለኝም፡፡ ምናልባት የተወሰኑ ጉዳዮች ቢስተካከሉ ጥሩ ነው፡፡ የትኞቹ ካልከኝ በርከት ስለሚሉ መጽሐፌ ውስጥ ስለተካተቱ ያንን ማየት የሚሻል ይመስለኛል፡፡

  • ፡- ባለፉት ሁለት አሥርት ዓመታት የነበረውን የማንነት ፖለቲካ እንዴት ይገልጹታል?

  አቶ ውብሸት፡- አራት ትዝብቶች ናቸው ያሉኝ፡፡ የስልጤ በሕዝበ-ውሳኔ የተሰጠ ዕውቅና አንዱ አካሄድ ነው፡፡ ቡታጅራ ላይ የተከናወነው ውሳኔ ስህተት ስለነበር በፌደሬሽን ምክር ቤት አማካይነት ሕዝበ-ውሳኔ ተከናውኖ ዕውቅና አገኙ፡፡ ሁለተኛው ደግሞ የቅማንት ጉዳይ ነው፡፡ እነሱን በተመለከተ ሕዝበ-ውሳኔ አልተከናወነም፡፡ ይልቁንም የአማራ ክልል ምክር ቤት ውሳኔ ሲያሳልፍ ‹‹በላይ አርማጨሆና በጭልጋ አካባቢ ራሳቸውን ቅማንት ብለው የሚጠሩ ሕዝቦች ያሉ ሲሆን፣ ሌሎቹም ቅማንት እንደሆኑ ይቆጥሯቸዋል፤›› በማለት ዕውቅና የተሰጠበት ሒደት ነው፡፡ ይኼ ለስልጤ ከነበረው አካሄድ ፈጽሞ የተለየ ነው፡፡ የቅማንት የሚመስለው አካሄድ ደቡብ ክልልም ውስጥ ተከናውኗል፡፡ በ1987 ዓ.ም. በክልሉ ዕውቅና ተሰጥቷቸው የፌደሬሽን ምክር ቤት ወኪል የነበራቸው ብሔሮች 46 አካባቢ የነበሩ ሲሆን አሁን ወደ 56 ገደማ ናቸው፡፡ በመሆኑም ብዙም ኮሽታ ሳይሰማ ዕውቅና የተሰጣቸው አሉ ማለት ነው፡፡

  ሦስተኛው የሌሎቹ ደግሞ በፌደሬሽን ምክር ቤት ውድቅ የተደረጉ ጥያቄዎች ናቸው፡፡ እነሱ እያሉ ምክር ቤቱ ዕውቅና ነፈጋቸው፡፡ እንደ ስልጤም ሕዝበ-ውሳኔ አላደረጉም፡፡ እንደ ቅማንትም ምክር ቤቱ ዕውቅና አልሰጣቸውም፡፡ አንዳንዶቹ እንዲያውም በሕዝብና ቤት ቆጠራ ታውቀውም ወይም ተቆጥረው የፌደሬሽንም ምክር ቤት ግን አያውቃቸውም፡፡ በአንድ አገር ያሉ ሁለት ተቋማት የተለያየ ውሳኔ መኖር ለግጭትም መንስዔ ይሆናል፡፡ የቅማነት ጉዳይ ለዚህ ጥሩ ማሳያ ነው፡፡ ቅማንት በ1987 ዓ.ም. ከ170,000 በላይ ሕዝብ የነበረው ሲሆን፣ በ1999 ዓ.ም. ግን ስሙ የለም፡፡ እናም የማንነት ጥያቄ ተነሳ፡፡ መኖርህ ሲረሳ ያኔ ጥያቄ ይነሳል፡፡

  እናም አሁን በርካታ የማንነት ፖለቲካ ምሁራን እነቻርለስ ቴይለርን ጨምሮ፣ ዕውቅና ሰጪ የሚባል ሌላ ተቋም አያስፈልግም ባይ ናቸው፡፡ ለኦሮሞ ኦሮሞነት ከኦሮሞ ከራሱ ውጪ ሌላ ማን ያገበዋል? ለሌላውም እንደዚሁ፡፡ ይኼ አራተኛ ትዝብቴ ነው፡፡ ሕገ መንግሥቱ ሲረቀቅና ሥራ ላይ ሲውል የነበሩ ብሔሮች የማንንም ዕውቅና ሳይሹ ታወቁ፡፡ ለምሳሌ አማራ፣ ኦሮሞ፣ ትግሬ ወዘተ፡፡ እነዚህ የመሠረቱት የፌዴሬሽን ምክር ቤት ለሌሎች አላችሁ ወይም የላችሁ ባይ ሆነ ማለት ነው፡፡ ቻርለስ ቴይለር እንኳን ያልሰማ እልሃለሁ፡፡

  ለማጠቃለል ዕውቅና አሰጣጡ ብዙም ወጥ የሆነ አካሄድና ሥርዓት እየታየበት አይደለም፡፡ እንዲያውም የፌደሬሽን ምክር ቤት የዚህ ዓመት የመጨረሻ ስብሰባ ላይ የተወሰኑትን ውሳኔዎች በተመለከተ አንዱ ባለሥልጣን ስለምን የተወሰኑ ማኅበረሰቦች ዕውቅና እንዳላገኙ ሲናገሩ ‹‹ቋንቋ ስለሌላቸው ነው›› በማለት መልስ ሰጡ፡፡ ለማለት የፈለጉት የተለየ ቋንቋ የላቸውም ይመስለኛል፡፡ ግን ሕገ መንግሥቱ የሚለው የሚግባቡት እንጂ የተለየ ቋንቋ አይደለም፡፡ የቅማንትን ብንወሰድ አሁን ባለው ተጨባጭ ሁኔታ አምስት በመቶ የሚሆነው ሕዝብ እንኳን ቋንቋውን የሚናገር አይመስለኝም፡፡ ግን በአማርኛ ይግባባሉ፡፡ በአማርኛ የሚግባቡ ቅማንቶች፡፡ በእንግሊዝኛ የሚግባቡ ሬድ ኢንዲያንስ አይደሉ አሜሪካ ያሉት? እናም ሌላው ጉዳይ የተለየ ቋንቋ ማለትስ ምን ማለት ነው? ምን ያህል ፐርሰንት ከሌላ ቋንቋ ሲለያይ ነው ተለየ የሚባለው? እንግዲህ ወይ የሥነ ልሳን ምሁራን ሳይንሳዊ መሥፈርት ሊያስቀምጡና በዚያው ልንገዛ ይገባናል፡፡ ምክንያቱም መንጃ በከፊል ከካፋና በከፊል ደግሞ ከሸካ ጋር እንደ ቅርበታቸው ተመሳሳይ ናቸው እንጂ የተለዩ አይደሉም፡፡ ይልቁንም ልዩነቱ የዘየ ነው ካልን ወላይታ ከጋሞ፣ ጎፋ ከዳውሮ ጋር ያላቸውን ልዩነት የሥነ ልሳን ምሁራን ልዩነታቸው የዘዬ ነው የሚሉ አሉና ግልጽ አሠራር ሊዘረጋ ይገባል፡፡ እንደ ፖለቲካው ሁኔታ ብቻ መልስ መስጠት ዘላቂ ሰላም አያመጣም፡፡ እንጂ ካፋ ሂደህ ‹‹መንጃ ካፋ ነው ወይ?›› ብትለው መልሱ ፈጽሞ ‹‹አይደለም ነው›› የሚልህ፡፡ መንጃ የሆነውንም ብትጠይቀው ‹‹መንጃ መንጃ እንጂ ካፋ አይደለም›› ነው የሚሉህ፡፡ ካፋና ሸካዎች እንደዚያ ነው ያሉኝም ጓደኞች አሉኝ፡፡

  • ፡- በአግባቡ ያልተረዳነው የአንቀጽ 39 የትኛውን ክፍል ነው ይላሉ?

  አቶ ውብሸት፡- በጣም በአግባቡ ያልተረዳነው የቡድንና የግለሰብ መብትን ግንኙነት ነው፡፡ ይኼ አንቀጽ የሚደነግገው ስለ ቡድን መብት ነው፡፡ የግለሰቦችን መብት በተመለከተ በርካታ አንቀጾች ቢኖሩም የብዙዎቸ ትኩረት ስለቡድኖቹ ብቻ ነው፡፡ ከአንድ አካባቢ የሆኑ ግለሰቦች ተባረሩ ሲባል ትዝ የሚለን ብሔራቸው ነው፡፡ የተባረሩበትም ክልል ይሁን ወረዳ ያለፈቃድ እንደመጡ ብሔሮች መቁጠር አዝማሚያ ይስተዋላል፡፡ ሕገ መንግሥቱ ማንኛውም ኢትዮጵያዊ በየትኛውም የአገሪቱ ክልል ተዘዋውሮ የመሥራት መብትን ያረጋገጠ ቢሆንም፣ በተገቢው ሁኔታ ግን እንዲከበር እየተደረገ አይደለም፡፡ እዚህ ላይ ሕገ መንግሥቱ ሲፀድቅ አንዳንዶቹ የቡድንና የግለሰብ መብት ሲጋጩ የቡድን መብት ቅድሚያ እንደሚሰጠው የገለጹ ሲሆን፣ የመንግሥት የዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ ፖሊሲ ላይ አንዱ ከአንዱ ቅድሚያ ሊሰጠው አይገባም፡፡ ይልቁንም ሁለቱም በትይዩ ሥራ ላይ መዋል አለባቸው ይላል፡፡ ነገር ግን በአፈጻጸም ቀድሞ ቃለ ጉባዔው ላይ ያለው ይመስላል የሚተገበረው፡፡ እናም በአግባቡ ልንረዳው ይገባል እንጂ ቅድሚያ ለቡድን መብት የሚባል ሕገ መንግሥታዊ ድንጋጌም፣ አንድምታም የለም፡፡

  • ፡- አንቀጽ 39 ላይ መግባባትና መስማማት ቢመጣ አዲስና ጤናማ የሆነ አስተዳደር መጀመሪያ ይሆናል?

  አቶ ውብሸት፡- በትክክል! መምጣትም አለበት፡፡ አለበለዚያማ ያው መመለሳችን ነው፡፡ ወሳኝ የሆኑ የሕገ መንግሥት መርሆች ላይ መስማማት አለብን፡፡ የሚቀየረው ተቀይሮ ወይም ተሻሽሎ፡፡ በዚያ ላይ የብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ሉዓላዊ መሆን አንዱ የሕገ መንግሥት መርህ ነው፡፡ መርህ የሆኑ ጉዳዮች ላይ መስማማት ካልቻልን በዝርዝር ጉዳይ ላይማ ልንስማማ እንዴት ይቻለናል? ስምምነት ሲፈጠር አዲስ አስተዳደር ሥርዓት ሊኖር ግድ ይመስላል፡፡ አንዳንዶቻችን በዚህ ጉዳይ ጠርዝ ላይ የቆሙትን ወገኖች ተስማሙ እያልን እኮ ነው፡፡

  spot_img
  - Advertisement -

  ትኩስ ጽሑፎች

  ተዛማጅ ጽሑፎች

  - Advertisement -
  - Advertisement -