መንግሥት በቀጣዩ የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ በዘጠኝ ተፋሰሶች 915 ሺሕ ሔክታር መሬት በመስኖ ለማልማት አቀደ፡፡
ለማልማት ከታቀደው 915 ሺሕ ሔክታር የመስኖ ልማት መካከል 250 ሺሕ ሔክታር በውኃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስቴር፣ 330 ሺሕ ሔክታር በስኳር ኮርፖሬሽን፣ የተቀረው በክልሎች አማካይነት የሚለማ ነው ተብሏል፡፡
የመስኖ ልማቱ ይካሄድባቸዋል ከተባሉት መካከል በአማራ ክልል ጣና ዙሪያ በሚገኙት መገጭና ርብ ወንዞች፣ የዓባይ ገባር በሆኑት ጎመራ፣ ዥማና አገር ወንዞች፣ በኦሮሚያ ክልል በስምጥ ሸለቆ ተፋሰስ በሚገኘው ጊዳቦ፣ በትግራይ ክልል በተከዜና የተከዜ ተፋሰስ በሆነው ሁምራ ወንዞች፣ በደቡብ ክልል ብላቴና ሳጎ ወንዞች ተጠቃሾች ናቸው፡፡
በወንዞቹ ላይ የሚካሄደው የመስኖ ዲዛይንና ግንባታ የሚካሄደው በመንግሥት ቢሆንም አርሶ አደሮች፣ የግል ባለሀብቶችና የመንግሥት የልማት ድርጀቶች ተጠቃሚዎች ይሆናሉ ተብሏል፡፡
የውኃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስቴር ሕዝብ ግንኙነትና ኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ብዙነህ ቶልቻ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ቅድሚያ ተሰጥቷቸው በ2008 ዓ.ም. የሚጀመሩ ፕሮጀክቶች ለመለየት ውይይቶች እየተካሄዱ ነው፡፡
እነዚህን ፕሮጀክቶችን ለማካሄድ የሚያስፈልገው በጀት 240.3 ቢሊዮን ብር መሆኑን አቶ ብዙነህ ተናግረው፣ በጀቱ የሚሸፈነው ከመንግሥት፣ ከዕርዳታና ከብድር መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ይህ ፕሮጀክት ዕውን ከሆነ አሁን ያለውን ስምንት በመቶ የመስኖ ሽፋን ወደ 25 በመቶ ያሳድገዋል ተብሏል፡፡ የአምስት ዓመቱ የዕድገትና ትራንስፎርሜሸን ዕቅድ በዝናብ ላይ ጥገኛ ሆኖ የቆየውን የኢትዮጵያ ግብርና ዘርፍ፣ ወደ መስኖ ልማት የማሸጋገር ዕቅድ አለው፡፡
በተጠናቀቀው የመጀመርያው የዕድገትና ትራንስፎርሜሸን ዕቅድ ዘመን 679,352 ሔክታር መሬት መካከለኛና ከፍተኛ የመስኖ ልማት ማካሄድ የሚያስችል ዲዛይን ተሠርቷል፡፡ በተመሳሳይ ወቅት 199,304 ሔክታር የመካከለኛና ከፍተኛ መስኖ ልማት ግንባታ ሥራዎች መከናወናቸውን ብሔራዊ ፕላን ኮሚሽን ያወጣው ሰነድ ይገልጻል፡፡