እነሆ ከመገናኛ ወደ ኮተቤ ልንጓዝ ነው። ሾፌርና ወያላ ጎማ ተንፍሶባቸው እየቀየሩ ናቸው። በዚህ ስንሞላው በዚያ እየፈሰሰ፣ በዚያ ስናጠጣ በዚህ እየደረቀ፣ ደግሞ ወዲያ ስናፍስ ወዲህ እየተዘረገፈ ጉዳያችን ሁሉ በዋለበት ይቀራል። አንድ አይፈርድ ‘አንድ አይነድ’ ሆኖ ሰሚ ያጣው ኑሯችን ነገር ያብሰለስለናል። ተብሰልስለን የማንበስል፣ ተንተክትከን የማንገነፍል፣ ተንዶቅዱቀን የማንከነበልበት ምክንያትም ግራ ነው። እንዲያው ዝም እንዲያው ዝም። ይህ ነው የለ ያ ነው የለ። ብቻ መጓዝ። መሄድ! መሄድ! መሄድ! ፌርማታችን የትየለሌ፣ ባጣ ቆያችን እልፍ። ዘመን በዘመን ቢባዛ ሰቀቀናችን ጫፍ የማይደርስብን፣ ለአፍታ ከገዛ ህሊናችን መተያየት ማውጋት የፈራን ጤዛዎች . . . ። ፍጥረት በምኞቱ ቀለበት በመሻቱ ስልቻ እየተሞላ በከንቱነት የሚጋራው ጎዳናም አይናገር አይጋገር፣ እንዲያው ዓይን ዓይናችን ሲል ታሪክ መመዝገብ አቁሞ ተውሳክ ብቻ የወረራት ዓለም ውስጥ ያለን እንመስላለን።
ሳር ያለ ሐሳብ እየለመለመ፣ የሜዳ አበባ ያለ አትክልተኛ እያበበ፣ አዕዋፍ ያለ ጭንቅ አየር እየቀዘፉ የሰው ልጅ ለአንገት ማስገቢያ፣ ለዕለት ጉርሱ ሲታመስ . . . ሳቅ ሳቅም ይላል፤ እንባ እንባም ይላል። ፍልስፍናችን ያው የድግግሞሹ ሕይወታችን ውልድ ነውና ተደጋገመ ብሎስ ማን በምን ጥበቡ ይጠይቀናል? በዛና አነሰስ የማን አንጡራ ቃላት ናቸው? ዝምታስ ማን ያፀደው ሕገ መንግሥት ነው? የመሬትስ ነው የሰማይ? ስንጠይቅ ውለን ስንጠይቅ ብናድር ቋቱ አይሞላም። የድካማችን ደመወዝም የሰቀል ሽርፍራፊ አትሰፈርም። እንዲሁ ድካም፣ እንዲሁ ዋይታ፣ እንዲሁ ነገር፣ እንዲሁ ሁካታ እንደ ቀንና ሌት፣ ወራት ዘመናት ይፈራረቃሉ። መቆም የሚባል ነገር አይታሰብም። እንኳን ለመቆም እየተፍጨረጨርን ተኝተንም ካልተገላበጥን አይሆንም። ምናልባት የዘመኑ መርህ መገላበጥ የሆነው ለዚያ ይሆን?
“አልጨረሳችሁም?” ፊቷ መጠጥ ያለ ዘንካታ ወያላውን ታናግረዋለች። “ምናለበት ብትታገሱን? እንኳን እኛ ባቡሩን አልታገሳችሁም?” ወያላው ነገር ይፈትላል። በላብ ወርዝቶ ጎማውን እያጠበቀ ደግሞ አፍታ ሳይቆይ ግቡ ይለናል። ገባን። ሾፌሩ ሞተሩን አስነሳ። “የማን ነው ደፋር? ታክሲና ባቡር ያወዳድራል?” እያለች ልጅት መጨረሻ ወንበር ላይ ካጠገቤ ተቀምጣለች። እሷን ተከትሎ አንድ የሰውነቱ ውፍረት ቅጥ የሌለው ወጣት፣ “የት አባቴ ልገባ ነው?” ብሎ ይድበለበላል። ልጅት በግማሽ ጎኗ እኔ ላይ ተንጋላ (የእኔ ዕጣ ያደረሰው ‘ኢኮኖሚስቶቻችን እንደሚለኩት ይኼን ይኼን ጊዜ ልባችን ላይ ጊዜ ቢያጠፉ የኢኮኖሚ ዕድገቱን እንዴት የበለጠ ፈጣን ማድረግ እንደሚችሉ ይረዱ ነበር’ ያለኝ አንድ ተሳፋሪ ትዝ ይለኛል) እያሳለፈችው፣ “ይኼኔ ባቡሩ ሥራ ጀምሮ ቢሆን ኖሮ እንደ ኦሊምፒክ ቀለበቶች፣ ቀለበቶቻችን ባልተሳሰሩ ነበር፤” እያለችኝ ትስቃለች። መሀል መቀመጫ ላይ ከአንድ ጎልማሳ አጠገብ የተሰየመች ወይዘሮ ሰምታት፣ “ምናለበት ይኼን ባቡር አሥር ጊዜ ስሙን እያነሳችሁ በስቅታ ልትገድሉት ነው? ትናንት ለምርጫ ቅስቀሳ ፍጆታ ዋለ። ደግሞ ዛሬ አንድ በአንድ ለመወሰን? ጉድ እኮ!” ብላ ስታሽሟጥጥ ጎልማሳው ቀበል አድርጎ፣ “ኧረ መቀስቀሻም መገኘቱ ትልቅ ለውጥ ነው። ይኼንንስ ማን አየብን?” ብሎ ትግ ትጉን ጀማመረው። በማን አየብን እዚህ ከመድረሳችን ደግሞ ዘንድሮም ልንጓዝ ነው። መጓዛችንንስ ማን አየብን?
ጉዟችን ቀጥሏል። ጋቢና ከተሰየሙት አንዱ በስልክ ይነታረካል። “ስማ ስልኩ እኮ የሚሠራው በካርድ ነው፣ ፍሬ ፍሬውን አውራ፤” ይላል። እንኳን ስልኩ ሰውም በካርድ መሥራት ጀምሯል ኧረ!” ይላል ከመጨረሻዎቹ በዚያ ጥግ የተቀመጠው። “ታዲያ ካርድ መሙላት ያቃተው አለቀለት በለኛ?” ስትል ከሾፌሩ ጀርባ የተቀመጠች ዘመናይ ከሩቅ ቅርብ ሆና ማይኩን ተቀበለችው። “ለስንቱ ይሆን ከሆዳችን ቀንሰን ካርድ እየሞላን የምንዘልቀው? ያም አምጡ ይኼም አምጡ ባይ ሆኗል፤” ይላል ከጎኗ የተቀመጠ ቀጠን ያለ ወጣት። ሁሉም አጉርሱኝ ባይ ሆነ ብሎ ዝም ምንድነው ልጄ? ሁሉም ካልክ ዘንዳ አንተንም ጨምርና ንስሃ ግባ፤” አሉት ሦስተኛው ረድፍ ላይ የተሰየሙት ቄስ። “አይ አባት ጣት መቀሳሰሩን ትተን ሸክማችንን በጋራ መሸከም ብናውቅ፣ እስከ ዛሬ እርስ በርስ በዓይነ ቁራኛ ስንተያይ እንኖር ነበር?” ቢላቸው ከሰውነቱ ወይ ከኑሮ ማንኛው እንደ ከበደው ያላወቅንለት ወጣት፡፡ እሳቸውም መልሰው፣ “እሱስ ልክ ነህ ልጄ። ምን ይደረግ ያንዱን ሥጋ አንዱ መሸከም እያቃተው እኮ ነው፤” አሉት።
ነገር በፌስቡክ ብቻ የሚገባው ዝም ሲል ሌላው ሳቀ። ሼኩ በፈገግታ ጣልቃ ገቡና፣ “ይኼን ካወቅክ ዘንድ ሆድ አየሁ ማለትን እንደማያውቅ ከተረዳህ ይኼ ሁሉ ስብ ምንድነው? ለሰማዩም ለምዱሩም እኮ አይበጅም። ኧረ ለጤናም ጥሩ አይደለም፤” ሲሉት ወጣቱ ወዲያው የጨዋታውን መንፈስ ቀየረው። የሰውነቱ ውፍረት አገር እንደ ነቀዝ እየሰረሰ ከሚያፈርሰው ‘ብቻዬን ጠብድዬ ልሙት’ ብሂል ጋር መነካካቱ አናደደው መሰል ቁጣው ድምፁ ስርቅርቃ መሀል አታሞ እየደለቀ፣ “መሆንን ትተን መምሰል፣ መምሰል ካልን አይቀር ምናለበት እኛስ ስብ ጠናባቸው ብንባል? ቀለን ተቀብረን ማን አከበረን?” ብሎ አዋዝቶ የልቡን ተናገረ። ስንቱ ነው ግን የልቤን ልናገር እያለ ልቡን የሚያጣው እናንተ?!
ወያላችን ሒሳብ እየተቀበለ እጅ በእጅ መልስ ይመልሳል። “እሰይ እንዲህ እጅ በእጅ ውለታህን የሚመልስልህ አትጣ፤” ትለዋለች ወይዘሮዋ። “በገዛ መልሳችን ደግሞ የምን ውለታ ነው? እንዲህ እያልን መሰለኝ የገዛ ሀብታችንንና ርስታችንን በአረም ያስበላነው፤” አለ ጎልማሳው በስጨት ብሎ። “ምን ሆኖ ነው ግን ሰው ትንኝ ስትነድፈውም እባብ ሲነክሰውም እኩል የሚበሳጨው?” ትለኛለች ከጎኔ። እሷን ሰምቶ ጥግ የተቀመጠው፣ “ገበያው ነዋ። የሸቀጥና የአሻቃጭ ዘመን ብቻ ሆነ። ቴሌቪዥኑ ጀምሮ እስኪጨርስ ተገዛ፣ ተሸጠ፣ ይሸጣል፣ ግዙ፣ አውጡ፣ ክፈሉ ነው። ሬዲዮው ያው ነው። ውሸቱም እውነቱም አንድ ላይ ገበያ ይወጣል። ይኼው ከተማውም ሽያጭና ግዢ ማስታወቂያ በማስታወቂያ ብቻ ተጨናንቋል። ቁስ በቁስ ሆነናል በአጭሩ፤” ብሎ በረጂሙ ተነፈሰ። “ኧረ ቆጠብ አድርገህ ተንፍስ። በዚህ አያያዛችን አየርም ገበያ መውጣቱ ይቀራል ብለህ ነው?” ብለው ቄሱ እያረሩ ሳቁ። እያረሩ የሚስቁ ብፁአን ናቸው ተብሏል እንዴ?
ወደ መዳረሻችን ተቃርበናል። ወያላው የሰበሰበውን ገንዘብ አሥር ጊዜ ደጋግሞ እየቆጠረ ወደ ሰማይ ቀና ብሎ ይፈዛል። ክርኑን የሚያስደግፍባት የተሳፋሪ መቀመጫ ላይ የተሰየመው ተሳፋሪ “አይዞህ ገንዘብ ካለ ዝናብም ባይኖር በሰማይ መንገድ አለ፤” ይለዋል። “ይህ ዕድሌ አንድ ቀን የአውሮፕላን ‘አውታንቲ’ እስኪያደርገኝ እጠብቃለሁ። እዚያ ‘ሂተር’ ይዘህ ባትገባም፣ እንስሳት መጫኛ ውስጥ ባትደበቅም፣ ዕድሜ ለአየር ንብረት መዛባትና ለሙቀት መጨመር በብርድ ቀዝቅዞ በድን ሆኖ መድረስ ቀርቷል፤” እያለ የአንድ ቀን የስደት ህልሙን ከልቡ ያጫውተዋል። “በሊቢያ፣ በሱዳን፣ በኬንያ ሲገርመን ብለን ብለን በቦሌ ጀመርነው ደግሞ?” ይላል መሀል መቀመጫ የተሰየመው ጎልማሳ። ይኼኔ ጎን ለጎን የተቀመጡት የዕምነት አባቶች ተያዩ። ቄሱ፣ “ዕድሜ ለአየር ንብረት ለውጥና ሙቀት መጨመር አልክ አንተ? እግዚአብሔር ይቅር ይበልህ። አንተ ገና ለገና ያለ ቪዛ አውሮፕላን ጉያ ተደብቀህ የመሰደድ ሐሳብ አለህና ሌላውን ድርቅ ሲጫወትበት አይገድህም? ነውር አይደለም? እንዲህ ነው የምናስተምራችሁ?” ሲሉ ሼኩ በበኩላቸው፣ “አላህ ይኼን እየሰማ እንዴት የባሰ መዓት አያመጣብን። አፉ በለኝ ማለት ይበጃል እንጂ!” ብለው ተናገሩ።
አጥብቆ ጠያቂው በውፍረቱ አጨናንቆን የተቀመጠው ወጣት፣ “እንዲህ መሳ ለመሳ ተቀምጠው በአንድ አፍ ስለንስሃ የሚሰብኩ የሃይማኖት አባቶች አሉን። ከጥንት ጀምሮ ሲወርድ ሲዋረድ የምንኮራበት ባህልና ወግ አለን፡፡ ለፈጣሪ የቀረብን ነን ባዮች ነን። በነካ እጃችን መመፃደቃችን የትና የት ነው። ከአፍሪካ ቀዳሚ ስንል አይደክመን፣ ከዓለም ደረጃ አያጣንም ስንል እንውላለን። ዛሬም ግን ዝናብ ያጥረናል። ተውትና ሌላውን። ምንድነን እኛ?” ብሎ ሲደነፋ ቄሱ ዘወር ብለው አይተውት፣ “ወንጌል ‘ይኼ ሕዝብ በአፉ ያከብረኛል ልቡ ግን እኔ ዘንድ አይደለም’ እንዳለው ሆኖብን ይሆናላ። እናንተ የዚህ ዘመን ልጆች ሲነግሯችሁ አትሰሙም። ገንዘብ ገንዘብ ብላችሁ ልትሞቱ ነው። ፀሎታችሁ ዝናብ ሳይሆን ገንዘብ አዝንብልን ሆኗል። ይኼው ሰማዩም አኩርፏል። ኪሳችሁም እንደ ሆዳችሁ አይቶ አየሁ አልል አለ፤” ብለው ሲቆጡ ከጎኔ የተቀመጠችዋ፣ “ችግሮቻችን በጠቅላላ አንድ የበላይ አካል ላይ ካልተላከኩ ችግር መሆን አይችሉም ተብሏል እንዴ?” ብላኝ ፈገግ አለች። “እህ በማን እናላክ ቆንጂት? በማን ይላከካል? ለሁሉም ነገር ሰበብ እየተፈለገ እስከ መቼ?” ሲል አንደኛው ወያላው ውረዱ ብሎን ተንጋግተን ወረድን፡፡ “በሰበብ ጥላ ሥር ማለት ይኼም አይደል?” የሚል ጥያቄ መሰል አስተያየት ስንሰማ እየተሳሳቅን ወደ ጉዳያችን አመራን፡፡ መልካም ጉዞ!