እናት ባንክ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የተከፈለ ካፒታላቸውን 500 ሚሊዮን ብር ማድረስ እንዳለባቸው ያወጣው መመርያ የጊዜ ገደብ ከመጠናቀቁ በፊት የተከፈለ ካፒታሉን 500 ሚሊዮን ብር አደረሰ፡፡ የአክሲዮን ሽያጩን ማቆሙም ተገልጿል፡፡
ከባንኩ ያገኘነው መረጃ እንደሚያሳየው እናት ባንክ የተከፈለ ካፒታሉን 500 ሚሊዮን ብር ማድረስ መቻሉን ያረጋገጠው በሳምንቱ መጨረሻ ላይ ነው፡፡
ባንኩ ሥራ በጀመረ በሁለት ዓመት ተኩል ጊዜ ውስጥ ካፒታሉን 500 ሚሊዮን ብር ማድረሱም የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ መመርያን ሊያሟላ ያስቻለው ከመሆኑም በላይ፣ ከግል ባንኮች በሁለት ዓመት ጊዜ ውስጥ የተከፈለ ካፒታሉን 500 ሚሊዮን ብር ማድረስ የቻለ ባንክ ለመሆን መቻሉም ተጠቅሷል፡፡
ባንኩ የተከፈለ ካፒታሉን 500 ሚሊዮን ብር ማድረሱም ካለፈው ዓርብ ጀምሮ እየሸጠ የነበረውን አክሲዮን ሽያጭ የቆመ መሆኑንም ያገኘነው መረጃ ያስረዳል፡፡ የባንኩ ምክትል ፕሬዚዳንት ወ/ሮ ብርቱካን ገብረ እግዚ እንደገለጹት፣ ባንኩ ወደ ሥራ ሲገባ 6000 አካባቢ የነበሩት የባለአክሲዮኖች ቁጥር በአሁኑ ወቅት 10,800 ደርሰዋል፡፡
ከጠቅላላ ባለአክሲዮኖች ውስጥም ሴት ባለአክሲዮኖች 66 በመቶ ደርሰዋል፡፡ ባንኩ ሥራ ሲጀምር 64 በመቶው ሴቶች እንደነበሩ ይታወሳል፡፡ እናት ባንክ በ2007 በጀት ዓመት ከታክስ በፊት 71 ሚሊዮን ብር ማትረፍ ችሏል፡፡ በብሔራዊ ባንክ መመርያ መሠረት ካፒታላቸውን 500 ሚሊዮን ብር ማድረስ ያልቻሉ ሁለት ባንኮች ብቻ ቀርተዋል፡፡ እነርሱም ደቡብ ግሎባል ባንክና አዲስ ኢንተርናሽናል ባንክ ናቸው፡፡