Tuesday, December 5, 2023
- Advertisment -
- Advertisment -

በሕገ መንግሥቱ 20ኛ ዓመት የሚወራረዱ ሒሳቦች

ኅዳር 29 ቀን 1987 ዓ.ም. የፀደቀው ሕገ መንግሥት በሙሉ ኃይሉ ሥራ ላይ የዋለበትና የፌዴራል ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ መንግሥት የተመሠረተው፣ የዛሬ 20 ዓመት ነሐሴ 15 ቀን 1987 ዓ.ም. ነው፡፡ 11 ምዕራፎችና 106 አንቀጾች ያሉት ይህ ሕገ መንግሥት ለዘጠኝ ክልሎች መመሥረትና አገሪቷንም ከአሃዳዊ አስተዳደር ወደ ፌዴራልነት የቀየራት ነው፡፡ ይህ ሕገ መንግሥት የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ሁለንተናዊ የሰብዓዊ መብት ድንጋጌዎችንና ዓለም አቀፍ የፖለቲካና የሲቪል ስምምነቶችንም የገዛ ራሱ ሕግ ያደረገ ነው፡፡

የዛሬ 20 ዓመት ሕገ መንግሥቱ ፀድቆ ሥራ ላይ ከዋለ ጀምሮ በርካታ ሙግቶች ተሰምተዋል፡፡ አገሪቱ ከአሃዳዊ ወደ ፌዴራላዊ አስተዳደር መዛወሯ፣ በብሔር ላይ የተመሠረተው ፌዴራላዊ አከላለል፣ የመሬት ይዞታ ጉዳይ፣ የብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች መብት እስከ መገንጠልና የመሳሰሉት ዋነኛ የመነታረኪያ አጀንዳዎች ነበሩ፡፡ ዛሬም ንትርኮቹ ይሰማሉ፡፡ ከዚያ ባለፈም ሕገ መንግሥቱንና ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን በተመለከተ ተቃርኖዎችም አሉ፡፡ እነዚህ ከሕገ መንግሥቱ ጋር ያለፉትን 20 ዓመታት የተጓዙ ናቸው፡፡ እነዚህን የመወዛገቢያ አጀንዳዎችን ትተን፣ የአገሪቱ ከ96 ሚሊዮን በላይ ሕዝብ እየተዳደረበት ያለው የሕጎቹ ሁሉ የበላይ የሆነው ሕገ መንግሥት እንዴት እየተከበረ ነው የሚለው ጉዳይ ላይ መነጋገር የተሻለ ነው፡፡ ሕገ መንግሥቱ ከተከበረ ለዜጎች በርካታ ጥያቄዎች መልስ ያስገኛል፡፡ በእዚህ ላይ ሒሳብ ማወራረድ ተገቢ ነው፡፡

የሕገ መንግሥቱ መነሻ የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች በአገራቸው ዘላቂ ሰላምና ዋስትና ያለው ዴሞክራሲ እንዲሰፍን፣ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ዕድገታቸው እንዲፋጠን፣ የራሳቸውን ዕድል በራሳቸው የመወሰን መብታቸውን በመጠቀም፣ በነፃ ፍላጎታቸው፣ በሕግ የበላይነትና በራሳቸው ፈቃድ ላይ የተመሠረተ አንድ የፖለቲካ ማኅበረሰብ በጋራ ለመገንባት ቆርጠው መነሳታቸውን ይገልጻል፡፡ ይህንን ዓላማ ከግብ ለማድረስም የግለሰብና የብሔር ብሔረሰብ መሠረታዊ መብቶች መከበራቸው፣ የፆታ እኩልነት መረጋገጡ፣ ባህሎችና ሃይማኖቶች ያላንዳች ልዩነት እንዲራመዱ አስፈላጊነት ፅኑ ዕምነታቸው መሆኑን ይገልጻሉ፡፡ ሌሎች ተደጋጋፊ የሆኑ ሐሳቦችን በማውሳት ሕገ መንግሥቱ ከላይ ለተገለጹት ዓላማዎችና ዕምነቶች ማሰሪያ መሆኑን ያረጋግጣሉ፡፡ በእርግጥም ሕገ መንግሥቱ ባጎናፀፋቸው መብቶች የተደሰቱ፣ ቋንቋቸውንና ባህላቸውን በሚገባ የተጠቀሙ፣ በፌዴራል አወቃቀሩ ምክንያት የሥልጣን ባለቤት መሆን የቻሉ ወገኖች አሉ፡፡

