Wednesday, December 6, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊየአዲስ አበባ አስተዳደር የሊዝ ደንብና መመርያ እንዲሻሻል ወሰነ

የአዲስ አበባ አስተዳደር የሊዝ ደንብና መመርያ እንዲሻሻል ወሰነ

ቀን:

የከተማ ቦታ በሊዝ ስለመያዝ ኅዳር 2004 ዓ.ም. የወጣውን አዋጅ ቁጥር 721 መነሻ በማድረግ፣ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ያወጣቸው የሊዝ ደንብና መመርያ እንዲሻሻሉ ተወሰነ፡፡

የሊዝ ደንብ ቁጥር 49/2004 እና መመርያ ቁጥር 15/2005 እንዲሻሻሉ የተወሰነው ድንጋጌዎች አላሠራ በማለታቸው ነው ተብሏል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር መሻሻል ያለባቸውን ድንጋጌዎች ነቅሶ እንዲያወጣና የማሻሻያ ሐሳብ እንዲያቀርቡ፣ ኃላፊነቱን በሥሩ ለሚገኙት ለመሬት ልማትና ማኔጅመንት ቢሮና ለፍትሕ ቢሮ ሰጥቷል፡፡

ከሁለቱ የአስተዳደሩ ቢሮዎች የተውጣጣ የባለሙያዎች ቡድን ደንብና መመርያውን እየፈተሸ መሆኑ ታውቋል፡፡

በ2005 ዓ.ም. የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ካቢኔ ያወጣው ‹‹አገራዊ ፋይዳ ያላቸው ፕሮጀክቶች መስተንግዶ መመርያ ቁጥር 15/2005›› ከከተማ መሬት ሊዝ ደንብ ቁጥር 49/2004 ጋር እንደሚቃረን ተገልጿል፡፡ የሁለቱ ድንጋጌዎች ተቃርኖ ገፍቶ በመሄድ የከተማ ቦታ በሊዝ ስለመያዝ ከወጣው አዋጅ ቁጥር 721/2004 ዓ.ም. ጋር እንደሚቃረንም ተገልጿል፡፡

የመሬት ልማትና የፍትሕ ቢሮ ባለሙያዎች ዋናው አዋጅ ሳይነካ ደንቡና መመርያው ተጣጥመው እንዲሄዱ የሚያደርጉ ሐሳቦችን እንዲያመነጩ ኃላፊነት እንደተሰጣቸው መረጃዎች አመልክተዋል፡፡

የመሬት ባንክና ማስተላለፍ ጽሕፈት ቤት ምክትል ኃላፊ ወይዘሮ አፀደ ዓባይ የሊዝ ደንብንና መመርያውን ለማሻሻል ጥናት እየተደረገ መሆኑን አረጋግጠው፣ ነገር ግን የሚሻሻሉትን ነጥቦች ከመግለጽ ተቆጥበዋል፡፡

ነገር ግን ምንጮች እንደሚሉት፣ ማሻሻያ ይደረግባቸዋል ተብለው ከሚጠበቁ መካከል አገራዊ ፋይዳ ያላቸው ፕሮጀክቶች ዋነኞቹ ናቸው፡፡ ከወይዘሮ አፀደ ቀደም ሲል የመሬት ባንክና ማስተላለፍ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ የነበሩት አቶ ገብረ ሥላሴ አብረሃም የሕግጋቱ መቃረን ሥራ ሊያሠራ እንዳልቻለ ለመሬት ልማትና ማኔጅመንት ቢሮ በደብዳቤ ገልጸው ነበር፡፡ በደብዳቤው እንደተገለጸው የአገር ውስጥና የውጭ አገር አልሚዎች በተለያዩ ጊዜያት ለማኅበራዊ አገልግሎቶች ቦታ እንዲሰጣቸው መጠየቃቸውን ደብዳቤው አስታውሷል፡፡

ማኅበራዊ አገልግሎት የሚባሉት ሆቴል፣ ሞል፣ ሪል ስቴት፣ ሆስፒታል፣ የገበያ ማዕከላትና የጤና ተቋማት ናቸው፡፡ አልሚዎቹ የቦታ ጥያቄያቸውን ለከተማ አስተዳደሩ ከንቲባና ለመሬት ልማትና ማኔጅመንት ቢሮ ጥያቄ አቅርበዋል፡፡ ጥያቄያቸው ተፈጻሚ እንዲሆንም የከንቲባ ጽሕፈት ቤትና የመሬት ልማትና ማኔጅመንት ቢሮው ትዕዛዝ ሲያስተላልፉ እንደቆዩ የጽሕፈት ቤቱ ደብዳቤ ይገልጻል፡፡

ለአብነትም የተመሩለትን የሰባት ኩባንያዎች ግዙፍ ፕሮጀክቶች በደብዳቤው አያይዟል፡፡ ነገር ግን የመሬት ባንክና ማስተላለፍ ጽሕፈት ቤት እንደገለጸው፣ አገራዊ ፋይዳ ያላቸው ፕሮጀክቶች ይስተናገዱ እንኳ ቢባል፣ በሊዝ አዋጅ አንቀጽ 2 ንዑስ አንቀጽ 21 የሰፈረው ሐሳብ ከአገራዊ ፋይዳ መመርያ ቁጥር 15/2005 ጋር ይጋጫል፡፡ መመርያው በግልጽ እንዳሰፈረው ‹‹ልዩ አገራዊ ፋይዳ ያላቸው ፕሮጀክቶች›› ማለት ለኢትዮጵያ ዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ከፍተኛ ለውጥ የሚያመጡ፣ የልማት ፕሮጀክቶች ወይም የትብብር መስኮችን ለማስፋት ለሚደረጉ እንቅስቃሴዎች፣ አገሪቱ ከሌሎች አገሮች ጋር ለሚኖራት የተሻለ ግንኙነት መሠረት እንዲጥሉ በመንግሥት የታቀዱና የተወሰኑ ፕሮጀክቶች ናቸው በሚል ይደነግጋል፡፡ ይህም ከሊዝ አዋጅ ጋር የሚጋጭ ስለሆነ፣ ለአልሚዎቹ ጥያቄ ምላሽ ለመስጠት ችግር ፈጥሯል በማለት ደብዳቤው አትቷል፡፡

ከዚህ በተጨማሪም በሊዝ አዋጅ ቁጥር 721/2004 አንቀጽ 11 ንዑስ አንቀጽ 7 እና ይህንኑ ተከትሎ በወጣው መመርያ ቁጥር 11/2004 አንቀጽ 32 ንዑስ አንቀጽ 2 በግልጽ እንደተደነገገው፣ የማኅበራዊ አገልግሎት ፕሮጀክቶች የሚስተናገዱት በልዩ ጨረታ ነው ይላል፡፡ በሊዝ አፈጻጸም መመርያ አንቀጽ 34 ንዑስ አንቀጽ 8 ደግሞ በከተማ አስተዳደሩ ከንቲባ እየታዩ ለካቢኔው ለሚመሩ ልዩ አገራዊ ፋይዳ ላላቸው ፕሮጀክቶች የሚውሉ ቦታዎች የሚስተናገዱበት አሠራር ከሊዝ አዋጁ ጋር የሚጣረስ ነው በማለት ደብዳቤው ይገልጻል፡፡ አገራዊ ፋይዳ ያላቸው ፕሮጀክቶች ተለይተው በመንግሥት ለታቀዱና ለተወሰኑ ፕሮጀክቶች ከንቲባው የአገሮችን የተሻለ ግንኙነት መሠረት ያደረገ ስለሆነ ሊስተናገድ ይገባል እንዲል ዝርዝር ድንጋጌ ሊኖር እንደሚገባ ጽሕፈት ቤቱ በደብዳቤው ገልጿል፡፡

ጽሕፈት ቤቱ በድንጋጌዎቹ መጣረስ ምክንያት የአልሚዎችን ጥያቄ ማስተናገድ አለመቻሉን በደብዳቤው ገልጿል፡፡

የፌዴራል የሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን፣ በሊዝ አዋጁና አዋጁን በሚያስፈጽሙ ደንብና መመርያዎች ላይ ባካሄደው ጥናትም መሻሻል እንዳለባቸው ድምዳሜ ላይ መድረሱን አመልክቷል፡፡

ኮሚሽኑ፣ ‹‹የመመርያው አንዳንድ አንቀጾች በአፈጻጸም ወቅት አሻሚ ትርጉም እንዳይሰጣቸው፣ ከሊዝ አዋጅ ጋር ተዛማጅ የሆኑ አንቀጾችን በመጥቀስና ለትርጉም የሚዳርጉ የመመርያው አንቀጾች በአዋጅ ከተደነገጉ ድንጋጌዎች ጋር መጣጣም አለባቸው፤›› በማለት ለአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር አስተያየቱን ሰጥቷል፡፡

ከተለያዩ አቅጣጫዎች ሕግጋቱ አላሠራ ማለታቸው እየተገለጸ በመሆኑና አስተዳደሩም በማመኑ፣ ከንቲባ ድሪባ ኩማ ደንብና መመርያው ‹አሠሪ›› መሆን አለበት በማለት እንዲሻሻል ትዕዛዝ ሰጥተዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት አስተዳደሩ በራሱ የኃላፊነት ወሰን ውስጥ ያሉትን ደንብና መመርያ ለማሻሻል የሚያደርገው ሥራ ሲጠናቀቅ፣ በተለይ በልዩ ጨረታ እንዲስተናገዱ የተደረጉት የአገልግሎት ተቋማት በልዩ ሁኔታ ሊስተናገዱ የሚችሉበት ዕድል ሊፈጠር እንደሚችል ታምኖበታል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ታዋቂው የኤሌክትሮኒክስ ብራንድ አይቴል የስትራቴጂ ለውጥ አካል የሆነውን አዲስ አርማ እና መለዮ ይፋ አደረገ።

በአለማችን ታዋቂ ከሆኑት የኤሌክትሮኒክስ ብራንዶች መካከል አንዱ የሆነው እና...

የጠቅላላ ጉባኤ ስብሰባ ጥሪ ለሸገር አነስተኛ የፋይናንስ ተቋም አ.ማ ባለአክሲዮኖች በሙሉ

ለሸገር አነስተኛ የፋይናንስ ተቋም አ.ማ ባለአክሲዮኖች በሙሉ የሸገር አነስተኛ የፋይናንስ...

[የክቡር ሚኒስትሩ ጸሐፊ፣ የሌላ ሚኒስትር ጸሐፊ ከሆነችው የቅርብ ወዳጇ ጋር በስልክ እየተጨዋወቱ ነው]

አንቺ ግን ምን ሆነሽ ነው? ጠፋሁ አይደል? ጠፋሁ ብቻ?! ምን ላድርግ ብለሽ...

በሱዳን ላይ ያጠላው የመከፋፈል ዕጣና ቀጣናዊ ተፅዕኖው

የሱዳን ጦርነት ስምንተኛ ወሩን እያገባደደ ይገኛል፡፡ ጄኔራል አብዱልፈታህ አልቡርሃን...