በኢትዮጵያ አንዳንድ አካባቢዎች የክረምት ወቅት የሚገባበት እንደመልክዓ ምድሩ ገጽታ ቢለያይም በአብዛኛው አካባቢ ግን ወቅቱ የክረምት ነው፡፡ እንደ ክረምትነቱ በተለይም ሰኔ ግም (ም ይጠብቃል) ብሎ የሐምሌ ጭለማን አልፎ ነሐሴን በጎርፍ ሙላት ይሻገራል እየተባለ የሚነገርለት የአገሪቱ ክረምት፣ ዘንድሮ እንደሚጠበቀው አለመሆኑ እየታየ ነው፡፡ በሐምሌ ጭለማነቱ እምብዛም አልተስተዋለም፣ የሐምሌ መገባደጃ ላይ የምትታየው የሦስት ቀናቱ እኝኝም አልተከሰተችም፡፡ የፀሐዩን መግረር ያዩ ቤተ እምነቶችም ጸሎት ማወጃቸውም ተሰምቷል፡፡
በሌላ በኩል ክረምቱ በተመቻቸላቸው አካባቢዎች የእርሻው የዘሩ ሒደት ባግባቡ እየተከናወነ መሆኑም ይነገራል፡፡ ከበልግ በኋላ የመጣውን ክረምት ተከትሎ እንደየብሔረሰቡ የእርሻ ሥርዓት የዘር ሒደት እንደየባህሉና ትውፊቱ እንደሚከናወን ይታመናል፡፡
በትግራይ ክልል የሚገኘው የኩናማ ብሔረሰብ በክረምት ለዘር የሚደረግ ባህላዊ ሥርዓት አለው፡፡ ከቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለሥልጣን የፎክሎር ባለሙያው (ፎክሎሪስት) አበበ ኃይሉ በመስክ ባደረገው ጥናቱ በማኅበረሰቡ ዘንድ ከፍተኛ ዋጋ የሚሰጠውን ሥርዓት አስቀምጦታል፡፡
እንደ አቶ አበበ ማብራሪያ፣ በኩናማ በክረምት የዘር ጊዜ መድረሱን ለማሳወቅ የሚከናወን ራሱን የቻለ ባህላዊ ሥነ ሥርዓት አለ፡፡ የእርሻ ሥራና የዘር ጊዜ መድረሱን ለማሳወቅና ዘመኑ የሰላም፣ የዘሩት ለፍሬ የሚበቃበትና መጪው ዘመን የጥጋብና የጤና እንዲሆንላቸው ገበሬዎች ዘር ከመዝራታቸው ጥቂት ቀናት ቀደም ብሎ የሚያከናውኑት ትውፊታዊና ልማዳዊ ሥነ ሥርዓት ለጋላሽ እየተባለ ይጠራል፡፡ ለጋላሽ በኅብረተሰቡ ዘንድ ከፍተኛ ዋጋ የሚሰጠውና በየዓመቱ የሚከናወን ሥነ ሥርዓት ነው፡፡
ለጋላሽ ማለት ፀሎት ማድረስና የፀሎት ሥነ ሥርዓቱን ክንዋኔዎች የሚገልጽ ስያሜ ነው፡፡ ሥነ ሥርዓቱ የሚከናወነው ከሰፈር ወጣ ብሎ በሚገኝ ለዚሁ ተብሎ በተዘጋጀ ኮኦዳ በሚባል ስፍራ ነው፡፡ የለጋላሽ ሥነ ሥርዓት በኃላፊነት የሚመሩና የሚያስተባብሩ የመሬት ደኅንነት ጠባቂ ተብለው የሚታመንባቸውና ከመሬት ጉዳይ አንፃር የሚከሰቱ አለመግባባቶችንና ግጭቶችን እንዲዳኙ ኃላፊነት የተሰጣቸው ለጋመኔዎችና የአገር ሽማግሌዎች ናቸው፡፡ ማንም ገበሬ ለጋመኔዎች በይፋ የዘር ጊዜ መድረሱን ሳያሳውቁ በማሳው ዘር መዝራት አይፈቀድለትም፡፡ በዚህ ዓመታዊ የፀሎት ሥነ ሥርዓት ተሳታፊ የሚሆኑ ወንዶች ብቻ ናቸው፡፡ ሴቶች በዚህ ሥነ ሥርዓት መሳተፍ/ ሆነ በቦታው መገኘት አይፈቀድላቸውም፡፡ ሥነ ሥርዓቱ የሚከናወንበትን ቀን በይፋ የሚያሳውቁት የየአካባቢው ለጋመኔዎች ናቸው፡፡ በዕለቱ ገበሬዎች ለጋላሽ በሚከናወንበት ቦታ (ኮኦዳ) የመገኘትና ሥነ ሥርዓቱን የማካሄድ ባህላዊና ማኅበራዊ ግዴታ አለባቸው፡፡ ይህን ካላደረጉ በሰብላቸው ላይ መጥፎ ነገር ይደርሳል ተብሎ ይታመናል፡፡ በአስገዳጅ ሁኔታና ለጊዜው በሰፈር አካባቢ የሌለ ሰው ካልሆነ በስተቀር በለጋላሽ ሥነ ሥርዓት ላይ ከመሳተፍ ወደኋላ የሚል እንደሌለና ኅብረተሰቡም ሥነ ሥርዓቱ የሚከናወንበትን ቀን በንቃት እንደሚከታተል መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡ የለጋላሽ ሥነ ሥርዓት ሳይከናወን ከቀረ ወይም ሥነ ሥርዓቱ ሳይከናወን ዘር የሚዘሩ ገበሬዎች ካሉ የተዘራው ለፍሬ ላይበቃ፣ ዘመኑም የሰላምና የጤና ላይሆን ይችላል የሚል ቆየ እምነትና አስተሳሰብ አለ፡፡
ለጋላሽና እና እርድ
የለጋላሽ ሥነ ሥርዓት ሲከናወን በመጀመሪያ አንድ ቀይ ፍየልና አንድ በግ እንደ የመሬት ግብር ተደርጐ ይታረዳል፡፡ ከሚታረዱት ፍየልና በግ አንዳቸው ወንድ አንዷ ደግሞ ሴት ስትሆን ይህ ሳይሟላ ሥነ ሥርዓቱን ማካሄድ ደግ አይደለም ተብሎ ይታመናል፡፡ የፍየልና የበግ ደም ማፍሰስ ለመሬት ክብር ሲባል የሚፈስ ደም ወይም መሬት የተባረከች እንድትሆን ሲባል የሚቀርብ መስዋዕት ተደርጐ የሚታይበት ሁኔታ አለ፡፡ ለእርድ የሚቀርበው ፍየልም ሆነ በግ የቆዳ ቀለም በማናቸውም ሁኔታ ዥንጉርጉር ወይም ሌላ የተለየ ቀለም ያለው መሆን የለበትም፡፡ ምክንያቱን በተመለከተ አቶ አበበ ጥናታዊ ጽሑፋቸው የጠቀሷቸው የአገር ሽማግሌ እንዲህ አብራርተውታል፡፡
‹‹ፀሎት ሲደረግ ሁሉም ነገር ንጹህና የሚያምር ሆኖ መታየት አለበት፡፡ ቀይና ነጭ ቀለም ደግሞ ደስ የሚል ስሜትን ይጭራል፡፡ በሌላ በኩል ይህ ሥነ ሥርዓትም ከጥንት ጀምሮ የነበረና ከትውልድ ወደ ትውልድ ሲተላለፍ የመጣ እንደመሆኑ እኛ የአሁኑ ትውልድ ሰዎችም እምነቱን ተቀብለን ይህንኑ እየተገበርን እንገኛለን፡፡
የቀለም ምርጫው ደስ የሚልና የሚያምር ተደርጐ መታየቱ ሌላም ትርጉም አለው፡፡ ይኼውም የመሬት ቀለም አንድ ዓይነትና ደስ የሚል ነው ብለን ስለምናምን ከዚህ ውጪ ያለው እንደ መሬት ቀለም ደስ የሚል ነው ብለን አናስብም፡፡ በዚህ ምክንያት የጥንት ዝርዮቻችን ከመሬት አንፃር ተመልክተው የመረጡት ቀለም ቀይና ነጭ ሊሆን ይችላል፡፡››
ፎክሎሪስቱ አቶ አበበ ኃይሉ በጥናታቸው እንዳመለከቱት፣ ስለቀለም ምርጫ የተገለጸው እንደተጠበቀ ሆኖ ከጾታ አንፃር ለምን ወንድና ሴት እንዲሆኑ ተፈለገ የሚል ጥያቄም ሊነሳ ይችላል፡፡ እንዲህ መደረጉ ምናልባትም ከፈርቲሊቲ (Fertility) ወይም ዘርን ከመተካት ጋር በተያያዘ የጥንት ዝርዮቻቸው ዘንድ የነበረ እሳቤ ማሳያ ወይም የዚህ መገለጫ ተደርጐ ሊታይ ይችላል፡፡ በተመሳሳይ ሁኔታ ሥነ ሥርዓቱ የሚከናወንበት ዋና ምክንያት የተዘራ ለፍሬ እንዲበቃ ፀሎት ለማድረስና ለመሬት ያላቸውን ክብርና የህልውናቸው መሠረት መሆኑዋን ለመግለጽ እንደመሆኑ ተቃራኒ ጾታ ያላቸው የበግና ፍየል እርድ መደረጉ ትእምርታዊነት (ሲምቦሊክ) ለዘር ፍሬ መገኘትና ቀጣይነት የተቃራኒ ጾታዎች የሚኖራቸውን እኩል ድርሻ ማሳያ ተደርጐ ሊታይ ይችላል፡፡ እርድ ከተፈፀመ በኋላ ደሙ በንፁህ ዕቃ ተጠራቅሞ ለጋመኔዎች በየቤቱ በመዘዋወር መሬታቸው የተባረከች፣ የዘሩት ለፍሬ እንዲበቃ፣ ዘመኑ የሰላምና የጤና እንዲሆንላቸው እየለዩና እየመረቁ የዘንባባ ቅጠል በደሙ እያራሱ በየቤቱ በራፍ ላይ ይረጫሉ፡፡ እንዲህ ማድረግ ለጤና ደግ ነው ተብሎ ይታመናል፡፡
ቀመሳ
ከዚህ በመቀጠል ሥጋው ያለ ጨው በወንዶች ይጠበስና ታዳሚዎች ይቃመሳሉ፡፡ ሥጋው ልክ እንደ በረከት ተደርጐ የሚታይበት ሁኔታ አለ፡፡ ለታዳሚዎች ከመሰጠቱ በፊት ደግሞ ለመሬት ክብ ተብሎ ፈንጠቅ፣ ፈንጠቅ ይደረጋል፡፡ ቀደም ሲል እንደተገለጸው ሴቶች በሥነ ሥርዓቱ ላይ እንዲሳተፉ በባህሉ ባይፈቀድም በላጤነት የሚኖሩ ወይም ባሎቻቸው የሞቱባቸውና ገበሬ እማወራዎች ካሉ ከተጠበሰው ሥጋ የተወሰነው በእንጨት እየተሰካ ከበረከቱ እንዲቋደሱ በሚል በየቤታቸው ይላክላቸዋል፡፡ እንዲህ መደረጉ የእማወራዎቹ ባለቤቶች በሕይወት ቢኖሩ ኖሮ የሥነ ሥርዓቱ ታዳሚ ይሆኑ እንደነበር ታሳቢ በማድረግ ጭምር ነው፡፡
ክልከላ
ይህ ሥነ ሥርዓት እስኪፈጸም ከብቶች ወደ ዱር አይሰማሩም፣ ድንጋይ በወንጭፍ አይወረወርም፣ ሴቶች ደግሞ ወደ ወንዝ ሄደው ውኃ መቅዳትና እንጨት መልቀም አይፈቀድላቸውም፡፡ እነዚህ ክልከላዎች ከተጣሱ ፀሎቱ የሰመረ አይሆንም፣ የሚዘራው ለፍሬ አይበቃም፣ ፈጣሪና መሬት ይቆጣሉ ወዘተ. ተብሎ ይታመናል፡፡
ማሳረጊያ
ሥጋውን ከቀማመሱ በኋላ በለጋመኔዎችና የአገር ሽማግሌዎች መሪነት ሁሉም ታዳሚ በጋራ ፀሎት ያደርጋል፡፡ ፀሎቱ የሚያበቃው ሁሉም ፊታቸውን ወደ ምሥራቅ አዙረው ሁለት እጃቸውን ወደ ላይ ከፍ አድርገው በማንሳት ሦስት ጊዜ ቁጭ ብድግ እያሉ ፎሮ…..ሮ…..ሮ…..ሮ…..ሮ….. የሚል ድምፅ ካሰሙ በኋላ ነው፡፡ እንዲህ መደረጉ ወቅቱ የዘር ስለሆነ ፈጣሪ ድምጻቸውን ሰምቶ ዝናቡን እንዲቸራቸው ለመማጸን ነው፡፡ ፊታቸውን ወደ ምሥራቅ አቅጣጫ ማዞራቸው ደግሞ በኩናማዎች የሕይወት ፍልስፍና ጥሩ ነገር ሁሉ ዝናብን ጨምሮ የሚገኘው ወይም የሚመጣው ከወደ ምሥራቅ ነው ተብሎ ስለሚታመን ነው፡፡ ከዚህ በኋላ ገበሬዎች በየማሳቸው ዘር መዝራት ይጀምራሉ፡፡
በግለሰብ ደረጃ ደግሞ አንዳንድ ገበሬዎች ዘር ከመዝራታቸው በፊት ከየማሳቸው ላይ ዶሮ አርደው ደም ያፈሱና የዘሩን ለፍሬ እንዲበቃላቸው ፀሎት የሚያደርጉበት ጊዜ አለ፡፡ አንዳንዴ ከተገመተው በላይ ጥሩ ምርት ያመረቱ ገበሬዎች ሰብላቸውን ከአውድማ ከሰበሰቡ በኋላ እዚያው ውድማ ላይ ፍየል አርደው ምርቱ የሰላምና የጤና እንዲሆንላቸው የፀሎት ሥነ ሥርዓት የሚያደርጉበት ጊዜም አለ፡፡ እንዲህ መደረጉ ከወትሮው በተለየ ሁኔታ ምርት የተገኘ እንደሆነ ሞትም የዚያኑ ያህል ሊበዛ ይችላል፣ ጤናችንም ሊያስተጓጉል ይችላል የሚል አመለካከት ስላላቸው ነው፡፡ የታረደው ፍየል ደም እህል ከሚቀመጥበት ጐተራም ይረጫል፡፡