አቶ መርዓዊ ጎሹ አበበ፣ ችግር የገጠማቸው ኢንቨስተር
ከአፀደ ሕፃናት እስከ ዘጠነኛ ክፍል የተማሩት በካቴድራል ልደታ የወንዶች ትምህርት ቤት ነው፡፡ ዘጠነኛ ክፍል እያሉ ከቤተሰቦቻቸው ጋር ወደ አሜሪካ በመሄድ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በማጠናቀቅ ዩኒቨርሲቲ ገብተዋል፡፡ በዩኒቨርሲቲ ቆይታቸው የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን በፍትሕ አስተዳደር (Administration of Justice) አግኝተዋል፡፡ ሁለተኛ ዲግሪያቸውን በሕግ ካገኙ በኋላ ዶክተር ኦፍ ጁሪስፕሩደንስ መባላቸውን ተናግረዋል፡፡ አቶ መርዓዊ ከ16 ዓመታት የአሜሪካ ቆይታ በኋላ ወደ አገራቸው በመመለስ አገራቸውን ለማገልገል፤ በተለይ በትምህርት ዘርፍ የበኩላቸውን አስተዋጽኦ ለማድረግ ከፍተኛ ፍላጎት አላቸው፡፡ ቤተሰቦቻቸውን በመወከል በሕንፃ ግንባታና በተለያዩ ኢንቨስትመንቶች ላይ ለመሰማራት የሚፈልጉ ቢሆንም፣ በአንዳንድ የመንግሥት ተቋማት ያለው የተንዛዛ ቢሮክራሲ ችግር እየፈጠረባቸው መሆኑን ገልጸዋል፡፡ አቶ መርዓዊን ታምሩ ጽጌ አነጋግሯቸዋል፡፡
ሪፖርተር፡- ለ16 ዓመታት በአሜሪካ አገር ከኖሩ በኋላ ወደ አገርዎ ተመልሰዋል፡፡ በዋናነት የተመለሱበት ምክንያት ምንድነው?
አቶ መርዓዊ፡- እኔ ከልጅነቴ ጀምሮ ኢትዮጵያን እወዳታለሁ፡፡ መኖር የምፈልገውም እዚሁ ነው፡፡ ቤተሰቦቼ በመሄዳቸውና እኔም የትምህርት ዕድል በማግኘቴ ብሄድም፣ ተመልሼ አገሬ እንደምኖር ግን እርግጠኛ ነበርኩ፡፡ ሁልጊዜ እዛም ሆኜ የማስበውና የምፈልገው ከአገሬ ጋር የሚያስተሳስረኝን ነገር ማድረግ ነበር፡፡ በተለይ ከትምህርት ጥራት ጋር የተገናኘ ነገር ለመሥራት ፍላጎት ነበረኝ፡፡ ትምህርቴን እንደጨረስኩም በተለይ ከአንደኛ ክፍል እስከ 12ኛ ክፍል ያለው የትምህርት አሰጣጥ ሥርዓት የሚሻሻልበትን መንገድ የሚያሳይ ሐሳብ ይዤ መጣሁ፡፡
ሪፖርተር፡- ይዘውት የመጡት አዲሱ የትምህርት ማሻሻያ ሐሳብ ምንድነው?
አቶ መርዓዊ፡- አዲሱ የትምህርት ሐሳብ ከአንደኛ እስከ 12ኛ ድረስ ባለው የትምህርት ሥርዓት ውስጥ ፈተና መኖር የለበትም የሚል ነው፡፡ ፈተና አስፈላጊ አለመሆኑን የሚያስረዳ ሐሳብ ነው፡፡
ሪፖርተር፡- ለምን? ተማሪዎች በምን ይመዘናሉ?
አቶ መርዓዊ፡- ተማሪዎችን ከመፈተን ይልቅ ወደ ልምምድ ሥርዓት ማሸጋገር በጣም ጠቃሚ ነው፡፡ ተማሪዎች እየተዘጋጁ ያሉት ለዕውቀት ሳይሆን ለፈተና ነው፡፡ ይኸ ደግሞ ዕውቀት እንዳይኖራቸው የሚያደርግ ሥርዓት ነው፡፡ “በዚህ ትምህርት ፈተና እወድቅ ይሆን? አሪፍ ውጤት አገኘሁ…” እያሉ ከሚጨነቁ፣ በዕውቀት ላይ ትኩረት እንዲያደርጉ ፈተናው መቅረት አለበት፡፡ ከፈተና ሥርዓት ወደ ልምምድ ሥርዓት መግባት እንዳለባቸው የሚመክርና ውጤታማ የሆነ ሥርዓት ነው፡፡
ሪፖርተር፡- የልምምድ ሥርዓት ማለት ምን ማለት ነው?
አቶ መርዓዊ፡- ተማሪዎች በአማካይ (ከአንደኛ እስከ 12ኛ ክፍል ያሉ ተማሪዎች) በዓመት 80 ጊዜ ፈተና ይወስዳሉ፡፡ ይኸ ደግሞ ማወቃቸውን ለመመዘን የትምህርት ሥርዓቱ ያስቀመጠው መስፈርት ነው፡፡ አንድ የአንደኛ ወይም የሌላ ክፍል ተማሪ በአንድ ዓመት የትምህርት ቤት ቆይታው 80 ጊዜ ለፈተና ሲቀመጥ፣ አብዛኛውን የትምህርት ጊዜ የሚያሳልፈው በፈተናው እንዳይወድቅ ሲጨነቅ ነው፡፡ ይኸ የትምህርት ሥርዓት በመላው ዓለም ያለ ነው፡፡ ይኸ ሥርዓት ተማሪዎች ብቁ ሆነው እንዲወጡ የሚያደርግ አይደለም፡፡ ይኸንን ስል ሙሉ በሙሉ ሁሉም ውጤታማ አይሆኑም እያልኩ አይደለም፡፡ ከመቶ አሥር የሚሆኑት ውጤታማ ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ ነገር ግን በዓመት 80 ጊዜ ከሚፈተኑ፣ በዓመት 80 ጊዜ ቢለማመዱ፣ ማለትም የሚማሩት የትምህርት ዓይነት ምን ማለት እንደሆነና ወደ ሥራ ሲቀየር በነሱም ላይ ሆነ በሚኖሩበት አገር ላይ የሚያመጣው ተፅዕኖ በደንብ እንዲገባቸው ቢደረግ፣ ውጤታማ ያደርጋል፤ ብቁና በራሰ የሚተማመን ዜጋ ማድረግ ይቻላል የሚል ዕምነት አለኝ፡፡ 80 ጊዜ ለፈተና የሚቀመጥ ተማሪ ከፍተኛ ጭንቀት አለበት፡፡ ትኩረቱ ፈተናው ላይ ነው፡፡ ጥናቱም በዛች የፈተና ሥርዓት ዙሪያ ማሰላሰልና እሷኑው ለማወቅ ራሱን በተወሰነች ቦታ ላይ መወሰን ነው፡፡ ይኸ ደግሞ ዘና ብሎ ሳይጨነቅ የሚማረውን ትምህርት ከተለያዩ አቅጣጫዎች በማየት ተጨማሪ ዕውቀት እንዳይዝ ያደርገዋል፡፡ ይኸ ደግሞ የትምህርትን ዓላማ እንዲስት ያደርገዋል፡፡ በአሁኑ ጊዜ በዓለም ላይ የሚታይ ዋናና አሳሳቢ ችግር እየሆነ ነው፡፡
ሪፖርተር፡- የእርስዎ ሐሳብ መነሻው ምንድነው?
አቶ መርዓዊ፡- ከ11 ዓመት በፊት ወደ ኢትዮጵያ መጥቼ ነበር፡፡ በአጋጣሚ ከዕለታት አንድ ቀን ሐኪም ቤት ሄጀ ሳለ አንድ መርዝ የጠጣን ልጅ ሕይወት ለማትረፍ ሐኪሞች ሲረባረቡ ተመለከትኩኝ፡፡ ሁኔታው በጣም አሳዝኖኝ ጠጋ ብዬ ሁኔታውን መከታተል ጀመርኩኝ፡፡ በሐኪሞቹ ጥረት ያ ልጅ ከሞት ተረፈ፡፡ ዕድሜው 15 ይሆናል፡፡ ልጁ ወደ ሕይወቱ ሲመለስ “እኔ መሞት እፈልጋለሁ ለምን አዳንከኝ?” በማለት ሐኪሙ ላይ ጮኸባቸው፡፡ ንግግሩ በጣም የሚነካ ነበር፡፡ በዚህ ጊዜ እኔ “ይኸ ልጅ ለምን እንደዚህ ያለ ንግግር ሊናገር ቻለ?” ብዬ ማሰብ ጀመርኩ፡፡ ያ ልጅ በደንብ ታክሞ ወደ መልካም ጤንነቱ ሲመለስ አነጋገርኩት፡፡ ለምን መርዝ ጠጥቶ ራሱን ማጥፋት እንደፈለገ ስጠይቀው፣ “መኖር ምን ያደርጋል? ተምረህ ካልገባህ፣ ፈተና ተፈትነህ ከክፍል ወደ ክፍል ካላለፍክና ውጤታማ ካልሆንክ መኖር ምን ያደርጋል? ሁልጊዜ ፈተና በመጣ ቁጥር ከመጨነቅ ሞቶ መገላገል ይሻላል” የሚል ምላሽ ሰጠኝ፡፡ ይኸ ለኔ መነሻ ሆነኝ፡፡ ወደ አሜሪካን አገር ስመለስም ሐሳቡ በውስጤ መመላለሱን አላቆመም፡፡ ምንም እንኳን ሁሉም ነገር የተመቻቸበት፣ ለትምህርት ቅድሚያ የሚሰጥበትና ተማሪዎች ያለ ምንም ጭንቀት የሚማሩበት አገር መሆኑን ባውቅም፣ ተማሪዎች ስለፈተና ያላቸውን ግንዛቤ ለማወቅ የተለያዩ ትምህርት ቤቶች ተማሪዎችን መጠያየቅ ጀመርኩኝ፡፡ ከ80 በመቶ በላይ የሚሆኑ ተማሪዎች ፈተና የሚጠሉ ሆነው አገኘኋቸው፡፡ በዚህ ጊዜ ለምን ፈተና አይቀርም? ተማሪዎች ዕውቀት እንዲኖራቸው ከተፈለገ በሚማሩበት ትምህርት ዙሪያ ልምምድ ቢያደርጉና ከተግባር ጋር የተገናኘ ጥናት ቢያደርጉ ውጤታማ እንደሚሆኑ ዕምነቴ የፀና ሆነ፡፡ በዚህ ምክንያት ይኸንን ሐሳብ ለተለያዩ ምሁራን ሳማክር ሐሳቡን በፍጥነት ተግባራዊ ማድረግ ባይቻልም፣ መጀመሪያ በሐሳቡ ዙሪያ በመወያየትና ውጤታማነቱን መሠረት ለማስያዝ አስፈላጊ መሆኑን እንደሚያምኑበት ስለነገሩኝ፣ በሱ ዙሪያ እየሠራሁ ነው፡፡
ሪፖርተር፡- ሌላው ወደ ኢትዮጵያ የተመለሱበት ዓላማ በአገርዎት ኢንቨስት በማድረግ በልማት ዙሪያ ለመሥራት ቢሆንም፣ የገጠመዎት ችግር እንዳለ እየተናገሩ ነው፡፡ ስለችግሩ ቢነግሩን?
አቶ መርዓዊ፡- እኔ በአሜሪካ የዩኒቨርሲቲ ተማሪ እያለሁ፣ የኢትዮጵያ መንግሥት በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ወደ አገራቸው ተመልሰው በአገራቸው በፈለጉት የሥራ ዘርፍ መሰማራት እንደሚችሉ እየገለፀና ጥሪ እያደረገ ነበር፡፡ ይኸ የሆነው በ2000 ዓ.ም. አካባቢ ነው፡፡ በወቅቱ በተደረገው ጥሪ ማብራሪያ ሲሰጥ አዲስ አበባ ውስጥ ያሉት ሆቴሎች ያላቸው የመኝታ ክፍል ብዛት ዘጠኝ ሺሕ መሆኑንና ነገር ግን ከ30 ሺሕ በላይ መኝታ ክፍል ያላቸው ሆቴሎች እንደሚያስፈልጉ ነበር፡፡ ይኸንን ክፍተት ለመሙላት ዳያስፖራው እንዲሳተፍና የልማቱ ተጋሪ እንዲሆን ጥሪ ተደርጓል፡፡ ሁሉም ነገር እንደሚመቻች፣ የሚፈለገው ኢትዮጵያዊውና ትውልደ ኢትዮጵያዊው ዕውቀቱንና ገንዘቡን ይዞ እንዲመጣ ከፍተኛ ቅስቀሳ ተደርጎ ነበር፡፡ ይኸ በጣም ደስ የሚልና የሚያበረታታ ስለነበር እኛ እዚሁ የራሳችን ይዞታ ስለነበረን በሱ ላይ ለመሥራት አሰብን፡፡
ሪፖርተር፡- ያላችሁ የይዞታ መጠን ስንት ነበር? ቦታውስ ለልማት አመቺ ነበር?
አቶ መርዓዊ፡- ቦታው በቂርቆስ ክፍለ ከተማ ግሪክ ክለብ አካባቢ ነው፡፡ የይዞታው መጠን 1500 ካሬ ሜትር ስፋት ያለው ቦታ ነበር፡፡ መንግሥት ዕድሉን አመቻቻለሁ በማለቱ እናቴ መጣችና ፕሮፖዛል ተቀርፆ ለኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን አስገባች፡፡ መሥሪያ ቤቱም በደስታ ተቀብሎ የመሥሪያ ፈቃድ ሰጣት፡፡
ሪፖርተር፡- ምን ነበር ለመሥራት የፈለጋችሁት?
አቶ መርዓዊ፡- መንግሥት በተለያዩ አካባቢዎች የተለያዩ ግንባታዎች እንዲካሄዱ ያወጣው መመሪያ (አቅጣጫ) ነበር፡፡ በኛ ቦታ አካባቢ ባለ12 ፎቅ ለተለያዩ አገልግሎቶች የሚውል ሕንፃ መገንባት ይቻል ነበር፡፡ መንግሥት ባለው መሠረት ነው እናቴም ፕሮፖዛል ቀርፆ ያስገባቸው፡፡ የኢንቨስትመንት ፈቃድ አውጥታና ፕሮፖዛል አስገብታ እየተጠባበቀች እያለች ብዙ ችግሮች ተፈጠሩ፡፡
ሪፖርተር፡- የተፈጠሩት ችግሮች ምንድናቸው?
አቶ መርዓዊ፡- በወቅቱ የነበረን ወይም ያሳየነው ካፒታል አንድ ሚሊዮን ዶላር ነበር፡፡ እናቴ በትውልድ ኢትዮጵያዊ ስትሆን በዜግነቷ ግን አሜሪካዊ ነች፡፡ በመሆኑም የኢንቨስትመንት ፈቃድና ቢጫ መታወቂያ አግኝታለች፡፡ ፈቃዱንም ሆነ መታወቂያው የተሰጣት ያንን አንድ ሚሊዮን ዶላር ወይም ከ20 ሚሊዮን ብር በላይ ካፒታል ካሳየች በኋላ ነው፡፡ ሁሉ ነገር እንደማንኛውም አልሚ ከተሟላላት በኋላ ይዞታችን ባለበት ቂርቆስ ክፍለ ከተማ ችግር ተፈጠረ፡፡ ፕሮፖዛል ቀርፀን አስገብተን መልሱን በመጠባበቅ ላይ እያለን በድንገት በቦታው ላይ የነበረውንና በወቅቱ እየኖርንበት ያለውን ቤት አፍራሽ ግብረ ኃይል የሚባል ቡድን መጥቶ፣ ቤቱን በላያችን ላይ ዕቃዎቻችንን እንኳን ሳናወጣ አፈረሱብን፡፡ ማስጠንቀቂያ ሳይሰጠን፣ የቦታ ግምት ካሳና ተለዋጭ ቦታ ሳይሰጠን አፈረሱት፡፡
ሪፖርተር፡- ቤቱን ሊያፈርሱ ያነሳሳቸው ምክንያት ምንድነው?
