የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሬክስ ቲለርሰን ዛሬ የካቲት 29 ቀን 2010 ዓ.ም. ከኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ወርቅነህ ገበየሁ (ዶ/ር) ጋር በሰጡት መግለጫ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ምንም እንኳን ለስድስት ወራት የታወጀ ቢሆንም ጊዜውን መንግሥት ያሳጥረዋል ብለው እንደሚያምኑ ገለጹ፡፡
ዴሞክራሲ በኢትዮጵያ ገና 27 ዓመታት ማስቆጠሩንና በባህርይው ፈታኝ በመሆኑ ችግሮች ሊታዩ እንደሚችሉና ኢትዮጵያም አሁን ወሳኝ ወቅት ላይ እንደምትገኝ ገልጸዋል፡፡
‹‹ሰላማዊ የሆነ የሥልጣን ሽግግር እንዲኖር መንግሥት እየሠራ ያለውን ሥራ እናደንቃለን፤›› ያሉት ቲለርሰን፣ ‹‹የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ የሚታዩ አለመረጋጋቶችን ለማርገብ ቢያግዝም በአንዳንድ ዜጎች ላይ የዴሞክራሲያዊና የሰብዓዊ መብቶች ጥሰት ሊያስከትል ይችላል፤›› ሲሉ ሥጋታቸውን ገልጸዋል፡፡
የፖለቲካ አመራር የሆኑና ጋዜጠኞች ከእስር መፈታታቸውን ቲለርሰን አድንቀዋል፡፡
ከአገራዊ ጉዳዮች በዘለለ በተለይ ሶማሌና ደቡብ ሱዳን ላይ ትኩረት ያደረጉ አኅጉራዊና ቀጠናዊ ጉዳዮችን ቲለርሰን ከኢትዮጵያ አቻቸው ጋር መወያየታቸውም ታውቋል፡፡