Wednesday, June 19, 2024
- Advertisment -
- Advertisment -

ጎዳናዎችን ለመታዘብ ሳይሆን ላለማሳዘን ብንኖርስ?

በሐናንያ መሐመድ (አፋር)

የጎዳናዎች ጥግ ከአሰቃቂ ግድያ እስከ አስደሳቹ የስርቆሽ የፍቅር ጨዋታ፣ የዕለት ጉርስን ለማግኘት ከመሯሯጫ እስከ ዘርፎ ማምለጫ፣ ከሐሜት መጠረቂያ እስከ ድንቅ ሐሳብ ማፍለቂያ፣ ከእንስሳት መፈንደቂያ፣ እስከ ‹በኒ አደም› መቅበጫ፣ መታያና መድመቂያነት. . . ያገለግላሉ፡፡

የጎዳናዎች ጥግ የፍጥረታትን የሕይወት ዑደት በግርግር፣ በፀጥታ፣ በነፍሳት ሲርሲርታ፣ በእንስሳት ጋጋታ፣ በእኔ እበልጥ እኔ እበልጥ ፉክክር፣  በየጥጉ በተኙ ሰዎች የማንኮራፋት ድምፅ፣ በለማኞች (የኔ ቢጤ) ተስረቅራቂ የልመና ዜማዎች፣ በሐሳብ እየቆዘሙ በደመነፍስ በሚራመዱ ሰዎች፣ በደላላዎችና በወያላዎች ጩኸት፣ በሕፃናት ድብብቆሽ ጨዋታ፣ በሴት ጀንጃኞች የሹክሹክታ ወሬዎች፣ በፌዴራል ፖሊስ ከስክስ ጫማ፣ በባዶ እግር፣ በጋዜጣና በሎተሪ አዟሪዎች ድምፅ፣ በፈጣን ምግቦች (ሳንቡሳ፣ ጥብስና ቅቅል በቆሎና ቆሎ . . .) ሻጮች የግዙኝ ማስታወቂያ፣ በሊስቲሮዎች ‹‹ላሳምራት…?›› ልምጥምጥ ጥያቄ፣ በወፌፌ ሰዎች ከሩጫ ባልተናነሰ ዕርምጃ፣ በአቅመ ደካሞች ምርኩዝ፣ በዓይነ ሥውራን አቅጣጫ ጠቋሚ ዘንግ፣ በሕፃናት ፍንደቃ፣ መስማት የተሰናቸው ጠጋ ብሎ በምልክት መወያየትና ድንገት በተገናኙ ሰዎች የእንዴት ከረምክ ጥያቄ፣ ወዘተ . . . የጎዳናዎች ጥግ ያለመታከት ሲሰሙ ይውላሉ ያድራሉ፡፡

የጎዳናዎች ጥግ ያለ እረፍት ለ24 ሰዓታት በሥራ ላይ ናቸው፡፡ ቢመሽም ቢነጋም ለጎዳናዎች ልዩነት የለውም፡፡ የሰው ልጆች በምሽት ተደብቀው ወሲብ የፈጸሙበትን ጎዳና፣ በጠዋት በዓይናቸው ገልመጥ አድረገው ዓይተውት  ወደ እምነት ቦታ ይሄዱበታል፡፡ በቀን ከፖሊሶች ጋር በመሯሯጥ ፕላስቲክ አንጥፈው የሚነግዱበትን ያንኑ ጎዳና፣ ምሽት ሴተኛ አዳሪዎችና ፖሊሶች መልሰው ይሯሯጡበታል፡፡ በቀን በዓይናቸው ቃኝተው ያመቻቹትን የጎዳና ጥግ በሌሊት ማጅራት መትተው ይደበቁበታል፡፡ የጎዳናዎች ሆድ ከአምላክ ቀጥሎ ቻይ በመሆኑ ይመስልኛል ሳይፈልግ የሚያየውንና የሚሰማውን ነገር ችሎ ኑሮውን የሚገፋው፡፡ አንድ ቀን ጎዳናዎች በሙሉ አፍ አውጥተው ቢናገሩ የሰው ልጅ ምን ይውጠው ይሆን?

በነገራችን ላይ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የአገራችንን ጎዳናዎች ከጫት አስቃሚዎች ቀጥሎ እንደ ዝንብ የወረራቸው በየበረዳንውና በየጎዳናው የቡና ሻጮች ጀበናና ሲኒ ነው፡፡ በእርግጥ ይህ የጎዳና ቡና ሽያጭ ጥሩ ይመስላል፡፡ ስንት ዘግናኝ ነገር በየጎዳናው በሚከሰትባት አገራችን፡፡ የንፁኃን ደም እንደቀልድ የሚፈስበት፣ ተንገብግበው ተዋስበው የወለዱትን ልጅ የሚካካዱበት፣ አብረው ዘርፈው ሲካፈሉ የሚጣሉበት፣ ወዘተ . . .  ጎዳናዎችን በየሠፈራችን እናውቃቸዋለን፡፡ ዋናው ነገር ግን እነዚህ ጎዳናዎች በተንኮለኞች የንፁኃን ደም ቢፈስ፣ ለማይረባ ገንዘብ የሰው ሕይወት ቢቀጠፍ፣ የጨቅላ ልጅ ድንግልና በመደፈር ቢወሰድ፣ አደገኛ ምክክሮች ቢደረጉም ለማንም ሚስጥሩን ሳያካፍሉ፣ ቢከፋቸውም፣ ቢያሳዝናቸውም፣ ቢያስደስታቸውም አለመናገራቸው ለጎዳናዎች ከፈጣሪ የተሰጣቸውን ትዕግሥት ያሳየናል፡፡ እንደዚህ ባይንማ ኖሮ ስንቱ ሰው ፍርድ ቤት በሐሰት ሲረታ፣ ሌላው ያለወንጀሉ ሲፈረድበት፣ ፍርድ ሲገመደል. . .  ሄደው መመስከር በቻሉና በቃ . . . ባሉ ነበር፡፡ ስንት ክህደት በአደባባይ ሲፈጸም፣ ስንት ተንኮል ሲሸረብ፣ ስንት የእምነት ቃል ኪዳን ሲታሰር አብዛኛዎቹ ጎዳናዎች ምስክሮች ናቸው፡፡ ነገር ግን ዓይተው እንዳላዩ በዝምታቸው ፀንተው ይኖራሉ፡፡

የጎዳናዎች ጥግ ቡና መሸጫዎች ለሥራ ፈቱ፣ የሴት ድምፅ ለሚናፍቀው፣ የቡና አምሮት ላለበት፣ ሰው ለሚጠብቅ፣ በሚስቱ ላይ ቡና ሻጯን መደረብ ላማረው፣ ለጉዳይ መጨረሻ፣ አላፊ አግዳሚውን ለመታዘብና ዝም ብሎ ግራ ለገባው. . . ለሁሉም ሰው ያለማዳለት ያገለግላሉ፡፡ በተጨማሪም የጎዳናዎች ጥግ ቡና ሽያጭ ትርፋማ ከመሆኑም በላይ እንደ ጫት ቃሚዎች ሁሉ የቡና ጠጪዎችንም ቁጥር ለመጨመር የራሱ አስተዋጽኦ አለው፡፡ በዚህ ከቀጠለ ለኤክስፖርት ቀርቶ ለእኛም የሚሆን ቡና ለወደፊት መመረቱ ያጠራጥራል፡፡ ከሕፃን እስከ አዋቂ ቡና መጋት፣ ቦጨቅ ቦጨቅ ማድረግ አዲስ እየፈጠርናት ያለች አሪፍ ወይም አደገኛ ባህል እየሆነች ይመስለኛል፡፡ ይቅርታ እኔ እንደ ጎዳናዎች ዓይቼ እንዳላየሁ ሰምቼ እንዳልሰማሁ መሆን ስለማልችልበት ነው፡፡ ለትውልድ ከአሪፍ ጥሪት በተጨማሪ አሪፍ ግብረ ገብነት ይበልጥበታል ብዬ አምናለሁ፡፡ በሱስ ከተጠመቀ ሀብታም ይልቅ ማንነቱን ያልካደ፣ በሙስና ቅኝ ያልተገዛ፣ ኃላፊነቱን ተገን አድርጎ የማይሸቅጥ፣ ቢነጣም ቢገረጣም ነጫጭባ ደሃ የሚሻል ይመስለኛል፡፡ የሆዱ ወስፋት ቢጮህም ህሊናው ግን የገነትን ጣዕመ ዜማ እያዳመጠ ያሸልባል፡፡

የጎዳናዎች ጥግ እንደየአካባቢውና አገሩ የራሳቸውን ፈለግ፣ የራሳቸውን የአፈጣጠር ሕግ ተከትለው ኑሮዬ ብለው የተያያዙት ሕይዎት አላቸው፡፡ ለምሳሌ  የድሬዳዋ  ጎዳናዎች ጠዋት ቁርስና ቡና መሸጫ፣ የአትክልትና ፍራፍሬ ተራ ሆነው ያረፍዳሉ፡፡ ፀሐይዋ ከረር ማለት ስትጀምር ጫት መቃሚያና መሸጫ፣ መቦጫጨቂያ፣ በአርምሞ ሐሳብ ማውጫና ማውረጃ ይሆናሉ፡፡ ወደ ማታ ደግሞ የእግር ጉዞ (ወክ) ማድረጊያነት ያገለግላሉ፡፡ በተጨማሪም በእግር ጉዞ የደከማቸው ፍቅረኛሞች ወደ ጎዳናው ጥግ ጠጋ ብለው ይመጣመጡባቸዋል፡፡ ሰዓቱ ገፋ ሲል እነሱም በሰውነታቸው ሙቀት ይግማሉ፡፡ ይቺን ዓለም እስኪረሱ ጨለማውን ተገን አድርገው ይቀልጣሉ፡፡ እኩለ ሌሊት አካባቢ እዚሁ ቦታ ላይ የምሽት አራዊት የተለያዩ ነገር ለመብላት ጅራታቸውን ይቆሉበታል፡፡ እዚሁ ቦታ መጥተው በጠዋት ምስኪን እናቶች ፉል ይሸጡበታል፡፡ ሕይወትም ይቀጥላል፣ የኑሮ ዑደትም ይቀጥላል፡፡ የጎዳናዎች ጥግ ተግባርም በዚህ ቦታ እንደዚህ ይቀጥላል . . . ፡፡

በተጨማሪ የአፋሯን  መዲና ሰመራ ሎግያ ከተሞች ጎዳና ብንወስድ ጎህ ሲፈነጥቅ ጀምሮ የደላላዎች መፈንጪያና የጉልበት ሠራተኞች የዕለት ጉርስ መፈለጊያ በመሆን ያገለግላሉ፡፡ ወዲያው ፀሐይ ከመውጣቷ ወደ ሰመራ የመንግሥት ሠራተኞችን የሚወስዱ የሰርቪስ መኪናዎችና ታክሲ ተጠቃሚ ሠራተኞችን ትልቁ ጎዳና ያስተናግዳል፡፡ ትንሽ ፀሐይዋ ጎልበት ስትል ደግሞ ጫት ነጋዴዎች ባጃጆችንና ጋሪዎችን ተኮናትረተው ጫት ለማከፈፋል ይሯሯጡበታል፡፡ አምስት ሰዓት አካባቢ ጀምሮ ደግሞ በከባድ መኪኖች፣ በባጃጅና በሰርቪሶች ይጨናነቃል፡፡ አብዛኛውን ጊዜ መንገዶች ይዘጋሉ፡፡ ትራፊኮች ይሯሯጣሉ፡፡ ከዚያም በሐሩሩ ትርምስምሱ ይቀንስና ወደ ዘጠኝ ሰዓት አካባቢ ደግሞ ንዳዱ ሙቀት ባይቀንስም የሠራተኛውና የሰርቪሱ ጋጋታ መልሶ ይጀምራል፡፡

ምሽት ላይ ደግሞ እንደ ጉንዳን ሠራዊት የሰውን ትርምስ ሲታይ ማንም እቤት እንዳይሆን የተባለ ይመስላል፡፡ ይህም ትልቅ ጎዳና ነዋሪዎቿ ወደሚፈልጉበት እንዲሄዱበት ራሱን ሽው በሚለው ቀዝቃዛ ነፋስ ያስውባል፡፡ ምሽቱን በሙሉ በመንገደኞችና በጠጪዎች ሲናጥ ያመሻል፡፡ በዚህ ሁሉ መካካል ግን ከጂቡቲ የሚመለሱና የጭነታቸውን ዙር ወይም ምልልስ ለማፍጠን የሚቃትቱ ከባድ መኪኖች፣ እርግማን የማይፈሩ ብር ብር እያሉ የሚያስቸግሩ ባጃጆች ለ24 ሰዓት በዚህ ጎዳና ያለማቋረጥ ይሽከረከራሉ፡፡ በጣም የሚያስገርመው ግን የዱር አራዊትን  የሎግያ ሰመራ ከተማ ጎዳና አያውቃቸውም፡፡ በሌሊት እንዴ ሌላው አገር ጎዳና ከተማ ውስጥ ጅብና ነብር አለዚያም ሌላ አውሬ አይፈነጭባቸውም፡፡ በአገራችን ብዙ ዓይነት ባህሪይ ያላቸው ጎዳናዎች ሞልተዋል፡፡ አንዳንዶቹ ለሥራ፣ አንዳንዶቹ ለስርቆት፣ አንዳንዶቹ ለመዝናናትና ሌሎቹ ደግሞ ለሌላ ተግባር የተመቻቹ ናቸው፡፡

የወደፊቷን ኢትዮጵያ ምን እንደምትሆን ማሰብ ያደክማል፡፡ በአንድ ጎን እጅግ በጣም ጥሩ ልማት በሌላ በኩል እጅግ  ቀላል የሚመስሉ አደገኛ ክስረቶች በራሳችን ላይ እያሠለጠንን ይመስለኛል፡፡ አብዛኛው ሰው ጠዋት ተነስቶ በየመንገዱ ዳር የጀበና እየቃመ አለዚያም የጀበና ቡና እየጠጣ ያረፍዳል፡፡ ከሰዓት የማድ እንጀራ ማስቀመጫ የሚያክል ቅጠል ሰብስቦ ይቅማል ወይም ታቃቅማለች፡፡ ወጣት ጉብሎች ለ24 ሰዓታት ስልካቸው ዕረፍት የለውም፡፡ አንዱን እንደምታፈቅረው ተናግራ ዘግታ ‹‹ወይ የኔ ማር ንፍቅ ብለኸኛል ጠፋህ አኮ…›› ብላ ከሌላው ጋር ስታወራ የአሥራዎቹ አጋማሽ ጨቅላ እህትህን ትሰማታለህ፡፡ ‹‹አንተ ብለሽ አዋሪኝ…›› የሚል አምሳውን የደፈነ አዛውንት አባት፣ ሹገር ማሚ ለመሆን ከብጣሽ ልብስ እስከ ብጥስጣሽ የአራዳ ቋንቋ ተናጋሪ ባልቴት እናት ውሎዋ ያበሳጭሃል፡፡ የተረፈው ትውልድ ደግሞ በታዋቂና በአማላይ የቴሊቪዢን ሰዎች የሚተዋወቀውን ቢራ ሌሊቱን ሙሉ ሲገለብጥ ያድራል፡፡ ሕፃናቶችም አድገው እነዚህን ቢራዎች የሚጠጡበትን ቀን እየናፈቁ ያድጋሉ፡፡

 ሌላው ሚስትና ልጆቹን አለዚያም ደካማ ቤተሰቦቸቹን ትቶ በስካር ሲዋሰብ ሌሊቱን ያጋምሳል፡፡ የጠዋቱን የሥራ ጊዜ በአንጎበር ተጠቅልሎ በእንቅልፍ ያሳልፈዋል፡፡ እንደዚህ ዓይነቶቹ ሰዎች ሥራ ቢገቡም እንኳን እየተንጀባረሩ ደንበኞችን ማስተናገድ ሳይሆን ማማረር ቁጥር አንድ ተግባራቸው ይሆናል፡፡ ፈጥኖ እንዲጨረስለት የፈለገ የመጨበሻ አለዚያም የጫት፣ ካልሆነም የሻይ ጥሩ ብር መቦጨቅ ይኖርበታል፡፡ ምናልባት ቅጠል የማይበላ ወይም ቢራ የማይጠጣ፣ አለዚያም የኪስ ያለመደ  ከሆነ ፌስቡክና ዩቲዩብ ከፍቶ የተቀጠረበትን ዓላማ እስኪረሳ ሲጃጃል ታገኘዋለህ፡፡ ደንበኛ አስቀምጠው ‹‹ቆይ አንዴ ይቺን ቻት ልመልሳት›› ማለት እንደ መሠልጠን የሚቆጥሩትም የመንግሥት ሠራተኞች ሞልተዋል፡፡ መሰንበት ደግ ነው፡፡ ገና ብዙ እናያለን፡፡ እነዚህ ግን የሕይዎት ጎዳናዎች ጥግ ናቸው፡፡

እንደ አገራችን የተለያዩ ጎዳናዎች ሁሉ የመቐለ ጎዳናዎችም ልዩ ድባብ አላቸው፡፡ ከመቐለ ጎዳናዎች ጥግ ቡና የሚቸበቸብበት ሠፈር ቀበሌ 16 ይገኝበታል፡፡ ይህ ሠፈር በድሮው ሥርዓት ከኢትዮጵያ ሕዝብ በላይ እንዳይናገር እንዳይጋገር ተደርጎ የተጨቆነ ሠፈር ይመስላል፡፡ የዛሬን አያድርገውና በቃ አንገት ደፊ (ዓይን አፋር) ሠፈር ነበረ ማለት ይቻላል፡፡ ወታደራዊው መንግሥት ሲገረሰስ ከሁሉም ጎዳናዎች በላይ በጭብጨባ ደስታውን ያስተጋባ ይህ ሠፈር ሳይሆን አይቀርም፡፡ ወይም እነዚያን ግርማ ሞገስ የማይለያቸው ቆፍጣና የደርግ ባለሥልጣናትን ሲያጣ ስቅስቅ ብሎ አልቅሶም ሊሆን ይችላል፡፡

በዚህ ሠፈር በዚያን ጊዜ አይደለም የጎዳና ላይ ቡና ሽያጭ፣ ቡና ቤትና መዝናኛዎች ሊኖሩበት ቀርቶ ድምፁን ከፍ አድርጎ የሚናገርም ሰው አያልፍበት ነበር ይላሉ የዓይን እማኞች፡፡ ምክንያቱም አብዛኛዎቹ የዘመኑ ባለሥልጣናት በዚህ ሠፈር ይኖሩ ስለነበረ ነው፡፡ ‹መቕናይ ጽቡቅዩ›› ይሉሃል እንዲህ ነው፡፡ ዛሬ ደግሞ ማንኛውንም ወጣት፣ የየትኛውም አካባቢ ሰው፣ በየትኛውም ዕድሜ ክልል ያለ ግለሰብ ይህን ጎዳና ሳይረግጥ አይውልም፡፡ በቀበሌ 16 የሚሸጠው ቡና ብቻ አይደለም፡፡ ሐሳብህንም አንድ ሲኒ ቡና ፉት እያልክ ታወራርደዋለህ፡፡ ካሰኘህ ደጋግመህ ጉራህን ትቸረችርበታለህ፡፡ በተለይ አንዲት የግጥም መጽሐፍ ከጻፍክ ወይም እነ አቤል ጉዑሽ በድምፀ ወያኔ ካቀረቡህ፣ አለዚያም በአጋጣሚ ስታልፍ በቴሌቭዥን ከታየህ ወደ እዚህ ሠፈር ጎራ ማለት ይኖርብሃል፡፡ ‹‹አንተ አየንህ እኮ… ኮንግራ…›› የማትባለው ነገር የለም፡፡ ጉዳዩ ምንም ይሁን ምን በመታየትህ ብቻ እዚያ ተጎልቶ ቡና ከሚጨልጠው ሰው የተሻልክ ትሆናለህ፡፡ በተለይ ቡና ሻጯ ቴሌቭዥን ስለማታይ የአይኤስ አሸባሪ ብትሆንም አታውቅህም፡፡ ብቻ ድንገት ጆሮዋ የገባውን የሙገሳ ቃላት ሰምታ ‹‹አንተ ሃወይ…›› ብላ የደንበኝነትም የቅረበኝም ፈገግታ ታትረፈርፍሃለች፡፡

ስለጎዳናዎች ብዙ ብዙ ማውራት ይቻላል፡፡ የአዳማ ከተማን የምሽት የእግር ጉዞ፣ የአዲስ አበባን የመኪና ትርምስ፣ የአወዳይን የጫት ንግድ፣ የባቲን ለማኝ፣ የደብረ ብርሃንን ቆሎ ሻጭ፣ የሐረርን ሊስትሮ፣ የባህር ዳርን አዝማሪ፣ የደሴን በቆሎ ቸርቻሪ፣ የአክሱምን የተቀረፀ መስቀል ሻጮችና የጎንደርን ቱሪስት . . . መዘርዘር እንችላለን፡፡ ስለ እያንዳንዱ ብናወራ መጽሐፍም አይበቃን፡፡ ለምሳሌ ስለ አዳማ እግር ጉዞ ብናወራ ወደ ምሽት አካባቢ የቡና ቤት ሴቶችና የቤት ልጆች በግብር አንድ ዓይነት ይሆናሉ፡፡ የሚለያዩት የቡና ቤቷ ልጅ በነፃነት ከተከራየችው ቤት የዕለት ጉርሷን ለመሸፈን ስትወጣ የቤት ልጆች ደግሞ ከእናት ከአባታቸው ቤት ዘንጠው ዙሪያ ገባውን ገልመጥ እያደረጉ ጎዳናውን መቀላቀላቸው ነው፡፡ የባቲ ለማኞች ደግሞ ያለህን በሙሉ ከኪስህ ማውጣት እስኪቀራቸው ድረስ ዙሪያህን ይከቡሃል፡፡ ለአንዷ ከሰጠህ እንደ ሕፃን ልጅ ‹‹ለኔም…? ለእሷ ሰጥተህ›› ይሉሃል ኮስተር ብለው፡፡ አንዳንዴ አለባስህን ከጫማህ እስከ ራስህ መንጥረው እያዩህ እጃቸውን ይዘረጉልሃል፡፡ የባቲ ለማኞች መስጠት ግዴታህ እንደሆነም ይሰማቸዋል፡፡ አንተም አስተውለህ ለማየት ከሞከርክ ሙሉ ጤነኞችና ወጣት ለማኞችን  የምታበረታታ ከተማ ባቲ መሆኗን ትታዘባለህ፡፡

እንደ እኔ አመለካከት ጎዳናዎችን ለመታዘብ ሳይሆን ላለማሳዘን ብንኖር ደስ ይለኛል፡፡ ጎዳናዎች እንደ ሰው ልጆች ቢያለቅሱ፣ አፍ አውጠተው ቢናገሩ . . . ከምንገምተው በላይ በየዕለቱ አዳዲስ የኃጢያት ልምምዶች በየሠፈራችን እንደሚደረግ ያስረዱን ነበር፡፡ ያልፍልኛል ብላ የምትፍገመገመውን የማታ ተማሪ አስረግዞ ሽል ከማለት፣ ሕፃናቶችን ለሕገወጥ ግብረ ሰዶማዊነት ከመመልመል፣ ዘርፎ ከመደበቅ፣ የክቡሩን የሰው ልጅ ሕይወት በአላቂና ጠፊ ገንዘብ ከመቅጠፍ፣ ወዘተ . . ትውልዱ ራሱን ይጠብቅ ዘንድ በሁለተኛው ትራስፎርሜሽን ዘመን መንግሥት ከመጠጥ ፋብሪካ ይልቅ ልብ የሚገጥም ፋብሪካ ቢከፍት ጥሩ ሐሳብ ይመስለኛል፡፡ አለዚያም በየጎዳናዎቹ ጥግ ካሜራ መግጠም ቀላል ዘዴ ነው፡፡ አብዛኛዎቹ ፍርድ ቤትን ያጨናነቁ ክሶች ጎዳናዎች ጥግ ላይ የሚጀመሩ ወንጀሎች ናቸው ይባላል፡፡ ከጎዳናዎች ጥግ ላይ ቆመው ያላወሩ ፍቅረኛሞች፣ ያልዘረፉ ሌቦች፣ ያልተኮላኮሉ ልጃገረዶችን ጎዳናው ራሱ ይቁጠራቸው፡፡ የተፈጥሮ የሕይወት ሕግ ነውና የዝሆን ጆሮ፣ የአዞ ቆዳ፣ የእዮብ ትዕግሥት የተሰጣቸው ጎዳናዎች ሁሉንም ዓይተው፣ ሁሉንም ሚስጥሮች ሰምተው በዝምታቸው ዛሬም ይቀጥላሉ፡፡ የሰው ልጅም በተግባሩ ይቀጥላል፡፡ እኛም ወሬያችንን እንቀጥላለን፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡

 

spot_imgspot_img
- Advertisment -

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

Related Articles