Monday, June 24, 2024
- Advertisment -
- Advertisment -

በአጭር ጊዜ አመርቂ ውጤቶች የታዩበት የፐብሊክ ዲፕሎማሲ ዓበይት ገጽታዎች

በአሊ ሐሰን

 ዲፕሎማሲ በተለምዶና በጥሬ ትርጉሙ ሲወሰድ በመንግሥት ተወካዮች መካከል የሚደረግ ኦፊሴላዊ የሥራ ግንኙነትንና ድርድርን የሚገልጽ ሲሆን፣ ቃሉ ከግሪክ ቋንቋ የመጣ ነው፡፡ ትርጉሙም ሁለት ቦታ የታጠፈ ደብዳቤ፣ ከነገሥታት የተላከ ደብዳቤ ወይም ጽሑፍ ማለት መሆኑን መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ ሰፋ ባለ መልኩ ሲታይ የዘርፉ ምሁራን ለቃሉ ልዩ ልዩ ትርጓሜ የሚሰጡት ቢሆንም፤ ብዙውን ጊዜ ቃሉ ከዓለም አቀፍ ግንኙነት ጋር ተያይዞ የሚነሳ ነው፡፡ ንግድን፣ ጦርነትን፣ ኢኮኖሚን፣ ባህልን፣ አካባቢንና ሰብዓዊ መብቶችን በሚመለከት በዲፕሎማቶች በጋራ የሚካሄድን ዓለም አቀፋዊ ግንኙነት ይወክላል። መደበኛ ባልሆነ ወይም በማኅበራዊ አገላለጽ ዲፕሎማሲ ስትራቴጂካዊ ጥቅምን ለማግኘት፣ እንዲሁም ለጋራ ችግሮችና ተግዳሮቶች የጋራና ተቀባይነት ያላቸውን መፍትሔዎች ለማበጀት አንድ የተለየ ሰላማዊ  ዘዴ መጠቀምን  ያመለክታል፡፡

በኦክስፎርድ   የእንግሊዝኛ መዝገበ ቃላት ሦስተኛ ዕትም መሠረት ዲፕሎማሲ ማለት አንድ መንግሥት ከሌላው ጋር ሰላማዊ በሆነ መንገድ የሚያካሂደው ግንኙነት ሲሆን፣ በሌላ በኩል ደግሞ ዓለም ዓቀፍ ግንኙነቶችን በመምራት ረገድ የሚያገለግል ሙያ መሆኑን ያስረዳል፡፡

ከዚህ ከተለመደውና በመንግሥታት መካከል ከሚደረገው የዲፕሎማሲ አካሄድ በተጨማሪ፣ በተለያዩ አካላት የሚካሄዱ የተለያዩ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነቶች አሉ፡፡

ለጊዜው ትኩረታችን በፐብሊክ ዲፕሎማሲ ዘርፍ እንደመሆኑ፤ ጽንሰ ሐሳቡን በአጭሩ መመልከቱ  ተገቢ ነው። ፐብሊክ ዲፕሎማሲ አንድ የዲፕሎማሲ ዘርፍ ሲሆን፣ በተለይም አሁን ባለንበት በዘመነ ሉላዊነት (Globalization) ተቀባይነቱና ጠቀሜታው እየሰፋ የመጣ መስክ ነው፡፡ ይኼ የዲፕሎማሲ መስክ በተለምዶ መንግሥታት ከመንግሥታት ጋር ከሚያደርጉት የዲፕሎማሲ ግንኙነት ለየት ባለ መልኩ መንግሥታትን ብቻ ሳይሆን የሌላን አገር ኅብረተሰብና መንግሥታዊ ያልሆኑ አካላትን፣ ዩኒቨርሲቲዎችን፣ የጥናትና ምርምር ተቋማትን፣ ምሁራንን (think-thanks)፣ የሲቪክ ማኅበራትንና የመገናኛ ብዙኃንን  በተገቢው መልኩ በመጠቀም በአገራቸው መንግሥት ላይ ተፅዕኖ እንዲፈጥሩና ደጋፊ አመለካከት እንዲጎለብት ዒላማ አድርጎ ይንቀሳቀሳል፡፡ ፐብሊክ ዲፕሎማሲ አገሮች የሌሎች አገሮችን ሕዝብ ቀልብ በመሳብ ለራሳቸው ጥቅም የሚበጁ አመለካከቶችን ለማስረጽና ተፅዕኖ ለመፍጠር ሲሉ  የተለየዩ ሥልቶችን በመቀመር በመገናኛ ብዙኃን፣ በታዋቂ ሰዎች፣ በኪነ-ጥበብ ባለሙያዎች፣ በባህልና በትምህርት ልውውጦች፣ በተለያዩ ስፖርታዊ ፕሮግራሞች አማካይነት በየአቅጣጫው እንቅስቃሴ የሚካሄድበት የዲፕሎማሲ ዘርፍ ነው።

ይሁን እንጂ እዚህ ላይ ልብ ሊባል የሚገባው ጉዳይ ፐብሊክ ዲፕሎማሲ በመንግሥታት መካከል የሚደረገውን ተለምዶአዊ የዲፕሎማሲ አካሄድ የሚተካ ሳይሆን፣ ይኼን የዲፕሎማሲ አካሄድ የሚያራምዱትን የመንግሥት አካላት ከሕዝባዊው ዕይታ አንፃር (Public View) አማራጭ መፍትሔዎችን በመፈለግ ግጭቶችን ለማስወገድና ለመፍታት፣ በአገሮች መካከል ያሉ ግንኙነቶችን ለማጠናከርም ጭምር የሚያስችል ጥበብ ነው፡፡ ከዚህ አንፃር ግጭቶችን ከመፍታት አኳያ ሲታይ፣ ፐብሊክ ዲፕሎማሲ መንግሥታዊና መንግሥታዊ ያልሆኑ አካላት ግጭቶች ከመከሰታቸው በፊት በመከላከል ወይም የተከሰቱ ግጭቶችን በውይይት በመፍታት ሒደት የሚተባበሩበት ነው፡፡

በዘመነ ሉላዊነት አንድ አገር በሌላው ዘንድ ያለው ዕይታ ውጤት ነው፡፡  ይኼ ዕይታ ደግሞ በብሔራዊ ጥቅም ላይ ተፅዕኖ ያሳድራል፡፡ ይኼም ማለት የአንድ አገር ማኅበረሰብ ስለ ሌላ አገር የሚኖረው ትክክለኛ ወይም የተሳሳተ ግንዛቤ ከዚያ አገር ጋር ለሚመሠረተው ግንኙነት በጎ ወይም አሉታዊ ተፅዕኖ ያሳድራል፡፡ ስለሆነም የአገር ክብርና የገጽታ ግንባታ ሥራ አማራጭ የሌለው ተግባር ነው፡፡ የአገር ክብርና በጎ ገጽታ በቀላሉ ሊገነባ ስለማይችልና ከተገነባም በቀላሉ ሊጠፋ ስለሚችል ፐብሊክ ዲፕሎማሲ፣ ሚዲያ ስትራቴጂና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ለአንድ አገር መንግሥት እጅግ አስፈላጊ እየሆነ መጥቷል፡፡

ወደ አገራችን ስንመለስ ፐብሊክ ዲፕሎማሲ ኢትዮጵያ ትታወቅበት የነበረውን አሉታዊ ገጽታ በአዎንታዊ መልኩ ለመቀየርና የሌላው አገር ማኅበረሰብ ስለ አገራችን ሊያውቃቸው የሚገቡ እውነታዎች ማለትም የታሪክ፣ የባህል፣ ወዘተ… ጉዳዮችን በተመለከተ መረጃዎችን በተለያዩ ሥልቶች በማድረስ ማኅበረሰቡ ስለ አገራችን በጎ አመለካከት እንዲይዝና ጠንካራና ዘላቂ የሕዝብ ለሕዝብ ትስስር እንዲመሠረት በማድረግ፣ ተገቢው ግንዛቤ  እንዲኖረው በማስቻል፣ ወዳጆችን ለማፍራት ከፍተኛ ሚና ይጫወታል፡፡ በመሆኑም ፐብሊክ ዲፕሎማሲ በሕዝቦች መካከል መግባባት እንዲኖር የሚያስችል ለማድረግ የአገርን አስተሳሰብ፣ ግንዛቤ፣ ባህላዊ እሴትና ፖለቲካዊ ተቋማት፣ ብሔራዊ ግቦችንና ወቅታዊ የመንግሥት ፖሊሲዎችን በማሳወቅ ላይ ያተኮረ እንቅስቃሴ መሆን ይኖርበታል፡፡

