Tuesday, May 28, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ዜናበከባድ ሙስና ተጠርጥረው የታሰሩት የኦሮሚያ ክልል የቀድሞ ባለሥልጣን በነፍስ ግድያ ተጠረጠሩ

በከባድ ሙስና ተጠርጥረው የታሰሩት የኦሮሚያ ክልል የቀድሞ ባለሥልጣን በነፍስ ግድያ ተጠረጠሩ

ቀን:

‹‹መጠየቅ ካለብኝ በክልል እንጂ በፌዴራል አይደለም›› አቶ ወንድሙ ቢራቱ

ለመንግሥት መግባት የነበረበትን ተጨማሪ እሴት ታክስና ሌሎች የመንግሥት የግብር ገቢዎች በማጭበርበር በግላቸውና በዘመዶቻቸው ከ100 ሚሊዮን ብር በላይ በማካበት በከባድ የሙስና ወንጀል ተጠርጥረው የታሰሩት፣ የኦሮሚያ ክልል ገቢዎች ቢሮ ኃላፊ የነበሩት አቶ ወንድሙ ቢራቱ ሰው በመግደል ወንጀል መጠርጠራቸው ለፍርድ ቤት ተገለጸ፡፡

ነሐሴ 3 ቀን 2007 ዓ.ም. በቁጥጥር ሥር ውለው ነሐሴ 4 ቀን 2007 ዓ.ም. በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ሁለተኛ ወንጀል ችሎት ቀርበው 11 ቀናት ለተጨማሪ ምርመራ ተሰጥቶባቸው የነበሩት አቶ ወንድሙ፣ በሰው መግደል ወንጀል የፌዴራልና የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽኖች ያደረጉት የምርመራ መዝገብ ቀርቦ እየተጣራባቸው መሆኑ ተነግሯል፡፡

- Advertisement -

የፌዴራል የሥነ ምግባርና የፀረ ሙስና ኮሚሽን መርማሪ ቡድን ነሐሴ 13 ቀን 2007 ዓ.ም. ለከፍተኛው ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ተረኛ ችሎት ተጠርጣሪውን አቅርቧቸዋል፡፡ ቀደም ብሎ በተፈቀደለት ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ 13 ሚሊዮን ብር የተንቀሳቀሰበት ሰነድ ከባንክ ተፈልጐ መሰባሰቡን፣ በፌዴራልና በክልል ባሏቸው ቤቶች ብርበራ መካሄዱን፣ ከባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር የሲዲ መረጃ መሰብሰቡንና የሁለት ምስክሮችን ቃለ መቀበሉን መርማሪ ቡድኑ ለፍርድ ቤቱ አስረድቶ፣ የሚቀረው ምርመራ እንዳለ በመግለጽ ተጨማሪ 14 ቀናት የምርመራ ጊዜ ጠይቋል፡፡

መርማሪ ቡድኑ ተጨማሪ ቀናት የጠየቀበትን ምክንያት ለፍርድ ቤቱ እንዳስረዳው፣ ከአዲስ አበባና ከፌዴራል ፖሊስ የነፍስ ግድያ ወንጀል ምርመራ መዝገብ መጥቶለት፣ ምርመራው በደንብ መካሄዱን መገምገም ከፌዴራልና ከክልል የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች ተጨማሪ የሰነድ ማስረጃዎች መሰብሰብ፣ ከገቢዎችና ጉምሩክ የተለያዩ ሰነዶችን መሰብሰብ፣ ከኦሮሚያ ገቢዎች የኢንስፔክሽን ሪፖርት መሰብሰብና ሌሎች ተጠርጣሪዎችን መያዝ እንደሚቀረው አስረድቷል፡፡

በተጠርጣሪው ዘጠኝ ቤቶችና በአራት ከተሞች የተደረገውን የብርበራ መረጃ መተንተን፣ በአዲስ አበባ ዙሪያ ያሰባሰቡትን የመሬትና የቤት ባለቤትነት ሰነድና  ከተለያዩ ባንኮች ገንዘብ የተቀባበሉባቸውን ደረሰኞች ማስረጃ መሰብሰብ እንደሚቀረው፣ ቡድኑ ለፍርድ ቤቱ በማስረዳት የተጠየቀው ተጨማሪ የምርመራ ቀን እንዲፈቀድለት ጠይቋል፡፡

አቶ ወንድሙ በበኩላቸው ባቀረቡት ተቃውሞ፣ መርማሪው የፈለገውን ሰነድም ሆነ ሌላ ነገር ማግኘቱን ገልጸዋል፡፡ መርመሪዎች እሳቸውን ካሰሩ በኋላ መኖሪያ ቤታቸው በመሄድ የአምስት ዓመት ሕፃን ልጃቸው ላይ ሽጉጥ በመደቀን ያደረጉትን ማስፈራራት አምርረው ተቃውመዋል፡፡

ከታሰሩበት ዕለት ጀምሮ ማንም ቤተሰብ እንዳልጠየቃቸው፣ ምክንያቱ ደግሞ መርማሪዎቹ እንዳስፈራሯቸው መስማታቸውን ተናግረዋል፡፡ እሳቸው የክልል ተሿሚና የካቢኔ አባል መሆናቸውን በመግለጽ፣ መጠየቅ ካለባቸውም በክልል እንጂ በፌዴራል አለመሆኑን አስረድተዋል፡፡ ኮሚሽኑ በመገናኛ ብዙኃን ስማቸውን እያጠፋ መሆኑን በመግለጽ ትዕዛዝ እንዲሰጥላቸው ጠይቀዋል፡፡

የኮሚሽኑ መርማሪ በበኩላቸው አቶ ወንድሙ ያቀረቡትን አቤቱታ የሰሙት በዕለቱ ለችሎቱ ሲያስረዱ መሆኑን ገልጸው፣ እሳቸው እንዳሉት ሆኖ ከተገኘ ኮሚሽኑ በድርጊቱ ፈጻሚዎች ላይ ዕርምጃ እንደሚወስድ አሳውቀዋል፡፡ ሥልጣኑ የክልል ነው ስለመባሉ ግን፣ የግብር ጉዳይ የፌዴራሉ ጭምር መሆኑን በመጥቀስ አስረድተዋል፡፡ የቫትንና የጉምሩክ ቀረጥን በሚመለከት የማየት ሥልጣን የፌዴራል ፍርድ ቤቶች መሆኑንም አክለዋል፡፡

ፍርድ ቤቱ አቶ ወንድሙ ያቀረቡትን አቤቱታ በሚመለከት በሰጠው ትዕዛዝ ሕገ መንግሥታዊ መብታቸው መከበር እንዳለበት አሳስቦ በቤተሰብ፣ በዘመዶቻቸው፣ በሃይማኖት አባትና በሕግ አማካሪያቸው የመጐብኘት መብት እንዳላቸው በመግለጽ ኮሚሽኑ ተግባራዊ እንዲያደርግ አዟል፡፡

በሕፃን ልጃቸው ላይ ተደረገ የተባለው እውነት ከሆነና ማስረጃ ከቀረበ ዕርምጃ እንደሚወስድ አስጠንቅቆ፣ የኮሚሽኑ መርማሪ ቡድን በሕግና በአግባቡ መመርመር እንዳለበት፣ ከዚያ ውጪ የሆነ በግዳጅና በኃይል የሚገኝ መረጃን ውድቅ እንደሚያደርግ በማሳሰብ፣ መርማሪ ቡድኑ ለጠየቀው ተጨማሪ ምርመራ አሥር ቀናትን ፈቅዷል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የፋይናንስ ኢንዱስትሪው ለውጭ ባንኮች መከፈት አገር በቀል ባንኮችን ለምን አስፈራቸው?

የማይረጥቡ ዓሳዎች የፋይናንስ ተቋማት መሪዎች ሙግት ሲሞገት! - በአመሐ...

የምርጫ 97 ትውስታ!

በበቀለ ሹሜ      መሰናዶ ኢሕአዴግ ተሰነጣጥቆ ከመወገድ ከተረፈ በኋላ፣ አገዛዙን ከማሻሻልና...

ሸማቾች የሚሰቃዩት በዋጋ ንረት ብቻ አይደለም!

የሸማች ችግር ብዙ ነው፡፡ ሸማቾች የሚፈተኑት ባልተገባ የዋጋ ጭማሪ...

መንግሥት ከለጋሽ አካላት ሀብት ለማግኘት የጀመረውን ድርድር አጠናክሮ እንዲቀጥል ፓርላማው አሳሰበ

የሦስት ዩኒቨርሲቲዎች ፕሬዚዳንቶች በኦዲት ግኝት ከኃላፊነታቸው መነሳታቸው ተገልጿል አዲስ አበባ...