Sunday, June 23, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

‹‹ዳያስፖራዎች በፋይናንስ ዘርፉ እንዳይሳተፉ ጨርሶ መከልከል አልነበረባቸውም›› አቶ ኢየሱስ ወርቅ ዛፉ፣ ባለሀብት

spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

የኢትዮጵያ ዳያስፖራዎች በኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ውስጥ ያላቸው ተሳትፎ አነስተኛ እንደሆነ ይገለጻል፡፡ ካላቸው አቅም ጋር ኢንቨስትመንቱ ተመጣጣኝ እንዳልሆነም ሲነገር ቆይቷል፡፡ ዳያስፖራዎች በአገራቸው ለመሥራት ፍላጐት ቢኖራቸውም አሠራሮች የተመቻቹ ባለመሆናቸው ገድቧቸዋል ሲባልም ይደመጣል፡፡ ከእነዚህ መካከል በፋይናንስ ዘርፍ ውስጥ መግባት እንዳይችሉ መከልከላቸው አንዱ ነው፡፡ በዚህ ዘርፍ ለአገር በሚጠቅም ሥራ ላይ ተሳታፊ እንዳይሆኑ ገድቧቸዋል የሚለው አመለካከት መስተጋባት ከጀመረ ቆይቷል፡፡ በቅርቡ በተካሄደው የዳያስፖራ ሳምንት ላይ ይህ ጉዳይ ጥያቄ ሆኖ ቀርቧል፡፡ ዳያስፖራዎች በኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ውስጥ የላቀ ድርሻ እንዲያበረክቱ ካስፈለገ የአክሲዮን ኩባንያዎች አመሠራረት ሕግ መሻሻል የስቶክ ገበያም መጀመር ይኖርበታል የሚለውን በብርቱ የሚሞግቱ አሉ፡፡ ከእነዚህ ሞጋቾች መካከል ታዋቂው የኢንሹራንስ ባለሙያና ባለሀብት አቶ ኢየሱስ ወርቅ ዛፉ አንዱ ናቸው፡፡ በዳያስፖራዎች፣ በአክሲዮንና በስቶክ ገበያ ላይ ዳዊት ታዬ አነጋግሯቸዋል፡፡  

ሪፖርተር፡- የኢትዮጵያ ዳያስፖራዎችን ኢንቨስትመንት እንቅስቃሴና በቅርቡ በዳያስፖራ በዓል ላይ የተደረጉትን ውይይቶች እንዴት ይገመግሟቸዋል? ዳያስፖራዎች በኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ውስጥ በሰፊው እንዲሳተፉ ለማድረግ ምን መደረግ አለበት ይላሉ?

አቶ ኢየሱስ ወርቅ፡- ዳያስፖራዎች መጥተው መሰባሰባቸው፣ አገራቸውንና ቤተሰቦቻቸውን መመልከታቸው ጥሩ ነው፡፡ በተለይ አገሪቱ በምን ያህል ፍጥነት እየተንቀሳቀሰች መሆኗን ማየትና መገንዘባቸው ከመስማት በተሻለ ማሳመን ስለሚችል መምጣታቸው በጣም ጥሩ ነው፡፡ ከአንዳንዶቹ ጋር ከመምጣታቸው በፊት በግል ውጭ ሳገኛቸው የሚነግሩን፣ በተለያዩ አጋጣሚዎች ወደ አገራቸው በሚመጡበት ጊዜ የሚያነሱዋቸው ጥያቄዎች አሉ፡፡ አንዳንዶቹ ጥያቄዎች ሰሞኑን በተደረገው ውይይት ላይ አንስተዋል፡፡ በተቀናጀ መልክ ጥያቄዎቻቸውን አቅርበው መፍትሔ ያገኘ ውጤት እያየን ነው ማለት ግን አልችልም፡፡ ተጨባጭ ምላሽ አግኝተዋል ብሎ ለመናገርም ይከብዳል፡፡

ሪፖርተር፡- ለምሳሌ ምን?

አቶ ኢየሱስ ወርቅ፡- እስካሁን ድረስ የዳያስፖራ ኢንቨስትመንቶች ከምንጠብቃቸው አኳያ እጅግ በጣም አነስተኛ ናቸው፡፡ በመላው ዓለም ያሉ ዳያስፖራዎች መጡ ከተባለ በዕውቀትና በኢንዱስትሪ በኩል አይደለም፡፡ ከመጡት ውስጥ ምናልባት በርካቶቹ መጠነኛ በሆኑና በአነስተኛ ኢንቨስትመንቶች ላይ የተሰማሩ ናቸው፡፡

ሪፖርተር፡- ይህ ለምን የሆነ ይመስልዎታል?

አቶ ኢየሱስ ወርቅ፡- የተለያዩ ምክንያቶች አሉ፡፡ ሰሞኑን ዳያስፖራዎቹ ለክቡር ጠቅላይ ሚኒስትሩ ካቀረቡላቸው ጥያቄዎች መካከል አንዱን ላስታውስ እፈልጋለሁ፡፡ ይህ ጠያቂ ዳያስፖራ ተነስቶ ‘እኛ እያንዳንዳችንን እንደ ግለሰብ አቅማችን በጣም የተመጠነ ነው፡፡ ሁለት፣ ሦስት ሚሊዮን ብር ይዘን ብንመጣ በዚህ ገንዘብ ሊደረግ የሚችል ነገር የለም፡፡ ይሄ ነው የሚባል ሥራ ልንሠራበት አንችልም፡፡ ነገር ግን እያንዳንዳችን እንዲህ ያለ አቅም ካለን የብዙዎቻችን አንድ ላይ ሲቀናጅ ወሳኝ ሥራ ሊሠራ ይችላል፡፡ ይህንን ለማድረግ ግን ሁኔታዎች አልተመቻቹም፡፡ የመተማመን ችግርም አለ፤’ ብሏል፡፡ በአንዳንድ ሙከራዎቻችንም በጣም ብዙ ነገር አቃጥለናል ያሉም ነበሩ፡፡ ዳያስፖራው የሚናገረውና እኛም ብዙ የምናውቀው ነገር አለ፡፡ እኔ በእውነቱ ከማንም የተሻለ መልስ አለኝ ለማለት አልችልም፡፡ ነገር ግን እያንዳንዳችን ባንችልም በጋራ ብንሠራ ተብሎ የቀረበው ጥያቄ እጅግ መሠረታዊ ነው፡፡ ለዚህ የተሰጠው መልስ መቧደን ትችላላችሁ የሚል ነበር፡፡ በእኔ እምነት ጠያቂው እኮ ስለመቧደን ተናግሯል፡፡ ነገር ግን በመካከላችን መተማመን ኑሮ አብረን ለመሥራት የምንችልበት ሁኔታ የለም፡፡ አልተመቻቸም ነው ያለው፡፡

ሪፖርተር፡- ያልተመቻቸ ነገር ተብሎ በተገለጸው አባባል ላይ የእርስዎ አስተሳሰብ ምንድነው? መቧደን ትችላላችሁ ከተባለ በቂ መልስ አይሆንም?

አቶ ኢየሱስ ወርቅ፡- አንዴ የጀመርከውን ነገር እያነሳህ ትወቅጣለህ አትበለኝና አሁንም አንድ ነገር ላንሳ፡፡ ይህ የአክሲዮን ገበያ ሕግን ይመለከታል፡፡ በሕግ ማዕቀፍ የተቋቋመ የአክሲዮን ገበያ ያስፈልጋል የሚለው ጥያቄ በጽሑፍ ከቀረበ 17 ዓመታት ሆኖታል፡፡ በዚህ ጉዳይ ብዙ ጽፈናል፡፡ ብዙ ያወራን፣ ብዙ ጽሑፎችን በውይይት ቦታዎች ላይ ያቀረብን ሰዎች አለን፡፡ ለዚህ ጉዳይ መልስ የተነፈገበት ምክንያት ግን ለእኔ አይገባኝም፡፡ ይህ ጥያቄ ተመልሶ ቢሆን ተቧድኖ መምጣቱ ውጤት ያመጣ ነበር፡፡ ሕጉ ግን እስካሁን አልወጣም፡፡ ነገሩ የኒውክሌር ሳይንስ አይደለም፡፡ ኢኮኖሚስት መሆን የሚያስፈልግበትም አልነበረም፡፡ የአክሲዮን ገበያ ሕጋዊ ማዕቀፍ ኖሮት መሥራት ብንችል፣ ጥሩ መልስ ይሆናል ነበር፡፡

ሪፖርተር፡- የአክሲዮን ገበያ ሕጉ መውጣት ውጤት ሊያመጣ ይችላል ማለት ይቻላል?

አቶ ኢየሱስ ወርቅ፡- አዎ፡፡ ከዚህ የተሻለ መልስ የለም፡፡ ባለፉት 20 ዓመታት እንዳየነው ኢንሹራንስና ባንኮች በአክሲዮን እንዲሠሩ ሕግ ወጥቶላቸው በመሥራት ላይ ናቸው፡፡ መንግሥት ካወጣቸው ፖሊሲዎች ውስጥ እጅግ አርኪ ውጤት የተገኘው በፋይናንስ ዘርፍ ነው፡፡ ዛሬ በርካታ ባንኮች፣ ኢንሹራንሶችና ማይክሮፋይናንሶች ተፈጥረዋል፡፡ እነዚህ ተቋማት በሥራ ፈጠራም ይሁን የታክስ ገቢ በማስገኘትና በሌላውም ረገድ አስተዋጽኦ እያበረከቱ ነው፡፡ በተለይ ትንንሽ ገንዘቦችን ሰብስበው በሥራ ላይ ለሚያውሉ በማበደርም ትልቅ ሥራ እየሠሩ ነው፡፡ ይህ የአክሲዮን ኩባንያዎችን ጠቀሜታ ያሳያል፡፡

ሪፖርተር፡- ከፋይናንስ ዘርፍ ውጭ ባሉ ቢዝነሶች ላይ የአክሲዮን ግብይት ውጤታማነት እንዴት ይታያል?

አቶ ኢየሱስ ወርቅ፡- በሌሎቹም ውጤታማ ይኮናል፡፡ የበለጠ ውጤት የሚኖረው ግን የአክሲዮን ሕጉ ሲወጣ ነው፡፡ ለአፍሪካ ምሳሌ ይሆናል የተባለው የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ተቋቁሟል፡፡ ምን አለበት ታዲያ እንደ ቡናና ሰሊጥ፣ የአክሲዮኖች ልውውጥ ቢደረግ? እኔ የሚመስለኝ የሌለ ፍርኃት መፍጠራችን ነው፡፡ ምናልባት ያውቃሉ፣ የተማሩ የምንላቸውና የመንግሥትን ጆሮ ያገኙ አማካሪዎች ትልቅ ሚና እየተጫወቱ ነው፡፡ ምክንያቱም ብዙ ዳያስፖራዎች የፋይናንስ ዘርፉ ለምንድን ነው የማይፈቀድልን ብለው እሮሮ ያሰማሉ፡፡ ለእኛም ያነሳሉ፡፡ እኛ ባለአክሲዮን ብትሆኑ ደስ ይለናል፡፡ ነገር ግን የመንግሥት ሕግ አይፈቅድም እንላቸዋለን፡፡

ሪፖርተር፡- ዳያስፖራው በፋይናንስ ዘርፍ ውስጥ እንዳይገባ መከልከሉ ከሌሎች አገሮች ልምድ አኳያ ምን ይመስላል?

አቶ ኢየሱስ ወርቅ፡- በሌሎች አገሮችማ ዳያስፖራዎች እየተለመኑ በብዙ ነገሮች ውስጥ ይገባሉ፡፡ እዚህ ላይ ነው የአገራችን አማካሪዎች መሥራት ያለባቸው፡፡ ስለዳያስፖራው ጥቅም ምክር መስጠት ነበረባቸው፡፡ ወደፊት ግን ዳያስፖራዎች መግባታቸው የግድ ነው፡፡ በእኔ እይታ ዳያስፖራዎች በፋይናንስ ዘርፉ እንዳይሳተፉ ጨርሶ መከልከል አልነበረባቸውም፡፡ የጊዜ ጉዳይ ነው እንጂ ዳያስፖራዎች ብቻ ሳይሆኑ ዳያስፖራም ያልሆኑ መግባታቸው አይቀርም፡፡ እንዲህ ላለው ጉዳይ ለዳያስፖራዎች ልዩ ፈቃድ አያስፈልጋቸውም ነበር፡፡ ነገር ግን እነሱን እንደውጭ ሰው እየቆጠርናቸው ስለሆነ ነው ክፍተቱ የተፈጠረው፡፡ በአንድ በኩል አገራችሁ ነው፣ በሁሉም ነገር መሳተፍ ትችላላችሁ እየተባለ በሌላ በኩል ግን በፋይናንስ ዘርፍ ውስጥ አትገቡም ከምንል ባይሆን መያዝ የምትችሉት የባለቤትነት ድርሻ ይህን ያህል ብቻ ነው ብሎ በሕግ ገደብ አስቀምጦ በፋይናንስ ዘርፍ ውስጥ እንዲገቡ ማድረግ ይቻል ነበር፡፡ ለምሳሌ በአንድ የፋይናንስ ተቋም ውስጥ ኢትዮጵያዊ ያልሆኑ የአክሲዮን ባለቤቶች ለመግባት ቢፈልጉ መያዝ የሚችሉት የአክሲዮን ድርሻ እስከ 25 በመቶ ብቻ ነው የሚፈቀደው ልትል ትችላለህ፡፡ እንዲህ ባለ አሠራር አምስት ዓመት ከቆየህ በኋላ ሁኔታውን እያየህ አሠራሩን ልትለውጥ ትችላለህ፡፡

አምስት ዓመት ያልኩትም ነገሩን ረዘም አድርጎ በመያዝ በጣም ለሚፈሩት ማረጋገጫ ይሆናቸው ዘንድ በማሰብ ነው፡፡ ብቻ ምንም ይሁን ምን ዳያስፖራዎችም ሆኑ ሌሎች በፋይናንስ ዘርፉ ውስጥ እንዲገቡ ሒደቱ መጀመር አለበት፡፡ ምክንያቱም ገበያውን መክፈት ዓለም አቀፍ ጥያቄ መሆኑ ቀርቷል፡፡ ጥያቄው መቼና እንዴት የሚለው ብቻ ነው፡፡ ስለዚህ ከወዲሁ መጀመር ያለብን ጉዳዮች አሉ፡፡ ይህንን ሒደት ለማስጀመር ፍኖተ ካርታ (ሮድ ማፕ) ማውጣት ያስፈልጋል፡፡ ለምሳሌ የውጭ ሰዎች እዚህ በተቋቋሙ ድርጅቶች ውስጥ ባለአክሲዮን እንዲሆኑ ትፈቅዳለህ፡፡ ነገር ግን የራሳቸውን ተቋም እንዲያቋቁሙ ባለመፍቀድ ጭምር ሥራው እንዲጀመር ማድረግ ይቻላል፡፡

ሪፖርተር፡- ይህ እንዴት እንደሚሠራበት ቢያብራሩት?

አቶ ኢየሱስ ወርቅ፡- ለምሳሌ ሲቲ ባንክ ወይም ሌሎች የውጭ ባንኮች መጥተው ባንክ አቋቁመው ከሌሎች ባንኮቻችን ጋር እንዳይወዳደሩ ማድረግ ትችላለህ፡፡ ነገር ግን ባሉት የአገራችን ባንኮች ውስጥ እስከ 25 በመቶ አክሲዮን ገዝተው እስከተወሰነ ጊዜ ድረስ ይፈቀዳል የሚል አሠራር በመጀመር አቅም ማጎልበት ይቻላል፡፡ ይህንን አሠራር ከመፍቀድህ በፊት ያሉትን የፋይናንስ ተቋማት በአንድ ደረጃ ላይ አስቀምጠህ ማወዳደር ያስፈልጋል፡፡ ይሄ ባንክ የመንግሥት፣ ይሄ የፓርቲ የሚባለውን ማስቀረት ያስፈልጋል፡፡ እንደሚታወቀው በፖለቲካ፣ በሃይማኖትና በዘር የተቋቋሙ የፋይናንስ ተቋማት አሉ፡፡ ይሄ ለወደፊቱ መቅረት አለበት፡፡ ይኼንን ነው መጀመሪያ መለወጥ ያለብን፡፡ እውነተኛ በግል ባለቤትነትን በማስፈን የአገራችን ተቋማት ትንሽ ጊዜ እንዲወዳደሩ መንገድ መከፈት አለበት፡፡ እርግጥ አመሠራረታችን አስቸጋሪ ስለነበር ፈታኝ ሊሆን ይችላል፡፡ ነገር ግን አቅማችን ለውድድር የማይመጥን ሆኖ ሲገኝ ከሌሎች ጋር ተዋህዶ መሥራትም ይጠቅማል፡፡ ለምሳሌ 17 የሚደርሱትን ባንኮች አንዱን ከአንዱ አዋህደን ስምንት ጠንካራ ባንኮች ይበቁን ይሆናል፡፡ በኢንሹራንሱም እንዲሁ ነው፡፡ እንዲህ በማድረግ ጠንካራ የግል የፋይናንስ ተቋማት ተፈጥረው ቢያንስ ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክና ከኢትዮጵያ መድን ድርጅት ጋር መወዳደር የሚችሉ ተቋማትን ማፍራት ይቻላል፡፡ ስለዚህ አሸናፊ ሆኖ ለመውጣት የግድ ከሃይማኖት፣ ከዘርና ከመሳሰሉት አደረጃጀቶች መውጣትና ገበያውንም ለሁሉም ክፍት ማድረግ ያሻል፡፡

ሪፖርተር፡- ዳያስፖራዎች በፋይናንስ ተቋማት ውስጥ ገብተው መንቀሳቀሳቸው ሊሰጥ የሚችለውን ጠቀሜታ በተመለከተ በተለይ በተወሰነ ደረጃም ቢሆን በዚህ ዘርፍ ቢገቡ የውጭ ምንዛሪ ሊገኝ የሚችል ስለመሆኑ ከፋይናንስ ተቋማት በኩል ለመንግሥት የቀረበ ነገር አለእናንተስ ይህንን ሐሳብ አላቀረባችሁም?

አቶ ኢየሱስ ወርቅ፡- እናንተ ስትል እነማንን ማለት ፈልገህ ነው?

ሪፖርተር፡- እንደ እርስዎ ያሉ የፋይናንስ ተቋማት መሪዎችንና አስፈጻሚዎችን ማለቴ ነው፡፡

አቶ ኢየሱስ ወርቅ፡- የለንም እኮ፡፡ ይቅርታ አድርግልኝ እንዳለን አትቁጠረን፡፡ አሁን ባለንበት ሁኔታ የፋይናንስ ተቋማት የቦርድ ዳይሬክተሮች ምን ሥልጣን አላቸው ብለህ ትገምታለህ? ምን ያህልስ ተደማጭነት አላቸው ብለህ ትገምታለህ? የፋይናንስ ተቋማት ቦርዶች ወይም የቦርድ መሪዎች በአንድ ጉዳይ ተሰባስባችሁ ሐሳብ ስጡበት የተባሉበትን ጊዜ አላስታውስም፡፡ ስለዚህ የሉም፡፡ በቅርብ ጊዜ ተግባራዊ በሆነውና የፋይናንስ ተቋማትን የቦርድ ዳይሬክተሮች የሚመለከተው የብሔራዊ ባንክ መመርያ መሠረት ብዙ የተለወጠ ነገር አለ፡፡ እርግጥ ነገሩ መጥፎ ነገሮችም ነበሩበት፡፡ የቦርድ ዳይሬክተር ለመሆንና ከትርፍ ክፍፍሉ የሚገኘው ክፍያ ለማግኘት በጣም ብዙ መሻኮትና መራኮት ነበር፡፡ ነገሩን በደንብ አርገህ ከተመለከትከው፣ የፖለቲካ ፓርቲዎችም ምርጫ ሲገቡ መጀመሪያ ብዙ መሻኮትና መራኮት ያደርጋሉ፡፡ ታዲያ ባንክና ኢንሹራንስ ውስጥ ያሉ ሰዎች ልዩ ፍጡር ናቸው? ከዚህ የተለየ ምን ያደርጋሉ? ያው ናቸው፡፡ ለመወዳደር ስትገባ በተቻለ መጠን ለማሸነፍ ትገባለህ፡፡ ይህ ይታይ ነበር፡፡ ምናልባት አንዳንድ ጊዜ ከምትጠብቀው መስመር የወጣ ድርጊት ተፈጥሮ ሊሆን ይችላል፡፡ ይህ በሚሆንበት ጊዜ ጉዳዩን ተከታትለህ መቅጣት ያስፈልጋል፡፡ አለበለዚያ ግን የቦርድ ዳይሬክተር መሆን ይጠቅማል፤ ዋጋም አለው ብለህ አስበህ እንድትገባበት ያስፈልጋል፡፡ ባለአክሲዮኖች ሥራ ተሠርቶ ከተገኘው አንጡራ ትርፍ፣ ታክሱ፣ መጠባበቂያው በአጠቃላይ ሁሉ ነገር ተቀንሶ የተረፈች ገንዘብ ስትኖር ይቺን ያህል ደግሞ ይህንን ሥራ ለሠሩልን፣ ይህንን ጥሩ ውጤት ላስገኙልን ቦርድ ዳይሬክተሮች እንስጣቸው ቢሉ ለምንድን ነው የሚከለክሉት? ክልከላው ደግሞ ነገሮችን ለወጠ፡፡ በአዲሱ መመርያ ወደ ዳይሬክተርነት የሚመጡ ብዙ ሰዎች በዓመት 50 ሺሕ ብር ነው የሚፈቀድላቸው፡፡ አንዳንዶቹ ምናልባት በሚሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ ሊያገኙ ይችላሉ፡፡ በቅርቡ በጋዜጣ እንዳወጣውም አንዳንዶቹ ብድር ይደልላሉ፡፡ አንዳንዶቹ ዶላር ይደልላሉ፡፡ ምክንያቱም የእኔ ባንክ ነው፣ ተደማጭነት አለኝ ይህንን ያህል ዶላር እሰጥሃለሁ፣ በዶላር ለእኔ ይህንን ያህል ትከፍለኛለህ ይባላል፡፡ ይሄ ሲወራ የቆየ ጉዳይ ነው፡፡ ስለዚህ እንዲህ ወዳሉ ነገሮች ተገለበጠ ማለት ነው፡፡  

ሪፖርተር፡- በአጭሩ ዳያስፖራዎች በሕግ በተቀመጠ ገደብም ቢሆን ገብተው ቢሠሩ የሚሰጡትን ጠቀሜታ የተመለከተ ሐሳብ ከፋይናንስ ተቋማት የቀረበ ነገር የለም ማለት ነው?

አቶ ኢየሱስ ወርቅ፡- ዳያስፖራዎች እኮ በዚህ ዘርፍ ገብተው መሥራት ቢፈልጉ ምክንያት አላቸው፡፡ ሕጋዊ ማዕቀፍ ተፈጥሮላቸው በደንብ ቢሠሩ፣ አትራፊነታቸው ብቻ ሳይሆን ያለምንም ፍርኃት ምክንያታዊ ተጠያቂነት፣ ምክንያታዊ ግልጽነት አይተህ ኢንቨስት ልታደርግ የምትችለው እነዚህ የፋይናንስ ተቋማት ውስጥ ነው፡፡ እንደ ፋይናንስ ተቋማቱ ዓይነት ሌሎች ተቋማት ቢኖሩ ወይም ማቋቋም ቢችል ዳያስፖራም ይገባል፡፡ ስለዚህ የገንዘብ ተቋማት ስለሆኑ ብቻ ሳይሆን ሕጋዊ ማዕቀፍ ኖርዎት በደንብ ቢሠራ ለውጥ ይመጣል፡፡ ሁሉንም ወጥሮ ነገር ያድናል ማለት ግን አይደለም፡፡ በሌላ በኩል ብሔራዊ ባንክ የተቻለውን ያህል ክትትልና ቁጥጥር እያደረገ ባንኮችና ኢንሹራንሶች ከሞላ ጐደል ከሌሎች ተቋሞች ወይም ጫካ ውስጥ እየሰረጉ ከሚቀሩ የአክሲዮን ኩባንያዎች በጣም የተሻሉ ናቸው፡፡ ስለዚህ ዳያስፖራዎች እነዚህ ውስጥ ነው መግባት የሚፈልጉት፡፡ የአክሲዮን ገበያ ማቋቋም የውጭ ምንዛሪ ማግኛ አንዱ ዘዴም ይህ ነበር፡፡ በእውነቱ በዚህ ጉዳይ ላይ ወደኋላ የሚባልበት ምክንያት መኖር የለበትም፡፡ ፍርኃት ካልሆነ በስተቀር፡፡ የብዙዎቹ ፍርኃት ግን ስንሠራ ከቦታችን ከምንነሳና ከምንጠየቅ እንዲሁ አለመሥራቱና አለመጠየቁ ይሻላል የሚል ምርጫ ያደረጉ ይመስላል፡፡ ማን ተነሳሽነቱን ይወስድ? ማን ኃላፊነቱን ይውሰድ? ምክንያቱም ሥንሠራ የመሳሳት ዕድል አለ፡፡ የማይሠራ ብቻ ነው የማይሳሳተው፡፡ ስተሠራ ለመሳሳት እንደምትችል አውቀህ ለሚመጣው ስህተት ደግሞ ኃላፊነት የምትወስድበት መሆንህን እርግጠኛ ሆነህ ነው መግባት ያለብህ፡፡ ይህንን ዓይነት ውሳኔ ለማድረግ መጽሐፍ ማንበብ ብቻ በቂ አይደለም፡፡ አንዳንድ ጊዜ በሥራ ውስጥ እየገባን የተሳሳትነው፣ ከስህተታችን የተማርነው የተሻለ መሥራት እንችላለን፡፡ ሌሎችን ማዳመጥ ያስፈልጋል፡፡ አንድ ነገር ስትናገር የማግለል ዕርምጃ ሊወስድብህ አይገባም፡፡ በተለይ ዳያስፖራዎች ያነሱት ጉዳይ አለ፡፡ ሕጐች ይወጡና እንዳልሆነ ሆነው ሲጣሱ ይታያሉ፡፡ ምንም የሚደረግ ነገር ግን የለም፡፡ ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሥራ ኃላፊዎችን ሥራዬ ብዬ አንዳንድ ነገር ተንፈስ ለማለት ሞክሬ ነበር፡፡ ብዙ ጊዜ ሬዲዮ ስለማዳምጥ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ኃላፊነትና ሥራዎች ተብሎ ጠዋት ጠዋት ረዥም ማስታወቂያ ይነገራል፡፡ ነገር ግን ያወጣው ሕግ ሲጣስ ዕርምጃ አልወሰደም፡፡ ‹‹እውነት በሆነና አንዱ በበቃኝ›› የሚል አባባል አለ፡፡ ስለዚህ ፓርላማው ሕግ ማውጣት ብቻ ከሆነ ዓላማው በእውነቱ ታክስ መክፈል አልነበረብኝም የምልበት ወቅት አለ፡፡ የሚወጣው ሕግ በግልጽ ሲጣስ፣ ሲነገረውና ስታሳየው እንኳ ምንም ዓይነት ዕርምጃ የማይወስድ፣ የማይንቀሳቀስ ከሆነ ምን ማለት ነው? እንዲህ ያሉ ነገሮችም መታየት አለባቸው፡፡

ሪፖርተር፡- የፋይናንስ ዘርፉን ክፍት ማድረግ ችግር ሊፈጥር ይችላል የሚል ሥጋትና አመለካከት አለ፡፡ ይህንን ሥጋት እንዴት መወጣት ይቻላል?

አቶ ኢየሱስ ወርቅ፡- ችግሩ ያለው እዚህ ላይ ነው፡፡ ለምንድን ነው ገበያችንን መክፈት የምንፈራው? ብዙጊዜ እንደምሰማው ገበያችንን መክፈት እንደ አርጂንቲናና እንደ ፊሊፒንስ በአንድ ቀን አዳር እንደሚፈርስ አድርገን ነው የምናየው፡፡ አሁን ያለው አሠራር ከጊዜው ጋር ተለውጧልና ባንኮችን ነፃ ማድረግ የማይቀር ስለሆነ መጀመር ያለብን አሁን ነው፡፡ ከመንግሥት ነፃ የምታደርገው እኮ ቀስ በቀስ ነው፡፡ የመጀመሪያው ዕርምጃ ደግሞ ለአገራችን ድርጅቶች የአገራችን ገበያ ነፃ መሆን አለበት ነው፡፡ ይህንን ስናደርግ የስቶክ ገበያውን ይዞ ነው፡፡ አሁን ካላቸው በላይ ተጨማሪ ካፒታል ይዘው እንዲያድጉ ለማድረግም የስቶክ ገበያ መኖር አለበት፡፡

ሪፖርተር፡- የስቶክ ገበያ ከተነሳ የአገራችን ስቶክ ገበያ ቀደም ብሎ ተጀምሮ እንደነበር ይነገራል፡፡ ባይሳካም የስቶክ ገበያን ለመፍጠር ተደጋጋሚ ሙከራ ተደርጓል፡፡ ቀደም ያለውን የስቶክ ገበያ አሠራር ምን ይመስል ነበር?

አቶ ኢየሱስ ወርቅ፡- መደበኛ የስቶክ ገበያ በአገራችን ተቋቁሞ አያውቅም፡፡ ምክንያቱም መደበኛ የስቶክ ገበያ ለማቋቋም የሚጠይቁ ወይም የሚያስፈልጉ በርካታ ነገሮች አሉ፡፡ በዛሬ ጊዜ አስፈላጊ ነገሮች በሚፈለገው ደረጃም ባይሆን ተሟልተዋል ማለት ይቻላል፡፡ የስቶክ ገበያን ለማስጀመር አንደኛ በስቶክ ገበያ ውስጥ መገበያየት የሚቻልባቸው ኩባንያዎች አሉ ወይ? ወይም በቅርብ ጊዜ ሊፈጠሩ ይችላሉ ወይ? ሒሳብ አያያዝና የሒሳብ አዋቂዎች አሉ ወይ? ኦዲተሮችስ አሉ ወይ? የሚለውን ጥያቄ መመለስ ስለሚያስፈልግ ነው፡፡ ምክንያቱም በስቶክ ንግድ አማካይነት የድርጅቶቻችን የፋይናንስ ይዘት መተንተንና መረዳት የሚችሉ ብዙ ሰዎች ያስፈልጉናል፡፡ በተለይ በስቶክ ገበያው ውስጥ መገበያየት የሚችሉ ኩባንያዎች ያስፈልጉናል፡፡ ዱሮ ከነበርንበት ዛሬ በብዙ እጅ የሚበልጡ ኩባንያዎች አሉን፡፡ በቀድሞ ጊዜ የነበረውን አሠራር በተመለከተ ግን መደበኛ የስቶክ ገበያ ሳይኖር በወቅቱ የነበሩ ትልልቅ ኩባንያዎች (የመንግሥትን ጨምሮ) እንደ ወንጂ ስኳር ፋብሪካ፣ እንደ ወረቀት ፋብሪካና ቅዱስ ጊዮርጊስ ቢራ ፋብሪካ ያሉት አክሲዮናቸው ይሸጥና ይለወጥ ነበር፡፡

ሪፖርተር፡- አክሲዮናቸው እንዴት ነበር ይሸጥ ይለወጥ የነበረው?

አቶ ኢየሱስ ወርቅ፡- እነዚህ ኩባንያዎች አክሲዮናቸው ይሸጥ ይለወጥ የነበረው ብሔራዊ ባንክ ውስጥ በብሔራዊ ባንክ ገዥ መሪነት ወይም ሰብሳቢነት በሚተዳደር ‹‹ሼር ዲሊንግ ግሩፕ›› በሚባል አካል ነበር፡፡ በአሥራ አምስት ቀን አንድ ቀን እየተሰበሰቡ የአክሲዮን ድርሻ ይሸጡና ይገዙ ነበር፡፡

ሪፖርተር፡- ኩባንያዎቹ ለሽያጭ የሚያቀርቡትን አክሲዮን የሚገዙት እነማን ነበሩ?

አቶ ኢየሱስ ወርቅ፡- ገንዘብ ያላቸው ግለሰቦችና ድርጅቶች ናቸው፡፡ የተሸጠበት ዋጋ ደግሞ በኢትዮጵያን ሔራልድ ጋዜጣ ይታተም እንደነበር ትዝ ይለኛል፡፡ በአንዳንዶቹ ጋዜጦች ላይ የወጣው መረጃ አለኝ፡፡ በዚህ ቀን የወንጂ ሸዋ ስኳር ፋብሪካ አክሲዮን ድርሻ በዚህን ያህል ዋጋ ተሸጠ፣ የቅዱስ ጊዮርጊስ ቢራ ድርሻ በዚህ ዋጋ ተገበያየ፣ እየተባለ ሕዝብ እንዲያውቀው በጋዜጣ ይታተማል፡፡ ይህንን ሥራ የሚሠራው ሼር ዲሊንግ ግሩፕ የሚባለው አካል ነበር፡፡ ይህንን ሥራ ለመሥራት ይህ አካል የተለየ ሕግ አላስፈለገውም ነበር፡፡

በግሩፑ ውስጥ የሚሸጡና የሚገዙ ሰዎች ራሳቸው ለራሳቸው ብቻ ነው አክሲዮን ግብይት የሚያደርጉት፡፡ ተገበያዮቹ ግብይት የሚያደርጉት ለራሳቸውና ለራሳቸው ብቻ ነው፡፡ ለሌላ ሰው አትገዛም ለሌላ ሰውም አትሸጥም፡፡ አትገዛም፡፡ ስለዚህ ጉዳዩ ሦስተኛ ወገን የሌለበት ነው፡፡ በዚህ መሠረት ሲሠሩ ቆይተው ደርግ ሲመጣ ብዙ ድርጅቶች በመሸጣቸው መግዛትና መሸጥ ቆመ፡፡ ከዚያ ወዲህ ግን ከ1991 ዓ.ም. ጀምሮ በአዲስ አበባ ንግድ ምክር ቤት አነሳሽነት የስቶክ ኤክስቼንጅ ፕሮሞሽን ካውንስል ጊዜያዊ ኮሚቴ ተቋቋመ፡፡ ዘጠኝ አባላት ነበሩበት፡፡ ኮሚቴው ስለ ስቶክ ኤክስቼንጅ የሚያስፈልገውን ጥናት ሠርቶ ለመንግሥት ትልመ ሐሳብ (ፕሮፖዛል) ለማቅረብ ይሠራ ነበር፡፡ በርካታ ጐበዝ ሰዎች ተሳትፈውበትና ብዙ መዋለ ነዋይ ፈሶበት ጥናቱ ተሰናድቶ ካለቀ በኋላ በልዩ የጠቅላይ ሚኒስትሩ አማካሪ በኩል ለመንግሥት ቀርቦ ነበር፡፡

ሪፖርተር፡- ምን ምላሽ አገኛችሁ?

አቶ ኢየሱስ ወርቅ፡- የደረሰን መልስ በአሁኑ ጊዜ ስቶክ ኤክስቼንጅ ማቋቋም ቅድሚያ የሚሰጠው አይደለም የሚል ነው፡፡ መልሱ በጽሑፍ አልነበረም የተሰጠን፡፡ ነገር ግን በንግድ ምክር ቤቱ በኩል ግፊት ማድረጉን ቀጠልን፡፡ የስቶክ ገበያን የተመለከቱ ውይይቶች በተለያዩ መድረኮች ላይ ብዙ ተብሎላቸው ነበር፡፡ ብዙ ጥናቶችም ቀርበው ነበር፡፡ ከዓመታት በፊት በመቀሌ ዩኒቨርሲቲ ውይይት ተደርጐበታል፡፡ ከዚያን ጊዜ ወዲህ ግን ስቶክ ኤክስቼንጅን የሚመለከቱ ሙከራዎች ሲደረጉ ይከሽፋሉ፡፡   

ሪፖርተር፡- የስቶክ ገበያን ለማስጀመር ብዙ ጥረት መደረጉን ገልጸውልኛል፡፡ ነገር ግን አገልግሎቱ ሥራ ላይ እንዳይውል እንቅፋቱ ምን ነበር? ለምንስ የሚከሽፍ ይመስልዎታል?

አቶ ኢየሱስ ወርቅ፡- ለምን እንደሆነ አላውቅም፡፡ እንግዲህ የግሌን አስተሳሰብ ነው መስጠት የምችለው፡፡ ምክንያቱም የስቶክ ገበያ ጉዳይ በመንግሥት ቅድሚያ የሚሰጠው ጉዳይ አይደለም ከመባሉ ውጭ ዝርዝር ነገር አልተሰጠንም፡፡ እኔ የሚመስለኝ ግን ምናልባት የአገሪቱን መዋለ ነዋይ መንግሥት ሊያውለው በሚፈልገው ቦታ እንዳይውል ሊያደርግ ይችላል፣ ሌሎች ኢንቨስተሮች ወደሚፈልጉት ቦታ ሊፈስ ይችላል በሚል ሥጋት ይመስለኛል፡፡ ስለዚህ ነገሩ ከመንግሥት ቁጥጥር ውጭ ሊሆን ይችላል ከሚል ፍርኃት የመነጨም ሆኖ ይሰማኛል፡፡

ቀደም ብዬ እንደገለጽኩት በስቶክ ገበያው ሊጠቀሙ የሚችሉ ኩባንያዎች ብዙ አልነበሩም በሚል ይሆናል የሚል ግምትም አለ፡፡ እርግጥ ነው ይህ ያስኬዳል፡፡ ነገር ግን ስቶክ ገበያው ለመጀመር ይህንን ያህል ብዙ ኩባንያዎች አያስፈልጉም፡፡ የሌሎች አገሮች ልምድና አጀማመርን ስናይ በተወሰኑ ኩባንያዎች ማስጀመር የሚቻል መሆኑን እንረዳለን፡፡ በሌላ በኩል ግን ከርዕዮተ ዓለም አኳያ ስቶክ ገበያ የኒዮሊበራል መሣሪያ ወይም ማስፈጸሚያ ስለሆነ የሚደገፍ ባለመሆኑም ሊሆን ይችላል፡፡ በግልጽ እንዲህም ባይባል አንዱ ምክንያት ይሄ ሊሆን ይችላል፡፡ በኋላም ከአንዳንድ ጽሑፎች አንብቤ እንደተረዳሁት ይሄ የማግለል አካሄድ በስቶክ ገበያ ላይ ስላረፈ በተቻለ መጠን እንዳይበረታታ የማድረግ ነገርም ይመስላል፡፡  

ሪፖርተር፡- ብሔራዊ ባንክ የስቶክ ገበያን ለማስጀመር እየሠራ ነው ይባላል፡፡ ይህ መረጃ አላችሁ?

አቶ ኢየሱስ ወርቅ፡- የብሔራዊ ባንክ መረጃን ብዙ ጊዜ አታገኘውም፡፡ የብሔራዊ ባንክ ብቻ ሳይሆን አንዳንድ መረጃዎችን ለማግኘትና ሐሳብ ለመስጠት የማትችልባቸው አጋጣሚዎች አሉ፡፡ የሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ እስካሁን ድረስ ወረቀቱ ቀርቦ እስቲ ሐሳብ ስጡበት አልተባለም፡፡ ወረቀቱን የያዙ ሰዎች ወረቀቱን ለራሳቸው ይዘው ነው መግለጫ የሚሰጡት፡፡ እንዲህ ዓይነቱ ሁኔታ ሐሳብ ለማካፈልና አስተያየት ለመስጠት አያስችልም፡፡ አንዳንድ ጊዜ እንደ ቂልም ሊያደርግህ ይችላል፡፡

 የዚህ ዕቅድ ሰነድ ብዙ ተጠይቆ ያልተገኘ ነው፡፡ ሰሞኑን በተካሄዱ በስብሰባዎች ላይ ጉዳዩ ተነስቶ ስለዕቅዱ የሚያሳየውን ሰነድ ለምን አትሰጡንም ተብሎ ተጠይቋል፡፡ የተሰጠው መልስ ገና ጨርሰን ስላልሠራን ነው የሚል ነው፡፡ ትልመ ሐሳብ ተጽፎ ሳይቀርብ ምንድነው የምትወያየው? እኔ እንጃ የቅደም ተከተሉ ጉዳይ አስቸጋሪ ነው፡፡ ለማንኛውም የስቶክ ገበያን ለመፍጠር የተነሳነው በዚያን ወቅት መንግሥት፣ የመንግሥት ተቋማትን ለግል ዘርፉ በሽያጭ ወይም በሁለትዮሽ ባለቤትነት ማስተላለፍ ፖሊሲ አድርጌ ወስጃለሁ ብሎ ይህንን ያስተናግድ ስለነበር ነው፡፡ እኛ የአክሲዮን ገበያ እንዲኖር እንገፋ የነበረው አንዱ ምክንያት መንግሥት ለሚሸጣቸው የመንግሥት ተቋማት አንድ ከበርቴ እንዳይወሰዱ ነው፡፡ አንዱ መጥቶ የ100 እና የ500 ሚሊዮን ብር ቼክ እንዲጽፍለት የሚፈልገው ለምንድነው? ከዚህ ይልቅ ለሕዝቡ መሸጥ የማይቻለው ለምንድን ነው? ሕዝቡ እኮ አምስት ሺሕ፣ አሥር ሺሕ፣ 40 ሺሕ ብር አውጣጥቶ በአክስዮን ሊገዛቸው ይችል ነበር፡፡ በሕግ የተጠበቀ የአክሲዮን ግብይት ቢኖር ብዙዎቹን የመንግሥት የልማት ድርጅቶች በአክሲዮን ይገዛቸው ነበር፡፡ ዛሬም ሊገዛ ይችላል፡፡ በአክሲዮን አዳዲስ ተቋማትን ማቋቋም ይቻላል፡፡ ይሄ ነገር ለምን ወደኋላ እየተጐተተ እንደሆነ አላውቅም፡፡ ከብሔራዊ ባንክ በኩል አሁን የምንሰማው የቦንድ ገበያን የሚመለከት ነው፡፡ ስለቦንድ ገበያ ጥናት ተደርጐ በቅርብ ጊዜ ውስጥ ሥራ ላይ ይውላል የሚል ነው፡፡ ይሄንን ጉዳይ ስታስብ ደግሞ የማንን ቦንድ ነው የምትሸጠውና የምንለውጠው የሚል ጥያቄ እንድትጠይቅ ያደርግሃል፡፡ በአክሲዮን ገንዘብ አሰባስቦ ሥራ በማቋቋም በጣም ውጤታማ የሆኑ ፕሮጀክቶችን አይተናል፡፡ ለምሳሌ የራያ ቢራን አክሲዮን ብትወስድ፣ ጊዜውን ጠብቆ የሁለት ቢሊዮን ብር ኢንቨስትመንት በሥራ ላይ አውሏል፡፡ 2,500 ግለሰቦችና ድርጅቶች ገንዘባቸውን አዋጥተው ይህንን ድርጅት ከፈጠሩት፣ እንዲህ ያሉ ድርጅቶችን እኮ ብዙ መፍጠር እንችላለን፡፡ ሕግና ኮንትራንትን ማስከበር የሚቻልበት ሁኔታ ቢፈጠር፣ በአክሲዮን በመሰባሰብ በጣም ብዙ ፕሮጀክቶችን ማቋቋም ይቻላል፡፡ የውጭ ምንዛሪ ምንጭም ነው፡፡ አክሲዮን የምትሸጠው እኮ በዶላር ነው፡፡ ለምንድን ነው የምንፈራው? እነዚህ ሁሉ በጣም ያስፈልጋሉ ብዬ አስባለሁ፡፡ ነገር ግን ፍርኃት ያለ ይመስለኛል፡፡

ሪፖርተር፡- ፍርኃቱ ከምን የመነጨ ይመስልዎታል?

አቶ ኢየሱስ ወርቅ፡- እንግሊዞች ‹‹ስለሞት ለማወቅ መሞት የለብህም፤›› ይላሉ፡፡ እኛ ያሉን ፖሊሲ አውጭዎች አይደሉም፡፡ የንድፈ ሐሳብ ቀማሪዎች ናቸው፡፡ አብዛኛዎቹ የንድፈ ሐሳብ ሰዎች ናቸው፡፡ ጽሑፍ አንብበው ወይም ሲነበብላቸው አድምጠው ያንን የሚያብሰለስሉ ናቸው፡፡ ሥራ አቋቁመው፣ ሥራ ፈጥረው ትልቅ ሀብት አደርጅተው ለመሥራት ልምድ ያላቸው አይደሉም ለማለት ፈልጌ ነው፡፡  

ሪፖርተር፡- የብሔራዊ ባንክ መመርያም ተፅዕኖ አሳድሯል? አደጋ አለው እያሉኝ ነው? ምን መደረግስ አለበት?

አቶ ኢየሱስ ወርቅ፡- ነውና!! አንዳንድ ሰዎች ስንናገር ተዳፋሪዎች እንባላለን፡፡ እንዲያውም በተቻለ መጠን እንዳንሰማ ወይም ድምፃችንን ከምናሰማበት ቦታ እንድንገለል ይደረጋል፡፡ በግልጽም ተደርጓል፡፡ ሰጐን አዳኝ ሊገላት ሲመጣ ጭንቅላቷን አሸዋ ውስጥ ትቀብራለች፡፡ በእሷ ቤት ጭንቅላቷን አሸዋ ውስጥ በመቅበሯ አዳኟ አይነካኝም ከሚል ነው፡፡ አንዳንድ ጊዜ የአገራችንን ሁኔታ ስመለከተው ከሰጐኗ ድርጊት ጋር ይመሳሰልብኛል፡፡ እኛ በግልጽ እስካላየነው ድረስ መጥፎ ነገር ቢደረግም እንደ ጉዳት አይቆጠርም፡፡ በግልጽ መወራት የሚገባው ነገር በድብቅ እንዲሠራ እናደርገዋለን፡፡ ራሳችን በምንፈጥረው የሕግ ከባቢና በመሳሰሉት ነገሮችና ግዴታዎች ማለቴ ነው፡፡ አሁን ባናየውም ክፉው ነገር እየተደረገ ነው፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች