ሰኞ ነሐሴ 11 ቀን 2007 ዓ.ም. የደቡብ ሱዳን ተቀናቃኞችን ለማደራደር በተደረገው ጥረት ውጥረት በተፈጠረበት ሰዓት፣ ከግራ ወደ ቀኝ የኢጋድ ዋና ጸሐፊ አምባሳደር ማህቡብ ማዕሊም፣ የኢጋድ ምክትል ሊቀመንበር ኡሁሩ ኬንያታ፣ የኢጋድ ሊቀመንበር ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝና የአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ዶ/ር ንኮሳዛና ድላሚኒ ዙማ በዋና አደራዳሪው አምባሳደር ሥዩም መስፍን የሚደረግላቸውን ገላጸ በዚህ ሁኔታ ነበር በትኩረት ሲያዳምጡ የነበሩት፡፡
*************
ፍቅር መጨረሻ
አንቺ ከፍ ብለሽ ቀና ብዬ ሳይሽ
ያመኛል አንገቴን አዘቅዝቄ ልይሽ
አውቃለሁ አትችይም አንቺም ማለት ቀና
እኔን ዝቅዝቅ ማየት ታልሚያለሽና
ጐረቤቶቻችን አይወዱም ግልፅ ነው
እኛ ከፍ ብለን ሊያዩን ቀና ብለው
እኛም አንወድም ለቅፅበት ላንዳፍታ
ቀና ብሎ ማየት የነሱን ከፍታ
ማንም ቀና እንዳይል እንዳይዝል አንገቱ
ማንም እንዳይወጣ ከዝቅጠት ዑደቱ
አንዱ አልፎለት ሌላው እንዳይግል ቅናቱ
እንዳይናጋብን ማጣት አንድነቱ
አንድ ላይ እንነስ ባንዴ እንስነፍና
አብረን እንቆርቁዝ አብረን እንተኛና
ከዛሬ ጀምሮ ቃል ገባሁኝ ግቢ
ዘመድ አዝማድ ልጥራ ጐረቤት ሰብስቢ
ሁላችን በአንድነት ሁነን በጉባኤ
ከዚህ ድንበር ላናልፍ እንግባ ሱባኤ
ተስፋ ያደረገ ተስፋው እንዲጠፋ
ፈጥኖ የተራመደ ተፋጥኖ እንዲደፋ
አንዳችን ላንዲችን ጠባቂ ሁነነው
አብረን እንቀመጥ እንዲሁ እንዳለነው
የአብሮ መኖራችን ዋናው መሠረቱ
ከፍ ዝቅ አይልም እኩል ነው ፍጥረቱ
መዘወት ይሻላል ፊት ለፊት ተፋጦ
እንዳንረባበሽ አንዱ ካንዱ በልጦ
ዛዲያ እንዴት ይደረግ ምንድነው ብልሃቱ
ፍቅርን ለመጨረስ ይህ ነው አብነቱ
- ጁን 29/ፓሪስ ተፈሪ ዓለሙ
- ተፈሪ ዓለሙ፣ ‹‹የካፊያ ምች›› (2007)
**************
‹‹71 ሊሆነኝ ነው የሚሰማኝ ግን 30 እንደሆንኩ ነው››
በመጭው ወር 71 ዓመት የሚሆናቸው የዩጋንዳው ፕሬዚዳንት ዮዌሪ ሙሴቬኒ ምንም እንኳ ዕድሜአቸው እየገፋ ቢሆንም፣ አቋማቸውና ጤናቸው የ30 ዓመት ወጣት እንደሚመስል ባለፈው ሳምንት በካዮንጋ ከተማ መናገራቸውን ዘኒው ቪዥንና ዴይሊ ሞኒተር ዘግበዋል፡፡
ፕሬዚዳንት ሙሴቬኒ ይህ የሆነው አኗኗራቸው ጤናማ በመሆኑና ጤናቸውን አደጋ ላይ ሊጥሉ ከሚችሉ እንደ አልኮልና ዘማዊነት ያሉ ነገሮች ራሳቸውን በማቀባቸው እንደሆነ አስረድተዋል፡፡
‹‹ጤናዬን በጣም እጠብቃለሁ፡፡ አልኮል አልጠጣም ለዚህም ነው አሁንም ጠንካራና ኃይለኛ የሆንኩት፡፡ የእናንተም ጤና ሀብት በመሆኑ ጤናችሁን ልትጠብቁ ይገባል፡፡ ኦቦቴን፣ ኢዲያሚንን፣ ኦኬሎንና ጆሴፍ ኮኒን ተዋግቻለሁ አሁንም ግን ጠንካራ ነኝ›› ብለዋል፡፡
የጤናማ አኗኗር አቀንቃኝ የሆኑት ሙሴቬኔ፣ ከዚህ ቀደም ቢቢሲ ሀርድ ቶክ ላይ አሳ፣ ዶሮና የአሳማ ሥጋ እንደማይበሉ ተናግረው ነበር፡፡ ብዙ ጊዜ ዩጋንዳውያን ጤናማ ባልሆነ የኑሮ ዘዬ ሕይወታቸውን እንደሚያጡ ሲናገሩም ይደመጣሉ፡፡
*******************
‹‹ብሽቅ!››
ኤደንብራ ውስጥ የሚገኙት የዊቨርሊ ደረጃዎች ነፋስ ይበዛባቸዋል፡፡ ካመት ዓመት ያለማቋረጥ ኃይለኛ ነፋስ እንደነፋስ ነው፡፡ ታዲያ አንድ ቀን አንዷ ሴት ወይዘሮ ባቡር ልትሳፈር ተቻኩላ ደረረጃዎቹን እየሮጠች ወጥታ ስትጨርስ ነፋሱ ገለባት፡፡ ተናዳ ያያት ሰው መኖሩን ለማወቅ ዞር ብላ ስትመለከት አንዱ ከታች ያጮልቃል፡፡
‹‹ወደ ሥራህ ብትሄድ አይሻልም!?›› አለችው በተግሳጽ፡፡
‹‹እሺ፣ እሄዳለሁ፤ ግን ትላንትም የለበሽው ይህንኑ የውስጥ ሱሪ ነበር አይደል?›› አላት፡፡
****************
ፖሊሲ ጣቢያ
ሰውየው በመርሴዲስ መኪና ስርቆት ቢወነጀልም ድርጊቱን አለመፈፀሙን አምርሮ በመግለፁና በጠበቃውም ብርታት ነፃ ይዋጣል፡፡ ሪገር ግን በማግስቱ ወደ ፖሊስ ጣቢያ ገስግሳ ይሄድና፣ ‹‹ያዓ ጠበቃዬን እንድትይዙልኝ ላመለክት ነው የመጣሁት›› ይላል፡፡
የጣቢያው ኃላፊ ተገርመው፣ ‹‹ለምን? ነፃ ያወጣህ እሱ አልነበረም እንዴ?›› አሉት፡፡
‹‹እሱማ ነው! ሆኖም ያገልግሎቱን ዋጋ ልከፍለው ስላልቻልሁ የሠረቅኳትን መርሴዲስ መኪና ነጥቆኝ ስለተወሰረ ነው የከሰስኩት፡፡››
- አረፈዓይኔ ሐጐስ ‹‹የስኮትላንዳውያን ቀልዶች›› (2005)
*************
ሒላሪ ክሊንተንን እንዳትመርጡ የሚል መልዕክት የሐዘን መግለጫ ላይ ወጣ
በኒው ጀርሲ የ63 ዓመት አዛውንት ሕይወታቸው ከማለፉ በፊት ባለቤታቸው የሐዘን መግለጫ ሲያወጡ መልዕክቱ ‹‹ሒላሪ ክሊንተንን እንዳትመርጡ›› የሚል እንዲሆን በመጠየቃቸው የሐዘን መግለጫው በመጨረሻ ክሊንተንን እንዳትመርጡ የሚል መሆኑን አሶሽዬትድ ፕሬስ ዘግቧል፡፡
የአዛውንቷ ባለቤት ኢሌን ፋይድሪክ ሚስታቸው ፖለቲከኛ እንዳልነበሩ ነገር ግን እ.ኤ.አ. የ2012 የቤንጋዚውን የአሜሪካ ኤምባሲ ጥቃትን ተከትሎ ሒላሪ ክሊንተንን መጥላት መጀመራቸውን ተናግረዋል፡፡
እሳቸው እንደገለጹት ሚስታቸው ሕይወታቸው ከማለፉ ከጥቂት ሳምንታት በፊት ምንም እንኳ የመጨረሻው ውሳኔ የእሳቸው ቢሆንም የሐዘን መግለጫው ላይ ‹‹እባካችሁ ለሒላሪ ክሊንተን ድምፃችሁን አትስጡ›› የሚል መልዕክት እንዲሰፍር ጠይቀዋቸዋል፡፡ እሳቸውም የሚስታቸውን ቃል ጠብቀዋል፡፡