‹‹ሁሉም ነገር ያልፋል፤ ቅያሜዬና ቁስሌ ሁሉ ሽሯል፤ ያሰሩኝንና የደበደቡኝን ሁሉ ይቅር እላቸዋለሁ፤ አሁን ነፃ ነኝ፤ ቀለልና ዘና ያለ ስሜት ይሰማኛል፤›› ይህ ጽሑፍ ከአማኑኤል የአዕምሮ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ሕመምተኞች መካከል በአንዱ የተጻፈ ነው፡፡ ጽሑፉ የሰፈረው በልሙጥ ወረቀት ላይ በእንግሊዝኛ ቋንቋ ሲሆን፣ ወደ አማርኛ መልሰነዋል፡፡
ባለፈው ሳምንት በሒልተን አዲስ ሆቴል ‹‹በመስመር ውስጥ›› የተሰኘ የሥዕል ዐውደ ርዕይ ተዘጋጅቶ ነበር፡፡ ዐውደ ርዕዩ በሆስፒታሉ የሚታከሙ ከ60 በላይ የአዕምሮ ሕሙማን የሠሯቸው ሥዕሎች ለዕይታ የበቁበት ሲሆን፣ ሌሎች ጽሑፎችን ያሰፈሩ ታካሚዎችም ነበሩ፡፡
‹‹ታሪኬ በጣም ያሳዝናል፤ ምስኪን ደሃ ነኝ፤ አገሬን እወዳለሁ፤ ባንዲራዬንም፤›› ከጽሑፎቹ አንዱ ነው፡፡ የሕክምና ባለሙያዎች ለአዕምሮ ሕሙማን ፈውስ እንዲረባረቡ የሚጠይቅ ጽሑፍ ከሥዕል ጋር ያቀረበ ሕመምተኛም ተጠቃሽ ነው፡፡ ሥዕሎቹ ሕሙማኑ በተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮች ዙሪያ ያላቸውን ምልከታ ያንፀባርቃሉ፡፡ በሥራዎቻቸው የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ፣ ተፈጥሮአዊ አካባቢዎችና ሰዎች በተደጋጋሚ ይስተዋላሉ፡፡
የአዕምሮ ሕሙማኑ ላለፉት ሰባት ወራት በሠዓሊ ይድነቃቸው ሙሉጌታና ሠዓሊት ሰብለ ወልደአማኑኤል ሥልጠና ወስደዋል፡፡ ሠዓሊያኑ ከሕክምና ባለሙያዎች ጋር በመተባበር በሳምንት ሦስት ቀን በሆስፒታሉ እየተገኙ ሕሙማኑ ራሳቸውን በሥነ ጥበብ እንዲገልጹ አርት ቴራፒ የሰጧቸው ሲሆን፣ በስተመጨረሻ የሕሙማኑን ሥራዎች አሰባስበው ለሕዝብ ዕይታ አቅርበዋል፡፡
አርት ቴራፒ (የሥነ ጥበብ ሥራዎችን በመጠቀም ሕክምና መስጠት) በተቀረው ዓለም ቢለመድም፣ ኢትዮጵያ ውስጥ በስፋት ተሠርቶበታል ማለት የሚያስደፍር ነገር የለም፡፡ ሙዚቃ፣ ሥነ ጽሑፍ፣ ሥዕል፣ ዳንስና ሌሎች የኪነ ጥበብ ዘርፎች ከተለመደው አሠራር ውጪ ለሕሙማን ተደራሽ የሆኑበት አጋጣሚም አናሳ ነው፡፡ አርት ቴራፒ የአዕምሮ ሕመምተኞች በፈጠራ ሥራዎች ራሳቸውን እንዲገልጹ፣ ከጭንቀት ዕፎይታ እንዲያገኙ ይረዳል፡፡ አርት ቴራፒ ሕሙማን የሚገኙበትን አዕምሯዊ ሁኔታ በማንፀባረቅ ለሕክምና ሒደት አጋዥ እንደሆነና በተለያየ ዓይነት የአዕምሮ ሕመም ለሚሰቃዩ ግለሰቦች ሕክምናም ከፍተኛ አስተዋጽኦም እንዳለው ይገልጻል፡፡
ሠዓሊያኑ አርት ቴራፒ ኢትዮጵያ ውስጥ በስፋት አለመሰጠቱንና ቢሰጥ ያለውን ጠቀሜታ ከግምት ውስጥ በማስገባት ወደ አማኑኤል እንዳመሩ ሠዓሊ ይድነቃቸው ይናገራል፡፡ ‹‹ለዓመታት ለራሳችን ለፍተናል፤ ከእኛ አልፈን ደግሞ ለሌሎች በጎ እናድርግ በማለት ነበር ወደ ሆስፒታሉ ያቀናነው፤›› በማለት ይገልጻል፡፡ የአዕምሮ ሕሙማንን ለማከም ሥነ ጥበብን እንደ አማራጭ መውሰድ ያለውን ጠቀሜታ ይናገራል፡፡
ሥልጠናውን ሲጀምሩ፣ ከሕሙማኑ መካከል ‹‹እስከዛሬ ለምን ዘገያችሁ?›› የሚል ጥያቄ የሰነዘሩ ነበሩ፡፡ ይድነቃቸው ይህ አስተያየት ሲደርሰው የተሰማውን ስሜት ያስታውሳል፡፡ ‹‹በወቅቱ በጀመርነው እንቅስቃሴ ደስተኛ ብሆንም እጅግ እንደዘገየን ተሰምቶኛል፤›› ይላል፡፡
በሥልጠናው ሕሙማኑ መደሰታቸውን ይገልጹ እንደነበር ይናገራል፡፡ ሕሙማን አዕምሮአቸውን የሚያፍታቱበት አጋጣሚ አናሳ እንደሆነና አርት ቴራፒው ስሜታቸውን ያለምንም ገደብ እንዲገልጹ እንደረዳቸው ያምናል፡፡
ሥልጠናው ስድስተኛ ወሩን ካገባደደ በኋላ ይድነቃቸውና ሰብለ 35 ሠዓሊያን ሆስፒታሉን እንዲጎበኙና ለሕሙማኑ ሥልጠና እንዲሰጡ ጋብዘዋል፡፡ የሥነ ልቦና እንዲሁም የሥነ ጥበብ ተማሪዎችም ተጋብዘው ነበር፡፡
ይድነቃቸው እንደሚለው፣ ሆስፒታሉ ለአርት ቴራፒ በጀት መድቦ በቋሚነት እንዲሰጥ በተለያየ የሙያ መስክ የተሰማሩ ግለሰቦች ስለጉዳዩ ግንዛቤ ሊኖራቸው ይገባል፡፡ ባለሙያዎችን ወደ ሆስፒታሉ የጋበዙበት ምክንያትም ለተሳትፎ ለማነሳሳት ነው፡፡ ከጋበዟቸው ሠዓሊያን መካከል ሥዕሎቻቸውን ሸጠው የገንዘብ ድጎማ ለማድረግና ሥልጠና ለመስጠትም ፈቃደኛ የሆኑ ሙያተኞች ማግኘታቸውን ያስረዳል፡፡
የአዕምሮ ሕሙማኑ ሥራዎች ለሕዝብ ዕይታ በመብቃታቸው የተሰማውን ደስታ የሚገልጸው ሠዓሊው፣ አርት ቴራፒ በሥዕልና የአዕምሮ ሕመም ብቻ መወሰን እንደሌለበትም ይናገራል፡፡ ‹‹ሁላችንም በሙያችን አስተዋጽኦ ማድረግ አለብን፤ አርት ቴራፒን ለሌሎችም ሕመምተኞች መዋል ይቻላል፤ በጅማሮአችን ደስተኛ ብንሆንም በቂ ነው ማለት አይደለም፤›› ይላል፡፡
የአማኑኤል ሆስፒታል ዋና ሥራ አስኪያጅ፣ የሥነ አዕምሮ ስፔሻሊስት ዶ/ር ዳዊት አሰፋ እንደሚናገሩት፣ አርት ቴራፒ ከአዕምሮ ሕክምና ዘዴዎች አንዱ ሲሆን፣ ሥነ ጥበብ ሕሙማን ራሳቸውን የሚገልጹበት አንድ መንገድ ነው፡፡ ሆስፒታሉ በአርት ቴራፒ (በቴአትርና ሥነ ጽሑፍ ዘርፍ) መንቀሳቀስ የጀመረው ከሁለት ዓመት በፊት ነበር፡፡ በሆስፒታሉ በበጎ ፈቃደኞች የተቋቋመ የቴአትር ቡድን ይገኛል፡፡ አስተባባሪው አርቲስት ፋሲል ግርማ ሲሆን፣ ቡድኑ ‹‹ጉዞ ለአዕምሮ ጤና›› በሚል በ11 ከተሞች እየተዘዋወረ ቴአትሮችን አቅርቧል፡፡ ቡድኑ ጎዳና የወደቁ የአዕምሮ ሕሙማንን ወደ ሆስፒታሉም ያመጣል፡፡ ለሆስፒታሉ ሙያዊ እገዛ ከሚያደርጉ መካከል ገጣሚ ዮሐንስ ሞላና ደራሲ እንዳለጌታ ከበደ ይጠቀሳሉ፡፡
ዶ/ር ዳዊት ፣‹‹ኪነ ጥበብና የአዕምሮ ሕክምናን ለማቀናጀት ጥረት እያደረግን ነው፤ ዘርፉ ለሕክምና ካለው አስተዋጽኦ በተጨማሪ ከኅብረተሰቡ ጋር የተሻለ ቅርርብ ይፈጥራል፤›› ይላሉ፡፡ በተለያየ የሕመም ደረጃ ላይ የሚገኙ ግለሰቦችን ያዳረሰው የሥዕል ሥልጠናው፣ በሕሙማኑ ጤና ላይ መሻሻል እንዳሳየም ያክላሉ፡፡
አያይዘውም ከአዕምሮ ሕክምና ባለመያዎች ጎን ለጎን በተለያየ ሙያ የተሰማሩ ግለሰቦች ቢሳተፉ አመርቂ ውጤት እንደሚመጣ ይገልጻሉ፡፡ ለአዕምሮ ሕመምተኞች ማንኛውንም ሰው ዕገዛ ማድረግ እንደሚችል በመጠቆም፣ ሆስፒታሉ ከሕዝብ ጋር የሚገናኝባቸውን መንገዶች የማስፋት ዕቅድ እንዳላቸው ይናገራሉ፡፡
ዶ/ር ዳዊት በአርት ቴራፒ ዙሪያ ፈተናዎች እንደሚገጥሟቸውም ይናገራሉ፡፡ ዋነኛ የሚሉት የገንዘብ እጥረትን ነው፡፡ አስፈላጊ ግብዓቶችን ለማሟላት የመንግሥት በጀት በቂ አይደለም፡፡ ዕርዳታ የሚያደርጉላቸው ግለሰቦች ቢኖሩም ወጪያቸውን ሙሉ በሙሉ አይሸፍንም፡፡ የሥዕል ዐውደ ርዕይ መዘጋጀቱ ገንዘብ ለማሰባሰብ እንደሚረዳቸውና ገቢው ለአርት ቴራፒ እንደሚውል አያይዘው ይገልጻሉ፡፡
ሥልጠናውን ከሠዓሊ ይድነቃቸው ጋር የሰጠችው ሠዓሊት ሰብለ ከዚህ ቀደም ለዓይነ ሥውራን አርት ቴራፒ ሰጥታለች፡፡ ሥነ ጥበብ መድኅን የሚሆናቸው ሕሙማን እንደሚኖሩ ትናገራለች፡፡ ጥበብ ለሁሉም መዳረስ አለበት የምትለው ሠዓሊቷ፣ የሥነ ጥበብ ተማሪዎች እንዲሁም ሠዓሊያን አስተዋጽኦ ቢያበረክቱ በአጭር ጊዜ ለውጥ እንደሚመጣ ታምናለች፡፡
የአርት ቴራፒ አልጋ በአልጋ እንዳልሆነ ከዶ/ር ዳዊት ጋር ትስማማለች፡፡ ስለዘርፉ ግንዛቤ ያላቸውና ለመሳተፍ ፈቃደኛ የሆኑ ጥቂት እንደሆኑ ትጠቅሳለች፡፡ ስለ አርት ቴራፒ ፍቱንነት ጥያቄ የሚያነሱም አሉ፡፡ ሰብለ ግን በሌሎች አገሮች በአርት ቴራፒ የተመዘገበው ለውጥ በኢትዮጵያም ዕውን እንደሚሆን ተስፋ ታደርጋለች፡፡ ሥልጠናውን ሲሰጡ ከጊዜ ወደ ጊዜ በሕሙማን ላይ ለውጥ እንዳስተዋለችና የሕክምና ባለሙያዎች በበለጠ ለሕክምና ሊገለገሉበት እንደሚችሉ ታክላለች፡፡
እሷ እንደምትለው፣ ባለሙያዎች ሲበራከቱ የአርት ቴራፒ ቀጣይነት ይረጋገጣል፡፡ ‹‹አርት ቴራፒ ስለአዕምሮ ሕሙማን ያለውን ግንዛቤ በመለወጥ ረገድ አንድ ዕርምጃ ነው አሁንም ግን ብዙ ይቀራል፤ ሁሉም ባለድርሻ አካላት ቢረባረቡ ሥልጠናው ሰባት ወር ሙሉ ላይወስድም ይችላል፤›› ትላለች በጉዳዩ ላይ ሁሉም አካል ኃላፊነት እንዳለበት ስትገልጽ፡፡
ሌላው አስተያየት ሰጪ ቃልኪዳን አድማሱ ክሊኒካል ሳይኮሎጂስትና በአማኑኤል ሆስፒታል የተሀድሶ ሕክምና ክፍል አስተባባሪ ነው፡፡ በተሀድሶ ሕክምና ክፍል (ሪሀብሊቴሽን ሴንተር) ውስጥ ኦክፔሽናል ቴራፒ (የሥራ ሕክምና)፣ ሪክሬሽናል ቴራፒ (የመዝናናት ሕክምና) እና (ሳይኮ ቴራፒ) የጋራ ምክክር ሕክምና ክፍሎች ይገኛሉ፡፡ በሪክሬሽናል ቴራፒ ዘርፍ ሙዚቃ፣ ሥዕል፣ ዳንስና ድራማ ይገኛሉ፡፡ እሱ እንደሚለው፣ ሕመምተኞች ወደዚህ ክፍል ከመጡ በኋላ የማዕከሉ ባለሙያዎች ለአርት ቴራፒ ብቁ የሆኑትን መርጠው ነው ሥልጠናውን የጀመሩት፡፡
‹‹አርት ቴራፒ ታማሚዎች ስሜታቸውንና አስተሳሰባቸውን የሚገልጹበት ሲሆን፣ ለእኛ ደግሞ ስለባህሪያቸው፣ ስላለፉበት መንገድ፣ ስለሚገኙበት ሁኔታና ስለወደፊት ዓላማቸው የሚያሳውቀን ነው፡፡ የሚሥሉት ሥዕል ከሕይወት ገጠመኞቻቸው ጋር ተቀናጅቶ የሚገኘው ምላሽ ለሐኪሞች ግብዓት ይሆናል፤›› ይላል፡፡
አማኑኤል ክኒን ላይ ብቻ ያተኮረ ሆስፒታል ተደርጎ እንደሚወሰድና ይህ ጅማሮ ሕክምናው በተለያየ መንገድን እንደሚሰጥ እንደሚያሳይ ይገልጻል፡፡ ለአዕምሮ ሕክምናና ለሕሙማኑ አነስተኛ ግምት በሚሰጥበት አገር ስለ አርት ቴራፒ መበልፀግ ማውራት ቢከብድም፣ አመለካከቱን በመቀየር በተለያየ የሙያ መስክ የተሰማሩ ባለሙያዎችን ማሳተፍ እንደሚገባ ይናገራል፡፡
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የአዕምሮ ሕክምና መምህርና ሐኪም ዶ/ር መስፍን አርዓያ ሆስፒታሉ ቀድሞ የነበረውን የሕክምና አሰጣጥ አሁን ካለው ጋር ያነጻጽራሉ፡፡ ከጣልያን የአምስት ዓመት ቆይታ በኋላ በቀድሞው የአገር ግዛት ሚኒስቴር የተቋቋመው ሆስፒታሉ፣ ለዓመታት ሕክምና የሚሰጠው በውጪ ባለሙያዎች ነበር፡፡ ሕሙማን ወደ ሆስፒታሉ ከገቡ በኋላም በፍጥነት አይወጡም ነበር፡፡
በተለይ ከ1980ዎቹ በኋላ በዘርፉ አገልግሎት የሚሰጡ ኢትዮጵያውያን ባለሙያዎች ከመብዛታቸው ባሻገር፣ አርት ቴራፒን የመሰሉ መንገዶች መጀመራቸው በሕክምናው የታየ ለውጥ እንደሆነ ይናገራሉ፡፡ ‹‹ከ30 ዓመታት በፊት በጣት የምንቆጠር ሐኪሞች ነበርን፡፡ ዛሬ ቁጥሩ ጨምሯል፤ የኪነ ጥበብ ሰዎችም እየተሳተፉ ነው፤ ይህ ደግሞ የሕሙማኑን መገለል ይቀርፋል፤›› ይላሉ፡፡
በአዕምሮ ሕክምና ዘርፍ የሚያገለግሉ ባለሙያዎች ከመብዛታቸው ጎን ለጎን በመጠኑም ቢሆን በየአካባቢው በአዕምሮ ሕመም የሚሰቃዩ ግለሰቦችን ለመድረስ ተችሏል ይላሉ፡፡ መቐለ፣ ሐረር፣ ሐዋሳና ጅማ የአዕምሮ ሕክምና ከሚሰጥባቸው አካባቢዎች ጥቂቱ ናቸው፡፡ ቀድሞ ከተለያዩ አካባቢዎች ወደ አማኑኤል ታስረው የሚመጡና በሆስፒታሉ የሚቀሩ ሕሙማን ነበሩ የሚሉት ዶክተሩ፣ አሁን ለውጥ ቢኖርም ችግሩ ሙሉ በሙሉ አለመቀረፉን ይገልጻሉ፡፡ በአዕምሮ ሕመም የሚሰቃዩና አዳማጭ ያጡ እንዳሉ በመጠቆም፣ ወደ ሕክምና መወሰድ እንዳለባቸው ያክላሉ፡፡
ባለፉት ጊዜያት የነበሩ የጥበብ ሥራዎች የአዕምሮ ሕሙማንን ከግምት ያስገቡ እንዳልነበሩ አስታውሰው፣ ጅማሮዎች እንዲጠናከሩ ያሳስባሉ፡፡ በተለይም ከከተማ ውጪ ያሉ ሕሙማንን ለመድረስ ያላሰለሰ ጥረት መደረግ እንዳለበት ይናገራሉ፡፡ ዶ/ር መስፍን፣ ‹‹አዕምሮ ከሰውነት ክፍል ክቡሩ ነውና እንክብካቤ ያስፈልገዋል፤ የአዕምሮ ሕመም በማንም ላይ ሊደርስ የሚችል በመሆኑ ሁሉም በየሙያው ቢያግዝ መልካም ነው፤›› የሚል መልዕክትም ያስተላልፋሉ፡፡