– ሰባት ደላሎች በቁጥጥር ሥር ሲውሉ በአንዱ ላይ ክስ ተመሠረተ
ወደ ተለያዩ ዓረብ አገሮች የሚሄዱ ኢትዮጵያውያንን ሞት፣ አካል መጉደልና እንግልትን እየደረሰባቸው በመሆኑ መንግሥት እንዳይሄዱ ዕግድ የጣለ ቢሆንም፣ በተለይ ቀደም ብሎ ስደት በማይታወቅባቸው ገጠራማ አካባቢዎች ቁጥራቸው ከፍተኛ የሆኑ ወጣቶች በሕገወጥ መንገድ እየተሰደዱ መሆኑን፣ መንግሥት ሐምሌ 4 ቀን 2007 ዓ.ም. አስታወቀ፡፡
ሕገወጥ የሰዎች ዝውውር ተከላካይ ብሔራዊ ምክር ቤት የ2007 ዓ.ም. ዕቅድ አፈጻጸምን አስመልክቶ ባደረገው ግምገማ፣ በፌዴሬሽን ምክር ቤት ተሰብስበው ለነበሩ ባለድርሻ አካላት እንደተገለጸው፣ ሕገወጦችን መከላከል የሚያስችል እስከ ሞት ድረስ ቅጣት የሚጥል ሕግ ከማውጣት ባለፈ፣ ለማስፈጸም ተግቶ የሚሠራ አካል ባለመኖሩ ችግሩን ማቆም እንዳልተቻለ ተገልጿል፡፡
በአማራ፣ በትግራይ፣ በኦሮሚያና በደቡብ ክልሎች በሕገወጥ የሰዎች ዝውውር ላይ ጥሩ ሥራ የተሠራና የተሻለ ውጤትም የታየበት መሆኑን የገለጹት የምክር ቤቱ ሰብሳቢ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ አቶ ደመቀ መኰንን፣ የሕገወጥ ደላሎች አሠራር በየጊዜው ስለሚቀያየር የዜጐች ጉዳት እየጨመረ መምጣቱንና የተደረገውም ጥረት አርኪ አለመሆኑን ተናግረዋል፡፡
በዜጐች ላይ እየደረሰ ያለውን ጉዳትና አደጋ የሚመጥን እንቅስቃሴ አለመደረጉን የተናገሩት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ይህ የሚያሳየው የሕገወጥ ደላሎቹ መተላለፊያ የሆኑት ክልሎች፣ መንግሥትና ኅብረተሰቡ ባለመግባባታቸው ነው ብለዋል፡፡ በአገራቸው ሠርተው መለወጥ የሚችሉ በርካታ ዜጐች ለከፋ ጉዳት እየተዳረጉ መሆናቸውንም አክለዋል፡፡ በዜጐች ላይ እየደረሰ ያለው ጉዳት የአገርን ገጽታ ጭምር የሚያበላሽ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡
በቱሪስት ቪዛ እየተሰደዱ ያሉት ዜጐች ቁጥር እየጨመረ መምጣቱንና ዕግድ በተጣለባቸው ኳታርና የመን ሕጋዊ ሽፋን እየተሰጣቸው ለከፋ አደጋ እየተጋለጡ የሚገኙ ዜጐች ጉዳይ አሳሳቢ ደረጃ ላይ መድረሱን የገለጹት ደግሞ፣ የጠቅላይ ሚኒስትሩ አማካሪ አቶ ሰለሞን ተስፋዬ ናቸው፡፡ ሕገወጥ ደላሎችን ወደ ሕግ ለማቅረብ የተቀናጀ አሠራር የሚያስፈልግ ቢሆንም፣ እስካሁን ክልሎችም ሊተገብሩት ባለመቻላቸው አሳሳቢ ደረጃ ላይ መድረሱን ጠቁመዋል፡፡
አቶ ደመቀ ሕገወጥ ደላሎች ባለሁለት ፎቅ ሕንፃ በመገንባት ሀብታቸውን ሲያፈሩ፣ በሕገወጥ ደላሎችና የጉዞ መስመር የሄዱ ወጣቶች ግን የአውሬ ሰለባ እየሆኑ እንደሆነ ጠቁመው፣ ሁሉም የኅብረተሰብ ክፍል ተባብሮ ሊታገል እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡ መንግሥት በተለይ በኢትዮጵያውያን ላይ የሳዑዲ ዓረቢያ ዜጐች ግድያ፣ አካል ማጉደልና ከፍተኛ እንግልት ካደረሱ በኋላ በሕጋዊ መንገድ ፈቃድ አውጥተው የውጭ አገር ሥራና አሠሪን የሚያገናኙ ኤጀንሲዎች ሥራቸውን እንዲያቆሙ በመደረጉ፣ በከፍተኛ ችግር ውስጥ መሆናቸውን እየገለጹ ይገኛሉ፡፡
መንግሥት በአጭር ጊዜ አሠራሩን አስተካክሎ ኤጀንሲዎቹ ሥራቸውን እንደሚቀጥሉ የገለጸ ቢሆንም፣ የቤት ኪራይና የሠራተኛ ደመወዝ እየከፈሉ ከነገ ዛሬ ሥራ እንደሚጀምሩ የሚጠባበቁ ቢሆንም፣ መንግሥት ስለነሱ ምንም ሳይባልና የስብሰባው አካልም ሳያደርጋቸው መቅረቱ እንዳሳዘነው የኤጀንሲዎች ማኅበር ገልጿል፡፡ ብሔራዊ ምክር ቤቱ እንዳረጋገጠው፣ በአሁኑ ጊዜ በከፍተኛ ሁኔታ ዜጐች እየተሰደዱ መሆኑን የሚናገሩት ኤጀንሲዎቹ፣ ሕንፃ መገንባት ብቻ ሳይሆን ሌሎች ከፍተኛ ሀብቶችን ሕገወጥ ደላሎች እያከማቹ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በሌላ በኩል በሕገወጥ የሰዎች ዝውውር ሥራ በመሰማራት የተጠረጠሩ ሰባት ግለሰቦች በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን ፖሊስ አስታውቋል፡፡ የፌዴራል ፖሊስ ከዓለም አቀፍ የፖሊስ ድርጅት (ኢንተርፖል) ጋር በመተባበር ባደረገው ክትትል ኬንያ፣ ታንዛኒያና ሱዳን ውስጥ የነበሩት እነዚህን ሕገወጥ ደላሎች ወደ ኢትዮጵያ እንዳስመጣ ተገልጿል፡፡ በሌሎች አገሮች በቁጥጥር ሥር የዋሉት ሕገወጥ ደላሎች አገር ውስጥ ካሉ ደላሎች ጋር ግንኙነት በመፍጠር፣ በሕገወጥ መንገድ በርካታ ዜጐችን ወደ ተለያዩ አገሮች ይልኩ እንደነበር የፌዴራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ዘርፍ የሕገወጥ ሰዎች ዝውውር ወንጀል ምርመራ ዲቪዚዮን ኃላፊ ምክትል ኮማንደር ወንድሙ ጨማ ተናግረዋል፡፡
በቦሌ ክፍለ ከተማ ውስጥ ነዋሪ መሆኑ የተገለጸው አቶ መሐመድ ሐሰን የተባለ ተጠርጣሪ ደላላ ደግሞ፣ ሰባት ወጣቶችን በሱዳንና በሊቢያ አድርጐ ወደ አውሮፓ እንደሚልካቸው በማነጋገር፣ ከጅግጅጋ ወደ አዲስ አበባ አምጥቷቸው አዲስ አበባ ላይ በቁጥጥር ሥር ውሎ ክስ ተመሥርቶበታል፡፡ ግለሰቡ በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ ሁለተኛ ወንጀል ችሎት ስምንት ክሶች የተመሠረተበት ሲሆን፣ የዋስትና መብቱን ተነፍጐ በማረሚያ ቤት እንዲቆይ ተደርጓል፡፡
ግለሰቡ ሐረር ከተማ ውስጥ ከሚገኙ ግብረ አበሮቹ ጋር በመቀናጀት፣ ሰባቱን ወጣቶች ከጅግጅጋ ወደ አዲስ አበባ አስመጥቶ ካዛንችስ አካባቢ በአንድ ሆቴል ውስጥ አልጋ ከያዘላቸው በኋላ፣ ማንም ቢጠይቃቸው ኢትዮጵያዊ እንዳልሆኑ እንዲናገሩ በማስጠንቀቅና ኢትዮጵያዊ መሆናቸው ከታወቀ ለስደት የመጡ መሆናቸው እንደሚታወቅና ሊታሰሩ እንደሚችሉ በመንገር፣ መታወቂያቸውን መፀዳጃ ቤት ውስጥ እንዲከቱ ማድረጉን የዓቃቤ ሕግ ክስ ያስረዳል፡፡
ዓቃቤ ሕግ ስምንት ክሶችን የመሠረተበት አቶ መሐመድ፣ ወጣቶቹን ለመምከርና ለማስጠንቀቅ ያደረገው ሙከራ ብዙም ቀናት ሳይጠቀምበት በቁጥጥር ሥር መዋሉን ክሱ ይገልጻል፡፡ በሱዳንና ሊቢያ አድርገው ጣሊያን እንደሚገቡ የተነገራቸው ወጣቶቹ፣ ለጉዞው የሚጠበቅባቸውን ክፍያ ሊቢያ ሲደርሱ ለቤተሰቦቻቸው በመደወል፣ እንዲልኩላቸው እንደሚያደርጉ ተስማምተው እንደነበር ክሱ ይገልጻል፡፡ ተከሳሹ ድርጊቱን እንዳልፈጸመ የገለጸ ቢሆንም፣ ዓቃቤ ሕግ አራት ምስክሮችን አሰምቶ ፍርድ ቤቱ እንዲከላከል ብይን በመስጠት፣ ለጥቅምት 30 ቀን 2008 ዓ.ም. ቀጥሮታል፡፡