Saturday, June 22, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊበከፍተኛው ፍርድ ቤት የፀናው የአዕምሮአዊ ንብረት ጥበቃ ጽሕፈት ቤት ውሳኔ ታገደ

በከፍተኛው ፍርድ ቤት የፀናው የአዕምሮአዊ ንብረት ጥበቃ ጽሕፈት ቤት ውሳኔ ታገደ

ቀን:

የኢትዮጵያ አዕምሮዊ ንብረት ጥበቃ ጽሕፈት ቤት ከአንድ ዓመት በፊት ሚያዝያ 28 ቀን 2006 ዓ.ም. በክራውን ሆቴል (Crown Hotel) እና በክራውን ፕላዛ (CROWNE PLAZA) ላይ ያስተላለፈው ውሳኔ በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ሐምሌ 30 ቀን 2007 ዓ.ም.  የፀና ቢሆንም፣ ክራውን ሆቴል ጉዳዩን ወደ ፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት በመውሰዱ ታገደ፡፡

ክራውን ሆቴል በፍርድ ቤቱ ውሳኔ ቅር በመሰኘት የሕግ ስህተት ብቻ ለሚያየው የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት አቤቱታውን በማቅረቡ፣ የከፍተኛው ፍርድ ቤት ምክትል ፕሬዚዳንት አግደውታል፡፡

ሲክስ ኮንትኔንትስ ሆቴልስ ኢንክ (Six Continents Hotels Inc) በዓለም አቀፍ ደረጃ ታዋቂና ዝነኛ መሆኑን የገለጸውን ክራውን ፕላዛ (CROWNE PLAZA)፣ የንግድ ምልክት ለማስመዝገብ ለኢትዮጵያ አዕምሮአዊ ንብረት ጽሕፈት ቤት ያቀረበውን ጥያቄ፣ ክራውን ሆቴል (Crown Hotel) ሐምሌ 7 ቀን 1987 ዓ.ም. የንግድ ምልክት አድርጎ ማስመዝገቡን ገልጾ ለጽሕፈት ቤቱ አመልክቶ ነበር፡፡ ጽሕፈት ቤቱ መቃወሚያውን ተመልክቶ ክራውን ሆቴል በንግድ ምልክቱ ላይ የቅድሚያ መብት እንዳለው በመግለጽ፣ ክራውን ፕላዛ ያቀረበውን የንግድ ምልክት ምዝገባ ጥያቄን ውድቅ አድርጎት ነበር፡፡ ውድቅ ያደረገውም በአዋጅ ቁጥር 501/98 አንቀጽ 7(1) መሠረት ተመሳሳይ የንግድ ምልክት መሆኑን በመጥቀስ ነበር፡፡

የአዕምሯዊ ንብረት ጥበቃ ጽሕፈት ቤት ውሳኔውን ሰጥቶ ባለበት ሁኔታ፣ ፀሜክስ ግሎባል ኢንተርፕራይዝ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር የተባለ ድርጅት ለንግድ ምልክትና ኢንዱስትሪያዊ ንድፍ ጥበቃና ልማት ዋና የሥራ ሒደት፣ ግንቦት 9 ቀን 2005 ዓ.ም. አቤቱታ ማቅረቡን ሰነዶች ያመለክታሉ፡፡ ድርጅቱ ያቀረበው አቤቱታ አዲስ አበባ ከተማ ውስጥ ባለአምስት ኮከብ ሆቴል እየገነባ መሆኑንና የሆቴሉ ስያሜም ከክራውን ፕላዛ ጋር የተገናኘ መሆኑን በመጥቀስ፣ ሲክስ ኮንትኔንታል ሆቴልስ ኢንክ ለጽሕፈት ቤቱ ያቀረበው የንግድ ምልክት ምዝገባ ተግባራዊ እንዲሆን መጠየቁንም ሰነዶች ያስረዳሉ፡፡

ጽሕፈት ቤቱም ድጋሚ ጥያቄውን በማስተናገድ ክራውን ፕላዛ የሚለው የንግድ ምልክት፣ ክራውን ሆቴል ከሚለው የንግድ ምልክት ጋር ተመሳሳይነት እንዳለው በመግለጽ፣ ውድቅ ያደረገውን ውሳኔ ቀልብሶታል፡፡ ክራውን ፕላዛ የንግድ ምልክት ከኢንቨስትመንት አኳያ ለአገር የሚሰጠው አስተዋጽኦ ከፍተኛ መሆኑን በመግለጽ አቤቱታውን ተቀብሎ የሁለቱን ንግድ ምልክቶች አወዳድሯል፡፡

ክራውን ፕላዛ እንዲመዘገብለት ያቀረበው የንግድ ምልክት በዕይታ፣ በንባብና በድምፀት የሚለያይ መሆኑን ጽሕፈት ቤቱ ገልጿል፡፡

ጽሕፈት ቤቱ  በሰጠው ማብራሪያ እንደገለጸው፣ ሁሉቱ የንግድ ምልክቶች ለሆቴል አግልግሎት የሚውሉ ናቸው፡፡ የእነዚህን አገልግሎቶች የሚጠቀሙ አግባብነት ያላቸው የኅብረተሰብ ክፍሎች በአንፃራዊነት ከሌሎች አገልግሎቶች አኳያ ሲታይ የኢኮኖሚ አቅማቸው፣ የትምህርት ደረጃቸውና የማገናዘብ አቅማቸው ከፍተኛ የሆኑ  ናቸው፡፡ በመሆኑም ሁለቱ የንግድ ምልክቶች መሳከር የመፍጠር አቅማቸው በጣም አነስተኛ መሆኑን ጽሕፈት ቤቱ ገልጿል፡፡

ክራውን ሆቴል የካቲት 20 ቀን 2006 ዓ.ም. ለጽሕፈት ቤቱ ባቀረበው አቤቱታ፣ መስከረም 10 ቀን 2006 ዓ.ም. ክራውን ፕላዛ ያስመዘገበው የንግድ ምልክት ከእሱ ጋራ እንደሚመሳሰል በመግለጽ ተጠቃሚውን ኅብረተሰብ የሚያሳስትና የሚያሳክር መሆኑን ጠቅሶ፣ ከፍተኛ ቁሳዊ ጉዳት የሚያደርስበት ስለሆነና በአዋጅ ቁጥር 686/2002 አንቀጽ 24(3በ) እና (ነ) እንዲሁም አዋጅ ቁጥር 501/98 አንቀጽ 6 እና 7 ድንጋጌዎች እንደሚጥስ ጠቁሞ፣ ያቀረበውን መቃወሚያ ጽሕፈት ቤቱ ውድቅ አድርጎበታል፡፡ ጽሕፈት ቤቱ በሰጠው ውሳኔም ክራውን ፕላዛ በሚል መጠሪያ የተመዘገበው የንግድ ምልክት ክራውን ሆቴል ከሚለው የንግድ ምልክት ጋር መሳከርን የማይፈጥርና አግባብነት ያላቸው የኅብረተሰብ ክፍሎችን የማሳሳት አቅሙ አነስተኛ መሆኑን በመጠቆም፣ ክራውን ፕላዛ መመዝገብ የሚችል መሆኑን ገልጿል፡፡ ሁለቱም የየራሳቸውን ምልክት ተጠቅመው መሥራት እንደሚችሉ ሁለቱም ወገኖች በተመሳሳይ ሁኔታ የሕግ ጥበቃ አግኝተው በሥራ ላይ እንዲውሉ ሚያዝያ 28 ቀን 2006 ዓ.ም. በቀድሞው የጽሕፈት ቤቱ ዋና ዳይሬክተር አቶ ብርሃኑ አዴሎ የፀደቀው ውሳኔ፣ ሐምሌ 30 ቀን 2007 ዓ.ም. በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ፀንቷል፡፡

