Saturday, November 26, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - Advertisment -
  - Advertisment -

  ግምገማዎች አይድበስበሱ!

   በገዥው ፓርቲ ኢሕአዴግ አባል ድርጅቶችም ሆነ በመንግሥት መዋቅሮች ውስጥ የሚካሄዱ ግምገማዎች ጥራታቸው በጣም እየቀነሰ ነው፡፡ በሀቅና በጥንካሬ ሳይሆን በማድበስበስ የሚታለፉ ግምገማዎች እየበዙ ነው፡፡ ኢሕአዴግ በቅርቡ ጠቅላላ ጉባዔውን ለማድረግ በዝግጅት ላይ ይገኛል፡፡ ከዚያ በፊት አራቱ አባል ድርጅቶችም እንዲሁ፡፡ ኢሕአዴግ በ5ኛው ጠቅላላ ምርጫ ከአጋሮቹ ጋር የፓርላማውን መቀመጫዎች ሙሉ በሙሉ ተቆጣጥሯል፡፡ በሕዝብ ውስጥ የሚነሱ ፋታ የማይሰጡ የብሶት አቤቱታዎች ስለተበራከቱ ጠንካራ ግምገማ ያስፈልገዋል፡፡

  ኢሕአዴግ በአገሪቱ ውስጥ አሉ የሚገባሉ ችግሮችን በአስቸኳይ የመፍታት ኃላፊነት አለበት፡፡ ነገር ግን በየደረጃው የሚያደርጋቸው ግምገማዎች ምን ይመስላሉ? አገርን የሚያህል ትልቅ ነገር ለመምራት ከሚያስፈልጉ በጣም መሠረታዊ ጉዳዮች መካከል የሕግ የበላይነት ማስከበር፣ ሰብዓዊና ዴሞክራሲያ መብቶችን ማክበር፣ የሕዝቡን ሰላምና ደኅንነት መጠበቅ፣ መልካም አስተዳደር ማስፈንና የመሳሰሉት ይጠቀሳሉ፡፡ በእነዚህ መስኮች የተከናወኑ ሥራዎችን በሚገባ ገምግሞ ትክክለኛ አመራር ለመስጠት ዝግጅት አለ ወይ? ይኼ በሚገባ መታየት አለበት፡፡ በአስቸኳይ፡፡

  በአሁኑ ጊዜ ሕዝቡ ከገዥው ፓርቲም ሆነ ከመንግሥት የሚጠብቀው ብዙ ነው፡፡ በመጀመርያ ደረጃ በየደረጃው የሚገኙ ሹማምንትና ካድሬዎች ሥራዎቻቸውን እንዴት እያከናወኑ ነው? የሚለው በጥልቀት መፈተሽ አለበት፡፡ የመልካም አስተዳደር ችግር ሲወሳ በመጀመርያው ረድፍ ላይ የሚገኙት ሹማምንት ጉዳይ መነሳት አለበት፡፡ ሥራቸውን በአግባቡ የሚያከናውኑ ያሉትን ያህል፣ በፍፁም ደንታ ቢስነትና ራስ ወዳድነት ሕዝቡን የሚያስለቅሱ ሹማምንት ሞልተዋል፡፡ በመንግሥታዊ አገልግሎት መስጫ ተቋማት፣ በፍትሕ አካላት፣ በተለያዩ አደረጃጀቶችና በልዩ ልዩ ዕርከኖች በሚገኙ የአስተዳደር አካላት ውስጥ የሚገኙ ኃላፊነት የማይሰማቸው ወገኖች ሕዝብ እያስመረሩ ናቸው፡፡

   ግልጽነት፣ ኃላፊነትና ተጠያቂነት የሌለባቸው እነዚህ ኃይሎች በሕዝብ ላይ በየቀኑ ምሬት ያባብሳሉ፡፡ የመንግሥት ከፍተኛ ባለሥልጣናት የመልካም አስተዳደር ችግርን በየተገኘው መድረክ ቢያወሱምና መፍትሔ ይፈለግለታል ቢሉም ጠብ የሚል ነገር የለም፡፡ እንዲህ ዓይነቱ አገር የሚያምስ ችግር በጠንካራ ግምገማ ካልተፈተሸ ዋጋ የለውም፡፡ የይስሙላ በመሆኑም የሥርዓት አልበኞች መጫወቻ ሆኗል፡፡ ገዥው ፓርቲ የሚታወቅበት ጠንካራ ግምገማ በንኖ በመጥፋቱ የራስ ወዳዶችና በሙስና ኔትወርክ የተሳሰሩ ኃይሎች ጉልበት ጠንክሯል፡፡

  በተለያዩ መሥሪያ ቤቶች ውስጥ ሙስና ዋነኛው የሥራ ማስፈጸሚያ ሆኗል፡፡ ‹‹ጉዳይ  ገዳይ›› በሚባሉ ደላላዎች አማካይነት የሚፈጸመው ሙስና ከባለጉዳይ ዜጎች አልፎ የውጭ ኢንቨስተሮችን ጭምር እያስመረረ ነው፡፡ መረጃ ለመጠየቅ፣ ፈቃድ ለማግኘት፣ መሬት ለመረከብ፣ ግዥ ለመፈጸም፣ ከባንክ ለመበደር፣ የውጭ ምንዛሪ ለመጠየቅ፣ የኤሌክትሪክ፣ የውኃና የስልክ መሠረተ ልማቶች ለማስገባት፣ ወዘተ ሙስና ከሌለ ምንም አይፈጸምም፡፡ መንገዶች ሲገነቡ፣ የጋራ መኖሪያ ቤቶች ሲሠሩ፣ የተለያዩ የልማት ተግባራት ሲከናወኑ የድርሻቸውን ካላነሱ ንቅንቅ የማይሉ በኔትወርክ የተሳሰሩ ሙሰኞች በርክተዋል፡፡

  በየመሥሪያ ቤቱ ከተላላኪ ጀምሮ እስከ ትልቁ ሹም ድረስ ፊታቸው የሚፈታው በጉቦ ነው፡፡ ሥነ ምግባራቸውን ጠብቀው በአገልጋይነት መንፈስ ተግባራቸውን የሚያከናውኑ ትጉኃን በረባ ባልረባው እየተገመገሙ በብስጭት እንዲለቁ ሲገደዱ፣ በሙስና ኔትወርክ የተያያዙት እየፈነጩ ነው፡፡ በእነሱ ላይ የሚካሄደው ግምገማ የይስሙላ ወይም ደካማ በመሆኑ አገር እየተጎዳች ናት፡፡ አገር ወዳዶችና ቅኖች እየተገፉ ነው፡፡ በተድበሰበሰቡ ግምገማዎች ምክንያት ለአገር የሚጠቅሙ ንፁኃን እየተጎዱ ነው፡፡

  በዚህ ዘመን የሚካሄዱ ግምገማዎች ራሳቸውን በሚገባ ባደራጁ ኃይሎች እየተጠለፉ፣ ብዙዎቹ የግምገማ መድረኮች የሚያተኩሩት ምክንያታዊ ያልሆኑ ጉዳዮች ላይ ነው፡፡ አልፎ አልፎ ጠጠር ያሉ ግምገማዎች እንደሚደረጉ ቢሰማም በእከክልኝ ልከክልህ ብሂል ሒስና ግለ ሒስ ተደርጎ ይታለፋል፡፡ ከበድ ያለ ጥፋት አድርሰዋል የተባሉ ለጊዜው ከኃላፊነታቸው ይነሱና በአማካሪነት ወይም በሌላ ሹመት ቦታ ይለውጣሉ፡፡ የከፋ ከሆነም ለጊዜው ዞር ይደረጉና ባልታሰበ ወቅት ሌላ ቦታ ቱባ ባለሥልጣን ሆነው ብቅ ይላሉ፡፡ በኔትወርክ መተሳሰር አንደኛው ጥቅሙ ብሶበት የተጋለጠን ግለሰብ ከክስና ከእስራት ማትረፍ ብቻ ሳይሆን መልሶ ማሾምም ነው፡፡ ይኼ በተደጋጋሚ ታይቷል፡፡ የመከኑ ግምገማዎች ውጤት ይኼ ነው፡፡

  ኢሕአዴግ ድሮ ይታወቅበት የነበረው ጠንካራ ግምገማ ትልልቅ የሚባሉ አመራሮቹን ሳይቀር የማይምር ነበር፡፡ ከአመራርነት ከማባረር ጀምሮ እስከ እስር ቤት ድረስ የሚዘልቀው ግምገማ ለምን ቀረ? ጨከን ብሎ በሙስና የተዋጡ ሹማምንትን መክሰስ፣ ብቃት የሌላቸውን ማግለል፣ በሥልጣን ያላግባብ የሚባልጉትን ማባረር፣ ከሕዝብ በላይ ለመሆን የሚፈልጉትን በሕግ ቋንቋ ማነጋገር ለምን ተፈራ? ትናንት ምንም ያልነበራቸው ዛሬ በራሳቸው፣ በቤተሰቦቻቸውና በቢጤዎቻቸው ስም የተያዙ ግዙፍ ሀብቶችን ከየት አመጣችሁት ማለት ለምን ከበደ? በየቦታው ሕዝቡ የእነ እከሌ ብሎ የሚጠራቸው ንብረቶች ጉዳይስ በግልጽ ይገመገማል? የሚያስተባብል ካለስ በግልጽ ይታወቃል? የነጠረ ግምገማ ካልተደረገ በስተቀር የፀረ ሙስና ትግሉን ውኃ ይበላዋል፡፡ የሕዝብ ሀብት ይዘረፋል፡፡ የተድበሰበሱ ግምገማዎች ባሉበት ውጤቱ ዜሮ ነው፡፡

  አገር የሚያስተዳድረው መንግሥት ውስጡን እንዴት እያየ ነው? የሕዝቡን ስሜት ይፈትሻል ወይ?  መረጃዎቹን የሚያገኛቸው እውነቱን እያዛቡ ከሚያቀርቡ ሪፖርቶችና ከሐሰተኛ ሚዲያዎች ነው? ወይስ የተጣራ የሕዝብ መረጃ አለው? በኑሮ ውድነት የሚጠበሰው ሕዝብ በስሙ የመጡትን መሠረታዊ የፍጆታ ዕቃዎች የሚዘርፉት አሉ፡፡ አስተዳደራዊ በደል የሚፈጽሙበት ሞልተዋል፡፡ በየደረጃው በኔትወርክ የተሳሰሩ ሙሰኞችና ኃላፊነታቸውን በአግባቡ መወጣት የማይችሉ ሹማምንት በሚፈጽሙት የተደራረበ በደል ሕዝብ እያለቀሰ እንባውን የሚያብስለት የለም፡፡ እነዚህ ወገኖች በጠንካራ ግምገማ የሚፈትናቸው ስለሌለ ራሳቸውን ከሕግ በላይ አድርገዋል፡፡ ሕግ ባለበት አገር ውስጥ ሕገወጦች በሕዝብ ላይ ሲቀልዱ ዝም ሲባል ያስፈራል፡፡ በተድበሰበሱ ግምገማዎች ላይ ስማቸውን ደፍሮ የሚጠራ ስለሌለ እንደልባቸው ይፏልላሉ፡፡ አደገኛ አካሄድ ነው፡፡

  የአገሪቱን ፓርላማ ሙሉ በሙሉ ተቆጣጥሮ አገሪቱን ለመምራት የተዘጋጀው ኢሕአዴግ ውስጡ የተሰባሰቡ የጥፋት ኃይሎችን ይዞ የሚቀጥለው እስከ መቼ ነው? አገሪቱ በልማት ያሳየችውን እመርታ የመጨረሻው የስኬት ጣሪያ አድርጎ እያየ በርካታ ጥፋቶችን ማረም ያቃተው ኢሕአዴግ የግምገማውን ጉዳይ ችላ ማለቱ ያስተዛዝባል፡፡ ከዚህ በፊት ያጋጠሙትን የመሰንጠቅ አደጋዎች ሳይቀር በፅናት የተቋቋመው ኢሕአዴግ፣ የሙሰኞችና የአገር አጥፊዎች ዋሻ መሆኑም ይደንቃል፡፡ ሥራ መሥራት አቅቶአቸው ኢንቨስተሮችን የሚያማርሩ፣ በገዛ አገራቸው ሠርቶ የመክበር ህልም ያላቸውን የሚያጨናግፉ፣ ከራሳቸውና በጥቅም ከተሳሰሩዋቸው ውጪ የአገር ህልውና ጉዳይ የማይሰጣቸውና በአጠቃላይ ለአገር ፀር የሆኑ ግለሰቦችን የት ድረስ ነው ተሸክሞ የሚጓዘው? እነዚህ ለራሱ ለሥርዓቱም ጭምር የማይበጁ ወገኖች በአገር ላይ እየቀለዱ በተድበሰበሰ ግምገማ ሲሸፈኑ አደጋው ለአገር ነው፡፡ የተድበሰበሱ ግምገማዎች አያስፈልጉም! ግምገማዎች አይድበስበሱ!  

  በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

  የኢትዮጵያ መንግሥት ባለሥልጣናት ዩክሬንን እንዲጎበኙ ጥያቄ ቀረበ

  በመካከለኛው ምሥራቅና አፍሪካ የዩክሬን ልዩ መልዕክተኛ ከአቶ ደመቀ መኮንን...

  በፍላጎት ላይ የተመሠረተ ብሔራዊ አገልግሎት የተካተተበት አዋጅ ለፓርላማ ቀረበ

  የከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ወይም የዩኒቨርሲቲ ትምህርታቸውን ያጠናቀቁ ወጣቶች በፈቃደኝነት...

  ሰርጌ ላቭሮቭ ለዲፕሎማቲክ ማኅበረሰቡ በአዲስ አበባ በሰጡት መግለጫ ምዕራባውያንን አጣጣሉ 

  የሩሲያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሰርጌ ላቭሮቭ ለአፍሪካ አገሮች ላደረጉት...
  - Advertisment -

  ትኩስ ፅሁፎች

  የትርፍ መጠኑን በ127 በመቶ ያሳደገው አቢሲኒያ ባንክ ካፒታሉን በ2.5 ቢሊዮን ብር እንዲያድግ ወሰነ

  የአቢሲኒያ ባንክ ዳይሬክተሮች ቦርድ የባንኩ  ካፒታል በ2.5 ቢሊዮን ብር...

  አዋሽ ባንክ ካፒታሉን 55 ቢሊዮን ብር ለማድረስ ወሰነ

  የአዋሽ ባንክ ዳይሬክተሮች ቦርድ ዛሬ ህዳር 17 ቀን 2015...

  ከብሔራዊ ባንክ እውቅና ያገኘው ፔይሊንክ አክሲዮን ማህበር ምሥረታውን አካሄደ

  ከገንዘብ ንክኪ ነፃ የሆነ የዲጂታል ክፍያ ሥርዓት ለመተግበር ያቀደው...

  የተወሳሰበው ሰላም የማስፈን ሒደት

  የደቡብ አፍሪካ የሰላም ስምምነት ተፈርሞ ብዙም ሳይዘገይ የኬንያው ቀጣይ...
  spot_img

  ተዛማጅ ፅሁፎች

  የሰላም ስምምነቱ ተግባራዊ ይደረግ!

  የሰላም ስምምነቱ ‹‹ታጥቦ ጭቃ›› ሊሆን የሚችልባቸው ምልክቶች እየተስተዋሉ ነው፡፡ ሚሊዮኖችን ለዕልቂት፣ ለመፈናቀል፣ ለከፍተኛ ሰብዓዊ መብት ጥሰትና መሰል ሰቆቃዎች የዳረገው አውዳሚ ጦርነት በፕሪቶሪያው ስምምነት መሠረት...

  ዘረፋ የሚቆመው በተቋማዊ አሠራር እንጂ በዘመቻ አይደለም!

  ኢትዮጵያ ውስጥ ሌብነት ከመንግሥት አቅም በላይ ሆኖ ለያዥ ለገናዥ ሲያስቸግር ከማየት በላይ አሰቃቂ ነገር የለም፡፡ በፌዴራል፣ በክልሎችና በከተማ አስተዳደሮች መረን የተለቀቀው ሌብነት አስነዋሪ መሆኑ...

  ሰላም ዘላቂ የሚሆነው ቃል ሲከበር ብቻ ነው!

  እንደ አለመታደል ሆኖ የሰሜን ኢትዮጵያ አውዳሚ ጦርነት ውስጥ ለሁለት ዓመታት ከተከረመ በኋላ የሰላም መንገድ ተጀምሯል፡፡ በአገር በቀል ሽምግልና ማለቅ የነበረበት ከአገር ውጪ አስጉዞ፣ በባዕዳን...