ዓለም አቀፍ የባለሙያዎች ቡድን በታላቁ የህዳሴ ግድብ ላይ ያቀረባቸውን ሁለት ምክረ ሐሳቦች ለመተግበር የተቋቋመው የሦስትዮሽ የቴክኒክ ኮሚቴ የመረጣቸው ሁለት አማካሪ ድርጅቶች በሚያቀርቡት የቴክኒክ ሪፖርት ላይ፣ ነሐሴ 14 ቀን 2007 ዓ.ም. በአዲስ አበባ ውይይት ይጀመራል፡፡ ውይይቱ ቀጠሮ የተያዘለት በቴክኒክ ሪፖርቱ ላይ ለመወያየት ቢሆንም፣ ድርጅቶቹ ሪፖርቱን ለማዘጋጀት ቅድመ ሁኔታ ማቅረባቸው ታውቋል፡፡
በውኃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስቴር የወሰንና ወሰን ተሻጋሪ ወንዞች ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ተሾመ አጥናፌ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ስብሰባው የተቀጠረው አማካሪ ድርጅቶቹ ባቀረቡት የቴክኒክ ሪፖርት ላይ ለመወያየት ነበር፡፡ ነገር ግን የቴክኒክ ሪፖርቱን ለማዘጋጀት ቅድመ ሁኔታ በማቅረባቸው ስብሰባው በቅድመ ሁኔታዎቹ ላይ ይነጋገራል፡፡ የቴክኒክ ፕሮፖዛሉን ለማዘጋጀት መመርያዎችን እንደሚያስተላልፍም እንደሚጠበቅ አመልክተዋል፡፡ በእነዚህ ሁኔታዎች ላይ ስምምነት ላይ ሲደረስ ከአማካሪ ድርጅቶቹ ጋር ስምምነት እንደሚፈራረሙም አቶ ተሾመ ጠቁመዋል፡፡
አማካሪ ድርጅቶቹ በደብዳቤ ቅድመ ሁኔታዎችን ለሦስቱም አገሮች ቢያሳውቁም፣ አቶ ተሾመ ግን ቅድመ ሁኔታዎቹ ምን ምን እንደሚያካትቱ ከመግለጽ ተቆጥበዋል፡፡ ምክንያቱ ደግሞ የሦስቱ አገሮች የቴክኒክ ኮሚቴ አባላት በተናጠል መረጃ ስለማይሰጡ ነው፡፡
በመስከረም ወር 2007 ዓ.ም. ከኢትዮጵያ፣ ከግብፅና ከሱዳን አራት አራት ባለሙያዎች የተወከሉበት የሦስትዮሽ የቴክኒክ ኮሚቴ የተቋቋመ ሲሆን፣ በሚያዝያ ወር 2007 ዓ.ም. በዕጩነት ከቀረቡት ዘጠኝ አማካሪ ድርጅቶች መካከል የፈረንሣዩ ቢአርኤል ግሩፕና የኔዘርላንዱ ዴልታ ሬስ ኩባንያዎች መርጠዋል፡፡ ኩባንያዎቹ ከተመረጡ በኋላ በሦስቱ አገሮች መካከል በተፈጠረ አለመግባባት ወዲያው ወደ ሥራ መግባት አለመቻላቸውን መዘገባችን ይታወሳል፡፡
ይሁንና በሐምሌ ወር መጨረሻ በሱዳን ካርቱም በተደረገው የሦስትዮሽ የቴክኒክ ኮሚቴው ስብሰባ ቢአርኤል ግሩፕ ዋና የፕሮጀክቱ ተጠሪ ሆኖ 70 በመቶውን ጥናት እንዲያከናውን፣ ዴልታ ሬስ ደግሞ የተቀረውን 30 በመቶ ጥናት እንዲያከናውን ተስማምተዋል፡፡
ቢአርኤል ግሩፕ ከኢትዮጵያ ጋር በርካታ ፕሮጀክቶችን በመሥራቱና ዕጩ ሆኖ የቀረበውም በኢትዮጵያ በመሆኑ ግብፅ ከፍተኛ ጥርጣሬ እንዳላት ምንጮች ለሪፖርተር መግለጻቸው ይታወሳል፡፡ ዓለም አቀፍ የባለሙያዎች ቡድን ያቀረባቸው ሁለት ምክረ ሐሳቦች ግድቡ በፍሰት፣ በማኅበራዊና አካባቢያዊ ሁኔታዎች ላይ የሚኖረው ተፅዕኖ ላይ ተጨማሪ ጥናቶች እንዲያከናወኑ ሲሆን፣ ግድቡ እየገፋ ጥናቱ ገና አለመጀመሩ ግብፅን ይበልጥ ሥጋት ላይ እንደጣለ ይነገራል፡፡
ኢትዮጵያ ግድቡ ግብፅ ያመጣል ብላ የምትሠጋውን ተፅዕኖ እንደማይፈጥር በተደጋጋሚ በመግለጽ ላይ ትገኛለች፡፡ የሁለቱ አገሮች ግንኙነትም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ መሻሻሎች እየታዩበት ሲሆን፣ ለዚህ ማሳያ የሚሆነው የግብፅ ፕሬዚዳንት አብዱልፈታህ ኤልሲሲ በመጋቢት ወር 2007 ዓ.ም. ኢትዮጵያን መጎብኘታቸውና በቅርቡም ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ የስዊዝ ካናል ማስፋፊያ ፕሮጀክት ምርቃት ላይ መገኘታቸው ነው፡፡