Saturday, April 1, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የኢትዮጵያ አየር መንገድ 3.5 ቢሊዮን ብር አተረፈ

- ማስታወቂያ -

ተዛማጅ ፅሁፎች

የኢትዮጵያ አየር መንገድ በታሪኩ ትልቁ የሆነውን የተጣራ 3.5 ቢሊዮን ብር አተረፈ፡፡

አየር መንገዱ ሰኔ 2007 ዓ.ም. በተጠናቀቀው እ.ኤ.አ. 2014 – 2015 የበጀት ዓመት 49.4 ቢሊዮን ብር ገቢ ያስገባ ሲሆን፣ 4.7 ቢሊዮን ብር ከታክስ በፊት ለማትረፍ ችሏል፡፡ ባለፈው በጀት ዓመት አየር መንገዱ 46.5 ቢሊዮን ብር ገቢ ሲያገኝ፣ 3.15 ቢሊዮን ብር የተጣራ ትርፍ ማግኘቱ ይታወሳል፡፡

በሰኔ 2007 ዓ.ም. በተጠናቀቀው የ2014 – 2015 በጀት ዓመት የኢትዮጵያ አየር መንገድ 6.4 ሚሊዮን መንገደኞችና 329,000 ቶን ክብደት ያለው ጭነት አጓጉዟል፡፡ ባለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት አየር መንገዱ ስድስት ሚሊዮን መንገደኞችና 187,000 ቶን ጭነት አመላልሷል፡፡

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ተወልደ ገብረ ማርያም ለሪፖርተር እንደተናገሩት፣ ይህ አመርቂ ውጤት ሊገኝ የቻለው የኩባንያው ሠራተኞችና የማኔጅመንት አባላት ጠንክረው በመሥራታቸው ነው፡፡

የኢትዮጵያ አየር መንገድ የቀረፀውን ራዕይ 2025 በመባል የሚታወቀው የ15 ዓመት የዕድገት መርሐ ግብር ተግባራዊ ማድረግ ከጀመረ አምስት ዓመት እንዳስቆጠረ የገለጹት አቶ ተወልደ፣ በሁሉም መመዘኛዎች በመርሐ ግብሩ የተቀመጡትን ዕቅዶች ቀደም ብሎ ማሳካቱን ተናግረዋል፡፡

አየር መንገዱ እ.ኤ.አ. በ2025 ወደ 90 ዓለም አቀፍ መዳረሻዎች እንዲኖሩት አቅዶ የነበረ ቢሆንም፣ በአሁኑ ወቅት ወደ 91 ዓለም አቀፍ መዳረሻዎች በመብረር ላይ ይገኛል፡፡ ይህም ዕቅዱን አሥር ዓመት አስቀድሞ ማሳካት ችሏል፡፡

በራዕይ 2025 መሠረት እ.ኤ.አ. በ2015 አየር መንገዱ 63 አውሮፕላኖች እንዲኖሩት ያቀደ ቢሆንም፣ በአሁኑ ወቅት የ77 አውሮፕላኖች ባለቤት ለመሆን ችሏል፡፡ ትርፍን በተመለከተ እ.ኤ.አ. በ2014 – 2015 በጀት ዓመት 2.9 ቢሊዮን ብር የተጣራ ትርፍ ለማትረፍ አቅዶ 3.5 ቢሊዮን ብር የተጣራ ትርፍ ለማግኘት ችሏል፡፡

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ገቢ እ.ኤ.አ. በ2004 – 2005 በጀት ዓመት 490 ሚሊዮን ዶላር የነበረ ሲሆን፣ በአሥር ዓመት ውስጥ በ500 ፐርሰንት በማሳደግ 2.42 ቢሊዮን ዶላር አድርሶታል፡፡

የኢትዮጵያ አየር መንገድ የ3.5 ቢሊዮን ብር የተጣራ ትርፍ ማግኘት የቻለው፣ በርካታ ታዋቂ የአፍሪካ አየር መንገዶች ከፍተኛ ኪሳራ ባስመዘገቡበት ወቅት ነው፡፡ የደቡብ አፍሪካ፣ የግብፅና የኬንያ አየር መንገዶች በበጀት ዓመቱ ከፍተኛ ኪሳራ እንደደረሰባቸው አስታውቀዋል፡፡

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ተፎካካሪ የሆነው ኬንያ ኤርዌይስ 293 ሚሊዮን ዶላር መክሰሩን ከሁለት ሳምንት በፊት ይፋ አድርጓል፡፡ ደቡብ አፍሪካ ኤርዌይስ 223 ሚሊዮን ዶላር፣ ኢጅፕት ኤር ደግሞ 350 ሚሊዮን ዶላር ኪሳራ አስመዝግበዋል፡፡

እ.ኤ.አ. የ2014 – 2015 በጀት ዓመት ለአፍሪካ አየር ትራንስፖርት ዘርፍ ፈታኝ እንደነበር የሚገልጹት አቶ ተወልደ፣ የኢቦላ ወረርሽኝ መከሰት ከፍተኛ ቀውስ መፍጠሩን አስረድተዋል፡፡ የዓለም የነዳጅ ዋጋ መቀነስ ለአየር መንገዶች መልካም አጋጣሚ ቢፈጥርም በተቃራኒው እንደ ናይጄሪያ፣ አንጎላና ጋቦን ያሉ ዋና ነዳጅ ላኪ የአፍሪካ አገሮች ኢኮኖሚ በነዳጅ ዋጋ ማሽቆልቆል ምክንያት ክፉኛ በመጎዳታቸው በአየር ትራንስፖርት መንገደኞች ፍሰት ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ እንደፈጠረ አቶ ተወልደ ተናግረዋል፡፡

የዩሮ ምንዛሪ ማሽቆልቆል በአፍሪካ ኢኮኖሚዎች ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ማሳደሩን፣ እነዚህ ሁሉ ተፅዕኖዎች በአጠቃላይ በአፍሪካ የአየር ትራንስፖርት ዕድገት ላይ የሦስት በመቶ ቅናሽ ማድረሳቸውን አቶ ተወልደ ተናግረዋል፡፡

የኢትዮጵያ አየር መንገድ 8,000 ሠራተኞች ያሉት ሲሆን፣ በአቪዬሽን አካዴሚው ላይ 80 ሚሊዮን ዶላር ኢንቨስት በማድረግ የማሠልጠን አቅሙን በከፍተኛ ደረጃ አሳድጓል፡፡ የመማሪያ ክፍሎችና የመኝታ ቤቶች ሕንፃ በመገንባት የተለያዩ ዘመናዊ የበረራና የጥገና መማሪያ መሣሪያዎች በመግዛት ላይ የሚገኘው የአቪዬሽን አካዴሚ፣ 4,000 ተማሪዎችን የማሠልጠን አቅም አለው፡፡ በአሁኑ ወቅት 1300 አብራሪዎች፣ የአውሮፕላን ጥገና ቴክኒሽያኖች፣ የበረራ አስተናጋጆችና የማርኬቲንግ ባለሙያዎች በማሠልጠን ላይ ይገኛል፡፡

በተመሳሳይ አየር መንገዱ ዘመናዊ የአውሮፕላን ጥገና ማዕከል፣ የካርጎ ተርሚናልና የምግብ ማደራጃ ማዕከል በከፍተኛ ወጪ በመገንባት ላይ ይገኛል፡፡ የአውሮፕላኖቹን ቁጥር በእጥፍ ለማሳደግ እንደ ቦይንግ 777፣ 737 ማክስ፣ 787 ድሪምላይነርና ኤርባስ 350 ያሉ ዘመናዊ አውሮፕላኖች ግዢ ፈጽሞ በመጠባበቅ ላይ ይገኛል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች