– የፖለቲካ እስረኞች ምሕረት እንዲደረግላቸው ጠይቋል
– የዳያስፖራ ልማት ባንክ ይቋቋም ተብሏል
መንግሥት የዳያስፖራ ፖሊሲን ይፋ ካደረገ ከሁለት ዓመት በኋላ በአገር አቀፍ ደረጃ በያመቱ እንዲካሄድ በወሰነው መሠረት፣ ዘንድሮ ለመጀመሪያ ጊዜ በተሰናዳው የዳያስፖራ ቀን በርካታ ቅሬታዎች ከዳያስፖራው ለመንግሥት ኃላፊዎች ቀረቡ፡፡
በተለያዩ አገሮች እንደሚኖሩ ከሚገመቱት ሁለት ሚሊዮን ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን መካከል አምስት ሺሕ ያህሉ ለአምስት ቀናት በሚሊኒየም አዳራሽ ሲካሄድ ቆይቶ እሑድ ነሐሴ 10 ቀን 2007 ዓ.ም. በሚጠናቀቀው የዳያስፖራ ቀን በዓል ላይ መሳተፋቸውን፣ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ በዚህ መሠረት ነሐሴ 7 ቀን 2007 ዓ.ም. በተደረገ ውይይት ወቅት የዳያስፖራ አባላቱ በመንግሥት በኩል የሚገጥሙዋቸውን ችግሮች በመዘርዘር ቅሬታቸውን አሰምተዋል፡፡
መንግሥት እንዲያስተካክል ከተጠየቀባቸው ጉዳዮች መካከል የዳያስፖራው ማኅበረሰብ በቢሮክራሲ ውጣ ውረድና በመረጃ እጦት የሚደርስበት እንግልት ይጠቀሳል፡፡ በተለይ ነዋሪነታቸው በእንግሊዝ የነበረውና ወደ አገር ቤት ከመጡ ሁለት ዓመታት ያስቆጠሩት አቶ ሀብቴ ፈረደ፣ ከቱርክ በወኪልነት በባቡር መስመር ግንባታ ላይ ለማሳተፍ ያመጡት ኩባንያ በቢሮክራሲ ሳቢያ ፋይናንሱን ወደ ኬንያና ወደ ኡጋንዳ ለመውሰድ መገደዱን ተናግረዋል፡፡ ሜጀር ግሩፕ የተባለውን የቱርክ ኩባንያ አፈላልገው ማምጣታቸውን የገለጹት አቶ ሀብቴ፣ ኩባንያው 375 ኪሎ ሜትር ርዝመት ያለውንና ከአዋሽ-ወልዲያ እስከ ሃራ ገበያ የሚዘረጋውን የባቡር መስመር ለመገንባት ጨረታውን አሸንፎ እንደነበር ይናገራሉ፡፡
ይህ ኩባንያ ለፕሮጀክቱ የሚያስፈልገውን 1.7 ቢሊዮን ዶላር ለማምጣት የአንድ ዓመት ጊዜ ተሰጥቶት እንደነበር አስታውሰው፣ ከዓለም አቀፍ የፋይናንስ ምንጮች 1.9 ቢሊዮን ዶላር ለማግኘት ችሎ እንደነበርም ጠቅሰዋል፡፡ ይሁን እንጂ ኩባንያው ለፕሮጀክቱ የሚያስፈልገውን ገንዘብ ከማምጣቱ አንድ ወር ቀደም ብሎ፣ ፕሮጀክቱ ያፒ መርከዚ ለተባለ ለሌላ የቱርክ ኩባንያ ተላልፎ ተሰጥቷል፡፡ ጉዳዩን በማስመልከት የኢትዮጵያ ባቡር ኮርፖሬሽንን ሲጠይቁ፣ ሌሎች ያልተነኩ ፕሮጀክቶች ስላሉ እነዚያ ላይ ትሳተፋላችሁ እስከዚያ ጠብቁ የሚል ምላሽ እንደተሰጣቸው ተናግረዋል፡፡
አቶ ሀብቴ እንደሚሉት፣ መንግሥት ከዚህ በኋላ በቅርብ ጊዜ ውስጥ ሌሎች አዳዲስ የባቡር ፕሮጀክቶችን ያስጀምራል የሚል ዕምነት ያጣው የቱርኩ ኩባንያ፣ በኢትዮጵያ ኢንቨስት ሊያድርግ ያመጣውን ገንዘብ ወደ ኬንያና ኡጋንዳ ወስዷል፡፡ ይህ ሊሆን የቻለው ግን የገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ሚኒስቴርና የኢትዮጵያ ባቡር ኮርፖሬሽን ተገቢውን ምላሽ ሊሰጡ ባለመቻላቸው እንደሆነ አክለዋል፡፡ ውይይት እንዲደረግ በተደጋጋሚ ቢጠይቁም አንድ ጊዜ ሚኒስቴሩ ሌላ ጊዜ ኮርፖሬሽኑን ይመለከተዋል በሚል ተደጋጋሚ ምክንያት ኩባንያው ሳይሳተፍ መቅረቱን ገልጸዋል፡፡ በመድረኩ በዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅዶች ላይ አስረጅ ሆነው የቀረቡትና ጥያቄው በቀጥታ የተሰነዘረላቸው የገንዘብና ኢኪኖሚ ልማት ሚኒስትር ዴኤታው አቶ አህመድ ሺዴ ምላሽ ሳይሰጡበት አልፈውታል፡፡
ከአቶ ሀብቴ በተጨማሪ በኢትዮጵያ ኤምባሲዎች በኩል የሚታደሰውን የትውልደ ኢትዮጵያዊነት መታወቂያ አገልግሎት ለማግኘት የሚገጥማቸውን ውጣ ውረድ የገለጹም ነበሩ፡፡ ከኤምባሲ ሠራተኞች ተገቢውን መረጃና ማብራሪያ የሚሰጣቸው በማጣት ብቻ በእያንዳንዱ የሰነድ ልውውጥ እስከ 40 ዶላር እየከፈሉ እንደሚቸገሩ አባላቱ አስታውቀዋል፡፡ በውጭ አገር ፍች ከፈጸሙ በኋላ የጋራ ንብረታቸውን ጠቅልለው በመምጣት ባዶ ለሚያስቀሯቸው ባሎቻቸው ፈቃድ እየተሰጠ ችግር ላይ እንደወደቁ የተናገሩ ሴቶችም እያለቀሱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ዶ/ር ቴድሮስ አድሃኖምንና አቶ አህመድን መፍትሔ እንዲሰጧቸው ተማጽነዋል፡፡
በአሜሪካ ለ30 ዓመታት መኖራቸውን ለሪፖርተር የገለጹት ወይዘሮ ሰብለ ነቢየልዑል፣ ወደ ኢትዮጵያ ጠቅልለው በመምጣት በቆዳና በውበት ክብካቤ ላይ የሚሠራ ‹‹ዚኒያ ኤስቴቲክስ ኤንድ አንታይ ኤጂንግ ክሊኒክ›› የተባለው የጤና ተቋም ሥራ በጀመሩ በጥቂት ጊዜ ውስጥ ያለማስጠንቀቂያ እንዲዘጋባቸው መደረጉን ተናግረዋል፡፡ የኢትዮጵያ የምግብ፣ የመድኃኒትና የጤና ክብካቤ አስተዳደርና ቁጥጥር ባለሥልጣን ላቀረበላቸው ቅድመ ሁኔታ የአንድ ዓመት ጊዜ እንዲሰጣቸው ቢጠይቁም፣ ከስምንት ወራት በላይ ሊሰጣቸው እንደማይችል ገልጾ ክሊኒካቸው ሊዘጋ መቻሉን ጠቁመዋል፡፡ ክሊኒኩ ፈቃድ ያወጣው አሜሪካ በሚገኙት የወይዘሮ ሰብለ አጋር በሆኑት ዶ/ር ስም በመሆኑ እየተመላለሱ እንዲሠሩ፣ ወይም የአንድ ዓመት ጊዜ ተሰጥቷቸው በአሜሪካ የሚያስፈልጉ ጣጣዎችን ጨራርሰው እስኪመጡ ክሊኒካቸው ከሚዘጋ፣ እስከዚያው ድረስ ተመጣጣኝ በሆኑ የሕክምና ባለሙያዎች ሥራውን ለማስኬድ እንዲፈቀድላቸው ያቀረቡት ጥያቄም ውድቅ እንደተደረገባቸው አስረድተዋል፡፡ እስካሁን አሥር ሚሊዮን ብር ከግል ሀብታቸው ኢንቨስት ማድረጋቸውንም ገልጸዋል፡፡
ከክሊኒኩ ባሻገር አቬላሜድ ቢዝነስ ቴክኖሎጂ የተሰኘ የመረጃና የትንተና ተቋም ለመመሥረት ሲንቀሳቀሱ ቢቆዩም፣ በገጠማቸው ውጣ ውረድ ሳቢያ እውን ሊያደርጉት እንዳልቻሉ የሚናገሩት ወይዘሮ ሰብለ፣ እስከቻሉት ጊዜ ድረስ ሞክረው የማይቻል ከሆነ ግን ወደ ኬንያ ሊወስዱት ወይም ወደ መካከለኛው ምሥራቅ ሊያቀኑ እንደሚችሉ ተናግረዋል፡፡ በአሜሪካ ሳይቀር ጥቂቶች ብቻ የሚገለገሉበት የዚህ ዓይነቱ ክሊኒክ ተፈላጊነቱ ከፍተኛ በመሆኑ፣ ጥያቄ እየቀረባለቸው እንደሚገኝም አስረድተዋል፡፡
በመድረኩ ለባለሥልጣናቱ ከቀረቡ ጥያቄዎች መካከል የፖለቲካ እስረኞችና በሃይማኖት ምክንያት የታሰሩ ካሉ እንዲፈቱ የሚለው ይገኝበታል፡፡ መንግሥት በፖለቲካና በሃይማኖት ምክንያት ያሰራቸው ሰዎች እንዳሉ እንሰማለን ያሉት ጥያቄ አቅራቢዎች፣ ምሕረት እንዲያደርግ ጠይቀዋል፡፡ ከዚህ ባሻገርም ለዳያስፖራው ጥያቄዎች መፍትሔ ሊሆኑ ይችላሉ ከተባሉት መካከል የዳያስፖራ ልማት ባንክ እንዲቋቋም፣ ገለልተኛ የዳያስፖራ ኮሚሽን እንዲመሠረት፣ የዳያስፖራው አባላት በአክሲዮን መደራጀት የሚችሉበት ዕድል እንዲሰጥ የሚጠይቁት ይጠቀሳሉ፡፡ ዶ/ር ቴድሮስና አቶ አህመድ ለቀረቡላቸው ጥያቄዎችና ማስተካከያ ይደረግባቸዋል ስላሏቸው የመልካም አስተዳደር፣ የመንግሥት አገልግሎትና መሰል ጉዳዮች ላይ ማሻሸያ እንደሚደረግ ገልጸዋል፡፡ በፖለቲካና በሃይማኖት ጉዳይ ታሰሩ ስለተባሉት ሰዎች ጉዳይ ሚኒስትሮቹ በቀጥታ ምላሽ ሳይሰጡበት አልፈዋል፡፡
ተደጋግመው ለባለሥልጣናቱ ከቀረቡት ችግሮች ባሻገር የዳያስፖራው መድረክ ለዶ/ር ቴድሮስ አፍቅሮት የታየበትም ነበር፡፡ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ እንደ አንድ ታዋቂ አርቲስት ከፍተኛ ጭብጨባና ፉጨት ተስተጋብቶላቸዋል፡፡ ፎቶ አብረዋቸው እንዲነሱ የሚጠይቋቸውና ፊርማቸውን እንዲያኖሩላቸው የሚወተውቱም በርካቶች ነበሩ፡፡ ከዚህ በላይ ደግሞ ሎሬት ሰዓሊና ገጣሚ ገብረክስቶስ ደስታ ከደረሰው ስደት ተኮር ግጥም በመዋስ የመግቢያ ንግግራቸውን አሰምተዋል፡፡ አንጋፋው ድምፃዊ ዓሊ ቢራን በማጀብም አንጎራጉረዋል፡፡
በሌላ በኩል ለአሥረኛ ጊዜ በተካሄደው ዓመታዊ የዳያስፖራ ኢንቨስተሮች ሽልማት ሥነ ሥርዓት ላይ፣ የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ቢዝነስ ፎረም አምባሳደር ግርማ ብሩን ጨምሮ ሁለት ኢንቨስተሮችን ሸልሟል፡፡ ሐሙስ ነሐሴ 7 ቀን 2007 ዓ.ም. ምሽቱን በሸራተን አዲስ በተካሄደ ሥነ ሥርዓት አምባሳደር ግርማ ብሩ ለዳያስፖራ ኢንቨስትመንትና የንግድ መስኮች ላበረከቱት ድጋፍ ‹‹የዓመቱ የቢዝነስ ሻምፒዮና›› ተብሎ የተሰመውን አምና በአሜሪካ የተጀመረውን የተቋሙን ሽልማት ከዶ/ር ቴድሮስ እጅ ተቀብለዋል፡፡ ዶ/ር አከዘ ጣዕመና አቶ ታምራት በቀለ በጤና ዘርፍ ባደረጉት ኢንቨስትመንትና አስተዋጽኦ ልዩ ተሸላሚ ሆነዋል፡፡
ዘንድሮ የልዩ አስተዋጽኦ ተሸላሚ እንደሚሆኑ ይፋ የተደረጉት በኢትዮጵያ የሕምክና አገልግሎት ዘርፍ በመንቀሳቀስ ላይ የሚገኙ ሁለት ባለሀብቶች ናቸው፡፡ ከቢዝነስ ፎረሙ በተገኘው መረጃ መሠረት በአሜሪካ ሲማሩና ሲሠሩ ቆይተው ወደ ኢትዮጵያ በመምጣት ኢንቨስት በማድረግ ትልልቅ የሕክምና ተቋማትን የሚያንቀሳቅሱት አቶ ታምራት በቀለና ዶክተር አከዛ ጣዕመ ናቸው፡፡
አቶ ታምራት የኢንተርናሽናል ክሊኒካል ላብራቶሪስ እህት ኩባንያ ለሆነው ሜድፋርም ሆልዲንገስ አፍሪካ መሥራችና ዋና ሥራ አስፋጻሚ ናቸው፡፡ እ.ኤ.አ. በ2004 ከአሜሪካ ወደ ኢትዮጵያ በመመለስ የላቦራቶሪውን ተቋም በአዲስ አበባ መሥርተዋል፡፡ በአፍሪካ ዓለም አቀፍ መሥፈርቶች የጤና ክብካቤ ዕውቅና በማግኘት የሚሠራ ተቋም ለመሆን የበቃ ላቦራቶሪ መሆኑን መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ በኢትዮጵያ ብቸኛው ፈቃድ ያገኘ ተቋም በመሆን የሚንቀሳቀሰው ይህ ላቦራቶሪ፣ ባለፉት አሥራ አንድ ዓመታት 900 ሺሕ ደንበኞችን ማፍራት መቻሉም የኩባንያው ዝክረ ታሪክ ይዘረዝራል፡፡ ባለትዳርና የአምስት ልጆች አባት የሆኑት አቶ ታምራት ኑሯቸው በአዲስ አበባ ካደረጉ ሰንብተዋል፡፡
ዶ/ር አከዛ በበኩላቸው የቅዱስ ያሬድ ጠቅላላ ሆስፒታልንና በቅርቡም አሜሪካን ሜዲካል ሴንተርን ከሸሪኮቻቸው ጋር በመመሥረት፣ በሜዲካል ዳይሬክተርነት እየሠሩ ይገኛሉ፡፡ ከዚህ በተጨማሪም በግል ሆስፒታሎች ማኅበር ፕሬዚዳንትነት ማገልገላቸውም ይታወቃል፡፡ የሦስት ልጆች አባት የሆኑት ዶ/ር አከዛና አጋሮቻቸው የመሠረቷቸው የሕክምና ተቋማት፣ በአዲስ አበባና በአጎራባች አካባቢዎች ለሚኖሩ አንድ መቶ ሺሕ ታካሚዎች አገልግሎት እየሰጡ እንደሚገኙ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ በአሁኑ ወቅትም ግማሽ ቢሊዮን ብር በሚጠጋ ካፒታል የሜዲካል ቱሪዝም ይፈጥራል ያሉትን ዘመናዊ ሆስፒታል ለመገንባት እየተንቀሳቀሱ እንደሚገኙ ታውቋል፡፡ ባለፈው ዓመት አቶ አዲስ ዓለማየሁና አቶ ዘመዴነህ ንጋቱ በአሜሪካ በተካሄደው ሥነ ሥርዓት ተሸላሚ እንደነበሩ ይታወሳል፡፡