መካኒሳ አካባቢ ባቱ ኮንስትራክሽን በመባል የሚታወቀው ሠፈር መግቢያ ላይ ያለ ያረጀ አስፋልት ነው፡፡ አስፋልቱ ብዙ ርቀት የሚወስድ አይደለም፡፡ ከጥቂት ሜትሮች በኋላ መንገዱ የጭቃ ይሆናል፡፡ እግረኞች በመንገዱ ሲተላለፉ ጭቃው እንዳያዳልጣቸው ከዛም አልፎ መሬቱ ያቆረው የዝናብ ውኃ ውስጥ እንዳይገቡ ተጠንቅቀው ነው፡፡ ይኸው መንገድ መኪኖችንም የሚያላውስ አይደለም፡፡
መንገዱ ክረምት ላይ በዝናብ በበጋ ደግሞ በፍሳሽ እንደሚጥለቀለቅ የአካባቢው ነዋሪዎች ይናገራሉ፡፡ በተለይ በክረምት ወቅት ኃይለኛ ዝናብ ሲዘንብ ጎርፍ ወደ መኖሪያ ቤታቸው ሰተት ብሎ ይገባል፡፡ ነዋሪዎቹ የውስጥ ለውስጥ መንገዱ እንዲሠራላቸው ለአካባቢው አስተዳደር አቤት ቢሉም ምላሹ እንደዘገየባቸው ይናገራሉ፡፡
ከነዋሪዎቹ አንዱ አቶ ሸምሱ ሀሰን ጎርፍ በተደጋጋሚ ቤታቸው እንደገባ ይናገራሉ፡፡ አቶ ሸምሱ የሚተዳደሩት ግቢያቸው በራፍ ላይ በከፈቱት ዳቦ ቤት ነው፡፡ እሳቸውና ቤተሰቦቻቸው ክረምት በመጣ ቁጥር ይሳቀቃሉ፡፡ በአንድ ወቅት ኃይለኛ ዝናብ ይጥልና ግቢያቸው በጎርፍ ይሞላል፡፡ በግቢው መግቢያ ላይ የነበረው ዳቦ ቤታቸው ውስጥ የነበረው ፉርኖ ዱቄት እንዲሁም በሱቁ ያስቀመጡት ገንዘብ ሳይቀር በውኃ ይዋጣል፡፡ የአካባቢው ነዋሪዎች ተረባርበው ጎርፉ የሚወርድበትን መንገድ ቢቀይሱም ዘላቂ መፍትሔ አልሆነም፡፡
እሳቸው እንደሚሉት፣ ፍሳሽ የሚወርድበት ቱቦ በባለሙያ መሠራት አለበት፡፡ ለዚህም የአካባቢው ነዋሪዎች ተሰባስበው መንገድ አሠሪ ኮሚቴ አዋቅረዋል፡፡ ኮሚቴው የነዋሪዎቹን እሮሮ ለሚመለከተው አካል አሰምቶ መንገድ እንዲሠራላቸው ቢጠይቁም እስካሁን (አምስት ዓመት ያህል) አጥጋቢ ምላሽ አላገኙም፡፡
‹‹መንገዱ ባለመሠራቱ ፍሳሽ መውረድ አልቻለም፤ ውኃው እንዲወርድ ለማድረግ ቢሞከርም አልተቻለም፤ ሥራ መሥራት መኖርም አልቻልንም፤›› ይላሉ፡፡ በበጋ ከሌላ አካባቢ የሚወርድ ፍሳሽ ከእሳቸው ደጃፍ ሲተኛ የቆሻሻ ሽታ አላስወጣ አላስገባ እንደሚላቸው ይናገራሉ፡፡ ክረምት ላይ ዝናብ ቆሻሻውን ጠራርጎ ሽታው ቢጠፋም ጎርፍ የበለጠ ያሠጋቸዋል፡፡
በሠፈራቸው የውስጥ ለውስጥ መንገድ አለመዘርጋቱ ከዕለት ዕለት ኑሯቸው ባሻገር በአካባቢው ያለውን ገበያ እንደሚያቀዘቅዝም ይናገራሉ፡፡ በእርግጥ ብዙ አካባቢዎች በነዋሪዎችና የየአካባቢው አስተዳደር ኅብረት የውስጥ ለውስጥ መንገዳቸው ኮብልስቶን ወይም ጠጠር ተነጥፎበት ይስተዋላል፡፡ እዛው መካኒሳ አካባቢ ካሉ የግል ቤቶችና ኮንዶሚኒየሞች መካከል መንገድ የተሠራላቸው ቢኖሩም ዝርጋታው ሁሉንም አካባቢዎች ያዳረሰ አይደለም፡፡
በአካባቢው ወደ አሥር ዓመት ያህል የኖሩትና የመንገድ አሠሪ ኮሚቴው አስተባባሪ አቶ ግርማ ባህሩ የአካባቢው ነዋሪዎች በተደጋጋሚ ያቀረቡት ጥያቄ ምላሽ አለማግኘቱን ያስረዳሉ፡፡ በየዓመቱ ክረምት ላይ ቤታቸው በጎርፍ የሚጥለቀለቅባቸው ነዋሪዎች ጥቂት አይደሉም፡፡ እሳቸውም እንደ አቶ ሸምሱ መፍትሔ የሚሆነው ውኃ ውስጥ ለውስጥ የሚፈስበት መንገድ ሲቀየስ ብቻ ነው ይላሉ፡፡
ከመንገድ ሥራው መዘግየት ጋር በተያያዘ በየዓመቱ በአካባቢው የሚከሰቱ አጋጣሚዎች ብዙ እንደሆኑ አቶ ግርማ ይናገራሉ፡፡ እንደሁልጊዜው አንድ ክረምት ላይ የሰባት ዓመት ልጅ በጎርፍ ይወሰዳል፡፡ ጎርፉ ሕፃኑን ይዞ ጥቂት ሜትሮች ከተጓዘ በኋላ ነዋሪዎች ተረባርበው አውጥተውት ሕይወቱ ተርፏል፡፡ ያ አጋጣሚ ለነዋሪዎቹ ያሉበትን የአደጋ መጠን ያሳያቸው አስደንጋጭ ዕለት ነበር፡፡
‹‹መንገዱን ለመሥራት አቅም ያለው አካል ችላ ብሎታል፤›› የሚሉት አቶ ግርማ፣ በበጋም ቢሆን አቧራና የውኃ ፍሳሽ እንደሚያስቸግራቸው በመግለጽ ነው፡፡ የባቱ ኮንስትራክሽን አካባቢ ነዋሪዎች በጣም የሚያሠጋቸው አካባቢው ለወባ ተጋላጭ መሆኑ ነው፡፡ ለረዥም ጊዜ መንገዱ ላይ ውኃ ረግቶ ሲቆይ አልጌ እንደሚሠራና የነዋሪዎች ጤና አደጋ ውስጥ መውደቁን ይናገራሉ፡፡
ነዋሪዎቹ ለመንገድ ሥራው አስፈላጊ የሆነውን ወጪ ለማሟላት ፈቃደኛ ቢሆኑም ከአካባቢው አመራሮች አፋጣኝ ምላሽ አለማግኘታቸው አጣብቂኝ ውስጥ እንደከተታቸው ያስረዳሉ፡፡ የአካባቢው ነዋሪዎች ተነሳሽነት እስካሳዩ ድረስ የሚመለከታቸው አካላት ኃላፊነታቸውን ሊወጡ ይገባል ሲሉ ያሳስባሉ፡፡
በቅርቡ ወደ አካባቢው የገቡት አቶ ቴዎድሮስ አብርሃ ‹‹ከከተማ በወጡ አካባቢዎች እንኳን መንገድ ሲሠራ በከተማው እምብርት እንዲህ ያለ መንገድ መኖሩ ያሳፍራል፤›› ይላሉ፡፡ መንገዱ የሚያስተናግደው ሕዝብና መኪና የትየለሌ ሆኖ ሳለ ሥራው መጓተቱ አጠያያቂ ነው ይላሉ፡፡
አቶ ቴዎድሮስ ለአካባቢው ነዋሪዎች ለጊዜውም ቢሆን መፍትሔ ይሆናል ብለው መንገዱን አምስት ቢያጆ አፈር አልብሰዋል፡፡ አፈሩ ዝናብ ያቆረበትን መንገድ ለጊዜው ቢደፍነውም ዘላቂ አይደለም፡፡ አንዳንድ ነዋሪች ደግሞ ውኃ ወደግቢያቸው እንዳይገባ በሲሚንቶ መዝጊያ ቢያበጁም ለውጥ አላመጣም፡፡
በጉዳዩ ዙሪያ ያነጋገርናቸው የንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ የፋይናንስና ኅብረተሰብ ጉዳዮች ኦፊሰር አቶ መልካሙ አሰፋ እንደሚናገሩት፣ የባቱ ኮንስትራክሽን አካባቢ ነዋሪዎች መንገድ እንዲሠራላቸው ጥያቄ ቢያቀርቡም ያላሟሏቸው ቅድመ ሁኔታዎች አሉ፡፡ ኃላፊው እንደሚናገሩት፣ የአካባቢው ነዋሪዎች ፍላጎታቸውን የሚገልጽ ቃለ ጉባዔ ጽፈውና መስማማታቸውን በፊርማቸው አስታውቀው ለመስተዳድሩ ማሳወቅ አለባቸው፡፡ በክረምት ገንዘብ ማሰባሰብ እንጂ የመንገድ ግንባታ ስለማይኖር በ2008 ዓ.ም. እንዲጀመር በዚህ ዓመት ቅድመ ሁኔታዎችን መፈጸም አለባቸው ይላሉ፡፡
አቶ መልካሙ እንደሚሉት፣ በዛው ክፍለ ከተማ በቀጣና የተከፋፈሉ ወደ 38 የሚደርሱ ማኅበሮች አሉ፡፡ ኮሚቴ አዋቅረውና ገንዘብ አዋጥተው ከመስተዳድሩ በሚደረግላቸው ድጋፍ መንገድ በማሠራት ላይ ያሉ፣ ያጠናቀቁም ይገኙበታል፡፡ ‹‹በእኛ በኩል የሚያስፈልገውን እገዛ ለማድረግ ኅብረተሰቡ ቅድመ ሁኔታዎችን ማሟላት አለበት፡፡ ለመንገድ መሥሪያ የሚያስፈልገውን 70 በመቶ ገንዘብ ካሰባሰቡ በኋላ እኛ 30 በመቶውን እንሸፍናለን፤›› ይላሉ፡፡ የመንገድ ሥራው በአግባቡ መካሄዱን የሚከታተል አካል ከነዋሪዎቹ ኮሚቴና ከመስተዳድሩ እንደሚውጣጣም ይገልጻሉ፡፡ አቶ መልካሙ የአካባቢው ነዋሪዎች ከማመልከት በዘለለ ምንም እንዳላደረጉ ቢናገሩም፣ ያነጋገርናቸው ነዋሪዎች ጥረታቸው ችላ መባሉን ይገልጻሉ፡፡
እንደ ባቱ ኮንስትራክሽን አካባቢ ሁሉ የውስጥ ለውስጥ መንገድ ያላገኙ ሠፈሮች ቢኖሩም፣ አግኝተው በመንገድ መበላሸት የሚቸገሩም አሉ፡፡ ገርጂ የሚገኘውና ሰላም ሠፈር በሚባል የሚታወቀው አካባቢ ተጠቃሽ ነው፡፡ ከነዋሪዎቹ የተውጣጡ ግለሰቦች ኮሚቴ አዋቅረው፣ ገንዘብ ተሰባስቦና ጨረታ ወጥቶ ኮብልስቶን ቢነጠፍም መንገዱ ሲሠራ ፍሳሽ ማስወገጃ አልተበጀለትም፡፡ በተለይ በቤቶች ጥጋ ጥግ ላይ ኮብልስቶኑ ተነቃቅሎም ይታያል፡፡
አቶ ዓለም ተስፋዬ በአካባቢው ለ20 ዓመታት ኖረዋል፡፡ በ2002 ዓ.ም. ነዋሪዎች ተሰባስበው መንገድ ሥራው መጀመሩን ያስታውሳሉ፡፡ ‹‹መንገዱ በ2004 ዓ.ም. ቢጠናቀቅም፣ ጥራቱን የጠበቀ ባለመሆኑና የፍሳሽ መውጫ ባለመኖሩ ቤታችን በየዓመቱ በጎርፍ ይጥለቀለቃል፤›› ይላሉ፡፡ አቤቱታቸውን ለቦሌ ክፍለ ከተማ መስተዳደር በተደጋጋሚ ቢያስታውቁም መፍትሔ እንዳላገኙ ያስረዳሉ፡፡
‹‹ገንዘባችንን ከፍለን ስናሠራ ኃላፊነቱንም እየሰጠን ነው፤ ሥራው በጥራት መሠራት አለበት፤ ቅሬታ ካለንም በአግባቡ መስተናገድ አለብን፤›› ይላሉ አቶ ዓለም፡፡ ችግራቸውን በፎቶግራፍና በቪዲዮ በተደገፈ መረጃ ቢያቀርቡም አንዱ አካል ወደ ሌላው እየመራቸው እንደሆነ ይናገራሉ፡፡
ጎርፍ ቤታቸው በገባበት ወቅት ከቤት ቁሳቁስ በተጨማሪ በርካታ ሰነዶች እንደተበላሹባቸው ይናገራሉ፡፡ መንገዱን የሚያሠሩትን የኮሚቴ አባላትና የወረዳውን መስተዳደር ቦታው ድረስ ወስደው ችግሩን እንዳሳዩዋቸው ይገልጻሉ፡፡ መፍትሔ አለመገኘቱ ክረምት በመጣ ቁጥር በፍርኃት እንዲዋጡ አስገድዷቸዋል፡፡
የዛው አካባቢ ነዋሪ ወ/ሮ ሙሉ ፀጋዬ ተመሳሳይ አስተያየት ሰጥተውናል፡፡ ኮብልስቶን ለማንጠፍ ገንዘብ ሲሰባሰብ ሳዐውዲ ዓረቢያ የነበሩ ቢሆንም ካሉበት ገንዘብ ልከው አዋጥተዋል፡፡ ወደ አገራቸው ተመልሰው ከሦስት ልጆቻቸው ጋር መኖር የጀመሩት መንገዱ ከተጠናቀቀ በኋላ ነበር፡፡ ኮብልስቶኑ ወደእሳቸው ቤት ያጋደለ መሆኑ ቢያሠጋቸውም የጎላ ችግር እንደሚፈጠር አልገመቱም ነበር፡፡
አንድ ምሽት ኃይለኛ ዝናብ ሲጥል ቤታቸው ውስጥ ጎርፍ ይገባል፡፡ ልጆቻቸውን ከቤታቸው ይዘው ወጥተው ሆቴል ከማደር ውጭ አማራጭ አልነበራቸውም፡፡ በጎርፍ ሲቸገሩ መንገዱ ሲሠራ የተደፈነውን የውኃ መውጫ ድንጋይ ፈንቅለው ለመክፈት ተገደዋል፡፡ በተጨማሪም ጎርፍ ወደ ቤታቸው እንዳይገባ የቤታቸውን መግቢያ ከቀደመው ከፍ እንዲል ቢሲሚንቶ አስለስነዋል፡፡ የውኃው መጠን ቢቀንስም ሙሉ በሙሉ መከላከል አልተቻለም፡፡ ወ/ሮ ሙሉ እንደሚናገሩት፣ በቀላሉ መስተካከል የሚችል መንገድ ብዙ ወጪ እያስወጣቸው ነው፡፡
የአዲስ አበባ ዋና ዋና ጎዳናዎች እንዲሁም የውስጥ ለውስጥ መንገዶች ዝርጋታ ከጊዜ ወደ ጊዜ ቢስፋፋም ብዙዎች በመንገድ ዝርጋታ ቅድሚያ የሚሰጠው ለየትኞቹ አካባቢዎች ነው? ሲሉ ይጠይቃሉ፡፡ መንገድ ከተሠራ በኋላ ቅሬታ ሲኖርስ የሚያስተናግደው አካል የሚሰጠው ምላሽ ምን ያህል አፋጣኝ ነው? የሚል ጥያቄም ይነሳል፡፡ ከመሠረተ ልማቶች አንዱና አስፈላጊ የሆነው የመንገድ ዝርጋታ እንደ አቶ ሁሴንና አቶ ዓለም መኖሪያ ላሉ አካባቢዎች የሥጋት መንስኤ ሆኗል፡፡
የአዲስ አበባ መንገዶች ባለሥልጣን ዋና ሥራ አስኪያጅ ኢ/ር ፈቃደ ኃይሌ እንደሚናገሩት፣ የአንድ አካባቢ ነዋሪዎች በሚያቀርቡት ጥያቄ መሠረት ከሚሠሩ የውስጥ ለውስጥ መንገዶች በተጨማሪ ባለሥልጣን መሥሪያ ቤቱ ኃላፊነት ወስዶ የሚያሠራው መንዶች አሉ፡፡ ከአሥር ሜርት በታች የሆኑ መንገዶችን በጥምረት ይሠራሉ፡፡ የኅብረተሰብ ተሳትፎ ኤጀንሲዎች በየወረዳው ያሉ ነዋሪዎችን አሰባስበው የመንገድ ግንባታው የደረሰበትን እንቅስቃሴ ለባለሥልጣኑ ያሳውቃል፡፡
ኢ/ር ፈቃደን መንገድ እንዲሠራላቸው ጠይቀው በቶሎ ምላሽ ስለማያገኙ አካባቢዎች ጠይቀናቸው ነበር፡፡ እሳቸው እንደሚሉት፣ አንድ መንገድ የሚወስደው ጊዜ ከሌላው የተለየ ሲሆን፣ እስከ አራት ዓመት ከዛም በታች የሚፈጁም አሉ፡፡ ‹‹ባለሥልጣኑ ከውስጥ ለውስጥ መንገዶች ውጪ ሰፋፊ መንገዶችን ሌሎችንም በየቅደም ተከተላቸው ይሠራል፤ ሥራው የሚዘገየው ካለው ብዛት አኳያ ነው፤›› ይላሉ፡፡
ሌላው ተያያዥ ጉዳይ የውስጥ ለውስጥ መንገዶች ሲሠሩ ደረጃቸውን የጠበቁ የማድረግ ጉዳይ ነው፡፡ እንደ ሥራ አስኪያጁ ገለጻ፣ መንገዱን የሚያሠራው አካል ክትትል ማድረግ ይጠበቅበታል፡፡ ባለሥልጣን መሥሪያ ቤቱ እንደ መስፈርት ያስቀመጠው የመንገዶቹ የፍሳሽና ሌሎችም አስፈላጊ ነገሮች የተሟሉለት መሆን እንዳለበት ነው፡፡ መንገዶች ከተሠሩ በኋላ ተፈትሸው መቅረብ እንዳለባቸውም ያክላሉ ይላሉ፡፡ ከመንገዱ ጋር በተያያዘ የሚነሱ ቅሬታዎች ቢኖሩም አሠሪው ያስተካክላል፡፡
እስካሁን አዲስ አበባ ውስጥ በ113 ወረዳዎች ከ1,300 ኪሎ ሜትር በላይ የውስጥ ለውስጥ መንገድ ተሠርቷል፡፡ ከ1,120 ኪሎ ሜትር በላይ የጠጠር መንገድ ተሠርቷል፡፡ የውስጥ ለውስጥ መንገድ ጥያቄ ሲቀርብ መጀመርያ በጠጠር ተሠርቶ ማኅበረሰቡ ከተደራጀ በኋላ በኮብልስቶን ይቀየራል፡፡ ባለሥልጣን መሥሪያ ቤቱ ሁሉንም ለማዳረስ ሲል አነስተኛ ወጪ መድቦ በጠጠር እንደሚሠራ ተናግረዋል፡፡ ያሉት በርካታ የመንገድ ጥያቄዎች ቀስ በቀስ እንደሚመለሱም ይገልጻሉ፡፡