Friday, April 19, 2024

‹‹የትግራይ ሕዝብ የሥርዓቱ ተጠቂ እንጂ ተጠቃሚ አይደለም›› አቶ ዳዊት ገብረ እግዚአብሔር፣ ኢንቨስተር

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

በትግራይ ክልል በዓደዋ ከተማ ተወልደው እዚያው ያደጉት አቶ ዳዊት አባታቸው ቀኛዝማች ገብረ እግዚአብሔር አብርሃ በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዘመን የፓርላማ አባል ነበሩ፡፡ በቀድሞ የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዩኒቨርሲቲ ሥር የመምህራን ኮሌጅ አድቫንስድ ዲፕሎማ አግኝተዋል፡፡ የመሳፍንት ሥርዓት አቀንቃኝ አይዳለሁም ቢሉም ለንጉሡና ለራስ መንገሻ ሥዩም ከፍተኛ ክብር አላቸው፡፡ የአብዮቱ መፈንዳት ተከትሎ በአዲስ አበባና በባህር ዳር በኋላም በአስመራ በአስተማሪነት ለአጭር ጊዜ ከሠሩ በኋላ፣ ከአማፂዎቹ ጋር ግንኙነት መመሥረታቸው በመታወቁ ለግድያ ሲፈለጉ በሻዕቢያ አማካይነት ካርቱም ወደነበረው የሕወሓት ቢሮ እንዲሻገሩ ተደርጓል፡፡ ከዚያም ከሕወሓት ኃላፊዎች ጋር በመነጋገር ወደ አቡዳቢ (የተባበሩት ዓረብ ኤምሬትስ) የሚሄዱበት አጋጣሚ ተፈጥሮ፣ እዚያው አካባቢ ለትግሉ አስፈላጊውን ድጋፍ እያደረጉ የራሳቸውን ሥራ ጀምረው የግላቸው ኩባንያም አቋቁመዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ የንግድ እንቅስቃሴ እያደረጉ ይገኛሉ፡፡ በተለይ በቅርቡ ወደ ገበያ የገባው ራያ ቢራን በማቋቋም ግንባር ቀደም ሚና ተጫውተዋል፡፡ ፋብሪካው የ1.8 ቢሊዮን ብር ኢንቨስትመንት ሲሆን፣ 25 በመቶው የእሳቸው ድርሻ ነው፡፡ ከዚህ ቀደም ከሪፖርተር ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ አንዳንድ የመንግሥት ባለሥልጣናት ፋብሪካው እንዳይቋቋም እንቅስቃሴ ማድረጋቸውን ተናግረው ነበር፡፡ በስማቸው በተቋቋመው ግብረ ሰናይ ድርጅት ከ250 ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ በቋንቋ፣ በባህልና በታሪክ ላይ ለመሥራት በመቐለ፣ በዓደዋና በአክሱም ከተሞች ተንቀሳቅሰው በመንግሥት ባለሥልጣናት እንቅፋት እንዳጋጠማቸው ይናገራሉ፡፡ ‹‹ለአገሬ ያመጣሁትን ስጦታ እንኳን መቀበል አልቻሉም›› በማለት የሕወሓት አመራሮችን የሚወርፉት አቶ ዳዊት፣ በተለይ በክልሉ ተንሰራፍቷል የሚሉትን ሥርዓት አልበኝነት፣ የአመራር ድክመትና የዓላማ መዘንጋት ለመታገል ቆርጠው መነሳታቸውን ይናገራሉ፡፡ የትግራይ ሕዝብ ለሥርዓቱ ከፍተኛ መስዋዕትነት ቢከፍልም፣ በዚህ ዘመን ከመቼውም ጊዜ በላይ ለስደትና ለልመና ተዳርጓል ከሚሉት አቶ ዳዊት ገብረ እግዚአብሔር ጋር የማነ ናግሽ ቆይታ አድርጓል፡፡ 

ሪፖርተር፡- እዚህ ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉዎት ለትርፍ የሚሠራ የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴና የምግባረ ሰናይ ሥራዎችዎ ምን ይመስላሉ?

አቶ ዳዊት፡- የቢዝነስ እንቅስቃሴ እያደረግኩ እንጂ አተረፍኩ ማለት አልችልም፡፡ አንደኛው ኢንቨስትመንታችን የራያ ቢራ ነው፡፡ እሱም ገና ለትርፍም አልበቃም፡፡ ትርፋማ የሚባለው ትርፍ ሲገኝ ብቻ ነው፡፡ ከቢዝነሱ የበለጠ ደስታ የሚሰጠኝ ቢኖር የግብረ ሰናዩ ሥራ ነው፡፡ እሱ ዛሬ የጀመርነው አይደለም፡፡ በጽንሰ ሐሳብ ለተወሰነ ጊዜ ቢቆይም ፈቃድ የተገኘው የዛሬ ሦስት ዓመት ነው፡፡ ራያ ቢራ ኢትዮጵያ ውስጥ ትልቅ ኢንቨስትመንት ነው፡፡ በአካባቢው የሥራ ዕድል ፈጥሮ፣ ሰው ይብዛም ይነስም ይጠቅማል፡፡ ፋብሪካው ከተቋቋመ ጊዜ ጀምሮ እስካሁን ብዙ ሰዎች በተለያዩ የሥራ መስኮች ተሳትፈዋል፡፡ ከተቻለ ለቢራው ግብዓት የሚሆን እዚያው ለማምረትና ገበሬዎችን ተጠቃሚ ማድረግ ነው ዓላማችን፡፡

ዳዊት ግብረ ሰናይ በአሁኑ ጊዜ ከ50 በላይ የሚሆኑ ወላጅ የሌላቸውን ሕፃናትን ያሳድጋል፡፡ ትምህርት ቤት ይሠራል፣ ይደጉማል፣ ቤተ ክርስቲያን ይሠራል፣ ወይም ይጠግናል፡፡ ዋናው ዓላማው ግን የትግራይን ቋንቋ፣ ባህልና ታሪክ የሚጠናበትና የሚበለፅግበት መንገድ ማመቻቸት ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ከዚህ ግብረ ሰናይ ጋር በተያያዘ መቐለ፣ አክሱምና ዓድዋ ከተሞች ላይ አንዳንድ ፕሮጀክቶች ቀርፀው እንቅፋት እንደገጠመዎት ይነገራል፡፡ ጉዳዩን ሊያስረዱኝ ይችላሉ?

አቶ ዳዊት፡- መቐለ ላይ የታሰበው ፕሮጀክት የቋንቋና የባህል ትምህርት ቤት፣ እንዲሁም የወጣቶች መዝናኛ ማዕከል ነው፡፡ የዓደዋው ፕሮጀክት ከዓደዋ ድል ጋር በተያያዘ ሙዚየም ለመሥራት ነበር፡፡ አክሱም ካለው ታሪክ አንፃር የጥንት ፍልስፍናና ቅርስ ላይ ጥናትና ምርምር ለማድረግ ነበር፡፡ ለዚህ የቀሰቀሰኝ አንድ ጊዜ መቐለ ላይ ሄጄ ወጣቱ ጊዜውን እንዴት እንደሚያሳልፍ ካየሁ በኋላ ነው፡፡ አንድ ቤት ኮፊ ሐውስ ነው፣ ቀጥሎ ያለው ከረምቡላ ቤት ነው፣ ሌላኛው ባር ነው፡፡ እንደዚያ እያለ ነው የሚሄደው፡፡ ወጣቶች በእነዚህ ቤቶች ነው የሚያሳልፉት፡፡ ሁለተኛ ቋንቋችን በተመለከተ ያለው ውድቀት ነው ያነሳሳኝ፡፡ እያንዳንዱ ሱቅ ላይ የምታየው እንኳ በአማርኛ ነው የተጻፈው፡፡ በአማርኛ የሚጻፍበት ምክንያት አልገባኝም፡፡ አገሪቷ በሙሉ በአማርኛ ብቻ መጻፍ አለበት የሚል ፖሊሲ አላየሁም፡፡ ትግራይ ራሱን የቻለ መንግሥት ነው፡፡ የተታገለውም የራሱ አስተዳደር ለመፍጠር ነው፡፡ እንደዚያ ከሆነ እንግዲህ ቅድሚያ መስጠት ያለበት ለራሱ ነው፡፡ እንግዲህ የማየው ነገር በሙሉ ከትግሉ ዓላማ ጋር የሚፃረር ነው፡፡

እንግዲህ የመቐለ ፕሮጀክት ሐሳቡ ተፀንሶ ከሚመለከታቸው አካላት በተደጋጋሚ ተነጋግረንበት ቦታ ከመረጥን በኋላ፣ እንፈራረም ብለው ጠርተውኝ ስንሄድ ‹‹ሠርታችሁ ለእኛ ካላስረከባችሁ አንፈቅድም›› የሚል ነው፡፡ ሠርተን ማንም ሊያስተዳድረው አልነበረም ዓላማው፡፡ ከመሥሪያው ጀምሮ የሚካሄድበት በጀትም ተቀምጦለታል፡፡ ያንን ፕሮጀክት ሠርተን ለእነሱ ብንሰጣቸው አንደኛው ዓላማውም አይገባቸውም፡፡ እኛ በቀየስነውና ባለምነው መንገድ ሊያስኬዱት አይችሉም፡፡ ሁለተኛ ለፕሮጀክቱ የተቀመጠ በጀትም የለም፡፡ እንግዲህ ተመላልሰን መፍትሔ ማግኘት አልተቻለም፡፡ አክሱም ቦታ ምረጡ ብለውን ከመረጥን በኋላ ወደ ክልል ተወስዷል አሉን፡፡ እዚያው ድረስ ሄደን በተደጋጋሚ ብንጠይቅ መልስ ማግኘት አልቻልንም፡፡

የዓደዋም እንደዚሁ ቦታውን በሊዝ ወስደን በኋላ የሙስና ነገር ሊኖረው ይችላል በሚል ለአንድ ዓመት እንዲጣራ በማለት ካጓተቱት በኋላ እንግዲህ የተገኘ ሙስናም የለም፡፡ ባይሆን የወሰድነው መሬት የሕዝብ ነው፣ የምንሠራውም ለሕዝብ ነው፣ በነፃ ሊሰጠን ይገባ ነበር ወይ? የሙስና ትርጉም አልገባቸውም ወይም ሆን ብለው የፈጠሩት እንቅፋት ነው፡፡ ዋናው ዓላማውም እኔን አናደው ሥራውን እንዳቆመው ነበር፡፡ ሥራው ተደናቅፏል፡፡ ለሦስት ዓመት የከፈልንበት ሊዝም መልሰውታል፡፡ ገንዘባችንን ግን አልመለሱልንም፡፡ ስለሆነም እነሱ ባሉበት አልሄድም፡፡ ክርክር ላይ ነው ያለነው፡፡      

ሪፖርተር፡- በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች በሪዞርትና በሌሎች ሥራዎች እየተንቀሳቀሱ ይገኛሉ፡፡ በክልሉ የተለየ እንቅፋት አይተዋል?

አቶ ዳዊት፡- በመሠረቱ እነዚህ ሰዎች እዚያ ቦታ ላይ ለምን ቁጭ እንዳሉ ማወቅ ያለባቸው መሰለኝ፡፡ እነሱ የሕዝብ አገልጋዮች እንጂ በሕዝብ ተገልጋዮች አለመሆናቸውንም ማወቅ ነበረባቸው፡፡ እዚያው ቦታ የተቀመጡት ክልሉን በኢኮኖሚ ለማልማት ነው፡፡ ልማት ለማምጣት ደግሞ እኔን የመሰሉ ሰዎች ፈልገው፣ ለምነው ወደ አገር ቤት ማስገባት ነበረባቸው፡፡ እኔ እስከማውቀው ድረስ እንኳንስ ለትርፍ ተብሎ የታሰበ ኢንቨስትመንት ይቅርና ይህንን ለአገሬ የሰጠሁትን ስጦታ እንኳን ለመቀበል ፍላጐት የላቸውም፡፡ ከምን የተነሳ ነው የሚል ጥያቄ ከተነሳ አንደኛው የፖሊሲው ድክመት ነው፡፡ እኔ አለሁልህ፣ ልጄ አትሥራ ዓይነት ነገር ነው፡፡ ሕወሓት የሚሠራው ካልሆነ ሌላው እንዲሠራ አይፈለግም፡፡ እነሱ ያልሠሩትን የምትሠራ ከሆነ ደግሞ የበለጥካቸው ስለሚመስላቸው እንዲሠራ አይፈልጉም፡፡ እኔ እነሱን ለመብለጥ ሳይሆን፣ ጉድለቱን ለመሙላት ነበር፡፡ ቢሠሩት ኖሮማ እንደዚህ ዓይነት ሥራ ውስጥ አልገባም ነበር፡፡ መቐለ ወጣቱ የሚውልበት ምን ዓይነት ፓርክ ወይም ላይብረሪ ነው ያለው? እነሱ ይህንን ማድረግ አልቻሉም፡፡ በግለሰብ ደረጃ ሲደረግ ስድብ መስሎ ነው የተሰማቸው፡፡

ከኢንቨስትመንት ጋር በተያያዘ ግን እኔ ትግራይ ውስጥ ኢንቨስት አላደረግኩም፡፡ ራያ ቢራ ደግሞ የእኔ አይደለም ሼር ካምፓኒ ነው፡፡ እዚህ ላይ ግን ማስቀመጥ የምፈልገው ራያ ቢራ እንዳይቋቅም የሕወሓት ባለሥልጣናት ታጥቀው የተነሱበት ድርጅት ነው፡፡ በቀጥታ ብቻ ሳይሆን ከእነሱ ጋሻ ጃግሬዎች ጭምር ነው፡፡ ትግራይ ውስጥ ያሉት ባለሀብቶች ሼር እንዳይገዙ ትዕዛዝ ተላልፎላቸዋል፡፡ በዚህ እልህ ነው ሼር እንዲገዛና እንዲያልቅ ያደረግኩት፡፡ ለራያ ቢራ መሥራቾች የተነገራቸው በአካባቢው የሚፈለገው ጠርሙስ ፋብሪካ እንደነበር ነው፡፡ ይኼው እስካሁን አልተሠራም፡፡ የሕዝብ ገንዘብ ይዘውት ቁጭ ብለዋል፡፡ ስለዚህ ራያ ቢራ ፋብሪካ የ1.8 ቢሊዮን ብር ፕሮጀክት እንዲሠራ አልፈለጉም ነበር፡፡ እንግዲህ ይህንን እንደዚህ ካሉ ሌላው እንዴት ነው እንዲሠራ የማይፈቅዱት? የትግራይ ሕዝብ ኑሮው ምን ላይ የተመሠረተ ነው? ገቢው ከየት ነው? ከእርሻ ነው? ከሁመራ በስተቀር ትግራይ ውስጥ ለእርሻ የሚውል መሬት አለ? ፋብሪካና ማዕድን ትግራይ ውስጥ የሉም፡፡

ምናልባት መቐለ ላይ እዚህም እዚያም ብቅ ብቅ የሚሉ ቪላዎች አይቶ ሰው መቐለ አደገች ተመነደገች የሚባለው ነገር አለ፡፡ እነዚህ ቤቶች በዳያስፖራ የተሠሩ ናቸው፡፡ ተመሳሳይ ቪላዎቹ አዲስ አበባ ውስጥ 50 ሺሕ 60 ሺሕ ብር የሚከራዩ ናቸው፡፡ መቐለ ላይ ግን ተመሳሳይ ቪላዎች 3 ሺሕ፣ 4 ሺሕ ብር ቢከራይ ነው፡፡ እሱም ተከራይ ከተገኘ ነው፡፡ እሱን መክፈል የሚያስችል አቅም ያለው ነዋሪ የለም፣ ገቢ የለውማ፡፡

ሪፖርተር፡- ለዚህ ሥርዓት መጠንሰስ ከመጀመርያው ተሳታፊ ነበሩ፡፡ አንድ ወንድምዎን (ሐየት) እና ሁለት እህቶችዎን (ርግበና አልማዝ) በትግሉ አጥተዋል፡፡ ከቤተሰብዎም በርካታ ሰዎች መስዋዕት ሆነዋል፡፡ ሕወሓት የተነሳበት ዓላማውን ሰቷል የሚል አቋም አለዎት?

አቶ ዳዊት፡- በእርግጠኝነት አዎ! እኔ አንዲት ዓረፍት ነገር ተናገርኩ እንጂ፣ እኔ በአይጋ ፎረም ከተናገርኩ በኋላ ሕዝቡ ምን እያለ ነው? በማኅበራዊ ሚዲያ የሚጻፈውን አይተሃል? እኔ በተናገርኳት ጫፍ ትግራይ ውስጥ ምን ዓይነት ስሜት ፈጠረ ነው ጥያቄው፡፡ እንግዲህ ስለ ትግሉ ካነሳን ብረት የተሸከመ ሁሉ ታገለ ማለት አንችልም፡፡ ሜዳ የወጣ ሦስት ዓይነት ሕዝብ ነው፡፡ አንደኛው የደርግ ግፍ አንገፍግፎት ከዚያው ለመሸሽ ሲል ሜዳ የገባ አለ፡፡ ትግሉን አምኖበት አይደለም፡፡ ሁለተኛው ጓደኛው ስለሄደ ፋሽን ሆኖበት የሄደ ይኖራል፡፡ ሦስተኛ ዓላማውን አምኖበት የወጣ ይኖራል፡፡ ሕወሓት ደርግን አሸንፎ አዲስ አበባ ሲገባ አንዱን ከሌላው መለየት አትችልም፡፡ ጦርነት ሜዳ ውስጥ ከገባህ ደግሞ ገድለህ ራስህን ታድናለህ ወይም ትገደላለህ፡፡ ስለዚህ ጦርነት ውስጥ አልነበሩም ማለት አይደለም፡፡ እያነጋገረን ያለው የዓላማና የእምነት ጉዳይ ነው፡፡ ከዚያ በኋላ ወደ አገር ስትመለስ ግን ትግሉን አምኖበት የገባ፣ ሕዝቡን ወደ ተሻለ ደረጃ ከፍ ለማድረግ፣ ሕወሓት የተመሠረተበት ዓላማ ላይ ፀንቶ የተመለሰ ካለ አሁንም በእምነቱ የፀና ታጋይ ነው፣ ሕዝብ ነው፡፡ ሌላው በጥባጩ ማን ነው ብለን ስንጠይቅ መልሱ ከተማ እንደገባ ራሱንና ቤተሰቡን ለማደራጀት ሲያስብ የነበረው ነው፡፡ ቅድም ካስቀመጥኩልህ ከሦስቱ ሁለቱ ናቸው አሁን አልፎ አልፎ የምናያቸው፣ ሥልጣን ላይ ያሉት፡፡ ለግል ክብር ሲሉ የተሰጣቸውን ኃላፊነት ትተው የራሳቸውን ማንነት ሲያዳብሩ እናያለን፡፡ ትግራይን ለማገልገል እኮ የትምህርት ደረጃ አያስፈልገውም፡፡ በአሁኑ ጊዜ ትግራይ ውስጥ ያሉት ባለሥልጣናት የትኞቹ ነበሩ ብለህ ብትጠይቀኝ ከሦስቱ ሁለቱ ነበሩ ብዬ ነው የማምነው፡፡ አልያማ ሕዝብን የሚጠቅም ጠፍቶባቸው አይደለም፡፡ ራስ መንገሻ ሥልጣን ላይ ቁጭ ብለው መንደላቀቅ ጠፍቶባቸው አይደለም፡፡ ለሕዝብ ብለው ነበር ራሳቸውን ታች በረሃ ወርደው ድንጋይ ሲገፉና ሲቆፍሩ የምናያቸው የነበረው፡፡ አሁን ያሉት ግን ምን ዓይነት ናቸው? እውነት ለሕዝብ ብለው ለዓላማ የወጡ ነበሩ ወይ ብትለኝ አይደሉም ብዬ ነው የምደመድመው፡፡         

ሪፖርተር፡- እዚህ ድምዳሜ ላይ የደረሱት በእርስዎ ላይ በደረሰ ችግር የተነሳ  ይሆን? ወይስ የሥርዓቱ መገለጫ መሆኑን አምነውበታል?

አቶ ዳዊት፡- በእኔ ላይ የደረሰ በተጨባጭ አፌን ሞልቼ እንድናገርና እምነቴ ላይ ቆሜ ሥርዓቱን እንድታገለው አደረገኝ እንጂ የምሰማው ብዙ ነው፡፡ ለዚህም ነው ከጥቂት ሆቴሎች በስተቀር ትግራይ ውስጥ አንድም ሰው መሥራት የማይፈልገው፡፡ ምን ዓይነት በደል ቢደርስባቸው ነው የሚለው እነሱን መጠየቅ ነው፡፡ የትኛው ኢንቨስተር ነው ትግራይ ሂዶ የተመቻቸ ሁኔታ ተደርጎልኛል ብሎ የሚናገረው? ጀምሮ ወይም አቋርጦ የወጣ ካልሆነ በስተቀር፡፡ በተባለ ሳይሆን እኔ ራሴ ላይ የደረሰውን ነው እየተናገርኩ ያለሁት፡፡ ግብረ ሰናይ የመሰለ ስጦታ መቀበል ያልፈለገ መንግሥት የትኛውን ኢንቨስትመንት ነው መቀበል የሚችለው? ይኼ አሳሪ የሆነ አንድ ለአምስት የሚባል ሥርዓት የተዘረጋው ለሕዝቡ ታስቦለት ሳይሆን፣ ሕዝቡን እንዴት ልሰረው ተብሎ የመጣ ነው፡፡ አፉ እንዳይናገር፣ ዴሞክራሲያዊ መብቱን እንዳይጠቀም፣ እንዲታፈን የሚያደርግ ነው፡፡ ትግራይ ውስጥ ሰላም አለ የሚባለው ውሸት ነው፡፡ ሰላም የለም፡፡ ሰላም ቢኖር በየቀበሌው ሚሊሻ ታጥቆ የሚኖረው ከማን ሊያድነኝ ነው? እጅህን አንሳ እየተባለ የሚጠብቅ? ወይስ እኔ ከሌለሁ ሰላም የለም በማለት አስፈራርቶ ለመግዛት እንዲመቸው ነው፡፡    

ሪፖርተር፡- እዚህ ላይ ላቋርጥዎትና ጥያቄ ላንሳ፡፡ አንደኛ ሥርዓቱ በተለይ የትግራይን ሕዝብ ከሰው በላው ከደርግ ሥርዓት የገላገለ መሆኑ ይታወቃል፡፡ ሁለተኛ ባለፉት 24 ዓመታት በሕዝቡ እየተመረጠ ሥልጣን ላይ የቆየ ሥርዓት ነው፡፡ አሁን ከሚናገሩት ጋር እንዴት አብሮ ይሄዳል?

አቶ ዳዊት፡- መልሼ አንተን ልጠይቅህ፡፡ ደርግ ጨቋኝ ነበር ብለኸኛል፡፡ ደርግ ጨቋኝ ያደረገው ማን ነው? ገዳይ እንዲሆን ያደረገው ምንድነው? ወይስ እግዚአብሔር ሲፈጥረው ገዳይ አድርጎ ነው የፈጠረው? ለመሆኑ ደርግን አጠፋን እንላለን? ደርግንስ የፈጠረው ማን ነው? እሱ ሌላ ጥያቄ ነው፡፡ አንተ ተፈላሰፍበት፡፡ እኔ ግን የማወዳድረው ደርግንና ኢሕአዴግን አይደለም፡፡

ሪፖርተር፡- ከሰላም አንፃር ነው የእኔ ጥያቄ?

አቶ ዳዊት፡- ቆየኝ…ሰላምም የነበረው በጃንሆይ ጊዜ ብቻ ነው፡፡ ያኔ ቀበሌ የሚባል አልነበረም፡፡ የቀበሌ ጠባቂ አልነበረም፡፡ ሚሊሻ የሚባል አልነበረም፡፡ ሰላም ሁለት ዓይነት ነው፡፡ አንደኛው የውጭ ሰላም፣ ጦርነት የሌለበት ነው፡፡ ሁለተኛው የውስጥ ሰላም ነው፡፡ የትግራይ ሕዝብ የውጭ ሰላም አግኝቷል፡፡ ጦርነት የለም፡፡ በጃንሆይ ጊዜም ጦርነት አልነበረም፡፡ በደርግ ጊዜ ጦርነት ነበር፡፡ ደርግን የፈጠረው ማነው? እኛ ነን የፈጠርነው፡፡ ያጠፋነው ደግሞ እኛው፡፡ ደርግ ለሥልጣኑ ተቀናቃኝ መጣበት፡፡ በሥልጣኑ ላይ ለመቆየት ደግሞ የሚቻለውን ያህል ገደለ፡፡ ትክክል ነው ማለት አይደለም፡፡ ብዙ ግፍ ሠርቷል፡፡ በጃንሆይ ጊዜም እንቅስቃሴዎች ሲጀመሩ በዚያን ወቅት ወጣቶች ተገድለዋል፡፡ እነ ጥላሁን ግዛው ተገድለዋል፡፡ በኢሕአዴግ ጊዜ ደግሞ የ97ቱን ስናነሳ ትክክል ነው አይደለም ሌላ ጉዳይ ነው፡፡ አሁን አዲስ አበባ ያለው ጎረምሳ ተነሥቶ መንግሥት እገለብጣለሁ ቢል ኢሕአዴግ አይገድልም? ስለዚህ በደርግ በአንድ በኩል እገነጠላለሁ የሚል በኤርትራ በኩል ተነስቶበታል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ በትግራይ ውስጥ ሕወሓት ተነስቶበታል፡፡ ደርግ ምን ማድረግ ነበረበት? በዚያን ጊዜ እንኩላችሁ ብሎ መልቀቅ ነበረበት? እንደ ራሱ ቢያደርግ አሁን የምናውቃት ኢትዮጵያ ትኖር ነበር? ስልህ በምን ምክንያት በምን አካሄድ ካልሆነ በስተቀር የተሰጠውን ኃላፊነት ለመወጣት ሲል ማንም ሰው የሚያደርገው ነው፡፡ እናስብ ደርግን ሥልጣን ከያዘ በኋላ ኢሕአዴግ፣ መኢሶን፣ ሕወሓት፣ ሻዕቢያ ባይኖሩ ገዳይ ይሆን ነበር?

ስለዚህ እሱ ከደርግ ገላገለን የሚለው ጥሩ ሽፋን አይደለም፡፡ ጥሩ ከደርግ ገላግሎናል፡፡ የደርግ ሥርዓት ምንም ተቀናቃኝ ባያጋጥመው አሁን ኢትዮጵያ ምን ትሆን ነበር ብለህ ብትጠይቀኝ መገመት አልችልም፡፡ በዚያን ጊዜ የነበሩ ምሁራን ግን ይበልጣሉ፡፡ የጃንሆይ ፍሬዎች አዋቂዎች ነበሩ፡፡ በዚያ ጊዜ እስካሁንም ድረስ ያሉት ጎበዝ ኢንጂነሮች የጃንሆይ ፍሬዎች ናቸው፡፡ አዲስ አበባ የምታየው ቸርችል ጎዳና ፈረንሳይን [ፓሪስን] ለማስመሰል ነበር ዓላማው፡፡ ብዙ የታቀደ ዕቅድ ነበር’ኮ፡፡ ያኔ እኮ ኮሜርሻል ፋርሚንግ ነበር፡፡ ጀርመን ለመሄድ’ኮ ቪዛ አያስፈልግም ነበር፡፡ በጃንሆይ ጊዜ’ኮ ስደት አልነበረም፡፡ ተምሮ ይመለሳል እንጂ እዚያ እቀራለሁ የሚል ዜጋ አልነበረም፡፡ ስለዚህ ያነሳኸው አከራካሪና አነጋጋሪ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- እንደዚያ ከሆነ በጃንሆይ ጊዜ ታላቁ አብዮት ለምን ተነሳ? በደርግ ጊዜስ ያ ሁሉ አመፅ ለምን ተነሳ? ሥልጣን ላይ የቆው ኢሕአዴግ በተለይ ደግሞ ሕወሓት ግን ላለፉት 24 ዓመታት እየተመረጠ ነው ሥልጣን ላይ የቆየው ነው የሚባለው፡፡ አለበለዚያ ለምን አሁን ሥልጣን ላይ ያለው ሥርዓት ተመሳሳይ ተቃውሞ አላጋጠመውም? እንደዚያ ከሆነ ለምን ፀጥ ያለ ነገር እናያለን?

አቶ ዳዊት፡- በመጀመሪያ ነገር የምትናገራቸው ነገሮች እውነትነት የላቸውም፡፡ ማንንና ማን ነው እያወዳደርን ያለነው? በዚያን ጊዜ ማን ነበር? አሁን ማን ነው ያለው? እንግዲህ ንገረኝ ካልከኝማ፣ በጃንሆይ ጊዜ ትምህርት ቤት ጠዋት ጠዋት ወተት ነበር የምንጠጣው፡፡ በንግሥተ ሳባ በዚያን ጊዜ የነበረው የትምህርት ጥራት ተወው፡፡ ሦስተኛና አራተኛ ክፍል ሆነን ኮምፖዚሽን (በእንግሊዝኛ) እንጽፍ ነበር፡፡ የአሁኑ ዩኒቨርሲቲ ያጠናቀቀ ተማሪ እንደዚያ መጻፍ አይችልም፡፡ ምርጫ የምትለውም አባቴ በጃንሆይ ጊዜ ነው በዓደዋ የተወዳደረው፡፡ [የቀኛዝማች ገብረ እግዚአብሔር አብርሃ የምረጡኝ ቅስቀሳ የያዘ ፖስተር አውጥተው እያሳዩ] አሁን የትኛው የፓርላማ አባል ነው ይህንን ዓይነት የምረጡኝ ቅስቀሳ የሚጽፍ? የተጻፈውን እየው፡፡  

ሪፖርተር፡- የአገሬው ሰው የሚያውቀው ከኤርትራ በብዙ ሺሕ የሚቆጠሩ ወጣቶች ወደ ኢትዮጵያም ጭምር መሰደዳቸውን ነው፡፡ ለአይጋ ፎረም በሰጡት ቃለ ምልልስ ‹‹ከትግራይ የሚሰደድ ወጣት አይበልጥም ወይ?›› ብለዋል፡፡ ምን ማለት ነው?

አቶ ዳዊት፡- እኔ የተናገርኩት ሳይሆን ራሱ መስተዳደሩ የተናገረው ነው፡፡ ከሳዑዲ ብቻ የተመለሰ፡፡ ባህር አቋርጦ፣ ሕይወቱን ሰውቶ፣ በየበረሃና በየባህሩ ሳዑዲ የገባ፣ በበረሃውም ሆነ በሳዑዲ ከተያዙት የትግራይ ብቻ 30 ሺሕ ነበር፡፡ ሱዳን ውስጥ በስደት ላይ ያለው የትግራይ ተወላጅ ስንት ነው? ደቡብ አፍሪካ ውስጥ፣ ኬንያ ውስጥ ያለው የትግራይ ስደተኛ ስንቱ ነው? አውሮፓ ውስጥ ያለው ስደተኛ ስንት ነው? በረሃ ላይ ታርዶ ኩላሊቱ ወጥቶ የቀረው ስንት ነው? እዚሁ አዲስ አበባ በልመና ላይ የተሰማራው ስንት ነው? አንድ መንግሥት ሕዝብን መራሁ ብሎ የሚኩራራው እኮ በቅድሚያ ለወጣቱ ነገሮችን አመቻችቶ ከስደት ሲታደግ ብቻ ነው፡፡ በደርግ ጊዜ የተሰደደው ማንም ኢትዮጵያዊ ሕይወቱን ለማዳን ነው፡፡ በአሁኑ ጊዜ እየተሰደደ ያለው ግን ሕይወቱን ለመምራት ብሎ ነው፡፡ የሚበላ የሚጠጣ አጥቶ ነው፡፡ ትዳር ይፈልጋል፡፡ መኖር ይፈልጋል፡፡ ይህንን ማድረግ ስላልቻለ ነው ስደት እየሄደ ያለው፡፡ ከጦርነት ለመሸሽ አይደለም፡፡ ይህንን ማድረግ ያልቻለ መንግሥት በምንድነው የሚኩራራው?

ሕዝቡ አሁን በውኃ ጥም እየተገረፈ ነው ያለው፡፡ ሕወሓት ሥልጣን ላይ እያለ ስንት ዓመቱ ነው? 24 ዓመት ሙሉ ሥልጣን የያዘ አንድ መንግሥት ንፁህ ውኃ ማቅረብ ካልቻለ እስከ መቼ ነው ተሸክመኸው የምትሄደው? ዩኒቨርሲቲ ተከፈተ ይባላል፡፡ ትግራይ ውስጥ መቐለ ዩኒቨርሲቲ፣ አክሱም ዩኒቨርሲቲና የመሳሰሉት አሉ፡፡ ምን ዓይነት ለውጥ አመጡ? ከዩኒቨርሲቲ ተመርቆ ድንጋይ መፍለጥ ከሆነ ወይም ከብት ማርባት ከሆነ እንግዲህ ማስተርሱን ጨርሶ ሁለትና ሦስት ከፍታ እየጠበቀ በቴሌቪዥን ሲታይ ምን ዓይነት ብክነት ነው? ይኼ እኮ የአገር ሀብትን ጉድጓድ ውስጥ እንደመጣል ነው፡፡ ዩኒቨርሲቲ’ኮ የሚሠራው ከሕዝብ በግብር በተሰበሰበ ገንዘብ ነው፡፡ ሰው ተምሮ ቁም ነገር እንዲሆን እንጂ ኮብልስቶን እንዲሠራ አይደለም፡፡ ኮብልስቶን ለመሥራት፣ አምስት ከብቶችን ለማርባት ዩኒቨርሲቲ ውስጥ መግባት አያስፈልግህም፡፡ እኛ እያነጋገረን ያለው ይኼ ነው፡፡  

ሪፖርተር፡- በአንዳንድ የግል ሚዲያዎችና በማኅበራዊ ሚዲያዎች የትግራይ ሕዝብ የሥርዓቱ የተለየ ተጠቃሚ እንደሆነ ነው የሚጻፈው፡፡

አቶ ዳዊት፡- ማንም ሰው የመሰለውን ሊያወራ ይችላል፡፡ ግን አይቶ ነው ያወራው ወይስ በአሉባልታ ነው? መጠየቅ ያስፈልጋል፡፡ የትግራይ ሕዝብ የሥርዓቱ ተጠቂ እንጂ ተጠቃሚ አይደለም፡፡ ይኼንን የምለው ያለምክንያት አይደለም፡፡ የትግራይ ሕዝብ ተጠቃሚ የሚሆንበት ምን አለው? በተፈጥሮ ካየነው ከዓለም አሉ ከሚባሉ ደሃ አገሮች አንዷ ኢትዮጵያ ናት፡፡ በተጨባጭ የምናየው ደግሞ ትግራይ በኢትዮጵያ ካሉት ክልሎች ደሃ ናት፡፡ የድህነት መነሻው ብዙ ነው፡፡ አንደኛው ለብዙ ዓመታት የጦርነት አውድማ ሆና ስለቆየች፡፡ ጦርነት ማለት ውድመት ማለት ነው፡፡ በአፄ ዮሐንስ፣ በአፄ ምንሊክ፣ በአፄ ኃይለ ሥላሴ፣ በደርግና በኢሕአዴግም ጊዜ ትግራይ የጦርነት አውድማ ሆና ነው የቆየችው፡፡ ሁለተኛ ተፈጥሮአዊ አቀማመጥ ነው፡፡ ለእርሻ አመቺ አይደለም፡፡ ድንጋያማ አካባቢ ነው፡፡ ስለዚህ መሬቷ ለእርሻ አመቺ ሆኖ ለኮሜርሻል ፋርሚንግ ትርፋማ በመሆን ገቢ ለማግኘት አቅም የላትም፡፡ ሦስተኛ በመስተዳድሩ ባለው ጠባብ አስተሳሰብ የተነሳ ፋብሪካዎች የሉም፡፡ ኢንዱስትሪዎችም ማዕድናትም የሉም፡፡ የትግሉ መነሻ ሆና ሳለ፡፡ በግልጽ ደግሞ ስንት የክልሉ ተወላጅ በትግሉ ጊዜ ሜዳ ላይ እንደቀረ የሚታወቅ ነው፡፡ መቁጠር የማይቻለው ደግሞ ብዙ መስዋዕትነት የከፈለ ሕዝብ ነው፡፡ የለውጡ ተጠቃሚ ግን አይደለም፡፡

እንግዲህ የተለያዩ ክልሎች የራሳቸውን መስተዳደር መሥርተው የሥርዓቱ ተጠቃሚ ናቸው፡፡ በአሁኑ ጊዜ ኢትዮጵያ 11 በመቶ አደገች ብለን እናወራለን፡፡ ትክክል ነው፡፡ የተለያዩ ተቋማት የመሰከሩለት ስለሆነ ጥያቄው የኢትዮጵያ ዕድገት ሁለት አኀዝ ነው እያልን የምናወራ ከሆነ፣ ትግራይስ በዚያ ደረጃ አድጋለች ወይ? መልሱ አይደለም ነው፡፡ ትግራይ ያደገችው በግማሽ ፐርሰንት ነው፡፡ እንዲያውስ ማደግ ቀርቶ አሉታ ነው ከተባለ የኢትዮጵያ ዕድገት ትግራይን አይገልጽም ማለት ነው፡፡ ትግራይ አደገች የምንል ከሆነ ደግሞ ስንት በመቶ? ከምን የመነጨ? ብለን መጠየቅ አለብን፡፡  

ሪፖርተር፡- እንግዲህ የችግሩ መነሻ በአብዛኛው የተፈጥሮ ጉዳይ ከሆነ መንግሥት በክልሉ የተለየ ፖሊሲ መከተል ነበረበት ነው ወይስ…?

አቶ ዳዊት፡- የአንድ መንግሥት ኃላፊነት ልማትን ማጣጣም ነው፡፡ ኋላቀር የሚባሉ ክልሎች አሉ፡፡ የተለየ ድጎማ ይደረግላቸዋል፡፡ እንግዲህ ያንን ነገር ለትግራይ ታሳቢ መሆን አልነበረበትም? በእኩልነት የምንተያይ ከሆነ? እንግዲህ በአንድ አገር የሀብት ክፍፍል ጥያቄ የሚነሳ ከሆነ፣ የትኛው አካባቢ በምን ይልማ የሚል ፖሊሲ ይወጣና በእርሻ ማደግ የሚችለውን በእርሻ፣ የማዕድን ቦታ ከሆነ በማዕድን እንዲያድግ ይደረጋል፡፡ በእነዚህ ተጠቃሚ ያልሆነ ደግሞ በሌላ መንገድ እንዲካስ ይደረጋል፡፡ የትግራይ ሕዝብ አብዛኛው የሚኖረው ከውጭ በሚመጣ የሐዋላ ገቢ ነው፡፡ ቅድም ያልናቸው በየቦታው የሚሠሩት ሁሉም ቤቶች የዳያስፖራ ናቸው፡፡ ከትግራይ ውጪ ያለው የሠራው ነው፡፡ አንድ ቀን ከተመለስኩ ብሎ የሚሠራው፡፡ ስለዚህ ሌላ አወራ ተብሎ አይወራም፡፡ ወሬ ወሬ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ምናልባት የብቃትና የአቅም ችግር ኖሮበት ከሆነ፣ ሕውሓት እንደ ድርጅት የቀደሙት አመራሮቹን በሌላ አዲስ አመራር እየተካ እንደሆነ ይናገራል፡፡ ምናልባት ከአዲሱ አመራር የለውጥ ተስፋ አያደርጉም?

አቶ ዳዊት፡- የችግሩ ምንጭ ግለሰቦች ናቸው ወይስ ፖሊሲው? የሚል ነገር ነው መታየት ያለበት፡፡ መተካካት የሚባለው ሰውን በሰው መተካት ማለት አይደለም፡፡ የማይሠራውን ፖሊሲ ጭምር በሌላ መተካት ማለት ነው፡፡ የጃንሆይ አስተዳደር ከዘመኑ ጋር አልሄደም ተብሎ ነው አብዮቱ የተነሳው፡፡ እንደገና የደርግ ኮሙዩኒዝም አላዋጣንም ብሎ የተነሳው ነው ሌላ ፖሊሲ ይዞ የመጣው፡፡ አሁን ደግሞ የትግራይ ሕዝብ አላዋጣንም እያለ ነው፡፡ ፖሊሲው ሌላ ቦታ እየሠራ ከሆነ ጥሩ ነው፡፡ በሌላ በኩል ትግራይ የኢትዮጵያ አካል እንጂ ኢትዮጵያ ትግራይ አይደለችም፡፡ እያንዳንዱ ራሱን የቻለ መንግሥት ነው፡፡ ትግራይ ራሱን የቻለ መንግሥት፣ ኦሮሚያ፣ አማራ ራሳቸውን የቻሉ መንግሥታት ናቸው፡፡ በትልቁ ጥላ ሥር ሆነው የየራሳቸው የቻሉ መንግሥታት ናቸው፡፡ እያንዳንዱ ራሱ መሥራት አለበት፡፡ እንግዲህ ሌሎች ብሔሮችን መውቀሴ አይደለም፡፡ ሌሎቹ ጥሩ እየሠሩ ነው፡፡ ፖሊሲው እየሠራ ነው፡፡ ትግራይ ላይ ግን እየሠራ አይደለም፡፡     

ሪፖርተር፡- ከአይጋ ፎረም ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ ‹‹በመለስ ስም መነገድ መቆም አለበት›› ብለዋል፡፡ ምን ለማለት ፈልገው ነው?

አቶ ዳዊት፡- አዎ! በየግድግዳው ተለጥፎ የምታየው ‹‹መለስ እንዲህ አለ››፤    ‹‹መለስ እንዲህ ብሎ ነበር››፣ ‹‹የመለስ ራዕይ እንከተል›› የሚል ነው፡፡ በተጨባጭ የምታየው ግን እሱን አያንፀባርቅም፡፡ እኛ የማናውቀው ወይም ደግሞ እነሱ ብቻ የሚያውቁት የአቶ መለስ ራዕይ አለ ብዬ አላምንም፡፡ የአቶ መለስ ራዕይም አይደለም፡፡ እነሱ የሚሠሩት ግን ከአቶ መለስ ጋር የሚፃረር ነውና ከዚያ እንዲቆጠቡ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- በዚያው ቃለ መጠይቅ ‹‹ቤተሰብ እንጂ አገር በባልና በሚስት አይመራም›› ብለው ነበር፡፡ ባልና ሚስት ተመሳሳይ የፖለቲካ አቋም ኖሯቸው በአንድ ድርጅትና ሥርዓት ውስጥ ባለሥልጣናት ሆነው ሊገኙ አይችሉም?

አቶ ዳዊት፡- ባልና ሚስት ሌሊት ሲመካከሩበትና ሲነጋገሩበት ያደሩትን ጉዳይ ቢሮ ድረስ መጥተው፣ ሌላ ሐሳብ ይዘው መምጣት አይችሉም፡፡ እንግዲህ የሚያነታርካቸው ጉዳይም ካለ ይዘው ሊገቡ ነው ማለት ነው፡፡ እሱ እንዳይመጣ ደግሞ ወይ እሷ ወይ እሱ አፋቸው መያዝ አለበት ማለት ነው፡፡ የፖሊት ቢሮ አባላት የተሰየሙት የተለያየ ሐሳብ ይዘው መጥተው ተብላልቶ የተለያየ ሐሳብ ይዘው እንዲወጡ ነው፡፡ የፖሊት ቢሮ አባላት ዘጠኝ ከሆኑ፣ ባልና ሚስት ገብተው ግን ስምንት ሆኑ ማለት ነው፡፡ ይኼ ደግሞ በፖሊት ቢሮ ብቻ ሳይሆን በማዕከላዊ ኮሚቴም የተላለፈ ጉዳይ ነው፡፡ ባልና ሚስት የአንድ ኮሚቴ አባል የሚሆኑበት ምክንያት ምንድነው? ዓላማውን ሳተ፡፡ ዳር ድንበሩ የት ላይ ነው የሚሆነው፡፡ ሚስት ከባሏ የበለጠ ሰው ልትመርጥ ነው? ወይስ እሱ ከእሷ የበለጠ ሊመርጥ ነው? ፖለቲካ’ኮ ነው፡፡ መለኮታዊነት አይደለም፡፡ ሥልጣን ነው፡፡ የትኛዋ ሚስት ናት ባልሽ ከሥልጣን ይውረድ አይውረድ ተብላ የምትጠየቀው? ይውረድ ብላ ልትመርጥ ነው? ጥቅሟ’ኮ ተጎዳ፡፡ በጣም ወሳኝ በሆነበት ወቅት ላይ ሚስቱ ናት ባሏ ከሥልጣን ላይ ይውረድ ብላ የምትመልሰው?

ሁለተኛ ያነሳሁት ጉዳይ የፖሊት ቢሮ አመራረጡ ላይ ነው፡፡ እንግዲህ ስለ ዴሞክራሲ ነው እያወራን ያለነው፡፡ የብዙኃኑን ሕዝብ ድምፅ ነው የምንከተለው፡፡ እንግዲህ እዚያ አካባቢ የሚደረጉ ጨዋታዎችን ወደ ጎን ትቶ ከራሱ አብልጦ የሕዝብን ጥቅም ማስቀደም አለበት፡፡ ቅድም ካልናቸው ከሁለቱ አንዱ ከሆነ ግን በዚህ ይቀጥላል፡፡ አሥር ጊዜ እንዲህ ስለሆነ ነው እንዲያ ነው የሚል ነገር አይሠራም፡፡ ሕዝብ የሚፈልገው የሚበላ ነው፡፡ ንፁህ ውኃ ነው፡፡ እንግዲህ ባለፉት 24 ዓመታት እንዲህ ዓይነት ችግር ያለበት አመራር ነው የቆየው፡፡ እውነተኛ ታጋይ ከሆነ፣ ከአቅሜ በላይ ነው መርቃችሁ አሰናብቱኝ ማለት ይችላል፡፡ ውጭ አገር እንደምናየው እንኳንስ እሱ የፈጠረው ስህተት ከእሱ ጋር የተያያዘ ስህተት ከተፈጠረ በራሱ ፈቃድ ሥልጣን ይለቃል፡፡   

ሪፖርተር፡- ባለፉት ሁለት ጉባዔዎች የተወሰኑ በገዛ ፈቃዳቸው ራሳቸውን ከፓርቲው ያገለሉ አሉ፡፡

አቶ ዳዊት፡- እንግዲህ እነዚህ ምናልባት ትክክለኛ ታጋዮች ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ ለበጎ ነገር ይሆናል ራሳቸውን ያገለሉት፡፡ አዲስ ኃይል እንዲመጣ አዲስ ጉልበት አዲስ አስተሳሰብ እንዲመጣ ነበር፡፡ መተካካት ማለት ግን አበበን በከበደ መተካት አይደለም፡፡

ሪፖርተር፡- በትግራይ ውስጥ ከቋንቋ፣ ከባህልና ከታሪክ ጋር በተያያዘ ለመሥራት ፍላጎት አለዎት፡፡ ምናልባት ቱሪዝምን እንደ አማራጭ ዘርፍ ተመልክተውት ያውቁ ይሆን?

አቶ ዳዊት፡- ትግራይ የታደለች ነች የምንለው ነገር ካለ ይኼ ነው፡፡ የመጀመርያው የአይሁድ ሃይማኖት ትግራይ ውስጥ ነው የነበረው፡፡ የእስልምና ሃይማኖት የገባው እዚህ ነው፡፡ ቁጥር ስፍር የሌላቸው ስንት የጥንት ታሪክ የያዙ ገዳማት አሉ፡፡ ግብፅ ትልቁ ገቢዋ ከቱሪዝም ነው፡፡ ሌላውም አካባቢ የራሱ መስህብ አለው፡፡ ትግራይ በጣም ድንቅ የሆነ የቱሪስት መስህብ ቦታዎች አሉ፡፡ ለምንድነው የትግራይ መንግሥት ትኩረት ያልሰጣቸው? እንግዲህ የአስተሳሰብ ችግር ነው የሚሆነው፡፡ የትግራይ መንግሥት እዚህ ላይ ትኩረት ሰጥቶ እሱን ቢያስተዋውቅ ብዙ ገቢ ያገኝ ነበር፡፡ ሊሆን አልቻለም፡፡ እንግዲህ አንድ መንግሥት ወደቀ ስንል መመዘኛው የሕዝቡ ኑሮ ነው፡፡ እርሻ በሌለበት የግብርና ፖሊሲ እየተከተለ ተፈትኖ ወድቋል፡፡ እኔ ስሠራ የነበረው ቱሪዝምን ለማስፋፋት አልነበረም፡፡ ባህልና ቋንቋ ላይ ነው፡፡ ምናልባት ቅርሱን፣ ባህሉንና ቋንቋውን ለማዳን ነው፡፡ ለቱሪዝም አስተዋጽኦ ያደርግ ይሆናል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -