Thursday, September 21, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ኪንና ባህልእልባት ያጣው የፊልም ስርቆት

እልባት ያጣው የፊልም ስርቆት

ቀን:

‹‹ላምባ›› በኩላሊት በሽታ የተያዘችን ታዳጊ ሕይወት ለማትረፍ ብዙ ውጣ ውረድ የሚያይ የቤተሰብን ታሪክ መነሻ ያደረገ ፊልም ነው፡፡ ሚያዝያ 29 ቀን 2007 ዓ.ም. ተመርቆ በተለያዩ በሲኒማ ቤቶች እየታየ ነበር፡፡ ከሳምንታት በፊት ግን ፊልሙ ተሰርቆ በግለሰቦች እጅ መግባቱ ተሰማ፡፡ የፊልሙ ደራሲና አዘጋጅ አንተነህ ኃይሌ፣ ስለ ፊልሙ መሰረቅ ያወቀው በደረሰው የስልክ ጥሪ ነበር፡፡ ከፊልሙ ፕሮዲውሰር ጆሴፍ ኢቦንጎ ጋር  በመሆን ፊልሙ ታየ ወደ ተባለት ቦታ ካመሩ በኋላ ፊልሙን ይዞ በተገኘው ግለሰብ ጥቆማ እየተመሩ ምንጩ ላይ ለመድረስ መጣጣር ጀመሩ፡፡

በአንድ ምሽት ወደ 15 የሚጠጉ የፊልሙ ኮፒ ያላቸው ሰዎች ጋር ተፋጠጡ፡፡ አንዳቸው ከሌላቸው ማግኘታቸውን ገለጹላቸው፤ ብዙም ሳይቆይ ፊልሙ ከቁጥጥራቸው ውጪ በፍጥነት ይሰራጭ ጀመረ፡፡

አንተነህ እንደሚለው፣ የፊልሙ የምስልና ድምፅ ጥራት እንደተጠበቀ ሆኖ ሕጋዊ ባልሆነ መንገድ መሠራጨቱ፣ ፊልሙን ከሠሩ ባለሙያዎች ኦሪጅናል ሲዲዎች ከአንዱ መቀዳቱን አመላክቷቸዋል፡፡ ‹‹ፊልሙ እኛው አካባቢ በተፈጠረ ክፍተት በአቅራቢያችን ካሉ ሰዎች እጅ መውጣቱን አውቀናል፤›› ይላል፡፡

 ጉዳያቸውን ለፖሊስ ሲያሳውቁ አብረዋቸው ከሚሠሩ ባለሙያዎች መካከል የሚጠረጥሯቸውን በእምነት ማጉደል ክስ እንዲመሠርቱባቸው ቢነገራቸውም አንተነህ በተቃራኒው፣ ‹‹አብዛኞቹ አጠገባችን ያሉት ጓደኞቻችን ናቸው፤ እነሱን በማሳሰርና ምርመራ በማድረግ ሒደት ማለፍ ስላልፈለግን ክስ አልመሠረትንም፤›› ይላል፡፡

ፊልሙ በመሰረቁ ምክንያት የዕይታ ጊዜውን ሳያጠናቅቅ ከሲኒማ ቤቶች ለመውጣት ተገዷል፡፡ ‹‹ላምባ››ን በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት እንዲሁም በተለያዩ አገሮች ተዘዋውሮ የማሳየት ዕቅድም ተሰርዟል፡፡

‹‹ፊልሙ በስፋት እየታየ ነበር፤ በቀጣይም መታየት የሚችልበት ዕድል ነበረው፤›› የሚለው አንተነህ፣ ፊልሙ የሚያጠነጥንበት ርእሰ ጉዳይ የተመልካችን ቀልብ እንደሳበ ይናገራል፡፡ ፊልሙ ስለ ኩላሊት በሽታ ግንዛቤ ለመፍጠርና ለሚገነባው የኩላሊት ሕክምና ማዕከል ድጋፍ ለማሰባሰብ ታቅዶ የተሠራ መሆኑን በማጣቀስ፣ ፊልሙ መሰረቁ ዓላማቸውን እንዳደናቀፈው በሐዘኔታ ይገልጻል፡፡ ፊልሙን የተመለከቱ ግን በአጭር የጽሑፍ መልዕክትና በሌላም መንገድ ማዕከሉን እያገዙ ይገኛሉ ይላል፡፡

ከአንድ ዓመት በላይ የወሰደው ፊልሙ፣ ወደ 800,000 ብር ወጪ እንደተደረገበትና  በባለሙያዎቹ ላይ የደረሰረባቸው ኪሳራ ከባድ መሆኑን ይናገራል፡፡ ‹‹እጅግ የለፋሁበት ፊልም እንደ ተራ ነገር በሰው ፍላሽ ላይና በኢንተርኔት ላይ ተጭኖ ማየት ያማል፤ ነገስ ሌላ ፊልም የምሠራው ማንን አምኜ ነው?›› ሲል የሚጠይቀው ባለሙያው፣ በጉዳዩ ተጠያቂ የሚያደርገው ሕዝብና መንግሥትን ነው፡፡ አንድ ተመልካች በአነስተኛ ገንዘብ ፊልም መመልከት ሲችል፣ የተሰረቀ ፊልም በመቀበልና በማሰራጨት ሙያተኞችን ያከስራል፡፡ መንግሥት ለዘርፉ ተገቢውን የሕግ ከለላ እየሰጠ እንዳልሆነና ወንጀለኞች የሚቀጠቡት ሕግ መጥበቅ እንደሚገባውም ያስረዳል፡፡ በሌላ በኩል ፊልም ለማሳየት በየሲኒማ ቤቱ ሲዲ የመበተን ሒደት  ፊልሞችን  ለስርቆት ይዳርጋልና አሠራሩ መለወጥ አለበት ይላል፡፡

እንደ ‹‹ላምባ›› ሁሉ በርካታ ፊልሞች ሲኒማ ቤት እየታዩ እንዲሁም የዕይታ ጊዜያቸውን አጠናቀው በሲዲ ከተለቀቁ በኋላ በተለያየ ሁናቴ በሕገወጥ መንገድ ይሰራጫሉ፡፡ የፊልሞች ሕገወጥ ሥርጭት የኢትዮጵያ ሲኒማ ብቻ ሳይሆን የበርካታ አገሮች ራስ ምታት ነው፡፡ ባለሙያዎችን በእጅጉ የሚያከስረው የፊልሞች ስርቆት ለማስቆም የሚመለከታቸው ተቋሞች ቢረባረቡም ብዙም ለውጥ ማምጣት አልቻሉም፡፡  ችግሩን ለመቅረፍ የሚደረጉ ጥረቶች መጠነኛ ማሻሻል ቢያሳዩም፣  ከጊዜ ወደ ጊዜ የስርቆት መንገዱ እየተለዋወጠና እየተራቀቀ እንደመጣ የዘርፉ ባለሙያዎች ይናገራሉ፡፡

ከኢትዮጵያ የኦዲዮ ቪዥዋል አሳታሚዎች ማኅበር ባገኘነው መረጃ መሠረት ከ2001 ዓ.ም. ጀምሮ 15 ፊልሞች ተሰርቀዋል፡፡ ‹‹ሜድ ኢን ቻይና››፣ ‹‹ላ ቦረና››፣ ‹‹ፍቅርና ገንዘብ››፣ ‹‹11ኛው ሰዓት››፣ ‹‹ፍቅር ሲፈርድ›› እና ‹‹ፍቅርና ዳንስ›› ይገኙበታል፡፡ በሲዲ የተለቀቁ ፊልሞችን በሕገወጥ መንገድ አባዝተው የሚቸረችሩ ግለሰቦች እንዳሉ ሆነው፣ ፊልሞችን ከሲኒማ ቤት የተለያየ ቴክኖሎጂ ተጠቅመው የሚሰርቁቱም አሉ፡፡  

የኢትዮጵያ የኦዲዮ ቪዥዋል አሳታሚዎች ማኅበር ሥራ አስኪያጅ አቶ ኃይላይ ታደሰ ጥቂቱን ይናገራሉ፡፡ አንድ ፊልም ላይ በጥምረት የሚሠሩ ፕሮውዲሰሮች ወይም ሌሎች ባለሙያዎች በአንዳች ምክንያት ሲጋጩ፣ አንዳቸው ሌላቸውን ለመጉዳት ፊልሙን ለሦስተኛ ወገን አሳልፈው ይሰጣሉ፡፡ የፊልም ፕሮሞተሮች በአዲስ አበባ ወይም በክልል ከተሞች ለማሳየት በሚንቀሳቀሱት ወቅት ከጥንቃቄ መጉደል አልያም ሆን ተብሎ ፊልም የሚጠፋበት አጋጣሚ አለ፡፡ አንድ ፊልም ሲኒማ ቤት ውስጥ ከሚታይበት ዲስክ ማጫወቻ ላይ በኬብል ወይም ሌላ ኤሌክትሮኒክ መሣሪያ ሊቀዳ ይችላል፡፡ ፊልሞችን ከሲኒማ ቤት ስክሪን ላይ በሞባይል በመቅዳት በብሉቱዝና ሌላም መንገድ የሚያሰራጩ ግለሰቦችም አሉ፡፡

አቶ ኃይላይ እንደሚሉት፣ ፊልሞች ሲኒማ ቤት ሳሉ በመስረቅ የቅጂ መብት ጥሰት የፈጸሙ ሦስት ግለሰቦችን ሕግ ፊት አቅርበዋል፡፡ ከእነዚህ ውስጥ ‹‹የተቃጠሉ ገጾች›› የተሰኘ ፊልምን ሰርቀው እጅ ከፍንጅ የተያዙት ይጠቀሳሉ፡፡ ፊልሙ የተሰረቀው በአንድ ግለሰብ ሲሆን፣ የፊልሙ ፕሮውዲሰር ገንዘብ ካልከፈለች ፊልሙን እንደሚለቀው ነገሮ ያስፈራራታል፡፡ ፕሮዲወሰሯም ለማኅበሩ አሳውቃ አስይዛዋለች፡፡ ተመሳሳይ የመብት ጥሰቶች ከአምስት እስከ አሥር ዓመት በሚደርስ ጽኑ እስራትና አንድ ፊልም ታይቶ ሊያስገኝ የሚችለውን ገንዘብ ከሞራል ካሳ ጋር ያስቀጣል፡፡

የፊልሞች መሰረቅ ከባለሙያዎች በተጨማሪ አገሪቱንም መጉዳቱ እሙን ነው፡፡ የማኅበሩ ሥራ አስኪያጅም፣ ‹‹የፊልሞች መሰረቅ ውስብስብ የሆነ ቀውስ ያስከትላል፤ ባለሙያዎች ማድረግ ከሚገባቸው ጥንቃቄ ባሻገር ፊልሞችን ለማስጠበቅ ከሲኒማ ቤቶች ጋር በመደራደር አንዳች መፍትሔ ሊፈልጉ ይገባል፤›› ይላሉ፡፡

ብሩክ ታምሩ የፊልም ደራሲ፣ አዘጋጅና ፕሮዲውሰር ሲሆን፣ ‹‹ብርር…››፣ ‹‹ነቄ ትውልድ›› እና ‹‹የአራዳ ልጅ›› የተሰኙ ፊልሞች ሠርቷል፡፡ ‹‹ነቄ ትውልድ›› ይታይ በነበረበት ወቅት የገጠመውን አካፍሎናል፡፡ ፊልሙን አድማስ ሲኒማ ቤት ከሚያዩ  ተመልካቾች አንዱ የፊልሙን የመጀመርያ 40 ደቂቃዎች በሞባይሉ ይቀዳ ኖሯል፡፡ ተመልካቹ የድሬዳዋ ዩኒቨርስቲ ተመራቂ ተማሪ ነበር፡፡ ብሩክ ወደ ሲኒማ ቤቱ ተጠርቶ ከሄደ በኋላ ተመልካቹን ፖሊሲ ጣቢያ ቢወስደውም ተማሪው የነበረበትን የትምህርት ደረጃና ቀጣይ ሕይወት ከግምት በማስገባት ክስ አልመሠረተም፡፡ ፖሊስ ጣቢያ ያገኛቸው ሕግ አስከባሪዎች ላይ ግን በዘርፉ የግንዛቤ ክፍተት እንዳለባቸው መታዘቡን ይናገራል፡፡ አሁን እየታየ ያለው ‹‹የአራዳ ልጅ›› የተመሳሳይ ጥቃት ሰለባ ሆኗል፡፡ አየር ጤና የሚገኘው ጥበብ ሲኒማና ሐዋሳ ከተማ ውስጥ ፊልሙን በሞባይላቸው የቀረፁ ሰዎች እጅ ከፍንጅ ተይዘዋል፡፡

‹‹አዲስ አበባ ውስጥ ብቻ ወደ 20 ሲኒማ ቤቶች አሉ፤ ሁሉም ሲኒማ ቤቶች በአንድ ጊዜ ፊልሙን በሚያሳዩበት ጊዜ ሰዎች ብንመድብም ሲዲዎች የሚጠፉበት አጋጣሚ ይፈጠራል፤›› ይላል፡፡ በእነዚህ ክፍተቶች የፊልም ሲዲዎችን ከመስረቅ ወደ ኋላ የማይሉ መኖራቸውንም ይናገራል፡፡ መሰል ስርቆቶች ከፊልም ሠሪዎች ከሲኒማ ቤቶችም ቁጥጥር ውጪ እንደሆኑም ያክላል፡፡

ብሩክ እንደሚለው፣ አንድ ፊልም በርካታ ሙያተኞችን በማሳተፍ ሰፊ የሥራ ዕድል ከመፍጠሩ አንፃር መሰረቁ የብዙዎችን ጉሮሮ የሚዘጋ ነው፡፡ ፊልሙ በተለያየ መንገድ ከሠሪዎቹ እጅ ቢወጣም፣ ፊልሙን የሚያገኙ ግለሰቦች ኃላፊነት ሊሰማቸው ይገባል፡፡ የተሰረቁ ፊልሞች ባለሙያዎችንና ዘርፉን ከመጉዳት በዘለለ በዩቲዩብ የሚጫኑ በመሆናቸው ለስርቆት የጎላ ጥቅም እንደማያስገኙ ያስረዳል፡፡

ፊልም ከ15 ብር ጀምሮ እስከ 150 ብር ድረስ እንደየተመልካቹ አቅም ማየት እንደሚቻል በማጣቀስ፣ በገንዘብ የጎላ ለውጥ ለማያመጣ ነገር ባለሙያዎችን መጉዳቱ መቆም አለበት ይላል፡፡ ‹‹ሰዎች የተሰረቀ ፊልም አናይም ቢሉ ለውጥ ማምጣት ይቻላል፤›› የሚለው ብሩክ፣ ፊልም ሠሪዎች ፊልማቸው ሊሰረቅ እንደሚችል እየገመቱ ሲሠሩ ላለመክሰር በአነስተኛ ዋጋ ጥራቱን ያልጠበቀ ፊልም ለመሥራት እንደሚገደዱ ያስረዳል፡፡

አስተያየታቸውን የሰጡንን ፊልም ሠሪዎች ሐሳብ የሚጋራው ሌላው የፊልም ባለሙያ ያሬድ ሹመቴ ነው፡፡ የፊልም ሥራ የሚጠይቀው ገንዝብ ተመድቦለት በቀላሉ አይሠራም ይላል፡፡ አንጡራ ሀብታቸውን አሟጠውና ከዛም በላይ ብድር ገብተው  ፊልም የሚሠሩ ጥቂት አይደሉም፡፡ ፊልሞች ሲሰረቁ ባለሙያዎች ከሚደርስባቸው የገንዘብ ኪሳራ ባሻገር፣ በተሠሩበት የጥራት ደረጃ አይታዩም፡፡

እሱ እንደሚለው፣ የምስልና የጽምፅ ጥራት የሌላቸው የተሰረቁ ፊልሞች ባለሙያዎችን እጀ ሰባራ ያደርጋሉ፡፡ ፊልሞች ሲኒማ ቤት እየታዩ በሕገወጥ መንገድ ከተሰረቁና ከሲኒማ ቤት ከወረዱ፣ በሲዲ ታትሞ የመሸጥ ዕድላቸውም ይዘጋል፡፡ ይህም  ፕሮዲውሰሮችን ከዘርፉ ያሸሻል፡፡ አንድ ፊልም ሲሰረቅ በፊልሙ ላይ በተሳተፉ ሙያተኞች መሀከል አለመተማመንንም ይፈጥራል፡፡

ያሬድ ከሚያቀርባቸው የመፍትሔ ሐሳቦች አንዱ ሲኒማ ቤቶች ኃላፊነት የሚወስዱበትን አሠራር መዘርጋት ነው፡፡ በፊልም ፕሮዲውሰሮችና ሲኒማ ቤቶች መሀከል ፊልምን የማሳየትና አሳትሞ የማከፋፈል ድርሻ የሚወስዱ አከፋፋዩችን ማሳተፍም ያስፈልጋል፡፡ በሌሎች አገሮች የተለመደና በኢትዮጵያ ሲኒማም ቢለመድ መልካም ነው የሚለው ደግሞ የፊልሞች ኢንሹራንስ ነው፡፡

ዘርፉን መታደግ የሚችሉት ተመልካቾችም ባለሙያዎችም እንደሆኑ ያሬድ ይናገራል፡፡ ‹‹ጥበቡ ውስጥ ያሉ አንዳንድ ሰዎች ዝም ይላሉ፤ ሕገወጥ ቅጂም በየቤታቸው ያያሉ፤ ፊልም ሕጋዊ በሆነ መንገድ እስከሚወጣ ድረስ ዕርም ሕገወጥ ቅጂ አላይም ማለት አለባቸው፤›› የሚለው ባለሙያው፣ ተሞክሮዎቹን አካፍሎናል፡፡ መንገድ ላይ ሕገወጥ የፊልም ቅጂ የሚሸጡ ሰዎች ይገጥሙታል፡፡ ከሻጮቹ ጋር ግብ ግብ ውስጥ ይገባና ፍርድ ቤት ይደርሳሉ፡፡ ሻጮቹም ሁለት ዓመት እስራት ተፈርዶባቸዋል፡፡

በጉዳዩ ላይ የኢትዮጵያ ፊልም ሠሪዎች ማኅበር ምን እንቅስቃሴ ያደርጋል የሚል ጥያቄ ይዘን የማኅበሩን ምክትል ሊቀመንበር ደሳለኝ ኃይሉን አነጋግረናል፡፡ በዓለም አቀፍ አእምሯዊ ንብረት ጥበቃ እንዲሁም በኢትዮጵያው ጽሕፈት ቤት አንድ ባለሙያ የቅጂ መብቱ ሲጣስ የሚደርስበት የኢኮኖሚና ሞራል ውድቀት በግልጽ ቢቀመጥም፣ በግንዛቤ እጥረት ብዙዎች ሕጉን ይተላለፋሉ ይላል፡፡ ‹‹የባለሙያዎችን መብት መጣስ ተለምዷል፡፡ ሕዝብ የሠለጠነ የሚባለው አዕምሯዊ ንብረትን ሲያከብር ነው፤›› የሚለው ምክትል ሊቀመንበሩ፣ ማኅበሩ እንደ መፍትሔ የሚያስቀምጠው የፊልም ፖሊሲ መረቀቅን እንደሆነ ይገልጻል፡፡ ፖሊሲው ሲጸድቅ ለውጥ እንደሚኖር እምነቱ ነው፡፡ የፊልም ስርቆት ከሌሎች ንብረቶች ስርቆት በምንም እንደማይለይ ኅብረተሰቡ መገንዘብ እንዳበለትም በአጽንኦት ይናገራል፡፡

የፊልም ሠሪዎች መብት ካልተጠበቀ የፈጠራ ሥራዎች እንደማይበረታቱ ገልጾ፣ ‹‹የፊልም ስርቆት በማንኛውም ሃይማኖት ኃጢያት፣ በሕግ ወንጀል፣ በባህላችንም ነውር ነው፡፡ ሕግ አውጪውም ሆነ ሕግ አስፈጻሚ አካል ትኩረት ሰጥቶት ጠንካራ ዕርምጃ ሊወሰድ ይገባል፤›› ይላል፡፡ ፊልም ሠሪዎች በማኅበራት ቢታቀፉ መብታቸውን ለማስጠበቅ የሚያደርጉት እንቅስቃሴ ተሰሚነት እንደሚያገኝም ያክላል፡፡

በቅጂና ተዛማጅ መብቶች ጥበቃ በዋነኝነት የሚሠራው የኢትዮጵያ አዕምሯዊ  ንብረት ጽሕፈት ቤት በ2006 ዓ.ም. በዘጠኝ ከተሞች ጥናት አካሂዶ ነበር፡፡ በጥናቱ መሠረት ኦሪጅናል ፊልሞችን የሚመለከቱ ሰዎች 49.5 በመቶ ሲሆኑ፣ 52.7 በመቶ የቅጂ መብታቸው የተጣሰ ፊልሞች ያያሉ፡፡ ጽሕፈት ቤቱ የኮፒራይት የማኅበረሰብ ዕውቀት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ተድላ ማሞ፣ ፊልሞች ሲኒማ ቤት በመታየት ላይ ሳሉ የሌብነት ሰለባ መሆናቸው የቅጂ መብት ጥሰት ከፍተኛ ደረጃ ላይ መድረሱን እንደሚያመላክት ይናገራሉ፡፡ ጽሕፈት ቤቱ ከጊዜ ወደ ጊዜ ዘመን አመጣሽ ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም የሚደርሰውን የመብት ጥሰት ለመከላከል የተለያዩ መንገዶች ይጠቀማል ይላሉ፡፡ በጽሕፈት ቤቱ ተይዘው እስራትና የገንዘብ ቅጣት የተፈረደባቸው እንዲሁም ፍርዳቸውን በመጠባበቅ ላይ ያሉ ይገኙበታል፡፡

አቶ ተድላ እንደሚናገሩት፣ ብዙ ሙአለ ንዋይ እየፈሰሰበት ያለው የፊልም ዘርፍ ከሌሎች ኪነ ጥበባዊ ውጤቶች ጋር ተዳምሮ ለአገሪቱ ኢኮኖሚ የራሱ አስተዋጽኦ ያበረክታል፡፡ ከአራት በመቶ እስከ አምስት በመቶ የሚሆነውን የአገሪቱን ጠቅላላ የአገር ውስጥ ምርት (ጂዲፒ) የሚሸፍነው ዘርፍ፣ አሁን ካለው የጠነከረ ጥበቃ ያሻዋል ይላሉ፡፡ የፍትሕ አካላት ስለጉዳዩ ያላቸውን ግንዛቤ እንዲያዳብሩ መደረግ እንዳለበትና አሁን ያሉ እንቅስቃሴዎች በክልል ከተሞችም ተደራሽ መሆን እንዳለባቸው ያክላሉ፡፡ የቴክኖሎጂውን መራቀቅ በመከተል ሕግና ደንቦች ለባለሙያዎች ተገቢውን ከለላ የሚሰጡ መሆን እንደሚገባቸውና የጉዳዩ ባለቤት የሆኑ ፊልም ሠሪዎች ያላቸውን ተሰሚነት ተጠቅመው ቅስቀሳ ቢያደርጉ መልካም ነው ይላሉ፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ባለሙያዎች ኮሚሽን ሪፖርት ምን ይዟል?

ለአሜሪካ ድምፅ አማርኛ ዝግጅት የስልክ አስተያየት የሰጡ አንድ የደንበጫ...

መንግሥት በአማራ ክልል ለወደሙ የአበባ እርሻዎች ድጋፍ እንዲያደርግ ተጠየቀ

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአማራ ክልል የተፈጠረው ግጭትና አለመረጋጋት በቢዝነስ...

አምናና ዘንድሮ!

እነሆ መስከረም ጠብቶ በአዲስ መንፈስ ተሞልተን መንገድ ጀምረናል። ‹‹አዲስ...