Monday, April 15, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ስፖርትብዙዎችን ያስቆጨው የአትሌቲክስ ውጤት

ብዙዎችን ያስቆጨው የአትሌቲክስ ውጤት

ቀን:

ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ አትሌቲክስ ሻምፒዮና ላይ ለመካፈል ለወራት ያህል አዲስ አበባ ከሚገኙ አትሌቶች እንዲሁም በውጪ ተቀምጠው ልምምድ የሚያደርጉትን ጨምሮ ለ15ኛው የቤጂንግ ዓለም አቀፍ ውድድር ለማድረግ ወደ ሥፈራው  ካቀኑ አምስተኛ ቀናቸውን ይዘዋል፡፡

ኢትዮጵያዊያን አትሌቶች ከዚህ በፊት በረዥም ርቀት በኦሊምፒክ ደረጃና በዓለም አቀፍ ውድድሮች በተከታታይ ከአንድ እስከ ሦስት በመግባት ውድድሮቹን በመጨረስ ዓለምን በማስደመም አረንጓዴው ጎርፍ የሚል ስያሜን ማትረፋቸው ይታወሳል፡፡

በዘንድሮ የቤጂንግ ዓለም አቀፍ አትሌቲክስ ሻምፒዮና ላይ ለመሳተፍ 33 አትሌቶች ዝግጅታቸውን አድርገው ወደሥፍራው ቢያቀኑም እንደቀድሞ አትሌቶች ለብዙዎቹ የስፖርት ቤተሰቦች ደስታ በደስታ ማድረግ የተሳናቸው ይመስላሉ፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

ነሐሴ 16 ቀን 2007 ዓ.ም. በቤጂንግ የወፍ ጎጆ ስታዲየም በኢትዮጵያ አቆጣጠር በ8፡35 ደቂቃ ላይ የጀመረው የማራቶን ውድድር በሌሊሳ ዴሲሳ፣ የማነ ፀጋዬና ለሚ ብርሃኑ ቢመራም፣ ለመጀመርያ ጊዜ በውድድሩ ታሪክ ኤርትራዊው አትሌት ባሸነፈበት ውድድር ግርማዬ ገብረሥላሴ በ2፡12፡28 በመግባት ሌሊሳን ዴሲሳ አስከትሏል፡፡

በተመሳሳይ ቀን ፕሮግራም መሠረት በውድድሩ የኢትዮጵያ አትሌቶች በአሥር ሺሕ ሜትር ፍጻሜ በወንዶች ሙክታር እንድሪስ፣ ኢማና መርጋና ሞስነት ገረሙውን ቢያካትትም በኬንያዎች የተደራጀው የበላይነትና በእንግሊዛዊው ሞ ፋራ አልቀመሴነት ብልጫ ተወስዶባቸው አሥረኛና 11ኛ ደረጃን በመያዝ የብዙዎችን ኢትዮጵያውያን አንገት ያስደፋ ውጤት አስመዝግበዋል፡፡

በተመሳሳይ ሁኔታ በሴቶችም አሥር ሺሕ በሴቶች ሲጠበቅ የነበረው የኢትዮጵያኖች የበላይነት ድጋሚ በረዥም ርቀት ያላቸውን እምነት እንዲያጡ አድርጓቸዋል፡፡ በርቀቱ ገለቴ ቡርቃ፣ አለሚቱ ሃሮየና በላይነሽ ኦልጅራ ኢትዮጵያን ሲወክሉ፣ ሁለተኛ፣ ሰባተኛና ዘጠነኛ ሆነው አጠናቀዋል፡፡

በዓለም አቀፍ ማኅበረሰብ ዘንድ በአትሌቲክሱ ስፖርት በተለይም በረዥም ርቀት ሩጫ አሸናፊነት በመታወቅ ከጃፓኗ ቶኪዮ የኦሊምፒክ የማራቶን ውድድር ጀምሮ በፈር ቀዳጁ ሻምበል አበበ ቢቂላ ኢትዮጵያን በማስጠራት በረዥም ርቀት፣ በሴቶች ከደራርቱ ቱሉ ጀምሮ እስከ ጥሩነሽ ዲባባ እንዲሁም በወንዶች ከኃይሌ ገብረሥላሴ፣ ቀነኒሳ በቀለ መልካም የሚባል የኦሊምፒክና የዓለም አቀፍ ውድድሮች ጀርባ ትልቅ ስም ማስመዝገብ ተችሏል፡፡

አምስተኛ ቀኑን በያዘው 15ኛው የዓለም አቀፍ አትሌቲክስ ሻምፒዮና ላይ የሜዳሊያ ሰንጠረዥ አንድ ወርቅ በአትሌት ገንዘቤ ዲባባ እንዲሁም ሁለት የነሐስ በማራቶን ሌሊሳ ዴሲሳና በሴቶች አሥር ሺሕ ገለቴ ቡርቃ አማካይነት ማስመዝገብ ቢቻልም በቀጣይ የአትሌቲክሱ ዕጣ ፋንታ ምን ላይ ሊወደቅ እንደሚችል የብዙዎች ሥጋት መሆኑ አልቀረም፡፡

የቀድሞ የኢትዮጵያ 10,000 እና 5,000 ሜትር አትሌት ገብረ እግዚአብሔር ገብረማርያም በቤጂንጉ የዓለም ሻምፒዮና ላይ የተመለከተው የአሥር ሺሕ ወንዶችና ሴቶች ውጤት ቅር እንዳሰኘው ለሪፖርተር ተናግሯል፡፡

እንደ አትሌት ገብረ እግዚአብሔር ገብረማርያም ገለጻ ከሆነ  የኢትዮጵያ አትሌቶች በተለይ በቡድን መሥራት ያለባቸውን ሥራ በደንብ እንዳልሠሩ የሚያመለክት ውጤት እንደሆነ ተናግሯል፡፡

በተጨማሪም በሴቶች ኬኒያዊቷ ቪቪያን ቼሮየት ወልዳ ተነስታ ማሸነፏ የሚደነቅና ኬንያውያን ምን ያህል ለውድድሩ ትኩረት ሰጥተው እንደተዘጋጁ የሚያሳይ እንደሆነም አክሏል፡፡

የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽንምም ከሥነ ልቦናና ከአየር ንብረት አንፃር በተገቢው መንገድ በማስረዳት ጉዳዩ ምን ዓይነት ትኩረትና ጥንቃቄ እንደሚያስፈልገው ቀደም ብሎ መሠራት እንደነበረበት አመልክቷል፡፡

የቀድሞ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን 5,000 እና 10,000 አሠልጣኝ አቶ ሁሴን ሼቦ አትሌቶቹ አንድ ላይ አለመሥራታቸውና በተለያዩ ሰዎች ማለትም ግማሽ በማናጀር፣ ግማሹ ደግሞ በግል በመሥራት የቡድን ሥራ ላይ እንደተቸገሩና በሌሎች ተፎካካሪዎች የበላይነት እንደተወሰደባቸው ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

ኢትዮጵያ የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና መዘጋጀት ከጀመረበት ጊዜ ጀምሮ በ15ቱም መሳተፏን አስታውሰው፣ በተፎካካሪዎች ለመጀመርያ ጊዜ ከኬንያ ውጪ በሆኑ ተፎካካሪዎች መበለጧ አዲስ ታሪክ እንደሆነም ገልጸዋል፡፡

በውድድሩ ጥሩ ልምድ ያላት ያለፈው ዓለም ሻምፒዮና የነሐስ ሜዳሊያ አሸናፊዋ በላይነሽ ኦልጂራና የወጣቶች ሻምፒዮናዋ አለሚቱ ሃሮዬ ከፍተኛ ግምት የተሰጣትን ገለቴ ቡርቃን ለማገዝ ከወንዶች ቡድን በተሻለ የቡድን ሥራ ሲሠሩ ተስተውለዋል፡፡

በዕለቱ የታየው የቡድን ሥራ ያለፉትን አረንጓዴ ጎርፎችን ቢያስታውሰንም ገለቴ ቡርቃ የወርቅ ሜዳሊያ ለኢትዮጵያ ማምጣት አልቻለችም፡፡

ገለቴ ቡርቃ እግር በእግር እየተከታተለች ውድድሩን መቆጣጠር ብትችልም ቶሎ አፈትልካ አለመውጣቷም ዋጋ አስከፍሏታል፡፡ በዚህ መሠረት ከኬኒያዊቷ የ2011 የርቀቱ ሻምፒዮና ቪቪያን ቼሪዮት ጋር በመታገል 31፡41፡77 በሆነ ሰዓት በመግባት ብር ሜዳሊያ ማጥለቅ ችላለች፡፡

የመጀመርያውን ወርቅ ማምጣት የቻለችው የ24 ዓመቷ ገንዘቤ ዲባባ በ1,500 ሜትር ውድድር ላይ ከዳዊት ሥዩም ጋር በመሆን ርቀቱን 4፡08፡09 በሆነ ሰዓት አጠናቃ የወርቅ ጥማት የነበረበትን የኢትዮጵያ ልዑካን ተስፋ እንዲሰንቅ አድርጋለች፡፡

ኢትዮጵያ ባለፉት ዓለም አቀፍ ሻምፒዮና ላይ ስትካፈል በጀግናው ኃይሌ ገብረሥላሴ አማካይነት ስቱትጋርት ላይ እ.ኤ.አ. 1993፣ ጉተንበርግ 1995፣ ሲቪላ አቴንስ 1997 እና 1999  እንዲሁም በጌጤ ዋሚ አቴንስ 1999፣ በደራርቱ ቱሉ አሥር ሺሕ ኤድመንተን 2001፣ በገዛኸኝ አበራ ማራቶን ኤድመንተን 2001፣ በጥሩነሽ ዲባባ 5,000 ሜትር ፓሪስ 2003፣ 10,000 ሜትር ሔልሲንኪ 2005፣ ያሸነፉበት ውድድር በስፖርት ወዳጆች ውስጥ ትልቅ ትውስታን ጥሎ አልፏል፡፡

እ.ኤ.አ. በ2013 በሞስኮ ሎዝንከ በተደረገው 14ኛው ዓለም አቀፍ አትሌቲክስ ሻምፒዮና ኢትዮጵያን ሦስት የወርቅ፣ አራት ነሐስና ሦስት የብር ሜዳሊያ በማምጣት ከዓለም ስድስተኛ በመሆን አጠናቃለች፡፡

በቻይና ቤጂንግ በመካሄድ ላይ ባለው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ላይ በተለያዩ ርቀቶች የሚወዳደሩ አትሌቶች ቀሪ ውድድሮች ይቀሩታል፡፡ ምንም እንኳ ትልቅ ተስፋ የተጣለበት ውጤት ተስፋ ቢያስቆርጥም ባለፉት ውድድሮች ላይ የታዩትን የወንዶች አሥር ሺሕና የሴቶች አሥር ሺሕ ክፍተቶች በማሻሻልና ካለፉት በአትሌቲክሱ ኢትዮጵያ ያላትን ዕውቅና ለማስጠበቅ ዛሬ የሚከናወኑት የ5,000 ሜትር ፍጻሜ ዮሚፍ ቀጀልቻ፣ ሀጎስ ገብረሕይወትና ደጀን ገብረመስቀልን የሚሳተፉበት ውድድር ይጠበቃል፡፡

እንዲሁም 1,500 ሜትር የወርቅ ሜዳሊያ አሸናፊዋ ገንዘቤ የምትሳተፍበት የ5,000 ሜትር ውድድርና በሴቶች ማራቶን ትርፊ ፀጋዬ፣ ማሬ ዲባባና ትዕግሥት ቱፋ የሚጠበቁ አትሌቶች ናቸው፡፡  

ኢትዮጵያ በዚህ የአትሌቲክስ ሻምፒዮና ላይ ያጣቸውን ውጤት በቀጣይ ፌዴሬሽኑ መሥራት ያለበትን የቤት ሥራ ለመመልከት ይረዳዋል ተብሎ ይታሰባል፡፡

ከዚህ ጋር በተያያዘ በኤድመንተን እ.ኤ.አ. 2001 ማራቶን አሸናፊ የነበረው ገዛኸኝ አበራ አትሌቲክሱ አሁን ካለበት ደረጃ የተሻለ ውጤት ለማምጣት ከፍተኛ የሆነ ፕሮጀክት ተቀርጾ መሠራት እንደሚገባውና ፌዴሬሽኑም ይህንን ለማሳካት ጠንክሮ በመሥራት ድሮ የነበረውን ታሪክ መመለስ አለበት ሲል አስተያየቱን ሰጥቷል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ያልተቃናው የልጆች የንባብ ክህሎት

አንብቦና አዳምጦ መረዳት፣ የተረዱትን ከሕይወት ጋር አዋህዶ የተቃና ሕይወት...

እንስተካከል!

ሰላም! ሰላም! ውድ ኢትዮጵያውያን ወገኖቼ እንዲሁም የሰው ዘር በሙሉ፣...

የሙዚቃ ምልክቱ ሙሉቀን መለሰ ስንብት

የኢትዮጵያ ዘመናዊ ሙዚቃ በ1950ዎቹ እና በ1960ዎቹ በኪነ ጥበባትም ሆነ...

‹‹ደስታ›› የተባለችው አማርኛ ተናጋሪ ሮቦት በሳይንስ ሙዚየም

‹‹እንደ ሮቦት ዋነኛው አገልግሎቴ ውስብስብ የሆኑ የቴክኖሎጂ ውጤቶችንና አሠራሮችን...