Tuesday, November 28, 2023
- Advertisment -
- Advertisment -

የዝናብ እጥረቱ አደጋ እንዳይፈጥር ከመሥራት ውጪ አማራጭ የለም!

በአገሪቱ የተለያዩ ክፍሎች በዝናብ አለመኖር ምክንያት ከወዲሁ የታዩ ሥጋቶች አሉ፡፡ የቡቃያዎች መውደምና የእንስሳት ዕልቂት ታይቷል፡፡ በየአሥር ዓመቱ የሚከሰተው የኤልኒኖ ክስተት የሆነው ድርቅ አደጋ እንዳይፈጥር መንግሥትና የሚመለከታቸው አካላት ከፍተኛ ርብርብ ማድረግ ይኖርባቸዋል፡፡ የዘንድሮው ክረምት የዝናብ እጥረት ቢስተዋልበትም፣ አልፎ አልፎ የሚጥለው ዝናብ ሳይባክን ሥራ ላይ መዋል አለበት፡፡ አነስተኛ አርሶ አደሮችና ትላልቅ ግድቦች ከሚዘንበው መጠነኛ ዝናብ የሚገኘውን ውኃ መከተር አለባቸው፡፡ በዝናቡ መዛባት ምክንያት የተዘናጉ አካላት ካሉም የተገኘውን ውኃ አቁረው እንዲይዙና የተለያዩ ተክሎች እንዲለሙ ማድረግ የግድ ነው፡፡ ይህ ካልሆነ ግን ከአስፈሪው ድርቅ ጋር መፋጠጥ አይቀሬ ይሆናል፡፡ መሠረታዊ የሆኑ አንዳንድ ጉዳዮችን እናንሳ፡፡

  1. የመረጃ ልውውጡ የተጠናከረ ይሁን

ከብሔራዊ ሚቲዎሮሎጂ ኤጀንሲ የሚወጣው የአየር ፀባይ ትንበያ መረጃ፣ ከመንግሥት ውሳኔ ሰጪዎች ጀምሮ እያንዳንዱ አርሶ አደር ድረስ በተጠናከረ መንገድ መድረስ አለበት፡፡ በመረጃዎች መጓተት ወይም በተገቢው መንገድ አለመተላለፍ ምክንያት፣ በተለይ ለድርቅ የሚጋለጡ አካባቢዎች ተጎጂ ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ መንግሥት ሰሞኑን የዝናብ እጥረቱን አስመልክቶ በሰጠው መግለጫ፣ መረጃዎች ቀደም ብለው መታወቃቸው በብዙዎች አካባቢዎች እርጥበትን ማቆየት፣ የዝናብ ውኃ ማከማቻ ጉድጓዶችን መቆፈርና መሰል የግብርና ሥራዎች ላይ ቅድመ ዝግጅቶች መደረጋቸውን ቢገልጽም፣ በተወሰኑ አካባቢዎች የሚፈለገውን ያህል ሥራ ባለመሠራቱ የችግሩ ተጠቂዎች መኖራቸውን አመልክቷል፡፡

ብዙ ጊዜ እንደሚባለው ግልጽነት፣ ኃላፊነትና ተጠያቂነት በሌለበት ሁኔታ ውስጥ በደንታቢሶችና ኃላፊነት በማይሰማቸው ሰዎች ምክንያት ጉዳቶች ይደርሳሉ፡፡ መረጃን መደበቅ ወይም ሥራ ላይ እንዳይውል ማድረግ በሕዝብ ላይ ጉዳት ስለሚያደርስ ከፍተኛ ጥንቃቄ ሊደረግበት ይገባል፡፡ ወቅታዊና ትኩስ መረጃዎች በተገቢው መንገድ እንዲፈሱ በማድረግ በአገር ላይ አደጋ የሚደቅነውን የድርቅ አደጋ መከላከል ይቻላል፡፡ በተቋማት መካከልም መረጃዎች ሳይባክኑ በትኩስነታቸው ሥራ ላይ እንዲውሉ መትጋት ያስፈልጋል፡፡ ጤፍ ወይም የተለያዩ ሰብሎችን የዘሩ አርሶ አደሮች በዝናቡ መዘግየት ወይም አለመኖር ምክንያት ተስፋ ሳይቆርጡ፣ የተለያዩ የምግብ አዝርዕቶችን፣ የአትክልትና የፍራፍሬ ዓይነቶችን እንዲያበቅሉ መረጃውን ማቀላጠፍ ተገቢ ነው፡፡ ከአርሶ አደሮች ጋር በመላ አገሪቱ ይሠራሉ የተባሉ ከ60 ሺሕ በላይ የሆኑ የግብርና ኤክስቴንሽን ሠራተኞችም የመረጃው አካል ሆነው እንዲረባረቡ ማድረግ የግድ ነው፡፡ ለመረጃ ልውውጡ ከፍተኛ ትኩረት ይሰጥ፡፡ ያንዣበበው አደጋ ይቀንስ፡፡  

  1. ድርቅ የሚቋቋሙ የተሻሻሉ ዘሮች ይቅረቡ

በአገሪቱ የተለያዩ ክፍሎች የሚገኙ የግብርና ምርምር ማዕከላት የሚያወጡዋቸው ድርቅን መቋቋም የሚችሉ የተሻሻሉ ዘሮች ትኩረት ይደረግባቸው፡፡ ዝናቡ መጣሁ ቀረሁ በሚልበት በዚህ ወቅት ከመደበኛ ዘሮች ይልቅ በእነዚህ ላይ ትኩረት ቢደረግ በመጠነኛ ዝናብ ምርት ማግኘት ይቻላል፡፡ ከዚህ ቀደም ይገኝ የነበረውን ያህል ምርት ማግኘት ባይቻልም እንኳ፣ በተነፃፃሪ ሁኔታ ደህና የሚባል ምርት ለማግኘት ድርቅ የመቁቋም ችሎታ ያላቸውን ዘሮች መቀጠም የችግሩን ጫና ለማቃለል ጠቃሚ ነው፡፡ ለዚህም የምርምር ማዕከላቱ በሙሉ አቅማቸው ይረባረቡ፡፡

የዝናብ እጥረት በሚያጋጥምበት ወቅት ብቻ ሳይሆን በመደበኛውም ጊዜ ቢሆን፣ የአገሪቱ ግብርና በተሻሻሉ ዘሮች፣ በዘመናዊ ቴክኖሎጂዎችና በነባሩ አገር በቀል ዕውቀት ቅንጅት መመራት አለበት፡፡ ችግሩ የከፋ በሚሆንበት ጊዜ ደግሞ ያለውን የአየር ፀባይ የሚላመዱና የሚቋቋሙ ዘሮችንና ዘመናዊ አሠራሮችን ተግባራዊ ማድረግ ጠቃሚ ነው፡፡ በተለይ በዝናብ እጥረት ጉዳት የደረሰባቸው አካባቢዎች በቀጥታ ወደ ምግብ ተረጂነት እንዳይሸጋገሩ ከፍተኛ ጥረት መደረግ ስላለበት፣ ይህ ጉዳይ በብርቱ ይታሰብበት፡፡ አስፈሪውን አደጋ ለማስቀረት በጣም ጠቃሚ ነው፡፡

  1. የዋጋ ንረት እንዳይፈጠር ጥረት ይደረግ

በአገራችን ለዋጋ ንረት መከሰት ከሚጠቀሱ ምክንያቶች መካከል የግብይት ሥርዓቱ በሥርዓተ አልበኞች መወረሩ ነው፡፡ በሕገወጥ ደላሎችና ገበያውን በሚያምሱ ስውር ኃይሎች ምክንያት ሰው ሠራሽ የዋጋ ንረት በሚፈጠርበት አገር ውስጥ፣ የዝናብ እጥረት ድርቅ ያስከትላል ተብሎ ሲሰጋ የዋጋ ንረቱ መጠን አሻቅቦ ይጨምራል፡፡ ምንም እንኳ መንግሥት የዝናብ እጥረት በታየባቸው አካባቢዎች የደረሰውን ጉዳት ለመመከት ከምግብ መጠባበቂያ ክምችት ድጋፍ እያደረገ መሆኑንና ለዚህም 700 ሚሊዮን ብር በጀት መመደቡን ቢያስታውቅም፣ በገጠርና በከተማ ነዋሪዎች ላይ የከፋ ጉዳት እንዳይደርስ መዘጋጀት አለበት፡፡ አጋጣሚዎችን ሁሉ ለራሳቸው ጥቅም ሊያውሉ የሚፈልጉ አልጠግብ ባዮች የዋጋ ንረቱን እንዳያባብሱ የማድረግ ኃላፊነት የመንግሥት ነው፡፡

መንግሥት ችግሩ ቢከሰት እንኳ አገሪቱ ራሷን ለመደጎም የሚያስችል በቂ ክምችት መኖሩን ገልጾ፣ ፈጥነው የሚደርሱ ሰብሎችን ለማምረት ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን አስታውቋል፡፡ ነገር ግን በፍጥነት እየተለዋወጠ ካለው ተጨባጭ ሁኔታ አንፃር በምግብ ምርቶችም ሆነ በሌሎች መሠረታዊ የፍጆታ ዕቃዎች ላይ የዋጋ ንረት የዜጎችን ሕይወት እንዳይፈታተን ማድረግ አለበት፡፡ በደህናው ጊዜ ምክንያታዊ ባልሆኑ የዋጋ ንረቶች የሚመቱ ዜጎች ወቅታዊውን ችግር ታከው በሚመጡ ስግብግቦች የበለጠ ተጎጂ እንዳይሆኑ መደረግ አለበት፡፡ ይህም ከፍተኛ ርብርብ ይጠይቃል፡፡ አለበለዚያ አደጋው የከፋ ይሆናል፡፡ በተጨማሪም በውኃ እጥረት ምክንያት የመጠጥ ውኃና የኤሌክትሪክ ኃይል መስተጓጎል ሊያጋጥም ስለሚችል፣ ይህም በብርቱ ሊታሰብበት ይገባል፡፡ አደጋው የከፋ እንዳይሆን ርብርብ ይደረግ፡፡

  1. አዝጋሚ አሠራሮች ይወገዱ

መረጃ ከመስጠት፣ ወቅታዊ ሁኔታዎችን ከማሳወቅና ተግባራዊ እንቅስቃሴዎችን ከመምራት አኳያ የተለመዱ አዝጋሚ አሠራሮች መወገድ አለባቸው፡፡ ወቅቱ አገሪቱ በጣም ከሚያስፈራ የድርቅ ተጋላጭነት ጋር የተፋጠጠችበት በመሆኑ መንቀራፈፍ አያስፈልግም፡፡ ከዚህ በፊት በድርቅና በረሃብ ምክንያት በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጎቻችን በረገፉበት አገር ውስጥ፣ ዝናብ ሲጠፋ ወይም ድርቅ ሊከሰት ነው ሲባል ብዙዎችን ያስበረግጋል፡፡ በዚህ ወቅት ፈጣንና ተግባራዊ የሆነ እንቅስቃሴ እንጂ አዝጋሚ አሠራር አያስፈልግም፡፡ የመላ አገሪቱ ቀልብና ልቦና በዝናብ እጥረቱ ሊፈጠር የሚችለውን አደጋ ለመቀልበስ ይዋል፡፡ በአዝጋሚነት የተለከፉና ሥራ የሚያደናቅፉ ገለል ይደረጉ፡፡ ወቅቱ እነዚህን አይፈልግም፡፡ አሁን የሚያስፈልጉት ያንዣበበውን አደጋ በብቃት መቀልበስ የሚችሉ ብቻ ናቸው፡፡

በአጠቃላይ መንግሥት ወቅታዊውን ሁኔታ እየተከታተለ መረጃ ከመስጠት በተጓዳኝ የችግሩን አሳሳቢነት አግዝፎ ማየት አለበት፡፡ ከመጠባበቂያ ክምችትም ላይም ሆነ ሌላ በጀት መድቦ ጫናውን እንደሚቋቋም ከመግለጽ በተጨማሪ፣ በሕዝቡ ላይ ሊከሰት የሚችለውን ያልተጠበቀ ተፅዕኖ በሚገባ ማየት ይኖርበታል፡፡ በዓለም ዙሪያ ዘንድሮ በኤልኒኖ ክስተት ምክንያት ድርቅ፣ የውኃ ሙላትና ጎርፍ እየታዩ ቢሆንም፣ እንደ አገር ጠንከር ብሎ ችግሮችን በፅናት መቋቋም ተገቢ ነው፡፡ በዚህ ዘመን ከጥንካሬ በላይ ጠቃሚ ነገር ባለመኖሩ መበርታት የግድ ይላል፡፡ በመዘናጋት ወይም በችላ ባይነት ምክንያት ችግሩን ወደ ጎን መግፋት አደጋ አለው፡፡ ችግሩን ለማድበስበስ መሞከርም በዜጎች ሕይወት ላይ ቁማር መጫወት ነው፡፡ ዋናውና ወሳኙ ነገር ሙሉ ለሙሉ ለችግሩ መፍትሔ መረባረብ ብቻ ነው፡፡ ስለሆነም የዝናብ እጥረቱ አደጋ እንዳይፈጥር በርትቶ ከመሥራት ውጪ አማራጭ የለም!

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች

ለሲኒመር ትሬዲንግ አ/ማ አባላት በሙሉ የጠቅላላ ጉባኤ የስብሰባ ጥሪ

ለሲኒመር ትሬዲንግ አ/ማ አባላት በሙሉ የጠቅላላ ጉባኤ የስብሰባ ጥሪ ሲኒመር ትሬዲንግ...

የባህር በር በቀጣናዊ ተዛምዶ ውስጥ

በበቀለ ሹሜ መግቢያ በ2010 ዓ.ም. መጋቢት ማለቂያን ይዞ ዓብይ አህመድ በጠቅላይ...

ሥጋት ያስቀራል ተብሎ የሚታሰበው የጫኝና አውራጅ መመርያ

በአዲስ አበባ ከተማ በሕገወጥ መልኩ በመደራጀት ማኅበረሰቡ ላይ እንግልትና...

ማወቅ ወይስ አለማወቅ – ድፍረት ወይስ ፍርኃት?

በአሰፋ አደፍርስ ወገኖቼ ፈርተንም ደፍረንም የትም አንደርስምና ለአገራችን ሰላምና ክብር...

ከድህነት ወለል በታች ከሆኑት አፍሪካዊያን ውስጥ 36 በመቶው በኢትዮጵያ ናይጄሪያና ኮንጎ እንደሚገኙ ተጠቆመ

‹‹ለሺሕ ዓመት በድህነት ውስጥ የነበረች አገርን በአሥር ዓመት ልንቀይር...
spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

ፖለቲካዊ ችግሮች ፖለቲካዊ መፍትሔ ይፈለግላቸው!

መንግሥት ከኦነግ ሸኔ ጋር በታንዛኒያ ዳሬሰላም ከተማ ሲያካሂድ የነበረው ንግግር ያለ ውጤት መጠናቀቁን ካስታወቀ በኋላ፣ በኦሮሚያ ክልልም ሆነ በሌሎች ቦታዎች ሰላም ለማስፈን የነበረው ተስፋ...

ኢትዮጵያን ከግጭት ቀጣናነት ማላቀቅ የግድ ነው!

ፍሬ አልባ ፖለቲካዊ ልዩነቶች ወደ ግጭት እያመሩ ለአገርና ለሕዝብ የማያባራ መከራ ሲያቀባብሉ፣ ከትናንት ስህተቶች ለመማር ፈቃደኛ ያልሆኑ ፖለቲከኞችና ተከታዮቻቸው በእሳት ላይ ቤንዚን እያርከፈከፉ ጠማማ...

አስጨናቂውን የኑሮ ውድነት የማርገብ ኃላፊነት የመንግሥት ነው!

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ማክሰኞ ኅዳር 4 ቀን 2016 ዓ.ም. ለጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ካቀረቡላቸው ጥያቄዎች መካከል አንደኛው የኑሮ ውድነትን በተመለከተ ነበር፡፡...