Tuesday, November 28, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የአዲስ አበባ የኤሌክትሪክ ኃይል ማሠራጫ መስመሮች በ600 ሚሊዮን ዶላር ሊቀየሩ ነው

ተዛማጅ ፅሁፎች

–  መንግሥት ከዚህ በኋላ አዳዲስ ዩኒቨርሲቲዎች እንደማይገነባ አስታወቀ

በአዲስ አበባ የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት ላይ የፈጠረውን የኃይል መቆራረጥ ለማስቀረት፣ በከተማዋ የተዘረጋውን ያረጀና ሥርዓት ያልያዘ የኃይል ማሠራጫ መስመር፣ በ600 ሚሊዮን ዶላር ወጪ ለመቀየር ዝግጅት ተጀመረ፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ባለፈው ረቡዕ ነሐሴ 13 ቀን 2007 ዓ.ም. መንግሥታዊ ካልሆኑ ድርጅቶችና ከመላው አገሪቱ ከተውጣጡ የኅብረተሰብ ተወካዮች ጋር በተደረገው የውይይት መድረክ ላይ እንደገለጹት፣ የኃይል መቆራረጡን ለማስቀረት የማሠራጫ መስመሮች ይቀየራሉ፡፡

በኃይል መቆራረጡ ላይ በተደረገው ጥናት መሠረት በአሁኑ ወቅት በከተማዋ ውስጥ ያሉ የኤሌክትሪክ ኃይል መስመሮች ከማርጀታቸውም በላይ፣ ዝርጋታቸውም የተዘበራረቀ በመሆኑና የሚታየውን የኃይል አቅርቦት ችግር ለመቅረፍ መስመሮቹ እንዲየቀር መወሰኑንም ገልጸዋል፡፡

ለአምፑል የተዘረጋ መስመር ሳይቀር ማሽኖች ሳይቀር እየተጠቀሙበት በመሆኑ በኃይል ሥርጭቱ ላይ እየፈጠረ ያለው ችግር ከፍተኛ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገልጸው፣ ይህንንም ለማስተካከልና ፈር ለማስያዝ የሚያስፈልገው 600 ሚሊዮን ዶላር መገኘቱን፣ በቅርቡም ስምምነቱ ተፈጽሞ ወደ ተግባራዊ ሥራ እንደሚገባ አስታውቀዋል፡፡

የኃይል እጥረቱ ምክንያት አገሪቱ በስፋት እየገባችበት ካለው የልማት ጉዞ ጋር የተያያዘ መሆኑን የጠቀሱት አቶ ኃይለ ማርያም፣ ‹‹ከዚህ ቀደም የአገሪቱ የኃይል አቅርቦት 400 ሜጋ ዋት በነበረበት ወቅት መብራት ጠፍቶ አያውቅም፡፡ ምክንያቱም የምንጠቀመው ለአምፑል ብቻ ስለነበር፤›› በማለት ችግሩ ከኃይል ፍላጎት መጨመር ጋር የተያያዘ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ ‹‹ዛሬ አነስተኛና ጥቃቅን ተቋማት ማሽኖች አሉዋቸው፡፡ አንዳንዶቹ ማሽኖች በአንድ አካባቢ የተሰባሰቡ፣ ሌሎች ደግሞ በመኖሪያ ቤቶች ጭምር የሚገኙ በመሆናቸው በኃይል ሥርጭቱ ላይ ተፅዕኖ አሳድሯል፤›› ብለዋል፡፡

ማሽኖቹ ባሉበት አካባቢ የሚገኙ ትራንስፎርመሮችና የኃይል ማሠራጫዎች መስመር ለማሽን ተብለው የተተከሉ ባለመሆናቸው፣ በአሁኑ ጊዜ በአዲስ አበባም ሆነ በክልል እንዲህ ያለውን የተዘበራረቀ አሠራር ማስተካከል ያስፈልጋልም ብለዋል፡፡

‹‹በአዲስ አበባ ያለው መጀመርያውኑ ተዘበራርቋል፤›› በማለትም የትኛው የመኖሪያ ሠፈር እንደሆነ? የትኛው የማሽን ሠፈር እንደሆነ? የትኛው የኢንዱስትሪ መስመር እንደሆነ እንኳን ባለመታወቁ፣ የማሠራጫ መስመሮቹን በአዲስ የመቀየሩና ተያያዥ ሥራዎችን ማከናወን ግን ለችግሩ መፍትሔ ይሆናል ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትሩ አስረድተዋል፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ የፌዴራል መንግሥት እስከ 2017 ዓ.ም. ድረስ አዳዲስ ዩኒቨርሲቲዎችን የማይገነባ መሆኑንና ከየወረዳው የሚቀርበውን ‹‹ዩኒቨርሲቲ ይገንባልን›› የሚል ጥያቄ እንደማይስተናገድም፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዚሁ የውይይት መድረክ ላይ አስታውቀዋል፡፡

በዕለቱ ጠቅላይ ሚኒስትሩ አፅንኦት እስዲሰጠው በጥብቅ ባሳሰቡበት የዩኒቨርሲቲ ግንባታዎችን በሚመለከተው ማብራሪያቸው፣ መንግሥት ከዚህ በኋላ የዩኒቨርሲቲ ግንባታዎች ውስጥ የመግባት ፍላጎትና ዕቅድ የሌለው መሆኑን ነው፡፡ ይህንኑ የመንግሥት አቋም በውይይት መድረክ ላይ የነበሩ ከየክልሉ የተወከሉ ተሰብሳቢዎች ወደመጡበት ሲመለሱ ይህንን መልዕክት ይዘው እንዲሄዱም አስገንዝበዋል፡፡

በሚቀጥሉት አምስት ዓመታት እንዲገነቡ ከተፈቀዱት 13 ዩኒቨርሲቲዎች ውጪ ምንም ግንባታ እንደማይካሄድ ነው፡፡ የዩኒቨርሲቲ ግንባታዎች ጥያቄዎች አስገራሚ መሆናቸውን ጭምር የተናገሩት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ከ600 በላይ ከሚሆኑ የአገሪቱ ወረዳዎች ጥያቄውን ያላቀረበ አለ ለማለት እንደማይቻል ጠቁመዋል፡፡

የወረዳ አመራሮች ሳይቀሩ የአገር ሽማግሌዎችን እየመረጡና የብሔር ብሔረሰብ ልብሶችን በማልበስ ወደ ጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት በመላክ ጭምር፣ ይህንኑ የዩኒቨርሲቲ ይገንባልን ጥያቄ እስከማቅረብ መድረሳቸውን አመልክተዋል፡፡               

ከዚህ በኋላ ተጨማሪ ጥያቄዎች ማስተናገድ የማይቻልና ለ600 ወረዳዎችም ዩኒቨርሲቲ ለመገንባት የሚያስችል አቅም እንደሌለ ተናግረዋል፡፡ በሚቀጥሉት አምስት ዓመታት የሚገነቡትን፣ የመከላከያና የሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲን ጨምሮ በፌዴራል ደረጃ ያሉት ዩኒቨርሲቲዎች ቁጥር 50 የሚደርስ በመሆኑ፣ ከዚህ በኋላ ትኩረት ተሰጥቶ የሚሠራው የዩኒቨርሲቲዎችን አቅም ማጎልበት ላይ ብቻ ነው ብለዋል፡፡

የመንግሥት ከፍተኛ ትምህርት ተቋማቱ ጥራት ያለው ትምህርት እንዲሰጡ ማጠናከርና የምርምር ማዕከል ማድረግ ይገባል እንጂ፣ አዳዲስ ዩኒቨርሲቲዎች እየገነቡ መሄዱ ‹‹የቆጡን አወርድ ብላ የብብቷን ጣለች›› ወይም ‹‹እንደ ደርግ መፈክር የማትረባ ፍየል ዘጠኝ ትወልዳለች፣ እሷም ትሞታለች ልጆችዋም ያልቃሉ›› የሚሉትን አባባሎች በመጥቀስ የመንግሥትን አቋም አስታውቀዋል፡፡

መንግሥት ዩኒቨርሲቲዎች ጥራት እንዲኖራቸው ለማድረግ ብርቱ አቋም ያለው መሆኑን የገለጹት አቶ ኃይለ ማርያም፣ ‹‹ያሉትን ዩኒቨርሲቲዎች በጥራት ብቁ እንዲሆኑ ማድረግ ላይ ካልተረባረብን፣ ግማሽ የተቀቀለ ሰው እየፈራን የትም አንደርስም፤›› በማለት የሚቀርቡ የልማት ጥያቄዎች አቅምን ያገናዘቡ መሆን እንዳለባቸው አስገንዝበዋል፡፡

አሁን በፌዴራል ደረጃ የተገነቡት ዩኒቨርሲቲዎች ለሁሉም የአገሪቱ ክፍሎች በቂ መሆናቸውን በማስረዳት፣ በፌዴራል ደረጃ ያለው አቋም ይህ ቢሆንም ክልሎች ግን አቅም ካላቸው የራሳቸውን ዩኒቨርሲቲ ሊገነቡ ይችላሉ ብለዋል፡፡

በሰሞኑ የምክክር መድረክ ላይ የትምህርት ጥራት ጉዳይ ተደጋግሞ የተነሳ ሲሆን፣ መንግሥትም ችግሩ መኖሩን በመገንዘብ እንደሚሠራ ተናግረዋል፡፡ በሌላ በኩል ግን ዩኒቨርሲቲዎች አካባቢ ያለው የሙስና ጉዳይ አሳሳቢ ደረጃ ላይ መገኘቱን አቶ ኃይለ ማርያም ሳይገልጹ አላለፉም፡፡

ይህንንም ችግር፣ ‹‹በአሁኑ ጊዜ በአንዳንድ ዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ እየታየ ያለው ኪራይ ሰብሳቢነት በውጭ ካለው ያልተናነሰና የባሰ ነው፤›› በማለት ገልጸውታል፡፡ በቅርቡ የፌዴራል ዋና ኦዲተር መሥሪያ ቤት ይፋ አድርጎት የነበረው ሪፖርት በዩኒቨርሲቲዎች አካባቢ ብልሹ አሠራሮች መታየታቸውን ያስረዳል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች