Monday, April 15, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ሜቴክ የሽያጭ መመዝገቢያ መሣሪያ ለማምረት ከገቢዎች ጋር እየተነጋገረ ነው

ተዛማጅ ፅሁፎች

የኢትዮጵያ ብረታ ብረት ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን (ሜቴክ) የሽያጭ መመዝገቢያ መሣሪያ (ካሽ ሬጂስተር ማሽን) በአገር ውስጥ ለማምረት፣ ከኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ጋር በመነጋገር ላይ ነው፡፡

ኮርፖሬሽኑ ከገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ኃላፊዎች ጋር በጉዳዩ ላይ ሁለት ጊዜ የተወያየ መሆኑን፣ የአዋጭነት ጥናት ለማድረግ ይረዳው ዘንድ የገበያ ሁኔታ ግምገማ ከባለሥልጣኑ መጠየቁን፣ የባለሥልጣኑ የታክስ መረጃ አስተዳደር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ዮሐንስ ግዛው ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

ኮርፖሬሽኑ ወደ ማምረት ሥራው የሚገባ ከሆነ የተለያዩ የሶፍትዌር ፕሮግራም አማራጮች ላይ እንዲያተኩር፣ የፍተሻ፣ የብቃትና የዋስትና ጉዳዮችን ማረጋገጥ እንደሚገባው፣ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር የብቃት ፍተሻ ማከናወን እንደሚያስፈልግና በሌሎች ጉዳዮች ላይም በባለሥልጣኑ ማብራርያ እንደተሰጠው ገልጸዋል፡፡

ኮርፖሬሽኑ ወደ ማምረት የሚገባ ከሆነ በአገሪቱ የታክስ ሕግ መሠረት የታክስ ማበረታቻ እንደሚያገኝም አቶ ዮሐንስ ገልጸዋል፡፡

የገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን የሽያጭ መመዝገቢያ መሣሪያ በአገር ውስጥ እንዲመረት የሚያበረታታ መሆኑን የገለጹት አቶ ዮሐንስ፣ የግል ባለሀብቶችም በእዚህ ዘርፍ ውስጥ እንዲገቡ እንደሚፈልግና የተወሰኑ የግል ኩባንያዎችም የሽያጭ መመዝገቢያ መሣሪያ በአገር ውስጥ ለመገጣጠም ፍላጎት ማሳየታቸውን ጠቁመዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት የሽያጭ መመዝገቢያ ለማስገባት የውጭ ምንዛሪ ማግኘት አስቸጋሪ እንደሆነ፣ ይኼንን ችግር ለመቅረፍም ማሽኑ በአገር ውስጥ ሊመረት እንደሚገባ አስረድተዋል፡፡

ከዚህ በተጨማሪ በአሁኑ ወቅት ወደ አገር እየገቡ ያሉ ማሽኖች አምራች የሆኑ ድርጅቶች ወደ ሌሎች የንግድ ሥራዎች በመዘዋወራቸው፣ አቅራቢዎች የመለዋወጫ ችግር ውስጥ እየወደቁ መሆኑም ሌላው የተረጋገጠ ችግር እንደሆነ አቶ ዮሐንስ ጠቁመዋል፡፡

የሽያጭ መመዝገቢያ መሣሪያ መጠቀም የተጀመረው እ.ኤ.አ. በ2008 ሲሆን፣ በሦስት ዓመታት ጊዜ ውስጥ 4,386 ታክስ ከፋዮች ብቻ ተጠቃሚ ነበሩ፡፡ በአሁኑ ወቅት ከ90,000 በላይ ታክስ የሽያጭ ማመዝገቢያ ማሽኖች በጥቅም ላይ ይገኛሉ፡፡

ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ያወጣውን መመዘኛ አሟልተው የሽያጭ መመዝገቢያ መሣሪያ ከቀረጥ ነፃ ከውጭ እያስገቡ ለተጠቃሚዎች እያቀረቡ የሚገኙት ስድስት ድርጅቶች ናቸው፡፡

እነዚህም ፔትራም፣ ሐሮን ኮምፒዩተር፣ ኦሜዳድ፣ ጁፒተር ትሬዲንግ የጅምላ ንግድ አስመጪ ድርጅት፣ አዲስ ሆም ዴፖ፣ አይፒኤስ ትሬዲንግና አምባሰል ትሬዲንግ ናቸው፡፡

የሽያጭ መመዝገቢያ መሣሪያ መጠቀም በሚያስገድደው ሕግ መሠረት፣ ግብር ከፋዮች የሽያጭ መመዝገቢያ መሣሪያዎቻቸውን በየዓመቱ የገዙበት ድርጅት በመሄድ ማስመርመር ይጠበቅባቸዋል፡፡

ይሁን እንጂ ይህ ኃላፊነት በአሁኑ ወቅት ግብር ከፋዮችን በማማረር ላይ ይገኛል፡፡ ምክንያቱ ደግሞ ምንም ዓይነት ብልሽት ለሌለበት መሣሪያ ለወጪ መዳረጋቸው አንዱ ሲሆን፣ ሌላው ደግሞ አቅራቢዎች ማሽኑ እንደተበላሸ አድርገው ለመለዋወጫ ግዥ በማለት ከፍተኛ ዋጋ የሚጠይቃቸው መሆኑን ይገልጻሉ፡፡

የገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ችግሩ መኖሩን እንደደረሰበት በቅርቡ የገለጸ ሲሆን፣ ችግሩን መፍታት የሚቻለው ግን ከግብር ከፋዩ ጋር በመተባበር መሆኑን አስታውቋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች