Wednesday, June 19, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ይድረስ ለሪፖርተርእንደ ኢንቨስትመንቱ ለማኅበራዊ ኃላፊነትም እንሩጥ

እንደ ኢንቨስትመንቱ ለማኅበራዊ ኃላፊነትም እንሩጥ

ቀን:

እ.ኤ.አ. ጁላይ 12 ቀን 2015 በወጣው ካፒታል ጋዜጣ ላይ የአገራችን የሩጫ ንጉሥ ኃይሌ ገብረሥላሴ ‘Ending Extreme Poverty’ በሚል አርዕስት አስከፊ የአገራችንን ድህነት የሚገልጽበት እንዲሁም ለዘለቄታው መፍትሔ እንዲፈለግለት የሚያስፈልገውን ይህንን ችግር በዝርዝር ገልጾታል፡፡

በተለይ መንግሥት በመልካም አስተዳደር እንዲሁም የውጭ መንግሥታትና መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች በችግሩ ላይ እንዲረባረቡ አሳስቧል፡፡ በአሁኑ ጊዜ አገራችን በዕድገት ጎዳና ላይ እየገሰገሰች መሆኗንም መሆኑንም አስገንዝቧል፡፡

በዚሁ ጽሑፍ ውስጥ የጀግናው ኃይሌ እናት ብዙ ልጆች መውለዳቸውና በዚሁ በወሊድ ችግርና በጉስልቁልና ምክንያት ዕድሜው አሥር ዓመት በሆነው ወቅት ሕይወታቸው እንዳለፈ አትሌቱ አስተዛዝኖ ገልጾታል፡፡

- Advertisement -

በእርግጥ ‹‹የእናት ሞትና የድንጋይ መቀመጫ እያደር ይቆረቁራል፤›› ይባላል፡፡ ጀግናችን ሊያዝን ይገባዋል፡፡ ‹‹ዝናብ ሳለ ዝራ፣ እናት ሳለች ኩራ፤›› የሚለው የአባቶቻችን ብሂል አለመገጣጠሙ ግን ይቆጫል፡፡

የዚህ ጽሑፍ ዋናው ቁም ነገር ግን የኃይሌ ገብረ ሥላሴን ዓላማ ለማጠናከርና ሥር የሰደደውን የአገራችን ችግር ለመቅረፍ መጀመርያ እኛው ኢትዮጵያውያን ቅድሚያ ወስደን ተረባርበን ወደ መፍትሔው ልንጓዝ ይገባል የሚል ነው፡፡

ከራሱ ከኃይሌ ገብረ ሥላሴ ብንጀምር መልካም ይመስለኛል፡፡ በአገራችን ውስጥ ካሉ አንደኛ ደረጃ ኢንቨስተሮች ውስጥ ጀግናችን ኃይሌ ይመደባል፡፡ ላቡን አንጠፍጥፎ ባስመዘገበው የሩጫ ውጤት አገሩን አኩርቶ ለራሱም ተጠቃሚ ሆኗል፡፡ በአሁኑ ጊዜ ብዙ የንግድ ድርጅቶችን በማቋቋም በርካታ ኢትዮጵያውያን የሥራ ዕድል እንዲያገኙ ያደረገ ባለውለታችን ነው፡፡ እውነቱ ግን ከባህር ማዶ የሚገኙ ታዋቂ የስፖርት ጀግኖች  ድህነትን ለማጥፋት በሚያደርጓቸው እንቅስቃሴዎች ውስጥ እንደ ኬንያው አትሌት ፖል ቴርጋት ያሉት በቀጥታ እንደሚሳተፉ በመገናኛ ብዙኃን ተደጋግሞ ሲገለጽ ሰምተናል፡፡ ስለዚህም የእኛው ባለውለታ ጀግናው ኃይሌ ገብረ ሥላሴ ድህነት ለማጥፋት የሚረዱ የተለያዩ ፕሮጀክቶችን ከመቅረጽ ጀምሮ ተሳትፎ ቢያደርግ፣ ብዙዎችን ይታደጋል የሚል ዕምነት አለኝ፡፡

በአሁኑ ጊዜ በአገራችን እንደ ‹‹ሙገር ሲሚንቶ ፋብሪካ›› ለአካባቢው የሚያደርገውን ቀና የሆነ እገዛ ሌሎቹም ትላልቅ የግል ድርጅቶች ለምሳሌ ባንክ፣ ኢንሹራንስና ሌሎች ድርጅቶች ለአገሪቱ ትልቅ እገዛ ማድረግ ይችላሉ፡፡ በሌሎች አገሮች የድርጅቶች ማኅበራዊ ኃላፊነት የሚባል አሠራር የተለመደ ነው፡፡ ድርጅቶች በየዓመቱ ከሚያገኙት ትርፍ እየቀነሱ ለተቸገሩ ወገኖች ለእኛም ጭምር እንደሚለግሱ የታወቀ ነው፡፡

ለምንድነው ይህ ዓይነት አካሄድ በአገራችን የማይለመደውና የማይስፋፋው? በመሆኑም ግንባር ቀደም ሆነው ይኼንን ‹‹የችሮታ ሥራ›› አስተባብረው ሌላውን ለመደገፍ እንደ ኃይሌ ገብረ ሥላሴ ዓይነት ሕዝባዊነትን የተላበሱ ባለሟሎች ያስፈልጋሉ እላለሁ፡፡  

በርካታ ወጣት ኢትዮጵያውያንን መርዳት ያለብን ጊዜ አሁን ነው፡፡ በርካታ የሥራ መሰክ የሚፈጥሩበትን ሒደት ልናመቻችላቸው ይገባል፡፡ ይኼ ሳይሆን ቀርቶ ‹‹መዘግየት›› ከተፈጠረ ችግሩ የትየለሌ እየሆነ ሊቀጥል ይችላል፡፡

ጀግናው ኃይሌ ገብረ ሥላሴ በዓለም አቀፍ የሩጫ ውድድሮች ላይ በድል ሩጫውን አጠናቆ ሲያበቃ ከሽልማቱ በፊት ከዓይኑ ዕንባ ኮለል ብሎ ሲወርድ እኔም በየጊዜው ከእሱ ጋር ማልቀሴን አልዘነጋም፡፡ ስለዚህም የጀመረው የኢንቨስትመንት ተግባር ጎልብቶ ቀጣይነቱ እስኪረጋገጥ ድረስ ከዚህ ጎን የሰብዓዊ ተግባራት ጅምሩን በማስተባበር ያጠናክራል የሚል ዕምነት አለኝ፡፡ ጥያቄዬም ከማሳሰቢያ ጭምር ነው፡፡

በመጨረሻም በዚህ ዓመት ከቢቢሲ ጋር ባደረገው ቆይታ ስለጀመረው አንዳንድ እንቅስቃሴ ሲገልጽ፣ በአሁኑ ጊዜ በማዕድንና በእርሻ ኢንቨስትመንት መስኮች ላይ ለመሠማራት ማቀዱን አስታውቋል፡፡ ይህ መልካም አካሄድ ነው፡፡

በአገራችን ሻለቃ ኃይሌ በሩጫውም ሆነ በኢንቨስትመንቱ ከስፖርተኞች ፋና ወጊ ቢሆንም፣ ሌሎች የእሱን እግር ተከትለው በኢንቨስትመንቱ መሳተፍ የጀመሩትን ብርቅዬ የአትሌቲክስ ጀግኖቻችንም ይኼ መልዕክት ይመለከታቸዋል፡፡

(አቹማ አሰላ፣ ከአስኮ)

****

ስለአስተያየትዎ ቢያስቡበት

ሁልጊዜም እንደማደርገው የሐምሌ 12 ቀን 2007 ዓ.ም. ዕትም የሆነውን የእሑድ ጋዜጣ ሳነብ፣ በሳምንቱ ገጠመኝ ርዕስ ሥር ‹‹ወዜን አልሽጥም›› በማለት በአቶ ያሬድ ሹመቴ የተጻፈውን በማየቴ ምላሽ ለመስጠት ወደድኩ፡፡ ምክንያቱም ጸሐፊው በጽሑፋቸው ኅብረተሰቡ ላይ ያለውን የንጽህና ግንዛቤ ያላካተቱ ከመሆኑም ባሻገር ልክ ደራሲ የፊልም ስክሪፕት ሲጽፍ ወይም ድርሰት ሲደርስ ግነት ሊፈጥር ያሰበበት ቦታ ላይ እንደሚጻፈው የተጋነነ ነው፡፡

አቶ ያሬድ በጽሑፋቸው ባህር ዳር ከተማ ላገኟት ልጅ (ልብስ አጣቢ) ከኅብረተሰቡ ‹‹ገዛሁት›› ያሉትን ልብስ ተባዩን እንድታስለቅቅልኝ ሰጠኋት ወዘተ. እያሉ ከቀጠሉ በኋላ ከዚያው አካባቢ አለፍ በማለት ከሌሎች ሰዎች በተጨማሪ ልብስ በመግዛት ላይ በነበሩበት ወቅት በአካባቢው ኃላፊዎች ማረፊያ ቤት እንዲቆዩ ሲደረጉ ገዛሁት ባሉት ልብስ ላይ ያለው ተባይ እንዳይወጣ በማሰር ፍራሽ አድርጌ ተኛሁበት በማለት አስፍረዋል፡፡

ይህ አባባል ኅብረተሰቡን ጥላሽት እንደመቀባት ይቆጠራል፡፡ ምክንያቱም የአካባቢው ኅብረተሰብ ልብሱ ተባይ እስኪይዝ ሳያጥብ ሊቆይ ይቅርና ከመፀዳጃ ቤት እንዲሁም ከመኖሪያው በር ላይ በሚያገኘው ቁሳቁስ የእጅ መታጠቢያ አዘጋጅቶ በመጠቀም ላይ ያለ ሕዝብ ነው፡፡

ከዚህም ባለፈ ኅብረተሰቡ በመጠኑም ቢሆን በዘመኑ ቴክኖሎጂ በመጠቀም ስለ ንፅህና አጠባበቅ ግንዛቤ እያገኘ ነው፡፡ ‹‹የመጀመርያ ፊልም›› ሠራሁ ብሎ ራስን ለማሻሻጥ ከመሞከር ባለፈ ኅብረተሰቡን በማስተማር ግንዛቤውን ሊለውጥ የሚችል ሥራ በመሥራት ለወጡበት ኅብረተሰብ ውለታ ከፋይ መሆን እንጂ ሕዝቡን ጥላሸት በመቀባት የበሉበትን ወጭት ሰባሪ መሆን አያስፈልግም፡፡

(ቢኒያም እሸቱ፣ ከዋሽንግተን)

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የንብረት ማስመለስ ረቂቅ አዋጅና የሚስተጋቡ ሥጋቶች

ከሰሞኑ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የቀረበው የንብረት ማስመለስ ረቂቅ...

የመጨረሻ የተባለው የንግድ ምክር ቤቱ ምርጫና የሚኒስቴሩ ውሳኔ

በአገር አቀፍ ደረጃ ደረጃ የንግድ ኅብረተሰቡን በመወከል የሚጠቀሰው የኢትዮጵያ...

ሚስጥሩ!

ጉዞ ከካዛንቺስ ወደ ስድስት ኪሎ፡፡ የጥንቶቹ አራዶች መናኸሪያ ወዘናዋ...