Tuesday, December 5, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

በሩን ገርበብ አድርጉት?

እነሆ ከካዛንቺስ ወደ አራት ኪሎ ልንጓዝ ነው። ዛሬም እንንገላወዳለን። ‘ጎዳናው መንገዱ…’ እያለ በሆዱ የሚያዜመው በሐሳብ ተጠምዶ ይነካዋል፡፡ ማንን? መንገዱን፡፡  ‘እከሌን ምሰል፣ እንደ እከሌ ካልሆንክ’፣ ‘እንደ እከሊት ካልተዳርሽ ካልከበድሽ’ እየተባልን፣ የሆኑትን ለመምሰል በምንደፋፈርበት የ‘ሞዴሎች’ ምድር ያሰቡልንን መንገድ ዛሬም ያለመታከት ይዘነዋል። አጥብቀው ያሰሩልን ሸክም የት ፌርማታ ስንደርስ ፈተን አውርደን እንደምንጥለው አናውቅም። የራሳችን ያልሆነውን ዛሬም በባአለ አደራነት በጫንቃችን ተሸክመን አላወረድነውም። እንዳንመለስ ‘ይህ የእኔ አይደለም! ይህ ያንቺ አይደለም!’ እንዳንባባል፣ ‘አጥብቆ ያሰረ ዘቅዝቆ ይሸከማል’ የሚል ሸባቢ የተረት ዘብ አስቀምጠውብናል። ማጥበቃችንን እንጂ አስተሳሰራችንን እንዳናጠና፣ ጆንያችን መሙላቱን እንጂ በምን እንደሞላናው እንዳናስተውል ያደረገን፣ ይህ ሸክም አበረታች ተረት እንደሆነስ ማን ያውቃል?

ሲተረክ ዘበት መሳዩ ኑሯችን ከጫፍ እስከጫፍ ቢበጠር ያለፈቃዳችን የተሸከምናቸው አቁማዳዎች ስብስብ ነው። ይህን አስበው አንዳንድ አፈንጋጮች ‘ዘራፍ’ ሲሉ ‘ማንም ያሰበውን የሆነ የፈለገውን ያገኘ የለም’ በምል አፅናኝ መሳይ፣ በስውር ከንቱነትን ባነገተ ንግግር ወደ ቦታው ይመለሳል። ‘ልማት ከማሰብ ይጀምራል’ ብለው የሚሟገቱልን የንቃተ ህሊናችን ማነስ ተቆርቋሪዎች ሳይቀሩ ደጋግመው በዚህ አዙሪት ውስጥ ሲገኙ ስናይ ደግሞ ወደለመድነው የኮከብ ቆጣሪነት ኑሮ ገብተን እንደበቃለን። በተደበቅንበት ጎሬ ‘ሕይወት እንደ ማራቶን ናት’ ሲባል እንሰማና ‘ሞት ካልወሰደን በቀር 42 ኪሎ ሜትር አትሞላም ማለት ነው?’ እየተባባልን መሽቶ ይነጋል። እንግዲህ እንዲህ እንደዛሬ ጥቂት ለመራመድ፣ ጥቂት ስለልማት ለማሰብ፣ ጥቂት ስለዕድገት ለመከራከር፣ ጥቂት ስለለውጥ ለማውጠንጠን ደግሞ በፈንታው በነገዎቻችን ውስጥ ተስፋ አላስቀምጠን ይላል። ‘ለምን እንራመዳል? ለምን ለታክሲ እንሠለፋለን?’ እያልን ዝለን ሳንጨርስ በ‘እነማን ያውቃል የነገን?’ በእነ ‘መሰንበት ደጉ’ በእነ ‘እንገናኛለን ጤና ሰላም ካለ፣ የሞተ ተጎዳ መቃብር ውስጥ ያለ’ ግፊት ተስፈንጥረን፣ ለሚቀጥለው ፌርማታ እንራኮታለን። “አዳራሹ ሰፊ በሩ አልጠበባችሁ፣ በተራ በተራ ምነው መግባታችሁ?” ብሎ ጥያቄውን በቅኔ ለሚያርብ መልሱ የመሰንበት ተስፋ አይመስላችሁም?

ጉዟችን ተጀምሯል። ወያላው የሚደገፋት መቀመጫ ላይ እንዳመጣላቸው የሚናገሩ ገራገር እናት ተሰይመዋል። እንደነገሩ ሸብ ያደረጓትን ወደ መሀል አናታቸው የሸሸች ሻሽ እያስተካከሉ ይበሰጫጫሉ። ከእሳቸው ንጭንጭ ደግሞ የወያላው ይብሳል። “ቆይ እኔምለው ብለን ብለን ጫት ‘ኢምፖርት’ ማድረግ ጀምረናል እንዴ? ነው ቅጠሉም እንደ ሰው መሬቱ ያመነምነው ጀመር? ይህቺ አሁን የመቶ ብር ናት ሲባል መቶ ብር ጆሮ ቢኖረው ሱባዔ አይገባም?” ይላል። አጠገቤ የተቀመጡት እናት ቀበል አድርገው፣ “ኧረ ዝም በል አንተ። አታፍርም? እውነት መቶ ብር ቢሰማ በአንተ ነው በእሱ (ጫት ላለማለት ከብዷቸው) ሱባዔ የሚገባው? ንገረኛ በል። ኑሮ ኑሮ ከማለት ሱስን ማራገፍ ይቅደም መጀመሪያ፤” አሉት። “እንዴ በገዛ ምርቃናችን ምነው ተበሳጩ እርስዎ? መቼም ባናውቅም ብቻ ወደፊት፣ የዕድገት ሕመማችን ሲለቀን መካከለኛ ገቢ ካላቸው አገሮች ተርታ እስክንሠለፍ ገና እንመረቅናለን። አይገርምዎትም። ስንቱ ለውጥ ተርቦ ጫማ ቀቅሎ እንዳልበላ እኛ በጫት እንጫጫ?” ብሎ አንጋጠጠ፡፡

“የባሰ አታምጣ! የሚናገሩትን አያውቁምና ይቅር በላቸው። የጫቱንም የእህሉንም ማሳ አንድ ላይ ስላቀላቀሉት አንተው ጠብቀው። እንደየወጋችንና እምነታችን ሁሉም ያስፈልገናልና፤” ሲል አንዱ አጉተመተመ። “ድሮም ከእናንተ ጋር መከራከር፤” እያሉ ሴትዮዋ ወደ ሻሻቸው፣ “ይኼ ሻሽ ደግሞ። በሽበቴ የማፍር መሰለው እንዴ አሥር ጊዜ እንደ ዘመኑ ሰው የሚንሸራተተው? እንግዲያማ ገመና የሚሸፍን ሰው ጠፍቷል፤” ብለው ሻሻቸውን አውልቀው ቦርሳቸው ውስጥ ከተቱት። ተጎንጉኖ ለሦስት እየተገመደ የሚወርደው ጥጥ የመሰለ ፀጉራቸው ክፉና ደጉን በወግ ያጠኑበት ዕድሜ ቀላል እንዳልሆነ ይናገራል፡፡ ‘የእርጅና በረከት ከርስ በመሙላት ብቻ አይገኝም። ቀናውን ከጠማማው በመለየት እንጂ’ የሚለን ይመስላል። የመምረጥና የማስተዋል መብታችንን ምርጫ ካልደረሰ አልጠቀምበት ያልን ነዋ የምንመስለው!

“እስኪ ‘ቫት’ ተመዝጋቢ ሳንሆን ቶሎ ሒሳብ ወጣ ወጣ አድርጉ፤” እያለ ወያላው ተሳፋሪዎችን መጠየቅ ጀመረ። “አድርጎልን ነው? እናንተ ያስቀራችሁብኝ መልስ ቢጠራቀም ይኼኔ ስንት ጤና ጣቢያ ይገነባ ነበር?” ብሎ ከጀርባዬ የተሰየመ ጎልማሳ ብሶቱን ማራገፍ ጀመረ። “እነሱ መልስ ቢመልሱ ጤና ጣቢያውስ መቼ ያስፈልገን ነበር?” ስትል አጠገቡ የተቀመጠች ወጣት ገባችበት። ጎልማሳው መልሶ፣ “እነማ? የሳንቲሙን ማለትሽ ነው ወይስ የመልካም አስተዳደርና የዴሞክራሲ ጥያቄያችንን መልስ?” አላት። ወጣቷ ደነበረች ስንል ቆፍጠን ብላ፣ “ያው ናቸው ሁሉም። ምን ካለው ምን ለየው አይደል የሚባለው?” አለች። ሐሳቧን ያድበሰበሰባት የጠፋት ተረት ሳይቆረቁራት።

ይኼ ሳይቋጭ ደግሞ ሦስተኛው ረድፍ ላይ የተቀመጡ ጓደኛማቾች ቀጠሉ። “አንቺ መቼ ዕለት የታሰረ ሰው ልጠይቅ ሄጄ የሆንኩትን ነግሬሻለሁ?” ስትል ቀጠን ያለችዋ ደበልበል ላለችዋ መልከ መልካም ወዳጇ፣ “ለአንድ ሁለት ቀን አረፍ ብለሽ ውጪ ተባልኩ እንዳትይ?” ብላ መሳቅ ትጀምራለች። “እሱ አንድ ነገር ነው። ‘መታወቂያሽ የአገልግሎት ጊዜው ሁለት ቀን አልፎታል’ ብሎ ጥበቃው ሙልጭ አድርጎ ሰደበኝ ብልሽ ታምኛለሽ?” በማለት ስትነግራት ጓደኛዋ ደግሞ፣ “እንኳን ቢሰድብሽ ቢሰቅልሽ አምንሻለሁ አይዞሽ፤” ስላለቻት ተቀባይዋ ተሳፋሪዎች “ወራጅ” ለማለት አቆበቆቡ። ወርደው ቢሸሹም ሌላ የሠልፍና የነገር ወረፋ መልኩን ቀይሮ እንደሚጠብቃቸው አሰቡ መሰል ተውት። መሸሻ ሲጠፋ እያዩ እንዳላዩ፣ እየሰሙ እንዳልሰሙ ሆነው ካልተጓዙ እህ ሌላ ምን መላ አለ? ‘መላ ያጣ ነገር’ አለ አዝማሪው!

ጉዟችን ቀጥሏል። ጫፍ ተይዞ ዳዴ ባዩ ዴሞክራሲያችን ይነተረካል። “አዳሜ የመታወቂያውን ‘ኤክስፓየር ዴት’ ሳይውቅ ስለሥልጣን ‘ኤክስፓዬር ዴት’ ይፈተፍታል። አይገርምም?” ይላል አንድ ፀጉረ ጨብራራ ከመጨረሻ ወንበር። “ኤድያ ሐበሻን ጀርምና የዴሞክራሲ እጦት ሲገለው አላየንም። እኛን እየገደለን ያለው የማናውቀው አገር ናፍቆት ነው፤” ይላል ከጎኑ። “እኔን በል ወንድሜ። ያለፈቃዳችን አታደራጀን፤” ትላለች ፓንክ የተቆረጠች ደንዳና። “ኦ ያውም ሳትደራጁ አገራችሁ ላይ መኖር የሚያምራችሁም ለካ አላችሁ?” ብሎ የፊተኛው ተናጋሪ ሲያሽሟጥጥ፣ “ኮንዶሚኒየም ላይ ከኖርክ አይበቃህም? ተደራጅቶ መኖር ማለት ያ መሰለኝ። ሌላ ካለህ እዚያው በፀበልህ፤” አለችው ቱግ ብላ። ወዲያው ጆሮ የሚበሳ ጩኸት ተሰማ። እዚያው መጨረሻ ወንበር ጥጉን ይዞ የተቀመጠ ተሳፋሪ የቻይና ስልኩን አውጥቶ አንቴናውን ዘርግቶ የቴሌቪዥን ሥርጭት ለመከታተል መከራውን ያያል።

“ኧረ እባክህ ጣቢያውን እስክትፈልግ እንኳ ቀነስ አድርገው፤” ብሎ ጎልማሳው ቢናገረው፣ “ዴሞክራሲያዊ መብቴ መሰለኝ፤” ብሎ መልሶ ጮኸበት። “ጆሮ የማደንቆርም ነው መብትህ?” አለው ጎልማሳው የበለጠ እሳት ጎርሶ፣ “አንተም የመሸሽ ዴሞክራሲያዊ መብት አለህ፤” መለሰ ቴክኖሎጂ ብርቁ። ጣቢያ ፍለጋውን ሲቀጥል፣ “ወንድሜ እንኳን የሰው ልጅ በረሮም በአቅሟ ሁለት አንቴና ነው ያላት። ወደን መሰለህ እንዴ በሌለ አቅማችን ዲሽ በዲሽ የሆንነው? ዞር ዞር ካላልክ አንድ አንተ ብቻ፣ በአንድ የአንተ ብቻ መብት፣ በአንድ አንቴና የምትፈልገውን ማግኘትም መሆንም አትችልም። ያውም እንኳን የቴሌቪዥን የስልክ ኔትወርክም አንድ ሥፍራ እንደ ጅብራ ካልተገተርክ በማይገኝበት አገር? አብደሃል?” አለውና ፀጉረ ጨብራራው ድምፁን ቀነሰልን። ‘ሲታሰር ወኔ ሲፈታ ወደ እሱ’ በሆነ ቄንጥ ካልተነጋገርን በቃ መከባበርና መተሳሰብ ቀረ ማለት ነው? ወይ አዱኛ ብላሽ!?

ወደ መዳረሻችን ተቃርበናል። ጋቢና የተቀመጡ ተሳፋሪዎች ስለ 40/60 የቁጠባ ቤት አከፋፈላቸው አንስተው ይጫወታሉ። ቀስ በቀስ ሁሉም ስለመኖሪያ ቤት ችግሩ እያወጋ አንዳንድ ይባባል ጀመር። አንዱ፣ “አሉላችሁ የእኔ አከራይ ‘እራት በልተሃል? ለሽንት ወጥተሃል?’ እያሉ ሲጠይቁኝ አምሽተው ‘አልጋ ውስጥ ነህ?’ ሲሉ ‘አዎ’ ካልኳቸው ቆጣሪ ያጠፋሉ፤” ሲል አጠገቤ የተቀመጡት እናት ቀበል አድርገው፣ “ምን ሞኝ ናቸው አንተ? ቆጣሪ መለሱ አልመለሱ ደግሞ። መብራት እንደሆነ ድንገት ከጠፋበት ቢመጣ ጠፍቶ አዳሪ ነው፡፡ ድንገት ሲበራ ካደረም ጠዋት ሂያጅ ነው። ምስኪን…፤” ይሉታል። አንዱ ደግሞ “አሉላችሁ ደግሞ የእኔ…፤” ብሎ ሲጀምር ሁሉም ወደ እሱ ዞረ። “በወር በወር መታወቂያዬን ‘ኮፒ’ ያስደርጉና ይይዛሉ፤” ብሎን ዝም ሲል ግራ ገብቶን ተያየን። “ፖሊስ ጣቢያ ነው እንዴ የተከራየኸው?” ሲል ጨብራራው ያላግጣል። ጎልማሳው፣ “እኮ ለምን?” ብሎ ሲጠይቀው “አሸባሪ እንዳልሆን እየሰጉ መሆኑ ነዋ!” ብሎ መልሶ በገዛ እንግልቱ ልቡ እስኪፈርስ ይስቃል።

“እውነታቸውን ነው። ዘንድሮ እኮ ከቋሚ ተሠላፊው የባሰው ተጠባባቂው ነው፤” ብላ ከጎልማሳው አጠገብ እሷም ብትሆን እንደማትለቀው በ‘ፎርም’ ትነግረዋለች። “ስንት ዓይነት ኑሮ አለ?” ብለው ጥቂት አጉረምርመው ደግሞ ከጎኔ ቀጠሉ። “አንድ የማከራያት ‘ሰርቪስ’ አለችኝ። ታዲያ የተከራየኝ ወጣት ነው። እንዲያው ባየሁት ቁጥር በተለይ ደግሞ ቀን አንጀቴ ይንቦጀቦጃል። ይምሽለት ብቻ  . . . ሰው እንዳይሆን ሆኖ ሰክሮ አንዷን አቅፎ ካልገባ አይሆንለትም። ጠዋት መክሬው ማታ  ከሌላኛይቱ ጋር ነው። ነገም ያው ከተነገ ወዲያም እንደዚያው። ብቻ እንደ ግል ቤት ሁሉን የሚችል የለም፤” ብለው ከመናገራቸው ጉንጩ በጫት ተወጥሮ ሊፈነዳ የተቃረበው ወያላችን “መጨረሻ” ብሎ በሩን ከፈተው። በተከፈተው በር ለመውረድ ስንጋጋ የኪራይ፣ የአከራይና የቁጠባ ኑሯች ተጣፍቶ እፎይ የምንልበት ዘመን ደጅ የሚጠብቀን እንመስል ነበር። “ተስፋ ባይኖር ኖሮ ምን ይኮን ነበር? ተስፋ አስቆራጮች እንደ አሸን በሞሉበት ዘመን ተስፋ ሰንቆ መኖር ምንኛ መታደል ነው?” የሚሉት አዛውንቷ ናቸው ከታክሲው ወርደው የሚቀጥለውን መንገዳቸውን እያመቻቹ፡፡ ያቺ ደንዳና ባለ ፓንክ ደግሞ፣ “አይ ማዘር! ተስፋና ትዝታ እሹሩሩ በሚባሉበት አገር በጅምላ ሳይሆን በግል ነው ማሰብ፡፡ አለበለዚያ ሁሉም ነገር ተረት ተረት ይሆንና ስንተርት ዘመኑ ይነጉዳል…” ስትል እኛም አደነቅን፡፡ “በር ዘግተን ብንቀመጥ ኖሮ ይኼ ሁሉ ወግ የት ይገኝ ነበር? ኧረ በሩን ገርበብ አድርጉት፡፡ ዘግታችሁ አትፈትፍቱ፡፡ በአደባባይ ጉባዔ ዘርግተው ካወጁ በኋላ የምን ወሬ መንፈግ ነው?” እያለ አንዱ ወፈፍ ያደረገው እየተናገረ አካባቢውን ሲገለማምጥ እኛም ወደ ጉዳያችን፡፡ መልካም ጉዞ!              

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት