Tuesday, April 16, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ኪንና ባህል‹‹ንባብ የስኬት ድባብ›› በሐዋሳ ሊካሄድ ነው

‹‹ንባብ የስኬት ድባብ›› በሐዋሳ ሊካሄድ ነው

ቀን:

ሐዋሳ ከተማ በሳምንቱ መገባደጃ ልዩ ልዩ የሥነ ጽሑፍ ክንውኖች የሚስተናገዱበት ዝግጅት አሰናድታለች፡፡ ‹‹ንባብ የስኬት ድባብ›› በሚል መሪ ቃል ነሐሴ 16 እና 17 ቀን 2007 ዓ.ም. በሚካሄደው ዝግጅት አንጋፋ ደራስያን ተሞክሯቸውን የሚያካፍሉበት፣ አንጋፋና አማተር ጸሐፍት ሥራዎች የሚስተናገዱበት፣ በከተማዋ ንባብ ነክ እንቅስቃሴ ላይ ያተኮሩ ጽሑፎች የሚደመጡበትና በሥነ ጽሑፍ ዙሪያ የተሠሩ ጥናቶች ለውይይት የሚቀርቡት እንደሆነ የአዘጋጁ ድርጅት ዋዜማ ሚዲያና ኮሙዩኒኬሽን ሥራ አስኪያጅ ኢዮብ ጽጌ ለሪፖርተር ገልጿል፡፡

እንደ ኢዮብ ገለጻ፣ ቅዳሜ ከሰዓት ሦስት ደራስያን እሑድም በተመሳሳይ ሰዓት ሦስት ደራስያን ከሕይወት ልምዳቸው የሚያካፍሉበት መድረክ ተዘጋጅቷል፡፡ የሚሳተፉት ደራስያን ዘነበ ወላ፣ ኃይለመለኮት መዋዕል፣ ዲያቆን ዳንኤል ክብረት፣ ይታገሱ ጌትነት፣ ዳንኤል ወርቁና አንዱዓለም አባተ (የአፀደ ልጅ) ናቸው፡፡

  የመድረኩ አዘጋጆቹ ደራስያኑ ተፅዕኖ መፍጠር ይችላሉ ብለው ያመኑባቸው እንደሆኑ ኢዮብ ተናግሯል፡፡ በሁለቱም ቀናት ስለተጋባዥ ደራስያን ማንነትና ሥራዎቻቸው የሚያወሱ ዝግጅቶች ይኖራሉ፡፡ ደራስያኑ በተለይም የሥነ ጽሑፍ ዝንባሌ ላላቸው ግለሰቦች መነሳሳትን እንደሚፈጥሩ ተስፋ ያደርጋል፡፡ ‹‹በሥነ ጽሑፍ ብዙ የሠሩ ደራስያን መጥተው ተሞክሯቸውን ሲያካፍሉ ወጣቶችም ተነሳሽነታቸው ይጨምራል፤››  በማለት ገልጿል፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

በዝግጅቱ ላይ በሥነ ጽሑፍና ቋንቋ ላይ ጥናትና ምርምር ያደረጉ የሐዋሳ ዩኒቨርሲቲ መምህራን ጽሑፎቻቸውን ያቀርባሉ፡፡ ከሚስተናገዱት የጥናት ጽሑፎች መሀከል በከተማዋ ስለሚዘጋጁ የሥነ ጽሑፍ ሥራዎች ይዘትና ሥርጭት የሚያትቱ ይገኙበታል፡፡ ሐዋሳ የሚኖሩና በተለያየ የሥራ መስክ የተሰማሩ ግለሰቦች ምልከታ የሚቀርብበት መድረክም እንደተዘጋጀ ሥራ አስኪያጁ ተናግሯል፡፡

 በዝግጅቱ ላይ ከከተማው ነዋሪዎች መሀከል ‹‹የንባብ አምባሳደር›› በሚል ስለ ንባብ ቅስቀሳ እንዲያደርጉ ዝግጅት ክፍሉ የመረጣቸው ግለሰቦች ይፋ ይደረጋሉ፡፡ ደራስያን፣ መምህራን፣ ጋዜጠኞች፣ የመንግሥት ሠራተኞችና ሌሎችም ተካተውበታል፡፡ በቅርቡ በአዲስ አበባ ኤግዚቢሽን ማዕከል ‹‹ንባብ ለሕይወት›› በሚል በተዘጋጀው የመጻሕፍት ዐውደ ርዕይ ላይ ‹‹የንባብ አምባሳደር›› በሚል የተመረጡ ግለሰቦች ወደ ሐዋሳ የመጋበዝ እቅድ እንዳላቸው ኢዮብ አስረድቷል፡፡  

በዝግጅቱ ላይ ሙዚቃ፣ ባህላዊ ውዝዋዜ እንዲሁም ሥነ ግጥም ይቀርባል፡፡ ለታዳሚዎች የጥያቄና መልስ ውድድር የተዘጋጀ ሲሆን፣ የመጻሕፍት ሽልማትም ይኖራል፡፡ እንደ አዘጋጁ ገለጻ፣ በሐዋሳ ከትምህርት መጻሕፍት ውጪ ያሉ የሥነ ጽሑፍ ሥራዎች ገበያ የተዳከመ ነው፡፡ በንባብ ዙሪያ የሚደረጉ እንቅስቃሴዎችም በስፋት አይስተዋሉም፡፡ ዝግጅቱ ይህንን ችግር ለመቅረፍ እንደ አንድ እርምጃ እንደሚወሰድ አስረድቷል፡፡

መጻሕፍት፣ የሙዚቃ አልበሞች፣ ፊልሞችና ሌሎችም ኪነ ጥበባዊ ሥራዎች በከተማዋ ሲመረቁ እንዲሁም በስፋት ሲሰራጩ አይስተዋልም ያለው ኢዮብ፣ ዝግጅቱ ከተማዋ ጥበባዊ ሥራዎች ማስተናገድ የምትችልበትን መንገድ በመቀየስ ረገድ ጠቀሜታ እንደሚኖረው ተናግሯል፡፡

ዝግጅቱ ወጣቶችን ያማከለ ሲሆን፣ ከተለያዩ አካባቢዎች ወደ ከተማዋ የሄዱ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችም ይሳተፋሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡ አዘጋጁ እንዳለው በቀጣይ በከተማዋ በንባብ ረገድ እንዲመጡ ለሚሿቸው ለውጦች ወጣቶች ላይ ማተኮራቸው ጠቃሚ ይሆናል፡፡

ሐዋሳ ከቱሪስት መዳረሻ ከተሞች አንዷ መሆኗንና መዝናኛዎች እንደሚገኙባት በማጣቀስ፣ የጥበብ እንቅስቃሴም ጠንካራ መሆን እንዳለበት ተናግሯል፡፡ ‹‹በብዙ የቱሪስት መስህቦች የምትታወቀው ከተማዋ፤ በንባብ ረገድም ብዙ ሊሠራባት ይገባል፤›› ይላል፡፡ አዘጋጆቹም በንባብ ረገድ የሚታየውን ክፍተት ለመሙላት እንዲቻል ዝግጅቱን በየሦስት ወሩ የማካሄድ እቅድ አላቸው፡፡

በተያያዥም በከተማዋ የሚሠራጩ ጋዜጦች፣ መጽሔቶችና መጻሕፍትን ቁጥር የመጨመርና ጀማሪ ጸሐፊዎች ሥራዎቻቸውን ለኅትመት የሚያበቁበትን ዕድል የማመቻቸት እቅድ አላቸው፡፡

የሐዋሳ ነዋሪ የሆኑትና በደቡብ ኤፍኤም ላይ ‹‹የጥበብ ጠብታ›› የሚል መሰናዶ ያላቸው አዘጋጆቹ ‹‹የንባብ አገራዊ ፋይዳ የጎላ ነው፤ በማንኛውም ዘርፍ ለውጥ ለማምጣት የሚቻለውም በማንበብ ነው፤›› የሚል ኃይለ ቃልም ሰንቀዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ቪር ጀነራል ትሬዲንግ ኃ/የተ/የግ/ማኀበር የጨረታ ማስታወቂያ

ቪር ጀነራል ትሬዲንግ ኃ/የተ/የግ/ማኀበር በገቢ እና በውጭ ንግድ እንዲሁም...

ያልተቃናው የልጆች የንባብ ክህሎት

አንብቦና አዳምጦ መረዳት፣ የተረዱትን ከሕይወት ጋር አዋህዶ የተቃና ሕይወት...

እንስተካከል!

ሰላም! ሰላም! ውድ ኢትዮጵያውያን ወገኖቼ እንዲሁም የሰው ዘር በሙሉ፣...

የሙዚቃ ምልክቱ ሙሉቀን መለሰ ስንብት

የኢትዮጵያ ዘመናዊ ሙዚቃ በ1950ዎቹ እና በ1960ዎቹ በኪነ ጥበባትም ሆነ...