Friday, December 8, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናኢንጂነር ይልቃል ዳግም የሰማያዊ ፕሬዚዳንት ሆነው ተመረጡ

ኢንጂነር ይልቃል ዳግም የሰማያዊ ፕሬዚዳንት ሆነው ተመረጡ

ቀን:

ከነሐሴ 16 እስከ ነሐሴ 17 ቀን 2007 ዓ.ም. ጠቅላላ ጉባዔውን ያካሄደው ሰማያዊ ፓርቲ፣ ኢንጂነር ይልቃል ጌትነትን ፓርቲውን እየመሩ እንዲቀጥሉ መረጣቸው፡፡

ባለፈው ቅዳሜና እሑድ የተከናወነው የፓርቲው ጠቅላላ ጉባዔ አዲስ አመራር ከመምረጥ ባለፈ፣ በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ውይይት አድርጓል፡፡ የፓርቲውን ደካማና ጠንካራ ጎኖቹን በመገምገም የተለያዩ ውሳኔዎችን እንዳሳለፈም፣ የፓርቲው የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ዮናታን ተስፋዬ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

የፓርቲው ፕሬዚዳንት ለመሆን በፍላጎት ራሱን ያቀረበ ዕጩ ስላልነበረ፣ አስመራጭ ኮሚቴው ተወዳዳሪዎች በጠቅላላ ጉባዔው እንዲጠቆሙ በማድረግ ስድስት ግለሰቦች ለፕሬዚዳንትነት እንዲወዳደሩ ማድረጉ ታውቋል፡፡ ከተጠቆሙት ግለሰቦች አምስቱ ራሳቸውን ከውድድር ያገለሉ ሲሆን፣ እስከ መጨረሻው ከፕሬዚዳንቱ ጋር ፉክክር ያደረጉት የፓርቲው የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ዮናታን ነበሩ፡፡

በፉክክሩም ኢንጂነር ይልቃል 136 ድምፅ በማግኘት ፓርቲውን ዳግም ለመምራት የተመረጡ ሲሆን፣ ተፎካካሪያቸው የነበሩት አቶ ዮናታን ደግሞ 60 ድምፅ አግኝተዋል፡፡ በዕለቱ ከነበሩት 206 መራጮች ውስጥ አራት አባላት ድምፅ እንዳልሰጡ፣ ሌሎች አራት ድምፆች ደግሞ ድምፅ ሳይሰጥባቸው ባዶውን እንደተከተቱና ሁለት የድምፅ መስጫ ወረቀቶች ደግሞ ኮሮጆው ውስጥ እንዳልገቡ አስመራጭ ኮሚቴው አስታውቋል፡፡

በጠቅላላ ጉባዔው የሁለት ቀናት ውሎ በርካታ ጉዳዮች መነሳታቸውን የገለጹት አቶ ዮናታን፣ ‹‹ፓርቲው በሦስት ዓመታት ውስጥ ራሱን የማስተዋወቅ ሥራ ላይ በማዘንበል በማጠናከር በኩል ግን ቸልተኝነት እንደታየና በዚያ በኩል ወደፊት ጠንካራ ሥራ መሠራት እንዳለበት ወስነናል፤›› በማለት የድርጅቱን ውስጣዊ ጥንካሬ መገንባት ቁልፍ ተግባር ሆኖ እንደሚቀጥል አስታውቀዋል፡፡

የድርጅት ጉዳይ አመራር በእስርና በተለያዩ ምክንያቶች መለዋወጥ የድርጅቱን ውስጣዊ ጥንካሬ ግንባታ እንዳወከ አቶ ዮናታን አስረድተዋል፡፡ የድርጅቱ መዋቅር ራሱ ክፍተት እንዳሳየ፣ በክልሎች ካሉ መዋቅሮች ጋር የግንኙነት ውስንነት መከሰቱም፣ ሌላው ከፍተኛ ውይይት የተካሄደበት ነጥብ እንደነበር አክለው ገልጸዋል፡፡

ሁለት ቀናት በፈጀው ጠቅላላ ጉባዔ የፓርቲውን ፕሬዚዳንት ኢንጂነር ይልቃልን የሦስት ዓመት የሥራ ቆይታና አመራር የሚቃወምና ተፈጽመዋል ያላቸውን ስህተቶች የሚዘረዝር አራት ገጽ ጽሑፍ ተበትኖ የነበረ ቢሆንም አቶ ዮናታን ግን፣ ‹‹በተበተነው ወረቀት ላይ የተነሱት ነጥቦች በአብዛኛው በአሉባልታ ደረጃ ያሉ ናቸው፤›› በማለት አጣጥለውታል፡፡

‹‹ወረቀቱን የበተነው ሰው ራሱን ይፋ አላደረገም፡፡ ያልተገባ ነገር ነው የተደረገው፡፡ ወረቀቱን የበተነው ሰው እዚያው ፓርቲው ውስጥ ያለ ደስተኛ ያልሆነ ሰው ይሁን፣ ወይም ከሌላ ቦታ የመጣ ሠርጎ ገብ ይሁን የተረጋገጠ ነገር የለም፡፡ ነገር ግን አብዛኛዎቹ በዚያ ደረጃ የተቀመጡት ነጥቦች ጫፍ የያዙና በአሉባልታ የተሞሉ መሆናቸውን ነው የምናምነው፤›› በማለት አብራርተዋል፡፡

የፓርቲውን ቀጣይ አቅጣጫ በተመለከተ ሲናገሩ ደግሞ፣ ‹‹እስካሁን በርካታ ሥራዎች ተሠርተዋል፡፡ እነዚህን ሥራዎች ስንሠራ ደግሞ በርካታ ድክመቶች ተስተውለዋል፡፡ ወይም ደግሞ በሥራ ላይ የሚያጋጥሙ ስህተቶችን ማስተዋል ተችሏል፡፡ ከእነዚህ ስህተቶች ትምህርት ወስዶ በተለይ ደግሞ በአብዛኛው የኢትዮጵያ ክልሎች ውስጥ ከመታወቅ ባለፈ ትርጉም ባለው ሁኔታ የድርጅት መዋቅሩን እናጠናክራለን፤›› ብለዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ታዋቂው የኤሌክትሮኒክስ ብራንድ አይቴል የስትራቴጂ ለውጥ አካል የሆነውን አዲስ አርማ እና መለዮ ይፋ አደረገ።

በአለማችን ታዋቂ ከሆኑት የኤሌክትሮኒክስ ብራንዶች መካከል አንዱ የሆነው እና...

የጠቅላላ ጉባኤ ስብሰባ ጥሪ ለሸገር አነስተኛ የፋይናንስ ተቋም አ.ማ ባለአክሲዮኖች በሙሉ

ለሸገር አነስተኛ የፋይናንስ ተቋም አ.ማ ባለአክሲዮኖች በሙሉ የሸገር አነስተኛ የፋይናንስ...

[የክቡር ሚኒስትሩ ጸሐፊ፣ የሌላ ሚኒስትር ጸሐፊ ከሆነችው የቅርብ ወዳጇ ጋር በስልክ እየተጨዋወቱ ነው]

አንቺ ግን ምን ሆነሽ ነው? ጠፋሁ አይደል? ጠፋሁ ብቻ?! ምን ላድርግ ብለሽ...

በሱዳን ላይ ያጠላው የመከፋፈል ዕጣና ቀጣናዊ ተፅዕኖው

የሱዳን ጦርነት ስምንተኛ ወሩን እያገባደደ ይገኛል፡፡ ጄኔራል አብዱልፈታህ አልቡርሃን...