Tuesday, November 28, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

የሰከነውና የሰከረው ይለይ!

ሰላም! ሰላም! በህልሜ ይመስለኛል። ሰው ሁሉ ደላላ ሆኖ አያለሁ። ሕፃኑ፣ አዋቂው፣ የተማረው፣ ያልተማረው ምን አለፋችሁ የቀረ የለም። የክፋቱ ክፋት ደግሞ ህልም ውስጥ ሆኜ ህልም እንደሆነ ገብቶኛል። ባለራዕይ ብትሆን አልፈኸው ልትሄድ ነው አትሉኝም?እንዲያው እኮ! ‹‹ለምንድነው የሥልጣንን ክፍፍል አለማወቃችን ሳያንስ ሰው ከአንድ ጎታ እንጀራ መሻማቱ?›› ብዬ አንዱን ልጠይቀው ስጎትተው ነቃሁ። ዕድገታችን ብቻ መሰላችሁ ፈጣን? ህልማችንም እኮ ነው ሳንጨብጠው ሽው እያለ ያስቸገረን። የምር! ብቻ ለማንም ምንም ሳልል፣ ማንጠግቦሽ አገነፋፍላ የሠራችውን ሽሮ ቀማምሼ ከቤት ወጣሁ። ያው ሐሳቤ ያለው ግን የህልሜ ፍቺ ላይ ነው። አራት ኪሎ አካባቢ የቀጠረኝ ከባድ መኪና ሊገዛ የሚፈልግ ደንበኛ ስለነበረኝ የምሄደው ወደዚያው ነው። ስደርስ ዓይኔን ማመን አቃተኝ። የተመረቀውም የተረገመውም ጋዜጣ ይዞ . . . አይገለማመጥ፣ አይተያይ፣ የሥራ ቅጥር ማስታወቂያ ላይ አፍጧል።

‹‹ምንድነው ይኼ ሁሉ ሰው?›› ስለው አንዱን አልፎ ሂያጅ፣ ‹‹እኔም መጀመሪያ ወዶ ዘማች መስሎኝ ነበር። ቆይቶ ነው ‘ሳይወድ አቀርቃሪ’ መሆኑን የደረስኩበት፤›› ብሎኝ ሄደ። ‘ምናለ እስኪ በቀጥታ ቢናገር’ እያልኩ በእሱ መናደድ ስጀምር የህልሜ ፍቺ አይከሰትልኝ መሰላችሁ? አገር ምድሩ ደላላ ሆኖ ያሳየኝ ለካ ፈላጊና ተፈላጊ እየተራራቁ የሄዱበት ዘመን ስለሆነ፣ ተንከራታች እንደሚበዛ ሲገልጽልኝ ነው። እሱ ሲገልጽ ደግሞ እስከ እንጥፍጣፊው አይደል? እኔ ራሴ የድለላ ሥራ ውስጥ የገባሁት የተዋጣለት ተንከራታች ከነበርኩ በኋላ መሆኑ ትዝ አለኝ። ሁሉም ነገር ወዲያው ገባኝ። ይኼ ሁሉ ወጣት ደላላ ሲሆን አሰብኩ። ያውም የተማረ ዲግሪ ያለው ደላላ። አስባችሁታል? እኔ በታክሲ ስዛክር ቤቱ ቁጭ ብሎ በ‘ቻት’ እና በ‘ኢሜል’ ሻጭና ገዢን፣ አከራይና ተከራይ ሲያገናኝ ሳልኩት። ‘ደግሞ የዚህ አገር ዲግሪ’ አትበሉ ‘ፕሊስ’፡፡ እንኳን የተማረው ፊደል የማይለየው መኀይም ሳይቀር ‘ሎግ ኢን-ሎግ አውት’ በቻለበት ዘመን እንዲህ ይባላል? ሆሆ!

በተያያዘ ጨዋታ ብዬ ልቀጥል አስቤ ሳቄ ቀደመ። ከአንድ ፈታላ ወዳጄ ጋር እያወራን ልክ እንዳሁኑ ‘በተያያዘ ጨዋታ’ ብዬ ልቀጥል ስል፣ ‹‹ምን ማያያዝ ያስፈልጋል? ከተያያዘ ዝም ብለህ አትቀጥልም? ደግሞ ከመቼ ወዲህ ነው ጨዋታ የሚያያዘው አንበርብር? አንተም እንደ ‘ኢቢሲ’ ወጥ ታሪክ ከፋፍሎ በማያያዝ ማውራት ተጋባብህ?›› አለኝ። ነግሬያችሁ እንደሆነ አላውቅም እንጂ ዜናን ልክ እንደ ‘ሲሪየስ ፊልም’ በ‘ሲዝን’ የሚያዘጋጅ ብቸኛ ጣቢያ ‘ኢቢሲ’ ነው’ ብሎ ያምናል። ለምሳሌ የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ዜና ዕረፍት ሲዝን፣ የኦባማ ጉብኝት ሲዝን፣ የዲያስፖራው ሲዝን ዓይነት ማለቱ ነው። እናም እንዲህ እያለ ይቀልዳል። ራሱ ቀልዶም ራሱ ይስቃል። ቀልደው የሚስቁ ጤነኞች ናቸው ብለን እንለፈው። አንተላለፍ ብለን እኮ ነው እንጂ መንገዱም በጦር ጠማኝ ያዝ ተደርጓል አልሰማችሁም?

 ምን ላያይዝ ነበር ተያይዤ የቀረሁት እናንተ? . . . አዎ . . . ውሎ አድሮ ህልሜንና ግጥምጥሞሹን ለባሻዬ አጫወትኳቸው። ሥጋቴን አልተናገርኩም። ሁሉን ዝርግፍማ ባህላችን አይደለም። ታዲያስ! ምን አሉኝ ታዲያ፣ ‹‹አሁንስ ቢሆን ደላላ ያልሆነ ማን አለ?›› ብለው ጀመሩ። ‹‹እንዴት?›› ስላቸው ‹‹በከንፈር የማይደልለን፣ በፎቶ የማይደልለን፣ በአነጋገር፣ በቅስቀሳ፣ በምርጫ፣ በአመጋገብ፣ በአለባበስ፣ በአሾፋፈር ኧረ ምኑ ቅጡ። ምን የማንደለልበት ነገር አለ?›› ሲሉ አፈጠጡብኝ። ‘እውነታቸውን እኮ ነው’ እያልኩ ፈዝዤ ቀረሁ። ‘እኔ ቤቴ ወገብ የሚሰብር አልጋ ላይ እየተኛሁ እከሌ ተንቀባሮና ልጥጥ ብሎ መኪና የሚነዳው ማን ስለሆነ ነው?’ ብሎ አንዱ መጥቶ ‘ኮሮላ’ ያጋዛሁት ደንበኛ አለ ለምሳሌ። ኋላ ሲያጣራ ለካ ‘እከሌ’ ያለው ሰው መንግሥት መሥሪያ ቤት በሹፍርና ተቀጥሮ ‹‹V8›› ሲነዳ ዓይቶት ነው። አንዱ ደግሞ (ነዳጃችንን ስናወጣው እንደ ጉዳችን የማያልቅ ያድርግልንና) እንደዚሁ ‘ፌስቡክ’ ላይ የተዋወቃት ልጅ ነበረች። ገና በአካል ሳይተያዩና ሳይጨባበጡ ሌት ተቀን እንጋባ እያለች አላስቀምጥ አለችው። ‘በቃ ላገባ ነው’ ብሎ ሠፈሩን አተራመሰው። ‘እሰይ’ ተባለ። ያው ከላይ እስከታች መበደር ነው የምናውቀው ቤተሰብ ተበዳድሮ ደገሰ። እንዲያው ግን፣ ‘ሙሽሪትን ይዘሃት መጥተህ አስተዋውቀን እንጂ’ ምናምን አይባልም? ለምንድነው ለድግስና ለጭፈራ የምንቸኩለው? ኧረ ያስተርጓሚ ያለህ!

 ኋላ የሠርጉ ቀን ደረሰና (ሁለተኛ ሚዜ እኔ ነበርኩ) ሙሽሪት ቤት ‘ፌስቡክ’ ላይ በተለጠፈልን የጉዞ መመሪያ (GPS መሆኑ ነው) እየተመራን ደረስን። የወጉን ‘እንግባ አናስገባም’ ተጋፍተን ስንገባ ሙሽራው በቆመበት የእንግርግሪት ወደቀ። ይቅርታ ለካ ‘ፌንት በላ’ ነው የሚባለው። ‘ሶሪ!’ ሽብር ሆነ። ‹‹ምንድነው?›› ሲባል የሚናገር የለም። ገሚሶቻችን ቀዝቃዛ ውኃ ስንቸልስበት ገሚሶቻችን የሳትነው መመርያ እንዳለ የሙሽሪትን ‘ፌስቡክ አካውንት’ እንጎረጉራለን። ለካ አጅሪት ሌላ፣ መከረኛው ‘ፌስቡክ’ ላይ የተሰቀለው ፎቶዋ እንቁ የመሰለች ሞዴል ሆኖ ነው። በአጭሩ አልተገናኝቶም ሆኖ ነው። እንኳን ሙሽራው እኛም ‘ፌንት’ መብላት አማረን። ደግሞ ይኼን ሰምተው ነገር ጠምዛዦች ሕዝቡ በረሃብ እየረገፈ ነው ብለው እንዳያወሩ እንጂ ‘ፌንት’ መብላቱስ ግድ የለም ይደርሳል!

 ይኼን ይኼን ሳስታውስ ስማችን እንዳይበላሽ ፈራሁ። ለነገሩ ምን ያልተበላሸ ስም አለን? የዚያን ደንበኛዬን ጉዳይ ዳር ለማድረስ እየተጣደፍኩ ከባሻዬ ልጅ ጋር ጥቂት ሰዓት ሳገኝ ፍርኃቴን ነገርኩት። እሱ ደግሞ ያው ቆርጦ ቀጥል ነው እንደምታውቁት። በተማረና ባልተማረ መሀል ያለ የቆርጦ አቀጣጠል ልዩነት ያን ያህል ቢሆንም የምሁሩ የባሻዬ ልጅ ግን ለየት ያለ ነው። ‹‹አንተ ደላላ የሚለው ስም ተበላሸ ብለህ ትጨነቃለህ? ምን ያልተበላሸ ስም፣ ምን ያልተወላገደ ትርጓሜ ያልያዘ ስም አለ? ነጋዴ ብትል፣ መንግሥት፣ ፍትሕ ብትል ዴሞክራሲ፣ ምርጫ ብትል ኮሚቴ፣ ስብሰባ ብትል ቢሮክራሲ ምን ትርጉሙን ያልሳተ ስም አለ?›› ሲለኝ የት ልግባ? የት ልግባ? ‹‹ኧረ እባክህ ሰው እንዳይሰማ ድምፅህን ቀነስ አድርግ›› ስለው፣ ‹‹ሰው ብትል ፈጣሪ፣ ወንድ ትላለህ ሴት፣ ባል ትላለህ ሚስት . . .›› እያለ ቀጠለዋ። ‘ምን ዓይነት ጣጣ ነው በገዛ እጄ እስኪ አሁን’ አልኩና ጥዬው ላጥ። ደሳሳ ጎጆዬን አቀና ብዬ ጠማማ ስያሜ ስቆጥር ለጥያቄ ብጠራ ለማን አቤት እላለሁ? የ50 ሆነ የ500 መቶ ብር ጥያቄ አለ ብልስ ማን አቤት ሊለኝ? አይደል እንዴ? እናም ባገኘው ቦታ ሁሉ ነገር እየዘረገፈ ያስቸገረኝን የባሻዬን ልጅ ምን እንደማደርገው እያሰብኩ ስጓዝ አንዱ ሊስትሮ ‹‹እ? ይጠረግልሽ? ነይ ቁጭ በይ›› ሲለኝ ሰማሁት። ዘወር ብዬ ሳየው አንድ ፍሬ ልጅ። ‘አሁን ከዚህ ልጅ ጋር ፆታዬን መልስ አልመልስም’ ትግል መግጠም አለብኝ? ብዬ እሱንም ጥዬው ሄድኩ። ታዲያ በዚህ ዓይነት በየሄድንበት ከታገልንማ ‘ምን ያላልንበት ዳገት የለ’ም ካለችው አህያ በምን ተሻልን? ነገሩን ማለቴ ነው ደግሞ ሌላ ነገር እንዳታመጡ!

እናላችሁ እንዲያም እንዲህ ብሎ ሥራ ሳልሠራ አላድርም። ደንበኛዬን የሚፈልገውን መኪና አጋዝቼው ‘ኮሚሽኔን’ ስቀበል ደግሞ ሌላ መጣ። ይኼኛው ዳያስፖራ ነው። የአገሪቷን ዕድገትና ፈጣን ለውጥ ታዝቦ ‘ኢንቨስት’ ለማድረግ እንዲመቸው ስድስት ወራት መቆየት ይፈልጋል። ለእሱና ነፍሰ ጡር ባለቤቱ የሚሆን እስከ 30 ሺሕ ብር የሚከራይ ቤት አግኝቼለት ሳሳየው ሰውዬው የለም። ‘አይ ሀብታም መቼ ይሆን ቀልብ ያለው?’ እያልኩ በውስጤ ሐሳብ እንዳበዛ ስነግረው፣ ‹‹ምን ላድርግ ብለህ ነው?›› ብሎ ጀመረ። ‘እንዴ ዳያስፖራም የሚያደርገው ያጣል? እንደ እኛ ሰው ነው?’ እያልኩ፣ ‹‹ምነው ችግር አለ?›› ስለው፣ ‹‹ሚስቴ አላስቀምጠኝ ብላለች። ለአገሯ አፈር አብቅቻት አፈር አማረኝ ትላለች። ጉለሌ አልቀረኝ ኮተቤ፣ መረሬ ትላለህ ቀይ፣ ዘግኜ ስወስድ ‘የለም ያማረኝ የ‘ስቴት’ አፈር ነው’ አትለኝ መሰለህ? ተመልሶ እዚህ በመምጣቱ ሐሳብ መጀመሪያም ደስተኛ አልነበረችም ‹‹ለነገሩ…›› ብሎ በብስጭት ተወራጨ። ‘እግዚኦ! ሰው በስንቱ አፈር ይልሳል?’ እያልኩ እንደምንም ቤቱን እንዲከራየው አግባባሁት። አደራ ለማንጠግቦሽ አልነገርኳትም ከአፋችሁ እንዳይወጣ። ደግሞ በኋላ ‘ዳያስፖራ’ መሆን አማረኝ ብትለኝ ‘አፈር ስሆንልሽ?!’ እያልኩ ለምኜም እንደማልይዛት አውቄዋለሁ። እህ! ጠፍቶ የኖረው ሁሉ ሲመለስ ፍሪዳ እየታረደ ሲያይ ቤት የሰነበተው ‘ሂድ ሂድ’ አይለውም ሊባል ነው? እንዴት ያለ የዋህነት ነው ባባ ጃሌው!

በሉ እንሰነባበት። ኪሴ በገንዘብ ተወጣጥሮ ሊቀደድ ደርሷል። ለተወሰኑ የጠርሙስ ቢራዎች የሚሆነኝን ቆንጥሬ የቀረውን ቤት ቀርቅሬ ወደተለመደችዋ ግሮሰሪ አመራሁ። እንደገባሁ በሩቁ ያየሁት የባሻዬን ልጅ ነው። ቀን ስላናደደኝ ለንቦጬን ጥዬ ሄጄ አጠገቡ ተቀመጥኩ። መናገር ሲጀምር አቋረጥኩትና ያማረለት ከመሰለው እንደተሳሳተ አስረዳሁት። ‹‹ምንም ቢሆን ያለኸው ሦስተኛው ዓለም ነው፤›› ሲል አንዱ ከሩቅ ልክ ውሎ ገባችን እንደሚያውቅ ሁሉ ሲናገር ሁለታችንም ክው አልን። ለካስ ሰውዬው ሌላ ጨዋታ ይዞ ነው። እፎይ ከማለታችን የባሻዬ ልጅ በጥሞና አንድ የግሪክ አፈ ታሪክ አጫወተኝ። ‹‹ሲሲፈስ ይባላል። በግሪክ አፈ ታሪክ የኦሎምፒያ አማልዕክት ዋና አለቃ በሚባለው ዚውስ የተፈረደበት ግዞተኛ ነው። ዚውስ የፈረደበት የባህር አምላክን ሴት ልጅ ጠልፎ ሲያስወስዳት ሲሲፈስ አይቶ ለባህር አምላክ ስለነገረው ነው። ፍርዱ ምን ይመስልሃል ታዲያ? አንበርብር?›› አለኝ። እንዲህ በተረትና በምሳሌ ሲያጫውተኝ ደስ ስለሚለኝ ‹‹ምኑን አውቄ?›› አልኩት ፈታ እያልኩ። ‹‹ፍርዱ አንድ ረጅም ተራራ ጫፍ ላይ እንደ ኳስ የሚንከባለል ግዙፍ ቋጥኝ እየገፋ ማድረስ ነው። አደረስኩት ሲል ግና ቋጥኙ ተመልሶ ይንከባለላል። በአጠቃላይ የእኛም ነገር እንደ ሲሲፈስ ሲሆንብኝ እየተናነቀኝ ነው፤›› ሲለኝ ተረዳሁት። በተለይ በተለይ፣ የተበላሹ ስሞቻችን ካልተስተካከሉ ትውልድ የሲሲፈስን ታሪክ ሲቀባበል እንደሚኖር ተገለጸልኝ። የተማረ ይግደለኝ እንዳልል ያልተማረ ነው የሚቀብረኝ። እስኪ ከመሞታችን በፊት የተበላሹ ስሞቻችንን ይስተካከሉ። ‘የተማረ እየገደለ ያልተማረ ይቀብረናል’ የሚለው አባባል ምን ማለት ነው? ቆይ ግን በሰከነ መንፈስ ስናይ እኮ አባባሉ ከበድ ይላል፡፡ ሰከን ስንልና ሰከር ስንል ልዩነቱ ቁልጭ ብሎ ይታየናል፡፡ ሰከን ያሉቱ አስተውሎት አላቸው፡፡ የሰከሩት ደግሞ ጌሾ ወስዷቸዋል፡፡ ስለዚህ የሰከነና የሰከረ ይለይ! መልካም ሰንበት!    

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት