Monday, June 24, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
እኔ የምለዉየስደት ነገር ሲነሳ እውነታው ወደ ጎን አይገፋ

የስደት ነገር ሲነሳ እውነታው ወደ ጎን አይገፋ

ቀን:

በሒሩት ደበበ

ሕገወጥም ይባል ሕጋዊ የአፍሪካዊያን ዋነኛ ችግር ነው፡፡ የአደጋው አስከፊነት አምራቹን ወጣት ኃይልና ዕምቁን ሀብት እያመከነ በመሆኑ ነው፡፡ በቅርቡ ኔሽን የተባለ የኬንያ ጋዜጣ አፍሪካ ከሙስናና ከኢቮላ ቀጥሉ ሕገወጥ ስደት (የሰዎች ዝውውር) የአፍሪካ አኅጉር ወቅታዊ ጠንቅ ሆኗል ሲል መዘገቡም ለዚሁ ይመስለኛል፡፡ አንዴ ጋብ ሌላ ጊዜ ሞቅ እያለ ችግሩ መቀጠሉም እየታየ ነው፡፡

በኢትዮጵያም ተመሳሳይ እውነት ያለው ነው፡፡ ዜጎች ሳይማሩና ገንዘብ ሳይኖራቸው ድንገት ብድግ ብለው የሚመኙት ስደት ነው፡፡ በተለይ ከአማራ፣ ከኦሮሚያና ከደቡብ ክልል በአንድ ወር እስከ 100,000 ብር ወጣቶች ከአገር የተሰደዱበት መረጃ የቅርብ ጊዜ ትውስታ ነበር፡፡ ይሁንና ባለፉት ሦስት ዓመታት መንግሥት ለጉዳዩ በሰጠው ከፍተኛ ትኩረት ‹‹በክልከላ›› ጭምር ችግሩ ትንሽ ጋብ ያለ መስሏል፡፡ ይሁንና አሁንም የስደት መንስዔውን መርምሮ፣ ዘለቂ መፍትሔ ማስቀመጥ ላይ አንድ ወጥ ዘዴ ካልተበጀ ችግሩ የሚቆም አልመሰለም፡፡

መንግሥት በተለይ ከሳዑዲ ዓረቢያ በግፍ ከ150,000 በላይ ዜጎች ከተመለሱ በኋላ በድንጋጤ የወሰዳቸው ዕርምጃ አሉ፡፡ ቢያንስ ወደ አገር የሚመጡትን ተቀብሎ ለማስተናገድና ለማደራጀት ተሞክሯል፡፡ ይሁንና የቅርብ መረጃዎች እንደሚያስረዱት ከተመላሾቹ መካከል ከግማሽ በላይ የሚሆኑት ተመልሰው ተሰደዋል፡፡ ‹‹ለምን?›› ብሎ መጠየቅ የመንግሥት ፋንታ ነው፡፡ እርግጥ አንዳንድ ክልሎች የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ሳይቀርፉ ለይስሙላ ተመላሾችን አደራጅተናል፣ ሥራ ፈጥረናል ቢሉም፣ ተገቢ ድጋፍ ባለማድረጋቸው ፍሬ ማፍራት አልተቻለም፡፡ በዚህ ላይ የተመላሾቹ ለሥራ የመነሳሳት ችግርና ጠባቂነት ብሎም ምንም ቢደረግ የስደት ሱሰኝነት ዋና እንቅፋት መሆኑን፣ ራሱ የሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር በቅርቡ ባስነበበው ጽሑፍ ገልጾታል፡፡

በመንግሥት ከፍተኛ አካላት ጭምር የተቋቋመው የፌዴራልና የክልል ሕገወጥ ስደት ተከላካይ ግብረ ኃይል ጊዜውን የጠበቀ ስብሰባ እያካሄደም ነው፡፡ አባላቱን በተለይ ግንዛቤ የማስጨበጥ ሥራ እየሠራና ሕገወጥ ደላሎች እንዲከሰሱና እንዲቀጡ ማገዙም አይታበልም፡፡ በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደረጃ የሚመራው (በፌዴራል ደረጃ) ይህ ግብረ ኃይል የስደትን ሥር ለይቶ ሰንኮፍን ስለመንቀሉ ግን ማሳያ አልተገኘም፡፡ ይልቁንም አሁንም ሕገወጥ ስደትና በተገኘው ቀዳዳ ማፈትለክ እንደቀጠለ መሆኑ ሲታይ ግብረ ኃይሉ የሚለው ሌላ ችግሩ ሌላ እየመለሰ ነው፡፡ ያልታዩ ጉዳዮችን እናንሳ፡፡

አውሮፓና አሜሪካ ሄዶ የሚሰደድ የመንግሥት ሠራተኛ ቁጥር ጨምሯል

ሕገወጥ ስደት ሲባል ዘወትር በአዕምሮአችን የሚመጣው ለዓረቡ ዓለም የጉልበት ሥራ እጅ እግሩን ይዞ በበረሃም ሆነ በውቅያኖስ አቋርጦ የሚሄደውን ስደተኛ ነው፡፡ ይኼም ቢሆን የሚገፋው የተሻለ ገቢ የመፈለግ ፍላጎት ብቻ አይደለም፡፡ ይልቁንም ድህነት፣ ኢፍትሐዊነት፣ የመልካም አስተዳደር እጦትና የባለቤትነት ስሜት መጓደል እንደሆነ መገንዘብ ይጠቅማል፡፡

ሌላው የሕገወጥ ስደተኛ መገለጫ ደግሞ በሌሎች አገሮች ግብዣ ወይም በመንግሥት ለሥልጠና፣ ለትምህርትም ሆነ ለሥራ ሲሄዱ ወጥተው የሚቀሩ ስደተኞችን ይመለከታል፡፡ ብዙ ጊዜ ጎላ ብሎ ሊነገር የሚችለው የመክዳት ዜና በከፍተኛ ባለሥልጣን ደረጃ በመሆኑ ወሬው አየር አይሞላ ሆኖ እንጂ፣ በኤክስፐርትና በአማካሪ ደረጃ በተለይ ወደ አውሮፓና አሜሪካ ወጥተው ያልተመለሱ ኢትዮጵያዊያን ቁጥራቸው ትንሽ አይደለም፡፡ እዚህም ላይ እውን የተሻለ ገቢ ከመፈለግ ብቻ ነው ወይስ በሥርዓቱ ላይ የማኩረፍና ነፃነትን የመፈለግ የሚለውን አንባቢያን ሊመረምሩት ይችላሉ፡፡

‹‹የከዱ የመንግሥት ኃላፊዎች››  በተመለከተ ከአገር ወጥተው ያልተመለሱትን ለመጠቃቀስ ያህል ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳዳር ብቻ ባለፉት አምስት ዓመታት 12 ሙያተኞችና የሥራ ኃላፊዎች መጥፋታቸውን መረጃዎች ያስረዳሉ፡፡ በዝርዝር ለማየት ከአዲስ አበባ መገናኛ ብዙኃን ኮፐን ሀገን 1፣ ደቡብ አፍሪካ 1፣ ኮሪያ ዴጉ 2፣ አሜሪካ 3 ሰዎች እንደወጡ ቀርተዋል፡፡ ከእነዚህ ውስጥ አብዛኛዎቹ ጋዜጠኞች ሲሆኑ የመንግሥት ካሜራዎችና መሰል ንብረቶችን ይዘው ተሰውረዋል፡፡ አሜሪካ ሄዶ የቀረ አንድ የቴክኖሎጂ መምርያ ባለሥልጣንም በሚሊዮኖች የሚቆጠር ገንዘብ የወጣባቸው የተለያዩ ንብረቶችን ሳያስረክብ መጥፋቱን  ከዚህ ቀደም በዚሁ ጋዜጣ ላይ አንድ አስተያየት ሰጪ ጽፈው ተመልክተናል፡፡

ውስጥ አዋቂዎች እንደሚሉት ከቀድሞ የአዲስ አበባ ከንቲባ ጋር ወደ ጀርመን በርሊን ለጉብኝት ከሄዱ አማካሪዎች መካከል ሁለቱ (አንዱ የትራንስፖርት ቢሮ ምክትል ኃላፊ) መቅረታቸው ካቢኔውን ያስደነገጠ ነበር፡፡ ሰንበት ብሎ የከተማው ምክትል ከንቲባ የነበሩ ሰው ዘለው አሜሪካ ገብተዋል፡፡ እኚህ የብአዴን ማዕከላዊ ኮሚቴ ደረጃ ላይ የደረሱ አንጋፋ ባለሥልጣን በኢትዮጵያ የጋዜጠኝነትና ማስታወቂያ መሥሪያ ቤቶች ከሚጠቀሱ ሙያተኞች በግንባር ቀደምነት የሚጠቀሱ እንደነበሩ ብዙዎች ይናገሩላቸዋል፡፡ በኋላ ከምክትል ከንቲባነት ወደ አማካሪነት ዝቅ ተደርገው የነበረ ቢሆንም አገር ጥለው ኮብልዋል፡፡

አገር ጥሎ የመሰደድ (በተለይ ለሥራም ሆነ ለሥልጠና እንደወጡ መቅረት) በክልሎችም ይታያል፡፡ በተለይ በአማራና በኦሮሚያ ክልሎች፡፡ በፌዴራል ደረጃም ከቅርብ ጊዜዎቹ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ልዩ ረዳት አሜሪካ መቅረት፣ የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባዔን ተከትለው ጀርመን አገር የተጓዙ ሁለት ሙያተኞች በተከታታይ መሰወር ለአብነት ይጠቀሳሉ፡፡

ታዲያ ‹‹ቀደም ባሉት ጊዜያት የክልል ርዕሰ መስተዳድሮች፣ ሚኒስትሮችና ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ካልተስማማቸው ወይም በሙስና የሚጠረጠሩ ይከዱ የለ? ምን አዲስ ነገር አለው?›› የሚል ጥያቄ የምታነሱ አንባቢያን ትኖራላችሁ፡፡ ልክ ነው መኮብለል ያለና የነበረ ነው፡፡ ነገር ግን ታማኝ ተብሎ፣ ሊጠቀም እንደሚችል ግንዛቤ ተይዞበት ሲሰጥ ከቀረ እንደ አገር በጥልቀት መፈተሽ ያለበት ፖለቲካዊም ሆነ ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ አለ፡፡

በእርግጥ አገራችን በእነኤርትራ ደረጃ ሕዝብ የሚሰደድባት አይደለችም፡፡ በስፖርት፣ በስብሰባም ሆነ በፐብሊክ ዲፕሎማሲ ተልዕኮ የትም ሄደው በፍቅር ወደ አገራቸው የሚመለሱ የመንግሥትና የሕዝብ ተወካዮች ብዙ ናቸው፡፡ ይሁንና ለትምህርትና ለሥልጠና በተለይ ከዩኒቨርሲቲዎቹ ተልከው አሁንም በአውሮፓና አሜሪካ ኑሯቸውን እያደረጉ የቀሩ ዜጎች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መምጣት ‹‹መላው ምንድነው?›› ሊባል ይገባል፡፡ በስም እከሌ እየተባሉ የሚጠቀሱ ባለሥልጣናት የት ናቸው ብንል መልሱ ከድተዋል ወይም ተሰደዋል ነው፡፡

በመካከለኛ ደረጃ ላይ ያለውም ልቡ ደጅ እያየ ነው

በቅርቡ ማኪያቶ እየጠጣን በስደት ጉዳይ ጨዋታ ያነሳልኝ ወዳጄ አነጋገር የአቋም ለውጥ አይቼበታለሁ፡፡ ከዚህ ቀደም በአገራችን እየሠራን ሸክሜንም ሆነ ደስታዬን በጋራ መካፈል አለብን የሚለው ይህ ሰው ‹‹ከኬኩም ሆነ ከደረቁ ቂጣ የየራሳችን ድርሻ›› በማለት ነበር ሐሳቡን የሚገልጸው፡፡ በዚህ እምነትም ከምንም ተነስቶ ጥረት በማድረግ ራሱንና ቤተሰቡን ለማስተዳደር መሞከሩን አይተናል፡፡ በሞራልና በሥነ ምግባር ረገድ ካለው ልዕልና አንፃርም አገር ግንባታውን ዘወትር የሚረሳ አልነበረም፡፡

አሁን ግን ልቡ ተሰዶ፣ እግሩ ከአገሩ ተነቅሎ፣ ቀልቡ አለመረጋጋቱን አየሁት፡፡ ስደትን ‹‹የወቅቱ ትክክለኛ አማራጭ›› ሲል የሚያስረዳበት ምክንያት ዳግም በቀደሚነት የገቢ ግብር ሥርዓቱ ነው፡፡ ይኼ ወዳጄ ዘመናዊ የወንዶች ፀጉር ቤቱ በኤሌክትሪክ መቆራረጥ ምክንያት ሥራ ስለፈታበት ሲበሳጭና ሥራው ሲበደል ነው የከረመው፡፡ አንዳንዴም በሩን ሳይከፍት፣ ‹‹ቶንዶሱን›› ሳይለኩስ ውሎ ቤት ኪራይ ሲከፍል ቆይቷል፡፡ ይሁንና ሰኔ መጥቶ የግብር ክፍያን በመክፈል የዜግነት ግዴታውን ለመወጣት ወደ ገቢዎችና ጉምሩክ መሥሪያ ቤት ሲሄድ ከስንት ውጣ ውረድ በኋላ ፍጹም ያልገመተው ክፍያ ተጣለበት፡፡ ‹‹የዕዳ ናዳ ወረደብኝ›› ሲል ይገልጸዋል፡፡

አስገራሚው ነገር እሱ በሚሠራበት የኦሮሚያ ክልል ፊንፊኔ ዙርያ ልዩ ዞን ባሉ ወረዳዎች (ሱሉልታ፣ ፉሪ፣ ሰበታ፣ ቡራዩ፣ ለገጣፎ) በኢፍትሐዊ መንገድ ትልቅ ሥራ ሠርተው ዝቅተኛ ግብር የሚከፍሉ አሉ፡፡ በትውውቅና በጥቅማጥቅም ይባል በሙስና የሕዝብ ድርሻ የሚቀሽቡ እንዳሉም አይቷል፡፡ ፈቃድ ሳያወጡ ሥራ የሚሠሩ ጭምር ሳይነሱ እንደፈለጉ ሲሆኑ ታዝቢያለሁ ይላል፡፡ ይሁንና እርሱ በቅንነት ከሠራውና ከትክክለኛ ገቢው የመንግሥት ድርሻ ለመስጠት ቢያስብም፣ ያልሠራበትን እንዲከፍል መገደዱ  ወደ ውጭ እንዲያማተር አድርጎታል፡፡

በዚህ ላይ በአገሪቱ አሁን በተጨባጭ ያለው የኑሮ ውድነት በአገር ውስጥ ሠርቶ በዝቅተኛ ገቢ ለመቋቋም (ሰርቫይቭ ለማድረግ) የሚቻል አይደለም ባይ ነው፡፡ የቤት ኪራይ፣ ትራንስፖርት፣ አልባሳትና ትምህርት (አቅምን ለማሻሻል) እያሰቡ በመኖር እንኳንስ ቤት መሥርቶና ልጅ ወልዶ ለመኖር፣ ስንቅ ለመጨበጥ ሊሞከር በመካከለኛ ደረጃ ውሎ ማደርም ከባድ ሆኗል ባይ ነው፡፡

እነዚህ የአንድ ሰው የሚመስሉ ዕይታዎች የሚናቁ አይደሉም፡፡ ወይም የብዙዎች አመለካከቶች አይደሉም ለማለት ያዳግታል፡፡ ከወራት በፊት አይኤስ በተባለው ሽብርተኛ ቡድን አንገታቸው የተቀላው ኢትዮጵያዊያን ሁኔታ የሚያሳዝን ቢሆንም፣ ይኼም ቢሆን ከመሰደድ አንቀርም ያሉ የከተማ ልጆች ያነሷቸው ችግሮች ነበሩ፡፡ ሥራ የለም፣ የሚፈጠረው የሥራ ዕድል የጉልበት ብቻ ነው፣ ገቢው በቂ አይደለም፣ ቤትና መኖሪያ አጣን፣ ቤተሰቦቻችን ከድህነት አልወጡም፣ ተመርቀን ቁጭ አልን፣ ወዘተ…የሚሉ ወጣቶች ድምፅ ተሰምቷል፡፡

በአገሪቱ በተለይ በአንዳንድ ክልሎች እንደ ልብ ተንቀሳቅሶ መሥራት አልቻልንም የሚሉም ነበሩ፡፡ ይኼ ጉዳይ ከፌዴራል ሥርዓቱ ጋር በተያያዘ በተለይ በሌላ ክልል የተወለዱ ዜጎችን የመግፋት ክስተት ታይቷል፡፡ በሕገ መንግሥቱ የሰፈረው የዜጎች በየትም የአገሪቱ ክልል የመዘዋወርና ሀብት የማፍራት መብት ሲጣስ ታይቷል፡፡ መንግሥት በሚፈጥራቸው የሥራ ዕድሎች እንኳን ተደራጅተው፣ መሥሪያና ማምረቻ አግኝተው ብድር ተመቻችቶላቸው ለመሥራት ያልቻሉም ነበሩ፡፡ ይህ እንግዲህ መሬት ላይ ያለው ሀቅ ከመሆኑ ባሻገር ወደ ስደት የሚገፋቸው ዜጎች በርከት እያሉ እንደሚመጡ አመላካች ነው፡፡

የአገራችን ታዳጊ ኢኮኖሚ ሊያረካው የሚችለው ሕዝብ ቁጥር ውስን ሊሆን እንደሚችል ግልጽ ነው፡፡ ያም ሆኖ ከሙስና የፀዳ፣ ፍትሐዊነትን የተላበሰና የሁሉንም ተሳትፎ የሚሸከም ከሆነ ቢያነስ በአስቸጋሪ ሁኔታ የሚሰደደው ወጣት ቁጥሩ ሊቀንስ ይችላል፡፡ መረጃዎች እንደሚያመለክቱት ባለፉት አምስት ዓመታት (የመጀመርያው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ) እንደ አገር በዋናነት በኮንስትራክሽን ዘርፍ ሆኖ በጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዝ ልማት ለስምንት ሚሊዮን ዜጎች የሥራ ዕድል መፈጠሩን መንግሥት ይፋ አድርጓል፡፡ ይህ አኃዝ በዕቅዱ ከተያዘው አንፃር ከእጥፍ በላይ ነው፡፡ ይሁንና ሰፊ ቁጥር ካላቸው ክልሎች አንፃር ሲታይ ድርሻቸው ደካማ ሆኖ ይታያል፡፡ 34 ሚሊዮን ሕዝብ ያለው የአማራ ክልል 1.6 ሚሊዮን የሥራ ዕድል ሲፈጠርበት 37 ሚሊዮን ሕዝብ ያለው ኦሮሚያ ደግሞ ሁለት ሚሊዮን የሥራ ዕድል ፈጥሯል ይላል መረጃው፡፡

በዚህ መነሻ ዛሬ ዋነኛው ከገጠር ወደ ከተማ የሚካሄድ ፍልሰትና ሕገወጥ ስደት እየበዛ የለው በእነዚህ አካባቢዎች ሆኗል፡፡ በእርግጥ ደቡብና ትግራይ ክልሎችም ከዚህ ችግር ነፃ አይደሉም፡፡ ስለዚህ የተጀመረው የኢኮኖሚ ለውጥና ዕድገት በተለይ ወጣቱን በእናት ምድሩ የሚቆይ፣ ከአገር ተሰዶ ባልተመቻቸና ትርፋማ ባልሆነ ሁኔታ በሰው አገር የሚኖረውንም የሚታደግ ሊሆን ይገባዋል፡፡

ዴሞክራሲና መልካም አስተዳደር ካልተሟላ ስደት አይቀርም

በዚች አገር እየመጣ ያለው የተሻለ ነገር በምንም መለኪያ ካለፉት ፀረ ዴሞክራሲያዊና ኋላ ቀር ሥርዓቶች ጋር የሚወዳዳር አይደለም፡፡ ‹‹በዚህ አገር ማድረግ አይደለም ማሰብ አይቻልም ነበር፡፡ አምስት ሆኖ በጋራ መጫወት ያሳስራል፡፡ የተከለከለ ጽሑፍ ማንበብ ያስገድላል…›› እያሉ የቅርብም ቢሆን የጨለማውን ዘመን በማውሳት ዛሬ ‹‹ገነት›› ማድረግ አይጠቅመንም፡፡ በዚያው ልክ ዛሬ ያለውን በጎ ጅምርና ተስፋ ሰጪ ሁኔታ ዓይንን ጨፍኖ ጥላሽት መቀባት ማንንም ሊጠቅም አይችልም፡፡

ከዚያ ይልቅ ዓለም የደረሰበትን፣ የሕዝቡን ፍላጎትና የሰብዓዊና የዴሞክራሲያዊ መብቶችን በመመርመር ጉድለቱን ለመሙላት መታገል ይስፈልጋል፡፡ ‹‹በቅድሚያ ዳቦ እንብላ›› በሚል አጉል ፈሊጥ የዴሞክራሲ ጥያቄን መግፋት ቢያንስ የዴሞክራሲ ኃይሎችን ያስበረግጋል፡፡ እዚህ ላይ መነሳት ያለበት ተጨባጭ ነገር አለ፡፡

ከላይ ከተጠቀሰው በመንግሥት በተፈጠረ ዕድል ከሚጠፋው ባልተናነስ በራሱ ሕጋዊና ሕገወጥ መንገድ ከአገር ውጭ የሚኮበልለው አንድ መነሻ ፖለቲካዊ አንድምታ እንዳይኖር መፈተሽ ያስፈልጋል፡፡ በአገር ውስጥ አገዛዙን (መንግሥትን) መደገፉ አልያም ተቃውሞ (ጠላት መሆን) የሚል ጫፍና ጫፍ ላይ መቆም ዝንባሌ ሊኖር አይገባም፡፡ በሕግና ሥርዓት የሚመሩ ፕሬሶች፣ የተጠናከርና በነፃነት የተደራጁ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ የአባላትን ዴሞክራሲያዊ ተሳትፎ የሚተገብሩ ማኅበራትና ለሕዝብ ጥቅም የሚሠሩ የመንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችም ያስፈልጋሉ፡፡

መንግሥትና ራሱ መንግሥታዊ መዋቅሮቹ ለሕዝብ ተጠሪ የሆኑ፣ ግልጽነትና ተጠያቂነትን የተላበሱ መሆን አለባቸው፡፡ የዴሞክራሲያዊ ተቋማት (ምክር ቤቶች፣ የሰብዓዊ መብት ተቋማትና፣ እንባ ጠባቂና ሌሎችም) የሚታመኑና ገልለተኛ ሊሆኑም ግድ ነው፡፡ እንደ ምርጫ ቦርድ፣ የመንግሥት መገናኛ ብዙኃን፣ የሃይማኖት ተቋማትና የትምህርት ተቋማትም ከአንድ ወገን አገልጋይነት ወጥተው ሁሉንም በእኩልነት የሚዳኙና የሚያቅፉ የወል ሀብት ሊሆኑ ግድ ይላል፡፡

ይህ ሳይሆን ቀርቶ ዴሞክራሲን ለመገንባትም ሆነ መልካም አስተዳደርን ለማስፈን መሞከር በአንድ እጅ ማጨብጨብ መሆኑ አይቀርም፡፡ አንዱን የሕዝብ ክፍል ማስከፋትና ማሽሽ ብቻ ሳይሆን ሌላኛውን መጥቀምና ማገዝም መፈጠሩ አይቀርም፡፡ እዚህ ላይ እንደ ፍርድ  ቤቶች፣ የፀጥታ ኃይሉ (ፖሊስ፣ መከላከያና ደኅንነት) እንደ ሕዝብ ዋስትናና የሕግ የበላይነት ጃንጥላዎች አድርጎ ማየት ይገባል፡፡

እስካሁን ባለው ሒደት እንደ አገር በጣም የከፋ የሰብዓዊም ሆነ የዴሞክራሲ መብት ጥሰት ባይፈጠርም፣ በፖለቲካ ዕምነታቸው የተገፉ (የታሰሩም ሆነ የሰደዱ) የሉም ማለት ያዳግዳታል፡፡ ከፕሬስ ነፃነት ጋር በተያያዘ በመንግሥትም ሆነ በራሱ ባነሳው በግሉ ፕሬስ መካከል በተፈጠረ ባላንጣነት የታሰሩ፣ የተሰደዱና ብዕራቸውን ሰቅለው ጎመን በጤና ብለው ቁጭ ያለ የሉም ማለትም ራስን ማታለል ነው፡፡ ከተነሳንበት ጭብጥ አንፃር ቁጥራቸው ትንሽም ሆነ ብዙ በዴሞክራሲያዊ ሥርዓት መጓደልና ተሳታፊነት መጥበብ የተሰደዱ እንዳይኖሩ መፈተሽ ተገቢ ነው፡፡

በቅርቡ የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ በኢትዮጵያ ጉብኝት ባደረጉበት ወቅት ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ “ዴሞክራሲያችን ለጋ ዕድሜ ያለውና ከረጅም ፀረ ዴሞክራሲያዊ ሒደት በኋላ የመጣ እንደመሆኑ ችግር የለውም ሊባል አይችልም፡፡ ጉዳዩ የህልውና በመሆኑ ግን ሒደቱን ለማሻሻል ዝግጁ ነን፡፡ እናንተም ልታግዙን ይገባል…” ባሉበት ቀና ሁኔታ ውስጥን መፈተሽ፣ ተቃዋሚዎችንና የተለየ አቋም ያላቸውን ወገኖች እንደ ሕዝብ ቆጥሮ ማዳመጥ፣ እንዲሁም ጉድለት የተባለን ከየትኛውም ወገን የሚነሳ ክስተት ማረም ከተቻለ ያለ ጥርጥር ሁለንተናዊ ለውጥ ይመጣል፡፡ አገራዊ ስሜትም ይበልጥ ይጎመራል፡፡ ስደቱም ይቀንስ ዘንድ ተጨማሪ አቅም ይፈጠራል፡፡

በቅርቡ ከኦሮሚያ ክልል ወደ ውጭ የወጡትም ሆነ ከሌላው ክልል ተሰደው በውጭ አገር የኖሩ የዳያስፖራ አባላት ወደ ኢትዮጵያ መምጣታቸውን አይተናል፡፡ የእነዚህ ወገኖች መምጣት መንግሥት ለትራንስፖርትና በአገር ቤት ለመስተንግዶ ወጪ ያወጣበት ጉዳይም ቢሆንም ፖለቲካዊ ትርፍ አለው፡፡ በአንድ በኩል ከአገር  በመውጣቱ የአገሩን ጉዳይ እርግፍ አድርጎ በመተው የባዕድነት ስሜት የተሰማውን ዞር ብሎ እንዲያስብ ያደርጋል፡፡ በሌላ በኩል በአመለካከት የትኛውም ዓይነት ልዩነት ቢኖርም በአገር ጉዳይ አንድ የመሆን ብሔራዊ መግባባትን ያሳድጋል፡፡

በውጭ የሚኖሩ ዜጎች (ዳያስፖራዎች) ወደ አገር ቤት መጥተው እናልማ፣ ዜጎችን እንርዳ ወይም እናሠልጥንና ቴክኖሎጂ እናሸጋገር ካሉም ትልቅ ኢኮኖሚያዊ ትርፍ ነው፡፡ እንደ አገር በሕጋዊ መንገድ አዋጭነት ያለውን ስደት ሳንገድብ፣ በሕገወጡ ድርጊትና በዜጎች ስቃይ ላይ ብቻ የተባበረ ክንዳችንን እናንሳ፡፡ ሕገወጥ ስደትን ለመቀነስም ሆነ ለማስቆም በሆደ ሰፊነት ዙርያ መለስ ምልከታና ዘላቂ መፍትሔ ማስቀመጥ ይጠቅማል የስደተ ነገር ሲነሳ እውነታው በፍፁም ወደ ጎን መገፋት የለበትም፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊዋን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡ 

 

 

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

አስጨናቂው የኑሮ ውድነት ወዴት እያመራ ነው?

ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ የኑሮ ውድነት እንደ አገር ከባድ ፈተና...

‹‹ወላድ ላማቸውን አርደው ከደኸዩት ወንድማማቾች›› ሁሉም ይማር

በንጉሥ ወዳጅነው   የዕለቱን ጽሑፍ በአንድ አንጋፋ አባት ወግ ልጀምር፡፡ ‹‹የአንድ...

የመጋቢቱ ለውጥና ፈተናዎቹ

በታደሰ ሻንቆ ሀ) ችኩሎችና ገታሮች፣ መፈናቀልና ሞትን ያነገሡበት ጊዜ እላይ ...

ጥራት ያለው አገልግሎት መስጠት የሚያስችል ሥርዓት ሳይዘረጉ አገልግሎት ለመስጠት መነሳት ስህተት ነው!

በተለያዩ የመንግሥትና የግል ተቋማት ውስጥ ተገልጋዮች በከፈሉት ልክ የሚፈልጉትን...