ፐብሊክ ዲፕሎማሲ እጅግ ሰፊ የዲፕሎማሲ መስክ በመሆኑ የኢትዮጵያ የፐብሊክ ዲፕሎማሲ እንቅስቃሴን ከዚህ በታች በተጠቀሱት ተግባራት ብቻ መገደብ አግባብ ባይሆንም፡፡ በአሁኑ ወቅት እየተከናወኑ ካሉ ሥራዎች አንፃር የኢትዮጵያ የፐብሊክ ዲፕሎማሲ እንቅስቃሴ በሚከተሉት ተደጋጋፊ ዓበይት ገጽታዎች ሊገለጽ ይችላል፡፡ የመረጃ ሥርጭት፣ የባህልና የትምህርት ልውውጥ፣ እንዲሁም በቀጥታ የሚካሄድ የሕዝብ ለሕዝብ ትብብር ከብዙ ጥቂቶቹ ናቸው፡፡ በእርግጥ ከላይ ለመጥቀስ እንደተሞከረው ፐብሊክ ዲፕሎማሲ እጅግ ሰፊ ሥራ በመሆኑ፣ የኢትዮጵያ የፐብሊክ ዲፕሎማሲ እንቅስቃሴ እነዚህን ተግባራት ብቻ ያካትታል ማለት አይደለም፡፡

እነዚህን ገጽታዎች ከዝርዝር ይዘትና አፈፃፀም አንፃር ስንመለከት፣ የመረጃ ሥርጭት በአገሪቱ እሴት የታከለባቸው መረጃዎችን የማሠራጨት ተግባር ሲሆን፣ እነዚህን መረጃዎች ለማሠራጨት የተለያዩ የማሠራጫ ሥልቶችን ይጠቀማል። ከሥልቶቹ መካከል የሬዲዮና የቴሌቪዥን ሥርጭት፣ የጋዜጦች፣ የመጣጥፎች፣ የድረ ገጽ ወይም  የሳይበር  ሚዲያን ይጠቀማል። ይህ የፐብሊክ ዲፕሎማሲ ገጽታ በአንፃራዊ ሁኔታ የሚፈለገውን ውጤት በአጭር ጊዜ ውስጥ ሊያስገኝ የሚችል በመሆኑ በአመዛኙ በስፋት ሊሠራበት ይገባል፡፡

በአንፃሩ ሌላው የኢትዮጵያ የፐብሊክ ዲፕሎማሲ እንቅስቃሴ ዓብይ ገጽታ የባህልና ትምህርት ልውውጥ ነው፡፡ ይህ የፐብሊክ ዲፕሎማሲ ገጽታ የሌላው ዓለም ሕዝብ ስለ አገራችን ሕዝብ በጎ አመለካከትና ተፅዕኖ እንዲኖረው የተለያዩ የባህል ልውውጥ ሥልቶችን በመጠቀም በጎ ገጽታን ቀስ በቀስ የማስረጽ ተግባር ሲሆን መንግሥት በባህል፣ በስፖርትና በትምህርት፣ ለአብነት በመምህራንና በተማሪዎች ልውውጥ፣ በእህትማማች ከተሞች ጉድኝቶች፣ በፓርላማ ለፓርላማ ግንኙነቶች፣ በስኮላርሽፕና በሌሎችም መስኮች የወዳጅነት ግንኙነቶችንና ትብብሮችን የዚሁ ተግባርና ፍላጎቱ ዒላማ የሆነውን ሕዝብ ከሚመራው መንግሥት ጋር በመመሥረት፣ ጥቅሙን ለማስጠበቅ ጥረት የሚያደርግበት ዘርፈ ብዙ እንቅስቃሴ ነው፡፡

በሕዝብ ለሕዝብ ትብብር ረገድ በዋናነት የሚነሳው የተለያዩ የባህል ልውውጦችና የኪነ ጥበብ ሰዎች ሚና ነው፡፡ ኪነ ጥበብ  የሕዝብ ለሕዝብ ትስስርን ለማጠናከር ከፍተኛ አስተዋፅኦ አለው፡፡ በዚህ ረገድ የአገሪቱን የፐብሊክ ዲፕሎማሲ እንቅስቃሴ የሚደግፉ ብዙ ታዋቂ አርቲስቶችና ግለሰቦች የሚገኙ በመሆናቸው ኢትዮጵያ ከፍተኛ አቅም ያላት አገር ናት፡፡ ለዚህም  አርቲስቶችን ጨምሮ የተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎችን ያቀፈውና የኢትዮጵያንና የግብፅን፣ እንዲሁም የኢትዮጵያንና የሱዳንን የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነት ለማጠናከር ወደ ካይሮና ካርቱም የተጓዘው የኢትዮጵያ የፐብሊክ ዲፕሎማሲ ቡድን በተለይ በካርቱም “የኢትዮጵያ ሳምንት” በሚል ስያሜ ያከናወነውን ኪነ ጥበባዊ ተግባር መጥቀስ ይቻላል፡፡

በዝግጅቱ ላይ ከሌሎች ተግባራት በተጨማሪ ባህላዊና ዘመናዊ የሙዚቃ ትዕይንቶች የቀረቡ ሲሆን፣ የሁለቱን አገሮች ሕዝቦች ይበልጥ ያስተሳሰረና የተሻለ መልካም ግንኙነትን ለመመሥረት የኢትዮጵያ የፐብሊክ ዲፕሎማሲ እንቅስቃሴ አንድ መሣሪያ ሆኖ የሚያገለግል ነው፡፡ የህዳሴ ግድብ ለልማትና ለጋራ ጥቅም መሆኑን በማመን ድጋፍ መገኘቱ፣ የኢኮኖሚ ትስስሩ ይጠናከር የሚለው መልዕክት ከሱዳን መንግሥትና ከቢዝነስ ዘርፍ መቅረቡ፣ ታሪካዊው አንድነት ጎልቶ መውጣቱ፣ ለኢኮኖሚና ለፖለቲካዊ ትስስርና ውህደት፣ ለፀረ ሽብርተኝነት ትግልና ለሰላም ዕውንነት በጋራ ሞዴል ለመሆን የሚቻል መሆኑና የጋራ መግባባት ላይ መደረሱ ከጉብኝቱ የተገኙ ውጤቶች ናቸው፡፡

በአጠቃላይ የኢትዮጵያ  ፐብሊክ ዲፕሎማሲ እነዚህን ዓበይት ገጽታዎች አጣምሮ የያዘ ሲሆን፣ ምንም እንኳን በአሁኑ ወቅት ያለው የአገሪቱ የፐብሊክ ዲፕሎማሲ እንቅስቃሴ አበረታች ውጤቶች የሚታይበት ቢሆንም፣ ይበልጥ የተሻለ ውጤት ለማምጣት ዘላቂነት ያለው መዋቅርና የአሠራር ሥርዓት ዘርግቶ ወጥነት ባለው አግባብ በመደበኛነት እንቅስቃሴውን የማካሄዱን ባህል በማስረፅ ማከናወን ይገባል፡፡

ስለሆነም በመረጃ ሥርጭት ረገድ አሁን ያሉ ጅምር ሥራዎችን ማስፋትና ማጠናከር ያስፈልጋል፡፡ ለፐብሊክ ዲፕሎማሲ እንቅስቃሴ ተግባር የሚውሉ መሥሪያዎችን (ዌብሳይት፣ ኢንተርኔት፣ ሲዲ ሮም፣ የኦዲዮና የቪዲዮ እንዲሁም የኅትመት ውጤቶች ማዘጋጃ አውታሮችንንና መረጃ አቅራቢ ምንጮችን) ማደራጀትና ለሚፈለገው ዓላማ ማዋል ለነገ የማይባል ተግባር ይሆናል፡፡

በአንፃሩ በባህልና ትምህርት ልውውጥ በኩል እየተሠሩ ያሉ ሥራዎችን በማስፋፋትና ምርጥ ተሞክሮዎችን በመቀመር፣ ከአገራችን ተጨባጭ ሁኔታ ጋር  በማዋሀድ ማከናወን ያስፈልጋል፡፡ የትምህርት ልውውጦች፣ ከተሞች ለከተሞች፣ ተቋማት ከተቋማትና  የፓርላማ ለፓርላማ ጉድኝት ሲመሠረት በተቻለ መጠን በነዋሪዎች ብዛት፣ በመልከዓ ምድራዊ አቀማመጥ፣ በዋና ዋና ማኅበራዊና አካባቢያዊ ጉዳዮች ዙርያ ተመሳሳይነትና ተመሳሳይ ፍላጎት ካላቸው አጋሮች ጋር ማድረግና በጉድኝቱ ሒደት ዜጎችንና አጠቃላይ ማኅበረሰቡን ማሳተፍ ይኖርብናል፡፡ ያለ ማኅበረሰብ ንቁ ተሳትፎ ጉድኝት ሊኖር አይችልም፡፡ ኃላፊነት ላይ ያሉ የመንግሥት ተወካዮች ፕሮጀክቶችን ለማስኬድ ሚና ቢኖራቸውም፣ ጉድኝቱ እነርሱን ብቻ ያቀፈ መሆን የለበትም፡፡ ከመንግሥት አካላት በተጨማሪ ትምህርት ቤቶች፣ የስፖርት ክለቦች፣ የማኅበረሰብ ድርጅቶችና ሌሎች ማኅበራት ሊሳተፉበት ይገባል፡፡ በተጨማሪም የጉድኝቱን ትክክለኛ ምሥል ለመፍጠር የጉድኝቱን ጥቅሞችና ለውጦች ለአጠቃላይ ሕዝቡ በተለይም ለመገናኛ ብዙኃን ግልጽ ማድረግ ጠቃሚ ይሆናል፡፡

ሌላው ሊሰመርበት የሚገባው ጉዳይ የጋራ ዓላማን በግልጽ አስቀምጦ መንቀሳቀስ ነው፡፡ ከጉድኝትና ትስስር የምንፈልገው ነገር ምንድነው?  ይኼ በጉድኝት ወቅት ሊታይ የሚገባው የመጀመርያው ጥያቄ መሆን ይኖርበታል፡፡ ጉድኝቱ በወቅቱ ባሉ አንገብጋቢ ችግሮች ላይ እንዲያተኩር ማድረግና በጉድኝት አማካይነት የሚከናወኑ ተግባራት የዜጎችን አንገብጋቢ ጥያቄዎች የሚመልሱ መሆን ይኖርባቸዋል፡፡ እነዚህ ጉዳዮች አካባቢ፣ ሰላም፣ ሥራ ፈጠራ፣ ስፖርት፣ ማኅበራዊ ፍትሕ፣ ወዘተ…ሊያካትቱ ይችላሉ፡፡

 የባህል ልውውጥና ጉድኝትን ለረዥም ጊዜና ቀጣይነት ላለው ግንኙነት አልሞ መፈጸም፣ የጉድኝት እንቅስቃሴዎችን በበጀት ማስደገፍና ፈንድ ማፈላለግ  ለስኬት ይበጃል፡፡ ምንም እንኳ በጥንቃቄ ቢሠራም ማንኛውም ድንበር ተሻጋሪ ጉድኝት ወጪን ይጠይቃል፡፡ ስለሆነም በኃላፊነት ቦታ ላይ የሚገኙ ሰዎች ለጉድኝቱ በጥቂቱም ቢሆን ዓመታዊ  በጀት መመደብ ቢችሉ ጠቃሚ ነው፡፡

የሕዝብ ለሕዝብ ትብብርን በተመለከተ በፐብሊክ ዲፕሎማሲ ቡድኑ የግብፅና የሱዳን ጉዞ ለወደፊቱ እንዴት መንቀሳቀስና ምን መሠራት እንዳለበት የሚያሳዩ ዕውቀትና ልምዶች ተገኝተዋል፡፡ በቀጣይ የፐብሊክ ዲፕሎማሲ ቡድኑ በተሻለ ሁኔታ በመንቀሳቀስ የኢትዮጵያንና የአጋሮቿን የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነት ወደ ላቀ ደረጃ ያደርሰዋል የሚል ዕምነት ተጥሎበታል፡፡

ጠቅለል ባለ መልኩ የኢትዮጵያ የፐብሊክ ዲፕሎማሲ እንቅስቃሴ የቅርብ ዓመታት ዕድሜ ያለው፣ አዲስና  እያደገ የሚሄድ ሲሆን፣ ከላይ እንደተጠቀሰው በአጭር ጊዜ ውስጥ አመርቂ ውጤቶች የተገኙበት እንቅስቃሴ ነው፡፡ ስትራቴጂካዊ ግባችን ግልጽና ተደራሽ በመሆን፣ ይኼ እንቅስቃሴ ይበልጥ ሊዳብርና ወደፊት ሊራመድ የሚችለው ደግሞ በተቀመጠው የፖሊሲ አቅጣጫ መሠረት ርብርብ ሲደረግ ነው፡፡ ከፐብሊክ ዲፕሎማሲ ቡድኑ ሥራ ጎን ለጎን ልዩ ልዩ ችሎታ ያላቸው አካላት በጎ ገጽታን በመገንባት ብሔራዊ ጥቅማችንን ማስጠበቅ የሚችሉበትን መድረክ ፈጥሮ መደገፍ ያስፈልጋል፡፡ የፐብሊክ ዲፕሎማሲ ቡድኑ በጎረቤት ለዚህም መንግሥትና መንግሥታዊ ያልሆኑ አካላት፣ ተቋማት፣ የሃይማኖት መሪዎች፣ የኪነ ጥበብ ባለሙያዎች፣  ምሁራን፣ የሲቪክ ማኅበራትና የመገናኛ ብዙኃን ተቋማዊ በሆነ መልኩ ቅንጅታዊ አሠራርን ዘርግተውና አቅማቸውን አዳብረው በብቃት መንቀሳቀስ ይጠበቅባቸዋል፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸው  [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡

 

 

 

spot_imgspot_img
- Advertisment -

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

Related Articles