Wednesday, February 28, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

በታክስ ማጭበርበር የተከሰሰው የእስራኤል ኩባንያ የያዛቸው መንገዶች ለሌላ ኮንትራክተር ሊሰጡ ነው

ተዛማጅ ፅሁፎች

በሙስናና በታክስ ማጭበርበር ክስ የተመሠረተበት የእስራኤሉ ትድሃር ኤክስካቬሽን ኤንድ ኧርዝ ሙቪንግ ኩባንያ፣ በአዲስ አበባ ከተማ የያዛቸውን ፕሮጀክቶች ሌላ ኮንትራክተር እንዲወስደው ወይም ባለሥልጣኑ በራሱ ኃይል ለመገንባት የሚያስችል ውሳኔ የአዲስ አበባ ከተማ መንገዶች ባለሥልጣን ቦርድ ሊያሳልፍ መሆኑ ተገለጸ፡፡

የባለሥልጣኑ ዋና ሥራ አስኪያጅ ኢንጂነር ፍቃዱ ኃይሌ፣ ዓርብ ነሐሴ 15 ቀን 2007 ዓ.ም. በመሥሪያ ቤታቸው በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ፣ ትድሃር ከያዛቸው ፕሮጀክቶች አብዛኞቹ የተጠናቀቁ ቢሆንም ከዚህ በኋላ ግንባታውን መቀጠል እንደማይችል በአማካሪዎች መረጋገጡን አስታውቀዋል፡፡ ቀሪዎቹ ሥራዎች እስከ ግማሽ ቢሊዮን ብር እንደሚገመቱም ጠቁመዋል፡፡

ከማዕድን ሚኒስቴር እስከ ውኃ ልማት ድረስ የባቡር መስመሩን ተከትሎ በመገንባት ላይ ያለው የተሽከርካሪና የእግረኛ መንገድ ባለሥልጣኑ በራሱ እንዲገነባው ወይም ለሌላ ኮንትራክተር መስጠት እንዳለበት፣ በአማካሪ መሐንዲሶችና በባለሥልጣኑ ስምምነት ላይ ተደርሷል ብለዋል፡፡ የእስራኤሉ ኩባንያ ከ149 ሚሊዮን ብር በላይ በታክስ ስወራ፣ ማጭበርበርና የአገር ውስጥ ገቢ ሠራተኞችን በሙስና መደለል ክስ የተመሠረተበት ሲሆን፣ የኩባንያው ባለቤትና ዋና ሥራ አስኪያጅ ሜናሽ ሌቪ በፌዴራል ሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን በቁጥጥር ሥር መዋላቸው ይታወሳል፡፡

ክሱን እየመረመረ የሚገኘው የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 18ኛ ወንጀል ችሎት፣ የኮሚሽኑ ዓቃቤ ሕግ ባቀረበው ማመልከቻ መሠረት የኩባንያው ባለቤት ንብረት የሆኑና በድርጅቱ ስም ተመዝግበው የሚገኙ 16 የተለያዩ ተሽከርካሪዎች፣ 21 የተለያዩ የግንባታ ማሽነሪዎች፣ ኩባንያው ለሠራው ሥራ የሚከፈል ከ50 ሚሊዮን ብር በላይ እንዲታገድ ትዕዛዝ ማስተላለፉን መዘገባችን አይዘነጋም፡፡ 

ድርጅቱ ለሦስት ተከታታይ ዓመታት ባደረጋቸው የንግድ እንቅስቃሴዎች ከሰበሰበው ገቢ ላይ፣ ለመንግሥት አሳውቆ መክፈል የነበረበትን የተጨማሪ እሴት ታክስ ፍሬ ግብር 2,132,817 ብር አለመክፈሉን፣ የተጨማሪ እሴት ታክስ ፍሬ ግብር ወለድ 4,141,387 ብር፣ መቀጫ 7,497,249 ብር በድምሩ 13,771,455 ብር ለመንግሥት አሳውቆ ባለመክፈሉና የኩባንያው ባለቤት የድርጅቱ ሥራ አስኪያጅ ሆነው በፈጸሙት ሕግን በመጣስ ታክስ ያለመክፈል ወንጀል መከሰሳቸውን የቀረበባቸው ክሱ ይገልጻል፡፡ በአጠቃላይ ከ143 ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ ገንዘብ መጠን መከሰሳቸው መዘገቡም ይታወሳል፡፡  

ኩባንያው በአዲስ አበባ ብዛት ያላቸውን የመንገድ ፕሮጀክቶችን የያዘ ሲሆን፣ አብዛኞቹ የቀሩት ሥራዎች የእግረኛ መተላለፊያ መንገዶች ግንባታ መሆናቸውን ኢንጂነር ፍቃዱ አስረድተዋል፡፡

ኩባንያው እስካሁን ላጠናቀቃቸው መንገዶች በኮንትራት ውሉ መሠረት ገንዘብ የተከፈለው ቢሆንም፣ ያላጠናቀቃቸውን ቀሪ መንገዶች ጨምሮ ያልተከፈሉት ገንዘቦች ግን በፀረ ሙስና ኮሚሽን ትዕዛዝ መሠረት እንደተያዙበት ኢንጂነር ፈቃዱ ገልጸዋል፡፡

ከስድስት ኪሎ ፈረንሳይ ሌጋሲዮን በመባል የሚታወቀው አካባቢ ሲገነባ የቆየው መንገድ ለመጠናቀቅ የእግረኞች መንገድ ግንባታ ብቻ የሚቀሩት በመሆኑ፣ ባለሥልጣኑ በራሱ ወይም በሌላ ኮንትራክተር አማካይነት ሊያጠናቅቀው ማቀዱም ተገልጿል፡፡

በሌላ በኩል ባለሥልጣኑ በተጠናቀቀው የ2007 በጀት ዓመት በአዲስ አበባ 694 ኪሎ ሜትር መንገድ ተገንብቶ የከተማው የመንገድ ሽፋን ከ17.5 በመቶ ወደ 20.1 በመቶ ማደጉን ዋና ሥራ አስኪያጁ አስታውቀዋል፡፡

በበጀት ዓመቱ እንዲገነቡ በዕቅድ ከተያዙት 88 ዋና ዋና መንገዶች ውስጥ 55 በግንባታ ላይ፣ ዘጠኝ በዲዛይን፣ 11 በፕሮጀክት ወሰን ማስከበርና 13 ፕሮጀክቶች በጨረታ ሒደት ላይ እንደሚገኙ ገልጸዋል፡፡

በመገንባት ላይ ያሉትም ሆኑ ተጠናቀው አገልግሎት እየሰጡ ያሉት መንገዶች በሽፋንም ሆነ በጥራት እየጎለበቱ ቢመጡም፣ የአገር ውስጥ ኮንትራክተር የአቅም ውሱንነትና የጥራት ችግር አሁንም አሳሳቢ ሆኖ መቀጠሉን አስረድተዋል፡፡

በአብዛኞቹ የመንገዶች ፕሮጀክቶች ላይ መጓተትና የጥራት ጉድለት እየታየ በመሆኑ ባለሥልጣኑ ራሱ እየገነባ የማገዝ ሥራ ለማከናወን መገደዱን ኢንጂነር ፍቃዱ ገልጸው፣ ከዚህ ባሻገር ግንባታቸው በተቀመጠው ጊዜ ያላለቁ መንገዶች ለክረምት ጎርፍ መጋለጣቸውና በነዋሪዎች ላይ ጫና እያደረሱ መሆኑንም አብራርተዋል፡፡

ኮንትራክተሮች ባለሥልጣኑ በሚፈልገው መንገድ እየሠሩ አይደለም ከማለታቸውም በተጨማሪ፣ በአገር ውስጥ ኮንትራክተሮች የሚታየው የአቅም ችግር ሥር መስደዱን ገልጸዋል፡፡ ሌላው ለባለሥልጣኑ ፈታኝ ችግር የሆነበት የወሰን ማስከበር ጉዳይ መሆኑን የገለጹት ኢንጂነር ፍቃዱ፣ ‹‹የወሰን ማስከበር ቢያንስ 80 በመቶ ሳይጠናቀቅ ወደ አዲስ ግንባታ መገባት የለበትም የሚል ስምምነት ላይ ብንደርስምማ፣ እስካሁን ድረስ የተሻለ ዕድገት አላሳየም፤›› ሲሉ ገልጸዋል፡፡

በአዲስ አበባ ከተማ በመገንባት ላይ ያሉ መንገዶች መጓተትና በኅብረተሰቡ ላይ የሚፈጠረው እንግልት መነሻው፣ ከዚሁ የወሰን ማስከበር ጋር እንደሚያያዝም አስታውቀዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች