Friday, June 9, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የቻይና የምንዛሪ ለውጥ ለኢትዮጵያ አምራቾች ፈተና

- ማስታወቂያ -

ተዛማጅ ፅሁፎች

–  የሰሊጥ ገበያ ሥጋት አጥልቶበታል

ከደንከል እስከ ኩርሙክ፣ ከጂግጂጋ እስከ አሶሳ፣ ከዓድዋ እስከ ሞያሌ፣ ከደባርቅ እስከ ጂንካ፣ ምናለፋን ከመሃል አገር የራቁትንና ጠረፋማ አካባቢዎችን ብቻም ሳይሆን መሃል ከተማውን ተዘዋውረን ብንታዘብ፣ አገሩ በሙሉ በባዕድ ምርቶች ከተጥለቀለቀ ስንት ዓመቱ፡፡ የአገሬው ሸማኔ፣ አንጥረኛው፣ ጡብ ሠሪው፣ ከብት አርቢው፣ አድላቢው፣ እህል አምራቹ ገበሬ፣ ሌላውም በምርት ሒደት ውስጥ የሚሳተፍ ኅብረተሰብ ተቧድኖም ሆነ ራሱን ችሎ ወደ ኢንዱስትሪነት ከማደግ ይልቅ በርካሽ ዋጋ እንደ ወፍ ዘራሽ በተባዛ የድንበር ማዶ ምርት ላይ ጥገኛ ሆኗል፡፡

ከዚህ የሚላቀቅበት ጊዜም ቅርብ አይመስልም፡፡ እነ ቡልኮ ከተማ አካባቢ ከራቁ ቆይተዋል፡፡ እነ ጋቢና ነጠላም ብዙ ዕድሜ ላይኖራቸው ይችላል፡፡ በተለይ ከሩቅ ምሥራቋ ቻይና መንጋጋ መቼም የሚላቀቅ አይመስልም፡፡ በየትኛውም አገሪቱ ክፍሎች ቢጓዙ፣ የቱንም ያህል ገጠራማ አካባቢ ቢደርሱ የቻይና ምርቶች እንደ አሸን ፈልተዋል፡፡ የሸማኔ እጅ የሚፈልትለውን ጋቢ በኢንዱስትሪ ሊመረት ባለመቻሉ፣ የቻይና ብርድ ልብሶች በርካሽ ዋጋ አገሬውን አጥለቅልቀዋል፡፡ ከቅርብ ጊዜ እንኳ መታዘብ እንደሚቻለው የቡና ማንከሽከሻ (ቡና መቁያ) ከቻይና እየተላከ የአገሬውን ቤት ሲያዳርስ ታዝበናል፡፡

እንዲህ ያለው ሁኔታ እየተስፋፋ ሊቀጥል እንደሚችልና መጤ ወይም የውጭ አገር ርካሽ ምርቶች ይበልጥ ሊያጥለቀልቁን የሚችሉባቸው ክስተቶች እየተንሠራፉ እንደሚመጡ ይጠበቃል፡፡ ለዚህ አንዱ ማሳያ የተደረገው ደግሞ ከሰሞኑ ቻይና በመገበያያ ገንዘቧ ላይ ያደረገችው የምንዛሪ ለውጥ ነው፡፡ ቻይና የመገበያያ ገንዘቧ የሆነውን ዩዋን የመግዛት አቅም በአራት ከመቶ እንዲቀንስ ማድረጓን ተከትሎ፣ ከአፍሪካ ኢትዮጵያ፣ ደቡብ አፍሪካና ናይጄሪያ ዕርምጃውን ጥሩም መጥፎም ዕድል ሆኖላቸዋል እየተባለ ነው፡፡ ቻይና ያልተጠበቀ የተባለውን የምንዛሪ ለውጥ ካደረገች ሁለተኛ ሳምንቷን ይዛለች፡፡ የአፍሪካ ተንታኞች የነገርየውን አሳሳቢነት እንዲያስረዱ ይጠበቃሉ፡፡ የምዕራቡ ዓለም ተንታኞች ግን የቻይና ዕርምጃ ያንቀጥቀጥ ደረጃ ላይ ባይደርስም ንዝረቱ ለአፍሪካ መሰማቱ ግን አልቀረም እያሉ ነው፡፡

የምንዛሪ ለውጥ ማለት ምን እንደሆነ ለማየት በአጭሩ ከዚህ ቀደም አንድ ዶላር ለመግዛት ያስፈልግ የነበረው የቻይና ገንዘብ 6.39 ሬንሚንቢ ዩዋን ነበር፡፡ አሁን በተደረገው ለውጥ ምክንያት አንድ ዶላር በ6.90 ዩዋን ይገዛል ማለት ነው፡፡ ስለዚህ አንድ ዶላር መግዛት የፈለገ የቻይና ነጋዴ ወይም ቱሪስት ይህን ያህል ዩዋን መክፈል አለበት ማለት ነው፡፡

የቻይና አድራጎት እየተቀዛቀዘ የመጣውን የአምራች ኢንዱስትሪዋን የወጪ ንግድ ለማሻሻል ብቻም ሳይሆን ጠቅላላ የኢኮኖሚ ዕድገቷ በአጭር ጊዜ ውስጥ ዝግ ማለት ከሚገባው በላይ በፍጥነት በመቀነሱ ልጓም ለማበጀት የወሰደችው ዕርምጃም ተድርጓል፡፡ ከዚህ ባሻገር ግን የዶላር እየበረታ መምጣት የመግዛት አቅሙ እያሻቀበ መጓዝ፣ የቻይናውን ዩዋን እንዲጠነክር አስገድዷል የሚሉ ተንታኞች እንደሚያምኑት፣ ቀስ በቀስ የቻይና ምርቶች እየተወደደ ከመጣው የሰው ኃይላቸው ጭምር ገበያ ላይ እንደ በፊቱ ርካሽ ሆነው እንደልብ አገሮችን ከማጥለቅለቅ ተቀዛቅዘው ታይተዋል፡፡ 

የቻይና መንግሥት የኢኮኖሚውን መቀዛቀዝ በመመልከት የወሰደው የምንዛሪ ለውጥ በአፍሪካ ጉዳቱ አመዝኖ ታይቷል፡፡ በቀላሉ መረዳት እንደሚቻለው የቻይና መገበያያ ገንዘብ ከሌሎች መገበያያ ገንዘቦች አኳያ የመግዛት አቅሙ እንዲቀንስ ሲደረግ፣ የቻይና ምርቶች ይበልጥ በርካሽ ዋጋ እንዲሸጡ ያስችላቸዋል፡፡ በአንፃሩ የአፍሪካ ምርቶች ለቻይና ገበያ ውድ ይሆናሉ ማለት ነው፡፡ ለአብነት ያህል ኢትዮጵያ ለቻይና የምትሸጠው ሰሊጥ ከወትሮው ዋጋው ውድ ስለሚሆን ቻይና እንደቀድሞዋ ላትገዛ ትችላለች ማለት ነው፡፡ በአንፃሩ የቻይና ሸቀጦች ለኢትዮጵያ ገበያ ከመቼውም ጊዜ ይልቅ ርካሽ ይሆናሉ፡፡ ይህም ቢባል ግን የኢትዮጵያ ምርት ገበያ የገበያ ሰሌዳ የሚያሳየው ከ30 እስከ 70 ብር በኩንታል ጭማሪ መኖሩን ነው፡፡ እስካሁን የምንዛሪ ለውጡ ትኩሳት ገና አልተሰማም ማለት ነው፡፡ ይህ ቢባልም ግን ሪፖርተር ያነጋገረቻው ሰሊጥ ነጋዴዎች፣ ዋጋው በሃምሳ ከመቶ እየወረደ እንደሚገኝ፣ የቻይና የምንዛሪ ለውጥም የመግዛት ፍላጎትን ይበልጥ እንዲቀንስ በማድረግ የገበያው ዋጋ ላይ ይበልጥ ተፅዕኖ ሊፈጥር እንደሚችል ይገልጻሉ፡፡

ይሁንና በዚህ ትንታኔ ከሚስማሙት መካከል ፕሮፌሰር ዶቦራ ብራውቲጋም ይጠቀሳሉ፡፡ ፕሮፌሰሯ በጆንስ ሆፕኪንስ ዩኒቨርሲቲ በአድቫንስድ ኢንተርናሽናል ስተዲስ ትምህርት ቤት፣ የዓለም አቀፍ ፖሊቲካል ኢኮኖሚ ፕሮፌሰር ከመሆናቸው ባሻገር በትምህርት ቤቱ የዓለም አቀፍ ልማት ፕሮግራም ኃላፊም ናቸው፡፡ ከዚህ በተጨማሪም የቻይና አፍሪካ ምርምር ተቋምንም ይመራሉ፡፡ ፕሮፌሰሯ በቅርቡ ለሲኤንኤን በሰጡት ትንታኔ መሠረት፣ በቻይና ገንዘብ ምንዛሪ ለውጥ ምክንያት ኢትዮጵያ እንደሌሎች የአፍሪካ አገሮች ተፅዕኖ ከሚደርስባቸው መካከል ተመድባለች፡፡ የቻይና ኩባንያዎችም ሆኑ ቻይናውያን ሸማቾች ከአፍሪካ በዶላር የሚገዟቸው ሸቀጦች ውድ እየሆኑ ስለሚመጡ የመግዛት ፍላጎታቸው ይቀንሳል፡፡ ሆኖም ግን የቻይና የምንዛሪ ለውጥ የኢኮኖሚዋን ዕድገት እንዲያንሰራራ የሚያደርገው ከሆነ ከአፍሪካ ሸቀጦችን የመግዛት ፍላጎት እንዲጨምር የማድረግ ዕድል እንደሚፈጠር ይታሰባል፡፡ ዋጋቸውም ይሻሻላል፡፡ አፍሪካውያንም በርካሽ ዋጋ የቻይና የቴክኖሎጂ ውጤቶችን፣ ስማርት ስልኮችንና አልባሳትን በገፍ ይገዛሉ፡፡ በርካሽ ዋጋ ከቻይና ብረት መግዛት ይቻላል፡፡

ይህ መሆኑ ለአፍሪካ አምራች ኢንዱስትሪ አደጋ ይሆናል ሲሉ ፕሮፌሰር ዲቦራ ይመክራሉ፡፡ ለአፍሪካ አምራች ኢንዱስትሪዎች ብቻም ሳይሆን ቻይናውያን ቱሪስቶችም ወደ አፍሪካ መምጣቱ ከሌላው ጊዜ ይልቅ ውድ ስለሚሆንባቸው እዚያው አገራቸው መዝናናቱን ሊመርጡ ይችላሉ ብለዋል፡፡ በአንፃሩ ከቻይና ይመጣሉ ተብለው የሚጠበቁ ኢንቨስተሮች ዶላር ለማግኘት የሚያወጡት የቻይና ገንዘብ በመጨመሩ ሳቢያ የመምጣታቸው ነገር ብዙም አያወላዳም፡፡

ኢትዮጵያ ዝቅተኛ ርካሽ የሰው ጉልበት እንዳላት ስትሰብክ፣ ዓለምም ይህንን ሲቀበልና የውጭ ኢንቨስትሮች ቢመጡ እንደሚያዋጣቸው ሲገነዘብ እንደነበር ቢታወቅም የአሁኑ የቻይና ዕርምጃ ግን ይህንንም ወደ ጎን የሚያደርግ ሆኖ ሊገኝ ይችላል እየተባለ ነው፡፡ በቻይና የሰው ጉልበት ውድ እየሆነ በመምጣቱ ፋብሪካዎች እየነቀሉ ወደ ኢትዮጵያ እንዲመጡ ሲወተወቱ፣ የቻይና ምሁራንም ይህንኑ ሲያስተጋቡ ሰንብተዋል፡፡ የምንዛሪው ለውጥ ግን የቻይና ግብዓቶችን ከወትሮው ዋጋቸው ቅናሽ እንዲሆኑ ስለሚያደርጋቸው ወደ ኢትዮጵያ ነቅሎ መምጣቱን እንዳይመርጡ እንቅፋት ሊሆን እንደሚችል ይታሰባል፡፡ እርግጥ እስካሁንም ይጠበቅ እንደነበረው ያለ የቻይና ኢንቨስትመንት ኢትዮጵያ ውስጥ የለም፡፡ ቻይና በኢትዮጵያ ብቻም ሳይሆን በአፍሪካ ኢንቨስት ካደረገችው ይልቅ ብድር በማቅረብ በምትገነባቸው መሠረተ ልማቶች የገዘፈ ስም አላት፡፡ በኢንቨስትመንት ረገድ ቱርክ ብቻዋን በኢትዮጵያ ኢንቨስት ያደረገችው ቻይና በአፍሪካ በጠቅላላው ካካሄደችው ኢንቨስትመንት የበለጠ ሆኖ ይገኛል፡፡

በርካታ የቻይና ኩባንያዎች ነቅለው ይመጣሉ የሚል ዕምነት የነበረው የኢትዮጵያ መንግሥት በርካታ መሠረተ ልማቶችን ሲገነባ ከርሟል፡፡ ቻይና የኢትዮጵያን የኢንዱስትሪ ፓርኮች ግንባታ እንደምትደግፍ፣ ኢትዮጵያ ለምታከናውናቸው የመሠረተ ልማት ሥራዎች ድጋፍ እንደምትሰጥ ደጋግማ ከመግለጽ በቀር የቻይና ቀጥታ ኢንቨስትመንት ወደ ኢትዮጵያ ስለሚመጣበት መጠን ከቻይና ወገን ሲነገር ብዙም አይደመጥም፡፡ ይልቁንም በተለያዩ ስብሰባዎች ቻይናውያኑ ሲናገሩ የሚደመጠው በኢትዮጵያ ኢንቨስት ማድረግ አስቸጋሪ መሆኑን ነው፡፡ ዋናው ምክንያታቸው የመንግሥት ቢሮክራሲና አሠራር ጎታታነት ነው፡፡ የጉምሩክ ጣጣዎችን ያነሳሉ፡፡ ይህም ሆኖ ሌሎች አገሮች ኢንቨስት ያደረጉትን ያህል ቻይናውያን ኢንቨስት አላደረጉም፡፡ በቅርቡ ተካሂዶ በነበረው የቻይና አፍሪካ ፎረም ላይ መንግሥት ከቻይና የሚመጣው ኢንቨስትመንት እየጨመረ እንዲመጣ ለማድረግ የመንግሥት ፍላጎት መሆኑን የገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ሚኒስትር ዴኤታው አቶ አህመድ ሺዴ መግለጻቸው አይዘነጋም፡፡

የምንዛሪ ለውጡ ሰበቦች

ቻይና የገንዘብ ምጣኔ ለውጥ ለማድረግ የተገደደችባቸው ምክንያቶች ከሚባሉት ውስጥ የኢኮኖሚዋ መቀዛቀዝ አንዱ መሆኑ ይጠቀሳል፡፡ እ.ኤ.አ. ከ1970ዎቹ ወዲህ እያስገመገመ የመጣው የቻይና ኢኮኖሚ፣ ለማገገሙ ምክንያት የሆነው ዝቅተኛ የደመወዝ ክፍያ፣ ከፍተኛ የአገር ውስጥና የውጭ ኢንቨስትመንት እንዲሁም በፍጥነት እየተስፋፋ የሚገኘው ርካሽ የኤክስፖርት ዘርፍ ነው፡፡

በአሁኑ ወቅት ቻይና መካከለኛ ገቢ ያላት አገር ናት፡፡ የዓለም ባንክ ባስቀመጠው መለኪያ መሠረት በዚህ ረድፍ የሚመደቡ አገሮች ዓመታዊ የነፍስ ወከፍ ገቢያቸው ከአራት ሺሕ እስከ 12 ሺሕ ዶላር ነው (ኢትዮጵያ መካከለኛ ገቢ ካላቸው ተርታ ለመሰለፍ ማቀዷን ልብ ይሏል፤ ይህም የነፍስ ወከፍ ገቢዋ በዝቅተኛው ረድፍ ከአንድ ሺሕ እስከ አራት ሺሕ ዶላር ባለው ክልል ውስጥ ይሆናል)፡፡ የቻይና ኢኮኖሚ በአሁኑ ወቅት ካለበት ደረጃ ለመድረሱ በብዛት እየተስፋፋ የመጣው አገር ውስጥ ፈጠራ፣ የአገር ውስጥ ፍጆታ እንዲሁም ከፍተኛ የቴክነኖሎጂ ውጤቶች የሆኑ ምርቶችን በገፍ ኤክስፖርት ለማድረግ መቻላቸው ሁሉ ተደማምሮ ግዙፍ ኢኮኖሚ ለመግንባት አስቻላቸው፡፡ ከዚህ ሁሉ በላይ ደግሞ የቻይና ኩባንያዎች ከቻይና ውጭ ኢንቨስት የማድረግ አቅምን ፈጠረላቸው፡፡

የቻይና መፈርጠምና የውጭ ኢንቨስትመንት ማብዛት አፍሪካን ጠቅሟል የሚሉት ፕሮፌሰር ዲቦራ፣ የቻይና ኢኮኖሚ ተስፋፊነትና ዕድገት የውጭ መጠባበቂያ ክምችቷን አበራክቶታል፡፡ እ.ኤ.አ. ከ2008 የዓለም የፋይናንስ ቀውስ ወዲህ በምዕራቡ ዓለም ባንኮች የተከማቹ ተቀማጭ ሒሳቦችን ወደ ብድርነት እንዲቀየሩ በማድረግ በአፍሪካ በርካታ የመሠረተ ልማቶችን ፋይናንስ ለማድረግ አስችሏታል፡፡ የቻይና ኢኮኖሚ ዕድገት ለአፍሪካ ሸቀጦች ዋጋ መሻሻልም ምክንያት ሆኖ ቆይቷል፡፡

ምንም እንኳ በቻይናና በአፍሪካ መካከል ያለው የንግድ ግንኙነት ለቻይና ያደላም ቢሆን፣ በሁለቱ ወገኖች መካከል ዓምና የነበረው የንግድ ግንኙነት 220 ቢሊዮን ዶላር አስመዝግቧል፡፡ ይህ ደግሞ ከአሜሪካ ጋር ከሚካሄደው የንግድ ግንኙነት ሦስት እጥፍ የሚበልጥ ሆኖ ይገኛል፡፡ ይህ ሁሉ ግን የአፍሪካ አምራቾችን ከጉዳት አልታደገም፡፡ የቻይናን ርካሽ ምርቶች መፎካከር የሚያስችል አቅም ስለሌላቸው፣ አገሮች በቻይና ምርቶች መጥለቅቀለቃቸውን ሊገቱ አልቻሉም፡፡

የአፍሪካ ጉዳት እንዳለ ሆኖ ቻይኖቹ የምንዛሪ ለውጡን ለማድረግ የተገደዱት የዶላር እየበረታ መምጣት የዩዋንን የመግዛት አቅም በግድ እንዲጨምር ስላስገደደው ነበር፡፡ በዚህ ዓመት በተለይ ዩዋን በ14 ከመቶ ጭማሪ እንዲያሳይ የተገደደው የዶላር አቅም መጎልበት በፈጠረው ጫና ነው፡፡ በአንድ ዓመት ውስጥ በታየው ለውጥ ሳቢያ በሐምሌ ወር ብቻ የወጪ ንግዳቸው በ8.3 ከመቶ እንዲቀንስ አስገድዷል፡፡ ይህም የአሜሪካ የተወዳዳሪነት አቅም ያመጣው ጫና ነበር፡፡ በዚህ ሳያበቃም በርካታ የቻይና ፋብሪካዎች ምርት ከማቆም አልፈው ሠራተኞችን እስከማሰናበት እንዲደርሱ አስገድዷቸዋል፡፡ በመሆኑም ከቀናት በፊት የተደረገው የምንዛሪ ለውጥ የቻይናን የወጪ ንግድ እንዲያንሰራራ አስችሎታል፡፡ በአንፃሩ የወርቅ፣ የድፍድፍ ነዳጅ፣ የመዳብ፣ የፕላቲኒየም እንዲሁም የጠገራ ብረት ገበያና ዋጋ እንዲቀንሱ አስገድዷል፡፡ በተንታኟ መሠረት የደቡብ አፍሪካ ማዕድን ዘርፍ ከአሥር ሺሕ በላይ ሠራተኞችን ለማሰናበት አስገድዶታል፡፡ ሌሎችም ከአፍሪካ የሚላኩ ሸቀጦች ዋጋ እንዲቀንሱ ሰበብ ሆኗል፡፡ ሆኖም ተስፋ አለ፡፡ እንደፕሮፌሰሯ ግምት በመካከለኛ ጊዜ የቻይና ኢኮኖሚ ካንሰራራ ለአፍሪካ ሸቀጦች የሚኖረው ፍላጎት ስለሚጨምር ዋጋው እንደሚያንሠራራ ይጠበቃል፡፡

 

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች