Tuesday, February 27, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

ጩኸት እንደ ሙዚቃ!

ሰላም! ሰላም! የቡና ሰዓት ደርሶ ማንጠግቦሽ በማንከሽከሻዋ ቡና ትቆላለች። ጎረቤት ተሰብስቧል። ‘ፌስቡክ’ እየተጋፋን ብንራራቅም፣ ፈጣሪ ይመስገነው ቡና ላይ ያለ ‘ሪኩዌስት’ እንሰባሰባለን። ልዩነቱ ታዲያ ፊት ለፊት ስንገናኝና ሳንተያይ ስናወራ አንድ አለመሆናችን ነው። አደራችሁን የምናገረው በተቃርኖ ስለተሞላው የግል ባህሪያችን ስለሆነ፣ ብዝኃነትን ጨፈለቀ እንዳትሉኝ። ሆሆ. . . ምን ይታወቃል የነገር መምጫው ብዬ እኮ ነው!  በውሸት ፈገግታ አሽሞንሙነን፣ ‘ሆድ ይፍጀው’ ብለን የምንቀብረውን ትዝብት እስኪ ‘ፌስቡክ’ ላይ ታዘቡት። ፓ! ስም ሐበሻ ያውጣ። ‹ልብቡክ› ነበር እኮ መባል የነበረበት! ፌሳችንማ መቼ ያስነቃና!

 ታዲያማ በገሃድ በመመሳሰል ፍልስፍና ስንታሽ እንውልና በዘመን አመጣሹ ‘የልብ መጸሐፍ’  ያበጠውን ስናፈነዳ እንውላለን። ያበጠ ማፈንዳትና ቦምብ ማፈንዳት ግን ይለያያል እሺ። አንዳንዱ ያበጠ አፈነዳሁ ባይ ይኼ የገባው አይመስለኝም። እንዲያው እኮ! ባሻዬን እዚያ የቡና ‘ሴሬሞኒ’ ላይ እንዲህ ስላቸው፣ “ምን ታደርገዋለህ? አንዳንዱ እኮ እሱ ብቻ ዓይን ያለው ይመስለዋል። እሱ ብቻ አፍ ያለው ይመስለዋል። እሱ ብቻ አዋቂ የሆነም አለ በእሱ ቤት። ለነገሩ እኛም በዕውቀትና በአዋቂ መሀል ያለውን ልዩነት በቅጡ አልረዳ ብለን የሙሴን በትር ጨብጫለሁ ያለንን ሁሉ መከተል ልማድ አድርገነዋል፤” ሲሉኝ ነበር።

ባሻዬ ሥጋታቸውን ሲቀጥሉ፣ “ይኼ ‘ፌስቡክ’ የምትሉት ነገር አንዳንዴ ሳስበው. . . ትንሽ ከቆየ፣ ከመሠረታዊ ፍላጎቶቻችን አንዱ እንዳይሆን ያሠጋኛል። አስበው እስኪ ነገ፣ ‘በምግብና በመኖሪያ ቤት ዋስትና ራሳችንን ችለናል/አልቻልንም’ እያልን እንደምንጨቃጨቀው፣ ‘የፌስቡክ አካውንት ባለቤትነት አልተዳረሰም/ተዳርሷል ስንባባል?” ሲሉኝ ነበር። አንዳንዴ የባሻዬ ‘ኢማጅኔሽን’ ያስደንቀኛል። ልጃቸው “ከዕውቀት ምናብ ይበልጣል” ብሎ ስለተናገረው ሳይንቲስት የነገረኝን እያውጠነጠንኩ የሚመጣውን ለማየት ተጨባጭና ተዳሳሽ ሁኔታ ብቻውን ዋጋ እንደማይኖረው ደላላ ብሆን እንኳን አስባለሁ። ማንጠግቦሽ አቦል ቀድታ ስትሰጠኝ ደግሞ በሥልጣኔና በዕድገት ስም እያደር ያጣሁት የአብሮ መብላትና የመጠጣት ባህል በሩቅ ለሩቅ ‘ቻትና ላይክ’ ሲቀየር ስላስተዋልኩ፣ ካጣሁት የበለጠ ወደፊት አጣዋለሁ ብዬ የምሠጋው ማኅበራዊ መስተጋብር ያጨልመኛል። ማን ነው ነበር ‘ካደረግነው ይልቅ ያላረግነው ባሰን’ ብሎ የዘፈነ ድምፃዊ?

ቡናዬን ላፍ ላፍ አርጌ ጀማው ሲበተን ካልተሠራ አይበላምና ወጥቼ መብከንከኔን ተያያዝኩት። ለነገሩ ሳይሠሩ መብላት እንደሚቻልም እያየን ነው። ይህቺ ቅድመ ቅጥያና ድኅረ ቅጥያ የሌላት ‘ይቻላል’ የሚሏት መፈክር ጉድ ሳትሠራን አልቀረችም። አንዳንዴ ግልጽ ያልሆነ አስተሳሰብና መፈክር እኮ ጥሩ አይደለም። እንዴት ነው? የዋጋ ዝርዝር የሌለው የምግብ ዝርዝር አይታችሁ ታውቃላችሁ? ድግስ ካልሆነ በቀር መቼም አታዩም። ይህቺ ‘ይቻላል’ የሚሏት መፈክርም እንዲያ ነው የምትመስለኝ። ተፈጥሯችን ሆኖ ደግሞ ቀኝና ግራ የሌለው ፎካሪና መፈክር ይመቸናል። ዋሸሁ? ‘ሆ በል!’ ሲሉን ‘ሆ’ አላልንም? ‘እናሸንፋለን’ ሲሉን አልተከተልንም? ‘እናቸንፋለን’ ሲሉንስ አልተካፈልንም? የሞት መዝሙር ሲያዘምሩን ሕይወት ላይ ጀርባችንን ሰጥተን ‘የጫማ ቁጥሬን አንብቢ’ አላልንም? ትናንት ክሰሉ ሲሉን ከከሰልን፣ እርገፉ ሲሉን ከረገፍን ዛሬ ማብራሪያ የሌላት መፈክር ሲሰጡን ለማብራራት የሚከብድ የአኗኗር ዘይቤ ብንቀይስ ምን አጠፋን ታዲያ?

ስለዚህ. . . (ስለዚህ ይላሉ ባሻዬ . . . ሰው እንጂ ነገር ረግጦ የሚያስረግጥ ሰው በመነመነበት ዘመን ነገር ሲያስረግጡ) ‘ማጭበርበር ይቻላል! መግፋት ይቻላል! መወስለት ይቻላል! መፋታት ይቻላል! መበዝበዝ ይቻላል!’ ወዘተ በሚሉ አፍራሽ መፈክሮች ውስጥ ውስጡን ብንዛባ ምን ይገርማል? ‘ለምን? ለማን? እንዴት? ወዴት?’ ሳናውቅ ‘የማይቻል ነገር የለም’ ተባብሎ ተስማምቶ እግዚኦ ምንድነው? በአራዳዎቹ ቋንቋ ‘መላ ለመምታት’ (በቀላሉ ብዙ ሳይለፉ የሚገኝ ገንዘብ ብለው ይገልጹታል) በየሄድንበት በሰው ተቀማጭ ሒሳብ ስንጣላ ብንውል አይቻልም? የሚቻለው ሳይነገረን በየት በኩል የማይቻለውን እንወቅ? ምን ዝም ትሉኛላችሁ? ባይሆን ለጥያቄ እንተጋገዝ እንጂ ጎበዝ!

ለነገሩ ለጥያቄም የምንሰንፈው ወደን ነው። ፈር መሳት እንጂ አቅጣጫ መያዝ ይጎረብጠናልና። ቀስት የምንፈልገው መፀዳጃ ቤት ሲጠቁመን ብቻ ሳይሆን አይቀርም። እውነቴን እኮ ነው። እሱንም ያው  የተፈጥሮ ግዴታ ሆኖ እንጂ ሳይንስ እንዲህ መጥቆ ማስተከል፣ ማስነቀል፣ ማጣመም፣ ማቃናት ተራ በሆነበት በዚህ ጊዜ ቢቻል ኖሮ የደረቅና የፈሳሽ ቆሻሻ ማጠራቀሚያ ከረጢቶቻችንን ከማሳሸግ ወደኋላ አንልም ብዬ እገምታለሁ። ከማፍረስና ከማሸግ ብቻ ልማት የሚጠብቁ በዝተዋላ! አንዱ “የመንደሬ ነዋሪ በመፀዳጃ ቤት እጥረት ተሰቃየ፤” ብሎ ‘ኢንቨስት’ ቢያደርግ ‘ሕገወጥ ግንባታ ገነባህ’ ተብሎ ‘አፍርስ!’ አሉት አሉ። “እሺ አፈርሳለሁ። ከማፍረሴ በፊት ግን በ‘ሰርጀሪ’ አፍንጫዬን ለማስደፈን የማወጣውን ወጪ መንግሥት ይቻለኝ፤” ብሎ መለሰ። ‘ግብረ ኃይል እያለ የምን ‘ሰርጀሪ?’ ብለው ከአፍንጫው ጀምረው ይሆን? ሃሃሃ . . .  ተውኝ አትነካኩኝ አለ ሰውዬው!

እንዲያው እኮ? ታዲያ ከባሻዬ ልጅ ጋር እንዲህ ስናወራ ያልኳችሁን ብነግረው፣ “እመነኝ ሆዳችንን ግን አናስቆልፍም። በምንም ተዓምር፤” ነበር ያለኝ። “ከተን ከተን ምን ልሆን ነው?” ስለው፣ “እሱን ሂድና ከአካባቾች አጥና” ብሎ ጥሎኝ ሄደ። ይኼን ጊዜ አንድ በሩቅ የማውቀው ሰው የተናገራት ነገር ትዝ አለችኝ። “ከአፍሪካውያን መደበቅ የምትሻውን ነገር መጽሐፍ ውስጥ አስቀምጠው፤” በሚል አባባል መነሻ ጨዋታ ጀምረን ስለሆዳችን ስናነሳ፣ “መጸሐፍ ምግብ ቢሆን ኖሮ ግን የሚተርፈን አይኖርም ነበር፤” ሲል ኮመከ። ለቅፅበት ከት ብዬ ስቄ፣ “አይደለም እንዴ?” ስለው ምን ቢለኝ ጥሩ ነው? “የለም ለእኛስ ሐሜትና ወሬ ጫፍም አይደርስ፤” ብሎ መለሰልኝ። በአንድ በኩል በልተን ለማማጥ እየተባላን፣ በሌላ በኩል በባዶ ጭንቅላት በድርቀት መሰቃየት መምረጣችን ምክንያቱ አይገባም። እስኪ የገባችሁ  ‘ፖስት’ አድርጉ። ወይ ቡና ላይ ተወያዩ!

ውሎ አድሮ ምን አጋጠመኝ መሰላችሁ? ባይውልም ባያድርም ለነገሩ ሕይወት በገጠመኝ የተሞላች ነች። አንድ ‘ኮሮላ’ አሻሽጬና አንድ ስቱዲዮ ኮንዶሚኒየም ቤት አከራይቼ፣ ደግሞ ወደሌላ ዘወር ከማለቴ ስልክ ተደወለልኝ። ከሳምንታት በፊት ፋብሪካ ሊተክል ወደ አገሩ የመጣ ዳያስፖራ ደንበኛዬ ነው። ከዚህ ቀደም ጠቀም ያለ ‘ኮሚሽን’ ከዚህ ሰው ስላገኘሁ ደግሞ ምን ፈለገ ብዬ ስልኩን ሳነሳው፣ “እባክህ ቶሎ ድረስ” ብሎ ተማጠነኝ። ድምፁ ብሶትም ንዴትም ይተፋል። ስከንፍ ሄድኩ። አግኝቼው የሆነውን ሲነግረኝ ማመን አቃተኝ። እያሽከረከረ ሳለ ሁለት የትራፊክ ፖሊሶች ያስቆሙታል። መንጃ ፈቃድ ሲጠይቁት የኖረበትን አገር መንጃ ፈቃድ አውጥቶ ያሳያቸዋል። ፓስፖርቱን ይጠይቁታል። ከማሽከርከሪያ ፈቃድና ከተሽከርካሪ ጋር በተገናኘ ብቻ ማንኛውም የትራፊክ ፖሊስ ያሻውን ሊጠይቅ እንደሚገባ እያወቀ ግራ ገብቶት ያሳያቸዋል።

“በዚህ ማሽከርከር የሚቻልበት ጊዜ አልፏል። መኪናውም አንተም ትታሰራላችሁ፤” ይባላል። “የምቀጣውን እቀጣለሁ እስከዚያ መኪናው ይታሰራል እንጂ እኔ ለምን እታሰራለሁ?” ሲላቸው (እንደ ነገረኝ) አንደኛው፣ “እሱን አሳየሃለሁ። ለዚህ ትዕቢትህ እንዲያውም እኔ በግሌ ሦስት ቀን ጨለማ ክፍል አሽግሃለሁ፤” ብሎ ደነፋ። እስኪበቃው አዋክበው በገዛ መኪናው ያለፈቃዱ ገብተው አንከውክወው ትራፊክ ጽሕፈት  ቤት ሲወስዱት የበላያቸው ተገርሞ፣ “ሕግ እኮ ማስተማሪ እንጂ ማንገላቻ አይደለም፤” ይልና ቅር ያለው ነገር ካለ እንዲያመለክት አደፋፍሮ ቅጣቱን ከፍሎ እንዲመለስ ሲልከው፣ ለዕለት ወጪው መድቦ በማንገቻ ቦርሳው የያዘው ገንዘብ የለም። “እና አሁን የጠራሁህ ባዶ ኪሴን ሆኜ ነው” አለኝ። “የጠፋው ገንዘብ ካወናበዱኝ ትራፊክ ፖሊሶች ኪስ ውጪ አይደለም፤” ብሎ ሊፋረድ ወደ ክስ ሲጓዝ ያለኝን አራግፌ ሰጥቼው ወደ ሥራዬ ተመለስኩ። አንዱ ሲክብ አንዱ እየናደ አንዱ ሲያጥር አንዱ እያፈረሰ ስደት ሰበብ የሚያጣው መቼ ይሆን ግን? ከኑግ ጋር የተገኘ ሰለጢስ አብሮ እየተወቀጠ ሕግ ይከበራል ብሎ እንዴት ተስፋ ይጣላል? ግምገማና ስብሰባስ እንክርዳዱን ካላጠራ ጊዜ ብቻ እያጠፋ እንዴት ይገፋል? ኧረ የወንፊት ያለህ?

 በሉ እንሰነባበት። ‘ዋን ዋን’ እንበል ተባብለን እኔና የባሻዬ ልጅ የሰርክ መቃጠሪያችን ወደሆነችው ግሮሰሪያችን አመራን። ከወትሮው የተለየ ምሳጤና ድባብ ግሮሰሪያችንን  ሰቅዞ ይዟታል፡፡ ሁሉም ‘ሞባይል’ ስልኩን ይዞ እንደፀናፅል ያንሿሿል። ዞር ስል ኮሽ-ኮሽ-ኮሽ ይላል። ዞር ስል ይንሿሿል። የማንጠግቦዝ ማንከሽከሻ ትዝ ብሎኝ፣ “ደግሞ ተብሎ ተብሎ በ‘ኢንተርኔት’ ቡና መቁላት ተጀመረ?” ስለው የባሻዬ ልጅ ሳቅ ብሎ “የሆነ ‘አፕሊኬሽ’ ነው፤” አለኝ። “ምንድነው እሱ?” ስለው፣ “ስልክህ ላይ የሚጫን ‘ሶፍትዌር’ ነው። ትከፍተውና ነቅነቅ ስታደርገው አንተ ካላህበት ሥፍራ በቅርብ ርቀት ላይ  የሚገኙ ባል ወይ ሚስት ፈላጊዎችን ያመጣልሃል፤” አይለኝ መሰላችሁ? ማመን አቅቶኝ ደጋግሜ ኳኳታውን ሳዳምጥ ከቆየሁ በኋላ፣ “ታዲያ ከዚህ ሁሉ ሰው አንድ የሚገናኝ ጠፍቶ ነው ሁሉም እየደጋገመ የሚያንሿሿው?” ብዬ ብጠይቀው “እሱ የምርጫ ጉዳይ ነው። አማራጭህ ብዙ ሲሆን አማራጭህ ሲጠብ ከምትቆጠበው በላይ ድምፅ ከመስጠት ትቆጠባለህ፤” ብሎ አስረዳኝ።

“እንዲያ ነው ነገሩ?” እያልኩ የሙዚቃውን ድምፅ ሿሿታው አሸንፎት ስጎነጭ እንደቆየሁ ትናንሽ ልጆች ሆያ ሆዬ እየጨፈሩ ተንጋግተው ገቡ። ‘የእኔማ እንትና ባለአይፎን ሲክስ’ ቢሉ ‘ባለመኪና’  ቢሉ ‘ባለሕንፃ’ ቢሉ ማን ሰምቷቸው? ሁሉም የሚያጠምደው ላይ አሰፍስፎ የሚሰማቸውም የሚያያቸውም አጥተው “ኧረ በቃ በቃ ጉሮሯችን ነቃ” እያለ አዝነው ሲሄዱ ቅስሜ ተሰበረ። ትውልዱ ባህሉን ረሳ ለማለት፣ መንግሥት ላይ ሁሉን ነገር ለመደፍደፍና ስህተት ብቻ ለመንቀስ አንደኞች ሆነን ያሰብነው ሲሆንና የምንፈልገው ሲሳካ ስናይ የያዝነውን ጥለን የማንደሰት የማናጨበጭብበት ምክንያት ምን እየሆን ነው፡፡ እናንተ? ዘለዓለም ትችት፣ ዘለዓለም ወቀሳ ብቻ?! አውጥቼ አውርጄ ስለደከመኝ እኔም በፈንታዬ “ኧረ በቃ! በቃ! ጉሮሮዬ ነቃ!” ብዬ ልጮህ አሰብኩና ተውኩት፡፡ ጩኸት እንደ ሙዚቃ በሚሰማበት ዘመን እስክታ እንውረድብህ ብባልስ? መልካም ሰንበት!     

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት