Monday, April 15, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የአርክቴክቶች ማኅበር የዲዛይን ውድድርና የሙያ ክፍያን ሕጋዊ ለማስደረግ እየሠራ መሆኑን ገለጸ

ተዛማጅ ፅሁፎች

የኢትዮጵያ አርክቴክቶች ማኅበር፣ የሕንፃ ዲዛይኖችን የሚያሠሩ አካላት እስካሁን እንደሚደረገው በጨረታ ግዥ ሳይሆን በዲዛይን ውድድር አማካይነት እንዲያሠሩ ለማድረግ እየሠራ መሆኑን ገለጸ፡፡ ለአርክቴክቶች የሚከፈለው የሙያ ክፍያም ዝቅተኛው መጠን በሕግ እንዲደነገግ የማድረግ እንቅስቃሴ ላይ እንደሚገኝ አስታውቋል፡፡

ለ17ኛ ጊዜ ዘንድሮ የሚያካሂደውን ጉባዔ፣ ዓውደ ርዕይና የሽልማት ሥነ ሥርዓት በማስመልከት ነሐሴ 13 ቀን 2007 ዓ.ም. ለጋዜጠኞች መግለጫ የሰጡት የማኅበሩ አመራር አባላት፣ በአገሪቱ የሚታየውን የዲዛይን ጥራት ችግሮች ለመቀነስ ይረዳሉ ከሚሏቸው መንገዶች መካከል አሠሪዎች የዲዛይን ውድድሮች አካሂደው ጥራትና ብቃት ያለውን ዲዛይን ለመምረጥ የሚችሉበት አሠራር መስፋፋት አንዱ አማራጭ ነው፡፡

ይህንን አሠራር ለማስፋፋት የሕግ ማዕቀፍ አስፈላጊ ቢሆንም በተለይ የመንግሥት የግዥ ሥርዓትን ተገን በማድረግ የዲዛይን ውድድር እንዳይካሄድ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች ችግር መፍጠራቸውን ኃላፊዎቹ ገልጸዋል፡፡ ምንም እንኳ የግዥ ሥርዓቱ የዲዛይን ጨረታዎችን ከሌሎች የግዥ ዓይነቶች ለይቶ መመልከት እንዳለበት ቢገልጹም ያለው ሥርዓትም ቢሆን የዲዛይን ውድድርን ከነጭራሹ ከሕግ ውጭ አላደረገውም ይላሉ፡፡

አቶ አማኑኤል ተሾመ የማኅበሩ ምክትል ፕሬዚዳንት ናቸው፡፡ አቶ አማኑኤል እንደሚያስረዱት፣ የመንግሥት የግዥ ሥርዓት ሦስት አካሄዶች አሉት፡፡ አንደኛው ዋጋን መሠረት ያደረገ ነው፡፡ ሁለተኛው ዋጋንና ጥራትን ያማከለ ሲሆን፣ በሦስተኛ ደረጃ ጥራትን ብቻ መሠረት ያደረገ ግዥ መፈጸም እንደሚቻል ይጠቁማል ያሉት አቶ አማኑኤል፣ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች በዚህ አሠራር ለመመራት የግዥ መመርያም እንደሚያግዛቸው ይገልጻሉ፡፡

የአርክቴክቶች ማኅበር በሕንፃ ዲዛይን ውድድርና ለዲዛይን በሚከፈለው ዝቅተኛ ክፍያ ላይ ሕጎችን በማውጣት የማኅበሩ አባላት እንዲተገብሩት እያደረገ እንደሚገኝ የገለጹት የማኅበሩ ፕሬዚዳንት አቶ ወንድወሰን ደምረው፣ ትልልቅ ፕሮጀክቶች የውድድር ሥርዓትን ላይ ተመሥርተው በመሠራታቸው ከመደበኛው የግዥ ሒደት ይልቅ ጥሩ ውጤት እያስገኙ መምጣታቸውን ይገልጻሉ፡፡ በዲዛይን ውድድር ከሚገነቡ ፕሮጀክቶች መካከል የአዲስ አበባ ቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ የ300 ሚሊዮን ዶላር የተርሚናል ማስፋፊያ ፕሮጀክት ዲዛይን፣ አዲስ ዲዛይን ስቱዲዮና አጋሮቹ የሠሩት፣ ሁለት ቢሊዮን ብር በሚጠጋ ወጪ እንደሚገነባ የሚታሰበውና ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሚገነባው ሕንፃ ዲዛይን፣ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ዋና መሥሪያ ቤት ሕንፃ ግንባታን ጨምሮ የግል ባንኮች ዋና መሥሪያ ቤት ሕንፃዎች፣ አጨቃጫቂው አዲሱ የብሔራዊ ስታዲየም ዲዛይን በውድድር የተመረጡ የዲዛይን ሥራዎች መሆናቸውን ኃላፊዎቹ ገልጸዋል፡፡

የአርክቴክቸር ዲዛይኖችን በውድድር ከማሠራት ባሻገር የሙያ ሥነ ምግባርን ለማስፈን ይረዳል የተባለለትን ይህንን አሠራር መንግሥት በሕግ እንዲያወጣው ማኅበሩ እየተንቀሳቀሰ እንደሚገኝና መንግሥትም ፍላጎት ማሳየቱን ኃላፊዎቹ ተናግረዋል፡፡ ሆኖም አቶ አማኑኤል እንዳስረዱት ይህንን ሥርዓት ማኅበሩ መተግበር ከጀመረ ስድስት ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡ ከዲዛይን ውድድር ባሻገር ለዲዛይን ሙያተኞች መከፈል የሚገባው ክፍያ አግባብነት እንዲኖረውና ወጥ እንዲሆን ዝቅተኛ የክፍያ ተመንን በማኅበሩ አባላት ዘንድ እየተተገበረ እንደሚገኝ ተገልጾ፣ ማኅበሩ ለዚህ የሚረዳ ቀመር በማዘጋጀት፣ የማኅበሩ ሕግ አድርጎ ሥራ ላይ ካዋለ ሰነባብቷል ያሉት አቶ አማኑኤል፣ በአሁኑ ወቅት ለዲዛይን ባለሙያዎች እየተከፈለ ያለው ገንዘብ ከሚታየው የግንባታ መስፋፋትና የገበያ ሁኔታ አኳያ ጥሩ የሚባል እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ ማኅበሩ እነዚህ ጉዳዮች በማስመልከት እንዲሁም ከሕንፃ ከፍታና ከመሬት አጠቃቀም በተለይም ከመኪና ማቆሚያ እጦትን መሠረት በማድረግ በተደረገው የሕግ ማሻሻያ ላይ ውይይት እንደሚደረግ ታውቋል፡፡ በመሃል ከተማ የሚካሄዱ የልማት ሥራዎች ከዲዛይን አኳያ ምን መምሰል አለባቸው በሚሉና ሌሎችም የመወያያ ርዕሶች እንደሚዳሰሱ ታውቋል፡፡

‹‹ሕንፃዎችን መገንባት ከተማን መገንባት ነው፤›› በሚል መነሻ ከነሐሴ 22 እስከ 23 ቀን 2007 ዓ.ም. በሸራተን አዲስ የሚካሄደው የማኅበሩ 17ኛ ዓመታዊ ጉባዔ ከሚያካሂዳቸው ውይይቶች በተጨማሪ 30 ያህል ኩባንያዎች የሚሳተፉበትን ዓውደ ርዕይና የሽልማት ሥነ ሥርዓት አሰናድቷል፡፡ ከተመሠረተ 24 ዓመታት ያስቆጠረው የኢትዮጵያ አርክቴክቶች ማኅበር፣ እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ ያን ያህል ጉልህ እንቅስቃሴ ያልነበረው ቢሆንም ከአምና ጀምሮ ግን ዓመታዊ ጉባዔውን በሸራተን ሆቴል እያካሄደ የሚገኝ ሲሆን፣ የደቡብ አፍሪካ ኩባንያ ከአገር በቀሉ ኢቴል አድቨርታይዚንግና ኮሙኒኬሽንስ የተባለ ኩባንያ በጋራ በመሆን አዘጋጅተውት እንደነበር ይታወሳል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች