Tuesday, April 23, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ማኅበራዊበህንዶች ይመራ የነበረው የኤሌክትሪክ አገልግሎት ማኔጅመንት በኢትዮጵያውያን ተተካ

በህንዶች ይመራ የነበረው የኤሌክትሪክ አገልግሎት ማኔጅመንት በኢትዮጵያውያን ተተካ

ቀን:

–  ዋና ሥራ አስፈጻሚው ከተቋሙ ውጪ በሚሾም እንደሚተኩ ተጠቁሟል

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት አመራርን ለሁለት ዓመታት ይመሩ የነበሩት የህንዱ ፓወር ግሪድ ኮርፖሬሽን ኦፍ ኢንዲያ ኩባንያ አመራሮች፣ የኮንትራት ጊዜያቸውን በመጨረሳቸው በኢትዮጵያውያን አመራሮች መተካታቸው ታወቀ፡፡

ከሁለት ዓመታት በፊት በአዋጅ ለሁለት ከተከፈለው የቀድሞ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ኮርፖሬሽን፣ የኢትዮጵያን ኤሌክትሪክ አገልግሎት አመራርን በኃላፊነት ይመሩ የነበሩት ዋና ሥራ አስፈጻሚውን ሚስተር ቪ.ኬ. ኮሬን ጨምሮ 13 ህንዳዊያን ነበሩ፡፡ ከዋና ሥራ አስፈጻሚው በስተቀር ሌሎቹ በአገልግሎቱ ዘርፍ ባሉ የኃላፊነት ቦታ ላይ ተመድበው የነበሩት በኢትዮጵያውያን መቀየራቸውን፣ ዋና ሥራ አስፈጻሚው ሚስተር ኮሬ ነሐሴ 11 ቀን 2007 ዓ.ም. የተተኩ አመራሮችን ሰብስበው ማስረዳታቸውን የሪፖርተር ምንጮች ገልጸዋል፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

በመላ አገሪቱ ያለውን የሥርጭት ሲስተም፣ የሽያጭና የጥገና ሥራዎችን የሚቆጣጠር ሥራ አስፈጻሚ በአቶ መስፍን ብርሃኔ መተካቱን የጠቆሙት ምንጮች፣ በሌሎቹም ማለትም በቅድመ መከላከልና አስቸኳይ ጥገና እንዲሁም በሽያጭ ዘርፍ ሌላ ኢትዮጵያዊ ሥራ አስፈጻሚ መመደቡንም ተናግረዋል፡፡

ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይልና አገልግሎት ቦርዱ የተላለፈ መልዕክት መሆኑን ህንዳዊው ሥራ አስፈጻሚው ለተተኪዎቹ ኢትዮጵያውያን ሲገልጹ፣ እሳቸውን የሚተካቸው የአገልግሎቱ ዋና ሥራ አስፈጻሚ የሚመደበው፣ ከሁለቱም መሥሪያ ቤቶች ውጪ በሆነ ሰው መሆኑን ለተሰብባቢው መናገራቸውን ምንጮች አረጋግጠዋል፡፡

የህንዱ ኩባንያ የአገልግሎት ዘርፍ ለሁለት ዓመታት ለማስተዳደር ኮንትራቱን ሲፈራረም አዳዲስ ደንበኞችን ለማፍራትና ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል፣ ኃይል በጅምላ ገዝቶ በችርቻሮ ለመሸጥ የነበረ ቢሆንም፣ በወቅቱ የኤሌክትሪክ ኃይል ዘርፍ አዳዲስ ፕሮጀክቶች ላይ አተኩሮ ይሠራ ስለነበር የኃይል ማመንጫ፣ ማስተላለፍና የማከፋፈያ ጣቢያዎች ግንባታ ከነሠራተኞቹ በአገልግሎቱ ሥር መቆየታቸውን ምንጮች አብራርተዋል፡፡

የህንዱ ፓወር ግሪድ ኮርፖሬሽን ኦፍ ኢንዲያ ከሳምንት በኋላ እ.ኤ.አ. ኦገስት 25 ቀን 2015 ኮንትራቱን አጠናቆ የሚሰናበት በመሆኑ፣ ላለፉት ሁለት ዓመታት አገልግሎቱ በሥሩ አድርጎ ሲያስተዳድራቸው የነበሩትን የኤሌክትሪክ ኃይል ዘርፎችከነሠራተኞቹ መመለሱንና በኃላፊነት ላይ የነበሩትን ህንዳውያንን በኢትዮጵያውያን መተካቱንም ተናግረዋል፡፡

በኢትዮጵያውያን የተተካው የኤሌክትሪክ አገልግሎት አመራር፣ ከኤሌክትሪክ ኃይል ጋር የሚገናኘው ኃይልን በጅምላ ለመግዛትና ለደንበኞች ለመሸጥ ብቻ መሆኑን ያስታወሱት ምንጮች፣ አገልግሎቱ የገዛውን ኃይል ከ2.5 ሚሊዮን በላይ ለሚሆኑ ደንበኞች በችርቻሮ የመሸጥና የኦፕሬሽን ሥራዎችን እንደሚያከናውን አስረድተዋል፡፡

ህንዳዊውን ዋና ሥራ አስፈጻሚ ይተካሉ የተባሉት ሰው፣ ከተቋሙ ውጪ ያሉ መሆናቸው አግባብ አለመሆኑን በመግለጽ የሚቃወሙ እንዳሉ ምንጮች ገልጸው፣ ምክንያታቸው ደግሞ ሥራው ውስብስብና ስለተቋሙ ሥራም ሆነ ሠራተኛ በቂ ዕውቀት ወይም መረጃ ያለው ሰው ካልሆነ ለመምራት አስቸጋሪ ይሆናል ከሚል እሳቤ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

ፓወር ግሪድ ኮርፖሬሽን ኦፍ ኢንድያ የኢትዮጵያ አሌክትሪክ አገልግሎት አመራርን ለሁለት ዓመት ለማስተዳደር ኮንትራት የተፈራረመው በነሐሴ ወር 2005 ዓ.ም. በ22 ሚሊዮን ዩሮ መሆኑ ይታወቃል፡፡

በሌላ በኩል የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይልና አገልግሎት ከ1,000 በላይ የሚሆኑ አመራሮች፣ ከሐምሌ 5 ቀን 2007 ዓ.ም እስከ ሐምሌ 8 ቀን 2007 ዓ.ም. ድረስ በሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ መሰብሰቢያ አዳራሽ ሲገማገሙ ከርመው፣ የተለያዩ ውሳኔዎችን ማስተላለፋቸውን ተሳታፊዎች ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

አመራሮቹ የ2007 ዓ.ም. ሥራ አፈጻጸምን ምን ታቅዶ ምን እንደተፈጸመ፣ አንድ ለአምስት፣ ኳሊቲ ሰርክልና ሌሎች የሥራ ማስፈጸሚያ መሣሪያዎችን ተጠቅመው ምን እንደሠሩ፣ በመጀመሪያው ዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ወቅት አጠቃላይ አፈጻጸምና የሁለተኛው ዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ወቅት በምን ሁኔታ አሠራሮችን በተሻለ ሁኔታ ማከናወን ስለሚቻልበት ሁኔታ መወያየታቸውን ተሳታፊዎቹ አስረድተዋል፡፡

የ2007 ዓ.ም. ሥራ አፈጻጸም ጥሩ መሆኑ ቢገለጽም ችግሮች እንደነበሩ መነገሩን የገለጹት ተሳታፊዎቹ፣ የኃይል መቆራረጥና የመሣሪያዎች ግብዓት ችግር በዋናነት የተጠቀሱት ችግሮች መሆናቸውን ጠቁመዋል፡፡ የማከፋፈያ ጣቢያዎችን የማሳደግ ሥራ የተሠራ ቢሆንም፣ ብዛት ያላቸው አዳዲስ ደንበኞች መምጣታቸውን ለኃይል መቆራረጡ እንደ ምክንያት መጠቀሱም ተገልጿል፡፡ የማሰራጫ መስመር ላይ የአቅም ማሳደግ ሥራና የቅድመ መከላከል ሥራ ባለመሠራቱ ትኩረት እንዲያደርግበት አቅጣጫ መስጠቱንም ተሳታፊዎቹ ገልጸዋል፡፡

በማሰራጫ መስመሮች ላይና አገልግሎት አሰጣጥ ላይ ችግር እንዳለ በውይይቱ መነሳቱን የጠቆሙት ተሳታፊዎቹ፣ ትራንስፎርመሩ በሜቴክ ተመርቶ እየቀረበ በመሆኑ ችግር ባይኖርም፣ መብረቅ መከላከያና ሌሎች ለትራንስፎርመሩ ግብዓት (አክሰስሪስ) እጥረት በመኖሩ ችግሩን እንዳባባሰው ተናግረዋል፡፡ የቆጣሪ ችግር ስላለም፣ የቅድሚያ ክፍያ አገልግሎት በአዲስ አበባና አዳማ ከተማ በተወሰነ መልኩ ከመስጠት ባለፈ ወደሌሎቹ ከተሞች አዳርሶ፣ መደበኛ ቆጣሪን ሩቅ ወደ ሆኑ ቦታዎች ማድረስ አለመቻሉ አንዱ ችግር ሆኖ መነሳቱንም አስረድተዋል፡፡

ቦርዱ በየሦስት ወራት እየተገናኘ ከላይ እስከ ታች ካሉ አመራሮች ጋር በመወያየቱ የሚያጋጥሙ ችግሮችን ለመፍታት ከፍተኛ ጥረት ሲያደርግ መቆየቱን ጠቁመው፣ አመራሩ የአሠራር ፖሊሲና አካሄድ እንዲያውቅ ትልቅ እገዛ በማድረግ መደነቁን ገልጸዋል፡፡ ከቦርዱ ባልተናነሰ ሁኔታ የውኃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስቴርም ጉልህ ሚና መጫወቱን አክለዋል፡፡

በሠራተኛውም ሆነ በአመራሩ ላይ የአመለካከት ችግር መኖሩ እንደተጠቆመ የገለጹት ተሳታፊዎቹ፣ አመራሩ ራሱን ፈትሾ ለውጥ ለማምጣት መጣር እንዳለበት በቦርድ ሰብባቢው ዶ/ር ደብረ ጽዮን ገብረ ሚካኤል ማሳሰቢያ መሰጠቱን ተናግረዋል፡፡

ላለፉት ሁለት ዓመታት የህንዱ ኩባንያ ኢትዮጵያውያን ኃላፊዎችን ተክቶ ሲሠራ ያመጣው ለውጥ ወይም የሠራው ሥራ ምን እንደሆነ እንዲገለጽላቸው ተሳታፊዎቹ ጠይቀው፣ ህንዳውያኑ በዋናነት የመጡት የኃይል መቆራረጥ ችግሩን ለመፍታትና የኔትወርክ አቅም ለማሳደግ የነበረ ቢሆንም፣ ከፍተኛ አቅም የሚፈልግ በመሆኑ በሁለት ዓመታት ውስጥ ሊፈታ የሚችል አለመሆኑን በስብሰባው እንደተገለጸ ተናግረዋል፡፡

ተቋሙ ተመሳሳይ አገልግሎት ከሚሰጡ ከዓለም አቀፍ ተቋማት ስታንዳርድ አኳያ እንዴት መሥራት እንዳለበት፣ ስለደንበኛ አያያዝ ፖሊሲና የአሠራር ሥነ ሥርዓቶችን በማስተካከል የሠራተኛ ምዘና ሥርዓቶች፣ የሠራተኛ ጥቅማ ጥቅምና አሠራሮችን አመዳደብ ሥርዓት ከሰነድ አያያዝ ሥርዓት አኳያ ህንዳውያኑ ልምድ መስጠታቸውን ሰብባቢው ማከላቸውን ተሳታፊዎቹ ገልጸዋል፡፡ ለሚቀጥሉት አምስት ዓመታት ስለሚተገበረው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ፣ ተቋሙ አቅሙን እንዴት እንደሚያሳድግና በደንበኞች እርካታ ላይ ትኩረት ሰጥቶ እንደሚሠራም ውይይት መደረጉን ተሳታፊዎቹ አስረድተዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ሰው መሆን ምንድን ነው? ቅርስና ማኅበራዊ ፍትሕ

በሱራፌል ወንድሙ (ዶ/ር) ዳራ ከጎራዎች፣ ከመፈራረጅ፣ ነገሮችን ከማቅለልና ከጊዜያዊ ማለባበስ ወጥተን...

ኢኮኖሚው ኢትዮጵያን እንዳያፈርሳት ያሠጋል

በጌታቸው አስፋው ኢትዮጵያን እንዳያፈርሱ የሚያሠጉኝ አንድ ሁለት ብዬ ልቆጥራቸው የምችላቸው...

የኢትዮጵያ የፖለቲካ ትግል በሕግ አምላክ ይላል

በገነት ዓለሙ የአገራችንን ሰላም፣ የመላውን ዓለም ሰላም ጭምር የሚፈታተነውና አደጋ...

በሽግግር ፍትሕ እንዲታዩ የታሰቡ የወንጀል ጉዳዮች በልዩ ፍርድ ቤት ሳይሆን በልዩ ችሎት እንዲታዩ ተወሰነ

የኤርትራ ወታደሮች በሌሉበትም ቢሆን ይዳኛሉ ተብሏል በፅዮን ታደሰ የሽግግር ፍትሕ የባለሙያዎች...