የዘንድሮው የመኸር ወቅት እያጣደፋቸው ካሉ አርሶ አደሮች መካከል አንዱ አርሶ አደር ተገኝ መኩሪያ ናቸው፡፡ ከአዲስ አበባ 60 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በምትገኘው የአደአ ወረዳ፣ ሲርባና ጉደቲ ቀበሌ ነዋሪ ናቸው፡፡ ነሐሴ 1 ቀን 2007 ዓ.ም. ማለዳ በማሳቸው ላይ ጤፍ ለመዝራት እየተዘጋጁ ነበር፡፡ ጤፍ ዘግየት ብሎ የሚዘራ በመሆኑ አቶ ተገኝ፣ ‹‹ዛሬ የመጨረሻው የጤፍ መዝሪያ ቀን ነው፡፡ በሌሎች ማሳዎች ላይ ዘርቼ ጨርሻለሁ፡፡ በዚህችኛው ማሳዬ ላይም ዛሬ የመጨረሻውን ዘር እዘራለሁ፤›› በማለት ይገልጻሉ፡፡
ዘንድሮ አየሩ የሰጠ፤ ዝናቡም ወቅቱን ጠብቆ የመጣላቸው በመሆኑ ምንም ችግር ያላጋጠማቸው እንደሆነም ያረጋግጣሉ፡፡ ‹‹ይኸው ስንዴውም በቆሎውም ጥሩ በቅሏል፤›› በማለት ከእያንዳንዱ ማሳቸው ጥሩ ምርት እንደሚጠብቁ ተስፋ ያደርጋሉ፡፡ አቶ ተገኝ ከሚገኙበት የአደአ ወረዳ ወደ 80 ኪሎ ሜትር ወይም ከአዲስ አበባ 130 ኪሎ ሜትር ርቀት፣ በአርሲ ዞን ዶዶታ ወረዳ ያሉ አርሶ አደሮች ግን እንደ አቶ ተገኝ በተስፋ የተሞሉ ለመሆን አልታደሉም፡፡ በዘንድሮ የመኸር ወቅት የዘሩት ዘር ምርት ይሰጠናል ብለው አይጠብቁም፡፡ ማሳቸውም እንደእነ አቶ ተገኝ ማሳ በውኃ የረሰረሰ አይደለም፡፡ በብርቱ ሥጋት ውስጥ የገቡ ስለመሆናቸው ከአንደበታቸው የሚወጣው ቃል ብቻ ሳይሆን ከዚህ ቀደም ያመርቱበት የነበረው መሬት ግርጣት ይመሰክራል፡፡ ከወራት በፊት የዘሩት በቆሎ እዚያው ከንችሮ ጨንግፎባቸዋል፡፡ ሰኔና ሐምሌ አካባቢውን በውኃ የሚሞላውና ማሳቸውን የሚያርሰው ዝናብ አናት በሚበሳ ፀሐይ ተቀይሮ መሬታቸው ደርቋል፡፡ ዝናብ እጦቱ በርትቶ የዘሩት ዘር ሳይቀር እንዳያፈራ አድርጓል፡፡ በዚህ ወቅት አካባቢያቸው በተለያዩ ሰብሎች አረንጓዴ ይለብስ እንደነበርም በዶዶታ ወረዳ በተለያዩ ቀበሌ ገበሬ ማኅበሮች ውስጥ ያገኘናቸው አርሶ አደሮች ይናገራሉ፡፡
በዶዶታ ወረዳ የዓለም ቀበሌ ያገኘናቸው የ51 ዓመቱ አርሶ አደር አቶ ጀማል ደነባ ዘንድሮ የገጠማቸው የዝናብ እጥረት ከዚህ ቀደም አጋጥሟቸው የማያውቅ መሆኑን ይገልጻሉ፡፡ በአንደኛው የማሳቸው ክፍል ግንቦት 10 ቀን 2007 ዓ.ም. የዘሩት በቆሎ በዝናብ እጦት እዚያው ከንችሮ መቅረቱን በሐዘኔታ የሚናገሩት አቶ ጀማል፣ ከዚህ በኋላ ምርት የማይሰጥ በመሆኑ ከብቶች ለቀውበታል፡፡ እርሳቸው ግን አሁንም ተስፋ ሳይቆርጡ ደቃቃ በሬዎቻቸውን ጠምደው ስንዴ ዘርተውበት የነበረውን መሬት እንደገና ገልብጠው በማረስ፣ ለምናልባቱ ብለው ቤተሰቦቻቸውን ሽንኩርት እያስተከሉ ነው፡፡ ይህም ለፍሬ የሚሆነው ዝናብ ከጣለ ነው፡፡
የስምንት ልጆች አባት የሆኑት አቶ ጀማል በዘንድሮ የመኸር ወር የጠፋው ዝናብ እርሳቸውን ብቻ ሳይሆን በዶዶታ ወረዳ ያሉ 12ቱንም ቀበሌዎች የዳበሰ ችግር እንደሆነ ይገልጻሉ፡፡ የወረዳው ግብርና ቢሮ ኃላፊ አቶ ጀማል ኑራ እንደገለጹት፣ በ2007/2008 የምርት ዘመን ከ12ቱ ቀበሌዎች በዘር ይሸፈናል ተብሎ ከሚጠበቀው ከ17,000 ሔክታር በላይ መሬት ከ420 ሺሕ ኩንታል በላይ ምርት ይጠበቅ ነበር፡፡ ነገር ግን የተከሰተው የዝናብ እጥረት የታሰበውን ማሳካት እንደማይቻል አመላካች ነው፡፡ እንደ ዶዶታ ሁሉ በአርሲ ዞን በተለያዩ ወረዳዎች ተመሳሳይ ችግር ተከስቷል፡፡ ከምዕራብ የአገሪቱ ክፍል ውጭ በአብዛኛዎቹ ክልሎች ያሉ ወረዳዎች ተመሳሳይ ችግር ውስጥ ገብተዋል፡፡
ይህ የብዙዎችን ስሜት የነካው የዝናብ እጥረት ዋነኛ መንስዔው ከኤሊኒኖ ክስተት ጋር የተያያዘ ነው፡፡ በዘንድሮው የክረምት ወቅት የተከሰተውን የዝናብ እጥረት በተመለከተ የብሔራዊ ሚቲዎሮሎጂ ኤጀንሲ በሰጠው መግለጫ በምዕራብ ትግራይ፣ አማራ፣ ደቡብ ኦሮሚያ ክልሎች የዝናብ እጥረቱ ተከስቷል፡፡ በአፋርና በሶማሌም ይኸው የዝናብ እጥረት የፈጠረው ተፅዕኖ ለእንስሳት ሕይወት መጥፋት ምክንያት መሆኑን ባለፈው ሐሙስ መንግሥት በይፋ አስታውቋል፡፡
ሐምሌ 30 ቀን 2007 ዓ.ም. የወጣው የግብርና ሚኒስቴር ይፋዊ መግለጫ፣ የዝናብ እጥረቱ በሰሜን ምሥራቅ፣ በከፊል መካከለኛ፣ በስምጥ ሸለቆና በምሥራቅ የአገሪቱ አካባቢዎች የዝናብ እጥረት መኖሩን ያመለክታል፡፡
በተለይም ዝናብ አጠር የሆኑ የአገሪቱ ክፍሎችና የስምጥ ሸለቆ አካባቢዎች የኤልኒኖ ክስተት አሉታዊ ተፅዕኖ ጐልቶ የታየባቸው አካባቢዎች ናቸው ብሏል፡፡
ይኸው መግለጫ አያይዞም፣ የሰሜን ምሥራቅ የምሥራቅ አርብቶ አደር አካባቢዎች ላይ የእንስሳት መኖና የውኃ እጥረት አጋጥሟል፡፡ ከዚህ መግለጫ በኋላ በአፋር ክልል ባሉ የተለያዩ ወረዳዎች ግመሎችና ፍየሎች ሞተዋል፡፡ የመጠጥ ውኃ ችግርም ተከስቷል፡፡ አርሶ አደሮች ከብቶቻቸውን መኖ ወዳለበት ስፍራ እየወሰዱ ነው፡፡
