Thursday, May 23, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ኪንና ባህልየተመራቂዎች ተስፋ ከዐውደ ርዕይ ባሻገር

የተመራቂዎች ተስፋ ከዐውደ ርዕይ ባሻገር

ቀን:

ዘንድሮ ከአለ የሥነ ጥበብና ዲዛይን ትምህርት ቤት ከሚመረቁ ተማሪዎች አንዱ አረጋ ሙላቱ ነው፡፡ የሚመረቀው ከግራፊክስ ትምህርት ክፍል ሲሆን፣ የመመረቂያ ሥራዎቻቸውን በትምህርት ቤቱ ጋለሪ እያሳዩ ካሉ ተማሪዎች አንዱ ነው፡፡ አረጋ መመረቂያውን ያዘጋጀው የዘመናዊነት መስፋፋት በማኅበረሰቡ የዕለት ከዕለት ሕይወት ላይ የሚያሳድረውን ተፅዕኖ በሚያሳዩ ሥራዎች ነው፡፡

እሱ እንደሚለው፣ በዘመናዊነት መስፋፋት ምክንያት የኅብረተሰቡ አኗኗር ችግር ውስጥ እንዳይወድቅ ጥንቃቄ ያስፈልጋል፡፡ የዘመናዊነት ሒደት ድንገቴ ሳይሆን ጤናማ ፍጥነትን የተከተለ መሆን እንዳለበት ሥራዎቹ እንደሚያስረዱ ይናገራል፡፡

ከዚህ ቀደም አረጋ ከሌሎች ተማሪዎች ጋር ዐውደ ርዕዮች ቢያቀርብም የመመረቂያው ዐውደ ርዕይ ልዩ እንደሆነ ይናገራል፡፡ ‹‹የአራት ዓመት ጭንቀት  ውጤት ነው፡፡ ከትምህርት ቤቱ ያገኘኋቸውን ነገሮች ለሕዝብ የማሳይበት ዐውደ ርዕይ በመሆኑ ትልቅ ቦታ እሰጠዋለሁ፤›› ይላል፡፡ ሥራዎቹን ለሕዝብ ከማቅረቡ ባሻገር ስለዘመናዊነት መስፋፋት ማስተላለፍ የፈለገውን መልዕክት ማሳየቱ እንዳስደሰተው ያክላል፡፡

- Advertisement -

ከምርቃት በኋላ የሚጠብቀው የሥነ ጥበብ ዓለም በውጣ ውረድ የተሞላ ሊሆን እንደሚችል ይገምታል፡፡ በግሉ መሥራት ከባድ ስለሚሆንም ከጓደኞቹ ጋር ስቱዲዮ የመጋራት ዕቅድ አላቸው፡፡ የመመረቂያ ዐውደ ርዕዩ በተከፈተበት ሰሞን ለሥዕል የሚመች ቤት እያፈላለጉ ነበር፡፡ ኅብረተሰቡ ለሥነ ጥበብ የሚሰጠው ዋጋ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተሻሻለ መምጣቱ ለተመራቂዎች መልካም ዕድል እንደሚፈጥር ያምናል፡፡ እሱ የሥነ ጥበብ ትምህርት ቤት ከገባበት ጊዜ አንስቶ ያስተዋላቸውን ለውጦችም ይጠቅሳል፡፡

ትምህርት ቤቱ ከተቋቋመበት ጊዜ አንስቶ በየዓመቱ የተመራቂ ተማሪዎችን ዐውደ ርዕይ ያዘጋጃል፡፡ የዘንድሮው ዐውደ ርዕይ የተከፈተው ነሐሴ 7 ቀን 2007 ዓ.ም. አመሻሽ ላይ ሲሆን፣ ቀዳማዊት እመቤት ወ/ሮ ሮማን ተገኝተው ነበር፡፡ ተመራቂዎች ሥዕል፣ ቅርጻ ቅርጽና ዲዛይን ያቀረቡ ሲሆን፣ ስለ ሥራዎቻቸው መጠነኛ መግለጫ በጽሑፍ አስፍረዋል፡፡ ለሥራዎቻቸው ያነሳሷቸውን ሁነቶች የገለጹም ነበሩ፡፡ ከነዚህ መካከል በሐረር ከተማ መስጊዶች ላይ ያተኮረ ሥራውን ያቀረበው ወሰን ጌታቸውና የሽሮሜዳ ሸማኔዎችን ጥበብ መነሻ ያደረገው ኤፍሬም ሙሉጌታ ይጠቀሳሉ፡፡

ዮሐንስ ሙላቱ የአርት ኤጁኬሽን ትምህርት ክፍል ተመራቂ ነው፡፡ በዐውደ ርዕዩ ያቀረበው ኢንስታሌሽን፣ ሥዕልና ፐርፎርማንስ ነው፡፡ ‹‹ዘ ራይተርስ ሩም›› (የጸሐፊው ክፍል) የተሰኘው መጠነኛ ክፍል ያሳያል፡፡ ወንበሮች፣ ጠረጴዛ፣ ቁምሳጥን፣ ኮሜዲኖና ሌሎችም የቤት ውስጥ መገልገያዎች ጋዜጣ ተለጥፎባቸው ይስተዋላሉ፡፡ ጅምር ጽሑፍ ያለበት ታይፕራይተርና በጋዜጣ የተጠቀለለ ኩባያ ከጸሐፊው ጠረጴዛ ላይ ይታያሉ፡፡

ለሥራው ያነሳሳው የሰው ልጅ ዕውነታን በሚያይበት መንገድና በእውነታ መካከል ክፍተት አለ የሚል ጽንሰ ሐሳብ ነው፡፡ ዮሐንስ እንደሚለው፣ ‹‹ዘ ራይተርስ ሩም›› የጸሐፊዎችን ዕይታና እውነታውን በንጽጽር ያቀረበ ነው፡፡

የመመረቂያ ዐውደ ርዕዩ ለተማሪዎች ጥሩ ተሞክሮ እንደሚኖረው ያምናል፡፡ በሥነ ጥበብ ሕይወታቸው ከትምህርት ምዕራፍ ወደ ሥራ መሸጋገሪያ መሆኑንም ይናገራል፡፡ ዮሐንስ በቀጣይ ከማኅበረሰቡ ጋር በቀጥታ የሚያገናኙትን ሥራዎች ማቅረብ ይፈልጋል፡፡ እንደ ምሳሌ የሚጠቅሰው ፐርፎርማንስ አርትና ማኅበረሰብ አቀፍ ፕሮጀክቶችን ነው፡፡ ትምህርት ቤት ሳሉ ስቱዲዮ ስላላቸው የግል ስቱዲዮ አላስፈለገውም፡፡ አሁን ግን እንደሌሎች ተመራቂዎች ሁላ ስቱዲዮ እያፈላለገ ነው፡፡ እንደ ስቱዲዮ ሁሉ ከትምህርት ቤቱ ያገኟቸው የነበሩ ነገሮች ተመርቀው ሲወጡ አለመኖራቸው ፈታኝ ቢሆንም፣ መሰናክሎችን እንደሚወጣ ተስፋ ያደርጋል፡፡

ሌላው ተመራቂ ሰለሞን ገለቴ ከፔይንቲንግ ትምህርት ክፍል ሲሆን፣ የመመረቂያ ሥራዎቹ የከተሜነት መስፋፋት በሕዝቡ አስተሳሰብ ላይ የሚያደርሰውን ተፅዕኖ ያሳያሉ፡፡ የከተሜነት መስፋፋትን ከሚያንፀባርቁ ሥራዎቹ ዘመናዊ ገጽታ የተላበሱ መኖሪያ ቤቶች  ይጠቀሳሉ፡፡ የተጨናነቁ አካባቢዎች በሰማይ ጠቀስ ሕንፃዎች በሚለወጡበት ወቅት ለዘመናት የተገነባው ማኅበራዊ ሕይወትስ ምን ይጠብቀዋል? ሲል ይጠይቃል፡፡

በዐውደ ርዕዩ የቀረቡት ሥራዎቹ ግንባታ የተስፋፋባቸው አካባቢዎችን፣ የግንባታ ሠራተኞችን፣ የቀደምት አካባቢዎችን ገጽታና ሌሎችም ለውጥን የሚያንፀባርቁ ሁነቶች ያሳያሉ፡፡ ዐውደ ርዕዩ ከበርካታ ሰዎች ጋር ለመገናኘት ዕድል እንደፈጠረላቸው ይናገራል፡፡ ወደፊት አብረዋቸው የሚሠሩ ጋለሪዎችና ኪውሬተሮች እንዳገኘ ይገልጻል፡፡ ከትምህርት ቤት ሲወጡ ፈተናዎች እንደሚጠብቋቸው ከአረጋና ዮሐንስ ጋር ይስማማበታል፡፡ አዲስ ምሩቃን በጋራ ቢሠሩ ወጪ በመጋራትና ሐሳብን በመካፈል ረገድ እንደሚጠቀሙ ይገልጻል፡፡

ሰለሞን ተመራቂ ተማሪዎች ከትምህርት ቤታቸው ድጋፍ ቢደረግላቸው ችግሮች ይቀሉላቸዋል ይላል፡፡ ትምህርት ቤቶች ወርክሾፖችን በማዘጋጀትና ተማሪዎችን በማሳተፍ ዕገዛ ሊያደርጉ እንደሚችሉ ይናገራል፡፡

የትምህርት ቤቱ መምህር ረዳት ፕሮፌሰር በቀለ መኮንን እንደሚናገረው፣ በየዓመቱ ተመራቂዎች የሚያቀርቡት ዐውደ ርዕይ የደረሱበትን ደረጃ የሚያሳይ ነው፡፡ ተማሪዎች ከተመረቁ በኋላ በሥነ ጥበብ ትምህርት ቤቱ በሚዘጋጁ ጥበባዊ ክንውኖች መሳተፍ እንዳለባቸው ያክላል፡፡ ከዓመት ዓመት የሴት ተመራቂዎች ቁጥር መጨመሩ ቤተሰብ የሚያደርሰው ተፅዕኖ መቀነሱንም ያመላክታል ይላል፡፡ በአንፃሩ ተመራቂዎቹ በሕይወታቸው በሚገጥሟቸው ውጣ ውረዶች ከሥነ ጥበብ ሲርቁ እንደሚታይ ይገልጻል፡፡ ዘንድሮ ከትምህርት ቤቱ የተመረቁት 19 ተማሪዎች ሲሆኑ፣  ዐውደ ርዕዩ እስከ ጥቅምት 6 ቀን 2008 ዓ.ም. ለሕዝብ ዕይታ ክፍት ሆኖ ይቆያል፡፡

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የማዳበሪያ አቅርቦትና ውጣ ውረዱ

በቅፅል ስሙ “The Father of Chemical Warfare” እየተባለ የሚጠራው...

የኢትዮጵያ ልማት ባንክ የትርፍ ምጣኔውን ከ70 በመቶ በላይ አሳደገ

ከሁለቱ መንግሥታዊ ባንኮች መካከል አንዱ የሆነው የኢትዮጵያ ልማት ባንክ...