አቶ መርዓዊ፡- ቦታው ለመልሶ ማልማት ይፈለጋል የሚል ነው፡፡ እኛ ለማልማት ሁሉን ነገር ጨርሰን የአስተዳደሩን መልስ እየጠበቅን መሆኑን ሰነድ እያሳየን ብንነግራቸውም “እናንተ እዚህ ማልማት አትችሉም” የሚል ወረቀት ይዘው መጥተው አፈረሱት፡፡ ንብረታችንን ለማውጣት እንኳን አፍራሽ ግብረ ኃይሉ አሻፈረኝ ብሎ ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርና ከፖሊስ ኃይል መጥቶ ነው ማውጣት የቻልነው፡፡ የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ መለስ ዜናዊ ሳይቀሩ ባደረጉት ጥሪ ወደ አገራችን መጥተን እናልማ ባልን አፍራሽ ግብረ ኃይል ለምን ይላክብናል? በአግባቡ ክፍለ ከተማው ሊያነጋግረን ሲገባ “በ24 ሰዓታት ውስጥ ቤቱን ለቃችሁ እንድትወጡ” የሚል ደብዳቤ ጠዋት ሰጥቶ ከሰዓት በኋላ ማፍረስ ምን ማለት ነው?
ሪፖርተር፡- በወቅቱ ለመንግሥት አካላት አላሳወቃችሁም?
አቶ መርዓዊ፡- አሳውቀናል፡፡ በስህተት ነው የፈረሰው በሚል፣ አፍራሽ ናቸው የተባሉ 11 ግለሰቦች እንዲታሰሩ ተደረገ፡፡ “ይኸን በማድረጋቸው ዕርምጃ ወስደናል” የሚል ደብዳቤ ጻፉልን፡፡ ይኸ ግን ማስመሰያ ነው፡፡
ሪፖርተር፡- ከዚያ በኋላ ምን አደረጋችሁ?
አቶ መርዓዊ፡- እኛ ጥያቄያችንን አላቆምንም፡፡ የማልማት አቅሙ አለን፡፡ እንድናለማ ይፈቀድልን በማለት እናቴ ወደ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ቢሮ ሄደች፡፡ በወቅቱ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ስለነበሩ ቀጠሮ ይዘውላት የነበረውን ነገር ሁሉ አስረዳቻቸው፡፡ ጽሕፈት ቤታቸው ለአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሊዝ ቦርድ ደብዳቤ በመፃፉ፣ ቦርዱ ውሳኔ አስተላለፈ፡፡ “በይዞታቸው ላይ ማልማት እንደሚችሉ፣ አቅሙ እንዳላቸው እየተናገሩ በመሆኑ እንዲያለሙ ይፈቀድላቸው” የሚል ውሳኔ አስተላለፈ፡፡ በቦርዱ ውሳኔ መሠረት እንዲያስተናግዱን የክፍለ ከተማውን ሹሞች ጠየቅን፡፡ ክፍለ ከተማ በቦርዱ ውሳኔ መሠረት መስጠቱን ትቶ ቦታውን ሸነሸነው፡፡ ይዞታችንን ከሸነሸነው በኋላ እናቴን “ነይና ዕጣ አውጪ” ብሎ ጠራት፡፡ እናቴ “ለምን ዕጣ አወጣለሁ? ይዞታየስ ለምን ይሸነሸናል? በምን ሕግ ነው የራሴን ይዞታ ከሌላ ሰው ጋር ተካፈይ የምትሉኝ? የራሴን ይዞታ አልከፋፈልም” ብላ መልስ ሰጠች፡፡
ሪፖርተር፡- አስተዳደሩ ሽንሸና ውስጥ የገባበት ምክንያት ምንድነው?
አቶ መርዓዊ፡- ለኛም ግራ የገባን ነገር እሱ ነው፡፡ ካርታ ያለው ቦታና የግል ይዞታ ለምን መሸንሸን እንደፈለጉ ስንጠይቃቸው፣ ማንም ምላሽ የሚሰጠን የለም፡፡ ዝም ብለው ከሸነሸኑ በኋላ ዕጣ እንዳወጡ በማስመሰል ከ1500 ካሬ ሜትር ይዞታ ላይ 350 ካሬ ሜትር ሰጡን፡፡ 400 ካሬ ሜትሩን በከፍተኛ የሊዝ ዋጋ እንድንወስድ በማድረግ በድምሩ 750 ካሬ ሜትር ሰጥተናችኋል አሉን፡፡ ከ1965 ዓ.ም. ጀምሮ ሲገበርበት የነበረን የራሳችንን ይዞታ ሸንሽነው ቦታውን በዕጣ እንዳከፋፈሉ በመግለጽ ለቦርድ አቀረቡ፡፡ ቦርዱም የቀድሞው ቦርድ የወሰነውን ትቶ የክፍለ ከተማውን ሪፖርት አፀደቀው፡፡ በ10 ቀናት ውስጥ በካሬ ሜትር 7100 ብር 400ውን ካሬ ሜትር እንድንወስድ ተደረገ፡፡ ይኸንንም 750 ካሬ ሜትር “ሰጠናችሁ” ያሉት ቤታችን ከፈረሰ ከአንድ ዓመት በኋላ ነው፡፡ ሰጠናችሁ ካሉን 750 ካሬ ሜትር ላይ የተወሰነው መንገድ የሚወጣበት ነው፡፡ ይኸ የሆነው በአካባቢው ላይ ሕንፃ ስለተገነባበትና ቦርዱ ሕንፃው እንዳይፈርስ ስለወሰነ ለመንገድ ማስፋፊያ ከ15 ሜትር በላይ ለኛ ከተሰጠው ቦታ ላይ ይወሰዳል፡፡
ሪፖርተር፡- ለሊዝ ቦርድ ወይም ለሌላ ለሚመለከተው አካል ቅሬታ አላቀረባችሁም?
አቶ መርዓዊ፡- በከፍተኛ የሊዝ ዋጋ በአሥር ቀናት ውስት እንድንከፍል የተጠየቅነው የ400 ካሬ ሜትር ቦታ ዋጋ በሲፒኦ አሠርተንና የቅሬታ ደብዳቤ ይዘን፣ ለክፍለ ከተማውና ለቦርዱ አቅርበናል፡፡ “በሰጣችሁን ቦታ ላይ ማልማት አንችልም፡፡ በባለሙያ አሳይተን እንደማይቻል ነግረውናል፤ መፍትሔ ይሰጠን” ብለን አመለከትን፡፡ የሰጡን ምላሽ፣ “ቅሬታ ስላቀረባችሁ ሲፒኦውንም አንቀበላችሁም ለቦርዱ ያቀረባችሁት ቅሬታ ምላሽ እስከሚሰጥ እንጠብቃለን” በማለት ክፍለ ከተማው መለሰን፡፡
ሪፖርተር፡- የሊዝ ቦርዱ ላቀረባችሁት ቅሬታ ምለሽ ሰጠ?
አቶ መርዓዊ፡- እስካሁን ምላሽ አልተሰጠንም፡፡ መንገድ የሚወጣበትን ቦታ እንዴት ግዙ ትሉናላችሁ? መፍትሔ ስጡን በማለት ለከተማ አስተዳደሩ በአካል ቀርበን ስንጠይቅ “መንገድ የሚገነባው መንገዶች ባለሥልጣን ስለሆነ፣ በሊዝ የገዛነው ቦታ ስለሆነ መገንባት አትችሉም” በሉና ተከራከሩ የሚል ምላሽ ሰጡን፡፡ ላለፉት ሦስት ዓመታት ይመለከታቸዋል ባልናቸው የመንግሥት ተቋማት፣ ለፌደራል ፀረ ሙስና ኮሚሽን፣ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ ኢንቨስትመንት ኮሚሽንና ሌሎችም ጋ ሄደናል፡፡ ምንም መፍትሔ አላገኘንም፡፡
ሪፖርተር፡- በአግባቡ ሊያስተናግዷችሁ ያልቻሉት ለምን ይመስልዎታል?
አቶ መርዓዊ፡- እኔ የሚመስለኝ ተጠያቂነትን መፍራት ነው፡፡ ምክንያቱም መንግሥት ያወጣው ደንብና መመሪያ አለ፡፡ “ለምን በደንቡና መመሪያው መሠረት አታስተናግዱንም?” ብለን ስንጠይቅ ማንም ምላሽ የሚሰጥ አካል የለም፡፡ ለከተማው ከንቲባ አራት ደብዳቤዎችን ጽፈን “የውሳኔ ሐሳብ ይቅረብበት” ብለው ለከንቲባ ጽሕፈት ቤት ቢልኩትም፣ ምላሽ የሚሰጥ የለም፡፡ ከአንድ ቢሮ ወደ ሌላ ቢሮ ከመንገላታት ባለፈ ተጠያቂነትን ወስዶ የሚያስተናግድ የለም፡፡ ከ2002 ዓ.ም. ጀምሮ ላለፉት ስድስት ዓመታት በመንከራተት ላይ ነን፡፡
ሪፖርተር፡- ምን ለማድረግ አስባችኋል?
አቶ መርዓዊ፡- የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ መለስ ዜናዊ “አገራችሁ ኢትዮጵያ ናት፤ ሌላ አገር የላችሁም፤ ምንም ዓይነት ችግር ቢያጋጥማችሁ እስከ መጨረሻው ድረስ መታገል አለባችሁ፡፡ እውነት እስካላችሁ ድረስ ድሉ የናንተ ነው” ብለዋል፡፡ እኛም እውነትን ይዘን የሳቸውን ንግግር አምነን በሕጋዊ መንገድ እየታገልን ነው፡፡ አሁንም ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያምም ሆኑ ሌሎች ለእውነት ታግለው ለሕዝብ እየሠሩ ያሉ አመራሮች፣ መፍትሔ እስከሚሰጡን እንታገላለን፡፡ እኛ ብዙ ኪሳራዎች ደርሰውብናል፡፡ እንደመጣንና እንደጠየቅን ተፈቅዶልን ቢሆን ኖሮ፣ ግንባታችንን ጨርሰን ነበር፡፡ አሁን የግንባታ ግብዓቶች ዋጋ የት እንደደረሰ ሁሉም ኢትዮጵያዊ የሚያውቀው ነው፡፡ የመንግሥትን ዓላማ የሚያስቱ አንዳንድ በኃላፊነት ላይ ያሉ አመራሮች ሊፈተሹ ይገባል፡፡ ከወረዳ እስከ ማዕከል ያለው አሠራር መፈተሽ አለበት፡፡ የሚመለከተው አካል ሁኔታውን መርምሮ የ“እናልማ” ጥያቄያችንን ምላሽ እንዲሰጠን አሁንም ተስፋ ሳንቆርጥ እንጠይቃለን፡፡ መንግሥት እንኳን የራስን ይዞታ ቀርቶ ከራሱ ሁሉን ነገር ማመቻቸቱን እየገለፀ ባለበት ሁኔታ፣ በሌላ በኩል ደግሞ ቢሮክራሲው ማነቆ ከሆነ አስቸጋሪ ስለሚሆን፣ ተጠያቂነት ያለበት አሠራር እንዲኖርና የሚወጡ ሕጎች በአግባቡ ሊተገበሩ ይገባል፡፡