መንግሥት በዝናብ እጥረቱ ሳቢያ እየታየ ያለውን ችግር ተገንዝቤ ተዘጋጅቻለሁ ቢልም እንደነአቶ ጀማል ያሉ አርሶ አደሮች ግን ከጭንቅ አልወጡም፡፡ ዝናቡን ይጥልላቸው ዘንድ ፈጣሪያቸውን እየተማፀኑ ነው፡፡ ዘግይቶም ቢሆን ሊዘንብ ይችላል በሚል እየጠበቁ ነው፡፡ ያለውን አማራጭ ሁሉ የሚጠቀሙ መሆኑን አቶ ጀማል ይናገራሉ፡፡ የአጋጣሚ ነገር ሆኖ የአቶ ጀማል ባለቤት አጠገባቸው የሉም፡፡ የሰባት ልጆቻቸው እናት ወደ ሳዑዲ ዓረቢያ ለሥራ ሔደዋል፡፡ እነዚህ ሁሉ ልጆች ያፈሩ ባለቤታቸውን ወደ ሳዑዲ እንዲሄዱ ያደረጉበት ምክንያቱ ደግሞ እንዲረዷቸው በማሰብ ነው፡፡
‹‹በቅርቡ ትመጣለች ብለን ነበር፤›› ያሉት አቶ ጀማል፣ ‹‹አሁን አየሩን ስናየው ጥሩ ስላልሆነ እዚያው ቆይታ የምትረዳንን ትርዳን ብዬ እንዳትመለስ ነግሬያታለሁ፤›› ብለዋል፡፡
‹‹ምን ላድርግ ብለህ ነው፡፡ አሁን የገጠመን ችግር በዚሁ ከቀጠለ ቢያንስ እዛው ቆይታ እንድትደጉመን ለማድረግ ነው፤›› ይላሉ፡፡ ይህንኑ ችግር ባህር ማዶ ላሉት ባለቤታቸው መናገራቸውንም ይገልጻሉ፡፡ ‹‹ካልሆነ እኮ ወደ ከብት ሽያጭ ልገባ ነው፤›› በማለትም የአየር ንብረት ለውጡ ያመጣባቸውን ጣጣ ተቋቁሞ ለማለፍ ባለቤታቸው ላይ እንዲጨክኑ እንዳደረጋቸው ይገልጻሉ፡፡
በዚሁ አካባቢ ያገኘናቸው አርሶ አደር ጐቤ ኡስማንም የዘንድሮው የአየር ለውጥ የተለየ መሆኑን ነው፡፡ ‹‹የዛሬን አያድርገውና አምና ይህንን ጊዜ አረም ጉልጐላ ላይ ነበርን፡፡ ይህ ዙሪያውን ገርጥቶ የሚታየው መሬት ሁሉ አረንጓዴ ለብሶ ነበር፡፡ ዘንድሮ ግን እንዲህ ሆነ፡፡ ነገሩ ተስፋ ያስቆርጣል፤›› ብለዋል፡፡
በዶዶታ ወረዳ የተከሰተው የዝናብ እጥረት በተለይ የተዘራ በቆሎ ላይ ያሳደረው ጉዳት ጐልቶ ይታያል፡፡ አርሶ አደሮቹ አገር ሰላም ብለው በግንቦት ወር የዘሩት በቆሎ ፍሬ አልባ ሆኗል፡፡ የግብርና ኃላፊው አቶ ጀማል እንደገለጹት፣ በወረዳቸው ከ2,300 ሔክታር በላይ መሬት ላይ የተዘራው በቆሎ፣ ሦስት ወር ቢሆነውም አንዲት ስንዝር እንኳ ከፍ አላለም፡፡ በዚህ ወቅት ወደ እሸትነት ይገባ ነበር የሚሉት አቶ ጀማል፣ አሁን ግን ለሁለትና ለሦስት ቀን ለከብቶች የሚቀርብ መኖ ከመሆን ውጭ ምንም ሊፈይድ እንደማይችል ይገልጻሉ፡፡
በዶዶታ መስመር የሚታየው የአየር ለውጥ በአካባቢው መልክዓ ምድር ላይ እያሳረፈ ያለው ተፅዕኖ ጎልቶ እየወጣ ነው፡፡ ሁሌም እንደሚሆነው ከሰኔ አጋማሽ ጀምሮ በዚህ መስመር ከመንገድ ግራና ቀኝ ተንጣሎ ዓይን ያጠግብ የነበረው አረንጓዴ መሬት አሁን ተራቁቷል፡፡ አልፎ አልፎ ከሚታይ አረንጓዴ ግራር በቀር ሌላ ነገር የለም፡፡ በዚህ ወቅት ዝናብ የማያጣው ይህ መስመር በርሃ ቀመስ አየር ሆኗል፡፡ ከጥቂት ዓመታት በፊት ዋናውን ጐዳና ይዞ አልፎ አልፎ ይታይ የነበረው መጠነኛና በመሬት መንሸራተትና መሰንጠቅ የተፈጠረው አነስተኛ ክፍተት አሁን በእጅጉ እየሰፋ መምጣቱንም መታዘብ ይችላል፡፡ በአካባቢው ጉልህ ተፈጥሯዊ ለውጥ እየታየ ነው፡፡ የተከፋፈተው መሬት እየሰፋ በመሆኑ ወደ መንገዱ መግባቱ የማይቀር ይመስላል፡፡
በዚህ መስመር ይበልጥ የአየር ንብረት ለውጡ ምን ያህል የከፋ መሆኑን የሚያሳየው ዶዶታ ወረዳ ውስጥ ያሉ አምራች የሚባሉ ቀበሌዎች በሙሉ ቀስ በቀስ ለዝናብ እጥረት ሰለባ የመሆናቸው ጉዳይ ነው፡፡ እንደ አካባቢው አርሶ አደሮች ገለጻ፣ ‹‹ከጨው ውጭ ማንኛውም ነገር ብንዘራና ብንተክልበት ያበቅል ነበር፤›› የሚሉት መሬት ዘንድሮ በዝናብ እጦት መዝራት ባለመቻላቸው የዘሩትም ቢሆን በመቃጠሉ ችግር ውስጥ ከቷቸዋል፡፡ ዝናቡ መጣሁ መጣሁ በማለቱ ግን ለማንኛውም ብለው ነሐሴ መጀመሪያ ላይ እንደገና መሬቱን ገልብጠው ከማረስ አልቦዘኑም፡፡
እንደ ወትሮው ቢሆን በዚህ ወቅት በሬዎችን ጠምዶ ማረስ አይታሰብም፡፡ በዚህ ወቅት ደቦ ጠርቶ አረም የመንቀል፣ መድኃኒት የመርጨትና የመኮትኮት ሥራ ነበር የሚሠራው የሚለው አርሶ አደር ደገፋ ሁንዴ ዘንድሮ ነገሩ ሁሉ ተቀያይሮበታል፡፡
ሰሞኑን ለአንድ ቀን ብቻ በአጋጣሚ የጣለው ዝናብ የዘሩበትን መሬት ገልብጠው ዝናቡ ደግሞ ከጣለም ጤፍ ለመዝራት እንደሚሞክር ይገልጻል፡፡ ዝናቡ ካልመጣ ግን ባዶ እጃችን ቀረን ማለት ነው ይላል፡፡
የተፈጥሮ ነገር ሆኖ ከዶዶታ በጥቂት ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በምትገኘው የሒጦሳ ወረዳ ላይ ግን ዓይን የሚሞላ ልምላሜ ይታያል፡፡ ግራና ቀኝ ለጥ ያለው ሜዳ በስንዴ ሰብል ተሸፍኗል፡፡ የሒጦሳ ወረዳ ሻጊሸረር ገበሬ ማኅበር ነዋሪ የሆኑት አቶ ባይሳ ለገሠ ከጐጇቸው ጐን ባለው ማሳቸው ላይ ግንቦት 8 ቀን 2007 ዓ.ም. የዘሩት በቆሎ ለምልሞ ይታያል፡፡ ሲታይም ጥሩ ምርት የሚሰጥ መሆኑን ይናገራል፤ እንደ ዶዶታው በቆሎ ከንችሮ አልቀረም፡፡
የአቶ ባይሳ እርሻ ብቻ ሳይሆን በዙሪያ ገባው የሚታየው ማሳ አረንጓዴ ነው፡፡ ለወጪና ወራጁም ጥሩ ስሜት ይሰጣል፡፡ አቶ ባይሳ ስሜት ግን የዘሩት በቆሎ ከጨነገፈባቸው የዶዶታ ወረዳ ገበሬዎች ያልተለየ ነው፡፡ የአካባቢው ልምላሜ ጥሩ ምርት የሚገኝ መሆኑን የሚያሳይ ቢመስልም፣ በቆሎው ዝናብ አጥሮት ስለቆየ ፍሬ የሌለው መሆኑን ይናገራሉ፡፡
ዝናብ ስላልነበር ማደግ ያለበትን ያህል አላደገም፡፡ ከዚህ በኋላ ዝናብ ቢመጣ እንኳ አያፈራም፡፡ ‹‹የስንዴውም ነገር መጨረሻው አለየም፡፡ ከዘነበ ይብዛም ይነስም የተወሰነ ልናገኝ እንችላለን፤›› ብለው፣ ይህ ካልሆነ ግን ከዘንድሮ የምርት ዘመን ብዙ የማይጠብቁ መሆኑን ያስረዳሉ፡፡
በሳምንቱ መጀመሪያ ላይ ብቅ ያለው ዝናብ በዚህ ከቀጠለ ግን የዶዶታ ነዋሪዎችንና መደበኛ ዝናብ የተነፈጉ የአገሪቱ አካባቢዎችን ተስፋ ያለመለመ ነው ተብሎ ተገምቷል፡፡ የብሔራዊ ሚቲዎሮሎጂ ኤጀንሲ ዳይሬክተር አቶ ፈጠነ ተሾመ እንደገለጹት፣ በሐምሌ ወር የጠፋው ዝናብ አሁን መታየት በመጀመሩ በአጋጣሚው ተጠቅሞ ሊከሰት የሚችለውን ሥጋት መቀነስ ይችላል፡፡
ዝናቡ መጣል ከቀጠለ እንደ አቶ ጀማል ያሉ አርሶ አደሮች ከንችሮ የቀረባቸውን በቆሎ ገልብጠው በማረስ ቢያንስ ቶሎ የሚደርሱ እንደ ድንች ያሉ ምርቶችን መትከል እንደሚችሉ እየተጠቆመ ነው፡፡ የግብርናው ኃላፊ አቶ ጀማልም ዝናቡ ከመጣ የምንወስደው ዕርምጃ ይህንኑ ነው ይላሉ፡፡ ‹‹ቶሎ የሚደርሱ ምርቶችን እንዲተክሉ ማድረግ ውኃ እንዲይዙና ወደ ማሳ እንዲያስገቡ መገፋፋት ነው፤›› ብለው፣ ከሦስት ሳምንት በፊት በዚህ አካባቢ ጉብኝት ያደረጉት የግብርና ሚኒስትር ዴኤታው አቶ ወንድይራድ ማንደፍሮ አሳስበው የሄዱት ይህንኑ እንደሆነ አቶ ጀማል ተናግረዋል፡፡
ይጠበቅ የነበረው ዝናብ ምርት ከመንፈጉ ሌላ ከብቶቻቸውንም እየጐዳ ነው፡፡ በዚሁ ከቀጠለ የበለጠ ጉዳት ሊከሰት ይችላል፡፡ የዝናብ እጥረቱ በተለይ እንደ ሶማሌና አፋር የሚኙትን የአርብቶ አደር ከብቶች ጎድቷል፡፡ እንደ ዶዶታ ወረዳ ሁሉ በዘንድሮው የዝናብ እጦት በሰሜን፣ በምሥራቅና በደቡብ ክልሎች የሚገኙ ወረዳዎችን በእጅጉ ጐድቷል፡፡ በአፋር ክልል እስከ ሦስት ወራት የዘለቀው የዝናብ እጦት የብዙዎችን አርብቶ አደሮች ጐጆ አንኳኩቷል፡፡ በተወሰኑ ወረዳዎች አርብቶ አደሮቹ ዕርዳታ እንዲሰጣቸው ጠይቀዋል፡፡
በአርሲ ዞን ዶዶታ ያገኘናቸው ሴት አርሶ አደሮች እንደሚገልጹት ደግሞ የመኖ እጥረቱ ላሞቻቸው ወተት እንዳይሰጡ፣ ወተት ንጠው ቅቤ አውጥተው በመሸጥ ያገኙ የነበረውን ገቢ አስተጓጉሎባቸዋል፡፡
በአሰላ ያገኘናቸው ቅቤ ነጋዴም ከጥቂት ወራት ወዲህ የተሰቀለው የቅቤ ዋጋ ምክንያቱ የዝናቡ መጥፋት መሆኑን ይናገራሉ፡፡ ከሦስት ወራት በፊት ከገበሬዎች አንዱን ኪሎ ቅቤ እስከ 100 ብር ይረከቡ ነበር፡፡ አሁን ግን አቅርቦቱም ስለቀነሰ አርሶ አደሩ ለሚያመጣው ቅቤ የሚረከቡበት ዋጋ ከፍ በማለቱ፣ አንድ ኪሎ ቅቤ ከ260 እስከ 280 ብር እየተሸጠ ነው፡፡ በአሰላ ቅቤ እንዲህ ተሽጦ እንደማያውቅና የዝናቡ መጥፋት በወተትና በወተት ተዋፅኦ ላይ ጭምር ተፅዕኖ እንደፈጠረ ይገልጻሉ፡፡
በአርሶ አደሮቹ ደጃፍ የሚታየው የጭድ ክምር በበጋ ወቅት ለከብቶቻቸው የሚጠቀሙበት ነው፡፡ በክረምት ይህንን ክምር እምብዛም አይጠቀሙበትም፡፡ ዘንድሮ ግን በዝናብ መጥፋት ሳቢያ የግጦሽ መሬቱ ስለተጐዳ በዚህ ወቅት መድረስ የነበረበት በቆሎም ስለሌለ አርሶ አደሮቹ የጭዱን ክምር ከወዲሁ እየጨረሱት ነው፡፡
እንደ አርሶ አደር ደገፋ ገለጻም ዝናቡ አሁንም በበቂ ሁኔታ ካልዘነበ አማራጩ ይህ ክምር ብቻ ነው፡፡ ችግሩ ክምሩ ካለቀ ነው፡፡ ለከብቶች የሚሆን ሳር ስለሌለ አሁን እየተጠቀምን ያለው ከዚህ ቀደም ያከማቸነውን ጭድ ነው የሚሉት አርሶ አደር ጀማል፣ አሁን ግን አገዳው ስለሌለ ወደ መኖ ግዥ መግባታችን አይቀርም ይላሉ፡፡
እንደርሳቸው ገለጻ የዘንድሮው ችግር ሁሉንም የወረዳውን ቀበሌ አደረሰ እንጂ ችግሩ በይበልጥ መታየት የጀመረው አምና ነው፡፡ አምና በተወሰኑ ቀበሌዎች ተመሳሳይ የዝናብ እጥረት ቢታይም የዘንድሮው ግን ከፍቷል፡፡
የዝናብ እጥረቱ የዘር መዝሪያ ጊዜን ማስተጓጐል ብቻ ሳይሆን፣ በክረምት ይሞሉ የነበሩ ወንዞች የውኃ መጠን እንዲቀንስ ምክንያት ሆኗል፡፡ ክረምቱ እስኪያልፍና ወንዙ እስኪጐል የመስከረምን መጥባት የሚጠባበቁ የአንዳንድ አካባቢዎች ነዋሪዎች ዘንድሮ በክረምቱ ወራት ያለችግር እየተሻገሩበት ነው፡፡
በዝናብ እጥረት ተጐጂ ሆነዋል ከተባሉ የደቡብ ክልል ዞኖች ውስጥ የጉራጌና የስልጤ ዞን ይገኝበታል፡፡ በጉራጌ ዞን በክረምት አያሳጡም የሚባሉ ወንዞች ሳይቀሩ መጠናቸው በማነሱ ያለ ችግር በቀላሉ እየተሻገሩ መሆኑን ከአካባቢው የመጡ ነዋሪዎች ይገልጻሉ፡፡
ኤልኒኖ የፈጠረው ሥጋት በአርሶ አደሮችና አርብቶ አደሮች ላይ በሚያደርሰው ተፅዕኖ የተገደበ አይደለም፡፡ ለኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት መስተጓጐልም ምክንያት ስለመሆኑ በግልጽ ተናግሯል፡፡ አቶ ፈጠነ የዝናብ እጥረቱ ለመጠጥ ውኃም ሥጋት ሊሆን እንደሚችል ጠቁመዋል፡፡
የዝናብ እጥረቱ ወንዞች መያዝ የነበረባቸውን የውኃ መጠን መያዝ እንዳይችሉ በማድረጉ ለመስኖ ሥራ እንቅፋት ይሆናል፡፡ የዝናብ እጥረቱ በዚሁ ከቀጠለ ውኃ መያዝ የነበረባቸው ግድቦች በሚፈለገው መጠን ውኃ ስለማያከማቹ የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት ላይ ተፅዕኖ ያሳርፋል፡፡ በኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት ላይ ችግር እንዳይኖር ግን ዝግጅት እየደረገ ነው ተብሏል፡፡
አርሶ አደሩ በተገኘው አጋጣሚ ሊያገኝ የሚችለውን ያህል ውኃ እንዲያቅብ እየተደረገ እንዳለው ሁሉ መንግሥትም ጠብ የምትለዋን ውኃ በግድቦቹ ለመያዝ እየተሠራ ስለመሆኑ አቶ ፈጠነ አስታውሰዋል፡፡
በጠቅላላው የዝናብ መዛባቱ ለመጪው ዓመት የምርት መቀነስ ምክንያት መሆኑ እንደማይቀር በግልጽ ተነግሯል፡፡ ስለችግሩ መከሰት ቀደም ብሎ መረጃ የነበረው መንግሥት እየተዘጋጀ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡
በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ መግለጫ የሰጡት፣ በሚኒስትር ማዕረግ የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ሬድዋን ሁሴን በተፈጠረው የአየር መዛባት ሊከተል የሚችለውን ጉዳት በማሰብ መንግሥት ቀድሞ መዘጋጀቱን አረጋግጠዋል፡፡ በአፋርና በአንዳንድ አካባቢዎች የደረሰውን ጉዳትም ጠቅሰዋል፡፡
በመጋቢት ወር ዝናቡ ወጣ ገባ እያለ በነበረበት ወቅት የዝናብ እጥረት ሊኖር እንደሚችል በመተንበዩ በግጦሽ፣ በከብቶችና በምርት ላይ ተፅዕኖ እንደሚኖረው በመገመቱ አስፈላጊው ዝግጅት መደረጉን ገልጸዋል፡፡
በትንበያው መሠረት መንግሥት የዝናብ እጥረት ለገጠማቸው አካባቢዎች ጉዳቱ ሳይሰፋ ምላሽ እንደተሰጠ አስታውቀዋል፡፡ መንግሥት በአንዳንድ አካባቢዎች ለከብቶች የሚሆን መኖ እየቀረበ ስለመሆኑ የሚገልጹት አቶ ሬድዋን፣ ውኃና ምግብ እንዲቀርብ ለተጠየቀባቸው አካባቢዎችም ማቅረብ ግድ ስለመሆኑ ተናግረዋል፡፡
እንደ ሚኒስትሩ ገለጻ በተፈጥሮ መዛባት ምክንያት የተከሰተውን ችግር ለመሸከም የሚያስችሉ ዝግጅቶች መደረጋቸውን፣ በቂ የእህል ክምችት እንዳለና ከሥር ከሥር የእህል ግዥ እንደሚፈጸም አብራርተዋል፡፡
በሚቲዎሮሎጂ ኤጀንሲ ትንበያ መሠረት በተለይ በሐምሌ ወር የታየው የዝናብ እጥረት በነሐሴ መጀመሪያ ላይ እየተለወጠና እየተሻሻለ በመምጣቱ ሥጋቱ ይቀንሳል ይላሉ፡፡ እንደ ዶዶታ ባሉ አካባቢዎች በሐምሌ የተዘራው ስንዴና ገብስ አሁን ውኃ ካገኘ ሊበቅል እንደሚችል ይገልጻሉ፡፡ ዝናቡ በዚህ ከቀጠለ ዘግይቶም ቢሆን የተዘራው ሊደርስ ይችላል የሚሉት የትንበያ ባለሙያዎቹ፣ ችግሩ በኤልኒኖ ምክንያት ምርቱ በሚደርስበት ወቅት ዝናብ ሊዘንብ ስለሚችል ይህንን ዘግይቶ የሚደርስ ምርት በቶሎ መሰብሰብ ግድ የሚል መሆኑ ነው፡፡
አቶ ፈጠነም ይህንን ያረጋግጣሉ፡፡ የዶዶታው የግብርና ኃላፊ ግን እንዲህ ዓይነቱ ተስፋ ቢኖርም ውጤቱ ያን ያህል አርኪ ይሆናል የሚል እምነት የላቸውም፡፡
የግብርና ሚኒስቴር ችግሩ መኖሩን ከመግለጽ ባለፈ መደረግ አለባቸው ብለው ካስቀመጧቸው ነጥቦች ውስጥ ከክልል እስከ ቀበሌ ያሉ የግብርና ባለሙያዎች በየዕለቱ የሚደርሳቸውን የሚቲዎሮሎጂ ትንበያ በመከተል ተግባራዊ ማድረግ እንደሚገባቸው ነው፡፡
በተለይ ዝናብ ባጠራቸው አካባቢዎች በዘር ያልተሸፈኑ ማሳዎች ላይ ረዥም ጊዜ የሚወስዱ ምርቶችን ከመዝራት ይልቅ በቶሎ ሊደርሱ በሚችሉ፣ ድርቀትን በሚቋቋሙ ሰብሎች እንዲሸፈኑ አሳስበዋል፡፡ በዝናብ እጥረቱ የሚፈጠር የመኖና የውኃ አቅርቦት እጥረት ብቻ ሳይሆን ጐን ለጐን ሊከሰት የሚችለውን በሽታ ለመከላከልም የተሟላ መድኃኒት፣ የበሽታ መከላከያ ክትባት መዳረስ እንደሚኖርበት ማሳሰቢያ ተሰጥቷል፡፡
መንግሥት በምርት ዘመኑ ሊፈጠር የሚችለውን ችግር ለመቋቋም ለአጭር ጊዜ የሚውል የ700 ሚሊዮን ብር በጀት መድቦ እየንቀሳቀሰ ነው፡፡ የዝናብ እጥረቱ የምርት መጠን ላይ የሚያሳድረው ተፅዕኖ ምን ያህል ሊሆን እንደሚችል ከወዲሁ ሊታወቅና ሊገለጽ ባይችልም፣ በየቀበሌው ያሉ የግብርና ባለሙያዎች ግን መረጃ በማሰባሰብ ላይ ናቸው፡፡
በተጠናቀቀው የ2006/2007 የምርት ዘመን ከ270 ሚሊዮን ኩንታል በላይ የግብርና ምርት ተመርቷል፡፡ በ2007/2008 በጀት ዓመትም 304 ሚሊዮን ኩንታል ይመረታል ተብሏል፡፡ በዘር የሚሸፈነው መሬት ደግሞ 12.7 ሚሊዮን ሔክታር እንደሚሆንም ግብርና ሚኒስቴር ገልጿል፡፡