የአዕምሯዊ ንብረት ጥበቃ ጽሕፈት ቤት የሰጠውን ውሳኔ የተቃወመው ክራውን ሆቴል (Crown Hotel) የንግድ ምልክቱን በሚመለከታቸው መሥሪያ ቤቶች እያሳደሰ ሲጠቀምበት ከ20 ዓመታት በላይ እንደሆነው ገልጿል፡፡ ክራውን ፕላዛ ግን ኢትዮጵያ ውስጥ የሆቴል ሥራ ለመሥራት ከሚመለከታቸው መሥሪያ ቤቶች ፈቃድ ሳያገኝ በቀጥታ ወደ ጽሕፈት ቤቱ መሄዱንም ጠቁሟል፡፡ ያቀረበውን የንግድ ምልክትም ክራውን ሆቴል ከሚለው ጋር ተመሳሳይ መሆኑን በመግለጽ ውደቅ አድርጎበት እንደነበርም ጠቅሷል፡፡ ሲክስ ኮንትኔንትስ ሆቴልስ ኢንክ ክራውን ፕላዛ በሚል የንግድ ስም በኢትዮጰያ ውስጥ የንግድ ሥራ ለመሥራት በንግድ ሚኒስቴር ሳይመዘገብ ወደ ኢትዮጵያ አዕምሯዊ ንብረት ጥበቃ ጽሕፈት ቤት በመሄዱ፣ የንግድ ምልክት ምዝገባ እንዲደረገለትም መጠየቅ  እንደማይችልና ሌሎችንም አግባብ አይደሉም ያላቸውን መቃወሚያዎች በመግለጽ ክራውን ሆቴል ይግባኙን አቅርቧል፡፡

ክራውን ፕላዛ (CROWNE PLAZA) በሰጠው ምላሽ እንደገለጸው፣ ክራውን ሆቴል ከሐምሌ 7 ቀን 1987 ዓ.ም. ጀምሮ በንግድ ሚኒስቴር ተቀማጭ የነበረውና ለተወሰነ ጊዜ ሲታደስ የቆየው (Crown Hotel Design/Logo) የሚል ንግድ ምልክት በአዋጅ ቁጥር 501/98 አንቀጽ 46(1) መሠረት ለዳግም ምዝገባ መቅረብ ቢኖርበትም ባለመቅረቡ መብት የለውም፡፡ ሲክስ ኮንትኔትስ ሆቴልስ ኢንክ ክራውን ፕላዛ በአገሪቱ ሕግ እንደ አንድ የንግድ ምልክት ለመመዝገብ ሊያልፋቸው የሚገባቸውን ሒደቶች ሁሉ በአግባቡ አልፎ፣ እ.ኤ.አ. በጥር 13 ቀን 2013 መመዝገቡንና የጥበቃ ጊዜውም እ.ኤ.አ. ከጥር 13 ቀን 2013 እስከ ጥቅምት 12 ቀን 2020 ድረስ የሚቆይ የንግድ ምልክት መሆኑ ገልጿል፡፡ በኢትዮጵያ ውስጥ የንግድ ሥራ መሥራት እንደማይችል የተገለጸውን በሚመለከት የንግድ ስምንና የንግድ ምልክትን ልዩነት ካለመገንዘብ የተነሳ መሆኑን አዋጅ ቁጥር 501/98፣ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ደንብ ቁጥር 273/2005 አንቀጸ (9)ን ካለመገንዘብ የተነሳ መሆኑን በመጠቆም ይግባኙን ተቃውሟል፡፡ ክራውን ፕላዛ ዘርዘር ያሉ ተቃውሞችን በማቅረብ ክራውን ሆቴል ያቀረበውን ይግባኝ ከመቃወሙም በተጨማሪ፣ ሁለቱም ወገኖች ሐምሌ 15 ቀን 2007 ዓ.ም የቃል ክርክር አድርገዋል፡፡

ፍርድ ቤቱም ለክራውን ሆቴል ቅሬታ ምላሽ የሆነው ክራውን ፕላዛ የንግድ ምልክት ምዝገባ በተደረገ ጊዜ የፀና የንግድ ምልክት ጥበቃ ይደረግለት ነበር ወይስ አልነበረም? የንግድ ስም ምዝገባ ማካሄድ ለንግድ ምልክት ምዝገባ ቅድመ ሁኔታ ነው ወይስ አይደለም? የክራውን ሆቴል የንግድ ምልክትና የክራውን ፕላዛ የንግድ ምልክት ተመሳሳይና አንድ ዓይነት ሊባሉ ይችላሉ ወይስ አይችሉም? ጽሕፈት ቤቱ የምዝገባ ጥያቄ ቀርቦለት ‹‹ተመሳሳይነት አለው›› ብሎ በአንድ ወቅት ውድቅ ያደረገውን ሌላ ጊዜ በማየት ተቀባይነት አለው በማለት መመዝገብ ይችላል ወይስ አይችልም? የሚሉ ጭብጦችን ይዞ መመርመሩን ገልጿል፡፡

ክራውን ሆቴል ያቀረበውን የንግድ ምልክት መመልከቱን የገለጸው ፍርድ ቤቱ፣ ክራውን ሆቴል የሚል ጽሑፍ ዘውድ የተሳለበትና የጣሪያው ክዳን የጀበና ቅርፅ የሆነ መለስተኛ አዳራሽ ፎቶ (ቃልና ምሥል) መሆኑን አብራርቶ፣ በስሙ በተመዘገበው ክራውን ሆቴል ዲዛይን (ሎጎ)  የንግድ ምልክት ላይ ያለው መብት የፀና መሆኑን አረጋግጧል፡፡ ክራውን ፕላዛ የመመዝገብ ጥያቄ ሊያቀርብ እንደሚችል የቀረበውን ተቃውሞ በሚመለከት፣ በሕግም ሆነ በማስረጃ ያልተደገፈ መሆኑን በመጠቆም ተቃውሞውን ውድቅ አድርጎታል፡፡

ምልክቶቹ አንድ ዓይነት ናቸው ስለመባሉ ፍርድ ቤቱ ዝርዝር ማብራሪያ ሰጥቶ በአዋጅ ቁጥር 501/98 አንቀጽ 2(12) መሠረት የንግድ ምልክት ምን ማለት እንደሆነ ካብራራ በኋላ፣ የንግድ ምልክቱ አንድ ዓይነት ወይም ተመሳሳይ ለማለት ምን ምን ሲሟሏ እንደሆነ በአዋጁም ሆነ በደንብ ቁጥር 273/2005 ባለመደንገጉ፣ ምልክቶቹ ተመሳሳይ ወይም አንድ ናቸው ማለት እንደማይቻል ገልጿል፡፡

በአጠቃላይ ጽሕፈት ቤቱ ክራውን ፕላዛ ያቀረበለትን የንግድ ምልክት ምዝገባ ጥያቄ ተቀብሎ በአዋጁ ቁጥር 501/98ና በደንብ ቁጥር 273/2005 መሠረት ሁለቱ ምልክቶች በዕይታ በንባብና በድምፀት የማይገናኙ መሆናቸውን መግለጹን በመጠቆም ክራውን ፕላዛ ያቀረበውና ያስመዘገበው “CROWNE PLAZA” የሚለው ምልክት ሊሰረዝ እንደማይገባ በመግለጽ ፍርድ ቤቱ የጽሕፈት ቤቱን ውሳኔ አፅድቆታል፡፡ ከፍተኛው ፍርድ ቤት ያፀደቀው ውሳኔ የሕግ ስህተት እንዳለበት በመቃወም የውሳኔው አፈጻጸም ተግባራዊ እንዳይሆን ክራውን ሆቴል ለፍርድ ቤቱ ባቀረበው አቤቱታ መሠረት፣ ቅሬታውን ለፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ለሰበር ሰሚ ችሎት እስከሚቀርብ ድረስ በከፍተኛው ፍርድ ቤት ምክትል ፕሬዚዳንት ፊርማ ውሳኔውን አሳግዷል፡፡

 

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የንብረት ማስመለስ ረቂቅ አዋጅና የሚስተጋቡ ሥጋቶች

ከሰሞኑ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የቀረበው የንብረት ማስመለስ ረቂቅ...

የመጨረሻ የተባለው የንግድ ምክር ቤቱ ምርጫና የሚኒስቴሩ ውሳኔ

በአገር አቀፍ ደረጃ ደረጃ የንግድ ኅብረተሰቡን በመወከል የሚጠቀሰው የኢትዮጵያ...

ሚስጥሩ!

ጉዞ ከካዛንቺስ ወደ ስድስት ኪሎ፡፡ የጥንቶቹ አራዶች መናኸሪያ ወዘናዋ...