አቶ ፈጠነ ተሾመ፣ የብሔራዊ ሚቲዎሮሎጂ ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር
በኢትዮጵያ የሚቲዎሮሎጂ አገልግሎት ጅማሮ ከሚሲዮናውያን ጋር የተያያዘ ነው፡፡ ለማሲዮናዊን ብቻ ታስቦ ይሰጥ የነበረው አገልግሎት ቀስ በቀስ ወደ መንግሥታዊ ተቋማት መሸጋገሩም ይነገራል፡፡ በመንግሥት መዋቅር ውስጥ የሚቲዎሮሎጂ አገልግሎት የሚሰጥ አንድ ዘርፍ በኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ሥር ተደራጅቶ ሲሠራ ነበር፡፡ በአቪዬሽን ሥር የነበረውም የሚቲዎሮሎጂ ዘርፍ ለአየር በረራ የሚያገለግል መረጃ በመስጠት ላይ ብቻ የተወሰነ ነበር፡፡ ከ1973 ዓ.ም. በኋላ ግን ራሱን ችሎ እንዲሠራ በወጣ አዋጅ ተጠሪነቱ ለውኃ ሀብት ሚኒስቴር ሆኖ የብሔራዊ ሚቲዎሮሎጂ አገልግሎት ድርጅት በሚል ስያሜ ወደ ሥራ ገባ፡፡ በዚህ ደረጃ መቋቋሙም ከዚህ ቀደም ለአቪዬሽን ብቻ ይሰጥ የነበረውን አገልግሎት በማስፋት ለውኃ፣ ለግብርና፣ ለቱሪዝም፣ ለኢነርጂ፣ ለስፖርትና ለመሳሰሉት ዘርፎች ሁሉ አገልግሎት እንዲሰጥ ተደርጓል፡፡ በተለይ በአሁኑ ወቅት ከአየር ንብረት ለውጥ ጋር በተያያዘ ያሉ መረጃዎችን በማጠናቀር እየሠራም ይገኛል፡፡ ሰሞኑን በተለያዩ አቅጣጫዎች እንደተሰማው የዘንድሮ የክረምት ወቅት ደረቃማ ሆኗል፡፡ የዝናብ እጥረት ተፈጥሯል፡፡ ይህም አብዛኛውን የአገሪቱ ክፍሎች አዳርሷል፡፡ እንደ አፋር ክልል ባሉ አካባቢዎች ለእንስሳት ሞት ሞክንያት ሆኗል፡፡ በሌሎች አካባቢዎችም ሰብል በማውደም የዘር ጊዜን አዛብቷል፡፡ የዝናብ እጥረቱ የተለያዩ ተፅዕኖዎችን እያሳደረ በመምጣቱ ወደፊትም የሚያስከትላቸው ችግሮች እንደሚኖሩ ይገመታል፡፡ የአየር ንብረት ለውጡን በተመለከተ ቅድመ መረጃ መስጠት ያለበት ደግሞ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ሚቲዎሮሎጂ ኤጀንሲ ነው፡፡ ከዚህ አንፃር በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ዳዊት ታዬ የኤጀንሲውን ዋና ዳይሬክተር አቶ ፈጠነ ተሾመን አነጋግሯል፡፡
ሪፖርተር፡- በአሁኑ ጊዜ በመላ አገሪቱ ምን ያህል የሚትዎሮሎጂ መረጃ መሰብሰቢያ ማዕከላት አሉዋችሁ?
አቶ ፈጠነ፡- በሁሉም ክልሎች ቅርንጫፎች አሉን፡፡ እንዲያውም በአንዳንድ ክልሎች ሁለትና ሦስት ቅርንጫፎች ከፍተን እንሠራለን፡፡ በዳይሬክቶሬት ደረጃ የተዋቀሩት ቅርንጫፎቻችን ደግሞ የክልል መንግሥታትን ጭምር ያማክላሉ፡፡ ለየአካባቢው ነዋሪዎች መረጃ ይሰጣሉ፡፡ ከዚህ ሌላ በእያንዳንዱ ቅርንጫፍ ዳይሬክቶሬት ሥር ከ100 እስከ 150 የሚደርሱ ጣቢያዎች አሉን፡፡ በአጠቃላይ በመላው ኢትዮጵያ ከ1,200 በላይ የሚቲዎሮሎጂ ጣቢያዎች ይዘን እየተንቀሳቀስን ነው፡፡
ሪፖርተር፡- ሁሉም ጣቢያዎቻችሁ መረጃ መሰብሰቢያዎች ናቸው?
አቶ ፈጠነ፡- አዎ መረጃ መሰብሰቢያዎች ናቸው፡፡ ጣቢያዎቹ ግን የተለያየ ደረጃ ያላቸው ናቸው፡፡ ከአንድ እስከ አራት ደረጃ ያላቸው ሲሆኑ፣ ለምሳሌ በአራተኛ ደረጃ ያስቀመጥናቸው ጣቢያዎቻችን የዝናብ መጠንን ብቻ የሚመዘግቡ ናቸው፡፡ ሁለተኛ ደረጃ ጣቢያዎች ደግሞ የዝናብ መጠንን፣ የሙቀት መጠንን፣ ከፍተኛና ዝቅተኛ የዝናብና የአየር ፀባይን በመመዝገብ መረጃ የሚሰጡ ናቸው፡፡ ሁለተኛ ደረጃ የሰጠናቸው ጣቢያዎችም የዝናብና የሙቀት መጠንን ከመለካትም በላይ ለግብርና ዘርፍ የሚያገለግሉ ሌሎች መረጃዎችን የሚመዘግቡ ናቸው፡፡ ለምሳሌ የአፈር ሙቀትንና የንፋስ ፍጥነትን ጭምር የሚመዘግቡ ናቸው፡፡ በአንደኛ ደረጃ የተደራጀና ‘ሲኖክቲክ’ የምንላቸው 17 ጣቢያዎቻችን ደግሞ የተለያዩ የሚቲዎሮሎጂ መረጃዎችን በማጠናከር በዓለም አቀፍ ደረጃ የማሰራጨት አቅም ያላቸው ናቸው፡፡ በእኛ አሠራር በእነዚህ ጣቢያዎች የሚሰበሰቡ መረጃዎች ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆኑ፣ ለሌሎች የውጭ ተቋማት አገልግሎት የሚሰጡ ጭምር ናቸው፡፡ በዓለም አቀፍ መሥፈርት መሠረት በቀን አምስት ጊዜ ‘ኦቭዘርቬሽን’ ይወሰዳል፡፡ ጠዋት በ12 ሰዓት፣ ረፋድ በሦስት ሰዓት፣ ቀን በስድስት ሰዓትና ምሽት በ12 ሰዓት ‘ኦቭዘርቬሽን ይወሰዳል፡፡ ይህንን መረጃ ለዓለም ሚቲዎሮሎጂ ድርጅቶችና የዓለም ሚቲዎሮሎጂ ድርጅት ላቋቋሟቸው የትንበያ ማዕከላት ይሰጣል፡፡
ለምሳሌ የኢጋድ “ክላይሜንት ፕሪዲክሸን ሴንተር” ለሚባለው ተቋም ጭምር እንሰጣለን፡፡ ከ17ቱ ትላልቅ ጣቢያዎቻችን የሚሰበሰበው መረጃ ለዓለም ይደርሳል፡፡ እንደ ቢቢሲ ያሉት ሚዲያዎች የኢትዮጵያን ትንበያ የሚያስቀምጡት ከ17ቱ ጣቢያዎች የተገኘውን መረጃ በመጠቀም ነው፡፡ የሚቲዎሮሎጂ መረጃዎቹን በፍጥነትና በዘመነ መንገድ ለማደራጀትም ሰው አልባ የሚቲዎሮሎጂ የመረጃ የቴክኖሎጂ መሣሪያዎችን እየተከተልን ነው፡፡ ከዚህ ቀደም አውቶማቲክ የነበረው የመረጃ ማዕከል በኤርፖርት ብቻ ነበር፡፡ አሁን ግን ይህንን መሣሪያ በመላ አገሪቱ እየተከለ ነው፡፡ ይህ ዘመናዊ የሚቲዎሮሎጂ መረጃ መቀበያ መሣሪያ ከየጣቢያው ያለውን መረጃ በመሰብሰብ በ15 ደቂቃ ለማዕከል ይለካል፡፡ የእነዚህ መሣሪያዎች ቁጥር 160 ደርሷል፡፡
ሪፖርተር፡- ከመላ አገሪቱ የሚሰበሰቡትን የሚቲዎሮሎጂ መረጃዎች ምን ያህል ጥቅም ላይ እያዋላችሁ ነው?
አቶ ፈጠነ፡- ጥቅማቸው በተለያየ መንገድ ሊገለጽ ይችላል፡፡ ለምርምር ሥራዎች ይጠቅማሉ፡፡ የአየር ንብረት ለውጡ እንዴት እየሄደ ነው? የሚለውንም ለማየት ያስችላሉ፡፡ ታሪካዊ መረጃዎቹ የነገንም ሒደት በምርምር ያመላክታሉ፡፡
ሪፖርተር፡- እዚህ ላይ ግን እስካሁን የተሰበሰቡ መረጃዎች የኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥ ምን ገጽታ እየያዘ መሆኑን ያሳያሉ? የአየር ንብረት ለውጥ እየታየ በመሆኑ ይህ የአየር ንብረት ለውጥ እንዴት ሊገለጽ ይችላል?
አቶ ፈጠነ፡- የአየር ንብረት ለውጥ ከየአገሮቹ ክንዋኔ ጋር ይያያዛል፡፡ የአየር ንብረት ለውጥን መግታት ይቻላል፡፡ የአየር ንብረት ለውጡን መግታት የሚቻልባቸው ሁኔታዎችም አሉ፡፡ ለምሳሌ በእኛ አገር እየተሠራባቸው ያሉ የተፋሰስ ጥበቃዎች እየተጠናከሩ ከሄዱ የአየር ንብረት ለውጡን ለመግታት አቅም ይኖረናል፡፡ ብዙ ጊዜ የአየር ንብረት ለውጥ ከሚመጣባቸው ምክንያቶች አንዱ የኢንዱስትሪዎች መስፋፋት ነው፡፡ ከኢንዱስትሪ የሚለቀቁት በካይ ጋዞች እየሰፉ ሲሄዱ ብክለት ይከሰታል፡፡ ከተሞች አካባቢም የተሽከርካሪዎች ጭስ አየሩን እየበከለ ይሄዳል፡፡ የመሬት መራቆትና የመሳሰሉት ለአየር ለውጥ የየራሳቸውን አስተዋጽኦ ያበረክታሉ፡፡ ከዚህ አኳያ የተፋሰስ ልማቱ ከተካሄደ ግን ኢንዱስትሪ ቢስፋፋ እንኳን ከኢንዱስትሪ የሚወጣውን ጢስ የሚመጥ ይሆናል፡፡ ዓለም ሲነካ ኢትዮጵያ አትነካም ማለት ባይቻልም፣ የተፋሰስ ልማቱ ግን ተፅዕኖውን መቀነስ ይችላል፡፡ የአየር ንብረቱን ሙሉ ሙሉ ለሙሉ መቆጣጠር ይቻላል ማለት ግን አይደለም፡፡
ሪፖርተር፡- የተፋሰስ ልማቱ የሚካሄድ ከሆነ በእርግጥ የሚፈጠረውን የአየር ንብረት ለውጥ መቋቋም ይቻላል?
አቶ ፈጠነ፡- ሙሉ በሙሉ ማስቀረት ባይቻልም መቀነስ ይቻላል፡፡ የኢትዮጵያ መንግሥት ስትራቴጂውም ይህ ነው፡፡ ለአየር ለውጥ የማይበገር አረንጓዴ ኢኮኖሚን መተግበር ነው፡፡ በተለይ በቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር የተጀመረውን የአረንጓዴ ኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ካጠናከርን ችግሩን እንቀንሳለን፡፡ ቻይና ብትሄድ ኢንዱስትሪዎቻቸው በሚለቁት ጋዝ መንቀሳቀስ የማይቻልበት ሁኔታዎች የሚፈጠሩባቸው አጋጣሚዎች አሉ፡፡ በእኛ አገር ሁኔታ አልፎ አልፎ ከኢንዱስትሪዎች የሚወጣውን የካርቦን ልቀት መቆጣጠርና መምጠጥ የሚችሉ የደን ተከላዎች ከተካሄዱ፣ ይህንን ስትራቴጂ መተግበር እንችላለን፡፡
ሪፖርተር፡- አሁን አንድ ወቅታዊ ሁኔታ አለ፡፡ በዘንድሮ የክረምት ወቅት ከፍተኛ የሆነ የዝናብ እጥረት በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ተከስቷል፡፡ ይህም ችግር ይፈጥራል ተብሎ ተሰግቷል፡፡ ይህ የአየር ንብረት ለውጥ መነሻው ምንድነው? እስካሁን ያለው ሒደትስ ምን ይመስላል?
አቶ ፈጠነ፡- የዝናብ እጥረት በአንዳንድ የዓለም አገሮች ተከስቷል፡፡ ይህም ከፓስፊክ ውቅያኖስ እየሞቀ ከሚወጣው ኤልኒኖ ከሚባለው ክስተት ጋር የሚያያዝ ነው፡፡ የአየር ሁኔታው መዛባቱና የዝናብ እጥረቱ አልፎ አልፎ መከሰቱ በኤልኒኖ ክስተት ተፅዕኖ ሥር መሆናችንን የሚያሳይ ነው፡፡ ለምሳሌ ኢትዮጵያ የምታስተናግዳቸው ሦስት ወቅቶች አሉ፡፡ እነዚህ የበልግ፣ የክረምትና የበጋ ወቅቶች በየአራት ወራት የተከፈሉ ናቸው፡፡ ከሦስቱ ወቅቶች ውስጥ እኛ ክረምት ብለን የምንጠራው ከሰኔ እስከ መስከረም ያሉትን አራት ወራቶች ነው፡፡ ከመስከረም በኋላ ያለውን ደግሞ በጋ ነው የምንለው፡፡ ስለዚህ የወቅት ትንበያ የምንሰጠው በዚህ መርሃ ግብር መሠረት ነው፡፡ በዚህ ዓመት የክረምቱ አገባብ ደህና ተብሎ የሚታይ ነበር፡፡ በእኛ አገር ቀመር ክረምት የሚገባው በሰኔ ወር ነው፡፡ ከዚህ አንፃር የዘንድሮው የክረምት ወቅት የመጀመርያው የሰኔ ወር አሥር ቀናት ደህና የነበረው ዝናብ እየቀነሰ መጥቶ ሐምሌ ላይ ሙሉ ለሙሉ ተለውጦ የዝናብ እጥረት ተፈጠረ፡፡ አሁን ነሐሴ ላይ ያለው ሁኔታ ግን ጥሩ የሚባል ነው፡፡ እንዲህ ዓይነቱን የአየር ለውጥ የሚያመጣው ኤልኒኖ ነው፡፡ ኤልኒኖ ደግሞ በኢትዮጵያ ሲከሰት የመጀመሪያ ጊዜው አይደለም፡፡ በተለያዩ ዓመታት ይከሰታል፡፡ ለምሳሌ እ.ኤ.አ. በ1997 ተከስቷል፡፡ በ1977 ዓ.ም. በተመሳሳይ የተፈጠረ ችግር እንደነበር ይታወቃል፡፡ እንዲህ ባሉ በኤልኒኖ ዓመታት ውስጥ ድርቅ የሚሆንባቸው ጊዜያት ይኖራሉ፡፡ በ1977 ዓ.ም. በተከሰተው ኤልኒኖ በጣም ብዙ ሰው ነው የተጐዳው፡፡ ኤልኒኖ በተከሰተ ጊዜ ከፍተኛ ተፅዕኖ ሊያሳድር የሚችልበት ሁኔታ ይፈጠራል፡፡ የተፈጠረውን ተፅዕኖ ለመግታት ደግሞ እንደ አገሮቹ ጥንካሬ ይለያያል፡፡ ከእኛ አገር ሁኔታ የኤልኒኖ ክስተት መነሻው ከፓስፊክ ውቅያኖስ እየሞቀ ከመሄድ ጋር ተያይዞ ነው፡፡
ሪፖርተር፡- ዘንድሮ በክረምት ወቅት የተፈጠረው የዝናብ እጥረት ከዚህ ቀደም በኤልኒኖ ሰበብ ምክንያት ከተፈጠረው የድርቅ ወቅት ጋር ያለው ልዩነት ምን ያህል ነው? ዘንድሮ የክረምት ወቅት በምንላቸው ሁለት ተከታታይ ወራት የዝናብ እጥረት ተከስቷል፡፡ ይህ ያልተጠበቀው የአየር ፀባይ መዛባት ከቀድሞው ክስተት ጋር እንዴት ማነፃፀር ይቻላል?
አቶ ፈጠነ፡- በኤልኒኖ ክስተቶች ውስጥ ብዙ ልዩነት አይኖርም፡፡ መጠናቸው ሊለያይ ይችላል፡፡ ኤልኒኖ እየተጠናከረ ሲሄድ የበለጠ ድርቅ እየሆነ ይሄዳል፡፡ መካከለኛ ደረጃ ልንለው እንችላለን፡፡ ከፍተኛ ደረጃ ሲደርስ ድርቁ ከፍተኛ ነው ማለት ነው፡፡ በዚህ ደረጃ ነው የምናየው፡፡ ከዚህ ውጪ ግን ያለፈውን ሁኔታ ስናይ ልዩ የሚያደርገው የኅብረተሰቡ የለውጥ ደረጃ ከፍ ብሎ መገኘቱ ነው፡፡ በ1977 ዓ.ም. ውኃ ማቆር፣ ውኃ መያዝ የሚባሉት ነገሮች አልነበሩም፡፡ ስለዚህ ድርቁ በተከሰተ ቁጥር ሕዝቡ ወዲያው ይጎዳል፡፡ ዘንድሮ ግን ይህ የኤልኒኖ ክስተት እንደሚኖር እንደታወቀ ባለው መዋቅር ከሕዝቡና ከመንግሥት ጋር ሲሠራ ስለነበር ሕዝቡ ጠብ የሚለውን ውኃ ሲይዝ ነው የቆየው፡፡ በትግራይ ክልል በተጨባጭ የሆነው ይህ ነው፡፡ ችግሩ አልተሰከሰተም ማለት አይደለም፡፡ የሕዝቡ ውኃን የመያዝ አቅምና የመቆጣጠር አቅም አዳብሯል፡፡ ይህ ችግር እንዳለ ተገንዝቦም ጠብ የሚለውን ውኃ ይይዛል፡፡ የሚገኘውን ውኃ ከያዝክ አደጋው ይቀንሳል፡፡ ለምሳሌ ግድቦች አካባቢ ውኃዎች መያዝ ይኖርብሃል፡፡ ያለበለዚያ የኤሌክትሪክ ኃይል በፈረቃ መሆኑ አይቀርም፡፡ የውኃ እጥረቱ ስለሚኖር ግድቦች መያዝ የሚገባቸውን ያህል ውኃ ላይዙ ይችላሉ፡፡ ስለዚህ እንዲህ ያሉ ቅድመ መረጃዎች ካሉ ችግሩን ለመግታት ይቻላል፡፡ መረጃውን ተጠቅመን ዕርምጃ መውሰድም ይኖርብናል፡፡ ዕርምጃው ወይም መፍትሔው አለመዝራት አይደለም፡፡ አንድ ወር ችግር ፈጥሯል፡፡ አሁን ደግሞ ዝናቡ በአንፃራዊነት እየተሻሻለ በመሆኑ ከዚህ በኋላም በተወሰነ ደረጃ ጥሩ ስለሚሆን ይህንን ውኃ መጠቀም ያስፈልጋል፡፡ ኤልኒኖ የራሱ ጠባይ ያለው ቢሆንም፣ የዘንድሮ የኤልኒኖ ሁኔታ ከቀደመው ሰፊ ልዩነት የለውም፡፡ የተቀራረበና ተመሳሳይ ነው ማለት እንችላለን፡፡ እ.ኤ.አ. በ1997 ከታየው ኤልኒኖ ጋር ተመሳሳይ ነው፡፡ ነገር ግን ኅብረተሰቡ በአየር ለውጡ ላይ ያገኘው ግንዛቤ እየጨመረ ከመምጣቱ ጋር ተያይዞ ይህንን ተፅዕኖ የመግታት አቅም እየዳበረ መጥቷል፡፡
ሪፖርተር፡- ይህ ክስተት ለመኖሩ አርሶ አደሩና አርብቶ አደሩ ዘንድ በትክክል መረጃው ቀደም ብሎ ደርሷል ማለት ይቻላል? መሥሪያ ቤታችሁ ችግሩ እንዳለ ቀደም ብሎ መረጃ እንዳለው ቢገለጽም፣ ችግሩ ስለመኖሩ በይፋ የተናገራችሁት ግን ዘግይታችሁ ነው፡፡ ለምን?
አቶ ፈጠነ፡- እኛ መረጃውን በአግባቡ ሰጥተናል፡፡ ወቅታዊው ትንበያ ላይ ተወያይተናል፡፡ መረጃ ከመስጠትም በላይ ሄደናል፡፡ የሰጠነውም መረጃ አዲስ ነገር አይደለም፡፡ ስናደርግ የነበረውን ነገር ነው የሠራነው፡፡ ለምሳሌ ባለፈው ዓመት ሁሉም የትንበያ ማዕከላት የኤልኒኖ ክስነት ይኖራል ብለው ነው የደመደሙት፡፡ ዘንድሮ አይደለም የደመደሙት፡፡ አምና ነው፡፡ በ2007 ዓ.ም. መጀመሪያ ላይ የኤልኒኖ ክስተት ይኖራል ብለዋል፡፡ ብሔራዊ ሚቲዎሮሎጂ ኤጀንሲ በዚህ ላይ ብዙ ሠርቷል፡፡ ከግብርናና ከውኃ ዘርፍ ተቋማት ጋር ባለው መዋቅር ተገናኝቶ ሠርቷል፡፡ በእኛ አደረጃጀትም ባሉን በ1,200 ጣቢያዎች ከክልል የግብርና ቢሮዎች ጋር እንዲሠሩ ተደርጓል፡፡ በሁሉም ደረጃ ከመጀመሪያ ጀምሮ ስትራቴጂ ተነድፎ በቅንጅት ሲሠራ ቆይቷል፡፡ በእኛ በኩል መረጃዎች አንድም ቀን የዘገዩበት ጊዜያት አልነበሩም፡፡ በሚዲያ እንደተላለፈውም የኢሕአዴግ ሥራ አስፈጻሚ ጉዳዩን ሲገመግመው ነበር፡፡ የበልግ አወጣጥና የክረምት አገባቡን በተመለከተ ሰፊ ጊዜ ወስዶ ገምግሟል፡፡ ስለዚህ መረጃው የተያዘበት ሁኔታ አልነበረም፡፡ ግልጽ ነው፡፡ መንግሥትም ሕዝብም ያውቃል፡፡
ሪፖርተር፡- መረጃው ወደ ታች ስለመውረዱ አረጋግጣችኋል? ምን ያህል ጥቅም ላይ ውሏል?
አቶ ፈጠነ፡- የግብርና የልማት ሠራተኞች በየቀበሌው አሉ፡፡ አርሶ አደሩ ከእነርሱ ጋር እንዲሠራ መረጃው ወርዷል፡፡ በየደረጃው ያሉ የአመራር አካላትም ይህንን መረጃ ተቀብለው ወደ ታች እንዲያወርዱት ተደርጓል፡፡ ይህ የመጀመሪያ የአሠራር ሥርዓት ነው፡፡ ሌላው የመረጃ ዘዴ ደግሞ ሚዲያ ነው፡፡ በተለይ በተደራሽነት ሬዲዮና ጋዜጣ ብልጫ አላቸው፡፡ ቴሌቪዥን ውሱን ነው፡፡ በእርግጥ የቴሌቪዥን ተጠቃሚዎች እየተበራከቱ ከመምጣታቸው ጋር ተያይዞ አርሶ አደሩ ዘንድ ለመድረስ ይቻላል፡፡ ነገር ግን አርሶ አደሮች የበለጠ መረጃውን ሊያገኙ የሚችሉት ባለው አደረጃጀት አብረዋቸው በሚሠሩ የግብርና ባለሙያዎች ነው፡፡ ሚዲያ የማይተካ ሚና ስላለው በዚህም መሥራት ያስፈልጋል፡፡ እስካሁን ባለው ሒደት ግን በትክክል መረጃው ተሰጥቷል፡፡ በዚህ መረጃ መሠረትም መንግሥት አስፈላጊውን ዝግጅት እንዲያደርግ ተደርጓል፡፡ የግብርና ባለሙያዎች ድጋፍ ምን መምሰል እንዳለበት ሁሉ ተቀምጧል፡፡ በተለይ አሁን የሚታየውን ውኃ የመያዝ ሥራ እንዲያከናውን መረጃው ወርዷል፡፡ ጠብ ያለችውን ውኃ እንዲያዝ አርሶ አደሩ ላይ ሰፊ ሥራ ተሠርቷል፡፡ ይህም ሆኖ ግን መረጃው ሁሉንም ቤት አንኳኩቷል ተብሎ መደምደም አይቻልም፡፡ በተቻለ መጠን ግን መረጃው እንዲዳረስ ተደርጓል፡፡
ሪፖርተር፡- ይህም ቢሆን እስካሁን በታየው የዝናብ እጥረት ጉዳት ይኖራል ተብሎ ተሰግቷል፡፡ ይህ ጉዳት እንዴት ይገለጻል? በእርግጥ በዚህ ሰሞን የተሻለ የሚባል ዝናብ እየታየ ነው፡፡ ነገር ግን እኛ በተመለከትናቸው አንዳንድ አካባቢዎች ለምሳሌ በአርሲ ዞን በዶዶታ ወረዳ ውስጥ ብቻ ከ2,300 በላይ ሔክታር መሬት ላይ የተዘራ በቆሎ ጠፍቷል፡፡ ይህ ያለውን ችግር አንድ ማሳያ ይሆናል፡፡ እንዲህ ያሉ ክስተቶች የሚያስከትሉትን ጉዳት ለመቀነስ ምን መደረግ አለበት? ለተፈጠረው ወቅታዊ ችግር በብሔራዊ ደረጃ በተቋቋመው ኮሚቴ ውስጥ አላችሁበትና ችግሩን ለመከላከል ምን ታስቧል?
አቶ ፈጠነ፡- ጉዳቱን ከመቀነስ አኳያ የተለያዩ ሥራዎች እየተሠሩ ነው፡፡ ዋናው ኤልኒኖ ተከስቷል፡፡ ይህን መሸሸግ አይቻልም፡፡ ይኼንን ተላምዶ መኖር ነው፡፡ ይህ አይምጣ ማለት አይቻልም፡፡ በህንድ በተከሰተው ኤልኒኖ በሙቀት ብዙ ሰው አልቋል፡፡ በፓኪስታን ተመሳሳይ ነገር ነበር፡፡ ስለዚህ ችግሩ መምጣቱ እየታወቀ አልመጣም ማለት አትችልም፡፡ ዋናው ነገር ይህንን ችግር መግታት ነው፡፡ ችግሩን ከመግታት አኳያ መከናወን ያለባቸው ሥራዎች እየተሠሩ ነው፡፡ አሁን በጠቀስከው አካባቢ ችግሩ እንደተከሰተ ይታወቃል፡፡ አርሲና ስምጥ ሸለቆ አካባቢ ችግር እንዳለ የእኛም መረጃ ያሳያል፡፡ በእነዚህ አካባቢዎች የተቀናጀ ሥራ መሠራት እንዳለበት መረጃ ተሰጥቷል፡፡ ስለዚህ እዚህ አካባቢ በቆሎው ባይሳካ በአጫጭር ጊዜ የሚደርሱ ለምሳሌ ድንችን የመሳሰሉ ምርቶችን መትከል ይችላሉ፡፡ የተለያዩ የአትክልትና የፍራፍሬ ምርቶችን መጠቀም ይቻላል፡፡ ከዚህ ውጪ ስንዴ ላይ ብዙም ችግር የለም፡፡ ስንዴው እንደበቀለ ነው፡፡ አሁን ደግሞ ዝናብ እየዘነበ ስለሆነ ተፅዕኖው ይቀንሳል፡፡ እንዲህ ዓይነቱ ችግር በሁሉም ክልሎች አይደለም ያለው፡፡ ምዕራብ ሙሉ ለሙሉ ችግር አልነበረም፡፡ ምዕራብ ኦሮሚያን ብትወስድ ብዙ ችግር አልነበረም፡፡ ይኼ ችግር በአነስተኛ ሰዎች ላይ ሊታይ ይችላል፡፡ ይህንን ለመከላከል ደግሞ መንግሥት የራሱን ዝግጅት ያደርጋል፡፡ በዚህ ረገድ የአደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ቢሮ የሚሠራው ሥራ አለ፡፡ የእኛን መረጃ በመጠቀም እየሠሩ ነው፡፡ ሌሎቹም እንደ ግብርና፣ የውኃና ሌሎች ዘርፎችም በየራሳቸው መንገድ የሚሠሩት ሥራ አለ፡፡ ትልቁ ነገር ቅንጅት መኖሩ ነው፡፡ ይህ ችግር መኖሩን ሁሉም ያውቃል፡፡ ተዘጋጅተዋል፡፡ ለምሳሌ ከጤና አንፃር ከአየር ንብረት ለውጡ ጋር ተያይዘው የሚከሰቱ በሽታዎችን ለመከላከል ዝግጅቱ የተጠናቀቀ ይመስለኛል፡፡ ምክንያቱም ግልጽ ነው፡፡ እኛ ተፅዕኖውን የመጠቆም ሥራ ነው የምንሠራው፡፡ ፈጻሚ አካላት ደግሞ ስትራቴጂ ነድፈው ይሄዱበታል፡፡ ለመቆጣጠር የሚያስችል ሥራ ይሠራል፡፡
ሪፖርተር፡- አሁን የታየው የዝናብ መጠን ከቀድሞው ጋር ሲነፃፀር ምን ያህል ወርዷል ማለት ይቻላል? የዝናብ እጥረቱ ከምዕራብ አካባቢ ውጪ በሁሉም ክልሎች አንዳንድ ቦታዎች ላይ ነበር፡፡ ስለዚህ የዘንድሮው የዝናብ እጥረት ሽፋን ሰፊ ነው ማለት አይቻልም? ይህ አያሰጋም?
አቶ ፈጠነ፡- ስፋቱን በተመለከተ የተለያየ ነው፡፡ ለምሳሌ ሶማሌ ክልል አሁን የዝናብ ወቅት አይደለም፡፡ ሶማሌ በዚህ ወቅት የሚያገኘው ዝናብ ካነሰበት ከብቶቹ ሊጎዱ ስለሚችሉ ያንን ማየት ነው፡፡ ስለዚህ እዚያ አካባቢ ላይ ጠንካራ ዝናብ ይኖራል ተብሎ አይታሰብም፡፡ በቦረናም ተመሳሳይ ነው፡፡ የክረምት ወቅታቸው ስላልሆነ በዚያ አካባቢ እምብዛም ተፅዕኖ አያሳድርም፡፡ ምክንያቱም የክረምት ወቅታቸው አይደለም፡፡ በአሁኑ ወቅት የዝናብ ወቅታቸው የሆኑ አካባቢዎች ግን አሉ፡፡ አፋር ላይ በተወሰነ ደረጃ ተፅዕኖ አለው፡፡ በዚህ አካባቢ ዝናቡ ቢኖር ሊጠቅም የሚችልባቸው ሌሎች ምክንያቶችም አሉ፡፡ ለምሳሌ አፋር አካባቢ የተለያዩ ግድቦች አሉ፡፡ እንደ ተንዳሆና ከሰም ያሉ ግድቦች ውኃ ይፈልጋሉ፡፡ እነዚህ ግድቦች ውኃ እንዲይዙ ማድረግ ተገቢ ነው፡፡ ከመስኖ ሥራ ጋር ተያይዞ ተፅዕኖ እንዳይፈጠር ባለው ክረምት ወቅት የግድ መያዝ ያለበት ውኃ እንዲይዝ ምክር ተሰጥቶ በዚያ መሠረት እየተሠራ ነው፡፡ ምክንያቱም ውኃው ለሸንኮራ አገዳ ያስፈልጋል፡፡ ስለዚህ ባለው አጋጣሚ ሁሉ መያዝ ያለባቸውን ውኃ መያዝ አለባቸው፡፡ ከተፅዕኖው አኳያ ይህ ይመከራል፡፡ አሁን እየታየ ያለው በተወሰነ ደረጃም ቢሆን የግድቡ የውኃ መጠን በሚሊ ሜትር እየጨመረ ነው፡፡ ቢሆንም ከዝናብ እጥረቱ አንፃር በቂ ውኃ ላይኖር ይችላል፡፡ በጥቅሉ ሲታይ ከመደበኛ በታች የሆነ ዝናብ ያገኙ አካባቢዎች እንዳሉ ሁሉ፣ ማግኘት ከነበረባቸውና ከመደበኛ በላይ ዝናብ ያገኙም አሉ፡፡ ወደ መደበኛ የተቀራረበ ዝናብ ያገኙ ቦታዎችም እንደነበሩ መረጃው አለ፡፡ ነገር ግን በአርሲና በምሥራቅ ሸዋ በስምጥ ሸለቆ አካባቢ የዝናብ እጥረት ነበር፡፡ በደቡብ ክልል ጉራጌና ስልጤ ዞንም ተመሳሳይ ችግር የታየበት ነው፡፡ ሐምሌ ላይ እጥረት ነበር፡፡ አንዳንድ ቦታዎች ላይ ደግሞ ዝናብ ጠፍቶ ይቆይና አንድ ቀን ከባድ ዝናብ ይጥላል፡፡ እሱን ለረዥም ጊዜ የመጠቀም አዝማሚያ ስለነበር ነው አደጋው ያልተከሰተው፡፡
ሪፖርተር፡- እንደህ ዓይነቱ ክስተት በየአሥር ዓመቱ የሚከሰት ነው ይባላል፡፡ በእርግጥ ይህ እየሆነ ስለመሆኑ የዘንድሮው የዝናብ እጥረት እያመለክትም? ለምሳሌ በ1977 ዓ.ም. በ1997 እና በ2007 ዓ.ም. ችግሩ ተከስቷል፡፡ የአሁኑ እንዴት ይታያል?
አቶ ፈጠነ፡- ዙሩ ተመሳሳይ ነው፡፡ በአሥር ዓመትም ሊከሰት ይችላል፡፡ በ12 ዓመትም ሊሆን ይችላል፡፡
ሪፖርተር፡- ስለዚህ አሥርና 12 ዓመታት እየቆጠረ የሚመጣ ችግር ነው ማለት ነው?
አቶ ፈጠነ፡- አዎ አለ፡፡ በእኛም ትንበያ የተመሳሳይ ዓመታት ክትትሉን ነው የምታየው፡፡ ታሪካዊ መረጃዎችን ተጠቅመን በ1997 እና በ2007 ተመሳሳይ ከሆነ የኤልኒኖ ክስተቱ እንዲህ የመምጣት ሁኔታ አለው፡፡ ተመሳሳይ ላይሆን ይችላል፡፡ ግን ዞሮ ዞሮ በእንዲህ ዓይነት ዓመታት ብዙ ጊዜ ይከሰታል፡፡
ሪፖርተር፡- በኢትዮጵያ የተፈጠረው ወቅታዊ ችግር በሌሎች አገሮች ተከስቷል?
አቶ ፈጠነ፡- በትክክል፡፡ ለምሳሌ የመን ውኃ የለም፡፡ ዝናብ የለም፡፡ በሱዳንም በተመሳሳይ የሚታይ ነው፡፡ ብዙ የአፍሪካ ቀንድ አገሮች የምንላቸው ላይ ተመሳሳይ ችግር አለ፡፡ ምክንያቱም ሲስተሙ አንድ ነው፡፡ በምዕራብ አፍሪካም ታይቷል፡፡ በምድር ወገብ አካባቢ ያሉ አገሮች ይህ ችግር ታይቶባቸዋል፡፡ እንዲያውም ኬንያ ባለፈው ዓመት በጣም ተጠቂዎች ነበሩ፡፡ ለዚህም ነው የኤልኒኖ ክስተት አምናም እንደነበር ሲከራከሩ የቆዩት፡፡ የእኛ ትንበያ ነው ትክክል የሆነው፡፡
ሪፖርተር፡- በዚህ ሰሞን ዝናብ መታየት ቢጀምርም ባለፉት ወራት የነበረው የዝናብ እጥረት የእርሻ ሥራዎችን አስተጓጉሏል፡፡ ይህም በሚቀጥለው ዓመት ምርት ላይ ተፅዕኖ ማሳደሩ አይቀርም፡፡ የተረጂዎችም ቁጥር ይበረክታል፡፡ የምርት መቀነሱና የተረጂዎች ቁጥር መጨመሩ ጉዳይ እንዴት ይታያል?
አቶ ፈጠነ፡- የምርት መቀነስ ይኖራል፡፡ በምርት ላይ ተፅዕኖ አለው፡፡ ምርት መቀነሱ አይቀርም፡፡ ምርት ሊቀንስ ይችላል፡፡ ነገር ግን ምርት እንዳይቀንስ መሥራት ይቻላል፡፡
ሪፖርተር፡- እንዴት? አሁን እኮ የዘር መዝሪያ ጊዜው አልፏል፡፡
አቶ ፈጠነ፡- አሁን ሁለት ነገሮች ነው የሚጠበቁት፡፡ አንዱ ሲዘራ የነበረውና ሐምሌ ላይ የተከሰተው ነገር አለ፡፡ ቢዘገይም ሊመረት የሚችልበት ዕድል አለ፡፡ ሁለተኛው ከኤልኒኖ ክስተት ጋር ተያይዞ በጋው ላይ የተጠናከረ ዝናብ ይኖራል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ አሁን እጥረት ነው ያለው፡፡ የበጋውን ትንበያ ገና የምንሰጥ ቢሆንም፣ በኤልኒኖ ዓመታት ከታየው ልምድ በበጋ ወቅት ዝናቡ ይጠነክራል፡፡ መስከረም ላይ ጠንከር ያለ ዝናብ ሊታይ ይችላል፡፡ ጠንከር ያለ ዝናብ ሲታይ አሁን ባለው ተጨባጭ ሁኔታ ውስጥ ሆኖ የበቀለውን እህል የማበላሸት ዕድሉ ይኖራል፡፡ ይህ እንዳይሆን ነው አርሶ አደሩ መሥራት ያለበት፡፡ ምርቱን ቶሎ የሚሰበስብ ከሆነ ሥጋቱ ይቀንሳል፡፡ ነገር ግን አሁን ምርት የያዘላቸውም ቢሆን ምርታቸው በቶሎ ካልተሰበሰበ በጋ ላይ ወቅቱን ያልጠበቀ ዝናብ ሲከሰት የደረሰውንም እህል ያበላሻል ማለት ነው፡፡ ይህ እንዳይሆን መሥራት ከተቻለ ተፅዕኖው እንዳይከሰት ማድረግ ይቻላል፡፡
አሁን ነሐሴ ላይ ጥሩ ከሆነ መስከረም ላይ አልፎ አልፎ መዝነቡ ስለማይቀር፣ ሐምሌ ላይ ከተከሰተው አሉታዊ ተፅዕኖ ወጪ እምብዛም ተፅዕኖ የሚያሳድር ነገር አይደለም (አሁን እያገኘ ከሄደ ማለት ነው)፡፡ ይህም ሆኖ በመደበኛው የዝናብ ወቅት ይገኝ ከነበረው ምርት ጋር እናነፃፅር ከተባለ ምርቱ የሚቀንስ መሆኑ ግን ምንም ጥርጥር የለውም፡፡ ይህም ትክክለኛ ዕርምጃ ካልተወሰደና በኋላ ወቅቱን ባልጠበቀ ዝናብ ሊበላሽ ስለሚችል ማለት ነው፡፡ ኤጀንሲው የተደራጀ መረጃ ይዞ የሚሠራው ሥራ እንዳለ ሆኖ፣ በእኛ አገር ሁኔታ እስካሁን ለትንበያ የምንወጣው ለአራት ወራት ነው፡፡ የበጋውን ትንበያ ደግሞ መስከረም ላይ እንሰጣለን፡፡ ኅብረተሰቡም ይህንን መረጃ መጠቀም አለበት፡፡ ተከታታይ መረጃዎችም ከዚህ በኋላ መደረግ የሚኖሩበትን የሚጠቁሙ ይሆናሉ፡፡
ሪፖርተር፡- ይህ የተፈጥሮ አደጋ ነው፡፡ በግልጽም የታየው ይኼው ነው፡፡ ከዚህ አንፃር ሊከተል የሚችለውን ችግር መንግሥት እንዴት ለመቅረፍ እየሠራ ነው ማለት ይቻላል? ተጨባጭ የሆነ ነገር አለ?
አቶ ፈጠነ፡- አደጋውን ለመቋቋም መንግሥት ሰፊ ሥራ እየሠራ ነው፡፡ መንግሥት ባለው ስትራቴጂ የግብርና ዘርፉን ብቻ አይደለም የሚያየው፡፡ የግብርና ዘርፍ አንዱ ነው፡፡ የውኃ ዘርፍም ከዚሁ ጋር የተያያዘ ነው፡፡ በተለይ የውኃ ዘርፍ ላይ ካለው የዝናብ እጥረት አንፃር የመጠጥ ውኃ እጥረት ሊከሰት ይችላል፡፡ ለመስኖ የሚሆን ውኃ ሊታጣም ይችላል፡፡ የእኛ የኤሌክትሪክ ኃይል ምንጭ ታዳሽ ኢነርጂ በመሆኑ ውኃ ከሌለ ተፅዕኖው ኤሌክትሪክ ላይም ይሆናል፡፡ ስለዚህ መንግሥት ይህንን ጉዳይ ቀድሞ ስለተገነዘበ ውኃ እየያዘ ነው፡፡ ጠብ የሚለውን ውኃ በግድብ እየያዘ ነው፡፡ ከዚህ ቀደም በየግድቦቹ የክረምቱን አኳኋን አይተህ ውኃ የምትለቅባቸው ሁኔታዎች አሉ፡፡ ለምሳሌ ከዚህ ቀደም አንድ ግድብ ከሞላና መያዝ ካለበት በላይ ከሆነ ግድቡን ለአደጋ ስለሚያጋልጥ ውኃው ይለቀቃል፡፡ በዚህ ዓመት ግን የሚለቀቅ ውኃ የለም ማለት ነው፡፡ የዘነበው ውኃ ሁሉ ይያዛል፡፡ በዚህ መንገድ ውኃን በመያዝ አደጋውን መቀነስ ይቻላል ማለት ነው፡፡
ኢንዱስትሪዎች ሥራቸውን እንዳያቋርጡና ኅብረተሰቡ የኤሌክትሪክ ኃይል ችግር እንዳይገጥመው ይደረጋል፡፡ እንዲህ ያሉ ሥራዎች ውኃን በሚመለከተው ዘርፍ የሚሠራው ነው፡፡ በዚህ ላይ ከመንግሥት ጋር እጅና ጓንት ሆነን እየሠራን ነው፡፡ በየጊዜው መረጃ እየተሰጠ ሲሆን በአሥር ቀናት ደግሞ ለእያንዳንዱ ዘርፍ በስማቸው የተጠናከረ መረጃ ይሄዳል፡፡ አንድ ጊዜ የተሰጠውን መረጃ ብቻ ሳይሆን በየጊዜው ያሉትንም መሻሻሎች በጋራ እየገመገምን ነው፡፡ መንግሥት ይህንን ይዞ ዕቅድ ያወጣል፡፡ የምግብ እጥረት ሊያጋጥም ይችላል ከተባለ የአደጋ ጊዜ ማኔጅመንት ያቅዳል ማለት ነው፡፡ ግድቡ ላይም የሚፈለገው ውኃ ካልተገኘ ሌሎች አማራጮች ሥራ ላይ ይውላሉ፡፡ ለምሳሌ ጄኔሬተር ሊገዛ ይችላል፡፡ ለጄኔሬተሮቹ የሚሆን ነዳጅ ያመቻቻል፡፡ ስለዚህ ውሳኔ ሰጪ አካላት በመረጃው መሠረት የራሳቸውን ስትራቴጂ ይነድፋሉ፡፡ ይሠራሉ፡፡ ሥራው ሰፊ ነው፡፡
ሪፖርተር፡- ሰሞኑን እንደተሰማው በዚህ የአየር ለውጥ ምክንያት በአፋር አካባቢ እንስሳት እየሞቱ ነው፡፡ እንዲህ ያሉ አደጋዎችን እንዴት ለመቆጣጠር ታስቧል? የአካባቢው ነዋሪዎች ከብቶቻቸውን የተሻለ የአየር ፀባይ አላቸው ወደተባሉ ሥፍራዎች እየወሰዱ ነው? ወደሌሎች አካባቢዎች እየሄዱ እየተደረገ ነው?
አቶ ፈጠነ፡- በአፋር አካባቢ የተከሰተው ተመሳሳይ ነው፡፡ ለምሳሌ ጎርፍ ቢሆን ጎርፍ ወደ ሌለበት አካባቢ ማንቀሳቀስ ትችላላህ፡፡ በበጋ ላይ ግጦሽ የሚዘጋጅበትና የመሰብሰብ ጉዳዮች ካልሆኑ በስተቀር፣ በአጭር ጊዜ የሚከሰቱ ነገሮች ላይ እንዲህ ነው ብሎ መደምደም ይከብዳል፡፡
ሪፖርተር፡- የአየር ንብረት ለውጡ ላልተጠበቀ ጎርፍ ምክንያት ሊሆን እንደሚችልም እየተነገረ ነው፡፡ በዚህም ሰበብ ጉዳት እንዳይደርስ ምን ዓይነት መረጃ ትሰጣላችሁ?
አቶ ፈጠነ፡- ኤጀንሲያችን የሚመጣውን የዝናብ መጠን ነው የሚነግረው፡፡ ይህንን መረጃ ይዘው ማኔጅ የሚያድርጉ የተፋፈስ ባለሥልጣናት አሉ፡፡ ለምሳሌ የአዋሽ ተፋሰስ ባለሥልጣን መሥሪያ ቤት አንዱ ነው፡፡ እነዚህ ባለሥልጣናት ናቸው ሥራውን የሚሠሩት፡፡ እነሱ ከእኛ የሚወስዱት ጎርፍ ይከሰታል፣ አይከሰትም የሚለውን መረጃ አይደለም፡፡ ያለውን የዝናብ መጠን የሚያመላክቱ መረጃዎችን ነው የምንሰጠው፡፡ ጎርፍ በሁለት ምክንያቶች ይከሰታል፡፡ አንዱ በጣም ዝናብ ሲሆን ነው፡፡ ሌላው ከማኔጅመንት ችግር ነው፡፡ ትንሽ ዝናብ ዘንቦ የፍሳሽ ማስወገጃ አጠቃቀማችን ዝቅተኛ ከሆነ ጎርፍ ሊከሰት ይችላል፡፡ ስለዚህ በሚሰጠው መረጃ መሠረት የጎርፍ አደጋዎችን እነዚህ አካላት ለመከላከል ዝግጁ እንዲሆኑ ይደረጋል፡፡ ከተለመደው የዝናብ መጠን በላይ ይህንን ያህል ሚሊ ሜትር ዝናብ ይዘንባል ከተባለ፣ ይህንን መረጃ ወስደው ተገቢውን ሥራ ይሠራሉ፡፡