የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽንን በፕሬዚዳንትነት ይመሩ የነበሩት ወ/ሮ ብሥራት ጋሻው ጠና የወከላቸው የአማራ ክልል ከሥልጣናቸው ቢያነሳቸውም፣ የዓለም አቀፍ አትሌቲክስ ፌዴሬሽኖች ማኅበር ግን ለከፍተኛው የምክር ቤት አባልነት በዕጩነት አቀረባቸው፡፡ ዓለም አቀፉ ፌዴሬሸን ከነሐሴ 13 ቀን 2007 ዓ.ም. ጀምሮ ለሁለት ቀን በቤጂንግ (ቻይና) በሚያካሂደው 50ኛው ጠቅላላ ጉባኤ ለምክር ቤቱ ለሴቶች ከተያዘው ስድስት መቀመጫ አንዱን ለመቆናጠጥ ወ/ሮ ብሥራት ከ10 በአትሌቲክስ በተወዳዳሪነትና በአመራርነት ካሳለፉ ዕጩ እንስቶች ጋር እንደሚወዳደሩ ማኅበሩ በድረ ገጹ ዘግቧል፡፡ ከአፍሪካ አህጉር ከኢትዮጵያ ሌላ ሞሮኳዊቷ የሎስአንጀለስ ኦሊምፒክ 400 ሜትር መሰናክል አሸናፊ ናዋል ኢል ማውታዋኬል መታጨታቸው ታውቋል፡፡ ኬንያ ለምክትል ፕሬዚዳንትነትና ለምክር ቤት አባልነት አንድ፣ አልጀሪያ፣ ቱኒዚያ፣ ሴኔጋል፣ ቤኒን፣ ናይጀሪያ ደግሞ አንድ አንድ ዕጩዎች አቅርበዋል፡፡