Monday, April 15, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ድርቅ ያጠላበት የዶዶታ ወረዳ

ተዛማጅ ፅሁፎች

አቶ ጀማል ኑር የዶዶታ ወረዳ ግብርና ቢሮ ኃላፊ ናቸው፡፡ በአካባቢው በተፈጠረው የዝናብ እጥረት ዙሪያ ዳዊት ታዬ አነጋግሯቸዋል፡፡

ሪፖርተር፡- በዶዶታ ወረዳ በዝናብ እጥረት አብዛኛው በሰብል መሸፈን ያለበት መሬት አልተሸፈነም፡፡ ችግሩ ምን ያህል ነው?

አቶ ጀማል፡- በእኛ ወረዳ ድርቅ አለ፡፡ ዝናብ በጊዜ መዝነብ አልጀመረም፡፡ ከጀመረ ወዲህም እየተቆራረጠ ነበር፡፡ እንዲያውም እየዘነበ ነው ማለት አይቻልም፡፡ በወር አንዴ ቢዘንብ ነው፡፡ የዘነበውም አነስተኛ ዝናብ ቢሆን በወረዳችን ውስጥ ያሉትን ሁሉንም ቀበሌዎች የማያዳርስ ነበር፡፡ በዚህ ምክንያት አርሶ አደሩ ባለው እርጥበት ዘሩን እንደዘራና ትንሽ ውኃ ወደ ማሳ በማስገባት እንዲጠቀም ምክር ስንሰጥ ቆይተናል፡፡ ቢሆንም ያለውን ችግር መቅረፍ ባለመቻሉ ችግሩ እንደቀጠለ ነው፡፡ በወረዳ ደረጃ የተለያዩ ሥራዎች እየተሠሩ ነው፡፡ ከችግሩ አሳሳቢነት አንፃር በወረዳችን አንድ ኮሚቴ ተቋቁሞ ጥናት እየተሠራ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ምን ዓይነት ጥናት?

አቶ ጀማል፡- ምን ያህል ተዘራ? ከተዘራው ውስጥስ ምን ያህሉ ያዘ? የሚሉና ሌሎች መረጃዎችን ለመሰብሰብ ነው፡፡ አሁን ግን ስንዴ የዘራው ሳይበቅል የቀረበት አርሶ አደር የተዘራበትን መሬት እንደገና ገልብጦ በማረስ ጤፍ እንዲዘራ እየተደረገ ነው፡፡ ይህም ቢሆን ጥሩ የሚሆን አይመስለኝም፡፡ ዝናቡ የለም፤ በጣም ችግር ውስጥ ነው ያለነው፡፡

ሪፖርተር፡- በወረዳችሁ ምን ያህል አርሶ አደሮች አሉ? ምን ያህል የእርሻ መሬት ነበር በዘር የሚሸፈነው?

አቶ ጀማል፡- በዚህ ዓመት በመኸር ወቅት 17,744 ሔክታር የሸፈነው መሬት የበቆሎ፣ የስንዴ፣ የገብስና ሌሎች የጥራጥሬ ምርቶች ናቸው፡፡ ከዚህ ምርቶች ውስጥ በግንቦት ወር የተዘራው በቆሎ እንዳለ ጠፍቷል ማለት ይቻላል፡፡

ሪፖርተር፡- ሙሉ ለሙሉ ጠፍቷል የሚባለው የተዘራ በቆሎ ማሳ ምን የህል ሔክታር ይሆናል?

አቶ ጀማል፡- በግንቦት ወር ውስጥ በ2,370 ሔክታር አካባቢ ነው፡፡ ከዚህ ውስጥ እየተረፈ ሊኖር ይችል ይሆናል እንጂ እስካቀሁን ከ60 በመቶው በላይ የተዘራ በቆሎ ጠፍቷል፡፡

ሪፖርተር፡- ከዚህ ቀደም እንዲህ ዓይነት ችግር ገጥሟችሁ ያውቃል?

አቶ ጀማል፡- አምና በእኛ ወረዳ ወደ ስምንት ቀበሌዎች ላይ እንዲህ ዓይነት ችግር ነበር፡፡ የዘንድሮው ግን ከአምናው የተለየ ነው፡፡ አሁን ችግሩ ሁሉንም ቀበሌዎች አዳርሷል፡፡ በምርት ጥሩ ናቸው የሚባሉ ቀበሌዎች ሳይቀሩ ዘንድሮ ተነክተዋል፡፡ ዝናብ ጠፍቷል፡፡ በእነዚህ አካባቢ በቆሎ ጠፍቷል፡፡ ሌሎች ሰብሎቻቸውም በዝናቡ እጥረት ሳቢያ የምርት እጥረት ይኖራል፡፡

ሪፖርተር፡- ዝናቡ ካልመጣና ችግሩ በዚሁ ከቀጠለ ከዚህ በኋላ ምን ለማድረግ አቅዳችኋል?

አቶ ጀማል፡- አሁን ማድረግ የሚኖርብን ነገር አለ፡፡ በሚቲዎሮሎጂ መረጃ መሠረት በዚህ ወር ዝናብ ይኖራል የሚል ግምት አለ፡፡ ነገር ግን አርሶ አደሩ በተገኘው እርጥበት መሬቱን እንዲንከባከብ ማድረግ ቀዳሚ ሥራችን ይሆናል፡፡ የግብርና ባለሙያዎቻችንም ወደ ቀበሌ ወርደው በተገኘው እርጥበት እንዲሠሩ ለማድረግ የማነሳሳት ሥራ እየተሠራ ነው፡፡ ከዚያ በኋላ ጥናት በማድረግ ችግሩን ለመንግሥት አሳውቀን አርሶ አደሮቹ መረዳት የሚችሉበትን ሁኔታ ለመፍጠር እየተንቀሳቀስን ነው፡፡

ሪፖርተር፡- እስካሁን በወረዳችሁ በዝናብ እጥረት የተፈጠረውን ችግር አሳውቃችኋል?

አቶ ጀማል፡- አሳውቀናል፡፡ የዞን አመራሮችም መጥተው ችግሩን አይተዋል፡፡ በፌዴራል ደረጃም የግብርና ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ወንድራድ መጥተው የመስክ ጉብኝት አድርገው  ችግሩ አስከፊ መሆኑን አይተዋል፡፡ አርሶ አደሩ በተቻለ መጠን እርጥበቱን ማሳ ውስጥ እንዲይዝና ለዚህም የግብርና ባለሙያዎች ተሰማርተው መሥራት እንዳለባቸው አሳስበዋል፡፡ እኛም ቀደም ብለን ስንንቀሳቀስበት የነበረ ጉዳይ ነው፡፡ 

ሪፖርተር፡- ችግሩ በሰብል ምርት ላይ ብቻ የተወሰነ አይደለም፡፡ ከብቶችም አደጋ ውስጥ መሆናቸውን አርሶ አደሮች እየተናገሩ ነው፡፡ እኛም እንደተመለከትነው የመኖ እጥረት አለ፡፡

አቶ ጀማል፡- ችግሩ አለ፡፡ በእኛ ወረዳ ዝናብ ከዘነበ ሳር ስለሚኖር የከብቶቻቸውን መኖ ፍላጎት በዚህ ይሸፍኑ ነበር፡፡ አሁን ግን ሳሩ የለም፡፡ በዚህም አሁን እየተጠቀሙ ያሉት በመጠባበቂያነት የያዙትን ገለባ ነው፡፡ ገለባው ደግሞ ያልቃል፡፡ ስለዚህ በከብቶች መኖ ጉዳይም ችግር ውስጥ ነው፡፡ እንደ ግብርና ለከብቶቹ ክትባት እንዲሰጥ የማበረታታት ሥራ ነው የሚሠራው፡፡

ሪፖርተር፡- ምን ዓይነት ክትባት?  

አቶ ጀማል፡- ከብቶችን የሚያበረታ ክትባት ነው፡፡ አርሶ አደሮቹ ከብቶቻቸውን ይህንን ክትባት እንዲወስዱ በማድረግ ብርታት እንዲያገኙ የሚያደርግ በመሆኑ አርሶ አደሮቹ  ይህንን እንዲያደርጉ እያበረታታን ነው፡፡ በተቻለ መጠን ግን እርጥበት ወዳለበት ቦታ አንቀሳቅሰው እንዲያቆያቸው ምክር እየሰጠናቸው ነው፡፡  

ሪፖርተር፡- ከዚህ ቀደም በነበረ ድርቅ ለተጐጂዎቹ ምን አድርጋችኋል?

አቶ ጀማል፡- በወቅቱ በነበረ ችግር በዚህ ዓመት ለ14,404 ተጐጂዎች ዕርዳታ እየተሰጠ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ይህ ዕርዳታ የተሰጠው ለአምና ተጐጂዎች ነው ማለት ነው?

አቶ ጀማል፡- አዎ፡፡ እነዚህ በስምንት ቀበሌ ውስጥ ዕርዳታ ያስፈልጋቸዋል ተብሎ የተሰጣቸው ናቸው፡፡

ሪፖርተር፡- ስለዚህ እንዲህ ባለው የአየር መዛባትና የዝናብ እጥረት ችግር ሲጠቃ ይህ አካባቢ ለሁለተኛ ጊዜ ነው ማለት ነው?

አቶ ጀማል፡- አዎ ለሁለተኛ ጊዜ የተፈጠረ ችግር ነው፡፡ በተለይ ስምንቱ ቀበሌ ሁለተኛቸው ነው፡፡ አራቱ ግን ለመጀመሪያ ጊዜ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- በአጐራባች ወረዳዎች ላይ ያለው የዘንድሮ የመኸር ሁኔታ ምን ይመስላል? መረጃ አለዎት?

አቶ ጀማል፡- በዙሪያችን ካሉ ወረዳዎች የተወሰኑ ቆላ ቀበሌዎች በድርቅ ተጠቅሰዋል፡፡ በአርሲ ዞን ደረጃ ወደ ሰባት ወረዳዎች ተመሳሳይ ችግር ውስጥ እንደሆኑ መረጃዎች እየተሰጡ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- አምና በነበረው ችግር በወረዳችሁ እናመርታለን ካላችሁት ምን ያህል አምርታችሁ ነበር?

አቶ ጀማል፡- አምና እንኳን በተፈጠረው ችግር ሊመረት ይችላል ተብሎ ተገምቶ ከነበረው ምርት 62 በመቶ ያህል ቀንሷል፡፡ 

ሪፖርተር፡- ምን ያህል ይመረት ነበር?

አቶ ጀማል፡- በዚህ ዓመት ከሁሉም ምርት ዓይነት 407,000 ኩንታል ይገኛል የሚል ነበር፡፡

ሪፖርተር፡- አሁን ተከሰተው የዝናብ እጥረት አንፃር በሚፈጠረው ችግር ይገኛል ብላችሁ ካሰባችሁት ምን ያህል ልታገኙ ትችላላችሁ?

አቶ ጀማል፡- ዘንድሮ ምን ይገኛል? እኔ እንጃ ከዚህ በኋላ ዝናቡ መዝነቡን እንኳን ቢቀጥል ከአሁን በኋላ ምርቱ እንደ ካቻምናው አይሆንም፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች