Monday, February 6, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊበፍሳሽ የሚፈተነው መርካቶ

በፍሳሽ የሚፈተነው መርካቶ

ቀን:

በአፍሪካ ትልቁ ክፍት ገበያ (Open Market) የነበረው መርካቶ ዛሬ የቀደሞ ገፅታው ተለውጧል፡፡ በፊት በዳሶችና ጉልት ንግድ ይደምቁ የነበሩ ቦታዎች በትልልቅ የገበያ ማዕከሎችና ሕንፃዎች ተተክተዋል፡፡ አንዳንድ ነጋዴዎች በሕንፃው ሲጠቀሙ፣ ሌሎች ደግሞ በቀድሞው ቦታቸው ይገኛሉ፡፡ መርካቶ ካሉበት ዘርፈ ብዙ ችግሮች መሠረተ ልማት አንዱ ነው፡፡ አብዛኛው የመርካቶ ክፍል ፍሳሽ ማስወገጃ ቦይ የለውም፡፡ በአንዳንድ ቦታዎች ላይም ፍሳሽ ተኝቶ ይታያል፡፡

ከዋናው አስፓልት ወደ ምናለሽ ተራ የሚወስደው መንገድ ላይ በዕድሜ የገፉ ሁለት እናቶች የበርበሬ ዛላ መድበዋል፡፡ በጎናቸው የሚያልፈውና መጥፎ ጠረን ካለው ፍሳሽ ለመሸሽ ሲሉም ፈንጠር ብለው ቆመዋል፡፡ በምናለሽ ተራ በርካታ ነጋዴዎች የሚገኙ ሲሆን፣ ፍሳሽ ያስቸገራቸውም መሬቱ እስኪደርቅ ዕቃቸውን ሳይፈቱ መጠበቅ ግዴታቸው ነው፡፡

ከምናለሽ ተራ ወረድ ብለው የሚገኙት ጭድ ተራና ሙቀጫ ተራ ልዩ ልዩ ብረታ ብረቶች በሚሸጡ ነጋዴዎች የተሞሉ ናቸው፡፡ የውስጥ ለውስጥ መንገዶቹም ከኮረኮንች የተሠሩ ሲሆን፣ ወጣ ገባ ይበዛቸዋል፡፡ አካባቢው ከሌሎቹ በተለየ በፍሳሽ ተበክሏል፡፡ የተቀናጀ የፍሳሽ ማስወገጃ ቦይም የለውም፡፡ ከየአካባቢው የሚመጣ ጎርፍም ከመንገዱ ላይ ተኝቷል፡፡ አካባቢውም በአስከፊ ጠረን ተበክሏል፡፡

ረባዳማውን የመንገዱን ክፍል ይዞ የሚጓዘው ፍሳሽ በመንገዱ መጨረሻ አንድ ጉድጓድ ውስጥ ይገባል፡፡ ከጉድጓዱ በላይም የወይዘሮ ዘይቱና ሐሰን የንግድ ቤት ትገኛለች፡፡ በወር 500 ብር በሚከፍሉባት ቤት ውስጥ መነገድ ከጀመሩ ሁለት ዓመታት አሳልፈዋል፡፡ ሙሉ ለሙሉ ከቆርቆሮ የተሠራችው ቤት ከማንኪያ አንስቶ በልዩ ልዩ ብረታ ብረቶች ተሞልታለች፡፡ እጅግ ጠባብ ስትሆን፣ ስፋቷ ከአንድ በአንድ ሜትር አይበልጥም፡፡ በአንዴ ከሁለት ሰው በላይ የመያዝ አቅም የላትም፡፡ ከየአካባቢው የሚመጣው ጎርፍ ወደ ውስጥ እንዳይገባ የበሩን ስር በእንጨትና በጨርቅ የሸፈኑ ቢሆንም በቤቱ ስር ከሚያልፈው መጥፎ ጠረን ማምለጥ አልቻሉም፡፡

ወይዘሮ ዘይቱና፣ መርካቶ ከመግባታቸው አስቀድሞ ምግብ ቤት ነበራቸው፡፡ ኑሯቸውም ደህና የሚባል ነበር፡፡ የባለቤታቸው ሕይወት ካለፈ በኋላ ግን ኑሮ እንደበፊቱ አልሆነላቸውም፡፡ ይቸገሩም ጀመረ፡፡ ምግብ ቤቱም እንደቀድሞው አላዋጣቸውም፡፡

ከዕለት ወደ ዕለት ኑሮ እየከበዳቸው የመጣው ወይዘሮዋም የዕለት ጉርሳቸውን ፍለጋ መርካቶ ገቡ፡፡ አሮጌ ብረታ ብረቶችን ከቆራሌው በመግዛትም ጥቂት አትርፈው መሸጥ ጀመሩ፡፡ በዚህ ሥራቸው በቀን እስከ 20 ብር የሚያገኙ ሲሆን፣ ኑሮን ለመግፋት ግን በቂ አልነበረም፡፡ ተጨማሪ ሥራ በመሥራት ገቢያቸውን ይደጉማሉ፡፡ አካባቢውን በማፅዳት የተወሰነ ገንዘብ ያገኛሉ፡፡ የሚሠሩበት ቦታ ለጤና ጠንቅ ቢሆንም፣ የተሻለ ቦታ ለመከራየት ግን አቅማቸው አይፈቅድም፡፡

የብዙ ባለሀብቶች መፍለቂያ እንደሆነ የሚነገርለት መርካቶ፣ በርካታ ድሆችም ይገኙበታል፡፡ ለንግድ ዓይነተኛ ስፍራ ሲሆን በአካባቢው ቦታ ለማግኘትም ከባድ ነው፡፡ ለዚህም በርበሬ ተራ አካባቢ ከወራት በፊት በካሬ ሜትር 350,000 ብር የተሸጠው ቦታ ምስክር ነው፡፡ የረዥም ጊዜ ታሪክ ያለው መርካቶ፣ ጥቂት የማይባሉ ሥራ ፈጣሪዎች እንደሚገኙበትም ይነገራል፡፡

ይሁን እንጂ በሀብታምና በደሀው ነጋዴ መካከል የተጋነኑ ልዩነቶች መኖራቸውን ብዙዎች ይናገራሉ፡፡ ልዩነቱም ገፅታዋ በተቀየረው መርካቶ ደሀ ነጋዴዎችን ከሥራ ውጪ እንዳያደርጋቸው ሥጋት ፈጥሯል፡፡

አዲስ የተገነቡት የገበያ ማዕከሎች አቅም የሌላቸው ነጋዴዎችን ያላገናዘቡ ከመሆናቸው ባሻገር፣ ታሪካዊ ይዘቱን እንዲያጣ አድርጎታል የሚሉ አሉ፡፡ መርካቶ የነበረው ቅርፅ ሳይለውጥ እንዴት ማሳደግ ይቻላል? በሚል ርዕሰ ጉዳይ ላይም ከጥቂት ሳምንታት በፊት በሳሮማሪያ ሆቴል ውይይት ተደርጎ ነበር፡፡

ውይይቱን ያዘጋጀው ኖህ ማርኬቲንግ ሲሆን፣ የተለያዩ ባለድርሻ አካላት ተገኝተው ነበር፡፡ የኖህ ማርኬቲንግ ባለቤት አቶ በላይ ጨብሲ ሲሆኑ፣ ከዓመታት በፊት መርካቶን ለማልማት ተዋቅሮ የነበረው ግብረ ኃይል አባል እንደነበሩ ይናገራሉ፡፡

እሳቸው እንደሚሉት፣ ከዓመታት በፊት ተቋቁሞ የነበረው ግብረ ኃይል መንግሥትና ነጋዴውን በማስተባበር መርካቶን የማልማት ዓላማ ያነገበ ነበር፡፡ በወቅቱ የተለያዩ ግዴታዎቹን ለመወጣትም ሞክሯል፡፡ ‹‹ከዛሬ 15 ዓመታት በፊት የነበረው ትልቅ ችግር ፅዳት ሲሆን መንገድና የፓርኪንግ ቦታ እጦትም ተጠቃሽ ናቸው፡፡ በወቅቱ ግብረ ኃይሉ ከተክለሃይማኖት እስከ ሰባተኛ አካባቢ የነበረውን የፅዳት ችግር ለመቅረፍም ችሎ ነበር፡፡ አካባቢውን በአረንጓዴ ለመሸፈን በተደረገ ጥረትም፣ ልዩ ልዩ አበቦችና ባህር ዛፎች ተክለናል›› በማለት የግብረ ኃይሉን ተግባር ይገልጻሉ፡፡

በአሁኑ ወቅት ግብረ ኃይሉ መፍረሱን የገለጹት አቶ በላይ፣ መርካቶ ዘርፈ ብዙ ችግሮች እንዳሉበት ይናገራሉ፡፡ ‹‹ኦፕን ማርኬት መሆኑ ቀርቷል፡፡ በሕንፃዎች ተተክቷል፡፡ ሕንፃዎቹም በዘፈቀደ የተገነቡ ሲሆን፣ ብዙዎቹም በአልሙኒየም ያጌጡ ናቸው፡፡ ይህም የቦታውን ታሪካዊ ይዘት የሚያሳጣ ነው፡፡ በሕንፃ መተካቱ የግድ አስፈላጊ ከሆነም ቅርፁን በአገሪቱ በሚገኙ ታሪካዊ ሕንፃዎች ማድረግ ይቻል ነበር›› ሲሉ የተገነቡት ሕንፃ ቅርፆች የአገሪቱን ቁሳዊ ባህል የማይወክሉ መሆናቸውን ይገልጻሉ፡፡

እንደእሳቸው ገለፃ፣ የመርካቶ ዕድገት ትንንሽ ነጋዴዎችን ያማከለ ሊሆን ይገባል፡፡ ‹‹ልማት ፎቅ ብቻ አይደለም›› የሚሉት አቶ በላይ፣ መርካቶ በትንንሽ ንግድ ተሠማርተው የነበሩና በኋላ ትልቅ ባለሀብቶች የሆኑ ማፍራት እንደቻለ ያስታውሳሉ፡፡ የዛሬው መርካቶም መሰል ባለሀብቶችን የማፍራት አቅም ሊኖረው እንደሚገባና የተሟላ መሠረተ ልማት እንደሚያስፈልግ፣ ለዚህም መንግሥትና ነጋዴው በመተባበር ሊገነቡ እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡

የአውሮፓ አገሮች መርካቶን የመሳሰሉ ታሪካዊ የንግድ ስፍራዎች አሏቸው፡፡ ብዙዎቹም በነበሩበት ይዘት ላይ የሚገኙ ሲሆን፣ ዕድሳትና ልማት ሲያስፈልጋቸውም ይዘታቸውን ሳይለቁ እንደሚታደሱ አቶ በላይ ይገልፃሉ፡፡ መርካቶ አንዱ የቱሪስት መስህብ ሲሆን፣ ከዓመታት በፊት 16 በመቶ የሚሆነው ከቱሪዝም የተገኘው ገቢ ከመርካቶ ይመነጭ እንደነበር ይናገራሉ፡፡ ይሁን እንጂ ዛሬ ላይ ያለው የመርካቶ ገፅታ በዘርፉ የሚገኘውን ገቢ እንደሚቀንስ ተናግረዋል፡፡

በውይይቱ መርካቶ ታሪካዊ ይዘቱን ሳይለቅ የሚያድግበትን መንገድ፣ የተቀናጀ የፍሳሽ ማስወገጃ ቦይ በመሥራት ለማረጋገጥ ከስምምነት ላይ ደርሰዋል፡፡ በዕለቱ ከጀርመን የመጣ የግንባታ ድርጅት መርካቶ ስለሚያስፈልገው የፍሳሽ ማስወገጃ ቱቦዎችም ገለፃ አድርጓል፡፡

ዶ/ር ተባረክ ልካ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በጂኦግራፊ ዲፓርትመንት የከተማ ልማት ትምህርት (Urban Development) መምህር ናቸው፡፡ በቅርቡም ትኩረቱን በመርካቶ ዙሪያ ያደረገ ጥናታዊ ጽሑፍ ሠርተዋል፡፡ በዋናነትም በመርካቶ የሚገኙ ልዩ ልዩ ንግዶች እንዴት መያዝ እንዳለባቸው ይገልፃሉ፡፡ መርካቶ ሀብታምና ድሀው ነጋዴ የሚተዳደሩበት እንደመሆኑ የግብይት ስፍራውን በትልልቅ የገበያ ማዕከሎች መተካት ተገቢ አይደለም ይላሉ፡፡ በሕንፃው መጠቀም የሚችሉት አቅሙ ያላቸው ብቻ ሲሆኑ፣ አቅሙ የሌላቸውን ከመጠቀም እንደሚያግዳቸው ይናገራሉ፡፡ ‹‹አሁን እየሄድን ያለንበት መንገድ ያስፈራል›› የሚሉት ዶክተሩ፣ መርካቶ የደሀው መተዳደሪያ መሆኑ እየቀረ እንደሆነ ይናገራሉ፡፡

በመርካቶ በርካታ ትንንሽ ነጋዴዎችና ሥራ ፈጣሪዎች ይገኛሉ፡፡ ብዙዎቹም ከእጅ ወደ አፍ የሆነ ኑሮ የሚገፉ ሲሆን፣ እነሱን ያላማከለው ልማት ብዙዎቹን ለሥራ አጥነት እንደሚዳርጋቸው ያስረዳሉ፡፡ በአካባቢው የሚታዩ የመሠረተ ልማትና ሌሎችም ማኅበራዊ ችግሮችን ለመቅረፍም የአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ የኮንስትራክሽንና ቤቶች ልማት ጽሕፈት ቤት የበኩሉን እየሠራ ይገኛል፡፡ ወይዘሮ ፍሬሕይወት ተስፋዬ የክፍለ ከተማው የኅብረተሰብ ተሳትፎ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ናቸው፡፡

እንደእሳቸው ገለፃ፣ ክፍለ ከተማው አሥር ወረዳዎች ሲኖሩት ማኅበረሰቡን በማወያየትና ያለበትን ችግር ነቅሶ በማውጣት መፍትሔ የሚሰጡበት አሠራር ይከተላሉ፡፡ በዚህም ለተወሰኑ ወረዳዎች የፍሳሽ ማስወገጃ ቱቦ ቀበራ ተሠርቷል፡፡ ይህም በሕዝቡ ተሳትፎና መንግሥት በሚሰጠው 35 በመቶ ማበረታቻ ድጋፍ የተሠራ ነው፡፡ በ2007 በጀት ዓመትም ከነጋዴው 62 ሚሊዮን ብር በማሰባሰብ መፀዳጃ ቤቶች፣ ኩሽና፣ መታጠቢያ ቤቶች ለመሥራትም ተችሏል፡፡

ይሁን እንጂ በወረዳ አንድ ምናለሽ ተራ እና አንዳንድ አካባቢዎች ላይ የታቀደውን ያህል ለውጥ ማምጣት አልተቻለም፡፡ ለዚህም ‹‹በዚህኛው ዓመት ትኩረታችንን የአሜሪካን ግቢ ላይ አድርገን ስንሠራ ነበር፤›› በማለት በቀጣይ ምናለሽ ተራ አንዱ የትኩረት አቅጣጫ መሆኑን ይናገራሉ፡፡

ዕቅድ የሚመነጨው ከቀጣናና ከመንደር ነው የሚሉት ወይዘሮ ፍሬሕይወት፣ በ2008 በጀት ዓመት ለመሥራት የታቀደው ነገር እንዳልደረሳቸው ገልጸዋል፡፡ ይሁን እንጂ ካለው የፍሳሽ ማስወገጃ ችግር አንፃር 20 ኪሎ ሜትር በላይ የፍሳሽ ማስወገጃ የቱቦ ቀበራ በየወረዳዎቹ ሊሠራ እንደሚችል ግምታቸውን ተናግረዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንና የመንግሥት ውዝግብ

የጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) መንግሥት ባለፉት አራት ዓመታት...

የኢትዮጵያ ካፒታል ገበያ ምሥረታ ዝግጅቶችና ከገበያው የሚጠበቁ ዕድሎች

ኢትዮጵያ ከ50 ዓመት በኋላ ዳግም የምታስጀምረውን የካፒታል ገበያ ዘመኑን...

አዲሱ የብሔራዊ ባንክ ገዥ ትኩረት የሚያደርጉባቸውን ቀዳሚ ጉዳዮች ይፋ አደረጉ

አዲሱ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥ ትኩረት አድርገው የሚሠሩባቸውን ቀዳሚ...

መንግሥት የደቡብ ሱዳን ታጣቂዎች ድንበር ጥሰው የሚያደርሱትን ጥቃት እንዲያስቆም ተጠየቀ

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውጭ ግንኙነትና የሰላም ጉዳዮች ቋሚ...