Tuesday, January 31, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊበዝናብ እጥረት ለተጎዱ ወገኖች 222 ሺሕ ሜትሪክ ቶን ስንዴ እንዲገዛ ተወሰነ

በዝናብ እጥረት ለተጎዱ ወገኖች 222 ሺሕ ሜትሪክ ቶን ስንዴ እንዲገዛ ተወሰነ

ቀን:

የአደጋ መከላከልና ዝግጁነት ኮሚቴ በዝናብ እጥረት ለተጎዱ ወገኖች 222 ሺሕ ሜትሪክ ቶን ስንዴ ከውጭ አገር ግዥ እንዲፈጸም ተወሰነ፡፡ ከውጭ አገር የሚገዛው ስንዴ ለመጠባበቂያ እህል ክምችት ገቢ እንዲደረግ ትዕዛዝ ተሰጥቷል፡፡

በግብርና ሚኒስቴር የአደጋ መከላከልና ዝግጁነት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ምትኩ ካሳ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ በተከሰተው የዝናብ እጥረት የምግብ ዋስትናቸው ለተናጋባቸው አርሶ አደሮችና አርብቶ አደሮች የዕለት ደራሽ ዕርዳታ እየተከፋፈለ ነው፡፡

የስንዴ ግዥው እንዲፈጸም የተወሰነው ከመጠባበቂያ እህል ክምችት ወጭ ተደርጎ ለተጎጂዎች የተከፋፈለውን ስንዴ እንዲተካ ለማድረግ እንደሆነም አቶ ምትኩ ገልጸዋል፡፡

የስንዴ ግዥ የሚፈጸመው በመንግሥት ግዥና ንብረት ማስወገድ አገልግሎት በኩል ሲሆን፣ አገልግሎት ድርጅቱ የስንዴ ግዥውን ለመፈጸም ጨረታ ለማውጣት እየተዘጋጀ መሆኑ ታውቋል፡፡

የመንግሥት ግዥና ንብረት ማስወገድ አገልግሎት ሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ መልካሙ ደሳሊ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ መሥሪያ ቤታቸው ቀደም ሲል የስንዴ ግዥ ሲፈጽም የቆየ እንደመሆኑ በቂ ልምድ አለው፡፡ በመሆኑም በአፋጣኝ ግዥ ለመፈጸም ጨረታ ያወጣል ብለዋል፡፡

በክረምት ወራት መጣል የነበረበት ዝናብ በአየር ፀባይ መዛባት ምክንያት መስተጓጎሉ ይታወቃል፡፡ ይህ ክስተት በክረምት ዝናብ ላይ በመመሥረት የግብርና ልማት በሚያካሂዱ አርሶ አደሮችና አርብቶ አደሮች ላይ ተፅዕኖ ማሳደሩ ተገልጿል፡፡

አቶ ምትኩ እንደገለጹት፣ ይህንን ተፅዕኖ ለመቅረፍ መንግሥት አራት ጉዳዮች ላይ ትኩረት በማድረግ እየሠራ ነው፡፡

እነዚህም ዘግይቶ በመጣል ላይ ያለውን ዝናብና ውኃ ማቀብ፣ በአጭር ጊዜ የሚደርሱ የማካካሻ ዘሮችን ለተጎጂ አርሶ አደሮች ማቅረብ፣ ለአርብቶ አደሮች የእንስሳት መኖ ማቅረብና ለተጎጂዎች የዕለት ደራሽ ዕርዳታ ማከፋፈል ናቸው፡፡

እነዚህ ተግባራት እየተከናወኑ ያሉት በአደጋ መከላከልና ዝግጁነት ኮሚቴ አስተባባሪነት ሲሆን፣ ኮሚቴውን ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ አቶ ደመቀ መኮንን ይመሩታል፡፡ በዚህ ኮሚቴ ውስጥ በዋነኛነት ግብርና ሚኒስቴር፣ የገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ሚኒስቴርና ብሔራዊ ሚቲዎሮሎጂ ኤጀንሲ ይገኙበታል፡፡

መንግሥት ለእነዚህ ሥራዎች 700 ሚሊዮን ብር በጀት ይዟል፡፡ አቶ ምትኩ እንደሚሉት፣ እስካሁን 20 ሺሕ ሜትሪክ ቶን እህልና 500 ሺሕ ሜትሪክ ቶን የተለያዩ አልሚ ምግቦች በዝናብ እጥረቱ ለተጎዱ የኅብረተሰብ ክፍሎች ተከፋፍሏል፡፡

ግዥ እንዲፈጸምለት የተወሰነው 222 ሺሕ ሜትሪክ ቶን ስንዴ በተያዘው በጀት ውስጥ አይካተትም ካሉ በኋላ፣ የስንዴ ግዥው የሚፈልገው በጀት ከጨረታ ሒደት በኋላ የሚታወቅ መሆኑን አቶ ምትኩ አስረድተዋል፡፡

መንግሥት በተጠናቀቀው በጀት ዓመት 300 ሺሕ ሜትሪክ ቶን ስንዴ ግዥ ፈጽሟል፡፡ አቶ መልካሙ እንደገለጹት፣ ለዚህ ግዥ 2.9 ቢሊዮን ብር ወጪ ተደርጓል፡፡

በ2007 ዓ.ም. የተገዛው ይህ ስንዴ ዋነኛ ዓላማው ዝቅተኛ ገቢ ላላቸው የኅብረተሰብ ክፍሎች መንግሥት በድጎማ ስሌት ያቀረበው መሆኑ ታውቋል፡፡

ነገር ግን በአሁኑ ወቅት እንዲገዛ የተወሰነው ስንዴ በዝናብ እጥረቱ ምክንያት ጉዳት ለደረሰባቸው የኅብረተሰብ ክፍሎች የተከፋፈለውንና በቀጣይነት የሚከፋፈለውን ስንዴ የሚተካ መሆኑ ተገልጿል፡፡   

 

 

 

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የገጠር መሬት ማሻሻያና የመሬት ባለቤትነት ጥያቄ በኢትዮጵያ

በኢትዮጵያ ከቅርብ ወራት ወዲህ መሬትን በተመለከተ ጠንከር ያሉ የለውጥ...

በፖለቲከኞች እጅ ያለው ቁልፍ

ኢትዮጵያ በተለይ ካለፉት አምስት ዓመታት ወዲህ ሰላሟ መረጋጋት አቅቶታል፡፡...

የኤክሳይስ ታክስ ረቂቅ አዋጅ ፓርላማው ያፀደቀውን አዋጅ የሚጥሱ ድንጋጌዎችን በማካተቱ እንዳይፀድቅ ተጠየቀ

ሰሞኑን ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የቀረበው የኤክሳይስ ታክስ ማሻሻያ...

በፀጥታ ችግር ሳቢያ ከተለያዩ አካባቢዎች ተፈናቅለው አማራ ክልል የገቡ ዜጎች ቁጥር 800 ሺሕ መድረሱ ተነገረ

በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል 112 ሺሕ ተማሪዎች ከትምህርት ገበታ ውጪ...