Monday, October 2, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊመንግሥት የዝናብ መስተጓጎሉ ያመጣውን ችግር የሚቋቋም በቂ አቅም አለኝ አለ

መንግሥት የዝናብ መስተጓጎሉ ያመጣውን ችግር የሚቋቋም በቂ አቅም አለኝ አለ

ቀን:

የዝናብ መስተጓጎል በሰዎችና በከብቶች ላይ ጉዳት ሊያስከትል እንደነበር አስቀድሞ ተተንብዮ ስለነበር፣ ችግሩን ለመቅረፍ ዝግጅት ሲያደርግ መክረሙንና ከዚህ የባሰ ችግር ቢመጣም ለመቋቋም የሚችል አቅምና ዝግጁነት እንዳለው መንግሥት አስታወቀ፡፡

የክረምቱ ዝናብ መዝነብ በሚገባው መጠንና ጊዜውን ጠብቆ እየዘነበ አለመሆኑ የመወያያ አጀንዳ ከሆነ ሰነባብቷል፡፡ በዚህም ምክንያት በአገሪቱ የተለያዩ ክፍሎች የድርቅ አደጋ መስተዋሉም ተዘግቧል፡፡ በተለይ በአፋርና በኢትዮጵያ ሶማሌ ክልሎች ከብቶች እየሞቱና ነዋሪዎችም የምግብ እጥረት እያጋጠማቸው እንደሆነ ተጠቁሟል፡፡ በዚህና በሌሎች ተያያዥ ጉዳዮች ላይ የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት ሚኒስትር አቶ ሬድዋን ሁሴን በጽሕፈት ቤታቸው ነሐሴ 7 ቀን 2007 ዓ.ም. መግለጫ ሰጥተዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት በአገራችን ዓለም አቀፍ ገጽታ ያለው የአየር ፀባይ ለውጥ ከሚያስከትሉት የንፋስ ዓይነቶች አንዱ የሆነው ኤልኒኖ መከሰቱ በብሔራዊ ሚቲዎሮሎጂ ኤጀንሲ በቅርቡ መረጋገጡ ይታወሳል፡፡ በተመሳሳይ አቶ ሬድዋን ኤልኒኖ  በአገሪቱ የተወሰኑ አካባቢዎች ላይ መከሰቱን ገልጸዋል፡፡ መነሻው ካለፈው ግንቦት ወር ጀምሮ ሲሆን፣ በአገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች ምልክቱን እንደሚያሳርፍ አስቀድሞ የተተነበየ እንደነበርም አስረድተዋል፡፡

‹‹የፓስፊክ ውቅያኖስ መሞቅና ከሙቀቱ ጋር የተያያዘ በአገራችንም ሆነ በሌሎች የአካባቢው አገሮች ላይ የራሱ ተፅዕኖ ያለው ምልክት ሊኖር እንደሚችል ታውቆ ነበር፡፡ ይኼው ክስተት በአገራችን የዝናብ እጥረት ወትሮም በሚያጋጥማቸው አካባቢዎች ላይ ሰፋ ብሎ እየታየ ነው፤›› ብለዋል፡፡

በምሥራቁ የአገሪቱ ክፍል፣ በሰሜን ምሥራቅ፣ በመካከለኛው የአገሪቱ ክፍል እንዲሁም በስምጥ ሸለቆ አካባቢ በሚገኙ ወረዳዎች ላይ ኤልኒኖ ምልክቱን እንዳሳረፈም አመልክተዋል፡፡ በከብቶችም ላይ ያሳደረው ተፅዕኖ ያለ ሲሆን፣ እንዲሁም በአንዳንድ አካባቢዎች ሰዎችንም ማገዝ ይጠይቃል፤›› ሲሉም አክለዋል፡፡ በተለይ በሰሜናዊ ሶማሌ ክልልና በአፋር የተወሰኑ አካባቢዎች በከብቶችም ላይ ጉዳቱ ጐላ ብሎ መታየቱንም ገልጸዋል፡፡

‹‹አስቀድሞም በመጋቢት አካባቢም ዝናቡ ወጣ ገባ እያለ በነበረበት ወቅት፣ የተወሰነ የዝናብ ወጣ ገባ ማለት ሊያጋጥም እንደሚችል ይህም በምርትም በከብቶች ግጦሽም ላይ የራሱ ውስንነት ሊያስከትል እንደሚችል ተተንብዮ ስለነበር፣ በመንግሥት በኩል አስፈላጊው ዝግጅት ሲደረግ ነበር፤›› በማለት አቶ ሬድዋን ችግር ሊከሰት እንደሚችል ታውቆ መንግሥት አስፈላጊውን ዝግጅት ማድረጉን አስታውቀዋል፡፡

በበልግ ወቅት የነበረው ሁኔታ በወቅቱ መንግሥት ባደረገው ዝግጅት በኅብረተሰብም ሆነ ችግሩ በነበረባቸው አካባቢዎችም ብዙም ሳይታወቅና  ጉዳቱ ሰፋ ሳይል ምላሽ ለመስጠት መሞከሩንም አመልክተዋል፡፡

‹‹ከመስከረም ጀምሮ በቂ ዝናብ ያልዘነበባቸው አንዳንድ አካባቢዎች ላይ ለከብቶች የሚሆን መኖንም የማድረስ ችግር ነበር፡፡ በአሁኑ ጊዜ ለከብቶችም መኖ የማቅረብና ሌሎች ከብቶችን የሚታደጉ የምግብ አቅርቦቶች እየቀረቡ ነው፤›› በማለት መንግሥት ለተከሰተው ችግር ምላሽ እየሰጠ እንደሆነ ጠቁመዋል፡፡

በተጨማሪም መንግሥት ውኃና በሰዎች ምግብም በአንዳንድ አካባቢዎች በማቅረብ ላይ እንደሚገኝ አስታውቀዋል፡፡ ይህንን ማድረግ የሚያስችል በቂ ክምችት አለ፡፡ መንግሥት በበቂ ሁኔታ ስትራቴጂካዊ ክምችት አለው፤›› ብለዋል፡፡

የተከሰተው ችግር አሁን ካለበት ደረጃ በላይ ቢሄድ መንግሥት ይህን ለመቋቋም ያደረገው ዝግጅት ምን ይመስላል የሚል ጥያቄ የቀረበ ሲሆን፣ ‹‹አሁን ካለበት ቢሰፋም ያንኑ ችግር መሸከም የሚያስችል ዝግጅት አለ፡፡ ከሥር ከሥሩ ደግሞ ጥቅም ላይ የሚውለውን እህል በግዥ ለመተካት ሒደቱ ተጀምሯል፤›› ሲሉ አቶ ሬድዋን ምላሽ ሰጥተዋል፡፡

እስካሁን ባለው ሁኔታ መንግሥት 700 ሚሊዮን ብር በጀት መድቦ አስፈላጊውን ዝግጅት እያደረገ እንደሆነና ይህንን መቋቋም የሚያስችል አቅም እንደተፈጠረም ገልጸዋል፡፡

ዝናቡ በአንድ በኩል ዘግየት ያለባቸው በሌላ በኩል ወጣ ገባ የሚልባቸው አካባቢዎች ላይ አልፎ አልፎ የሰብል መጐዳት አጋጥሟል፡፡ ይህም ሆኖ የተሻለ ዝናብ ያለባቸው አካባቢዎች ላይ ቀደም ሲል ሲደረጉ ከነበሩ ዝግጅቶችም ይበልጥ በመንቀሳቀስና ምርት በመጨመር፣ ጉዳቱ በደረሰባቸው ቦታዎች ላይ የሚጐዳውን ሰብል እንደ አገር ለማካካስ እየተሠራ ነው፤›› ሲሉም አቶ ሬድዋን አክለዋል፡፡

በሌላ በኩል ደግሞ ከጥቅምት ጀምሮ በተለምዶ ያልነበረ ዝናብ ይኖራል ተብሎ እንደሚጠበቅም ሚኒስትሩ ጠቁመዋል፡፡ በአንዳንድ አካባቢዎች ላይ በእነዚህ ጊዜያት ፈጠን ብለው መድረስ የሚችሉ የሰብል ዓይነቶችን ለአርሶ አደሩ በማቅረብና በአጭር ጊዜ በተወሰነ እርጥበት የሚደርሱ የሰብል ዓይነቶችን በመዝራት፣ ዝናቡ በአጠረባቸው አካባቢዎች ላይ ደርሶ የነበረውን ጉዳት አካክሶ ለመሥራትም ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን አቶ ሬድዋን ገልጸዋል፡፡

በዚህ ሒደት ውስጥ መንግሥት ያገኘው አንድ ትምህርት ወትሮም የዝናብ እጥረት ያጋጥማቸው የነበሩ አካባቢዎች ላይ በተፋሰስ ልማት የከርሰ ምድርና የገጸ ምድር ውኃ አቅምን ለማዳበር መጣር ያለበት መሆኑን ነው ሲሉም ተናግረዋል፡፡ አርሶ አደሩ ቢያንስ አንድ የመስኖ ወይም የውኃ ማሰባሰቢያ ዘዴዎችን በመጠቀም እርጥበትን ማሳው ላይ ማቆየት እንዲችል ለማድረግ የተጀመሩ ሥራዎች ውጤታማ እንደሆኑም አብራርተዋል፡፡

አሁን የተከሰተው ኤልኒኖ በ1989 እንዲሁም በ1997 ተከስቶ የነበረው ዓይነት ነው ብለዋል፡፡ ነገር ግን በሌሎች ጊዜያት ሲሰማ የነበረው ዓይነት የከፋ ጉዳት በማይደርስበት ሁኔታ ላይ የተደረሰው፣ ባለፉት ዓመታት የተሠራው የውኃ ማሰባሰብ ሥራ የእርጥበት ማቆየት ሥራዎች ውጤት እንደሆነና ቀደም ባሉት ጊዜያት ይደርስ የነበረው ጉዳት አያደርስም ብለዋል፡፡

ምንም እንኳን ውኃ የማሰባሰብ ሥራ ከፍተኛ ድርሻ የተወጣ ቢሆንም፣ በሁሉም አካባቢዎች በተገቢውና በእኩል ደረጃ አለመከናወኑን አቶ ሬድዋን አስረድተዋል፡፡ በዚህም ምክንያት ያን የእርጥበት ሥራ ያላቆዩ ሰዎች ይበልጥ እየተጐዱ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ ‹‹ይህንኑ በመውሰድ ኅብረተሰቡን ከዚህ በፊት የጀመረውን ጥረት አጠናክሮ እንዲቀጥል ማድረግ አስፈላጊ ሆኗል፡፡ ይህንኑ ተሞክሮ እያሰፋ የኅብረተሰቡን ግንዛቤ እያሳደጉ የመሄድ ሥራው ተጠናክሮ ይቀጥላል፤›› በማለት አብራርተዋል፡፡

የአፋርና የኢትዮጵያ ሱማሌ ክልል የሚዋሰኑባቸው አካባቢዎች ላይ ከዝናቡ መዘግየት ጋር ተያይዞ የተወሰኑ ከብቶች ጉዳት ለምን እንደደረሰባቸው ሲያስረዱም፣ ‹‹እዚህም አንዱ ምክንያት ረዘም ካለ ቦታ ውኃ ተጠምተው ይቆዩና ውኃ ያለበት ቦታ ደርሰው ቢጠጡም በከፊል የሞት አደጋ ይደርሳል፡፡ ከጥማቱ መጠንና ከሚወስዱት ውኃ ጋር ተያያዞ፣ አንዳንድ አካባቢ ላይ አስቀድመው ገና እንደተጠሙ ቶሎ ብለው ውኃ ወዳለበት አካባቢ አለመውሰድም እንዲሁ ጉዳት ያደረሰባቸው አሉ፤›› ብለዋል፡፡ ውኃ በቦቴ የማመላለሱ ጉዳይ አስቀድሞ ሲሠራበት የቆየና የነበረ ቢሆንም፣ አሁን ደግሞ ይበልጥ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አመልክተዋል፡፡

በሰዎች ላይ የደረሰ ጉዳት የለም ያሉት አቶ ሬድዋን፣ ‹‹በሕይወት ደረጃ የሚታይ ጉዳት የለም፡፡ ግን ዞሮ ዞሮ ቀለብ መድረስ ስላለበት ቀለቡ ቀደም ሲል በእህል መልክ እየሄደ ቆይቷል፡፡ አሁን ደግሞ በአልሚ ምግብ መልክ ተጠናክሮ እየተላከ ነው፤›› በማለት አስረድተዋል፡፡ ስለሆነም ምንም እንኳን የከብቶች ሞት ቢኖርም በሰው ላይ ከአካል መጐዳት ያለፈ ወደ ሕይወት የደረሰ አደጋ አለመድረሱን አስረድተዋል፡፡

‹‹እንዳለ የዝናብ መጥፋት አይደለም የዝናብ ባህሪ መለዋወጥ ነው፤›› ያሉት አቶ ሬድዋን፣ ‹‹መለዋወጡ ደግሞ አካባቢዎችን እየለያየ ነው የሚከሰተው፡፡ ግምቶቹ በየጊዜው ይታወቃሉ፡፡ ኤልኒኖ እንደሚኖር አስቀድሞ ተተንብዮ ነበር፡፡ ከበልግ ጊዜ ጀምሮ ምልክቶቹ ይታወቃሉ፡፡ ከሰኔ ጀምሮ ደግሞ ክረምቱ ላይ ይህ እንደሚያጋጥም ይታወቅ ነበር፡፡ ከዚህ በላይ የከፋ የሚሆንበት ሁኔታ የለም፡፡ ካለም በበቂ ሁኔታ ተዘጋጅተናል፤›› ብለዋል፡፡

ይህን ተከትሎ የዋጋ ንረት እንዳያጋጥም መንግሥት ምን እየሠራ ነው? ለሚለው ጥያቄ፣ ‹‹ለዋጋ ንረት የሚያበቃ ምክንያት አይኖርም፡፡ ምክንያቱም አንደኛ በሚኖረን ሰብል ላይ የከፋ ጉዳት አይደርስም የሚል ነው ትንበያው፡፡ ቦታ ይቀያይራል፡፡ አንዳንድ ቦታ ተጨማሪ ዕድል ያመጣል፡፡ አንዳንድ ቦታ ያለውን ይቀንሳል፡፡ ስለዚህ ሲካካስ ከሞላ ጐደል የሰፋ የምርት መቀነስ አይኖርም፤›› በማለት ምላሽ ሰጥተዋል፡፡ ሁለተኛ አሁንም የምርት መቀነሱ ባለባቸው አካባቢዎች አምርተው የተሻለ ምርት የማይጠብቁ ጉዳት የደረሰባቸው አካባቢዎችን የሚያካክስ ክምችት አለ ብለዋል፡፡

‹‹አንደኛ አቅማችን ተገንብቷል ሲባል ይህ ነው፡፡ የዛሬ አሥር ወይም አሥራ አምስት ዓመት ቢሆን ይህ ምልክት አለ ሲባል አገሪቱ በሙሉ በዕርዳታ እህል ትጥለቀለቅ ነበር፡፡ አሁን ወሬው የማይሰማው ይህን መከላከል የሚያስችል አቅም ራሳችን በመገንባታችን ምክንያት ነው፡፡ ስለዚህ ያለው እህል በቂ ነው፡፡ እርሱ ይወጣል፡፡ በሚወጣው ልክ ደግሞ እየተገዛ ይገባል፡፡ ስለዚህ ከሞላ ጐደል እጥረት እንዳይኖር ማድረግ ይቻላል፡፡ ስለሆነም ለዋጋ ንረት የሚያበቃ ምክንያት የለም፡፡ አጋጣሚውን የሚጠቀም ሰው አይኖርም አይባልም፡፡ በቂ ምክንያት ግን የለም፤›› ብለዋል፡፡

በአዲስ አበባ እየተከበረ ስላለው የመጀመሪያው ብሔራዊ የዳያስፖራ ቀንን በተመለከተ፣ ዳያስፖራው የተለየ ጥቅም እየተሰጠው ነው ወይ የሚል ጥያቄ የቀረበላቸው አቶ ሬድዋን፣ ‹‹እውነታውን ማየት ነው ጥሩ የሚሆነው፡፡ ቅድሚያውን ይዘው የዕለት ተዕለት ዴሞክራሲውም ላይ ልማቱም ላይ እየተሳተፉ ያሉት እዚሁ የሚገኙ ዜጐች ናቸው፤›› ብለው፣ ‹‹መንግሥት በየዕለቱ ድጋፍ እያደረገ ያለው አገር ውስጥ ላሉ አርሶ አደሮችና አገር ውስጥ ለሚንቀሳቀሱ ጥቃቅንና አነስተኛ አልሚዎችና አገር ውስጥ እየተንቀሳቀሰ ላለው ባለሀብት ነው፡፡ ነገር ግን የዳያስፖራው አባላት ኢትዮጵያዊ የሆኑም ትውልደ ኢትዮጵያዊ የሆኑትም ደግሞ በአገር ልማት ላይ የራሳቸው ድርሻ አላቸው ብሎ መንግሥት ያምናል፤›› በማለት መልሰዋል፡፡ ድርሻቸውን መወጣት እንዲችሉ የተለያዩ ዕድሎች ሊኖራቸው ይገባል የሚል እምነትም እንዳለ ገልጸዋል፡፡

‹‹በዚህ ረገድ አቅም ያላቸው አቅማቸውን አስተባብረው እዚህ በሚደረግ ኢንቨስትመንት ላይ እንዲሳተፉ ነው የተደረገው፡፡ ሌሎች ኢንቨስተሮችን ለምነን አባብለን የታክስ ዕፎይታ ሰጥተን ከቀረጥ ነፃ እንዲያስገቡ አድርገን ነው የምናመጣው፡፡ ዳያስፖራውም በዚህ ረገድ ለረጅም ጊዜ ከአገሩ ርቆ ስለቆየ በተለያየ መንገድ ያሰባሰበውን የሙያ ይሁን የገንዘብ አቅም አጠራቅሞ በዚህ አገር ልማት ውስጥ መሳተፍ እንዲችል፣ መጀመሪያ አገር ውስጥ ስላለው ጉዳይ ማወቅ አለበት፡፡ በአገር ውስጥ ስላለው ጉዳይ ማወቅ ካለበት ደግሞ በተለያየ መንገድ መጥቶ እንዲያይ ሁኔታዎች ሊመቻቹለት ይገባል፤›› ሲሉም አክለዋል፡፡

አገሪቱ ውስጥ ለሚያለሙ ባለሀብቶች ከሚደረገው ድጋፍ የተለየ ዳያስፖራ ስለሆነ የሚወሰድ ምንም ዓይነት ዕርምጃ የለም ያሉት አቶ ሬድዋን፣ ‹‹ዳያስፖራ ስለሆነ የሚታደል መሬት የለም፡፡ ዳያስፖራውም እንደማንኛውም ኢትዮጵያዊ ቤት የመሥራት ፍላጐት ካለው ደግሞ በማኅበር እየተደራጀና በተለያየ መንገድ ፕሮጀክት እያቀረበ መሥራት የሚችልበት ዕድል አለው፡፡ ስለዚህ ዕድሉን መጠቀም ከፈለጉ የኢንቨስትመንትም ሆነ ቤት የመሥራት ዕድሉ ተመቻችቶላቸዋል፡፡ ለእያንዳንዱ ሰው ከውጭ ተሳፍሮ ስለመጣ ብቻ የሚታደል መሬት ግን የለም፡፡ የሚደረገው ድጋፍ ተገቢ እንደሆነ፣ ይህ ተገቢነት ደግሞ ከልኩ ያላለፈ እንደሆነ በሚዛኑ መውሰድ ጠቃሚ ነው፤›› ብለዋል፡፡

የዳያስፖራን ጉዳይ በልዩ ሁኔታ የሚከታተል የዳያስፖራ ሚኒስቴር እንዲቋቋም ለቀረበው ጥያቄ የመንግሥት ምላሽ ምን እንደሆነ የተጠየቁት አቶ ሬድዋን፣ ‹‹የዳያስፖራ ሚኒስቴር ይቋቋማል የሚል የመንግሥት ዕቅድ የለም፡፡ ወደፊት ሁኔታው የሚጠይቅ ከሆነ እንደ ሁኔታው ታይቶ መወሰን ይቻላል፡፡ አሁን ባለው ግን ዋናው የመዋቅር ችግር ነው ተብሎ አልተወሰደም፡፡ ዋናው ግንኙነቱ በበቂ ደረጃ አልተጀመረም የሚል ነበር፡፡ አሁን የተጀመረውን ማጠናከርና ሒደቱ መሄድ እስከሚችለው ርቀት ድረስ ማድረግ ያስፈልጋል የሚል ነው፡፡ የዳያስፖራ ሚኒስቴር የመዋቅርና የታክቲክ ጉዳይ ነው የሚሆነው፡፡ መሠረታዊ የሆነ የስትራቴጂካዊ ጉዳይ አይደለም፡፡ ዋናው የሚሠራውን ሥራ ማወቅና መለየት ነው፡፡ የሚሠራው ሥራ በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ሥር ባለ አደረጃጀት ሥርም ጠንካራ ሰው፣ ጠንካራ አመራር እየተመደበለት ቢሄድም መልክ መያዝ ይችላል፡፡ ሁለተኛው የዳያስፖራውን ፍላጐቶች፣ የሚያስቸግሩትን ጉዳዮች ሰብሰብ አድርጐ ይዞ፣ በየተቋሙ በአንድ መስኮት ማገልገል የሚቻልበትን የተጀመረውን ሥራ አጠናክሮ መሄድ ነው የሚሆነው፡፡ ዞሮ ዞሮ ዳያስፖራው ኢንቨስት ሲያደርግም፣ ጉዳዮች ሲያጋጥሙትም በቀላሉ እንዲፈታለት ማድረግ ነው፡፡ በተለያዩ መንገዶች አሁን የተጀመረው ፕሮግራም እንዲካሄድ ማድረግ ነው፤›› በማለት ምላሽ ሰጥተዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ተመድንና ዓለም አቀፋዊ ሕግን ከእነ አሜሪካ አድራጊ ፈጣሪነት እናድን!

በገነት ዓለሙ በእኔ የተማሪነት፣ የመጀመርያ ደረጃ ተማሪነት ጊዜ፣ የመዝሙር ትምህርት...

የሰላም ዕጦትና የኢኮኖሚው መንገራገጭ አንድምታ

በንጉሥ ወዳጅነው ፍራንክ ቲስትልዌይት የተባሉ አሜሪካዊ ጸሐፊ ‹‹The Great Experiment...

ድህነት የሀብት ዕጦት ሳይሆን ያለውን በአግባቡ ለመጠቀም አለመቻል ነው

በአንድነት ኃይሉ ድህነት ላይ አልተግባባንም፡፡ ብንግባባ ኖሮ ትናንትም ምክንያት ዛሬም...