Sunday, June 16, 2024

የደቡብ ሱዳን ነገር ‹ውኃ ቅዳ ውኃ መልስ›

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

እ.ኤ.አ. በ2011 ዓ.ም. ለአኅጉሪቱ 55ኛ እንዲሁም ለዓለማችን 201ኛዋ አባል አገር በመሆን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅትን (ተመድ) የተቀላቀለችው ደቡብ ሱዳን የተወለደችበትን ሁለተኛ ዓመት እንኳ ሳታከብር ነበር በመሪዎቿ የፖለቲካና የዘር ሽኩቻ ለሌላ አስከፊ የጦርነት ማዕበል የተዳረገችው፡፡

የዘር ሐረጋቸው ዲንቃ ከሚባለው ጎሳ የሚመዘዘው የአገሪቱ ፕሬዚዳንት ሳልቫ ኪርና ከኑዌር ጎሳ የሚወለዱት የቀድሞው ምክትላቸው ዶ/ር ሪክ ማቻር መካከል በተፈጠረው የፖለቲካና የሥልጣን ሽኩቻ፣ አዲሲቷን አገር በጦርነት መለብለብ ከመጀመሩ ባሻገር በዘር መስመር ለሁለት ከፍሏታል፡፡

ሁለቱ መሪዎች ከ25 ዓመታት በላይ በአንድ ጎራ ተሠልፈውና ነፍጥ አንግበው ደቡብ ሱዳን በመነጠል ራሷን ነፃ እንድታወጣ ተፋልመዋል፡፡ ነገር ግን የሁለቱ የነፃነት ታጋዮች አንድነት ከነፃነት በኋላ ሁለት ዓመት እንኳን መዝለቅ አልቻለም፡፡ አብሮነታቸው እ.ኤ.አ. በሰኔ ወር 2013 ፕሬዚዳንቱ ምክትላቸውን በሙስናና በሥልጣን መወስለት ከሥልጣናቸው እስካስወገዱበት ዕለት ብቻ የቆየ ነበር፡፡

 ይሁን እንጂ የሁለቱ መሪዎች ሽኩቻ በዚያ አላበቃም፡፡ ይልቁንም እ.ኤ.አ. ታኅሳስ 14 ቀን 2013 የተዳፈነ የሚመስለው የፖለቲካ ረመጥ በድንገት ተያይዞ ዋና ከተማዋ ጁባን በጥይት እሩምታ ናጣት፡፡ ይኼ ድንገተኛ የጦርነት ፍንዳታ ከደቡብ ሱዳናውያን አልፎ  ወደ ጎረቤት አገሮች ዘልቆ መላውን ዓለም አስደንግጧል፡፡ የጦርነቱ እሳትም ሊጠፋ ባለመቻሉ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየከፋ 20 ወራትን አልፎ ዛሬም ድረስ እንደተቀጣጠለ ዘልቋል፡፡

‹‹እሳት ዳር ተቀምጦ ሞቀኝ ማለት አይቻልም›› የሚባለው ዓይነት የሆነባቸው የቀጣናው አገሮችና አኅጉሪቱም ወዲያው ነበር የራሳቸውን ሥጋት ከፍ አድርገው ለማሰማት የሞከሩት፡፡ በተለይም ኢትዮጵያን ጨምሮ የጦርነቱ ገፈት ቀማሽ መሆናቸው እንደማይቀር ቀድመው የተረዱት የምሥራቅ አፍሪካ የልማት በየነ መንግሥት ድርጅት (ኢጋድ) አባል አገሮች ሁለቱን ተፋላሚ ኃይሎች ከፍልሚያው እንዲቆጠቡ አሳስበው ነበር፡፡ ወዲያውም በአፍሪካ ኅብረት ይሁንታ ኢጋድ የማደራደር ተግባሩን ጀመረ፡፡ ነገር ግን ኢጋድ የማደራደሩን ተግባር ከጊዜ ወደ ጊዜ እያጠናከረው ቢሄድም፣ የእርስ በእርስ ጦርነቱ ከመቀዛቀዝ ይልቅ የባሰ እየተቀጣጠለ ሄዶ ዛሬ ድረስ ዘልቋል፡፡

በጦርነቱ እየተከሰተ ያለው የደቡብ ሱዳናውያን ሰብዓዊ ቀውስና ስደቱም እንዲሁ እየተባባሰ ሄዶ አስከፊ ደረጃ ደርሷል፡፡ መረጃዎች እንደሚጠቁሙት አሥር ሺሕዎች የሚሆኑ ዜጎች ተገድለዋል፡፡ ከአምስት ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ ሴቶች፣ ሕፃናት፣ አዛውንቶችና ወጣቶች በአገር ውስጥና ከአገር ውጪ ተፈናቅለው በስደት እየተሰቃዩ ይገኛሉ፡፡ በአገሪቱ የተከሰተው የዝናብ እጥረትና ድርቅ ደግሞ ሰብዓዊ ቀውሱን ከድጡ ወደ ማጡ እያስባለው ይገኛል፡፡

ኢጋድ ሁለቱን ተፋላሚ ወገኖች በማቀራረብ ጦርነቱን ለማስቆም ጥረት አጠናክሮ ቢቀጥልም ምንም ውጤት ሊያስገኝለት አልቻለም፡፡ በተለይ በዚህ ዓመት መጋቢት ወር ላይ ሁለቱ ወገኖች የመጨረሻ የተባለ የሰላም ስምምነት በአዲስ አበባ ቢፈርሙም፣ የሰላም ስምምነቱ ግን ከ24 ሰዓት በላይ ዕድሜ ሊኖረው አልቻለም፡፡

ጥረቱ ሁሉ መና የቀረበት ኢጋድም ለአፍሪካ ኅብረት እንዲሁም ለተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ሰላምና ደኅንነት ምክር ቤት ጉዳዩን አድርሶት ነበር፡፡ ነገር ግን ቀድሞም ቢሆን የኢጋድንም ሆነ የኅብረቱን ጥረት እንደሚደግፉ በቅርበት ሲገልጹ የነበሩት አሜሪካ፣ እንግሊዝ፣ ኖርዌይ፣ የአውሮፓ ኅብረትና ቻይናን ጨምሮ ዓለም አቀፈ ማኅበረሰብ የኋላ የኋላ ግፊት ማድረጉን ቀጥሎበት ነበር፡፡ ኢጋድ የተባለው አደራዳሪ ወገንም ስሙን ወደ ‹ኢጋድ ፕላስ› ቀይሮ ሁለቱ ወገኖች የእርቅ ሰነድ እንዲፈርሙ የሚያስገድዳቸው አዲስ የመፍትሔ ንድፈ ሐሳብ አቀረበ፡፡ በሰነዱም መሠረት ሁለቱ ወገኖች ድርድራቸውን አጠናቀው እስከ ነሐሴ 11 ቀን 2007 ዓ.ም. እንዲፈርሙ ይጠበቅ ነበር፡፡

በቅርቡ ኢትዮጵያን የጎበኙት የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ ሁለቱ ወገኖች የእርቅ ሰነዱን በተቆረጠላቸው የጊዜ ገደብ ካልተፈራረሙና ጦርነቱን ካላቆሙ፣ አገራቸው ‹‹ሌላ አማራጭ›› ለማየት እንደምትገድድ ማስጠንቀቃቸው ይታወሳል፡፡

በዚህም መሠረት በዋና አደራዳሪው አምባሳደር ሥዩም መስፍን አማካይነት ኢጋድ ፕላስ ላለፉት ሁለት ሳምንታት ሁለቱን ወገኖች በቀረበው ሰነድ ላይ በአዲስ አበባ፣ ፕሬዚዳንት ኪርም ሆኑ የቀድሞው ምክትላቸውና የአሁኑ ባላንጣቸው ዶ/ር ማቻር በተወካዮቻቸው አማካይነት ሲደራደሩ ከርመው ነበር፡፡

የዚሁ ድርድር ማጠቃለያ ላይ ግን ኪርና ማቻር ከእሑድ ነሐሴ 10 ቀን እስከ ሰኞ ዕለት ነሐሴ 11 ቀን 2007 ዓ.ም. አዲስ አበባ በሚገኘው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን የስብሰባ አዳራሽ ተገኝተው ፊት ለፊት ለመደራደር መጥተው ነበር፡፡ የኢጋድም መሪዎች የተገኙ ሲሆን፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ፣ የኬንያ ፕሬዚዳንት ኡሁሩ ኬንያታ፣ የኡጋንዳ ፕሬዚዳንት ዩዌሪ ሙሴቬኒ፣ የሱዳን ፕሬዚዳንት ኦማር ሐሰን አል በሽርና የጂቡቲ ፕሬዚዳንት እስማኤል ኡመር ጊሌ በአደራዳሪነት ተሳትፈዋል፡፡

እሑድ እስከ ምሽት ድረስ በነበረው ውይይት የእርቅ ሰነዱ ባካተታቸው የመደራደሪያ ነጥቦች ሁለቱም ወገኖች ተስማምተውበታል የሚሉ መረጃዎች ወጥተው ነበር፡፡ በዚህም የተነሳ ሰኞ ጠዋት እስከ አራት ሰዓት ድረስ የፊርማ ማኖር ሥርዓት ይጠበቅ ነበር፡፡ ነገር ግን በታሰበው ሰዓት ከተደራዳሪዎችም ሆነ ከአደራዳሪዎቹ በኩል ምንም ነገር ሳይሰማ ቀኑ ተገባዷል፡፡

ይልቁንም ከኢጋድ አባል አገሮች መካከል የአንዳንዶቹ መሪዎች ከስብሰባው በመውጣት ሲሄዱ መታየታቸው፣ ድርድሩ ችግር ሳይገጥመው እንዳልቀረ በውይይቱ አዳራሽ አካባቢ የጥርጣሬ መንፈስ በስፋት እንዲስተዋል አድርጎ፡

ከምሽቱ አሥራ ሁለት ሰዓት በኋላ ግን ዋና አደራዳሪው አምባሳደር ሥዩም ድርድሩ መጠናቀቁን ገልጸዋል፡፡ ነገር ግን አሁንም ቢሆን የአቶ ሥዩም ማብራሪያ ሌላ ያልተጠበቀ ጥያቄን ያጫረ መረጃ ነበር ያመጣው፡፡

‹‹ድርድሩ በስኬት ተጠናቋል፡፡ አሁን የመነሻ ፊርማውን ይፈራረማሉ፤›› በማለት ተናግረዋል፡፡ በተቃዋሚዎች በኩል ሙሉ ለሙሉ ለመፈረም የተስማሙ ቢሆንም፣ የሳልቫ ኪር መንግሥት በተወሰኑ ጉዳዮች ላይ የመጨረሻ ፊርማ ለማኖር ተጨማሪ ጊዜ ያስፈልገኛል በማለቱ ስምምነቱን ሙሉ በሙሉ ሳይፈርም መቅረቱን አደራዳሪዎች ገልጸው ነበር፡፡

ሁለቱን ተቀናቃኞች ሲያደራድሩ የቆዩት አምባሳደሩ፣ ፕሬዚዳንት ኪር አሉብኝ ያሉባቸውን ችግሮች ከሌሎች ባለሥልጣኖች ጋር ተመካክረው ወደ አዲስ አበባ በመመለስ ሰነዱን ሙሉ በሙሉ ለመፈረም እንደሚመጡ ገልጸዋል፡፡

‹‹በሥልጣን ክፍፍሉ ላይና ዘለቄታዊ ፖለቲካ መፍትሔው ላይ ሁለቱ ወገኖች እንደማፈራረሙ አሁንም ዕምነት አለ፡፡ የድርድሩ ሒደት ተስፋና ተስፋ መቁረጥ ተፈራርቀውበታል፡፡ ለሁሉም ኃይሎች መናገር የምንፈልገው የቀረችው ጭላንጭል ተስፋፍታ ለደቡብ ሱዳናውያን ብርሃን እንዲወጣ ቁርጠኛ እንዲሆኑ ነው፤›› በማለት የኢጋድ የወቅቱ ሊቀመንበር ጠቅላይ ሚኒስቴር ኃይለ ማርያም በወቅቱ ተናግረዋል፡፡ ምክትል ሊቀመንበሩ ፕሬዚዳንት ኬንያታ በበኩላቸው ስምምነት ባልተደረሰበት የፖለቲካ ጉዳዮች ላይ ተጨማሪ ጊዜ መሰጠቱን እንደሚያምኑበት ጠቁመዋል፡፡

‹‹ዛሬ አንድ ለውጥ ላይ ደርሰናል፡፡ ግድያ እንዲቆም፣ ጥይት የሚተፉ የጠመንጃ አፈሙዞች ፊታቸውን እንዲያዞሩ ተደራዳሪዎች ተስማምተዋል፡፡ ነገር ግን ሰላም ድል አድርጓል ብለን የምንፈነጥዝበት ጊዜ ላይ አልደረስንም፡፡ ሰላም ሒደት ነው፡፡ ሁሉንም ማካተት አለበት፤›› ብለዋል፡፡

‹‹የመነሻ›› ነው የተባለውን ፊርማ ፕሬዚዳንት ኪር ባለመፈረማቸው አሁንም በሁለቱ ተቀናቃኝ ቡድኖች መካከል ጦርነቱን ስለማስቆሙ ብዙዎች ጥርጣሬ አላቸው፡፡

በዕለቱም የተቃዋሚው አንጃ መሪ የሆኑት ዶ/ር ማቻር የተፈራረሙት የኤስፒኤልኤም ፓርቲ ዋና ጸሐፊ ከሆኑት ፓጋን ኦሙም ጋር ነው፡፡ ይህን ጥርጣሬ ደግሞ ከፍ ያደረገው በስተመጨረሻ የሥነ ሥርዓቱን መጠናቀቅ ተከትሎ ዶ/ር ማቻር የሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ነው፡፡

‹‹እኔ ወደዚህ አዳራሽ እስከገባሁበት ሰዓት ድረስ የማውቀው ሁለታችንም [ከኪር ጋር] እንደምንፈራረም ነው፡፡ እሳቸው ለምን እንደማይፈርሙ ከማንም አልሰማሁም ነበር፤›› ሲሉ ግራ መጋባታቸውን ተናግረዋል፡፡ ‹‹እኛ ወደ ጦርነት የገባነው አቅደንበት አይደለም፡፡ ሁሌም ቢሆን ጦርነቱን ለማቆም ዝግጁ ነን፡፡ የእሱን አለመፈረም አላውቅም ነበር፡፡ አሁንም ቢሆን አሉብኝ የሚላቸውን ችግሮች ቆም ብሎ እንዲያስብበት እንጠይቃለን፤›› ብለዋል፡፡

ዶ/ር ማቻር ለጦርነቱ ዋና ተጠያቂ አድርገው ፕሬዚዳንት ኪርን ቢከሱም፣ ሌላው ችግር ፈጣሪ የሚሏቸው የኡጋንዳውን ፕሬዚዳንት የዌሪ ሙሴቬኒን ነው፡፡

‹‹ከዚህ በፊት በተደጋጋሚ የኡጋንዳው መሪ ችግሮችን እያባባሱ እንደነበር ገልጫለሁ፡፡ በአሁኑ ውይይት ግን በደንብ በጋራ ከእሳቸው ጋር ተወያይተናል፡፡ ስምምነቱ ከተፈረመና ጦርነቱን ማቆም ከተቻለ እጃቸውን እንደሚያነሱ ገልጸውልኛል፤›› ሲሉ ዶ/ር ማቻር ለጋዜጠኞች ገልጸዋል፡፡

ቀደም ብሎ ዓለም አቀፍ ማኅበረሰቡ በተለይም የአሜሪካ መንግሥትና የአውሮፓ ኅብረት በሁለቱም ወገኖች ላይ ጠንከር ያለ ግፊት መጀመራቸው ይታወሳል፡፡

ከአሁኑ የ‹‹መነሻ›› ስምምነት በኋላ ግፊቱ ወደ ኪር መንግሥት ሊሆን እንደሚችል የሚያሳዩ ምልክቶች ከወዲሁ ብቅ እያሉ ነው፡፡ ይህ ደግሞ ፕሬዚዳንት ኪር ከውስጥም ከወጪም ፈተና እንዲበዛባቸው አድርጓል የሚሉም አሉ፡፡

ከሰኞ ዕለቱ ድርድር ቀደም ብለው ወደ አዲስ አበባ ለመምጣት አንገራግረውም ነበር፡፡ በተጨማሪም በኢጋድ ውክልና የማደራደሩን ተግባር እያከናወኑ ያሉትን አደራዳሪዎችን ጭምር ማብጠልጠልም ጀምረው ነበር፡፡ የደቡብ ሱዳን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር፣ ‹‹ዋና አደራዳሪው ከማደራደር ተግባር አልፈው ምን ማድረግ እንዳለብን መመርያ ሊሰጡን ሞክረዋል፤›› በማለት አምባሳደር ሥዩምን እስከ መወረፍም ደርሰው ነበር፡፡

ሁለቱ ተፋላሚዎች እርስ በእርሳቸው ከመካሰሳቸው አልፈው በሁለቱም ወገኖች መካከል የመከፋፈል አደጋ ማንዣበቡ ደግሞ፣ አጠቃላይ የሰላም ድርድሩን አደጋ ላይ ይጥለዋል ተብሎ ተሰግቶ ነበር፡፡

እሑድ ዕለት ኪር ወደ አዲስ አበባ ከመምጣታቸው በፊት አራት አገረ ገዢዎቻቸውን ከሥልጣን ማባረራቸው ተሰምቷል፡፡ እንዲሁም ዶ/ር ማቻር በበኩላቸው በሚመሩት የተቃዋሚ ጎራ በጦር አበጋዞች መካከል የመፈረካከስ ምልክት ታይቷል ተብሎም ነበር፡፡ በእርግጥ ዶ/ር ማቻር በዚሁ የአዲስ አበባው ቆይታቸው ወቅት አንድ ወታደር በዲሲፕሊን ጉዳይ ከማባረራቸው ውጪ ምንም ችግር የሌለባቸው መሆኑን ገልጸዋል፡፡ አባርሬያለሁ ያሉት ወታደርም ለኪር መንግሥት ለማሴር እንደተሞከረ ጠቁመዋል፡፡

ኢጋድ ማደራደር ከጀመረበት ካለፉት 19 ወራት ጀምሮ ሁለቱን ወገኖች ለማቀራረብ ብዙ ውጣ ውረዶችን አልፏል፡፡ ተፋላሚዎች ለሳባት ጊዜ ለመስማማት ሙከራ አድርገው እስከ መፈራረምም ደርሰው ነበር፡፡ ነገር ግን ስምምነቶቹ ተፋላሚዎችን ወደ መታኮሱ ከመግባት አላገዷቸውም፡፡

በተለይም የአሜሪካ ግፊት እንዳለበት የተነገረውን የእርቅ ሰነድ (Compromise Document) ላይ ድርድሩ የቀጠለ ሲሆን፣ ሰነዱ የሥልጣን ክፍፍልን በአግባቡ የሚመራ አስፈጻሚ አካልን መሰየምን ያካትታል፡፡ በሰነዱ መሠረት የአስፈጻሚው አካል 53 በመቶ የሚሆነውን የሥልጣን ድርሻ ለገዢው ፓርቲ (የሳልቫ ኪር መንግሥት) የሚሰጥ ሲሆን፣ 33 በመቶውን ለሌሎች የፖለቲካ ፓርቲዎች ለመስጠት የመፍትሔ ሐሳብ ያቀርባል፡፡ እንዲሁም 14 በመቶ የሚሆነውን ሥልጣን ለቀድሞ ታሳሪ ባለሥልጣናት እንዲሆን ያስቀምጣል፡፡

በአሁኑም የስምምነት ሒደት ተመሳሳይ ጥሰት እንደማይከሰት ማስተማመኛ የለም የሚለው ሥጋት ተንፀባርቋል፡፡

የአሁኑ ‹‹የዕርቅ›› ስምምነት ቢሆን ይፋ ከመደረጉ በፊት በተለይ መቀመጫቸውን አዲስ አበባ ያደረጉ የምዕራብ አገሮች ዲፕሎማቶች በውጤቱ ደስተኛ እንዳልነበሩ የሚያስገምቱ ሁኔታዎችም ተስተውለዋል፡፡ ዋና አደራዳሪው ውጤቱን ይፋ ከማድረጋቸው ከጥቂት ደቂቃዎች ቀደም ብለው ከ20 የሚበልጡ ዲፕሎማቶች በስብሰባው አዳራሽ ውስጥ ግራ በመጋባት ቆመው ታይተው ነበር፡፡ በሱዳንና በደቡብ ሱዳን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ልዩ ተወካይ ከሆኑት ትውልደ ኤርትራዊው ኃይሌ መንቆሪዮስ ዲፕሎማቶች የድርድሩን የመጨረሻ ድምዳሜ በጉጉት ለመስማት ሲሞክሩ ታይተዋል፡፡ ወዲያውም በአብዛኛዎቹ ላይ የታየው ገጽታ ድርድሩ ተስፋ ሰጪ እንዳልነበረ ያሳብቅ ነበር፡፡

በኋላም ቢሆን ግን አደራዳሪውን ጨምሮ በጠቅላይ ሚኒስቴር ኃይለ ማርያምና  በፕሬዚዳንት ኬንያታም ገጽታዎች ላይ የታየው ተመሳሳይ ስሜት ነው፡፡

በድርድሩ ሒደት የተገኙት የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ምክትል ዋና ጸሐፊ ጃን ኤልያስ፣ የደቡብ ሱዳናውያን ንፁኃን ዜጎች እንግልት ቅድሚያ ትኩረት እንዲሰጠው አሳስበዋል፡፡

‹‹በደቡብ ሱዳን ተወካዮች በኩል በየቀኑ የሰብዓዊ ቀውስ ሪፖርት ይደርሰኛል፡፡ ሕዝቡ መከራና ግፍ እየደረሰበት ሁሉንም ነገር ለሕዝቡ ሰላም ስንል አሳልፈን መስጠት ይገባናል፡፡ ደቡብ ሱዳናውያን ከአሥር ዓመታት እንግልት በኋላ እዚህ ላይ መውደቅ የለባቸውም፤›› በማለት መሪዎችን አሳስበዋል፡፡

ኢጋድም ሆነ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ምንም ያህል ቢጥሩም ስኬት ማስመዝገብ ተስኗቸዋል፡፡ ተፋላሚዎች ሰባት ጊዜ ያህል ተፈራርመዋል፡፡ ሰባት ጊዜም ስምምነታቸውን ጥሰውታል፡፡ መሪዎቻቸው እስከ መጨረሻ ድረስ ባለመጓዛቸው ደቡብ ሱዳናውያን አሁንም ለተጨማሪ ሁለት ሳምንታትን እንዲጠብቁ ግድ ብሏቸዋል፡፡ ቢያንስ ሰብዓዊ ቀውሱ ትንሽ ፋታ ያገኛል ተብሏል፡፡ ጥያቄው ‹ተኩስ ነገ ይሰማል? ወይስ አይሰማም?› ነው፡፡ ከማቻር ወይስ ከኪር ማንም እርግጠኛ አይደለም፡፡ ዓለም ግን የጥርጣሬ ዓይኗን ወደ ትንሿ አገር አነጣጥሯል፡፡ የአሜሪካ መንግሥት ቀደም ሲል በተለይ ሥልጣን ላይ ያለውን የደቡብ ሱዳን መንግሥት ላይ ማስጠንቀቂያ መሰንዘሩ ይታወሳል፡፡

‹‹የሰብዓዊ ቀውሱ አስከፊነት ትልቅ ደረጃ ደርሷል፡፡ አሁን የጥይት ድምፅ ፀጥ ሊል ይገባዋል፤›› በማለት የእንግሊዝ መንግሥት አስጠንቅቋል፡፡ የአውሮፓ ኅብረት በበኩሉ ከሰኞው የስምምነቱ ፊርማ ውጣ ውረድ በኋላ፣ ‹‹ስምምነቱ በአግባቡ ተግባር ላይ የማይውል ከሆነ ሌላ መዘዝ ሊያስከትል ይችላል፤›› በማለት ጠንከር ያለ ማስጠንቀቂያ አስተላልፏል፡፡

 

 

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -