Sunday, June 23, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ኪንና ባህል‹‹አገራችንን ስለምንወድ ብዙም ሳንጠብቅ እናገለግላለን›› ኮሜዲያን ልጅ ያሬድ

‹‹አገራችንን ስለምንወድ ብዙም ሳንጠብቅ እናገለግላለን›› ኮሜዲያን ልጅ ያሬድ

ቀን:

የቡሔ በዓልን ምክንያት በማድረግ ቦሌ አካባቢ የተሠባሰቡ ወጣቶች ተመሳሳይ ባህላዊ አልባሳት ለብሰው ‹‹ሆያ ሆዬ›› ይላሉ፡፡ ቦሌ መሰናዶ ትምህርት ቤት አካባቢ ከአንዱ መገበያያ ሕንፃ ወደ ሌላው ሲዘዋወሩ በለሆሳስ የሚሰማው ጭፈራቸው ለበዓሉ ልዩ ድባብ ሰጥቶታል፡፡ የቦሌ መሰናዶ ትምህርት ቤት ከጥግ እስከ ጥግ በማዳበሪያ ተሸፍኗል፡፡ ከማዳበሪያው አልፎ በመጠኑ የሚታየው የትምህርት ቤቱ አጥር እድሳት እየተከናወነ መሆኑን ያሳያል፡፡

የተሸፈነውን አልፈን ስንገባ ብዙ ወጣቶች በትምህርት ቤቱ አጥር ላይ ሥዕል ሲስሉ ተመለከትን፡፡ ወጣቶቹ ልዩ ልዩ ቀለማት ያላቸው ስፕሬዮች ተጠቅመው ይሥላሉ፡፡ ‹‹ጽዱ አዲስ››፣ ‹‹ጥበብ››ና ‹‹ቢ ዘ ቼንጅ ዩ ዋንት ቱ ሲ›› በትምህርት ቤቱ አጥር ከተጻፋ ጽሑፎች መካከል ናቸው፡፡

 ወጣቶቹ ቡሔን አካባቢን በማሳመር ለማሳለፍ ቆርጠው የተነሱ ይመስላል፡፡ ከወጣቶቹ አንዱ ኮሜዲያን ልጅ ያሬድ ነው፡፡ አጥሩ ላይ እየሣለ የሌሎቹን ወጣቶች ሥራዎችም ተዘዋውሮ ሲመለከት ነበር ያገኘነው፡፡ ልጅ ያሬድ እንደሚለው፣ የትምህርት ቤቱን አጥር አጽድተው ግራፊቲ አርት ማስፈር ከጀመሩ ቀናት ተቆጥረዋል፡፡ ከስለሺ ደምሴ (ጋሽ አበራ ሞላ) ጋር ሆነው የጀመሩት የጽዳት ዘመቻ በቆሻሻ የሚታወቁ አካባቢዎችን አፅድቶ በሥነ ጥበብ ለማሳመር ያለመ ነው፡፡ መነሻቸውን የቦሌ መሰናዶ ትምህርት ቤትን አጥር ቢያደርጉም ሌሎች አካባቢዎችን እንደሚያዳርሱም ይናገራል፡፡

ልጅ ያሬድና ጓደኞቹ ከሚሥሉበት ትምህርት ቤት አቅራቢያ በሚገኘው አዲስ ጉርሻ ሬስቶራንት ‹‹እንደ ሙዴ››፣ የተሰኘ የኮሜዲ ምሽት ከጀመሩ ወር ሊሞላቸው ነው፡፡ ኮሜዲያኖችንና ልዩ ልዩ ተሰጥኦ ያላቸው ግለሰቦችን የሚያስተናግደው ‹‹እንደ ሙዴ›› በየሳምንቱ ረቡዕ ምሽት በሬስቶራንቱ ይቀርባል፡፡ የቡሄ ዕለት የቀረበው ዝግጅት የተጀመረው አመሻሽ ላይ ነበር፡፡ ኮሜዲያን ልጅ ያሬድ ትዕይንቱን የጀመረው በዓሉን በሚመለከት ቀልድ ነበር፡፡

‹‹ዛሬ ሆያ ሆዬ እየሰማሁ ነበር፤ ጠዋት ልጆች መጡና እዛ ማዶ አንድ ብር፤ እዛ ማዶ አንድ ብር ሲሉ ተናድጄ ገና ጠዋት ከመንቃቴ ደህና ብር አትጠሩም? በአንድ ብር ምን ዓይነት ልክፍት ነው አልኩኝ፡፡ ግጥሙን ሲቀይሩት እዛ ማዶ አንድ አንበሳ እዚ ማዶ አንድ አንበሳ፤ የዚ ቤት ጌታ ባለ 40/60፡፡ አሉ›› ልጅ ያሬድ በቀልዱ ታዳጊዎቹ ወቅታዊ የሆነ ጉዳይ በማንሳት ገንዘብ የሚሰጠውን ሰው ልብ ለማራራት እንደሚጣጣሩ ያሳየበት ነበር፡፡

የልጅ ያሬድ ቀልዶች ልዩ ልዩ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ ያተኮሩ ነበሩ፡፡ በዕለት ከዕለት ሕይወት የሚያጋጥሙና ብዙዎች ልብ የማይሏቸው አጋጣሚዎች ይገኙበታል፡፡ እንደ ምሣሌ የሚጠቀሰው፣ ቃላት ሲጠብቁና ሲላሉ የሚሰጡትን የተለየ ትርጓሜ በአዝናኝ መልኩ ማቅረቡ ነው፡፡ ታዋቂ ድምጻውያንን ወረፍ የሚያደርጉ ቀልዶችም ታዳሚውን አዝናንተዋል፡፡ በሬስቶራንቱ የተገኙ ታዳሚዎችን ገጽታና አኳኋን ተመርኩዞ የሚሰነዝራቸው አስተያየቶች ከታዳሚው ጋር ያቀራረቡት ይመስላል፡፡

ማኅበረሰቡን ከሚፈታተኑ ችግሮች መሀከል የመሠረተ ልማት አለመዳረስ አንዱ ሲሆን፣ ከልጅ ያሬድ ቀልዶች አንዱም ይህንን ያንፀባረቀ ነው፡፡ ‹‹አንዱ ቻይናዊ ከኢትዮጵያ ወደ ቻይና ተመለሰ፡፡ አማርኛ ለመድክ ብለው ጠየቁት፡፡ በጣም ብዙ አማርኛ ለመድኩ (በተኮለታተፈ አማርኛ) አለ፡፡ እስኪ ትንሽ አማርኛ ንገረን ሲሉት፤ መብራት የለም፣ ውኃ የለም፣ ኔትወርክ የለምን ለምጃለሁ አለ፤›› የሚለው ይጠቀሳል፡፡

በምሽቱ ከልጅ ያሬድ በተጨማሪ ሌሎች ኮሜዲያንም ቀልዶችን አስደምጠዋል፡፡ በእግሩ የእንጨት ቁሳቁሶችን የሚሠራው ስንታየሁም የትዕይንቱ አካል ነበር፡፡ ልጅ ያሬድ እንደሚለው፣ የኮሜዲ ምሽቱ ማንኛውም ዓይነት ተሰጥኦ ላላቸው ግለሰቦች ክፍት ነው፡፡

ከጊዜ ወደ ጊዜ የስታንድአፕ ኮሜዲ ዝግጅት እየተለመደ መጥቷል፡፡ ኮሜዲያንን በጋራ እንዲሁም በተናጠል የሚያስተናግዱ የኮሜዲ ዝግጅቶች ታዳሚዎች ቁጥርም እየጨመረ ነው፡፡ በስታንድአፕ ኮሜዲ ዘርፍ የይሳቃል ኢንተርቴንመንት የኮሜዲ ምሽቶች ተጠቃሽ ሲሆኑ፣ ልጅ ያሬድም ከተሳታፊ ኮሜዲያኖች መሀከል ይጠቀሳል፡፡

መርካቶ፣ ሸማ ተራ የተወለደው ኮሜዲያኑ ያደገው ካራ ቆሬ አካባቢ ነው፡፡ ልጅነቱን ያሳለፈው ከሌሎች ታዳጊዎች ጋር ከብት እያገደ እንደነበር ይናገራል፡፡ ከገጠራማ አካባቢዎችና የገጠር ሕይወት ጋር ያለው ቁርኝት ጥብቅ መሆኑንም ይገልጻል፡፡ የሚኖረው ከዓለም ባንክ አልፎ በሚገኘው አንፎ ሰፈር ሲሆን፣ ቦታውን የመረጠው ለተፈጥሮ ያለውን ቅርበት ከግምት በማስገባት ነው፡፡ በአካባቢው የሥዕል ስቱዲዮ አለው፡፡ በአቅራቢያው ያሉና የሥዕል ዝንባሌ ያላቸው ወጣቶችን ያስተምራል፡፡ ከወዳደቁ ነገሮች ቁሳቁስ የመሥራት ልማድም አለው፡፡ ራሱን ለማስጌጥም የተፈጥሮ ውጤቶችን እንደሚመርጥ ይናገራል፡፡

ልጅ ያሬድ፣ ‹‹አንድም እንደ ራስተፈሪያን በሌላ በኩል ደግሞ ለአገሬ ልጅ ስለሆንኩኝ ልጅ እባላለሁ፤›› ይላል፡፡ ለአንድ ዓመት አሜሪካ ቆይቶ ወደ አገሩ ከተመለሰ በኋላ የተጀመረው ‹‹እንደ ሙዴ›› ተሰጥኦ ላላቸው ወጣቶች ዕድል ለመስጠት ያለመ እንደሆነ ይናገራል፡፡ ዛሬ የደረሰበት ደረጃ ለመድረስ በርካታ ውጣ ውረዶች እንዳለፈም ያስታውሳል፡፡

የኮሜዲ ምሽቱ ላይ ሥራዎቻቸውን የሚያቀርቡ ወጣቶች የዓመታት ጓደኞቹ ናቸው፡፡ ተሰጥኦዋቸውን ለማሳየት ያልፈነቀሉት ድንጋይ ባይኖርም ስኬት ላይ መድረስ ቀላል አልሆነም፡፡ ከመሀከላቸው አንዱ ሲሳካለት ሌሎችንም ማሰብ እንዳለበት ያምናል፡፡ የፈጠረው መድረክ ጓደኞቹን በችሎታቸው ሕዝብ እንዲያውቃቸው እንደሚረዳቸው  ይናገራል፡፡

በእሱ እምነት፣ ለወጣቶች በራቸው ክፍት የሆኑ ተቋማት ጥቂት ናቸው፡፡ ‹‹መድረክ ለማግኘት ከባድ ነው፤ ብዙዎች በወጣቶች ችሎታ አይተማመኑም፤›› ይላል፡፡ አገር ውስጥ ካሉ ሙያተኞች ይልቅ ውጭ አገር ያሉት የተሻለ ቦታ ሲሰጣቸው እንደሚታይ በሐዘኔታ ይገልጻል፡፡ አንዳንድ ባለሙያዎች አገር ውስጥ ካላቸው ዝና በበለጠ ውጪ ሀገር መታወቃቸውን ይጠቅሳል፡፡ እንደ ምሳሌ የሚያነሳው የሰርከስ ባለሙያዎችን ነው፡፡

እሱ እንደሚለው፣ ወጣቶች ችሎታቸውን የሚያሳዩበት መድረክ ሊመቻችላቸው ይገባል፡፡ የሥነ ጥበብ ጋለሪዎች እንዲሁም ሌሎች የጥበባት ማዕከሎች መስፋፋት እንዳለባቸውና ወጣቱ ትውልድ እንደሚናቀው ሳይሆን ታሪክ መሥራት እንደሚችል ይናገራል፡፡

በኮሜዲ፣ በግራፊቲ አርትና በተፈጥሮ ጥበቃ ዙሪያ የሚንቀሳቀው ያሬድ፣  በተፈጥሮ ጥበቃ ላበረከተው አስተዋፅኦ ከቀድሞው ፕሬዚዳንት ግርማ ወልደጊዮርጊስ ሽልማት አግኝቷል፡፡ ከጓደኞቹ ጋር የጥቁር አንበሳ ሆስፒታል የሕፃናት ክፍልን በሥዕል ማሳመራቸው ይጠቀል፡፡  ሥራውም ታማሚ ሕፃናት ሥዕሎቹን እያዩ መንፈሳቸው እንዲታደስ ለማድረግ ያለመ ነበር፡፡

 ‹‹አገራችንን ስለምንወድ ብዙም ሳንጠብቅ እናገለግላለን፤›› ይላል ልጅ  ያሬድ፡፡ አሁን መጠነኛ የሆነው ስቱዲዮአቸው ተከፋፍቶ የሥነ ጥበብ አፍቃሪዎች መዳረሻ እንደሚሆንም ተስፋ ያደርጋል፡፡

ልጅ ያሬድ በሚወደው የኢትዮጵያ ገጠራማ አካባቢዎች ላይ ያተኮሩ ቀልዶች ይስቡታል፡፡ የሚወዳቸውን ነገሮች በአግባቡ በመሥራትም ያምናል፡፡ ከልጅነቱ አንስቶ የኖረበት ጥበባዊ ሕይወት ደግሞ ትልቁን ድርሻ ይወስዳል፡፡ ግጥም፣ ሙዚቃ ፎቶግሪፊ የሚደሰትባቸው ተስጥኦዎቹ ናቸው፡፡

ኪነ ጥበቡ የሚያድገው ለዘርፉ ትኩረት ሲሰጥ ነው የሚለው ያሬድ፣ እሱን ከመሰሉ ጓደኞቹ ጋር በኪነ ጥበቡ ለውጥ ለማምጣት የሚያደርጉት ጥረት ያስደስተዋል፡፡ ከአዲስ አበባ ውጪ ባሉ የክልል ከተሞች እየተዘዋወሩ ሥራዎቻቸውን የማቅረብና በየከተማው ተሰጥኦ ያላቸውን የማውጣት እቅድ አላቸው፡፡

ልጅ ያሬድ ‹‹ጥበብ ሕይወቴ ነው፤ ጥበብ ከሌለ እኔ የለሁም ማለት ነው፤›› በማለት ለጥበብ ያለውን ፍቅር ይገልጻል፡፡ ወጣቶች ራሳቸውን ፈልገው እንዲያገኙና የአገራቸውን እሴት አጥብቀው እንዲይዙም ያሳስባል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

አስጨናቂው የኑሮ ውድነት ወዴት እያመራ ነው?

ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ የኑሮ ውድነት እንደ አገር ከባድ ፈተና...

‹‹ወላድ ላማቸውን አርደው ከደኸዩት ወንድማማቾች›› ሁሉም ይማር

በንጉሥ ወዳጅነው   የዕለቱን ጽሑፍ በአንድ አንጋፋ አባት ወግ ልጀምር፡፡ ‹‹የአንድ...

የመጋቢቱ ለውጥና ፈተናዎቹ

በታደሰ ሻንቆ ሀ) ችኩሎችና ገታሮች፣ መፈናቀልና ሞትን ያነገሡበት ጊዜ እላይ ...

ጥራት ያለው አገልግሎት መስጠት የሚያስችል ሥርዓት ሳይዘረጉ አገልግሎት ለመስጠት መነሳት ስህተት ነው!

በተለያዩ የመንግሥትና የግል ተቋማት ውስጥ ተገልጋዮች በከፈሉት ልክ የሚፈልጉትን...