እዚህ ሕገ መንግሥት ውስጥ የሰፈሩት ሐሳቦች በሙሉ ኃይላቸው ሥራ ላይ  ቢውሉ የአገሪቱን ሰላም ለማረጋገጥ፣ የዜጎችን ዴሞክራሲያዊና ሰብዓዊ መብቶች ለማስከበር፣ የአገሪቱን ሕዝብ ጥቅም፣ መብትና ነፃነት በጋራ በማሳደግ አንድ የኢኮኖሚ ማኅበረሰብ ለመገንባት ወሳኝ ግብዓቶች መሆን ይችላሉ፡፡ ያለፉትን ሃያ ዓመታት የአገሪቱን ጉዞ ስንገመግም ግን ተገኙ የተባሉ ድሎችን ያህል በርካታ ተግዳሮችም ታይተዋል፡፡ በተለይ በሕገ መንግሥቱ ውስጥ መሠረታዊ ሰብዓዊ መብቶችን በተመለከተ የተቀመጡት አንቀጾች ተግባራዊ ሊደረጉ ባለመቻላቸው፣ የሰብዓዊ መብት ጥሰትና የዜጎችን መብት ያለማስከበር መንግሥትን አስከስሰውታል፡፡ አሁንም በብርቱ እያስነቀፉት ነው፡፡

በሕገ መንግሥቱ ምክንያት በጦርነት ትታመስ የነበረች አገር ሰላሟ ቢረጋገጥም፣ በአገራቸው ባይተዋርነት ይሰማቸው የነበሩ ወገኖች ባለቤት የመሆን ስሜት ቢያድራቸውም፣ የመንግሥት ሥልጣን ቢጋሩም፣ አሁንም የሚቸግሩ ጉዳዮች ብዙ ናቸው፡፡ መንግሥት ብዙ ጊዜ ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱንና ሕገ መንግሥቱን ለመናድ ተነስተዋል በማለት በርካቶችን ሲከስና ሲያስቀጣ ቆይቷል፡፡ በዚህም ምክንያት በእስር ቤት ፍርዳቸውን እየተቀበሉ ያሉ በርካቶች ናቸው፡፡ ነገር ግን ራሱ መንግሥት የተለየ አመለካከት ያላቸውን፣ የሚቃወሙትንና አሠራርህን አንደግፍም የሚሉትን በሚከስበትና በሚያስርበት አገር ውስጥ፣ ራሱ የንግግር ነፃነትና ሰብዓዊ መብትን ሲጋፋ የሚጠየቀው እንዴት ነው? ዴሞክራሲ የህልውናዬ እስትንፋስ ነው እያለ ፀረ ዴሞክራሲ ተግባራትን ሲፈጽም ሒሳቡ እንዴት ነው የሚወራረደው? የመድበለ ፓርቲ ሥርዓቱ የፖለቲካ ምኅዳሩ በመጣበቡ ምክንያት ህልውናው እየከሰመ እያለ እንዴት ነው እየዳኸ ያለው ዴሞክራሲ ጉልበቱ የሚጠናው? ሌሎች ተጠቃሽ ችግሮችም አሉ፡፡

ሕገ መንግሥቱ በሕገ መንግሥት አርቃቂ ኮሚሽን አማካይነት ተረቆ ለሕገ ጉባዔ በቀረበበት ወቅት የነበረው የሐሳብ ጦርነት አይናፍቅም? በወቅቱ ለፓርላማው አንድ ድምቀት የነበሩት በግል የፓርላማ አባል የነበሩት ሻለቃ አድማሴ ዘለቀና የኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል ተወላጅ የሆኑት ዶ/ር አብዱልመጂድ ሁሴን መካከል የነበረው የሕገ መንግሥቱ ዕይታ (በተለይ አንቀጽ 39) እንዴት ይረሳል? በተለይ ሻለቃ አድማሴ ሕገ መንግሥቱ የፀደቀበትን ቀን ለኢትዮጵያ ሕዝብ የሐዘን ቀን ነው ሲሉ፣ ዶ/ር አብዱልመጅድ ደግሞ ለኢትዮጵያ ሕዝብ የነፃነት ቀን ነው ብለው ያቀረቧቸው መከራከሪያዎቻቸው ዕድሜ ለንግግር ነፃነት፣ ዕድሜ ለዴሞክራሲ አያስብሉም? ይኼ ዓይነቱ አንፃራዊ ዥንጉርጉርነትና ልዩነት ዛሬስ ከናካቴው አለመኖሩ አይቆጭም ወይ? እንደዚያ ዓይነት የተጋጋሉና በልዩነት የታጀቡ ሐሳቦች በራሱ በሕገ መንግሥቱ ጭምር ዕውቅና የተሰጣቸው እንደነበሩ ማን ይዘነጋል? የሕገ መንግሥቱ አንዱ ትሩፋት ይኼም ነበር፡፡

ይህ ሕገ መንግሥት በበርካታ ጎኖቹ እጅግ ክቡር የሆነውን የሰው ልጅ መሠረታዊ መብቶች በሕግ ያረጋገጠና ለአገር ታላቅ ጠቃሚ የሆነ የሕግና የፖለቲካ ሰነድ ነው፡፡ ነገር ግን እንዴት ነው እየተከበረ ያለው? ሕገ መንግሥቱ በሐሳብ መለያየት ሞት አይደለም ባለበት አገር ውስጥ ለተቃራኒ ሐሳቦች መንገድ መዝጋትና እኔን የማይመስል ለአገር ጠቃሚ አይደለም የሚለው ጉዳይ ከአገር አልፎ በዓለም አቀፍ ደረጃም እያስተቸ ነው፡፡ እያስወገዘ ነው፡፡ መንግሥት ለሕገ መንግሥቱ ምን ያህል ተገዝቷል? እንዴትስ ይተዳደርበታል? አገርንስ እንዴት እያስተዳደረበት ነው? በርካታ ጥያቄዎች አሉ፡፡ በሕግ አምላክ መባል አለበት፡፡

‹ዴሞክራሲ ማለት ምርጫ ብቻ አይደለም› እየተባለ ሲነገር እየተደመጠ ነው፡፡ በሰላማዊ ትግሉ ተሳታፊ የሚሆኑ ጠንካራ የተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲዎች የሚኖሩት የፖለቲካ ምኅዳሩ ሲሰፋና የመጫወቻ ሜዳው ለሁሉም እኩል ሲሆን ነው፡፡ በአገሪቱ ባለፉት ሃያ ዓመታት አምስት ምርጫዎች ተካሂደው አንድም ጊዜ ተቀራራቢነት ያለው ድምዳሜ ላይ መድረስ ያልተቻለው፣ በፖለቲካ ኃይሎች መካከል ስምምነት ባለመኖሩ ነው፡፡ የሕግ የበላይነት አለ በሚባልበት አገር ውስጥ ከሕግ በላይ የፖለቲካው ጡንቻ በማበጡ የአገሪቱ የፖለቲካ ኃይሎች ግንኙነት የደፈረሰ ሆኗል፡፡ በጥላቻ የተዋጠ ሆኗል፡፡ በዚህ ምክንያት የሕገ መንግሥቱ ወርቃማ አንቀጾች አረም ለብሰዋል፡፡

ሕገ መንግሥቱ የመንግሥትና የሃይማኖት መለያየትን በማያዳግም ሁኔታ በለያየበት ወሳኝ ዕርምጃው፣ መንግሥትና የፓርቲ ርዕዮተ ዓለም ከአንድ ምንጭ የተቀዱ እስኪመስሉ ድረስ ተደበላልቀዋል፡፡ ገዥው ፓርቲ የሚመራበትን ርዕዮተ ዓለም ከሕገ መንግሥቱም ሆነ ከሌሎች መንግሥታዊ መዋቅሮች ጋር ማደባለቁን ማቆም አለበት፡፡ አንዱ ትልቁ ችግር ይኼ ነው፡፡ ሕገ መንግሥቱ በራሱ መቆም የሚችል ትልቅ የአገር ሰነድ እንደመሆኑ መጠን የየትኛውንም ወገን ሐሳብ ሊሞረከዝ አይገባውም፡፡ ይህ ሲደረግ ሕገ መንግሥቱ ይከበራል፡፡ በሙሉ ኃይሉ ሥራ ላይ ይውላል፡፡ ያኔ የአገሪቱ ሰላም ሙሉ በሙሉ ዋስትና ይኖረዋል፡፡ የዜጎች ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች ይከበራሉ፡፡ አገር በነፃነት እየተራመደች ትበለፅጋለች፡፡

በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 9 ስለ የሕገ መንግሥት የበላይነት የተዘረዘረው እንዲህ ይላል፡፡ ‹‹ሕገ መንግሥቱ የአገሪቱ የበላይ ሕግ ነው፡፡ ማንኛውም ሕግ፣ ልማዳዊ አሠራር፣ እንዲሁም የመንግሥት አካል ወይም ባለሥልጣን ውሳኔ ከዚህ ሕገ መንግሥት ጋር የሚቃረን ከሆነ ተፈጻሚነት አይኖረውም፡፡ ማንኛውም ዜጋ፣ የመንግሥት አካላት፣ የፖለቲካ ድርጅቶች፣ ሌሎች ማኅበራት፣ እንዲሁም ባለሥልጣኖቻቸው ሕገ መንግሥቱን የማስከበርና ለሕገ መንግሥቱ ተገዥ የመሆን ኃላፊነት አለባቸው፡፡ በዚህ ሕገ መንግሥት ከተደነገገው ውጪ በማናቸውም አኳኋን  የመንግሥት ሥልጣን መያዝ የተከለከለ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ያፀደቀቻቸው ዓለም አቀፍ ስምምነቶች የአገሪቱ ሕግ አካል ናቸው፤›› ነው የሚለው፡፡ በተለይ ከሕገ መንግሥታዊ ድንጋጌ ውጪ ሥልጣን መያዝ የተከለከለ ነው ማለት፣ ከዚህ ሥርዓት ውጪም ሥልጣን ላይ መቆየት አይቻልም ማለት መሆኑ መታወቅ ይኖርበታል፡፡ በመሆኑም የሕገ መንግሥቱ 20ኛ ዓመት ሲታሰብ፣ ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ እንቅፋት የሆኑ ችግሮችና ሰብዓዊ መብትን የሚጋፉ ተግባራት ይወገዱ፡፡ በዚህ መንገድም ሒሳቦች ይወራረዱ!       

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች

በዓለም አቀፍ ደረጃ ሕይወታቸውን በኤድስ ምክንያት ላጡ ሰዎች 35ኛ ዓመት መታሰቢያ

ያለፍንበትን እያስታወስን በቁርጠኝነት ወደፊት እንጓዝ - በኧርቪን ጄ ማሲንጋ (አምባሳደር) በየዓመቱ...

እዚያ ድሮን… እዚህ ድሮን…

በዳንኤል ካሳሁን (ዶ/ር) ተዓምራዊው የማዕበል ቅልበሳ “በሕግ ማስከበር” ዘመቻው “በቃ የተበተነ...

ለፈርጀ ብዙ የማንነት ንቃተ ህሊናችን የሚጠቅሙ ጥቂት ፍሬ ነገሮች

በበቀለ ሹሜ ከጨቅላነት ጅምሮ ያለ የእያንዳንዳችን የሰብዕና አገነባብ ከቤተሰብ እስከ...

በሲሚንቶ ፋብሪካ ላይ የታየው ተሞክሮ በሌሎች ምርቶች ላይም ይስፋፋ!

ሰሞኑን በኢትዮጵም ሆነ በአፍሪካ ደረጃ ግዙፍ ስለመሆኑ የተነገረለትን የለሚ...
spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

የአስተሳሰብና የአስተዳደር ዘይቤ ለውጥ ያስፈልጋል!

ኢትዮጵያ ውስጥ ሕዝቡን በጋራ አስተሳስረው የሚያኖሩ በጣም በርካታ ማኅበራዊ እሴቶች አሉ፡፡ እነዚህ ለዘመናት ከትውልድ ወደ ትውልድ ሲሸጋገሩ የኖሩ እሴቶች አገር ለማቆም ትልቅ አስተዋፅኦ ነበራቸው፣...

ድጋፍና ተቃውሞ እኩል ይስተናገዱ!

ኢትዮጵያ ውስጥ ለረዥም ዓመታት ለመንግሥት ከሚቀርቡ ጥያቄዎች መካከል አንዱ የመብት መከበር ጉዳይ ነው፡፡ ዜጎች ተፈጥሯዊም ሆኑ ሕጋዊ መብቶቻቸው እንዲከበሩላቸው ለመንግሥት ጥያቄ ሲያቀርቡ፣ ጥያቄው የቀረበለት...

ፖለቲካዊ ችግሮች ፖለቲካዊ መፍትሔ ይፈለግላቸው!

መንግሥት ከኦነግ ሸኔ ጋር በታንዛኒያ ዳሬሰላም ከተማ ሲያካሂድ የነበረው ንግግር ያለ ውጤት መጠናቀቁን ካስታወቀ በኋላ፣ በኦሮሚያ ክልልም ሆነ በሌሎች ቦታዎች ሰላም ለማስፈን የነበረው ተስፋ...